ኦነግ ሲከተል የነበረው መንገድ ስህተት እንደነበር በይፋ በመናገር የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የተሰኘውን አዲስ ድርጅትና ወኪሎች ይዘው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት አቶ ሌንጮ ለታ ተቀባይ በማጣታቸው ወደመጡበት የተመለሱት ኦህዴድ ባቀረበው ተቃውሞ መሆኑ ታወቀ። የኢህአዴግ አፈ ቀላጤ የስላቅ መልስ ሰጡ። ኦዴግ (ኦዲኤፍ) በ2012 ምርጫ ሊጋበዝ እንደሚችል ቃል ተገብቶለታል።
የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በመነጠል ከኢትዮጵያ (“አቢሲኒያ አገዛዝ”) መገንጠልን አማራጭ አድርጎ ለግማሽ ምዕተ አመት ሲወድቅ ሲነሳ የኖረውን ኦነግ ሲመሩ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ፣ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር። የቀድሞው የትግል ጉዞ ስህተት እንደነበር በይፋ አስታውቀው ለድርድር ኢህአዴግ ደጅ የዘለቁት አቶ ሌንጮ ከጉዟቸው በፊት የተነሳባቸውን ተቃውሞ አስመልክቶ በሰጡት ማስተባበያ ከውሳኔያቸው ንቅንቅ እንደማይሉና በመጪው ምርጫ እንደሚሳተፉ አረጋግጠው ነበር።
ባለፈው ሳምንት ይፋ በወጣ መረጃ አቶ ሌንጮና ባልደረቦቻቸው የሚያናግራቸው በማጣታቸው አዲስ አበባን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።የጎልጉል የዜና አቀባዮች ምንጮቻችውን ጠቅሰው ከስፍራው እንዳሉት ከሆነ እነ አቶ ሌንጮ ቀደም ሲል ቃል ተገብቶላቸው ነበር። ኢህአዴግ እነ ሌንጮ አገር ቤት እንዲገቡ ማስተማመኛ ከመስጠቱም በላይ ሊደራደራቸው ፈቃዱ ነበር። በዋናነት ግን እነ ሌንጮን ኦህዴድ ብብት ውስጥ ማስገባት ነበር ዓላማው።
ኦህዴድ በጉዳዩ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም በመያዙና እነ ሌንጮ ድርጅቱ ደጅ እንዲጠጉ ባለመፍቀዱ፣ ኢህአዴግ ለጠቅላይ በሚጫወትበት የምርጫ ወቅት ላይ ኦህዴድን ማስቀየም ከመለስ ሞት ጋር ተያይዞ ተነስቶ የነበረውን ችግር እንዲያገረሽ ያደርገዋል ከሚል ስጋት ህወሃት እንደቀድሞው ኦህዴድ ላይ ጫና ማድረግ አልቻለም። በዚህም የተነሳ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ ወይም በእንግሊዝኛው ኦዲኤፍ) የሚያስተናግደው ሳያገኝ ሊመለስ ችሏል።
እነ ሌንጮ ወደ አዲስ አበባ እንዲያቀኑ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅና ዲማ ነገዎ ሚና ተጫውተው ነበር። በተለይም ፕሮፌሰሩ ኦስሎ በተደጋጋሚ በመምጣት ምክክር ማካሄዳቸውን እንደሚያውቁ የሚገልጹ ወገኖች፣ አቶ ሌንጮ እንዲህ ባጭር ጊዜ ዕቅዳቸው ከሽፎ ይመለሳሉ ብለውእንዳልገመቱ ይናገራሉ።
የጎልጉል የኦህዴድ ምንጭ “አረና እና ህወሃት መካከል ማንም ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ ኦዴግ እና ኦህዴድ መካከልም ይህ ሊከበር ይገባል” በሚል መቃወሚያ መቅረቡ ተናግረዋል። ምንጮቹ አያይዝውም እነ አቶ ሌንጮ በግል አቶ ስብሃትን ማግኘታቸውንና ከዛሬ አምስት አመት በኋላ በ2012 በሚካሄደው ምርጫ እንዲሳተፉ ድጋፍ እንደሚስጣቸው ማረጋገጫ እንዳገኙ አመልክተዋል። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የጀመረውን መንገድ እንደሚገፋበት ገልጾዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የኢህአዴግ አፈቀላጤ ሽመልስ ከማል፣ “አቶ ሌንጮና የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ እንደነበሩ አላውቅም ብለዋል” ሲል ሪፖርተር ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment