Monday, March 2, 2015

የአድዋ ድልና እኛ

 ዳንኤል አበራ (danlinet@yahoo.com)
 የካቲት 22፣ 2007 1.መቅድም ይህ የአድዋ 119ኛ አመት መታሰቢያ እኛና አድዋ በተሰኘ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያተኩራል። ድርሰቱ ስድስት ንኡሳን ክፍሎች አሉት። ሁላችንም በጦርነቱ በድሉም ወቅት ስላልነበርን የተጻፈ አንብበን ከምናውቀው አመሳክረን ነው ጽሁፉ የተዘጋጀው። የተጻፈ አንብበን ላልኩት የጳውሎስ ኞኞን ምክር ከልቤ አድርጌ ነው። ጳውሎስ ኞኞ ኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት በሚለው መጽሃፉ እኛ ስለራሳችን ስንጽፍ እናጋንናለን ስለዚህ የውጭ አገር ምእራባውያን የመሰከሩልንን ተጠቅሜያለሁ ይላል። የጳውሎስ አንደኛውን ምክር ከልብ ማድረግ ነው። ሁለተኛ ቢያሳዝንም እውነት ስለሆነ የሰዎች ስም በክፉ ይነሳል፤ አያት ቅድመ አያት ለሰራው ባንጠየቅም የአያቶቻችን ስም ሲነሳ አለመቀየም ነው። ከተቀየማችሁም ምን ይደረጋል ከመጻፍ አይቀርም። ራስ ደስታ ዳምጠው በሁለተኛው የጣሊያን ጦርነት የደቡቡን ውጊያ የመሩ ለጣሊያን ባደረ ሀበሻ ጠቋሚነት ነው ተይዘው የተገደሉት። አባታቸው ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ በትግራዩ ጦርነት ነው የተገደሉት።
አባትም ልጅም ተሰውተዋል ሲሆን እንዲህ ነው። ባንዳ በክፉ ይነሳል የባንዳ ልጅ ባንዳ ከሆነ ምን ይደረጋል? ባይሆን ልብ መግዛት ነው። ጽሁፉ ረዘም ይላል። ትእግስት ይኑራችሁ እያረፉ ማንበብም ይቻላል። ይህን የአያቶቻችንን ስጦታ ትርክት ላልሰማ አሰሙ! ላላነበበ አስነብቡ! አንዲት ውድ ሕይወታቸውን ሰውተው ሰው ላደረጉን አያት ቅድማያቶቻችን ፣ ሕይወት ለግሰው ያኖሩንን ወገኖቻችንን ባይሆን በዚህ እንዘክራቸው። የአድዋ ድልን ማሰብ መዘከር ወይም መጻፍ በኔ ባንተ ባንቺ የተወሰነ አይደለም። የሁላችንንም አእምሮ ጓዳ ፈታሽ ኩነት ነው። እስኪ በአራት ቀደምት ፀሀፍት ጥቅሶች እንሟሟቅ። እነሱን ሆነን የአድዋን ድል እናስበው! ዘላለም ምህረቱ “የባዶ እግር ኮቴ” በተሰኘ ጽሁፉ የአውሮፓውያንን መብት ረጋጭነት፤ ነፃነት ገፋፊነት፤ ባሪያ ፈንጋይነት እናም አድዋን አስመልክቶ ውብ በሆነ አገላለጽ ተርኮታል። አባቶች በልጆቻቸው ፊት ክብራቸው እንዳደፈ ሸማ በነተበበት ዘመን፤ ሚስቶች መከታ ጋሻየ ብለው በሚያምኑባቸው ባሎቻቸው ፊት በጭካኔ በተደፈሩበት ወቅት፤ ህፃናት በጨቅላነታቸው የልጅነት ጨዋታን ተነፍገው የነጭ ህፃናት መጫወቻ በሆኑበት በዚያ መራር የፅልመት ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይገመት ይቻላል ተብሎ የማይታሰብ ነገር ሆነ፡፡ መላው አፍሪካዊያን በባርነት ረግረግ በሚዳክሩበት ወቅት፤ ከወደ ጦቢያ ህልም የሚመስል ወሬ ተሰማ፡፡ ድፍን የጦቢያ ህዝብ ሀገሩ መወረሯን ሲሰማ፤ ገበሬው ሞፈርና ቀንበሩን ሰቀሎ ጦርና ጋሻውን አነገበ፤ በሮቹን ወደ በረት ከትቶ የጦር ፈረሶቹን አሰገረ፤ሸማኔው ማዳወሪያውን አሽቀንጥሮ ጎራዴውን ታጠቀ ፤ የሚወዳቸው ሚስትና ልጆቹን ተሰናብቶ ወደ ጠላት ገሰገሰ፡፡ ነፃነትን ተነፍጎ ሽህ አመት ከመኖር ለነፃነቱ ሲፋለም ነፃ ሁኖ ዛሬውኑ መውደቅን የመረጠው ድፍን ጦቢያ ህዝብ ለጠላት መትረየስ ደረቱን ሰጥቶ ወደፊት ገሰገሰ፡፡ ከጣሊያን መትረየሶች ድምፅ ይልቅ የአርበኞች ፉከራና ቀረርቶ የአድዋን ተራራ አናወጣት፡፡ እስከ ጉልበቱ የሚደርስ ቦቲ ጫማ አጥልቆ ከመጣው የጣሊያን ወታደር ዳና ይልቅ በወጉ ስንቅ እንኳን ሳይቋጥር ወደ ጠላት የተመመው አርበኛ የባዶ እግር ኮቴ ድፍን ምድሪቱን ናጣት፡፡ ዘላለም ይላል አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሕይወት ከፍለው ስለ ሰጡን ስጦታ “ነፃነት” ዛሬ ነፃ ሰዎች ነን፡፡ በባርነት ጭነት ቅስማችን ያልተሰበረ፤ በጭቆና ቀንበር ልባችን ያልተሸበረ፤ ጎንበስ ማለት የሚያንገሸግሸን: ቀና ብለን ኖረን ቀና እንዳልን ማለፍ የሚናፍቀን፤ የነጮችን ጥቃት ለመቋቋም ቆዳችን የሚሳሳብን፤ አልደፈር ባይ የጥቁር አፈር ትንታጎች ነን፡፡ የአድዋው መስፍን ነጋሽስ ቢሆን ዘላለም የቀሰቀሰብንን ነፃ መንፈስ በውብ ቋንቋ ለመግለፅ አልሰነፈም። መጀመሪያ አድዋ ነበረች። ከአድዋም ጋራ የአድዋ የነጻነት መንፈስ ነበር። አድዋ ይሁን አለች። የአድዋ ድል ሆነም። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአድዋ የነጻነት መንፈስ በምድሩ ሁሉ ላይ ሆነ። መንፈሱ ጠፍቶም አያውቅም፤ አይጠፋምም። ምኒልክ2 አድዋ ባይወለዱም የአድዋ ልጅ ናቸው። የአድዋን ያህል የምኒልክን ፖለቲካም ሆነ በታሪክ ውስጥ ያላቸውን ሚና የወሰነ ቦታ የለም። እርሳቸውም በተራቸው በአድዋ የአገራቸውን እና የአፍሪካን ታሪክ ለውጠዋል፤ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን በድጋሚ አሳይተዋል። ዛሬ ዛሬ መዝሙሩ “መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ” ማለት ሆኗል ይላል መስፍን። የአድዋ የነጻነት መንፈስ ይህን ሲሰማ መሸማቀቁ አይቀርም። እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ምኒልክስ ጣልያንን አስገብተው መንገድና ፋብሪካ ማስገንባት ይችሉ አልነበረምን? ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው የምኒልክ ኢትዮጵያ ሀብታም አገር ሆና ነበርን? ከድህነት መላቀቅን የሚጠላም የሚቃወምም የለም። የአድዋ የነጻነት መንፈስም በድህነት መኖራችንን አይቀበልም። ነገር ግን ከቁሳዊ ሰቀቀን መላቀቅ የዘመናችን የአድዋ የነጻነት መንፈስ ብቸኛና በቂ ግብ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የዜጎች መብትና ነጻነት የሚታፈንበትን፣ መድሎዎና ጭቆና ተቋማዊና ሕጋዊ ቅርጹን ለውጦ የሚቀጥልበትን አገዛዝ የአድዋ የነጻነት መንፈስ አጥብቃ ትጸየፈዋለች። የአድዋ የነጻነት መንፈስ ቸር ነው፣ ታጋሽ ነው፣ ሩህሩህ ነው፣ ታራቂ ነው። ታራቂዎቹን አያዋርድም፣ በታራቂዎቹ ላይ አያቅራራም። ክቡርነትዎ እና ወዳጆችዎ ሁሉ ወደ አድዋ እንዲመለሱ በዕለተ አድዋ ይጋበዛሉ። አድዋ እጇን ዘርግታ ትጠብቃችኋለች፤ የአድዋ ልጆች ወደ አድዋ ተመለሱ። የአድዋ የአጥንትና የስጋ ብቻ ሳይሆን የመንፈስም ልጆች ለሆናችሁት የአድዋ ልጆች፣ እኔም ወንድማችሁ ነኝ የአድዋ ልጅ። የአድዋ ልጆች ነን!' ዕድሜያቸውን ሙሉ ኢትዮጵያን እንዳገለገሉ፣ እንዳስተማሩ፣ ነፃ ሆነው እንደኖሩ ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምም የአያቶቻችንን ውለታ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘና በ2005 አ.ም. በታተመ ሞጋች መፅሀፋቸው “ሞታችሁ ለኛ ህይወት፣ ስቃያችሁ ለኛ ልማት፣ ውርደታችሁ ለኛ ክብር እንዲሆን መንፈሳዊ ወኔያችሁ ላስገደዳችሁ ሁሉ እዳችሁን ለመክፈል ባልችልም እንዳለብኝ አምናለሁ። የኢትዮጵያ አምላክ እዳውን ከፋይ ትውልድ ይላክላችሁ” ብለዋል። ሚራ ኔት ላለፉት ሁለት አመታት ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የአድዋ ድልን እንዘክር ብሎ የወራት ዘመቻ በፌስ ቡክ ያደራጀ ልጨኛ ወጣት ነው። ላለፉት ሀያ አራት አመታት በዚህ የታሪካችን ኩነት እና ግለሰቦች ላይ ተሰምተው የማይታወቁ ስም ማጥፋቶች፤ የነሱን ቅርስና ውርስ ለማጥፋት ያልተደረጉ የተቀነባበሩ የውስጥና የውጭ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ሚራ ኔትም ለዚህ ዘመቻ አቀንቃኞች መልዕክት አለው። የአድዋን ድል የምንዘክረው በታሪካችን ስለምንኮራ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አንዳንዶች ታሪክን በማድፋፋት ተወቃሽ ትውልድ ላለመሆንም ጭምር እንጂ፡፡ አድዋን ስናከብር ደማቸው የሚንተከተክ ብዙ አሳፋሪ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፤ እጃችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ የሚወዱ፣ የእነሱን የሰነፍ ተረት ተረት ብቻ እንድናደምጥ እንጂ፡፡ እኛ ይህን እንዳወቅን ሁሉ እነሱም እንዲያውቁ የምንፈልገው አንድ እውነታ ግን የሚከተለው ነው፡- ታሪክን ማሰብም ሆነ ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት እንዲገባ አጥብቀን ስለምናምን፣ ይህን ማድረግ ደግሞ የዜግነት ግዴታችንም በመሆኑ እንጂ። አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ለማናደድ ወይም የዘር ሃረግን በመምዘዝ ለይተን ልንመታው ያሰብነው አካል የለም፡፡ ልንኮራባቸው የሚገቡ ታሪኮቻችን ሲነሱ በባዶ ሜዳ ነገር በመምዘዝ መቃጠላችሁን አንወድም ዓላማችን አይደለምና፡፡ ግን ደግሞ እናንተ ተናዳችኋል ብለን ታሪካችንን ማሰብ አናቆምም፡፡ ቢሆንላችሁና አብረን ብናስብ ብንማማርም እሰየው፣ ካልሆነላችሁና መበሳጨቱን ከመረጣችሁ ደግሞ ከገዛ ብስጭታችሁ ጋር መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡ ሚራ ኔት ሲያሳርግም “ስለሆነም በታሪክህ/ሽ የምትኮራ/ሪ ቀናዒ ኢትዮጵያዊ ሆይ፡-እነሆ የአድዋን ድል አስመልክቶ በድምቀት ስለ አድዋ እንዘምራለን፣ ስለጀግኖቻችን እንተርካለንና ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ፡፡ዘላለማዊ ክብር ለአድዋ ጀግኖቻንን፤ ፍቅር እና አንድነት ለሁላችን!!!”። የሚሚ ኢትዮጵያዊት የቀድሞ ነገራችን ማሳረጊያ ትሆን ዘንድ እነሆ።3 “በአለም ህዝቦች ታሪክ ለነጭ ትዕቢት ድንበር አልባ የዘረኝነት መርዝ የማይገዛ ጥቁር ህዝብ መኖሩን ያስመሰከረ የዓድዋ ድል።” “የነጭን አንገት ያስደፋ በሀፍረት ያሸማቀቀ በፍርሀት ያርበደበደ ኢትዬጵያዊነት ኩራት አፍሪካነት ኩራት ጥቁርነት ክብር መሆኑን ያስመሰከረ የአፍሪካውያን ኩራት የዓድዋ ድል።” “ለነፃነታቸው ለህልውናቸው ለእናት ሀገራቸው ለሰንደቅ ዓላማቸው ለሰብአዊነታቸው ክቡር ህይወታቸው ገብረው ለዛሬ ላበቁን ወገኖች ዘላለማዊ ክብር ይሁን።” 2.ዋዜማው፦ ቅድመ አድዋ ትውስታ ከዘመነ መሳፍንት ተላቃ አንጻራዊም ቢሆን ወደ ተረጋጋ ማእከላዊ መንግስትነት የተሸጋገረችበት ዘመን። አባ ዳኘውም እምዬም እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩት ንጉሰነገስት አፄ ምኒልክ ስልጣን ያደራጁበት ህጻን አሻንጉሊት እንደሚጠይቀው ኢትዮጵያን ያሰሱ አውሮፓውያንን ባላሰለሰ የመሳሪያ ስጦታም ግዢም ጥያቄ የወተወቱበት ዘመን፤ ኋላም ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደጻፉልን «ባመጣው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ ተፈጠመ ጣሊያን አበሻ እንዳይደርስ» ከተባለለት የጣሊያን መንግሥት ጭምር የመሣሪያ ስጦታ የተሸነገሉበት ዘመን፤ አውሮፓውያን አለምን እንደ ቅርጫ ስጋ የተከፋፈሉበት ዘመን። ኢትዮጵያም የዚህ እጣ ፈንታ እንድትሆን በዝግ በሌለችበት ተወስኖ ለአፄ ምኒልክና መንግስታቸው መልእክት የተነገረበት ዘመን። ዘመኑ አፄ ምኒልክም መልክቱን ሰምተው እግዜር ይስጥልኝ ውሳኔያችሁን አልቀበልም ያሉበት፣ የጦርነትም ስጋት ያንዣበበት ዘመን ነበር ። ዘመኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከህዳር በሽታ ያገገመበት፤ ጣሊያን ከህንድ ባመጣችው የታመሙ ከብቶች የኢትዮጵያ ከብቶች ያለቁበት፣ ረሃብ ነግሶ ህዝቡንም ደቋቁሶ መንሰራራት እየታየ ያለበት ጊዜ ነበር። ዘመኑ ሲቻል በውድ ሳይቻል በግድ ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትውጥ የተዘጋጀችበት ነበር። የጣሊያኑ እንደራሴ አንቶኔሊ በውጫሌ ውል መፍረስ ሳቢያ የኢትዮጵያን መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ ረግጦ በይለያል ዘንድሮ አቅራርቶ በእትጌ ጣይቱም ባይገርምህ ላፈሩ ላገሩ ሆዱን ለጠጠር ግንባሩን ለጥይት የማይሰጥ ሰው እዚህ ያለ እንዳይመስልህ በሚል ምላሽ የተለያዩበት ነበር። ጣይቱ ምኒልክና ባንዳዎቹ ዘመዶቻቸው ጣይቱ አንቶኔሊን “የኔ ሴትነትና ያንተም ወንድነት የሚለየው እዚህ እንዳሻህ በተፈራገጥክበት የምኒልክ እልፍኝ ሳይሆን እዚያው ጦር ሜዳ ላይ ነው!!!…ሂድ!…ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ! እግሩን ለጠጠር፣ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ፣ ለአፈሩ ክብር አፈር ለብሶ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ” (ሜስ ደሞዝ፡ ከእቴጌ ጣይቱ ታሪካዊ ተውኔት) ብለው ከሸኙ በሁዋላ የጉያ ጠላትን መመንጠር መጀመራቸውን ድርሳናት ያወሳሉ። ክፉ ቀን በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ ጉድ እንዳየች ነው። የአድዋና እኛ ወጋችን ስለ ባንዳዎቹ አፈቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል ያወሳል። እነዚህ የጣይቱና የምኒልክ ስጋ ዘመዶች ናቸው። እንደ ገባኝ ለመንበረ መንግስቱ ቤተኛ ሆነው ሳለ ለጣሊያን ማደራቸው ሁለቱንም ጣይቱና ምኒልክን ግብግብ ነው ያደረጋቸው። እርግጥ ነው የሶስቱ ባንዳ መሆን ከሀዲ መሆን የጦርነቱን ውጤት አልቀየረውም። ቢሆንም ጣይቱና ምኒልክ በጣም ማዘናቸው መንገብገባቸው የሚታወቀው ምህረት ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “በሄዳችሁበት ይመቻችሁ!” አመላካች ነበር። የወጋችን መሰረት የባህሩ ዘውዴ Pioneers of change in Ethiopia ነው። እንደ ገባኝ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የለውጥ ሃዋርያት በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሀፋቸው የምዕራባውያን ትምህርት፣ ስልጣኔ እና ሃይማኖት ቀመስ ስለነበሩት ቀናኢ ኢትዮጵያውያን በጥሩ ሁኔታ አጥንተው አቅርበዋል። የባንዳዎቹም ወግ ከዚያው የተጨለፈ ነው።4 የቅድመ-አድዋ ዘመኗ ኢትዮጵያ የመንግስት ምክር ቤትም ውስጥ ሆነ በንጉሰነገስቱ ዘንድ የሀሳብ ማነቆና ሳንሱር የነበረ አይመስልም። የሀገሪቱ ነገስታትና ተወላጆቻቸው ተራው ህዝብም እና ምሁራኑም ሃሳባቸውን በነፃ ሲያንሸራሽሩ እንደነበር የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መጽሀፍ ብዙ አስደናቂ ብዙ አስደማሚ ትርክቶች ያስረዳሉ። ከአንቶኔሊ የቤተ መንግስት ድንፋታ በፊትም ሆነ በሁዋላ ጦርነት እንደሚኖር በወቅቱ ግንዛቤ ነበር። አብዛኛው ወገናችን አፍቃሬ-ሀገር፣ አፍቃሬ-ነጻነት ቢሆንም በወቅቱ የሶስቱ የአፈ-ቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል ጣሊያንን መደገፍ የአደባባይ ሀቅ ነው በዚያ ሀሳብ እና አቋም በማያስቀጣበት አስደማሚ ዘመን። በወቅቱ የብርቱ ፀረ-ጣሊያን አቋም አራማጅ ፊታውራሪ - የኛይቱ እትጌ ጣይቱ ነበሩ። እትጌ ጣይቱ ሁለት ተደጋጋፊ ድርጊቶችን ያራመዱ ይመስላል። በአንድ ወገን እንደነአለቃ አፅመጊዮርጊስ አይነቱን የጣሊያንን ሴራ ለቤተ መንግስቱ በማስታወቃቸው ዲፕሎማሲ እንዳያበላሹ የታሰሩትን ማስፈታት፤ በሌላ ወገን አፍቃሬ-ጣሊያን አቋም የነበራቸውን መመንጠር ነበር። ሁኔታውን አሹ ዋሴ እንዲህ ገልፆታል “ይህ ለአድዋ ጦርነት መነሳት ምክንያትና ዋነኛ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል አንቀፅ ፲፯ ላይ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት ቋንቋ አዋቂ ዓፄ ምኒልክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ አስራ ሰባተኛው አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት በመግለፅ ጉዳዩ ኢትዮጵያ የምትጐዳበት ስለመሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል ሲሆን እቴጌ በዚህ ወቅት ነገሮችን በጥንቃቄ ይከታተሉ ስለነበር ዓፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ሳይረዱ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ ቢያደርጉም እቴጌ ጣይቱ ግን እኒህ ሰው ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለዓፄ ምኒልክ በማስረዳት ከሦስት ዓመታት እስራት በኋላ ማስፈታቸው ይታወቃል። እቴጌ እንደተናገሩትም «ዓፅመ ጊዮርጊስ ቢታሰር ቢፈታም ለሀገሩ የሚገባውን ሠርቶ ነው። ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዮሴፍ፣ ጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳይስጠነቅቅዎ ቀረ?» በማለት የእቴጌ ጣይቱ የቁጣ መዓት ወደ ዮሴፍ ዞረ።” ሰማይ ከፍ ምድር ዝቅ ቢል በኢትዮጵያ ምድር ጣሊያንን ደግፎ ኢትዮጵያን ሰይፎ ለተሰለፈ ባንዳና ከሀዲ ከጣይቱ ነዲድ የሚያስጥል ምድራዊ ሀይል አልነበረም አፄ ምኒልክም ቢሆኑ። ጣይቱ ነፍስያቸው ነግራቸዋለች ባንዳን ከሀዲን ጉያ ይዞ እድገት፣ ባንዳን ከሀዲን ጉያ ይዞ እንቅስቃሴ፣ ባንዳን ከሀዲን ጉያ ይዞ ጦርነት የፈናጅራ መሆኑ፤ እኛስ የዛሬዎቹ ከዚህ ተምረን ይሆን? ካልተዘነጋኝ ስነቃላችንም ይህንኑ አስተሳሰባችንን ያንጸባርቃል። ጠላትማ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው፣ አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው። በዚህ ወቅት ነበር የእሳት ልጅ አመዶቹ፣ የጣሊያን ደጋፊዎቹ አፈ-ቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል በጣይቱ የቁጣ ነበልባል እቶን ፊት ተደንቅረው የተገኙት። ማን ይሆን የሚያስጥላቸው? ለመሆኑ አፈ-ቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል ማን ናቸው? የዘጌ ተወላጁ አፈወርቅ የጣይቱ የስጋ ዘመድ ሲሆን ለቤተ መንግስት ደጅ ጥናት ያስመጡት ጣይቱ ራሳቸው ናቸው። ጉግሳ በአድዋ ዘመቻ ወቀት የአትዮጵያ አልጋ ጠባቂ የነበሩት የዝነኛው የራስ ዳርጌ ልጅ ነው። ምኒልክ እና ጉግሳ ይዛመዳሉ፤ ራስ ዳርጌ የጉግሳ አባት የምኒልክ አጎትም ናቸው። ቅጣው የአዛዥ ዛማኑኤል ልጅ ሲሆን ሶስቱም የቤተ መንግስቱ ማደጎዎች ነበሩ። ይህ ለቤተ መንግስቱ ያላቸው ቤተኛነት እንዲሁም ለነገስታቱ ያላቸው የስጋ ዝምድና ለጣሊያን በመወገናቸው ከጣይቱ ቅጣት ሊያድንም ሊከልላቸውም አልቻለም። ምኒልክም ከጣይቱ በትር ሊያድኗቸው እንደማይችሉ ሲያውቁት አማካሪ ወዳጃቸውን አልፍሬድ ኢልግን እነዚህን ጎረምሶች ስዊዘርላንድ ውሰድና ቴክኒክ ትምህርት ቤት አስገባልኝ ብለው ሶስቱንም ስዊዘርላንድ ሰደው በዘዴ የሶስቱን ነፍስ አዳኑ። ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንዲሉ፣ በጦርነቱ ዋዜማ ቢያንስ ቢያንስ የምኒልክን ውለታ ዘንግተው አፈ-ቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስን፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌንና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤልን እዚሁ ኢትዮጵያ የጀመራቸው ባንዳነት ከተላኩበት ከስዊዘርላንድ ወደ ጣሊያን አስኮበለላቸው ከጣሊያን ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለመውጋት። የመኮብለላቸው እና ለጣሊያን ማደራቸው ወሬው ኢትዮጵያ ሲሰማ የምኒልክን አላውቅም የጣይቱን ግን እናንተው ገምቱ። እስቲ ይቺን ትርክት እንካፈል። አፈወርቅ ጣሊያን ሄዶም አላረፈም። ጣይቱን ዘመዴ ናት ብሎ አንጀት ሊያባባ የክርስቶስን ስቅለት የሚያሳይ ስእል ቢልክላቸው ጣይቱ እንዲህ አሉ “ይስቀልህ! ይ.....ስቀልህ! ስ..ቅ..ል ያድርግህ” አቤት መቃጠል! አቤት መንደድ!5 በጣሊያን በኩል ሲሮጥ የመጣን አህያ ጠበቅ አድርገህ ጫነው እንዲሉ ተንደርድረው እቅፏ የገቡላትን የቤተ መንግስት ቤተኞች ሸክፋ ለአፍሪካ ጦር አዛዧ ለባራቴሪ ኤርትራ ላከቻቸው እንደሚመችህ ተጠቀምባቸው ብላ። ጣሊያን እና ልበ - ተራራው ባራቴሪ ባንዶቹ እጁ እንደገቡለት ሀሳቡን ለማሳካት ከከሀዲዎቹ አንዱን በተለይ ጉግሳ ዳርጌን ነጥሎ የንጉስ ሳህለ ስላሴ የልጅ ልጅ፣ የራስ ዳርጌን የምኒልክ አጎትን የኢትዮጵያን አልጋ ጠባቂን ልጅ ጦርነቱ ተራዝሞ ባላባቱና ህዝቡ እርስ በርሱ ተባልቶ የምኒልክ አልጋ ይደክማል በማለት ምኒልክን ለማዳከም ጉግሳ ዳርጌን የአልጋው ይገባኛልን አጀንዳ አስነግቦ ነበር፤ ልብማ አለች አሉ ኤሊ። ዕድሜ ለአድዋ ሰማእታት! እድሜ ለአድዋ ጀግኖች! እድሜ ለጣይቱ! እድሜ ላባትና ለናቶቻችን! በለስ ለኢትዮጵያ ቀንቷት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። የከሃዲዎቹ እድል ፈንታቸው ምን ሆኖ ይሆን? የጣሊያን ያፍሪካ ጦር አምባላጌ፣ መቀሌ እና አድዋ ድል እንደተመታ ባራቴሪ ሶስቱን አፍቃሬ-ጣሊያን ባንዳዎች ሸከፈና ምጽዋ ሰደዳቸው። ባንዳዎቹ የጣይቱና የምኒልክ ዘመዶች አፈቄሳር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ልጅ ጉግሳ ዳርጌና ልጅ ቅጣው ዛማኑኤል አደራ የተሰጡት የምኒልክ ምስጢረኛና ወዳጅ አልፍሬድ ኢልግ አደራ-በል አደረጉኝ ብሎ ሲቃጥል መክረሙን ምኒልክ አውቀዋል። ምኒልክ ለኢልግ ማጽናኛ የላኩት ጦማር ኢልግን ማጽናናት ብቻ ሳይሆን በነዚህ ሶስት የቤተ-መንግስቱ ቤተኛ ባንዳዎች እሳቸውም እንደ ጣይቱ መናደዳቸውን የአድዋ ድልም እንኳን ንዴታቸውን አለማብረዱን ያሳያል። ምኒልክ ለኢልግ ያሉት ይህንን ነበር። “በነጉግሳና በነቅጣው ነገር ምን ያናድድሃል። እኔ መስደዴ ጥበብ የተማሩ እንደሆነ ይጠቀሙበታል ብዬ ነበር። አሁንም እኔን ጠልተው ከሄዱ የሄዱበት አገር ይኑሩ ጥጋባቸውን ይፈጽሙ። እኔንም እንምጣ ብለው ቢልኩብኝ አንድ ጊዜ ጠልታችሁኝ ሄዳችሁዋል ከሄዳችሁበት አገር ኑሩ ብዬ ላክሁባቸው። ለነዚያ ቀረባቸው እንጂ እኔን ምን ጎዱኝ ብለህ ነው።” እንደ ማሳረጊያ ይቺን ላክል ስለ አፈቄሳር አፈወርቅ። በሁዋለኛው ዘመን ነጋዴው፣ ደራሲው፣ ነጋድራሱ አፈወርቅ የፈረንጅ ክሶች የሚታየበት ፍርድ ቤትም ያስችል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጣሊያን ብድሯን ልትከፍል ኢትዮጵያን ወርራ አምስት አመት ስትቀጠቅጠን እንደገና የጣሊያን አቡካቶ ሆኖ፣ ለጣሊያን አድሮ፣ አፈ-ቄሳርነት ተሹሞ ያባቶቻችንን የናቶቻችንን መንፈስ ሲቀጠቅጥ ከርሞ ጣሊያን እንደወጣ ጅማ ተግዞ እዚያው ሞቷል። የአፈ-ቄሳር ሕይወት ይሄ ባንዳነት ይሄ ከሀዲነት በሽታ ይሆን እንዴ? አንዴ ከተጣባ የማይለቅ ያሰኛል። ወዳጄ አለም ስለ አፈ-ቄሳር