Saturday, March 21, 2015

ምርጫ ማላገጫ መሆኑ ማክተም ይኖርበታል። ምርጫ ያጣ ትውልድ!

SC
ብሶት ወለደኝ የሚለውና ጫካ መወለዱን የማይክደው ህወአት መራሹ የወያኔ መንግስት በምርጫ ተመርጬ ነው አገር የምመራው እያለ በከንቱ ሲመጻደቅ የአንድ ትውልድ ዕድሜ መቆጠሩ ነው። ህገ-መንግስቱ ባማሩ ቃላት ያሸበረቀ ጥራዝ ከመሆኑ ባሻገር ለህዝብ የፈየደው ጆሮ አደንቋሪነቱ ብቻ ነው። በተግባር የማይተርጎም ገዢዎች እንደፈልጉ የሚተረጉሙት ህገ -መንግስት የደብተራ ድግምት ከመሆን አይዘልም። ስልጣን የህዝብ መሆኑን ያላሳየ ስግብግብ ስርአት የነገሰባት አገር በትርጉም አልባ ምርጫ የአገርና የህዝብ ገንዘብና ጉልበት እንዲሁም የማይተካው ወርቃማ ጊዜ ለካድሬዎችና አለቆቻቸው ዕድሜ መቀጠያ እየሆነ የዕውር ድንብር መጓዙ ማክተም ይኖርበታል። አዲሱ ትውልድ የራሱን ዕድል ራሱ የሚወስንበት ጊዜ ዛሬ ነው።አሁን።
በፕሮፓጋንዳና በቁጥር ጋጋት ዳቦ መሆን ያልቻለ ዴሞክራሲና ነጻነት የትም አገር የለም። “ምርጫ” በህዝብ መልካም ፈቃድ በነጻ የውድድር ሜዳ ላይ በግልጽና ፍትሃዊ መንገድ ተከናውኖ ህዝብ የመረጠውን ለእንደራሴነት የሚሰይምበት መድረክ እንጂ ለአፈጮሌዎች ዕድሜ ልክ ስልጣን ላይ መደላደያ የአንድ ሰሞን የልጆች ሆያሆዬ መስል ባህላዊ ግርግር አይደለም። የመጻፍ፥የመናገር፥የመደራጀትና የሚፈልጉትን የፖለቲካ አስተሳሰብ በነጻነት ማራመድ ወንጀል በሆነባት የዛሬይቱ ኢትዮጲያ ምርጫ በትውልዱ ዕጣ ፈንታ ላይ መቀለጃ የብልጣብልጥ የፖለቲካ ቡድኖች የደራ ገበያ መሆኑ ማክተም ይኖርበታል።በህዝብና አገር መቀለድ የለበትም። አገሪቱ የሁላችንም አገር እንድትሆን ስር ነቀል ለውጥ የግድ ይላል። እስር ቤቶች ለአገራቸው ቅን በማሰባቸውና በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን በመግለጻቸው በተለይም ተጽፎ ባልተተርጎመው “ህገመንግስታዊ መብታቸው” በመጠቀማቸው ወንጀለኞች ተብለው በህግ ሽፋን መብታቸው ተገፎ የስቃይ ሰለባ ሆነዋል። የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በትውልዱ መልካም አስተሳሰብ ተቀርጾ ከኋላቀርና በታታኝ አመራር ተላቆ የአፍሪቃ ቀደምት ታሪካዊ ህዝብ መሆናችንን ለማደስ የሰቆቃ ስርአቱን ከጥፋት ግስጋሴው ልናስቆመው ግድ ይለናል። ስርአቱ የህዝብን ጥያቄ እስካልተቀበለ ድረስ ሊወገድ ይገባዋል። ባዶ የሚዲያ ዲስኩርና የአድገናል ከንቱ ቀረርቶ ቆሞ ትውልዱ ፍትህና ነጻነቱን አረጋግጦ ለሁሉም ኢትዮጲያዊ “የጋራ እናት የሆነች አገር “በነጻ አስተሳሰብ የምትመራ ህግ የሚከበርባት እውነተኛ አገር ወጣቱ እንዲመሰርት ማነቆውን መበጣጠስ ይገባል፡፡ ረሃብ፥ስደት፥ሰቆቃና ጭፍን ጥላቻ ተወግደው በመረጥናቸውና አመኔታ ስናጣባቸው በህዝባዊ ውሳኔ ልንተካቸው በምንችል የህዝብ ወኪሎች አገር እንድትመራ የነጻነት ጎዳናውን ለመጥረግ እጅ ለዕጅ ተያይዘን የምንጓዝበት ጊዜው ዛሬ ሳይሆን አሁን ነው። ያኔ ምርጫ በኢትዮጲያ ምድር ዘወትር በናፍቆት የምንጠብቀው የአለም ዋንጫችን ይሆናል። ወጣቱ ትውልድ ታሪክ ሰሪነቱን የሚያረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው።ከእንግዲህ ምርጫ ያጣ ትውልድ ሆነን መቀጥል አንችልም፡፡ ምርጫው በዕጃችን ነው።ህዝባዊ ንቅናቄ በማድረግ አማራጭ ያሳጡንን ሃይሎች በቃችሁ ልንል ጊዜው ግድ ይለናል።ተነሱ።እንነሳ።

No comments:

Post a Comment