መነሻዬ የሻለቃ ዮሴፍን ትግል ይቀጥላል የሚል ርእስ የሰጠው ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ የታተመው መጽሐፍ ነው። ያነበብኩት ቁጭትና ንዴት እየተሰማኝ ነበር። ለዚህ ሰውነት የሚጎዳ ስሜቴ ዋናው ምክንያት የመጽሐፉ ደራሲ እንደገለጸው፥ ጀኔራል አማን አንዶም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ዕድሉ እጃቸው ላይ ወድቆ ሳለ፥ የተሳለ ቢላዎ የያዙ አራጆች ወደቄራ እንደሚነዱት የደለበ በሬ ወደሚገደሉበት ሁኔታ ሲመሯቸው፥ ዓይናቸው እያየ እጃቸውን ሰብስበው በጥሞና መሄዳቸው ነው።
ደራሲው እንደሚለው ራሳቸው ጀኔራሉ የመረጧቸው ረዳቶቻቸው ወጣት የጦር መኳንንት (አንዱም ደራሲው ነበር) የደረሳቸውን መረጃ እየጠቀሱ ሲያስጠነቅቋቸው ሰልችቷቸው ኖሮ፥ “ስሙ፣ እኔ የምሰራውን አውቃለሁ፡ ዝም ብየ ባልተጣራ መረጃ አልጓዝም፡ እንድታውቁ የምፈልገው፣ አማን ማለት ደርግ ነው፣ ደርግ ማለት አማን ነው፡ ወደፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ነገር እንድታነሱብኝ አልፈልግም፡ እዚያም ያሉት እኮ ከማንም የሚያንሱ አይደሉም” አሏቸው። እንደ ሰንጠረዥ፥ እንደ ኳስ ጨዋታ፥ በአንድ ስሕተት የተመኘነው ለውጥ ገደል ገባ። የዚህ ግራ የገባው የጀኔራሉ አቋም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ወጣቶቹ ረዳቶቻቸው በደረሳቸው መረጃ ዐውቀውታል፤ ዶክተር በረከተ አብ ሀብተ ሥላሴ ረዳቶቻቸውን ትተው ከደርግ ጋር እንዲተባበሩ ስለመከራቸው ነው። በበረከት አስተያየት ጊዜው ሲደርስና ሲያመች ደርጎችን ማስወገድ ይቻላል፤ እነዚህን ግን አይቻልም። (ባይቻልና ለውጡን እነዚህ የአካዴሚ ምሩቆች ቢመሩት ምን ይሆን ነበር?) ልጽፍ ያሰብኩት እንኳን በጀኔራል አማን ስሕተት ስለባከነው ዕድል ሳይሆን፥ ጀኔራሉ ለእርዳታ የመለመሏቸው ወጣት የጦር መኳንንት ማንነት ስለሰጠኝ ትዝብት ነው። እነዚህ የጦር መኳንንት የጀኔራል አማንን ችሎታና በጦር ሠራዊቱ ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት በመተማመን እሳቸውን መሪ አድርገው ንቅናቄ ለማካሄድ ሞክረው ነበረ። የነዚህ ወጣት ሹማምንት ማንነት ሁለት ቁም ነገሮችን አሳይቶኛል። መጀመሪያ ስማቸውን፥ ገጽ 38 ላይ እንደተዘረዘረው ልቅዳው፤ የዚያን ጊዜ ማዕርጋቸው የሁሉም ሻለቅነት ነበር። አብዱላሂ ዑመር ሽመልስ መታፈሪያ አበራ ባንቲዋሉ ሁሴን አሕመድ ዮሴ ያዘው ካህሣ ወልደአብ ጎሹ ወልዴ እምቢበል አየለ እነዚህ ወጣት የጦር መኳንንት ከተለያየ ጎሳ መምጣታቸውን ስማቸው ይመሰክራል። ፍጹም የአማራ ስም ያላቸው በቍጥር በዛ ይላል። ግን ሁሉም አማሮች ናቸው ለማለት ፈጽሞ አይቻልም። ሌላው ቢቀር ጎሹ ወልዴ አማራ እንዳይደለ እናውቃለን። የነዚህ ወጣቶች በአንድ ቡድን ተስማምቶ መሰለፍ ሁለት ቁም ነገሮችን ያስገነዝበናል፤ አንደኛ፥ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጎሰኝነት አልነበረበትም፤ ሁሉንም ለሀገራዊ ቁም ነገር በአንድ ዓይነት ሙያ እኩል አሰልጥኖ ለግዳጅ እኩል አስሰልፏቸዋል። ሁለተኛ፥ ወጣቶቹም ለውጥ ለማምጣት አብረው ሲዶልቱ፥ ጎሰኝነት ኢትዮጵያውያንነታቸውን አላሰናከለባቸውም፤ ለአንድ ዓላማ በመተማመን በአንድነት ቆመዋል። ለአንደኛውም ሆነ ለሁለተኛው ቁም ነገር አለቃቸውና መሪያቸው ሊያደርጉት ያሰቡት አማን አንዶም ከማን ጎሳ እነደነበረ እናስታውስ። ሕዝብ የተመኘውን ለውጥ (ዲሞክራሲን) ትተው የጎሰኝነትን መርዝ የረጩብንና አሁን ደግሞ ሀገሪቷን የወረሷት ጉደኞች እስኪጨፍሩብን ድረስ፥ እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያና መንግሥቷ ከጥንት ጀምሮ እንደዚህ ነበሩ። የወረስናት ኢትዮጵያ ይኸን ትመስል ነበር፤ ነበር፡ ነበር! የጉደኞቹ መርዝ መጀመሪያ ጊዜ የተረጨው በተማሪዎቹ ንቅናቄ ውስጥ እንደነበረ እናስታውሳለን። ደርግ ድጋፍ ያገኘ መስሎት በኋላ እስኪያፈገፍግ ድረስ ኮሚኒዝም የሚባል የማባባሻ ዘዴ ከሶቬት ዩኒየን እያመጣ አፋፋመው። በፍልስፍናው ላይ ያሰበበትም ያላሰበበትም ሁሉም እኩል ሆይ አለለት። የሚያዳላን እንጂ ሁሉን እኩል የሚያይ አስተዳደርን ማን ይጠላል? ግን ፍልስፍናው “ኢትዮጵያ የጎሳዎች እስር ቤት ናት፤ አሳሪዎቹም አማሮች ናቸው” የሚል መሆኑ ቀደም ብሎ በፍልስፍና ደረጃ ቢታወቅም አሁን ሥር እየሰደደና በሥራ ላይ ሲውል አሠጋ። ይኸን ያነሣሁት ያልተሰማ አዲስ ታሪክ ለማሰማት ሳይሆን፥ ቀጥሎ ወደማነሣው ትዝብት እንዲያሸጋግረኝ ነው። ወጣቶቹ የጦር መኳንንት የጀኔራል አማንን መሪነት ካጡ በኋላ፥ የለውጡን አመራር ከደርግ ቀምቶ ቀና አቅጣጫ ለማስያዝ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ብዙ ጊዜ በሰዋራ ቦታ ላይ እየተገናኙ ተወያይተዋል። በአንዱ ስብሰባቸው ላይ አብዱላሂ (ዑመር) እንዲህ አለ፤ ይህንን በሀገራችን ላይ የተፈጠረውን አሰቃቂ ሁኔታ፣ እኛ አሁን ባለንበት ደረጃ፣ ልንለውጠው እንደማንችል አምናለሁ፡ ሆኖም ደግሞ፣ ይቅርታ አድርጉልኝና፣ እኔ በአደሬነቴ ሳየው፣ በሀገራችን ውስጥ ጭቆና አልነበረም ለማለት አልደፍርም፡ ይኽንንም ስል፣ ለውጡ አሁን በተያዘው መንገድ ፣ በእስራትና በጭፍጨፋ፣ ይቀጥል ማለቴ አይደለም፡ ነገር ግን፣ እኛ ምንም ማድረግ ካልቻልን፣ ምናለበት ለአንድ አመት ያህል፣ አብረን እየሠራን ብናየው፡ ደርግም እኰ፣ ሲረጋጋ፣ ምናልባት፣ ሕዝብ የሚቀበለውን ለውጥ፣ [ሊ]ያመጣ ይችል ይሆናል፡ ያ ካልሆነ ደግሞ፣ የዚያን ጊዜ እንደገና እንሞክራለን፣ ልብ እንበል፤ የጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ አመፅ ለውጥ ለማምጣት ነበር። የ“ትግል አይቆምም” ጸሐፊና ጓደኞቹም ያድሙ የነበረውና ትግሉን የቀጠሉት ለውጥ ለማምጣት ነበር። በሀገራችን የፖለቲካ ለውጥ ማስፈለጉን ማንም አይክደውም። ሕልማችን ጥንታዊት አገራችን ዘመናዊ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንባትና ሁላችንም በነፃነትና በእኩልነት እንድንኖር ነው። በአጭሩ ዲሚክራሲን እንደምንፈልገው አድርገን እንቀርጸዋለን እንጂ በአሁኑ ዘመን ተወዳዳሪ አይቀርብለትም። አብዱላሂ ዑመር ግን የለውጡን አስፈላጊነት ያየው ከዲሞክራሲና ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጻር ሳይሆን፥ ከጎሰኝነት ነው። በእሱ አእምሮ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውና የማያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን አሉ። የኢትዮጵያን ሕዝብ በአእምሮው ውስጥ ለውጥ ከሚያስፈልገውና ከማያስፈልገው ከፍሎታል። ይህ እምነት የአንድ አደሬ ነው ወይስ እንደዚህ የሚያምኑ ሌሎችም አሉ? አጭሩ መልስ የወያኔዎችን የጥርቃሞ ፓርቲ (ኢሕአዴግን) ዘርዝሮ ማየት ነው። “እነዚህ ወያኔ የፈጠራቸው ተቀጽሎዎች ናቸው” ብንልም፥ በፖለቲካው ደስተኞች የሉባቸውም ለማለት አንደፍርም። አሉባቸው። በሕዝብና በመንግሥት ዘንድ ሥር ሰድዶ የነበረው ኢትዮጵያዊነት እንዳይፋፋ፥ መጀመሪያ የተማሪዎቹ ንቅናቄ፥ ቀጥሎ ደርግ፥ አሁን ደግሞ ወያኔዎች ወኻ ከልክለው አጠውልገውታል። በምትኩ ጎሰኝነትን ስለተከሉበት፥ የትግሉ መልክ ተለውጧል። ለዚህ ነው የሀገር ወዳዱ የትግል ሰይፍ ሁለት ስለት ያለው መሆን ያለበት፤ አንዱ ጎሰኝነትን መጒመጃ ሲሆን ሁለተኛው ለጥንቱ (ለዲሞክራሲ) ትግል መንገዱን መጥረጊያ ይሆናል። በጎሰኞቹ እምነት መሠረት፥ ለውጥ የማያስፈልጋቸው (“ማ” አጥብቀን እንያዝ) የተባሉት እነማናቸው? “ኢትዮጵያ የጎሳዎች እስር ቤት ናት፤ አሳሪዎቹም አማሮች ናቸው” ከተባለ፥ ለውጥ የማያስፈልጋቸው አማሮቹ መሆናቸው ነው። ጉዳዩ ለውጥ የማያስፈልጋቸውን ኢትዮጵያውያን ለይቶ ከማወቅ ላይ አላቆመም። የችግሩ ምክንያት (የኢትዮጵያን ጎሳዎች አሳሪዎችና ጨቋኞች) እነሱ ስለሆኑ፥ ለውጥ ለማምጣት መፍትሔው “ለውጥ የማያስፈልጋቸውን” መምታት ነው ከሚለው ውሳኔ ተደርሷል። ይኼ እኮ ያንን ሁሉ የኢትዮጵያ ጎሳ በአማራው ሕዝብ ላይ በጠላትነት ማስነሣት፥ የአማራው ሕዝብ ሠላሳ ሚሊዮን ከሆነ ሕዝብን እርስ በርስ ማጫረስ ነው!! መፍትሔው ምንድን ነው? አማራውን ታጠቅ ማለት የባሰውን ማፋጀት ይሆናል። በዘር መደራጀት ደግሞ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የታሪክ ተቺዎች ርእስ አድርጎ መቅረት ይሆናል፤ በተለይ በአማራው ላይ አያምርበትም። ግን በዘር፥ በሃይማኖት፣ በጾታ፥ በቀየ፣ በሙያ መደራጀት ፍጹም አስከፊ ርምጃ ነው ወይ? መልሱ እንደ ድርጅቱ ዓላማ ነው፤ ሰዎች ድርጅት የሚያቋቁሙት ወይ ራሳቸውን ለመጠበቅና ባህላቸውን ለማዳበር፥ ወይም ሌላውን ለማጥቃት፥ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆንና በመንግሥት ንብረት የራስን ወገን ብቻ ለመጥቀም፥ ወይም የሌላውን ዘር፥ የሌላውን ሃይማኖት፣ ባለሌላውን ጾታ፥ የሌላውን ቀየ ነዋሪዎች፥ የሌላውን ሙያ አባላት ለማጥቃት ይሆናል። ይኼኛው ዓይነት ድርጅት በሕግ መከልከል፥ መኰነንም አለበት። ለመረዳዳት፥ ከዚያም አልፎ ሌሎችን ለመርዳት ከሆነ ግን በሕግ መፈቀድ፥ መደገፍም አለበት። እንዲያውም እኮ፥ የአንድ ሀገር የዲሞክራሲ መሠረት እንደዚህ ያሉ የተራድኦ ሕዝባዊ ድርጅቶች መብዛትና መጠናከር ነው። በአሜሪካን አገር የጥቁሮች ሰብአዊ መብት ሊከበር የቻለው ጥቁሮች ለመብታቸው ማስጠበቂያ ባዘጋጁት ድርጅት ጥረትና መሪነት ነው። የሴቶች ማኅበር የሴቶችን መብት ከማስከበር አልፎ፥ ሴቶች በፖለቲካ እንዲሳተፉ ቀን ከሌት እየሠራ ነው። በምርጫ ጊዜ፥ “የእስፓንኛ ተናጋሪዎች ድምፅ ወዴት ይሄድ ይሆን?” የሚለው ጥያቄና መልሱ የጋዜጦቹን የመጀመሪያ ገጽ ይይዛሉ። የተጠናከረ የአማርኛ ተናጋሪዎች (የአማሮች) የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ቢኖር፥ ለሀገሪቱ የሚሰጠው ጥቅም ወሰን አይኖረውም። እግረ-መንገዱንም በአማራነታቸው በየቦታው በተናጠል ስለሚጠቁት ድምፃቸውን ማስተጋባትና ለመርዳትም ፈጥኖ ለመድረስ ይችላል። ዋና ዓላማው ግን፥ ዕርቀ ሰላም ማውረድና ለዲሞክራሲ መዳበር አመርቂ አገልግሎት መስጠት ነው። የአማሮች ቊጥር ብዙ ነው ብለናል፤ በዚያ ላይ በደጉም በክፉውም ምክንያት ከሌሎቹ ጎሳዎች ጋር በደም የተሳሰረ ስለሆነ፥ ለአንድነት፥ ለነፃነት፥ ለእኩልነት የቆመን የፖለቲካ ተወዳዳሪ ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ ለመደገፍ ዝግጁ ነው። ለቍጥረ-ትንሽ ጎሳዎችም መከታ ይሆናል። ኢትዮጵያን ከዘራፊዎች ነፃ የሚያወጣት ፓርቲ የአማራው የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት የሚደግፈው ፓርቲ መሆኑን ወያኔዎች ስለሚያውቁ፥ አማራ እንዲደራጅ አይፈልጉም። በአንድ በኩል፥ “አማራ በዘር አይደራጅም” እያሉ አማራውን የሚያደናግሩትን፥ በሌላው በኩል፥ “አማራ እንደገና ሊገዛችሁ ነው” እያሉ ጎሳዎችን ከሥጋት ላይ የሚጥሉትን የሚሽረው የአማራ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ነው። አማርኛ ተናጋሪው እንዳይደራጅ የተጣለበትን የውጪ ተጽእኖና የውስጥ የሕሊና ደንቃራ አንሥቶ ለሦስት ግዴታ መደራጀት አለበት፤ አንደኛ፣ ከጎሳዎችና ከድርጅቶቻቸው ጋር ውይይት (dialogue) ለመክፈት። በውይይቱ ብዙ ነገሮች ይነሣሉ። አለመግባባት ካለ፥ ምክንያቱ ምንድንነው? መቸም ወያኔዎቹ ጎሳዎችን በአማራው ላይ ለማስነሣት የቀናቸው፥ ሻለቃ አብዱላሂ ዑመርም፥ “እኔ በአደሬነቴ ሳየው፣ በሀገራችን ውስጥ ጭቆና አልነበረም ለማለት አልደፍርም” ያለው ያለምክንያት ነው ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱ ምንድንነው? መሰማት አለበት። አማራውም ላለበት ክስ ሕዝባዊ ፍርድ ቤት አቋቁመን በሰባት ወይም ዘጠኝ ገለልተኛ ዳኖች ፊት መልስ መስጠት አለበት። ከሳሾችም ተከሳሾቹም የምሁራን ምስክሮች እየጠሩ ስለሚሟገቱ፥ ፍርድ ቤቱ ሕዝብ የሚታዘብብበር ትልቅ የምሁራን ጉባኤ ይሆናል። የተረታ ይክሳል፤ የረታ ይካሳል። ሁለተኛ፣ በምርጫ ጊዜ ኢትዮጵያ-አቀፍና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚጠቅም የኢኮኖሚ እድገት አጀንዳ ያለው ፓርቲ የሚያቀርበውን ተወዳዳሪ ለመደገፍ። ተወዳዳሪው የየትኛውም ጎሳ አባል፥ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሊሆን ይችለል። እንዲህ ያለ ድጋፍ ለመስጠት የድርጅቱ ቃል ኪዳን ይሆናል። ሦስተኛ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ በቋንቋው፥ በጾታው፥ በሃይማኖቱ ምክንያት መንግሥት ሲያጠቃው ፈጥኖ ለመድረስ። ድርጅቱ ሲቋቋም፥ ለምሳሌ ለተፈናቀሉት አማሮችና መሬታቸውን ለከበርቴ ተነጥቀው ለተባረሩት አኝዋኮች አለኝታ ይኖራቸዋል። አማርኛ ተናጋሪው ኢትዮጵያን ለማዳን ከአባቶቹ የወረሰው የታሪክ ግዴታ አለበት። ግዴታውን ለመወጣት ብዛቱና ታሪኩ ይረዳዋል። ታሪካችንን ስንመረምረው፥ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያን መንግሥታዊ ሥልጣኔ የመሠረተውና ያዳበረው፥ እንደ ግዕዝ ሴማዊ ቋንቋ ከሚናገረው ክፍል የሆነው የአማራው ሕዝብ ነው። ዛጔዎች ሥልጣኑን ለጥቂት ዓመታት ቢወስዱትም ያንኑ የአማራ ሥልጣኔ እያዳበሩ ተጓዙ እንጂ ሌላ ሥልጣኔ አላመጡም። አፄ ይኩኖ አምላክና ወራሲዎቹ ሥልጣኑን አስመልሰው፥ የጥንቱን ሥልጣኔ መጀመሪያ በሸዋ-አምሐራ፥ በኋላ በጎንደር አስፋፉት። አፄ ዮሐንስም የሥልጣኑን ማእከል ወደትግራይ አመጡት እንጂ፥ አክሱም ላይ የተመሠረተውን ሥልጣኔ አልለወጡትም። የዳኝነት ችሎታቸውን የሚያካሂዱት በአማርኛ ነበር። ንጉሡና በሳቸው ዘመን የነበሩ ሌሎቹ የትግራይ ባለሥልጣኖች ከውጭ አገር ጋር ይጻጻፉ የነበረው በአማርኛ ነበር። ደብዳቤዎቹ አሁንም በውጪ ሀገር መዛግብት ተከትተው ይገኛሉ። አማራው