Tuesday, March 17, 2015

“ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ ሆን ተብሎ የተቀየሰ ስልት ነው”

semayawiparty1
የሶዶ ፖሊስ 8 የሰማያዊ ዕጩዎችን በማሰር ቅስቀሳውን አስተጓጉሏል
• የጅማ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ተዘርፏል
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅስቀሳ እንዳያደርግ በፖሊሶች ክልከላና ወከባ እየደረሰበት እንደሚገኝ የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ኃላፊና ም/ሊቀመንበሩ አቶ ስለሽ ፈይሳ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ዛሬ መጋቢት 5/2007 ዓ.ም ፓርቲው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅስቀሳ ያደረገ ሲሆን በባህርዳርና ወላይታ ዞን ፖሊስ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ቅስቀሰውን ማደናቀፉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ሰማያዊ ፓርቲ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት የከተማው ፖሊስ “የምርጫ ቅስቀሳ አልተጀመረም” ብሎ ያዋከበ ሲሆን የፓርቲው አመራሮችና አባላት ቅስቀሳ መጀመሩን ገልጸው ስራቸውን እያከናወኑ በነበሩበት ወቅት “ህገ ወጥ ሰላማዊ ሰልፍ” አድርጋችኋል በሚል ሌላ ክስ 8 የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችንና ሌሎች አባላትን በማሰር ቅስቀሳውን እንዳደናቀፈ የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ታደመ ፈቃዱ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በባህርዳር ከተማ ፖሊስ “በሞንታርቮ ለመቀስቀስ ፈቃድ ስላላመጣችሁ መቀስቀስ አትችሉም” በሚል ፓርቲው ሊያደርገው የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ እንዳደናቀፈ የፓርቲው የምዕራብ ጎጃም ዞን ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጌታነህ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ‹ለምን ትከለክሏቸዋላችሁ?› በሚል ህዝቡ ፖሊሶቹን በማፋጠጡ በድምፅ መቀስቀስ ባንችልም በህዝቡ ድጋፍ የቅስቀሳ ወረቀቶችን በማሰራጨት የተሳካ ቅስቀሳ አድርገናል” ሲሉ አቶ አዲሱ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅት ቅስቀሳ ለማድረግ ምንም አይነት ፈቃድ እንደማያስፈልግ የገለፁት አቶ ስለሽ ፖሊስ የሚፈጥረው እንቅፋት ሆን ተብሎ ሰማያዊ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ የተቀየሰ ስልት ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም “የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን በመሰረዝ ፓርቲው ምርጫው ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ ጥረዋል፡፡ ይህ አልበቃ ሲልም የቅስቀሳ መልዕክቶቻችን በተደጋጋሚ በሚዲያ እንዳይተላለፉ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ህዝብ እንዳንደርስ በህገ ወጥ መንገድ በፖሊስ ማስቆም ጀምረዋል” ብለዋል፡፡
በሌላ ዜና የጅማ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ባልታወቁ ግለሰቦች መዘረፉን የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ “በ02/07/07 ሁለት ሰዓት ላይ አራት ግለሰቦች ጽ/ቤቱን በመስበርና የጽ/ቤቱን ጥበቃ አስፈራርተው በማባረር ለቅስቀሳ የተላከ 6 ሺህ ኦሮምኛ በራሪ ወረቀት እንዲሁም 3 ሺህ አማርኛ በራሪ ወረቀት፣ አንድ የፎቶ ካሜራ፣ አንድ ባነር፣ ለሸካ ዞን ሊላክ የተዘጋጀ 5 ሺህ በራሪ ወረቀት፣ 50 ፖስተር፣ አንድ የእጅ ሜጋ ፎን፣ ሁለት ባነር፣ በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲዘርፉ የጽ/ቤቱን ኮምፒውተርም ሰብረዋል” ሲሉ ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment