- ቤቶቹ ከቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ዐማኑኤል አጠገብ የተሠሩ ነበሩ
- በልደት ክብረ በዓል የቱሪስቶች ቁጥር መቀነሱ ኅብረተሰቡን አስደንግጧል
በቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም ከዐሥራ አንዱ ውቅር አብያተ መቅደስ ጋር በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት ጥንታውያን ቤቶች በእሳት ቃጠሎ መውደማቸው ተገለጸ፡፡ ባለፈው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ መንሥኤው ባልታወቀ ምክንያት በተነሣው የእሳት ቃጠሎ የወደሙት አራት ቤቶች የሣር ክዳን ያላቸው ፎቅ ቤቶች ሲኾኑ፣ የላሊበላን ጥንታዊ የቤቶች አሠራር የሚያሳዩ በመኾናቸው እየተጠገኑ እንዲጠበቁ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ በቃጠሎው የወደሙት ጥንታውያኑ ቤቶች፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርቶች መካከል በቅኔና ዜማ ትምህርት መስጫነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ ተገልጧል፡፡ ገኛ ቦታቸውም ከዐሥራ አንዱ አብያተ መቅደስ መካከል በታላቁ ቤተ መድኃኔዓለም እና በቤተ ዐማኑኤል አጠገብ ከ20 - 30 ሜትር ርቀት ላይ መኾኑ፣ የገዳሙ አስተዳደር ጽ/ቤት ለቅርሶቹ ደኅንነት ትኩረት ሰጥቶ በቂ ጥበቃና ክብካቤ እንደማያደርግ በካህናቱ እና ምእመናኑ የሚነሡበትን ስጋቶችና ተቃውሞዎች ያጠናከረ ነው ተብሏል፡፡ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት÷ የቃጠሎ አደጋው በደረሰበት ዕለት ሌሊት በሁለቱም አብያተ መቅደስ አካባቢ የገዳሙ ጥበቃ አባላት አልነበሩም፡፡