ሲገልፅ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ምንም አይነት ፀፀት አልነበረበትም፣ ጣሊያን ጣሊያን እንዳለ ነው ያረፈው። እርስዎ አንባቢ ምን ይላሉ? ኢትዮጵያውያንን ማስከዳት ባንዳና አስካሪ ማድረግ የጣሊያን ቅድመ ጦርነት የስነ-ልቡና ስራ ነበር። በርግጥም ተሳክቶለታል። ቢሆንም እንደ ራስ ስብሃት እና ሓጎስ ተፈሪ ግን (እንደ ሜስ ደሞዝ ራይሞንድ ጆናስን ዋቢ አድርጋ አገላለጽ) ተሰብከው ክደው አልቀሩም። ጣሊያን ቋጠርኩ ሲል ቋጠሮው ሲፈታ ኖሯል። ራስ ስብሃት በግዞት ወደ አምባላጌ ተልኮ ታሰረ። ራስ ስብሃት ከአምባላጌ እስር ቤት በጥቅምት 1895 የተለቀቀው በጣሊያኖች ምህረት ነበር። ከሳምንት በኋላ ከጣሊያን ጎን ሆኖ መንገሻን መውጋት ጀመረ። በመንገሻ ጭካኔ የተበሳጨው ሓጎስ ተፈሪም ከጣሊያን ጋር በመወገን መንገሻን ሲወጋ ቆይቷል። በ1895 ሰንአፈ ላይ መንገሻ ሲሸነፍ በርካታ የጦር መሣሪያ፣ የቁም ከብት እና የተለያዩ ንብረቶችን ከሸሸው ጦር ላይ በመዝረፉ ሃይሉን አጎልብቷል። በ1895 የመጨረሻ ወራት ላይ ኹለቱ ኢትዮጲያውያን ከጣሊያን ጎን ተሰልፈው ነበር። ራስ ስብሃት እና ሓጎስ ተፈሪን ከጎኑ ማሰለፍ የቻለው ባራቴሪ የ "ከፋፍለህ ግዛ" ዕቅዱን ለማሳካት አንድ እርምጃ ተራመድኩ ብሏል። የመንገሻን ኃይል በማሳሳትም የራሱን ሠራዊት ቁጥር ከፍ ከማድረግ አንፃርም የኹለቱ ተከታዮች ከጦሩ ጋር መቀላቀል አስተዋፅኦ አድርጎለታል። ራስ ስብሃት እና ሓጎስ ከአምባላጌ እና መቀሌ ዘመቻዎች በኋላ በተለይም በየካቲት ወር ላይ የምኒልክን እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ ነበር ባራቴሪን ለመክዳት የወሰኑት። በመኾኑም የካቲት 13 ቀን ኹለቱም ወታደሮቻቸውን ከነሙሉ ትጥቃቸው በማስኮብለል የጣሊያንን ካምፕ ለቀቁ። የእነ ስብሃት ሠራዊት ምኒልክ ካምፕ ሲደርስ የጀግና አቀባበል ነበር የተደረገለት። ስብሃት እና ሓጎስ ከፍተኛ ውዳሴ ተደረገላቸው። ( የምኒልክን ይቅር ባይነት ልብ ይሏል) ባራቴሪ የገመተው ኹለቱ የካዱት መንገሻ ዮሐንስን በመኾኑ በምንም መንገድ ወደ ኢትዮጲያ ሠራዊት እንደማይቀላቀሉ ነበር። የሠራዊቱን ወደ ምኒልክ መመለስ የኢትዮጲያን ውስጣዊ መረጋጋት ያረጋገጠ ሲሆን የባራቴሪን ከፋፍሎ የመግዛት ዕቅድም ጥያቄ ውስጥ ከተተው። የነራስ ስብሃትን መክዳት ተከትሎ የአጋሜ ነዋሪዎች በጣሊያን ላይ ማመፅ ጀመሩ በርካቶች ኹለቱን በመከተል የከዳውን የሠራዊት ቁጥር በሦስት እጥፍ ከፍ አደረጉት።6 የእነ ስብሃትን መክዳት ቀድሞ የሰማው የደብረዳሞ አካባቢ ነዋሪም ባራቴሪ ላይ በማመፅ ለምኒልክ ታማኝነቱን አረጋገጠ። የክተት አዋጁ የጦርነት አይቀሬነት እና የጣሊያን ጦር ቅብጥብጥነት እያየለ ትግራይን በመውረሩ ኢትዮጵያም ለፍልሚያ ተዘጋጀች። ዝነኛው የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅም ነጋሪት እየተጎሰመ ተለፈፈ። “እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…”(አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት" በተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ገጽ 226) 3. የአድዋ ጦርነት ውሎ ጦርነቱ ባለ ብዙ ገጽታ ነው። ለምሳሌ ሽፍቶችና ባንዶች ቀደም ሲል በነራስ ስብሃት እንዳየነው እንዳመጣጣቸው ተስተናግደዋል። “ለአገር ሲሆን ሽፍታም ይጨምት ነበር” ይለናል ወንድወሰን ውቤ። “ደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ በዓጤ ምኒሊክ ላይ ሸፍተው ከምኒልክ ጭፍሮች ጋር በጦርነት የተፈታተኑ ሰው ናቸው። በዚህም በትግራይ ዘመቻ ጊዜ በምኒሊክ ላይ እንደሸፈቱና በረሐ እንደገቡ ናቸው። ምኒሊክ ሕዳር 24 ቀን መርሳ ላይ ሰፍረው ሳሉ የደጃዝማች ጓንጉል መልክተኛ ከዓጤ ምኒሊክ ዘንድ መጣ።መልእክተኛውም “ጃንሆይ ከእርስዎ ተጣልቼ በረሐ ገብቻለሁ። አሁን ግን በአገሬ ላይ የውጭ ጠላት ስለመጣባት የእርስዎና የኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና መጥቼ ከእርስዎ ከጌታየ ጋር ሁኜ ያገሬን ጠላት ልውጋ ብለዋል” ብሎ ተናገረ። ዓጤ ምኒሊክም ተደስተው “ይምጣ ምሬዋለሁ” ብለው ላኩ። ደጃዝማች ጓንጉልም መጥተው ካጤ ምኒሊክ ጋር ተገናኙ። ሠራዊቱም መኳንንቱም በእንደዚህ ያለ ጊዜ መጥቼ ከጌታየ ጋር ልሙት በማለታቸው እጅግ ተደሰቱ።” (ጳውሎስ ኞኞ፣ዓጤ ምኒሊክ፣፬ኛ እትም 2006 ዓ.ም. ማንኩሳ አሳታሚ፤ ገጽ 167)። እሺ ያለውን በማባበል እምቢ ያለውን በጦር እንዲገብር ተድርጓል። ሚንጊ ስለአውሳው መሀመድ አንፋሪ “የጣሊያን ተስፋ” እንዲህ ተርኳል። “የአውሳው ባላባት መሀመድ አንፋሪ ምንም እንኳ ለተወሰነ ጊዜ የቱርክና የግብጦች ተፅዕኖ ቢደረግበትም ቱርኮችና ግብጦች ከተባረሩ በሗላ እንደገና ከንጉስ ሳህለ ስላሴና ከሸዋ መሳፍንቶች ጋር ግንኙነታቸውን አፅንተው ይኖሩ ነበር። በተለይም ከአውሮፓ ከፈረንሳይና ከኢጣሊያ በአሰብ በኩል የሚመጡ የጦር መሳሪያዎችንና ልዩ ልዩ እቃዎችን እየተቀበለ ወይም ለሚያደርሱት ሸኚ እየሰጠ ወደ አንኮበር በመላክ ግንኙነቱን ጠብቆ ይኖር ነበር። ንጉስ ሚኒልክም ንጉሰ ነገስት ከሆኑ ከሆኑ ወዲህ በመጀመሪያ ጊዜ ይኸው መልካም ግንኙነት አላቋረጠም ነበር። ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የጣሊያኖች ተፅዕኖ ማየል በተለያየ የስጦትና ማማለያ ሃሳቦችን በማቅረብ ሀሳቡን እንዲቀይር አደረጉት ከዚያም ግብር በመከልከሉ ዐፄ ሚኒልክን መክዳቱ ታወቀ። ኢጣሊያኖችም እሱን መሳሪያ አድርገው በአንኮበርና በሀረር ግንባር ጦር ሊልኩ ነው የሚል ወሬ ተሰምቶ ነበርና ዳግማዊ ምኒልክ የሸፈተወን መሀመድ አንፋሪን እንዲወጉ ሶስት መኳንንትን ላኩ እነዚህም ራስ ወልደጊዮርጊስ አቦየ፣ ደጃዝማች ተሰማ ናደውና የአንኮበሩ አዛዥ ወልደ ጻዲቅ በበላይ መሪነት ነበር።ሶስቱም መኳንንት ኢጣሊያኖች በጣም ተስፋ ያደረጉበትን መሀመድ አንፋሪን በጥር ፲፯ ቀን አሸነፉ። ከዚያም የአንኮበሩ ሊቅ አለቃ ዘወልድ አዛዥ ወልደ ጻዲቅ አውሳ ድል አድራጊነት በቅድሚያ እንደቀናው አንተም ምኒልክ በዓድዋ ደግመህ አሸንፍ ለማለት ቅኔ ተቀኙ ምኒልክ ድገም ድምፀ የብቦ እስመ ወልደ ጻድቅ ቀደመ ድምፅ ይባቤ በገቦ ዓልቦ ዘነገሰ ቅድመ ዚዓከ ወድሓረ ዚኣከ ዘይንነግስ ዓልቦ” (ምንጭ ካስትሮ ኔላ ቴራ ዴል ንጉስ ና ኢን አቢሲንያ ከሚባለው ከ አናራቶሪ መጽሀፍ ጳውሎስ ኞኞ እንዳሰናዳው)። ይህ የድል ብስራት በኢትዮጵያ ጦር ዘንድ እንደተሰማ ጦሩ ከፍተኛ ብርታት እንደተሰማው ተገልጿል።7 4.ጦርነቱ ጦርነቱ በድል ነው የተጠናቀቀው። ግን ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው። ከመቀሌና ከአድዋ ጦርነቶች ሁለቱን ለአስረጅነት እናውጋ። እኔ በምገኝበት ቀዬ የካቲት ወር ውስጥ የፍቅር ቀን ተብሎ ይዘከራል። አጋጣሚው ጥሩ ስለሆነ ስለ እትጌ ጣይቱ የመቀሌ እና አድዋ ጦርነት ተሳትፎ አንዳንድ ልል ነው፤ ተሳትፎው በዋነኛነት ፍቅርንና ህይወትን ስላካተተ። ነበርክ ወይ እንዳትሉ መጻህፍት አመሳክሬ ነው። አጼ ምኒልክ እድለኛ መሪ ነበሩ። ሹማምንቱ፣ ሳር ቅጠሉ ሁሉ አንድ ጉዳይ ከውኖ ሊያስመሰክር መጣደፉን መዛግብት ደጋግመው ያስነብቡናል። ምኒልክ አዋጅ አስነግረው ካዲስ አበባ ወደ ትግራይ በእግር ጉዞ ጀምረዋል። እነሱ አምስት ወር ያለማቁዋረጥ ለተጉዋዙት እኔን ዛሬ ደከመኝ። ቀድመው የደረሱት እና ቦታው የነበሩ መኳንንት ንጉሱ ሳይደርሱ የአምባላጌውን የጣሊያን ጦር ደርማምሰው መቀሌ ደርሰዋል። የአምባላጌው ድል ያጀገናቸው አባቶቻችን በራስ መኮንን መሪነት የመቀሌውን የጣሊያን ጦር ምኒልክ ከመድረሳቸው በፊት ለመምታት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ብዙ የሰው ሕይወት አስቀጠፈ። ዋና ጦር መቀሌ ደርሶ ምክር ሲቀመጡ ጣይቱ መኮንንን ምን ነካህ እንዴት ይህንን ሁሉ ሰው ታስጨርሳለህ ብለው ገሰጡ። ጻህፍት እንዳተቱት መኮንን ራሳቸውን በጣሊያን የመድፍ አረር ለማስጠፋት አፋፍ እንደቆሙ አሉላ ደርሰው ነው ምን ነካህ በማለት ያዳኑዋቸው። በወቅቱ የምኒልክ ጦርም የመቀሌን የጣሊያን ጦር ለማሸነፍ ከመኮንን የተሻለ የጦር መላ አልነበረውም። ሰው ብርቱው የመቀሌ ምሽግ ድረስ እየሄደ አለቀ። 1.1) ጣይቱና ፍቅርና መቀሌ የመቀሌን የጣሊያን ጦር ምሽግ ብርታት ጣይቱን ለፈጣን መላ ጋበዘ። ለአጃቢ ወታደሮቻቸው የመስዋዕትነት ግብዣ አቀረቡ ሕይወታችሁን ስጡኝ። የሚገርመው አንደኛ ለመስዋዕትነት የተጋበዙት የተላክንበትን አሸንፈን ተመልሰን መጥተን እንኖራለን የሚል ተስፋ ሰንቀው አይደለም በጀ ያሉት ራሳቸውን ለመስዋዕትነት አዘጋጅተው ነው። ሁለተኛ ጣይቱም ቢሆኑ ጥያቄያቸው ትሰዋላችሁ ነው። የሚገርመው የጣይቱ የመስዋዕትነት ክፍያው ነው። ማጭበርበር የለ፣ ታሪክ ያስታውሳችሁዋል የለ፣ ሀውልት ይቆምላችሁዋል የለ፣ ስማችሁ ይጠራል የለ ። ለቆማችሁት እሸልማለሁ፣ ለምታልፉ ተዝካራችሁን አወጣለሁ የሙት ልጆቻችሁን አሳድጋለሁ! በቃ። ከ600- 900 ወታደሮች ቀርበው ተሰናብተው ሄዱ። ከዛ ያለፈው ታሪክ ነው። እነዚያ ወታደሮች የመቀሌውን የጣሊያን ጦር የመጠጥ ምንጭ ያዙ። ጣሊያን የሆዱ ነገር አሸነፈውና የመቀሌው ምሽጉ ባስደናቂ ሁኔታ ተሰበረ። 1.2) ጣይቱና ፍቅርና አድዋ በጊዜው እንደነበረው ልማድ ጣይቱ ወይዛዝርቱና ደንገጡሮቻቸው ዓይነ-ርግብ (የፊት መሸፈኛ) አድርገው ነው ወደ ትግራይ ጉዞ ያደረጉት። ሰው አብሮ ሲኖር ከቤቱም ብቻውን ሲወጣ እንደሚፈጠረው ያለ ነገር በጉዞም ላይ ተፈጥሮዋል። የፊት መሸፈኛው ማንነትን ስለማያሳይ የተገለጠ እለት ድንቅነትም አለው። ከአድዋው የጣሊያን ጦር መሃል አሁን በዘመናችን ኮማንዶ እንደምንላቸው በሻለቆች የሚመሩ ልዩ ሐይል አጥፍቶ ጠፊዎች ነበሩበት። እነዚህ የጣሊያን አጥፍቶ ጠፊ ሐይላት በአድዋ ኮረብቶች የፈሰሰውን የኢትዮጵያን ጦር መሃሉን ለመምታት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በዚያ ግንባር የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ነቅሎ መሸሽ ጀመረ። ሽሽት የጀመረውን የሚያቆመው ሀይልም ያለ አልመስል አለ። ያኔ ነበር መለኛዋ ጣይቱ ወይዛዝርቱ ከነደንገጡሮቻቸው የፊት መሸፈኛቸውን ገልጠው ከጦሩ ጀርባ ብቅ ያሉት። ጣይቱን በዓይን የማየት መግነጢሳዊ ድንቅነት፣ በአጃቢውም ንጉስህ ሳይመለሱ እኔን ሴቷን አልፈህ የት ልትገባ ምን አገር አለህ? ነበረ የጣይቱ ንግግር። ሴት የላከው ሞት አይፈራም እንዲሉ የነጣይቱ መገለጥ እና ንግግር የጦሩን ሽሽት ከማስቆሙም ባሻገር ጦሩ ተመልሶ ወደ ውጊያ እንዲገባና የጣሊያንን አጥፍቶ ጠፊ ሐይላት ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፍ አድርጎ በማስቀጣት ነበር ጣይቱ የአድዋን ጦርነት መክሊታቸውን የተወጡት።ምን ይባላል? አጀብ- አጃ-ኢብ ከማለት በስተቀር።