በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ28 ዓመታት ያህል ያስተማሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና የሥራ ውሌ በሕገወጥ መንገድ ተቋርጧል በማለት ዩኒቨርሲቲውን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡
ዶ/ር መረራ የጡረታ ማራዘሚያ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ከዩኒቨርሲቲው ጋር ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የኮንትራት ቅጥር ተፈራርመው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
‹‹አስተዳደሩ ወደ ታች መውረድ አለበት ተብሎ አዲስ አሠራር ተፈጥሯል፡፡ አሁን መቅጠርም ሆነ ማባረር የሚፈጸመው በኮሌጅ ደረጃ ነው፡፡ የቀጠረኝ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ቅጥሩ አይቻልም ተባልኩ፡፡ ምክንያቱ እስካሁን አልተገለጸልኝም፡፡ ዕድሜ እንዳይባል እኔን ያስተማሩኝ ሰዎች አሁንም እያስተማሩ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዩኒቨርሲቲው ተገፍቼ የምወጣው ያው በፖለቲካ አቋሜ የተነሳ እንደሆነ ይታወቃል፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ የዩኒቨርሲቲው ውሳኔ ሕገወጥ ስለሆነ ተቃውመው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ለበርካታ ዓመታት በሥራ ባልደረባነት የዘለቁት ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከትምህርት ክፍሉ ፍላጎት ውጪ ዶ/ር መረራ በሥራቸው እንዳይቀጥሉ በማድረጋቸው ምክንያት ከመጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከትምህርት ክፍሉ ኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ከትምህርት ክፍሉ ኃላፊነት መልቀቃቸውን ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ለዶ/ር ወልደአምላክ በውቀት ከጻፉት ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment