ሰላም ወገኖቼ!! ተጠፋፋን። ግን አንለያይም። ድሮ የዘፈን ምርጫ ክፍለ ጊዜ ነበር። እሁድ እሁድ ወታደሮች ከደጀን፣ እናትና አባት፣ ቤተሰብ ከቤት ሆነው ይኮሞክሙት ነበር። አሁን ግን ለምን ተከለከለ? ባድመ፣ ሽራሮ፣ ዛላምበሳ፣ ገመሃሎ፣ ላከ ኤርትራም አሉ፤ ዘላበድኩ መሰለኝ … ብቻ የዘፈን ምርጫ ክፍለ ጊዜው ትዝ ብሎኝ ነው። ቀጭኑ ዘ-ቄራ ነኝ!!
“የለቅሶ ማስተላለፊያ የአየር ሰዓት/ክፍለ ጊዜ ቢጀመር ጥሩ ነው። ምርጫውን ያደምቀዋል” የሚል አስተያየት ሟርተኞች ያቀርባሉ። ግን ምን አለበት የከፋቸው ቢያለቅሱ። በየጓዳው እያለቀሱ ነው። አደባባይ ወጥተው ቢያለቅሱ ምን ነውር አለው? ለመለስ ደረት እየተመታ ሲለቀስ የአየር ሰዓት ተፈቅዶ የለ? ለሞተ ሰው ከተፈቀደ በህይወት ላለው፣ ግብር ለማያጓድለው ለምን ይከለካል? ወይስ ነዋሪው በሟች ተበልጧል?
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲባል የመለስ ለቅሶ በጊነስ ቡክ አለመመዝገቡ አያስገርምም። አማራ ደረት ሲደቃ፣ ደቡብ በዜማ ሲናባ፣ ትግሬ በለቅሶ ሲያዜም፣ ኦሮሞ እንባውን “ያ አባ ኮ” እያለ ሲያንዘቀዥቅ፣ ማን ቀረ? ሃይሌ ገ/ስላሴ ሲቃ ይዞት የእንባ “ቫት” ሲገብር … ድፍን አገር ሃዘን ሰብሮት፣ መሪው በድንገት እንደ ቡሽ ተስፈንጥረው ሲሄዱበት፣ ራዕያቸው ሲተንበት፣ ህልማቸው እንደ ጉም በድንገት ሲበተነበት፣ ጉሮሮው በድንገት ሲዘጋበት፣ ኑሮ ወደ ጎዳና ተዳዳሪነት ሲለወጥ፣ “የመጪው ጊዜ ብሩህነት” ሲደበዝዝ፣ እንዴት አያነባ? ጎበዝ ለመለሰ ዜናዊ ማን ያላነባ አለ?
መለስ አማረረን ብለው የተሰደዱ፣ በስደት ካምፕ የመለስን ፎቶ ሰቅለው ለቅሶ ተቀምጠዋል። ጠጅ ቤት፣ ጫት ቤት፣ … ምርጫ ሲመጣ ቀጭኑን ያመዋል። ምርጫ የግል ነው። የምርጫ ሰሞን ወሬ ለቃሚዎች ሲሳይ ይሆንላቸዋል። እገሌ ይህን አለ እያሉ በጀት ያስጨምራሉ። ወሬ ለመልቀም ይከንፋሉ። በየጫት ቤቱ ይራወጣሉ። ተናግሮ ማናገርና መልቀም። ጓደኞቻቸውን ማስበላት። አሳልፎ መስጠት። በህወሃት የባህር መዝገብ ማስመዝገብ።
አቶ መለስ አፈር አይክበዳቸውና (ለነገሩ አፈር ውስጥ አልገቡም) 99.6 በመቶ ምርጫን በማሸነፍ “ታሪክ መሰራቱን” ሲያበስሩ 96 በመቶ እንዲያሸንፉ ያደረጓቸው ወዳጆቻቸው ፊት ሰክረው ነበር። አራዳው መለስ በደስታ ቢሰክሩም መስታወት ቤት ውስጥ ሆነው መናገርን ግን አይረሱትም። ደስታ እየደቃቸው መስታዋት ቤት ውስጥ ሆነው “ኮራሁባችሁ” ሲሉ ከሲኤምሲ በ200 አውቶቡሶች ተጭነው መስቀል አደባባይ የደረሱ የኮብል ድንጋይ አንጣፊዎች አጨበጨቡ። በፉጨት አስተጋቡ። መለስ ደስታቸውን ሳያጣጥሙ ሾለኩ … ከመስታወት ቤት