ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው እርስዎ በአካባቢ ጥበቃና በዱር እንስሳት አያያዝ በግልዎ የሚያደርጉት ጥረት አለ፡፡ ከሰሞኑ አንድ የኬንያ ሚዲያ የኢትዮጵያ አናብስት ቁጥር በአደገኛ ሁኔታ እየተመናመነ መምጣቱንና ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ታሪካዊ ቁርኝት ያለው የአንበሳ ዝርያ ደብዛው ሊጠፋ እንደሚችል ጠቁሞ ነበር፡፡ ምን ተሰማዎት?
አቶ ግርማ፡- ይህን ዜና እንኳን አልሰማሁም፡፡ ይሁንና የአካባቢ ጥበቃና የዱር እንስሳት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ አይካድም፡፡ ቀደም ሲል የአገሪቱ ደን 60 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ ሦስት በመቶ [መንግሥት 15 በመቶ ደርሷል ይላል] አሽቆልቁሏል፡፡ ይህ ደግሞ በአየር ንብረቱ ላይና በብዝኃ ሕይወቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በዚህም ምክንያት የዱር እንስሳቱ ሌላ ምቹ መጠለያን በመሻት ይሰደዳሉ፡፡ ከአንበሳ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ፣ አንበሳ በባህሪይው ጥቅጥቅ ያለ ደን ሳይሆን በረዣዥም ሳር የተሞላ ሜዳማ አካባቢን የሚመርጥ ነው፡፡ ስለዚህ ከደን መመንጠር ጋር አይያያዝም፡፡ ሆኖም የሰዎች መስፋፋትና ተፈጥሮአዊው የእርስ በርስ የመተዳደን ሁኔታ ሲቀንስ አንበሳ ተፅዕኖ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በበኩሌ ለአንበሳ የተለየ ፍቅር የለኝም፡፡
ሆኖም አንበሳ የጀግንነትና የኩራት ምልክት በመሆኑ ደስ ይለኛል፡፡ አንበሳ ኃይሉ ክንዱ ላይ ነው፡፡ እንደሌላ አውሬ ተናካሽ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋርም የሚያያይዘው ጉዳይ ቀደም ሲል ነገሥታቱ በተለይም የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥትን ከአንበሳ ጋር ማዛመዱ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ‹‹ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ዘ እምነገደ ይሁዳ ሞኣ አንበሳ›› የሚል የንግሥና መጠሪያ (ማዕረግ) ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ልክ ነው ኢትዮጵያና አንበሳ የሚያገናኛቸው ታሪካዊ መሠረት አለው፡፡ እኔ በበኩሌ አንበሳን እወዳለሁ፣ በአሁኑ ወቅትም ሆለታ አካባቢ አሥር ያህል አንበሶች አሉኝ፡፡ አንበሳ በዙ (በግቢ) ውስጥ ታግቶ መቀመጥ የለበትም፡፡ የእኔ አንበሶች በሰፊ ቅጥር መጠለያ ነው የሚገኙት፡፡ ሰፊ ክልል በመሆኑ አንበሶች ብቻ ሳይሆኑ እንደ አቦ ሸማኔ ያሉ ሌሎች የዱር እንስሳትም ይገኛሉ፡፡ ጥቁር ጎፈር ያለውና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው አንበሳም እዚሁ ቦታ ይገኛል፡፡ የተባለው ዘገባ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንንም ነገር በደንብ አጣርቶ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡ አንበሳ ከኢትዮጵያ ሊጠፋ ይችላል የተባለው ግን አይመስለኝም፡፡ አይጠፋም፡፡ እኛም የተለየ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ መጠለያው የመማሪያና የመመራመርያ ክፍሎች ሁሉ አሉት፡፡ ወደፊት የአንበሶቹ ቁጥር ሲበራከት ልዩ ቦታ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ቤተ መንግሥት ለፕሬዚዳንትነት ከማምራትዎ በፊት ቤተ መንግሥቱን በደንብ ያውቁት እንደነበርና በቤተ መንግሥትም በንጉሡ ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በክብር የደነሱ መሆንዎ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
አቶ ግርማ፡- ልክ ነው፡፡ ንጉሡ 25ኛ በዓላቸውን ባከበሩበት ዕለት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ማለቴ ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱም እኮ ኢዮቤልዩ ነው የሚባለው፡፡ እናም በዚያን ቀን በርከት ያሉ እንግዶች ተገኝተው ነበር፡፡ በኋላ ሙዚቃ ተጀመረ፡፡ አልጋ ወራሽም ተነሱ፡፡ የጦር ሚኒስትሩም ራስ አበበ ያረጋል እንዲሁ ተነሱና ሞቅ ሞቅ ሲል በዕድሜም፤ በማዕረግም ትንሹ እኔ ስለነበርኩ እንድደንስ ተጋበዝኩኝ፡፡ ‹‹ፍራክ›› ታውቃለህ? ‹‹ፍራክ›› ማለት ስፔኖች በእንዲህ ያለ ልዩ ግብዣ ላይ የሚለብሱት ነጣ ያለ ልብስ ነው፡፡ እኔ በሲቪል አቪዬሽን ተጠሪነቴ ወደ ስፔንና ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች እሄድ ስለነበር አዲስ አልገዛሁም፡፡ ቀደም ሲል ከዚያ ያመጣሁት ነበረኝና ባለቤቴን ይዤ ተነሳሁ፡፡ እሷ ትንሽ ፈርታ ነበር፡፡ እህቷም እዚያው ነበረች፡፡ በኋላ ግን እንደምንም አስነሳኋትና ዋልዝ ደነስን፡፡ ከዚያም ሮክ ኤንድ ሮል ጨመርንላቸው፡፡ ንጉሡ በጣም ነበር የተደሰቱት፡፡ ወደኔ ጠረጴዛ ብቻ ሦስት ጠርሙስ ሻምፓኝ አስላኩልኝ፡፡ እኔ በደነስኩት ሌሎች ሰዎች ሻምፓኙን እየቀዱ መጠጣት ጀመሩ፡፡
ሪፖርተር፡- በዚያ ዕድሜና በእነዚያ ሁሉ ሹማምንት መሀል በተለይም በንጉሡ ፊት ለመደነስ ሲጋበዙ አልፈሩም?
አቶ ግርማ፡- እሱማ ትንሽ ያስፈራል፡፡ ግን ይኼ እኮ የተከበረ ቦታ ነው፡፡ ደጃች ውቤ ሠፈር እንኳን ደንሰን የለ እንዴ ብዬ ነበር ባለቤቴንም ያደፋፈርኳት፡፡ ከዚያ በኋላም አንድ ሁለት ጊዜ ደንሻለሁ፡፡ አንዴ ስለታወቅኩ ይጠበቅብኝ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- እንግዲህ የሥልጣን ዘመንዎን ጨርሰው አሁን በዕረፍት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሕይወት ከቤተ መንግሥት በኋላ ምን ይመስላል?
አቶ ግርማ፡- በጣም ጥሩ ነው፡፡ አሁን የተሻለ ነፃነት ይሰማኛል፡፡ ቤተ መንግሥት ፕሮቶኮሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንግዳ መቀበል መሸኘቱ፣ ደብዳቤ መቀበሉ ሁሉ ቀርቷል፡፡ አሁን ደስ ብሎኝ እየኖርኩ ነው፡፡ ያኔ ተሹሜ ስገባ የነበረው ስሜትም አስደሳች ነበር፡፡ ትንሽ አሞኝ የነበረ ቢሆንም እንደምንም ፓርላማው ሲከፈት ተገኝቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ግን አንዳንድ ጉዳዮች የያዝዎት ይመስላሉ፡፡ ይህ ራሱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢሮ ነው የሚባለው፡፡
አቶ ግርማ፡- አዎ እሱማ ቢሮ ነው፡፡ ደብዳቤዎች ይመጣሉ፣ አንዳንድ ቀደም ሲል የጀመርኳቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ልዩነቱ የቤተ መንግሥት ቢሮ አለመሆኑ ነው እንጂ እንግዶችም ይመጣሉ፡፡ ደብዳቤዎች ይፈረማሉ፡፡ እኔ እንደ ድሮው ደብዳቤ ቶሎ ነው ፈርሜ የምመልሰው፡፡ አላቆይም፡፡ ለዚያ ነው መሰለኝ ይኼው ቶሎ ቶሎ ይመጣል፡፡
ሪፖርተር፡- እንግዲህ እርስዎ በሦስቱም ሥርዓቶች ውስጥ አልፈዋል፡፡ በሥርዓቶቹ ላይ ምን ዓይነት አስተያየት አለዎት? አገሪቱ በእነዚህ ሥርዓቶችስ ያለፈችበትን ሁኔታ እንዴት ያጤኑታል?
አቶ ግርማ፡- ያው በንጉሡ ዘመን የነበረው ብዙም ለነፃነት ቦታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ አገሪቱም በንጉሣዊ የዘውድ አገዛዝ ሥር ስለነበረች ለመቃወምና ለውጥ ለማምጣት የሚያመች ሁኔታ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ንጉሡ የሠሯቸው ብዙ ጠቃሚ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ከዚያ ባልታሰበ ሁኔታ የመጣው ለውጥ በራሱ ሒደት ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ በመልካም ነበር የተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም ተማሪውን ያነሳሳና ሰፊውን የኅብረተሰብ ክፍል ያነቃነቀ ለውጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ለውጡ አስፈላጊ ነበር፡፡ በወቅቱ የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ነበርኩኝ፡፡ በሌላ በኩል የኢሕአዴግን መንግሥት ሳየው አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን አዲስ መንገድ የቀየሰ ነው፡፡ ዘጠኝ መንግሥታትን ፈጥሮ በአንድነት አንዱ አንዱን ሳይጫነው እንዲስተዳደር ነው የተደረገው፡፡ በበኩሌ የሽግግር መንግሥቱ ብዙ ርቀት ሊሄድ እንደሚችል አውቅ ነበር፡፡ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ ጥሩ ተዋፅኦ ነበረው፡፡ ሁሉንም ቡድን ማለት በሚያስችል መንገድ ያካተተ ነበር፡፡ በተለይ መለስን የማደንቀው የፌዴራል አስተዳደሩን በጥሩ ሁኔታ ያዋቀረ መሐንዲስ በመሆኑ ነው፡፡ አገሪቱ ከነበረባት የመበታተን አደጋ እንድትተርፍ የቀየሰው ዘዴ ትክክል ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ዋና ጉዳይ የኤርትራ ጉዳይ ነው፡፡ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የመንግሥታቱን አቋም በደንብ ለይተው ያውቃሉ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ እርስዎ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
አቶ ግርማ፡- ከኤርትራ ጋር ያለኝ ጉዳይ የተለየ ነው፡፡ ለ21 ዓመታት በኤርትራ ኖሬያለሁ፡፡ ሕዝቡን አውቀዋለሁ፡፡ ሕዝቡም ያውቀኛል፡፡ ቀደም ሲል በንጉሡ ዘመን ኢትዮጵያ እንደ አባት ኤርትራ እንደ ልጅ ሆነው እንዲተዳደሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተነደፈው ዘዴ ጥሩ ነበር፡፡ በኋላ ‹‹ነፃነት ወይም ባርነት›› በሚሉ አንዳንድ ኃይሎች ይህ ሁኔታ ፈተና ውስጥ እንዲወድቅ ተገዷል፡፡ በተለይ ንጉሡን ይህ ጥሩ ዘዴ አለመሆኑን የሚመክሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ይኼ ፌዴሬሽን ደግሞ ምንድነው?›› እያሉ ንጉሡን የሚያዘናጉ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ነበር ሳይሆን ቀረ፡፡ ንጉሡ ይህን መሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ሽፍታ ተፋጥሯል፡፡ ደርግም የነበረውን ሰላም አስቀጥሎ ለመጓዝ ሞክሯል፡፡ መዋጋት በነበረበት ጊዜ ደግሞ ተዋግቷል፡፡ እንደዚያም ሆኖ መሬቱ በጦርነት በተያዘ ጊዜ ምግብ በአውሮፕላን እየጫነ ሲመግብ የነበረውን ሁኔታ ለማስጠበቅ አስቦ ነበር፡፡ አልተቻለም፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከመግባቱ ሦስት ወራት ቀድሜ ነበር ከዚያ የተመለስኩት፡፡ በአስመራ የሰሜን ክፍላተ ሀገር የትራንስፖርትና መገናኛ ተጠሪ ሆኜ ነበር የማገለግለው፡፡ በኋላ ሁኔታዎች እየተቀያየሩ መጡ፡፡ እዚያ ካሉ አለቆቼ ጋርም አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ አንዱ እንዲያውም ይህን ሰውዬ አስረዋለሁ ማለት ጀመረ፡፡ ሁኔታው አስቸጋሪ ሲሆን እዚህ ተመልሼ መጥቼ መገናኛ አካባቢ ቢሮ ተሰጥቶኝ መሥራት ጀመርኩኝ፡፡ ሁኔታው እንደዚህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ያን ጊዜ በግርማዊነታቸው የቀጥታ ትዕዛዝ በመደረጉና እሳቸው ‹‹ፌዴሬሽን የሚባል ነገር ምንድነው?›› በሚሉ ሰዎች ተፅዕኖ በመውደቃቸው ሽፍታ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ በኢሕአዴግ በኩል ግን የኤርትራ መገንጠል ከብሔራዊ ስሜት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ኤርትራ ከዚያ በፊትም ከኢትዮጵያ ጋር አንድ አልነበረችም፡፡ በበኩሌ መለስ ጥሩ ‹‹ናሽናሊስት›› አልነበረም ብዬ አላስብም፡፡
ሪፖርተር፡- የአሰብንስ ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ግርማ፡- አሰብ የአፋር ነው እኮ፡፡ አንድ የአፋር ባላባት ወደቡን ለከሰል ማራገፊያነት አከራየው፡፡ ጣሊያኖች ገቡ፡፡ ጣሊያኖች አሰብን ከኤርትራ ጋር ቀላቀሉት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሰብ በአፋር ክልል መንግሥት ሥር መተዳደር ነበረባት፡፡ የሆነ ሆኖ ግን …
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ወገኖች ደርግን በኤርትራ ጉዳይ ተወቃሽ ያደርጋሉ፡፡ እርስዎስ?
አቶ ግርማ፡- ደርግ ኤርትራ ውስጥ ምን አደረገ አሉ? በመጀመሪያ ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ሞክሯል፡፡ መዋጋት በነበረበት ወቅት ደግሞ ተዋግቷል፡፡ ይኼ ደግሞ ከብሔራዊ ስሜት የሚመነጭ ነው፡፡ እንዲያውም መሬቱ በጦርነት በተከበበ ጊዜ እኮ ምግብና ነዳጅ በአየር እያጓጓዘ ሕዝቡን መግቧል፡፡ ኢሳያስ እንኳን ይህን ማድረግ ባለመቻሉ በቀን በሺሕ የሚቆጠር ዜጋ እየተሰደደ ነው፡፡ ያን ጊዜ የአየር ኦፕሬሽን ኃላፊ ነበርኩ፡፡ የሰላም ኮሚሽነር ሆኜ ነበር ወደ ኤርትራ የተጓዝኩት፡፡ እንዲያውም ንጉሡ ተወቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እሳቸው በኤርትራ ሕዝብ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር ነበር የሚታዩት፡፡ ይህን እያወቁ ነው እንግዲህ ፌዴሬሽኑን እስከ መጨረሻው ተግባራዊ ማድረግ ያቃታቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በሌላ በኩል የአደዋን ጦርነት በማንሳት አፄ ምንሊክ ኤርትራን በመተው መመለሳቸውን ችግሩ ሥር የሰደደ እንደነበር የሚናገሩትስ?
አቶ ግርማ፡- ከዚያ በፊትም እኮ በጉራዕና በሌሎችም ጦርነቶች ተሞክሯል፡፡ አልተቻለም እንጂ፡፡ ምንሊክ በነበረው መሣሪያና በቀረው የሰው ኃይል ወደዚያ ገፍቶ ቢሄድ ሌላ ጣጣ (ባክፋየር) ነበር የሚያደርገው፡፡ ስለዚህ ምንሊክ እስከቻለው ድረስ ሄዶ መመለሱ ጥሩ ብልኃት (ዊዝደም) ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን የጨዋታ ሕግና የተጫዋቾችን አቅም ነው ማየት የሚገባው፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ አሁን ኢትዮጵያና የኤርትራ ሁኔታ ምን ዕድል የሚገጥመው ይመስልዎታል?
አቶ ግርማ፡- እኔ በበኩሌ ወደ አንድነት የሚያጋድል ይመስለኛል፡፡ በአንድ መንግሥት ሥር እንተዳደር የሚለውን ግን አልቀበለውም፡፡ እኛም እንደፈለግን እንግባ እንውጣ፡፡ እነሱም እንደፈለጉ ይውጡ ይግቡ ነው፡፡ እንደ ጥሩ ጎረቤት ተሳስበን ተዋደን መኖር አለብን ነው የምለው፡፡ ብዙ የሚያቀራርበን ነገር አለን፡፡ ሕዝቡ በባህል የተሳሰረ ነው፡፡ እንደ በፊቱ እኔ እገዛሃለሁ፣ አትገዛኝም ሳይሆን በመከባበር መኖር ይቻላል፡፡ በበኩሌ ኢትዮጵያን የሚጠላ ኤርትራዊ አለ ብዬ አላስብም፡፡
ሪፖርተር፡- እስርዎና የተወሰኑ ግለሰቦች የጀመሩት የእርቅ ጉዳይስ ምን ደረሰ?