ምስጋና ለጣይቱ! ምስጋና ላባቶቻችን! ምስጋና ለናቶቻችን! ምስጋና ለነፃነት ፍቅር!8 ቁርጥራጭ ትርክቶች የአፄ ምኒልክ ስልተኛነትና የአድዋ ድል፤ አፄ ምኒልክ ስልተኛ ገዢ መሆናቸውን ታሪካቸው ሲያሳየን፥ እውነትም እኮ አድዋ ላይ የተገኘው ድል ከውጊያው ተጨማሪ በንጉሡ የጦር አቅድ አውጪነት ነው ለማለት ያስደፍራል። አንደኛ፤ ሹመት ሲሻኝ እንደጻፈው፥ አፄ ምኒልክ የአድዋ ጦርነት እንደሚነሣ ቀደም ብለው ስላወቁት፥ ሠራዊታቸው ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ ሲጓዝ እንዳይቸገር በሚሰፍሩበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ስንቅ ቀደም ብለው አከማችተው ነበር። ሁለተኛ፤ አድዋ ላይ የኢጣልያን የጦር ሠራዊት ከምሽጉ ውስጥ እንዳለ ሊገጥሙት ፈልጎ ነበር፤ አልፈለጉም። የመሸገን ጠላት ለማሸነፍ እንደማይቻል በአፄ ዮሐንስ ላይ ሰሐጢ ላይ ከደረሰው ሽንፈት ስለተማሩ፥ በዘዴ አስወጡት። የምኒልክ ጦር ተዳክሟል የሚል ሰላይ ላኩበት። እውነት መስሎት ሲወጣላቸው ልብ-ራሱን አሉት። ሦስተኛ፤ አፄ ምኒልክ ጦርነት እንደ ቸዝ ጨዋታ መሆኑን ያውቁ ነበር። በቸዝ ጨዋታ ንጉሡ ከሞተ፥ ሠራዊቱ እንዳለ ቢሆንም፥ ንጉሡ የሞተበት ተጫዋች ተሸናፊ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር መተማ ላይ ባደረገችው ጦርነት ያገኘችውን ድል ያጣችው ንጉሣችን አፄ ዮሐንስ ጦሩን ስለመሩት ነው። ንጉሡ ተመትተው ሲወድቁ፥ ሠራዊታችን ተበተነ። ከኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሞቷል። ግን ከሞቱት ውስጥ አንዱ ንጉሡ ቢሆኑ ኖሮ፥ የተሸነፈው ጠላት መሸሹን ትቶ ተመልሶ መጥቶ ድላችንን ይቀማን ነበር፤ አድዋም ሌላዋ መተማ ትሆን ነበር። ግን በንጉሡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦር ስልት ዐዋቂነት ጠላት ተሸነፈ(ምንጭ ያሬድ ሀበሻ)።በወጋችን ላይ ከጦርነቱ ውጪ ምኒልክን ለመግደል ጣሊያን ብዙ አጋሚዶዎችን አደጋ እንዲጥሉ መሳሪያ አሳታጥቆ ነበር። ጾምና የአድዋ ጦርነት የአድዋ ጦርነት የተደረገው በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የተደረገው የመቅደላ ጦርነትም በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነው የተካሄደው፡፡ ፆምና ውጊያ አብሮ ስለማይሄድ በአድዋ ጦርነት ወቅትም ግብፃዊውን ጳጳስ ሠራዊቱን ይፍቱትና እንደ ልቡ ይዋጋ ቢባሉም ባለመፍታታቸው ከኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት ጿሚ የሆነው እየፆመ ለመዋጋት ተገዶአል፡፡ በመቅደላ ውጊያም ግብፃዊው ጳጳስ ጦሩን አልፈታም እንዳሉ ይነገራል። የኦሮሞ ፈረሰኞች "… የጣሊያን ሠራዊት በመገስገስ ላይ የነበሩትን የኦሮሞ ፈረሰኞች በተመለከተበት ወቅት የሚገባበት ጠፋው። ቀድሞ በሠራዊቱ ውስጥ ስለ ኦሮሞ ፈረሰኞች የተነገራቸው ኋላ ቀር እና ተራ ተዋጊዎች እንደኾኑ ነበር። በጦር ሜዳ ላይ የተመለከቱት ግን ፈረሰኞቹ እጅግ ፈጣን እና የተካኑ መሆናቸው ነበር። የጀ/ል አርሞንዲ የበታች ከኾኑት መካከል ጂዮቫኒ ቴዶን ለሠራዊታቸው መሸነፍ ቁልፉን ሚና የተጫወቱት የኦሮሞ ፈረሰኞች መሆናቸውን መስክሯል። የወቅቱን አስፈሪ ሁኔታ ሲገልፅም " ፈረሰኞቹ ወደ ሸለቆው ሲወርዱ በድንገት የገነፈለ ጥቁር ባህር ይመስሉ ነበር" ብሏል። በወቅቱ ሌ/ኮ ጊለዮ እንዲሁም በመጨረሻ ራሱ ጀነራል አሪሞንዲ አንድ በአንድ መገደላቸውን ጠቅሷል። በርካታ የጦር መሪዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል። ሌ/ኮ ጋሪባልዲ ፔናዞ አና ሌ/ኮ ማዞሌኒ የአሮሞ ፈረሰኞችን ጦርና ጎራዴ በመፍራት በራሳቸው ሽጉጥ ራሳቸውን አጥፍተዋል። ቴዶኔ ሁኔየታውን ሲገልፅ በተለይ ኮ/ል ፔናዚ መጀመሪያ የተኮሰው ጥይት ስላልገደለው ለኹለተኛ ጊዜ ደረቱን በራሱ ጥይት መምታቱን ገልፇል። ራሱ ታዶኔ ቆስሌ የተማረከ ሲሆን ጦርነቱም በዚያው ተጠናቋል።..." (ራይሞንድን ዋቢ አድርጋ ሜስ ደሞዝ እንደተረከችው)።9 የአድዋ ጦርነት ባለውለታዎች “ደብዛዛዎቹ የአድዋ ጀግኖች” ስለ ደብዛዛዎቹ ጀግኖች ግርማሥላሴ ሰይፉ በእውቀቱ ስዩምን (አዲስ ጉዳይ ቁ.153) ጠቅሶ ባቀበለን ሁለት ትርክት ስለ ጦርነቱ ባለውለታዎች ወግ እንጀምር። 1)".... ታሪካችን የአዳራሽና የእልፍኝ ብለን እንክፈለዉ:: ሊቆቻችን የተጠመዱት "ባዳራሹ" የተከሰተዉን በመተንተን ነዉ:: የእልፍኙ (የጓዳዉ) ጀብዱ ብዙ አይወሳም:: እስቲ አስቡት እናቶቻችን ከ 600 ኪ.ሜ በማያንስ ርቀት ዉስጥ በየጣብያዉ ተንቀሳቃሽ ማድቤት እየገነቡ 100 ሺ ሰራዊት ለሁለት ወር ያህል በየቀኑ መመገብ ችለዋል:: ገ/ሥላሴ ይህንን ሲመሰክሩ ' (ሠራዊቱ) ሁለቱን ወር ሙሉ ግብር እየበላ ተጉዋዘ እንጂ ወታደር የስንቅ አቁማዳዉን አልፈታም' ይላሉ:: ያንን ሁሉ ሠራዊት በዚህ አይነት ቀጥ አድርጎ መመገብ መቻልን የመሰለ ምን ጀብድ ይገኛል!!! ይህንን ለማድረግ ሴቶች ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ለምኔ ብለዉ በምድጃ መለብለብ ነበረባቸዉ:: ግን ለአንዲት እንጀራ ጋጋሪ የቀረበ ፉከራ ሰምታችሁ ታዉቃላችሁ? አለመታደል ሁኖ የምጣድ ጭስ የባሩድን ጭስ ያክል ከያኒዎችን አይስብም:: ላገር ደም ማፍሰስ እንጂ ላገር ላብ ማፍሰስ እንደ አገልግሎት አይታሰብም:: ...”። 2)"... ቀረፂ ብሆን ኑሮ አድዋ ላይ የወጥ ድስት ተሸክሞ የቆመ ጀግና ቀርጨ አቆም ነበር:: ጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ ስለ አድዋ የጉዞ ስርዓት ሲዘግቡ 'ከጦሩ ጀርባ ጠንካራ ጠንካራ ሻንቅሎች ተመርጠዉ በበገፈጅ : በሰታቴ የተሰራዉን (ወጥ) በእንቅብ ተሸክመዉ ይዉላሉ' በማለት መስክረዋል:: <<በገፈጅ>ና <<ሰታቴ>> የትልልቅ ድስት ስሞች መሆናቸዉ ለዘመናዊ አንባቢ ማስታወስ አለብኝ:: በገፈጅ ሙሉ በግ የሚችል ድስት ነዉ:: ታድያ ለእናት ሀገሩ ሙሉ በግ ተሸክሞ በጦር ሜዳ ለዋለ ዜጋ መታሰብያ ሐዉልት ይነሰዉ? ለነገሩ ብዙዎቻችን አርበኛ ሲባል ወደ ዐይነ ህሊናችን የሚመጣዉ ጋሻና ጣር የተሸከመ ጎልማሳ ነዉ:: የጀግኖችን ምሳ በግዙፍ ድስት ተሸክሞ ዳገት የሚወጣዉን ቁልቁለት የሚወርደዉን ወጠምሻ እንደ አርበኛ ለመቀበል አልተለማመድንም:: ነገሩን አገላብጠን ከተመለከትነዉ የኒህ ስም የለሽ በገፈጅ ተሸካሚዎች አስተዋፅኦ ከነባልቻ ከነአሉላ አስተዋፅኦ ቢበልጥ እንጂ አያንስም:: እንዲያዉም እነ ባልቻ እነ አሉላ ጉልበታቸዉን የሚቆነጥሩት ከዚህ ድስት ሳይሆን ይቀራል?!” መቼምና በምንም መልኩ ቢታይ የጦርነት ደግ የለውም። በሕይወት ላይ፣ በአካል ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የመንፈስ ስብራት ቀላል አይደለም። አካባቢስ ቢሆን ቀላል ይበከላል እንዴ? የሃያ ሺና ሰላሳ ሺ ሰው እዳሪ፣ የደኑ መጨፍጨፍ ወዘተ የአካባቢው ነዋሪ አይናገረው እንጂ ዋና ገፈት ቀማሽ ነው። ችግሩ ከዚያም ያልፋል በፊውዳሉ ዘመን ነው አሉ። ያንዱ ባላባት ነፍጥ አንጋቢ ሲመሽ ለቀለብ እና ለአዳር ወደ አንዱ አርሶ አደር ቤት ይገባል። ከመስተንግዶው በላይ የአርሶ አደሩን ሚስት ይዞ ለማደር ስማ (የአርሶ አደሩን ሚስት እያመላከተ) ይቺ እህትህ ቁርጥ አንተን አይደል እንዴ የምትመስለው? ብሎ ይዟት አደረ። አርሶ አደሩም ስነ ቃል እንዳቆየልን ከአገር እኖር ብዬ ልጅ አሳድግ ብዬ ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ አንጎራገረ። አንድ ወዳጄ ወደ ገደለው እንግባ ይላል። ወደ ዋናው ጉዳይ እንደ ማለት ነው። የአምባላጌን የመቀሌን የአድዋን ጦርነት በተለይ አድዋን ስናስብ ድሉ እየጋረደን የማናያቸው ትናንሽ የሚመስሉ ግን ደግሞ ለድሉ መገኘት የነበራቸው ሚና ቀላል ያልሆኑ ግብአቶች አሉ። ወደ ትግራይ የዘመተው ወገን መቶ ሺ ይገመታል የጣሊያኑ ሰላሳ አርባ ሺ ሲታከለበት መቶ ሃምሳ ይሆናል። የቤት እንሰሳት ሲታከሉበት ቁጥሩን ማስላት ነው እንግዲህ። እነዚህ ሁሉ በልተው ጠጥተው ማደር አለባቸው። ይህ ጦርነት ከክተቱ እስከ ድሉ አምስት ወር የፈጀ መልሱን ካሰብነው ደግሞ ስምንት ዘጠኝ ወር ማለት ነው። የስምንት ወር የእግር ጉዞ፣ የስምንት ወር የመንገድ መኝታ፣ ዝናቡ ጸሃዩ ውርጩ ቁሩ ብርዱ ሀሩሩ፣ የዚሁ ሁሉ ሰውስ ስንቅ እንዴት ነበር? “እነበሶ እነድርቆሽ እነሽምብራ በስልቻ ባህያ ዠርባ ወይም በሰው ትከሻ አመት ወይም ይበልጥ ተጉዘው ስንቅ ሆነው በገልና በገምቦ ውሃ ተቀድቶ ያቡጀዲ ነጠላና ሱሪ ተለብሶ በእንደዚህ ያለ አኳሁዋን ተዘምቶ” (ተክለሀዋርያትን ባህሩ ዘውዴ እንደጠቀሰው) ለማተባቸው ያደሩ የሰሜን ኢትዮጵያ አርሶ አደር እና ካህናት ያላሰለሰ ርብርቦሽ ታክሎበት ነው ድል ማግኘት የተቻለው። ለማስታወስ ያህል ለማተባቸው አድረው የወገንን ድል የናፈቁ እንዳሉ ሁሉ ከጣሊያን መሳሪያ ተቀብለው የኢትዮጵያ ጦርን የወጉ አጋሚዶዎች ሽፍቶች እንደነበሩም ብዙ የፈረንጅ ድርሳናት እማኝ መቁጠር ይቻላል።10 ይሄም በዛ ተብሎ የአምባላጌ የመቀሌ የአድዋ ጦርነት ከመካሄዱ ቀደም ብሎ የህዳር በሽታ አገሩን አድቆት፤ ጣሊያኖች ከህንድ የታመሙ ከብቶችን አስመጥተው የኢትዮጵያን ከብት ያስጨረሱበት በዘመናችን እሳቤ እንደ ባዮሎጂካል ዋር ፌር የተጠቀሙበት ማግስት ነው ጦርነቱ የተካሄደው። በወጋችን ላይ ስንቅና ትጥቅን አስመልክቶ እንደ ዘመናችን ጦርነት ተበድሮ ውጊያ የለም። እያንዳንዷ ሳንቲም ከካዝና ወጥታ ነው አውሮፓ ኢትዮጵያ ላይ ኢምባርጎ አድርጋ ስለነበር ከጥቁር ገበያ ነው መሳሪያም ጥይትም የተሸመተው። አንዱ ወንድማችን ምኒልክ ካዝና ውስጥ ከ7-10 ሚሊዮን ብር ነበራቸው እሱ ስለነበራቸው ነው ያሸነፉት ይላል። እነ መንገሻ ምንም ስላልነበራቸው ነው ጣሊያን በቀላሉ ሰባብሮ ትግራይን የተቆጣጠረው የሚል ወግ አለው ብር ብቻውን ዋጋ ያለው ይመስል። ጥናቱን ቢገፋበት ግን ጦርነቱን ከኢኮኖሚ አንፃር ለማየት ጥሩ ግብአት ይሆናል። የሆነ ሆኖ ብር አይበላም ይሸመትበታል እንጂ። ለሸመታውም ለሁሉም እህሉም ውሀውም መገኘት አለበት። ይህንን ለአትዮጵያ ጦር እና ፈረስ የሚሆን ቀለብ ያለ ምንም ማንገራገር የተሸከመው የሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ የትግራይ አርሶ አደር ነው። የፍቅር የነጻነት ስጦታ። “ብታምኑም ባታምኑም” ይህ ስጦታ ለጦርነቱ ድል ወሳኝ ግብአት ነበር። ይህ የጦርነት ሸክም የሰማእታቱ አስከሬን እንዲቀብር የተተወለት ለአምባላጌ ለመቀሌ የአድዋ አርሶ አደር እና ካህን ነው። ይህ እንግዲህ የጣሊያን ጦር ባካባቢው የሰራውን የጸረ-ኢትዮጵያ ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ ግምትም አስገብታችሁ ነው። ተራውን ነዋሪ እንተወውና በጊዜው እኮ ራስ መንገሻም ሆኑ መኳንንቶቻቸው ለጣሊያን አድረው ነበር። አውአሎም የሳይኮሎጂካል ዋር ፌሩ ስራ የተሳካላቸው ለጣሊያን ያደሩ ስለነበር ነው። የትግራይ መኳንንቶች ወደ ምኒልክ ጎራ ሲመለሱ ኤርትራውያኑ በዚያው ነው የቀሩት። ይህ እንግዲህ ባሽ ባዙቆችን (መርሰነሪዎችን) ሳናነሳ ነው። ፊት ለፊት አይገለጽ እኛም ወዳጆቻችንን ላለማስቀየም አንናገረው እንጂ ያ ጦርነት ኤርትራ ውስጥ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ አፍን ሞልቶ ጣሊያን ያሸንፍ እንደነበር መገመት ይቻላል። የኢትዮጵያ ጦር መረብን ያልተሻገረበት አንዱ ምክንያት ያንን መቶ ሺ ጦር የሚያሳድር ቀለብ የማቅረብ ፍላጎት እንዳልነበር ቅድመ ጦርነት መረጃዎች ለምኒልክ ደርሰው ስለ ነበር ነው። ቅድመ እና ድህረ ጦርነት ሕይወቱንም ለኢትዮጵያ ነፃነት ለለገሰው ምስጋና ለድምፅ አልባው ለሰሜን ኢትዮጵያ አርሶ አደር እና ካህናት። ምናልባት መንገሻ ብር ቢኖራቸው አይሸነፉም ነበር ምኒሊክም ብር ስለነበራቸው ነው ያሸነፉት ያለው ወንድማችን ወግ በዛሬ እሳቤ ይሰራ ይሆናል። መስፍን ነጋሽ የአድዋ ልጆች ምኒልክ መለስ እና እኔ በተሰኘ ወጉ እንዲህ ይላል። “ዛሬ ዛሬ መዝሙሩ “መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ” ማለት ሆኗል። የአድዋ የነጻነት መንፈስ ይህን ሲሰማ መሸማቀቁ አይቀርም። እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ምኒልክስ ጣልያንን አስገብተው መንገድና ፋብሪካ ማስገንባት ይችሉ አልነበረምን? ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው የምኒልክ ኢትዮጵያ ሀብታም አገር ሆና ነበርን? ከድህነት መላቀቅን የሚጠላም የሚቃወምም የለም። የአድዋ የነጻነት መንፈስም በድህነት መኖራችንን አይቀበልም። ነገር ግን ከቁሳዊ ሰቀቀን መላቀቅ የዘመናችን የአድዋ የነጻነት መንፈስ ብቸኛና በቂ ግብ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የዜጎች መብታና ነጻነት የሚታፈንበትን፣ መድሎዎና ጭቆና ተቋማዊና ሕጋዊ ቅርጹን ለውጦ የሚቀጥልበትን አገዛዝ የአድዋ የነጻነት መንፈስ አጥብቃ ትጸየፈዋለች።” የጦርነቱ ገጸ ባህርያት 1) ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ) እና ደጃች ባልቻ (አባ ነፍሶ) ስለፊታውራሪ ገበየሁ አዲስ አበባ ድረስ ተማርኮ መጥቶ የነበረው የኢጣልያ መኰንን ፣ጆቫኒ ቴዶኒ የጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል.. <<በቢያን ኪኒና በማዘቶ ለሚመሩት መድፎች እየተመቱ አበሾች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶ ‹‹ፈሪ አንዴት ትሸሻላችሁ እኔ እንዴት እንደምሞት ለንጉሱ ሄዳችሁ ንገሩ›› በማለት ፈረሱን በአለንጋ አስነስቶ በግልቢያ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ፡፡እሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከታትሎ ገብቶ ከመድፎቹ ጋር ተጨፋጭፎና ገድሎ መድፈኞችን ማረከ፡፡የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የእኛዎቹ ጀግኖች አብረው በመውደቅ የእርሱን ሬሳ አከበሩት>> በማለት ገልጾታል፡፡ የአድዋን ስላሴ ጠላት አረከሰዉ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰዉ ፊታውራሪ ገበየሁ በጦርነቱ ተሰዋ ፡፡እርሱን የሚተካ ሌላ የአድዋ ጌጥ ፣ሌላ ጀግና በአድዋ ደምቆ ታየ….ባልቻ ሳፎ11 (ባልቻ አባ ነፍሶ)፡፡ እንዲህም ተባለ… ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤ ክብር ለአድዋ ጀግኖች ይሁን!!! (ምንጭ፡ ቁም ነገር መሃመድ) ምንጭ (የኢትዮጲያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሰ ፣በተክለጻዲቅ መኩሪያ ፤የአለም ምርጥ ጀግኖች፣ ከዋለለኝ እምሩ) 2) የአምባአላጌው ሰማዕት - ፊታውራሪ አባ ውርጂ የአድዋው ጦርነት ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ አምባላጌ ተራራ(አምባ) ላይ የመሸገውን የጠላትን ጠቅላላ የጦር አያያዝ ለመገመት በፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራ የሚመራ 1200 የሚያህል ጦር የአምባላጌን ዙሪያ አስሶ እንዲመለሥ ታዘዘ። ኅዳር 29 1888 ሊነጋጋ ሲል ጦሩ ተንቀሳቅሶ ከአምባው ተጠጋ የዚያን ጊዜ ከጣልያን ቃፊሮች ጋር ተገናኘ እና ተኩሥ ልውውጥ ሆነ። በሙሉ አምባው ላይ የነበረው የጣልያን ጦር ለውጊያ ተንቀሳቀሰ። የገበየሁ ጦር አምባውን ለመውጣት በሚሞክርበት ጊዜ የጣልያን ጦር ከላይ ወደ ታች ያጠቃ ጀመር። የኢትዮጵያ ወታደር ከፊት ያለው ጓደኛው ሲወድቅ እራሱም እስኪወድቅ ድረስ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አላለም። ሁኔታው ሲታይ የፊት መንገድ ብቻ እንጂ የኋላ መንገድ የሌለ ነበር የመሰለው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑ ከአምባው አናት ደርሰው የጨበጣ ውጊያ ጀመሩ። በዚህም ደህና እየቀናቸው ሄደ ጀኔራል ቶዞሊ ከወዲህ ከወዲያ እየተዘዋወረ በሚያዋጋበት ጊዜ ድንገት ፊታውራሪ አባ ውርጂ ከሚባል የራሥ መኮነን ሰው ጋር ተገናኘ፤ ሽጉጡን እስኪያወጣ ድረስ አባ ውርጂ ጊዜ አልሰጠውም። ትግል ገጥመው ተያይዘው ገደል ገቡ እና የሁለቱም የሕይወት ፍፃሜ ሆነ። በዚህ ምክንያት እንዲህ ተብሎ ተገጠመ፦ ጀኔራል ባህር ማጆር ቶዞሊ ማን ይነካዋል ያለ ፈጣሪ ገደል ሰደደው ውርጂ ፊታውራሪ (ምንጭ አበጋዝ ዘወሎ) 3) የአምባላጌ ሰማእታት ወንድምና እህት ጊድን ገብሬ የሚባል የላስታ እና የዋግ የጦር መሪ ነበር፤ እህቱም ጥይት በቀሚሥ ጫፍ እየቆረጠች ስታቀብል አብራ ተሰውታለች። እኒህ ሁለት የአንድ ሰው ልጆች ሕይወታቸውን ለሀገር እና ወገን ክብር ሲሉ በመሰዋታቸው እንዲህ ተብለው በግጥም ተሞግሰዋል፦ ጀግናው ጊድን ገብሬ የሜዳው ዝሆን ፈረሱን ጫኑለት ይነሳ እንደሆን ወፍጮ ቢወቅሩት አይለሰልስም በጊድን ግንባር ማንም አይደርሥም የጊድን እኀት ምጥን ወይዘሮ ጥይት አቀባይ እንዳመልማሎ (ምንጭ ያሬድ ሀበሻ)12 4) የኢዮብ ብርሃነ አያት እና አድዋ ኢዮብ ብርሃነ የአድዋ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ትውልድ ነው። ካያቱ የቀሰመውን ያካፍለናል። ኢዮብ እንዲህ ይላል። ይህ የምነግራችሁ ድርሰት አይደለም! ጀብደኝነትና ርካሽ ዝነኝነት ፍለጋም አድርጋችሁ አትውሰዱብኝ! እውነት ነው ትናንትና ማን ነበርን? በማን ደምና አጥንት ላይ ነው ዛሬ የቆምነው? ለነፃነት ክብር ብለው ከቤታቸው ወጥተው የቀሩ አያሌ ዜጎቻችን የማትተካ ሕይወታቸውን የማያቆጠቁጥ አካላቸውን አጥተዋል! ቢያንስ እያሰብናቸው ክብር እንሰጣቸው ዘንድ ይገባል ብዬ ስለማምን ነው የማጋራችሁ። አያቴ ነፍስሄር! አንድ ቁምነገር ነግሮኝ ነበር።ምን ያልነገረኝ ነገሮች አሉ? "ሥማኝ ልጄ ካለ አባት ነበር ብቻዋን እናቴ አሳደገችኝ!" ..."እኔ እንደ ተፀነስኩ አባቴ ከወንድሙ ጋር አብረው ወደ ጦር ሜዳ ሄዱ!"አቋረጥኩት የልጅነት ነገር! ..."አባቴ ተወልጄ ዐይኔን አላየም እኔም አባቴን አላውቀውም። አጎቴ እንኳን ሁለት ልጆች ነበሩት እናቴ እኔን ነፍሰጡር እንደሆነች ሁለቱም አባቴና አጎቴ ለጦርነት እንደዘመቱ እዛው ሞተው ቀሩ። እናቴ ሌላ አላገባም ብላ እኔን ብቻዋን በወጣትነትዋ ካለ ባል መከራዋን አይታ አሳደገችኝ!" "ባባ ለምን ሄዱ? እቤት ቁጭ ቢሉ እኮ አይሞቱም!" "አገር ሲወረር እቤት ቁጭ አይባልም እኔ አባትና አጎቴን ባጣም አገሬ ኢትዮጵያን አላጣሁም! እነሱ ሞተው ዐድዋ ላይ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል። እኔ በዛ እኮራለሁ የማላውቀው አባቴ እየናፈቀኝ በልጅነቴ አነባ ነበር! ልጆች ከአባታቸው ጋር ሲጫወቱ ሳይ ሆድ ይብሰኝ ነበር ሳድግ ግን ለምን አባቴ እንደሞተ ሳውቅ በመስዋዕትነቱ ኮራሁ! ተኮፍሼ ቁጭ አላልኩም እኔም የድርሻዬን ተወጥቻለሁ እሱን ደግሞ አባትህ ስታድግ ይነግርሃል!" "ዐድዋ ቀብሩን አይተኸዋል?" "አይ ልጅነት ጅልነት እኮ ነው!ሥማ ጀግና ቀብር የለውም ጀርባውን ሳይሆን ደረትና ግንባሩን ለአገሩ ይሰጣል አንተም ልትኮራ ይገባሃል የባንዳ የልጅ ልጅ አይደለህም!" "ባንዳ ምንድንነው ባባ?" "ባንዳ ማለት አገሩን ለባዕድ የሸጠ ለጥቅም የተገዛ ማለት ነው!" "ባንዳ አሁንም አገር ቤት አሉ ባባ?" "ባንዳ ድሮም ነበር አሁንም አለ ወደፊትም ይኖራል! አንተ ግን ዐድዋ ላይ በወደቀው አባቴ ደምና አጥንት ይዠሃለው! ስታድግ አገርህንና ወገንህን ከድተህ ከባንዶች ጋር አትወግን! ማንነትህን አትሽጥ! ከዚህ ውልፍት ካልክ ግን የቅድመ አያቶችህ አፅም እሾህ ሆኖ ይውጋህ!" እኔ እና የዐድዋ ድል በደም ማኅተም የታተመ የቃልኪዳን ቋጠሮ አለን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን የምንኮራበት ታላቅ ገድል ከባንዳዎች በስተቀር!!! (5) አባ መብራቴ ተማቹ ታሪክ ያስታወሳቸው ሰማእት። ኤድዋርዶ ስለ አባ መብራቴ ተማቹ ሃሮልድ ማርከስን ጠቅሶ የአባ መብራቴን ታሪክ ያወጋናል። “In the article he has written to a British Sun concerning the Battle of Adwa dated 1985, Harold Marcus remembered one forgotten historical figure named “Aba Meberatey Tamachu” who walked alone from his village in Debre Berhan all the way to Adwa empty handed with only a rock he picked up from a near by market. Soon after his arrival at the battle ground, Aba Mebratey was suddenly kidnapped by the Italians and hanged with a few other patriots who have fallen in the same fate of his. A war is agonizingly unkind and often destroys compassion then restore cruelty, Harold Marcus wrote, but history is so generous, because it leaves no one behind, not even Aba Mebratey Temachu, Ye Debre Berhan sew. So now, let us celebrate the well lived life of a fallen patriots, because of them we are free.”13 (6) ሀዘንተኛው ምኒልክ በ1896 ዓ.ም ማገባደጃ በአፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት በመገኘት አስገራሚ የኀዘን ትዕይንት ከተመለከቱት እስረኞች መካከል ኒኮላ ዲ'አማቶ አንዱ ነበር፡፡በወቅቱ የተመለከተውን የገለፀው በከፍተኛ ኀዘን ሆኖ ነበር፡፡ በጦርነቱ ልጆቻቸውን ወላጆቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን ያጡ ኀዘንተኞች በከፍታ ስፍራ ላይ በመስመር ቆመዋል፡፡ አፄ ምኒልክ በኀዘንተኞቹ መካከል ተቀምጠዋል፡፡ ንጉሡ ፊታቸው በኀዘን ስሜት ተሞላ ሲሆን በዝምታ ነበር የተቀመጡት፡፡ በርካታ ለቀስተኞች ጥቁር ኮፊያ እና ነጭ ጋቢ ለብሰው በዝግታ በንጉሱ ፊት ያልፉ ነበር፡፡ ንጉሡ ወንበር ፊት ሲደርሱ በማጎንበስ ለንጉሱ ሃዘናቸውን በመግለፅ የቤተ መንግስቱን ግቢ ለቀው ይወጡ ነበር፡፤ ለቅሶው ስነ ሥርዓት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ቀጥሎ ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓቱ አፄ ምኒልክ ለቅሶ ደራሾችን በክብር ሲያሰናብቱ ነበር፡፡(ሜስ ደሞዝ ራይሞንድ ጆናስን ዋቢ አድረጋ እንደተረከችው)። በአድዋ ጦርነት አያሌ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሠውተዋል። ይህንኑ ጥቂት የሙሾ ግጥሞች ይገልፃሉ፣ * በጠቅላላው ስለሞቱት፣ የዳኘው አሽከሮች እነሞት አይፈሬ እርግፍ እርግፍ አሉ እንደሾላ ፍሬ። * የሟች እናት እንዲህ ብላ ሞሾ አውርዳለች፣ የወታደር እናት ታጠቂ በገመድ ልጅሽ አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ ። በል አንተ አሞራ እንደምን ነው ሞቱ ባለሟሉ አንተ ነህ የበላህ ከፊቱ። ለዚያ ለወታደር መች ያዝንለት እጣ አሞራ እንኳን ወርዶ ፊቱን ነጭቶ ወጣ።። ሥጋ ይዞ አለፈ አሞራ በደጄ የታላቁ ይሁን የታናሹ ልጄ። ገረገራ ግቢ ምን ያንኮሻኩሻል ያዉ ወቶአደሩ ነው ከጉንዳን ይሸሻል። * እኅት ደግሞ በበኩሏ ወንድሟን ያጣች እንዲህ ብላ አለቀሰች፣ ካሞራም አሞራ ነጭ አሞራ አልወድም በልቶብኛልና ፈረስና ወንድም። * አንድ የተጉለት ሰው በዓድዋ ዘመቻ አንድ ልጁን ያጣ እንዲህ አለ፣ ይለቀስለታል ሁሉም በየቤቱ እንኳን ደኅና ገባህ ዳኘው ባለቤቱ።