ግዴታውን ለመወጣት የመጀመሪያ እርምጃው የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ማቋቋም ነው። የድርጅቱ መቋቋም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያስደስትና ተስፋ የሚያበሥር (የወያኔን ቡድን ብቻ የሚያሠጋ) መሆኑ በግልጽ ቃላት መቅረብ አለበት። አሁን አገራችን ባለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ስናየው፥ “አማራ መጣብህ” የሚለውን የወያኔ ማስፈራሪያ ከአማራ የተራድኦና የዕርቅ ድርጅት ሌላ ሊያሳፍርና ውድቅ አድርጎ ሰላም ሊያወርድ የሚችል ኀይል የለም። ለዚህ ደርሰት አስፈላጊነቱ ስላልታየኝ፥ “አማራ ማነው?” ከሚል፥ መልሱ ብዙ ገጽ ከሚፈጅ ጥያቄ ውስጥ አልገባሁም። ሁሉም ራሱን ስለሚያውቅ፥ “አማራ ነን” የሚል ሁሉ በሙሉ አባልነት፥ በድርጅቱ የዕርቅና የሰላም ዓላማ የሚያምን ግን “አማራ ነኝ” የማይል ኢትዮጵያዊ ደግሞ በደጋፊ አባልነት መመዝገብ ይችላል። ሳልረሳው፤ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑት ወጣት የጦር መኳንንት ጀኔራል አማን አንዶምን መሪ አድርገው ደርግን ለመጣል ሳይችሉ ሲቀሩ፥ ከአማን ሞት በኋላ ሌላ ሰፋ ያለ ሙከራ አድርገው ነበር። መሪዎቹ ያድሙ ከነበረብረት ቦታዎች አንዱ ኢንጂኔር ሞገስ ቡሩክ ቤት ሲሆን፥ ባለቤቱ ወይዘሮ ደረጃሽ ወርቅ ቅጣው ብትያዝ የሚደርስባትን እያወቀች ምንም ቅሬታ አላሳየችም። ያም ሲከሽፍ፥ ሞገስ ቡሩክ፥ ተፈሪ ተ/ሃይማኖት፥ ጸሐፊው ዮሴፍ ያዘው ቤተ ሰቦቻቸውን የትም በትነው፥ ኬላ ሰብረው ወጥተው ትግላቸውን እስከመጨረሻው በትጥቅ ትግል ቀጠሉ። የሻለቃ ዮሴፍ ያዘው ባለቤት ወይዘሮ ወይንሸት መኰንን ባሏን የሸኘችው፥” ብቻ እግዚአብሔርን የምለምነውና አንተንም አደራ የምልህ፣ ተይዘህ በዚህ ሳጥን (ጣቷን ወደቲቪው እየጠቆመች) ውስጥ እንዳላይህ ነው” በሚል መሪ ቃል ነበረ፤ የጀግና ሚስቶች!! ተፈሪ ወደቀ፤ ሁለቱ ከዓሥራ ሰባት ዓመት በኋላ ከሚስቶቻቸው ጋር ሊገናኙ ቻሉ። ታሪካቸው የሚያስገርምና የሚመዘገብ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን አማራውን ለዕርቅና ለሰላማዊ ለውጥ የማደራጀት ጥሪ ነው። ሞረሽ ወገኔ የሚባል ድርጅት እንዳለ አውቃለሁ። ማሳሰቢያየ በሐሳብ ደረጃ ተደንቆና ተኰንኖ እንዳይቀር፥ አስኳሉ ካለ አስኳሉን ማጎልበት ይቻላል። – See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/5335#sthash.jbZxJjIE.dpuf - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39779#sthash.gk4ghJa3.dpuf
No comments:
Post a Comment