አቶ ግርማ፡- የትም፡፡ በወሬ ደረጃ ነው ያለው፡፡ ሰውየውን [ኢሳያስን] ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከወያኔ ጋር አልደራደርም ይላል፡፡ እኛን ተቀብሎ መንግሥቱን ካልተቀበለ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጥረቱ አልተቋረጠም፡፡ ከዚህ በፊት ኖርዌጂያኖችም ሞክረው ነበር፡፡ የሃይማኖት አባቶችን ይዘው ጥረዋል፡፡ እነሱ በጀመሩት መንገድ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ እኔ በበኩሌ ሕዝቡን አውቀዋለሁ፡፡ ሕዝቡም ያውቀኛል፡፡ ይሰማኛል ብዬ ነው የጀመርኩት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ሆነው አይቀሩም ባይ ነኝ፡፡ አንድ ቀን እውን ይሆናል፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ በዓለ ሲመት ላይም ተገኝቼ ለካርዲናሉ [አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ] ይህንን በይፋ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የሚጠበቅብዎ ትልቁ የቤት ሥራ ይህ ነው ብያቸዋለሁ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ብዙ ካቶሊኮች ስለሚገኙና በቤተ ክርስቲያኒቱም ተፅዕኖ ይህ ሊሳካ ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ በእርስዎ የሚመራው የእርቅ ጉባዔ አሁን ወደ ካርዲናሉ ዞሯል ማለት ነው?
አቶ ግርማ፡- እኔም የዚሁ አካል ነኝ፡፡ ይህ የምተወው ጉዳይ አይደለም፡፡ ምናልባትም ከፍተኛ ደስታ የሚሰጠኝ እሱ ነው፡፡ አሁን ግን አቡኑ የደረሱበት መንፈሳዊ ሥልጣን እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ጉዳይን ለመፍታት የተሻለ አቅም አለው፡፡ እንግዲህ አንድ ላይ ሆነን እንጥራለን ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥትም ድጋፍ ይጠቅመናል፡፡ ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም እዚያው አሥመራ ድረስ ሄደን እንደራደራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በርካታ ዓመታትን ስላሳለፉበትና በኃላፊነት ስለመሩት የአቪዬሽን ተቋምስ ምን ይላሉ? አሁን የሚመለከቱት ሲቪል አቪዬሽን በጠበቁት መጠን አድጓል?
አቶ ግርማ፡- ይህን ጥያቄ ከአንድ ከአሥር ዓመት በፊት ብትጠይቀኝ ኖሮ መልሴ የተለየ ይሆን ነበር፡፡ በእኔ በኩል ሲቪል አቪዬሽንና አየር መንገዱ ዕድገታቸው አልተመጣጠነም፡፡ አቪዬሽን ስንል የበረራ ተቋሙ፣ ቴክኒክ ክፍሉና ሌላው ከበረራ ጋር የተያያዘውን ክፍል ያካትታል፡፡ በዚህ ረገድ የሚገባውን ያህል አድጓል ማለት ይከብዳል፡፡ አየር መንገዱ ግን ከሚጠበቀው በላይ ያደገ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዓለም ላይ ብዙ መዳረሻ ያለው መሆኑና አብረውት ከተመሠረቱ አየር መንገዶች ጋር ሲወዳደር በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቱ ነው፡፡ በአቪዬሽን ዳይሬክተርነቴ በእንግሊዞች ሥር የነበረውን ተቋም በመንግሥት ሥር በማድረግ ዕድገቱ እንዲፋጠን አድርጊያለሁ፡፡ የአቪዬሽን ሙያተኛ ብዙ ባልነበረበት ጊዜ እኔና