…" (ሜስ ደሞዝ ዳግማዊ ምኒልክ የአዲሱ ሥልጣኔ መስራች (ሥርገው ሐብለ ሥላሴ) ዋቢ አድርጋ) 5.የጦርነቱ፣ የድሉ ማግስት አንድምታው/ውጤቱ 5.1. “ምኒልክነትን የጠየቀው” የአድዋ ድል! (adwa12) “ … ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል ዛሬ ብርቅ በሆኑብን ሁለት እሴቶች ረድኤት የተገኘ ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ ጦርነት ሲገቡ ተስፋቸውን የጣሉት በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ14 መቆራቆስ ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡“መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል። “… አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡ ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡” “ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ “ርዕሰ-ብሔር ምኒልክ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደፊት ሲገሰግሱ የጣልያን ሰራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ወደ ምሽጉ ገባ፡፡ ምኒልክ በቀጣዩ ስትራቴጂ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ላይ ወደ ጠላት ምሽግ ሄደን እንዋጋ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ባብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ምኒልክም በብዙሃኑ ተሰብሳቢ የቀረበውን ሐሳብ ለማስፈፀም ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መንገሻ ዮሐንስ ዘግይቶ ስብሰባውን ከተቀላቀለ በኋላ “ምሽግ ድረስ ሄዶ መዋጋት በወገን ጦር ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብሎ መከራከር ጀመረ፡፡ ምኒልክም “እኔ አንዴ ወስኛለሁ፤ ውሳኔዬ ካልጣመህ በሊማሊሞ በኩል ማቋረጥ ትችላለህ” ብለው ሳያሸማቅቁት ሐሳቡ እንዲጤን አደረጉለት፡፡ ሐሳቡ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ፡፡ በድምፅ ብልጫ ያልሁት “ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ” የሚለውን የፅሐፌ ትዕዛዙን አማርኛ ተርጉሜ ነው”(adwa12)። “እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡” በዕውቀቱ ስዩም፤ምንጭ፡ ፍትህ፤ ቅጽ 5፣ ቁጥር 177፤ የካቲት 23፤2004ዓም እና ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ http://www.goolgule.com/adwa/. 5.2 ባንዳ፣ አስካሪ፣ ባሽ ባዙቅ፣ ጥሩምቡሌ፣ መርሰነሪ እንደ ማንኛውም ጦርነትና ድል ሁሉ የአድዋ ጦርነት እና ድል ዘርፈ ብዙ ነው። ከጦርነቱም ከድሉም በሁዋላ በተሳታፊው እና በቀጣዩ ትውልድ ላይ አሻራው ይኖራል። ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት ስለ ባንዳዎች በገንዘብ ተቀጥረው ወገናቸውን ለጠላት አሳልፈው ሰለሚሸጡ እናወጋለን። ባንዳ አስካሪ ባሽ ባዙቅ መርሰነሪስ ባድዋም ጦርነት ከጣሊያን አድረው ወገኖቻቸውን አስጨርሰዋል። የአድዋ ጦርነት በድል ሲጠናቀቅ ተይዘው የነበሩ መርሰነሪስ ይቀጡልኝ ብለው የትግራዩ ገዢ ራስ መንገሻ ከሰሱ። ፍርዱ ምን ይሁን የሚለው ክርክር ወደ ሁለት ብይን አደላ። የጣሊያን መንግስት እንዳደረገው ይገደሉ ወይም ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን እጅ እግራቸው ይቆረጥ። አንድ እግር አንድ እጃቸው ይቆረጥ ተብሎ ተወሰነ። አራት መቶ የሚሆኑት እጅ እግራቸው ተቆረጠ። የሞቱም ሞቱ የተረፉት ወደ ኤርትራ ሄዱ። ይህ በባንዳዎቹ ዘመዶች እና ትውልዶች ቅሬታ አስነስቷል። ቅሬታውን የሚያነሱ ወገኖች ባንዳ አስካሪ ባሽ ባዙቅ መርሰነሪስ ያስጨረሱት ኢትዮጵያዊ ጭራሽ ሲታያቸውም አይስተዋልም። ነዋሪነቱን ስዊዲን ያደረገው አማኑኤል ሳህለ ስለ አስካሪዎቹ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል። ቅጣቱ ክፉ ስለነበር ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በድጋሚ ሲወርሩ እና አምስት አመት ሲዋጉ ያስካሪዎች ቁጥር በአድዋ ከነበረው በጣም ያነሰ ነበር። ጣሊያኖች ተቀጥሮ ወገኑን የሚወጋ ባንዳ በማጣታቸው ከሊቢያ የትሪፖሊ አስካሪዎችን (ጥሩምቡሌዎችን) ማምጣታቸውን ይጠቅሳል። ገንዘቡ አጓጊ ሳይሆን ቀርቶ ሳይሆን የተያዙ እንደሆን የቅጣቱ ብርቱነት አስጨናቂ ስለነበር ነው ቅጥረኛ የጠፋው። አማኑኤል የመርሰነሪስ ባንዳዎች ቁጥር ካፍሪካ ውስጥ ትንሽ ቁጥር የነበረው በ1928-33 ኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ነው ይላል።15 5.3 የአድዋ ድል አለም አቀፋዊ ትሩፋት የአድዋ ድል 119ነኛ አመት መታሰቢያ በአል ቀን እየቀረበ ነው። እንደምናውቀው የአድዋ ወግ ቢጨለፍም አያልቅም። ሰሞኑን ስከታትብ ለነበረው እንደ መቋጫ እንዲሆንልኝ ትኩረቴ የአድዋ ድል አለም አቀፋዊ ትሩፋት ምንድን ነው? እውነት የአለምን የታሪክን አቅጣጫ ቀይሯል ወይ? ለሚለው ምላሽ መሻት ነው። መልሱ አዎንታዊ ነው። የዛሬው ወግ የፖል ሄንዝን መጣጥፍ A Battle (Adwa) for Ethiopiaʾs future and of worldwide significanceን መሰረት አድርጓል። የፖል ሄንዝን ጸሁፍ ተአማኒነት የሚጨምረው በሙያው ከሰላይነቱ በፊት ወታደር የነበረ ሲሆን፣ ስለላንም ከዲፕሎማቲክ አገልግሎት ጋር አጣምሮ አሜሪካንን ያገለገለ ነው። ነጩ ወያኔ በመባል የሚታወቀው ፖል ሄንዝ በንጉሱ የስልጣን ማገባደጃ ዘመን ባሜሪካ ኤምባሲ በጸሃፊ ሽፋን የሲአይ ኤ ቺፍ የነበረ በካርተር ዘመንም የNational Security Agency ምክትል ዳይሬክተር ሆኖ እሱ እንዳለው ደርግን ገዝግዞ ለመጣል ቪኦኤን ያቋቋመ ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ከሚጽፉ ምእራባዊያን መካከል የመለስ ዜናዊ ፌቨራይተም ነው (በግልጽ የሚታወቁት ሌሎቹ እንግሊዛዊው ክርስቶፈር ክላፋም፣ ግሪካዊው ጆን ማርካኪስ እንዲሁም ይሁዲው ሃጋይ አርሊሽ ተጠቃሾች ናቸው)። የአስራ ዘጠነኛው ምእተ አመት እየተገባደደ ሀያኛው እየገባ አውሮፓውያን ራሽያን ጨምሮ ነጭ ቢጫ ጥቁሩን አስገብረዋል። ነጻነት ነፍገዋል። የፈለጉትን ገድለዋል፤ ባሪያ ፈንግለዋል፤ አካባቢን፣ ሀብትን፣ ጉልበትን መዝብረዋል። ምክንያቱ በግልጽ ባይታወቅም ኢትዮጵያን በጦር ከማስገበር ይልቅ እንቃረጣት ብለው Tripartite agreement ተፈራርመው ምኒልክን እወቁልን ብለው ጦማር ሰደዋል። ምኒልክም ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ፣ ነገር ግን እኔ በሌለሁበት የተወሰነውን አላውቅም በማለታቸው ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረች፤ ድልም ተመታች። የድሉ ዜና እንደናኘ ሲጀመር የፈጠረው ድንጋጤ ነው። አውሮፓ ይህ ድንጋጤ ሳያልፍላት በስምንተኛው አመት ጃፓን ሌላዋን ልእለ ሀያል ራሽያን አሸንፋ አውሮፓን ኩም አደረገቻት። የኢትዮጵያ ድል የአውሮፓን በአለም ፖለቲካ የነበራትን ልእለ ሀያልነት የመጀመሪያው ሸራፊ ነው። ፖል ሄንዝ እንደሚለው ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው የኢትዮጵያ ድል የአውሮፓ ተሰሚነት የቁልቁለት ጉዞ መነሻ ነበር ብሏል። ድሉ አውሮፓ በተለይ እንግሊዝ ኢትዮጵያን በእኩል አይን አይታ የምስራቁን የደቡቡን የምእራቡን ድንበራችንን እንካለል ብላ በፊርማ አጽድቃለች። ድሉ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት መዳፍ ስር ሲማቅቁ የነበሩትን አፍሪካውያን እና ካረቢያን ጥቁሮች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ብርታት እና ምሳሌ ሆኗቸዋል። ድሉ ለጥቁር አሜሪካውያን ምሁራን ከፍተኛ የመንፈስ መነቃቃት እንዲያገኙ አድርጓል። ድሉ ቁጭት ፈጥሮ ከሰላሳ አመት በሁዋላ ፋሺዝም በጣሊያን ውስጥ ስር እንዲሰድ እና መሪ የፖለቲካ አይዲዎሎጂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ድሉ ኢትዮጵያን የተረጋጋ መንግስታዊ አስተዳደር ማስፈኑና በአጭር ጊዜ ውስጥ ታይቶ ወደ ማይታወቅ ዘመናዊነት እንድታድግ ረድቷታል። ፖል ሄንዝ እንደመሰከረው ጣሊያንም ሆነች ሌላ አውሮፓዊ ሀገር ኢትዮጵያ በምኒልክ አስተዳደር ስር ከአድዋ ድል በሁዋላ የአሳየችውን እድገት ማምጣት በፍጹም አይቻላቸውም ነበር ብሏል። 5.4. የአድዋን ድል ለምን እናከብራለን? ካሳሁን አለማየሁ በድረ ገፁ ሲገልፅ እኔ ለአድዋ ድል ልዩ ክብር የምሰጥበት ምክንያት፡ አድዋ 1) ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያገናኘ (የታሪክ መበጠስ እንዳይፈጠር ያደረገ) ነው፡- 2) የጥንቶቹን አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር የተመሰከረበት የጦርነት ድል ነው 3) ባህላችን ተጠብቆ እንዲኖር አስችሎናል፡- ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በባህል ቅኝ ግዛት ብንወረርም 4) የኢትዮጵያን አንድነት እውን ለማድረግ ያስቻለ ነው 5) ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ መድረክ እንድትታወቅና እንድትከበር ምክንያት የሆነ ነው 6) ነጻነታችንን አስከብረን መኖር እንደምንችል አስመስክረንበታል፣ 7) ለሌሎች ሀገራት ሕዝቦች አርአያ ሆኗቸዋል፡- ለነፃነታቸው በቁርጠኝነት እንዲታገሉ ምሳሌ በመሆን ለዓለም16 የነፃነት ትግልና ክብር ምሳሌ ሆኗል፡፡ 8) የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለማቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በአፍሮ አሜሪካዊያንና በአፍሪካዊያን እንዲቀነቀንና እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል 9) ጥቁር ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚችል (የሰው ዘር ሁሉ እኩል እንደሆነ) አውሮፓውያን ትምህርት ያገኙበት ድል ነው፡- በመሆኑም ቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል 10) ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረትና ጥንካሬ አድዋ ምክንያት ሆኗል 11) ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ በዕውቅና እንዲረጋገጥና ድንበሯን በአግባቡ ለመከለልም ጭምር አስችሏታል፡፡. 