በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ማሰብ የሚችልና የየድርጊታቸው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚችል አንድ ሰው እንዴት ይጠፋል? ተናገራችሁ ብሎ ማሰር፤ ጻፋችሁ ብሎ ማሰር፤ የፖሊቲካ ወረቀት በተናችሁ ብሎ ማሰር፤ … ያ ኤርምያስ ለገሰ ወደአምስተኛ ክፍል ግድም አድርሻለሁ ሲል ነበር፤ ታዲያ ይህ ሕገ መንግሥቱን ለማንበብ ያህል አይበቃም እንዴ? ይባስ ብለው በፍርድ የታሰሩ ሰዎች እንዳይጠየቁና ምግብ እንዳይገባላቸው ከለከሉ የሚባለው ምን ለማሳየት ነው? ጡንቻ! ያውም በእጃቸው ውስጥ ላለ እስረኛ! የተባበሩት መንግሥታት ያወጡአቸው ዓለም-አቀፍ ሕጎች ሁሉ አይሠሩም ማለት ነው? የወያኔ ሹሞች ሁሉ በእውነት ይሄ ሁሉ ግፍና ሕግን መረጋገጥ ውጤት የለውም፤ በእነሱ ላይም ምንም አያደርስም ብለው ያምናሉ? ብዙ ማሰብም አይጠይቅም፤ ሁሉንም፣ ግለሰቦችንም፣ ድርጅቶችንም፣ ዓለም አቀፉንም፣ ብሔራዊውንም ማስቀየም እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?
ሌላ የሚያስደንቅ ነገር ደሞ ይሰማል፤ በወህኒ ቤቶች እስረኞች በግድ ይቅርታ ጠይቁ እየተባሉ ነው አሉ፤ የምንርጫ ቦርድም ከማን ጋር ለመወዳደር እንደሆነ ባይታወቅም ፓርቲዎችን ይቅርታ ጠይቁ እያለ ነው አሉ፤ እንዴ! የይቅርታ ትርጉም ተለወጠ አንዴ? በግዴታ ይቅርታ የይቅርታን ዓላማ ድራሹን የሚያጠፋ ነው፤ ኧረ አስቡ! ወይም የሚያስብ ሰው ከቻይና ቅጠሩ!
No comments:
Post a Comment