የተወሰንን ሰዎች በውጭ አገር የቀሰምነውን ዕውቀት አበርክተናል፡፡ በአንድ ወቅት ከንጉሡ ጋር ያፋጠጠንን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡ በወቅቱ እኔ የአቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ነበርኩና የኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲካሄድ ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ አንዳንድ ሚኒስትሮቻቸው ‹‹ይህ መቶ አለቃ ያለ ግርማዊነትዎ ፈቃድ እንደፈለገው እየሠራ ነው፤›› ብለው ከሰውኝ ነበር፡፡ በኋላ እሳቸው መጥተው ከተመለከቱ በኋላ፣ ‹‹ግርማዊነትዎ ይህን እኮ እርስዎ ራስዎ የሚፈልጉትና ፈቃድዎን የሰጡበት ነው፤›› ብዬአቸው ሥራው ቀጥሏል፡፡ የአቪዬሽን ዘርፍ ብዙ የተደከመበት ነበር፡፡
የሆነም ሆኖ አሁንም ያለበት ሁኔታ ጥሩ ይመስላል፡፡ እነፓናማን የመሳሰሉ የላቲን የአሜሪካ አየር መንገዶች ከስመዋል ሉፍታንዛም እየተንገዳገደ ይመስለኛል፡፡ አስታውሳለሁ 57ኛው የአቪዬሽን ስብሰባ በአሜሪካ ተካሂዶ ነበር፡፡ እኔም ተገኝቼ ለአሜሪካኖቹ ኢትዮጵያ ውስጥ መላውን አፍሪካ የሚያካትት ፈረንሣይኛ ተናጋሪውንም ሆነ እንግሊዘኛ ተናጋሪውን የሚወክል ‹‹ኤር አካዳሚ›› እንዲቋቋም ጠይቄያቸው፣ ‹‹በል ሂድና መንግሥትህን አስፈቅድ›› አሉኝ፡፡ እኔ እዚህ ስመለስ ወንበሬ ተነቃንቋል፡፡ አሜሪካዊ ነው ተብዬ ወጥቻለሁ፡፡ ችግሩ የእኔ መውጣት ሳይሆን እኔን የሚተካ ሰው አለመኖሩ ነበር፡፡ ‹‹እንደ እነ መቶ አለቃ ግርማ ዓይነቱ እያለ አሜሪካ እንዴት አድርጋ ኢትዮጵያን ትርዳ?›› እየተባለ ይዘፈን ነበር፡፡ እኔ ቴክኒኩን ነበር የምናገረው፡፡ ቶሎ እንደግ፣ እነዚህን ወጣቶች አስተምረን ፓይለት እናድርግ ነበር የምለው፡፡ በእርግጥ አሩሻና ኮትዲቫር በጊዜው በአፍሪካ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ የእኛ ዕቅድ ግን የተለየ ነበር፡፡ እናም የእኔን ቦታ የሚተካ ሰው ተፈልጎ አሜሪካ አገር ተገኘ፡፡ የኤምባሲያችን ጸሐፊ ነበር፡፡ የማይቆረቁር፣ የማይጋፋ ተብሎ መጣ፡፡ በኋላ ‹‹አንድ እብድ መቶ አለቃ የማንችለውን ነገር አምጥቶ ተቸገርን፤›› ብሏል፡፡ እኔን አውሮፕላን ሲያይ ይሰክራል ብለው አውሮፕላን የማላይበት ቦታ ሰደዱኝ፡፡ በዚህ ምክንያት የአቪዬሽን ኮሌጁን አጣን፡፡ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ይህ ተሳክቶ ቢሆን ዛሬ ከደረስንበት እጥፍ በደረስን ነበር፡፡ አሁን አየር መንገዱ ብቻ ጎልቶ የወጣ ይመስለኛል፡፡ ሲቪል አቪዬሽኑና አየር መንገዱ ጎን ለጎን ነው ማደግ ያለበት፡፡ ምክንያቱም ፈቃጁም ሆነ የኦፕሬሽኑ ሥራ የሚሠራው በሲቪል አቪዬሽኑ ነው፡፡ ውስጡን ብዙ ለማወቅ ስላልፈለግኩ ብዙ አላውቀውም፡፡ የምሰማው ግን ጥሩ ይመስላል፡፡ በናቪጌሽን በኩል ያስመጧቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ በኤር ትራፊክ ኮንትሮል በኩልም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ያ ያበላሸነው አጋጣሚ ግን ሁሌም ይፀፅተኛል፡፡ እሱ ነበር የበለጠ ቦታ የሚያደርሰን፡፡
ሪፖርተር፡- ከሚደክሙባቸው ጉዳዮች አንዱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ እንዲቆም መጣር ነበር፡፡ እሱስ ከምን ደረሰ?