5.5 የአድዋ ድልን መዘከር ለምን ተጠላ? በአንዳንድ ወገኖች የአድዋ ድል በተለይ ደግሞ መሪው ምኒልክ ላይ ያላሰለሰ የጥላቻ ዘመቻ ይስተዋላል። በነገራችን ላይ ይሄ የጥላቻ ዘመቻ በጥቁሩም በነጩም ነው። የነጩ እንኳን ቁጭት ነው። የኛው የጥቁሮቹ ምን ይባላል? ሁኔ አቢሲኒያ ጥሩ አድረጎ አቅረቦታል ተከታተሉት። በጣም የምወዳት አባባል አለች “የቡሄ እለት ያበደ ሁሌ ሆ እንዳለ ይኖራል” የአድዋ ድል እለትም ያበደ ሁሌ እንደቃዠ ይኖራል፡፡ ስለአድዋ ድል ብዙ፣ በጣም ብዙ ተብሏል፡፡ ገናም ይባላል፡፡ አድዋ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ነጭን ድል ያደረገበት ጦርነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ በአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀች የጥቁሮች ምድር እንድትባል ምክንያት የሆነም ጭምር፡፡ ፍፁም የሆነ የሀገር ፍቅርና ጠንካራ አንድነት ከሰለጠነ ወታደራዊ ሀይል እንደሚሻል የታየበት፣ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች ትግል መነሳሳት ምክንያት የሆነ የውጊያ አውድማ ነው አድዋ፡፡ ይኼን ታሪካዊ ድል ግን ምሉዕ እንዳይሆን የሚያደርግ እንከን አልጠፋም፡፡ ከድሉ በኋላ አፄ ሚኒልክ ከጣሊያን መንግስት ጋር የተፈራረሙት ውል ከመረብ ወንዝ ባሻገር ያለውን ምድር (የአሁኗን ኤርትራ) ለጣሊያን አሳልፎ መስጠቱ ነው እንከኑ፡፡ በብዙ የታሪክ ሰዎች እንደሚታመነው አፄ ምኒልክ ስምምነቱን ያደረጉት በብዙ መስዋእትነት ያገኙት ድል እንዳይቀለበስ በመስጋት ነው፡፡ በወቅቱ በአብዛኛው የአገር ጥሪውን ተቀብሎ እርሻውን ጥሎ በመጣ ያልሰለጠነ የገበሬ ወታደር የተዋጉት ምኒልክ ከየካቲት ሃያ ሶስት በኋላ ጦርነቱን ለማስቀጠልና ጣሊያንን ፈፅሞ ጠራርጐ ለማስወጣት መቻላቸው ላይ ጥርጣሬ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ጦርነት የሚኖር ከሆነ ጊዜ ማግኘት የተሻለ መሆኑን ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ ገበሬውም ተመልሶ መሬቱን ማረስ ነበረበት፡፡ ይኼ እንግዲህ የብዙዎቹ የታሪክ ምሁራንና ኢትዮጵያውያን እምነት ነው፡፡ ልብ በሉ የብዙዎች እንጅ የሁሉም አላልኩም፡፡ ምክንያቱም ስምምነቱን አፄ ምኒልክ ሆን ብለው ኤርትራን አሳልፈው የሰጡበትና ህዝብን ከህዝብ እንደሚያበላልጡ ያሳዩበት ስምምነት አድርገው የሚረዱትና ሌላውንም በዚህ መረዳታቸው ለማጥመቅ የሚሞክሩ አካላት አሉ፡፡ 5.6 ዝክረ-አድዋ 1) ያመለጠ አጋጣሚ: የአድዋ ድል መቶኛ አመት ዝክረ በአል በፌስ ቡክ መድረክ በ ሚራ ኔት እና ሜስ ደሞዝ አርቆ አሳቢነት ከወር በፊት የተጀመረውን የ119 አመት ዓድዋን ድል በዓል በ‘ፌስቡክ’ እናክብር!!! አምድ ሳስብ ከዛሬ አስራ ዘጠኝ አመት በፊት ወደ ተፈጸመ ክስተት ያመለጠ አጋጣሚ: የአድዋ ድል መቶኛ አመት ዝክረ በአል በምናቤ ጭልጥ ብዬ ተጓዝኩ። በስርአቱ ተከብሮ ቢሆን ኖሮ አጋጣሚው ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአለምም፣ ለቱሪዝምም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርግ የነበረ የክፍለ ዘመን በአል ነበር። በነበረ ቀረ። የአድዋ እለት ወራሪው ጦር ቀን ጎደለበት አሸናፊው ትምክህተኛው ተዋረደ ተሸነፈ። ድህረ አድዋ ኢትዮጵያውያን የአድዋ ድህረ ጦርነቱ በክፈል ዘመን አንዴ የምንደርስበት መቶኛ አመት በተለያየ መንገድ ተዘክሯል። መሆን የማይገባውም ነገር ሆኗል። የአድዋ መቶኛ ዝክረ አመት በእኔ እይታ ለዚህ ትውልድ ያመለጠ አጋጣሚ ነው። አህአዴግ ያዋቀረው በነ እንደርያስ እሸቴ የተመራው ብሄራዊ ኮሚቴ የአድዋ መቶኛ ዝክረ አመት አድዋ ላይ ነው መከበር የሚገባው ሲል በአ.አ.ዩ በእነ ፕሮፌሰር መርእድ ወልዳረጋይ ወገን ደግሞ አድዋ ለአድዋ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ይዘት እና ትኩረት ስላለው ባለሙያም ትራንስፖርትም ምግብም መገናኛውም ሆቴሉም አዲስ አበባ ስለሚመች አዲስ አበባ በዋነኛነት መከበር ይገባዋል እሰጥ አገባ የነእንደርያስ እሸቴ ወገን እናንተ ማናችሁ እንዲያውም እርሱት በማለት አድዋ እንደ አንድ የመንደር ባዛር ሲከበር አዲስ አበባም ሲምፖዚየም ተካሂዷል።17 ሆነም ቀረ አድዋ አድዋነቱ ተምሳሌትነቱ ግን አሁንም በኢትዮጵያውያን ልብ እንዳለ ነው። ዛሬም እያደመቅነው እየዘከርነው እየተማርንበት ነው። በዚህ አስቆጪ ትዝታ መለስ እንድንል የ1996 የመስቀል አደባባይ ሰልፍና የአድዋ ፓርክን ለ‹‹መለስ አረንጓዴ ማዕከል›› መስጠት ንፍገት ወይስ ንቀት? የተሰኘ ጽሁፍ ብጋብዛችሁስ። Demonstration at Mesqel square and speech of Tamagne Beyene https://www.youtube.com/watch?v=LZPdsHHAc1o የአድዋ ፓርክን ለ‹‹መለስ አረንጓዴ ማዕከል›› መስጠት ንፍገት ወይስ ንቀት? http://www.ethiopianreporter.com/index.php/other-sections/law-and-politics/have-your-say/item/3053-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%B5%E1%8B%8B- %E1%8D%93%E1%88%AD%E1%8A%AD%E1%8A%95-%E1%88%88%E2%80%B9%E2%80%B9%E1%88%98%E1%88%88%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%8 8%A8%E1%8A%95%E1%8C%93%E1%8B%B4-%E1%88%9B%E1%8B%95%E1%8A%A8%E1%88%8D%E2%80%BA%E2%80%BA-%E1%88%98%E1%88%B5% E1%8C%A0%E1%89%B5-%E1%8A%95%E1%8D%8D%E1%8C%88%E1%89%B5-%E1%8B%88%E1%8B%AD%E1%88%B5-%E1%8A%95%E1%89%80%E1%89 %B5 5.7 አድዋ በኪነ ጥበብ አይን 5.7.1. አድዋ- አፈር - መሬት - ሀገር - እትብት - ህይወት - ሞት እዚህ ባለሁበት ቀዬ የፈረንጆቹ የካቲትን የጥቁሮች ታሪክ ወር በማለት በልዩ ልዩ ስነ ጥበባዊ ተግባራት ይዘከራል። በአብዛኛው ታዲያ የባርነት ታሪክ ነው። ሩህያው የምትንቀሳቀስ ሰው እኔ ምን ሆኜ ነው? ምን ተደርጎልኝ ነው ? ይህንን የባርነት ታሪክ ያመለጥኩት ብሎ መጠየቁ ያለ ነው። በተጓዳኙ የአድዋ ድልም በዚህ ወር መገባደጃ ላይ ይዘከራል። ልክ እንደ ባርነት ታሪክ ሁሉ ያባቶቻችን የናቶቻችን የቅድመ አያቶቻችን የአድዋ ድል ታሪክም መንፈስን ይጫናል፤ ደቁሶ ይይዛል በተለይ ደግሞ የእሳት ልጅ አመድ መሆናችን ስሌት ውስጥ ሲገባ። ባንዱ የየካቲት የጥቁሮች ታሪክ ወር የአድዋና አገር፣ የአገርና አፈርን ተጣምሮ ሳሰናስል አቦል የተሰኘ ሀዲስ ንጋት የኪነጥበብ መድረክ ያሳተመው መጽሀፍ እጄ ገባ፤ የከበደን ታሪክና ምሳሌን የበዕውቀቱ ስዩምን አፈር እንቆቅልህ የዮፍታሄ ንጉሴን አጥንቱን ልልቀመው በዋቢነት አከልኩና የአድዋና አገር፣ የአገርና አፈርን ተጣምሮ ያየሁበትን ወግ እነሆ። ሲቻል በውድ ሳይቻል በግድ ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትውጥ የተዘጋጀችበት ነበር ጊዜው። አንቶኔሊ የምኒልክን ጉባኤ ረግጦ በይለያል ዘንድሮ አቅራርቶ በእትጌ ጣይቱም ባይገርምህ ላፈሩ ላገሩ ሆዱን ለጠጠር ግንባሩን ለጥይት የማይሰጥ ሰው እዚህ ያለ እንዳይመስልህ በሚል ምላሽ የተለያዩበት ነበር ወቅቱ። የዛሬ መቶ አስራ ዘጠኝ አመት። ሲጀመር የአፈር ተምሳሌት በኢትዮጵያውያን ህይወት ውስጥ ሁነኛ ስፍራ አለው። ጣልያኖችም ያንን ያውቃሉ እንደ ከበደ ሚካኤሉ “ቹሊ” አባባል ከሆነ። አፈራችሁ እትብታችሁ ወጋችሁ ሃይል ስለሌላችሁ ይነጠቃል ነው የሚለው። የምትኮሩበት እንግዲህ እናንተ እኔ እዚህ ተወለድሁ አባቴ እዚያ ሞተ፣ ካያት ከቅድመ አያት የመጣው ርስቴ የሠራሁት ጎጆ ያቆምሁት ቤቴ ለምን ተነክቶብኝ በማለት ብቻ ነው ነገር ግን ነገሩን ስታመዛዝነው ሃይለኛ ይሔዳል ያስገብራል የትም መሬት የሁሉ ናት ባለቤት የላትም አፈር መሬት ሃገር እናት ነች ይለናል የሃዲስ ንጋት የኪነጥበብ መድረኩ ባዩ በየነ (2000፡135-6) በ«ፍቅር ወይስ ቂጣ» ግጥሙ። ያንቺ ፍቅር አያጠግበኝም ኩርማን እየበላሁ የጠኔ ህይወት እየገፋሁ ይል ይማረርና መለስ ብሎ ደግሞ እናትነቷ ቢጠናበት ዳሩ አንቺ አይደለሽ አመዳሙ እኔ ነኝ፤ ሥጋሽ አልቆ ፈርስሽ ላይ የጸነሰኝ፤ ያን ሁለ ወፈ-ሰማይ ግብር ያበላ እጅሽ ሲመገመግ ቢውል የማይደርቀው ጡትሽ ምነዋ እኔ ስወለድ ነጠፈ? ...18 እያለ ይጠይቃል ምስጢሩ ቢገለጽለት። ሲያሰኘውም «አበሳሽን እኖራለሁ» ይላታል ስደት ሆኖ የሃገር የአፈር ናፍቆቱ ውል ቢልበት፤ እንደዛሬው በልቶ ማደር ሳይናፈቅ፣ ሞት ሳይረክስ ፍቅር ሳያልቅ፤ የግሬን አፈር ጠርጌ ሳልሰደድ ሳልርቅሽ፣ አይደለም በስጋዬ በመንፈሴ ሳልለይሽ፤ የአፈር ሃገር ተምሳሌትነት በሃዲስ ንጋት የኪነጥበበ መድረኩ መድበል «አቦል» አይነተኛ ቦታ ይዟል። ታምራት ገበየሁ (2000፡202)«የማስቸግራችሁ» እያለ የሃገሬን አፈሯን ዘግናችሁ ትቢያዋን ቋጥራችሁ አምጡልኝ ይለናል። ሀገሬ ስትገቡ፤ ኢትዮጵያ ስትዘልቁ ... ብዬም አልላችሁ ግን አለ አንድ ነገር፣ የማስግራችሁ አፈሯን ዘግናችሁ ትቢያዋን ቋጥራችሁ አምጡልኝ ሃገሬን እናት ኢትዮጵያዬን። ዮሴፍ ያእቆብም ቢሆን ነፍስ አፈር ነወይ? እያለ ትግያውን ያሰየናል «ነፍስ» በተሰኘ ግጥሙ አፈር ነህ ይሉኛል ከቶ አፈር ነኝ ወይ? እንደ ጥላ ኮብላይ ጠፊ ከምድር ላይ... እኔ አይደለሁ አፈር ጥርኝ ጭብጥ ነገር... እሱኛው ነው፣ እሱኛው ነው በድን... ይህ ያፈር ያገር ነገራችን የዘመናችን ተዋነይን በ“ዕውቀቱ ስዩም”ንም አስደምሞት አስገርሞት ይሆን “አፈር እንቆቅልህ” ያለው።2 አፈር፦ በምድሬ ሥር፦ ማፍሪያ በጥፍሬ ሥር፦ ማፈሪያ በውኃ የማባርረው በደሜ የማስከብረው በልቤ ስይዘው፣ የሚያሸልመኝ በልብሴ ስይዘው የሚያስቀይመኝ የታሰበውም አልቀረ ጣሊያን በጄኔራሎቹ የሚታዘዘውን ጦሩን ክተት ብሎ አድዋ ደረሰ። ይኼኔ ነበር ዝነኛው የምኒልክ አዋጅ የተነገረው። የህዝቤን መጎሳቆል የከብቱን ማለቅ አይቼ ዝም ብለው እንድ ፍልፈል ምድር እየቆፈረ መሬታችንን ያዘ። ያልቻልህ በጸሎትህ የቻልህ በጉልበት እርዳኝ ወሳልተህ የቀረህ እንደሆነ ማርያም ምስክሬ ናት አልምርህም። ህዝቡም ጥሪውን ሰምቶ ክተት አለ ወደ ጦር አውድማ ወደ አድዋ። ኪነጥበብ ህዝቡን እንዲህ ታወድሰዋለች። ወደ ጦር ሜዳ በመደቡ ራስጌ ሰቅሎ ያኖረውን አወላልቆ ጠርጎ ናስማስር ብረቱን ወልውሎ እንደገና አስማምቶ ገጣጥሞ ጥይቱን አጉርሶ ቃታውን ለጉሞ በረዥም መቀነት ሸብ አርጎ ወገቡን በመቀነቱ ላይ ደርቦ ዝናሩን19 ሚስትና ልጆቹን ስሞ ተሰናብቶ ሄደ ገሰገሰ የባላገር ስንቁን በስልቻ አንግቶ አድዋ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ በአስገራሚ ሁኔታ ጦርነቱ እንደ ማንኛውም ጦርነት የሰው ህይወት ተገብሮበት ተጠናቀቀ አሸናፊም ተሸናፊም ተለየ። ሆኖም አድዋን ልዩ የሚያደገው ጦርነቱ አድዋ ላይ መካሄዱም አይደለም። ርግጥ ነው ጦርነቱ የኢትዮጵያንም የታሪክ አቅጣጫ ቀይሮአል። እሱን አልሄድበትም። ጦርነቱ -ድሉ ተስፋ ሰጪነቱ፤ ጦርነቱ ድሉ - ተምሳሌትነቱ ነው። ሲያንስ የተገፉ ህዝቦች ጥቁሮች በኃይለኛው ህዝቦች በነጮች ላይ ያገኙት ድል ስለሆነ ነው። ሲበዛ ደግሞ ደካሞች በትእቢተኞች ላይ ያሰገኙት ድል ምሳሌነቱ ነው ከበደ ሚካኤል በ “እሮሮ” እንደተቀኙት። እግዜር የሰውን ልጅ እንፍጠር ሲል ሠራ፣ ፋሺስቱ ብልህ ግን አድርጎ ምርመራ የሃያኛው ዘመን አዲሱ ፈላስፋ አለና ተነሳ የሰው ዘር እናጥፋ ... ሁሉም በየተራ ቀን ይጎድልበታል፣ አሸናፊ ደግሞ አንድ ቀን ይረታል። ... ትዕቢት ትመጣለች ውርደት አስከትላ የተመካ ሁሉ ይጠፋል በኋላ። የአድዋ እለት ወራሪው ጦር ቀን ጎደለበት አሸናፊው ትምክህተኛው ተዋረደ ተሸነፈ። አድዋ አድዋነቱ ተምሳሌትነቱ ግን አሁንም በኢትዮጵያውያን ልብ እንዳለ ነው። ዛሬም እያደመቅነው እየዘከርነው እየተማርንበት ነው። እንደ መቋጫ አንዱ ድህረ አድዋ መወድስ እስካሁንም የዘለቀ ኪናዊ ውበት የተላበሰ ግጥም የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ነው። አድዋን በኢትዮጵያ ህዝብ ትብብር ማሸነፋችንን አጉልቶበታል። አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣ ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣ ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ፣ ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ። ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣ ተሸዋ ጎበና ተትግሬ አሉላ ፣ ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣ አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣ አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ። 5.7.2 አድዋን በግጥም ስለ አድዋ ብዙ ብዙ ተገጥሟል፤ ተዘፍኗል። ካየን አዳም የዛሬ አመት (2006) ካካፈለን የእንዳለ ታየን ግጥም እንደምሳሌ እንይ። እንዳለ ታየ “እስኪ ቃል ምረጡ” ይለናል። “እስኪቃል ምረጡ” አደዋን ፦ ለመግለጽ ስነሳ ቃላቶች ያጥሩኛል አፉን እንዳልፈታ ህጻን ያደርገኛል እስኪ ሆሄ አዋጡ እስኪ ቃል ምረጡ የአድዋን ታላቅነት የሚገልጽ በቅጡ አቦ ሀረግ ምዘዙ ለጋራ ሸንተረር ለሜዳ ለወንዙ20 አደዋ ቅኔነው ብዙ ነው ትርጉሙ ባንድ ተቀላቅሎ ባንድ ተዋህዶ ያለ ወርቅ ከሰሙ አደዋ ሰማይ ነው እጅግ የመጠቀ በ ምኒሊክ ፀሀይ በጣይቱ ጨረቃ በአርበኞች ከዋክብት ውብ ሆኖ የደመቀ አደዋ ባህር ነው እጅግ የጠለቀ ዋኝተው ማይጨርሱት አድማሱ የራቀ አደዋ ምድር ነው ከአልማዝ ከ'ንቁ ከወርቅ የከበረ የመስዋእት አፅም በውስጡ ያኖረ አደዋ መቅደስ ነው የጥቁር ሰው ስጋ የተቆረሰበት የጀግኖች ቅዱስ- ደም የፈሰሰበት ጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ቁርባን የተፋተተበት አደዋ ወንዝ ነው አደዋ ጅረት የጥቁር ሰው ታሪክ የሚፈስበት ትውልዱ በኩራት የሚተምበት አደዋ መድረክ ነው የጀግኖች ጀግንነት የሚዘከርበት የሙታን ትነሳዔ የተሰበከበት አደዋ ቀስተ ዳመና ነው መሀላ ቃል ኪዳን ሰው ከራሱ ጋራ ሰው ከአምለኩ ጋራ ሰው ከሀገሩ ጋራ የተማማለበት ነፃነት ለማዳን ማንነት ለማዳን አደዋ ቀራኒዮ ጎለጎልታ አደዋ ለሰው ልጅ ሰውነት ስንት ሰው ተሰዋ? ለሀበሻ ሀበሻነት ስንት ሰው ተሰዋ? አደዋ አደዋ ነው ብዙ ያስፎከረ ብዙ ያስዘመረ አደዋ አደዋ ነው ዘላለም የሚኖር እስካሁን የኖረ ኤዲያ ፦ እፁብ ድንቅ አድርጌ ለመግለፅ ብመኝም አደዋን የሚገልፅ ቃላት አላገኝም ይህ ሁሉ ቢሆንም የአደዋን ታላቅነት መግለፅ ቢሳነኝም የአደዋ ፀሀይ ግን ዘላለም አትጠልቅም አቦ ሆሄ አዋጡ እስኪ ቃል ምረጡ የአደዋን አደዋነት የሚገልፅ በቅጡ አቦ ቃል ምረጡ!!! አቦ ሆሄ አዋጡ!!! የተወሰኑ መንቶዎች ሜስ ደሞዝ (ሥርገው ሐብለ ሥላሴን በዋቢነት) በአምዷ ካሰፈረችው21 ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ግዜ አበሻ በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ ተፈጠመ ጣልያን አበሻ እንዳይደርስ ውረድ እንውረድ ውረድ ካለቱ የሞተው ይሙት ታልቅስ እናቱ ዳግመኛ እንግፋ እስካለበቱ። ጣሊያንን ለመውጋት አራት ሁነን ሒደን አንዱ ተመለሰ ሦስታችን ስንቀር። ጣሊያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሊያጠጣው ገና ሊበጠብጥ ጃኘውን ቀናው። ባመጣው ወጨፎ በሠራው እርሳስ ወቃው አመረተው ያን የባሕር ገብስ ጃኘው ምኒልክ የኢትዮጲያ ንጉሥ። ቅዳሜ ተግዞ እሑድ ተበራየ መስኮብም ገረመው ጣሊያንም ጉድ አየ። ምኒልክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይኸን ግዜ አበሻ። ዳኘው የሰንበት ለት አበላ ታምር እኛ ለሰው መስሎን ከጅለን ነበር ነጩን አሳረደው ላሞራ ግብር። ምኒልክ ተጉዞ የምትጠይቁኝ ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ።" 6.ማጠቃለያ 6.1 ምን እንማራለን? የታሪክ ተመራማሪው ኤድዋርዶ እናንብብ እንትጋ እንወቅ ይለናል። “ስለ አድዋ ጦርነት 28 መጽሀፍት በ28 ታሪክ ጦማሪወች ስለተጻፈ ስለዚህ ታሪኩን የማወቅ ፍላጎት ያለው ያገኘውን መረጃ እያነበበ እና እውቀቱን እያሰፋ ይሄዳል እንጂ አንድ መጽሀፍ ብቻ አንብቦ በቃኝ ታሪክ አውቃለሁ እያለ መከራከር አይችልም። በተጨማሪ ደግሞ እስካሁን ድረስ ይህ አባቶቻችን በባዶ እግራቸው እና በራበው ሆዳቸው እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የአውሮፓ ወራሪ ድባቅ የመቱበት አኩሪ ታሪካቸው ፊልም ተስርቶ ለትውልድ አለመቀመጡ ያሳዝነኛል። ጋዜጠኛው አይዋሽም..... የጣሊያንን ጦርን በኤርትራ በኩል ተከትሎ የመጣው እና ወደጦሩ አውድማ በጠራው ሰማይ ላይ በመንጋ እየተንጋጉ ከሜዳው የወደቁትን የጥሊያን ወታደሮች የበሰበሰ በድን ሊመንችፉ የሚበሩትን አሞሮች አቅጣጫ ተከትሎ በመሄድ ታሪኩን የዘገበው የጥንቱ እንግሊዝ ጋዜጠኛ Thomas Hughes አንድም ሳይደብቅ ተርኮታል። ....የተቆራረጥውን እጅ ፤ እግር እና አንገት በየቦታው ተዝረክርኮ በአየሁ ቅፅበት ወደዚህ ግድም የመጣሁበትን ዕለት እየረገምኩ ከዛም በከባድ ፍርሀት ተውጬ ሸበጤን ጥዬ በሀይለኛ ጩኸት ቁጥቋጦውን አልፎ ወደሚገኘው ባዶ መንደር በሩጫ ተፈተለኩ....The frightened war reporter wrote”.22 6.2 የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል፦ሀውልቱ ያልታወቀው የጣሊያን ወታደር ሀውልት ምስጋና ለዶ/ር አበበ ሀ/ወይን ዶ/ር አበበ ሀ/ወይን በአድዋ ሲዘዋወር አንድ ሀውልት እይታው ይገባል። በካሜራው አስቀርቶት አካፍሎናል። ባጭሩ ሀውልቱ ላይ የተፃፈው ሲተረጎም እዚህ ለወደቅከው (የጣሊያን ወታደር) አንረሳህም ነው። ልብ በሉ ይሄ አድዋ ኢትዮጵያ ነው። እኛ ለጀግኖቻችን ለሰማእቶቻችን ምን አለን ያለ ምኒልክና አውአሎም ሀውልት በስተቀር? በእውነት ማዘን መቆጨት ይገባናል። በረከት የተሰኘ አንባቢ ሀውልቱን አይቶ ስሜቱን ሲገልጽ “ምን ማለት እንዳለብኝ እራሱ ላውቅ አልቻልኩም”። ማን ነበር “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ያለው ዮፍታሔ ንጉሴ ይሆን?23 አድዋ ሚሚ ኢትዮጵያዊት እንዳለችው በአለም ህዝቦች ታሪክ ለነጭ ትዕቢት ድንበር አልባ የዘረኝነት መርዝ የማይገዛ ጥቁር ህዝብ መኖሩን ያስመሰከረ የዓድዋ ድል ፤ የነጭን አንገት ያስደፋ በሀፍረት ያሸማቀቀ በፍርሀት ያርበደበደ ኢትዬጵያዊነት ኩራት አፍሪካነት ኩራት ጥቁርነት ክብር መሆኑን ያስመሰከረ የአፍሪካውያን ኩራት የዓድዋ ድል ፤ ለነፃነታቸው ለህልውናቸው ለእናት ሀገራቸው ለሰንደቅ ዓላማቸው ለሰብአዊነታቸው ክቡር ህይወታቸው ገብረው ለዛሬ ላበቁን ወገኖች ምን ይገባቸው ይሆን። 6.3 በኛ ትውልድ ስለ አድዋ ድል እና ስለ እኛ ምን ይሰማናል? የእሳት ልጅ አመድ ሆነን አንዲት ውድ ሕይወታቸውን ሰውተው ሰው ላደረጉን አያት ቅድማያቶቻችን ፣ ሕይወት ለግሰው ያቆሟትን አገር እንዳሻሽ ብለን ትተናታል። በሕይወት ዘመናችን ተከፍሎ የማያልቅ እዳ አለብን። ሁሉ ቢቀር በየመክሊታችን ንቁ ባለሙያዎች ለተተኪው ትውልድም ሊያልፍ የሚችል አንዳንድ ነገር ሰርተን እንለፍ! ቢሆንም ዘላለም እንዳለው ዛሬም ነፃ ሰዎች ነን፡፡ በባርነት ጭነት ቅስማችን ያልተሰበረ: በጭቆና ቀንበር ልባችን ያልተሸበረ፤ ጎንበስ ማለት የሚያንገሸግሸን: ቀና ብለን ኖረን ቀና እንዳልን ማለፍ የሚናፍቀን፤ የነጮችን ጥቃት ለመቋቋም ቆዳችን የሚሳሳብን፤ አልደፈር ባይ የጥቁር አፈር ትንታጎች ነን፡፡ በትውልዱ ሊጠየቅ የሚገባውን ጥያቄ ወንድወሰን ውቤ እንዲህ ሸጋ አድርጎ ገልፆታል። “ያጣሁት ጀግንነት እንዴት የጀግንነት እርሾ ከውስጤ ጠፋ? ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የአልገዛም ባይነት ሥሪት ነው። የኢትዮጵያዊያን እምቢተኝነት የነጭ ዘርን ወታደራዊና ሥነ-ልቡናዊ ልዕልናን ዓድዋ ላይ እስኪሰባብር ድረስ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በምድራቸው ላይ ለሠለጠኑት ባዕዳን ሎሌ ሆነውና በፍረሃት ቆፈን ተይዘው ኖሩ። ዓድዋ መጣና የጥቁር ሕዝብ እምቢታ በራሷ ኃይል እንደምታደርግ አረጋገጠላቸው። በልባቸው ውስጥም “ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን የፈጸሙትን ጀግነነንነት እንደግመዋለን!” የሚል የጀግንነት ወሳኝ ብርታት አደረ። እናም ቅኝ ገዥውን በሽምቅ ውጊያ ይተገትጉት ጀመር። ታዲያ ለአፍሪካ የተረፈ ጀግንነት ከበቀለባት ምድር በቅዬ እንዴት ጀግንነት አነሰኝ? ኢትዮጵያዊነቴን ማን ቀማኝ? የት ጣልኩት”? መስፍን ነጋሽም “ወደ አድዋ እንመለስ” ይለናል። ጦር በአዝማቹ፣ አገር በመሪው ይጠራ ሆኖ እንጂ አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል መሆኑ ለጠላትም ለወዳጅም የተረዳ ነው። እምዬ ምኒልክም በዚህ አይወቀሱም፣ አድዋን “የእኔ ብቻ” ብለው አያውቁምና። ቀድሞውንስ የጦርነቱን አዋጅ ሲያውጁ መቼ ቋንቋ ለይተው፣ ዘር ቆጥረው ተጣሩና። የወቅቱ አቅማቸው ብቻ ሳይሆን የአድዋም መንፈስ ይህን አይፈቅድላቸውም። እንኳንም አልፈቀደላቸው። ለአድዋ ዘመቻ ቤቱን ጥሎ ከየአገሩ ጥግ የተሰበሰበው የአገሬ ሰው ምንኛ ይደንቀው?! በጦርነቱ ብዙ የሚያስደንቅ ነገር ሆኗልና። ኀዘኑም ድሉም ያስደንቃል። የወራሪውን የግፍ ጥቃት በአካል የተቀበሉት የአድዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ምንኛ ጠንካሮች ናቸው! የእነርሱ የነጻነት መንፈስ ባይኖር የምኒልክ ጦር ጀግንነቱን የሚለኩስበት የተዳፈነ ረመጠ ባላገኘ ነበርና። ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አንሥቶ እስከ ስም አልባው የአድዋ አጥቢያ ጀግና፣ የድሉን ብርሃን ሳታዩ ላለፋችሁትም ሆነ በድሉ ደስታ ለተጠመቃችሁ፣ እኛን ልጆቻችሁን እና መላውን የሰው ልጅ በአድዋ የነጻነት መንፈስ አጥምቃችሁናልና ተመስገኑ፣ ክበሩልን። አራት ነጥብ። እነሆ የአድዋን ድል በዓላችን በማሰብ በተለየ ሁኔታ በድምቀት ስለ አድዋ እንዘምራለን፣ ስለጀግኖቻችን እንተርካለንና ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለአድዋ ጀግኖቻንን፤ ፍቅር እና አንድነት ለሁላችን!!! ዘላለማዊ ክብር የአድዋ ተራሮችን በባዶ እግራቸው ላቋረጡ፤ ለህዝባቸው ነፃነት አንድ ህይወታቸውን ላጡ ከፍታ ለነፃነት ፋኖ፡ ለምርጥ መሪነት ህያው ምሳሌ፡ ለጀግናው አጤ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ:: በ2008 አ.ም. ለመቶ ሀያኛው አመት የአድዋ ድል ዝክረ-በአል ያብቃን!!!

No comments:

Post a Comment