አቶ ግርማ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኅብረቱ ሊቀመንበር ሆኖ በተመረጠበት ወቅት ይህን ጉዳይ አጥብቆ እንዲይዘው ነግሬው ነበር፡፡ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራ ፓናልም (ቡድንም) ተቋቁሞ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ጥያቄው ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ቀርቦ ምላሹን እየተጠባበቅን ነው፡፡ ለክዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ቆሞ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አለመቆሙ ትክክል አይደለም፡፡ በበኩሌ ለአፍሪካ አንድነት ዕውን መሆን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡ ግዮን ሆቴልን እኮ ለእነሱ ብለው ነበር ያስገነቡት፡፡ የአፍሪካ አንድነት መሰብሰቢያንም እሳቸው ናቸው ያሠሩት፡፡ በምንም መሥፈርት ክዋሜ ንክሩማህ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የገነነ ክብር አልነበራቸውም፡፡ እሳቸው በደከሙበት ንኩሩማህ የአገሩ ባለሀብት ሆኖ መቀመጡ ትክክል አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ምናልባት በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የንክሩማህ ሚና የተለየ እንደነበር መገለጹ ይሆን?
አቶ ግርማ፡- በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴም ቢሆን የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ እንዲያውም ክዋሜ ንክሩማህ ከፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ በፊት በሞኖሮቪያው ግሩፕ ነበር፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ አንድነትን ካነሳን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ያህል የደከመ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል የምንለው፡፡
ሪፖርተር፡- ሐውልቱ እንዲቆም የታሰበው በአዲሱ የኅብረቱ ግቢ ነው ወይስ በቀድሞው?
አቶ ግርማ፡- ከተሳካልን እሳቸው ባስገነቡት የአፍሪካ አንድነት አዳራሽ ግቢ ውስጥ አፍሪካ ጎዳና ላይ ከሚገኘው አምፊ ቴአትር አጠገብ ነው፡፡ አዲሱማ የቻይና ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ታሪክ ጅማሬ ያለውና የእሳቸውም ውርስ (ሌጋሲ) መታሰብ ያለበት በቀድሞው ግቢ ነው፡፡ ያማ የቻይና ነው፡፡ ለክብሩም ደግሞ ራሳችን ባስገነባነው ቦታ ነው መሆን ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ከቤተ መንግሥት ከለቀቁ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር ይገናኛሉ?
አቶ ግርማ፡- ከኃይለ ማርያም ጋር አንድ ሁለቴ ተገናኝተን ነበር፡፡ ያው የተነጋገርነው ቀደም ሲል በገለጽኩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ምላሽ አልሰጠኝም፡፡ ከዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር አንድ ጊዜ ሚሊኒየም አዳራሽ በነበረ የአዛውንቶች ስብሰባ ላይ ተገናኝተናል፡፡ ዋንጫም ሸልሞኛል፡፡ እኔ በሆነው ባልሆነው እሸለማለሁ ዕድለኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋርስ የነበርዎ ቅርበት ምን ይመስላል? ከሥራ ውጭ የነበራችሁ ማኅበራዊ ሕይወትስ?
አቶ ግርማ፡- ከመለስ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ እሱ ‹‹ምሳ ብላ››፣ ‹‹እራት ብላ›› ይለኛል፡፡ እኔም ‹‹ቡና ጠጣ›› እለው ነበር፡፡ ተልዕኮውን የሚያውቅ ሰው ነበር፡፡ ላመነበት ነገር ይታገላል፡፡ አምኖም ያሳምናል፡፡ በሌላ በኩል ጨዋታም ያውቃል፡፡ አንድ ጊዜ አትሌቶችን ስንሸኝ ለደራርቱ ይመስለኛል ‹‹ይኼ ቦታ ቀላል አይምሰልሽ የኔን ፀጉር መልጦ የእሳቸውንም እግር ሰብሯል፤›› ብሎ አስቋታል፡፡ ሁሉንም ዓይነት ጨዋታ ያውቃል፡፡ ቀላሉንም ከባዱንም፡፡ እኔን በተለየ መልኩ ያከብረኛል፡፡ ‹‹እዚህ ዞር ዞር ብዬ ልምጣ፤›› ይለኛል፡፡ ‹‹ዓላግባብ ግዴታ ውስጥ እንዳትገባ፤›› እለዋለሁ፡፡ ብቻ ያሳዝናል፡፡ ያለ ዕድሜው ነው ያለፈው፡፡ 57 ዓመት ማለት ትንሽ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ላለመስማማትም እንስማማለን፡፡ እንከባበር ነበር፡፡ የመለስ ተሰጥኦ በቀላሉ የሚተካ አይደለም፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- በፕሬዚዳንትነትዎ ከአቶ መለስ ጋር የተከራከራችሁባቸው ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ግርማ፡- እንግዲህ ከፕሬዚዳንቱ እናንተ ምን እንደምትጠብቁ አላውቅም፡፡ በበኩሌ ያስደስቱኝን ነገሮች አሳክቻለሁ፡፡ የሞት ፍርድን ማስቀረት ቀላል አይደለም፡፡ ሌላ ቅር የሚለኝ አንድ ነገር ፕሬዚዳንቱ አንድ ሕግ ከፓርላማ መጥቶለት በ15 ቀናት ውስጥ ካልፈረመ ወይም ደግሞ ካልተቃወመ ሕግ ሆኖ ይወጣል የሚለው ነው፡፡ እኔ ግን ፈጣን ስለሆንኩ የሚታረም ነገር ካለው ቶሎ እንዲስተካከል አስተያየት አካትቼ እልካለሁ፡፡ ካልሆነም ተቃውሞዬን እገልጻለሁ፡፡ በዚህ ነበር መለስን የምሸውደው፡፡
ሪፖርተር፡- በቀድሞውና በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የሚታየዎት ልዩነት ምንድነው?
አቶ ግርማ፡- እገሌ ይበልጣል፣ እገሌ ያንሳል አልልም፡፡ ሁለቱም የተለያየ ሰብዕናና የዕውቀት ዝንባሌ ነው ያላቸው፡፡ መለስ በተፈጥሮ ብልህ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ የረቀቀ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ኃይለ ማርያም ጥሩ እየሠራ ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ዘንድሮ አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከተመለከቷቸው ምርጫዎች አንፃር እንዴት ይመዝኑታል?
አቶ ግርማ፡- የዘንድሮ ምርጫ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በሥልጣን ያለው ፓርቲ ሥልጣኑን ማጣት አይፈልግም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ብዙም ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ አይመስሉም፡፡ ይኼን ያህል ጠንካራ ተቃዋሚ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ የሚያሸንፍ ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በተቃዋሚዎች ላይ የሚመለከቱት ድክመት ምንድነው? በኢሕአዴግስ በኩል?
አቶ ግርማ፡- ኢሕአዴግ ቀደም ብሎ ነው ዝግጅቱን የጀመረው፡፡ እነ ኃይለ ማርያም ቀድመው ሕዝቡን ያነቃቁት ይመስለኛል፡፡ በተቃዋሚዎች ዘንድ ኢሕአዴግ ተሸንፎ በምርጫ የሚወርድ አይመስላቸውም፡፡ በዚያ ላይ የፖሊሲ አማራጭ በጥሩ ሁኔታ አያቀርቡም፡፡ የኢሕአዴግን ፖሊሲ ዘርዝረው አማራጭ አያቀርቡም፡፡ ይህም ሆኖ ሁኔታው ረብሻንና አለመረጋጋትን አስቀርቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ መፈጠር የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ለአገሪቱ የሚጠቅማት የክርክር መድረክ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሥልጣን ዘመንዎም ሆነ በሕይወት ታሪክዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምን እንዲያስታውስዎ ይፈልጋሉ?
አቶ ግርማ፡- በፕሬዚዳንትነት ዘመኔ ከሚገባው በላይ የሠራሁ ይመስለኛል፡፡ ፕሬዜዳንቱ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ 23 ሰው ከሞት ፍርድ አትርፌያለሁ፡፡ ይኼ ብዙ ሰዎችን ያነጋገረ ይመስለኛል፡፡ እነሱ ገዳይ ሆኑና እኛ ገዳይ መሆን የለብንም፡፡ ብዙ ጊዜ እኔ የራሴ መንገድ አለኝ፡፡ ያዋጣኛል፡፡ ተከስሼ ሄጄ ረትቼ መጥቻለሁ፡፡ ይሁንና በዚህ ልታወስ፣ በዚህ አልታወስ አልልም፡፡ የጀመርኩትን የደን ልማት እገፋበታለሁ፡፡ በላንጋኖ አካባቢ ጠፍቶ የነበረው የደን ሽፋን በሰባት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል፡፡ በረሃነት የሚባል ነገር እንዳይመጣ እንታገላለን፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ጉዳዮችንም እቀጥልባቸዋለሁ፡፡ ብዙ የምለው ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ የፕሬዚዳንትነት ዘመኔን መለስ ብዬ ሳየው መልካም እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንደመሰለው ይመለከተዋል ነው የምለው፡፡
No comments:
Post a Comment