ወደ ግራውንድ ሲቀነስ ወረዱ። እዛ ወከባ የለም። ጭብጨባና ፉጨት የለም። ራዕይ፣ ቅዠት፣ “ሌጋሲ”፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ህዳሴ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ኒዎሊበራል፣ ምናምን የለም። የዘላለም እረፍት … ቀጭኑ እንባ ባይረጭም ሃዘን ገባው።
የዜናዊ ልጅ ምነው ሞትን ሞተው በነበር? ቀጭኑ ጠየቀ። ሞት ያለ ሳይመስላቸው እንዲሁ በትዕቢት ማማ ላይ እንዳሉ ኮበለሉ። ቢያንስ ህዝብ የመምረጥና የመሻር ወሳኝ ሃይል እንዳለው አይተውና አሳይተው ቢነጉዱ ኖሮ እስከዛሬ ባነባን ነበር – ለነገሩ አይተዋል ማሳየት አቃታቸው እንጂ። ቀጭኑ መለስን የሚወቅሰው በዚህ ነው። ነጻ ትውልድ እንዲፈጠር አድርገው ቢያልፉስ ምን ነበር? የሚገርመው አሁንም ትምህርት የሚወስድ የለም። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ኦቦ ሃይለማርያም ማለቴ ነው። ከ96 ወደ 100 በመቶ ለማሳደግና ሲሞቱ ደቡብ ሱዳን፣ ፑንትላንድ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ የዘለቀ ሃዘን እንዲታወጅላቸው የሚተጉ ይመስላሉ። ሃይሌ ዕዳቸው ብዙ ነው፤ ለነገሩ የአገር መሪዎች ባለብዙ ዕዳ ናቸው፤ የሃይሌ ግን የበዛ ይመስለኛል፤ የራዕዩ፣ የሕዳሴው፣ የውዳሴው፣ የሌጋሲው፣ … ኧረ ስንቱ?! ራዕያቸውን፣ ሌጋሲያቸውን፣ … ተግባራዊ እናደርጋለን፤ እያሉ ስለ መለስ እንደሚናገሩት አንድ ቀን “ሞታቸውንም ተግባራዊ እናደርገዋለን” ብለው ንግግር ቢያደርጉስ? ለነገሩ ምን ይተገበራል? ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ህያዋን የሆንን? ወደ ጉዳዬ ልመለስ …
“እኒህ ፖለቲከኞች ነፍስ የላቸውም እንዴ” ስትል ማይሟ እናቴ ሁሌም ትጠይቃለች። ደግ ስራ ሰርቶና ተወድዶ መሞት ለምን እንደማይወዱ አይገባትም። ለመለስ ለቅሶ አልሄደችም። ለዚህ ነው መሰል የቀበሌው ሊቀመንበር አሁን ድረስ ይገላምጣታል። በነገራችን ላይ ያንዱ ቀበሌ ሊቀመንበር ባልደረባዬ ነበር። የመለስን ለቅሶ ቀበሌ ድንኳን አስተክሎ ሲያከናውን ወደ ጓሮ እየጠራሁ ጫት አጎርሰው ነበር። ድንገት ስናወራ “ለመለስ ለቅሶ ከልብህ አላዘንክም፣ መልፈስፈስ አሳይተሃል፣ ቁርጠኝነት አይታይብህም፤ …” ተብሎ መገምገሙንና 40 ሳይደግስ መሰናበቱን ነግሮኛል። አይ ግም-ገማ!!
አሁን ማን ይሙት እነዚያ ጎንደር ላይ አበል ከፍለው ደሃውን ሲያላቅሱትና በግምገማ ደረት ሲያስመቷቸው የነበሩት ሴቶች መለስን ያውቋቸዋል? ጋምቤላ አኙዋክ ምድር ለመለስ የሚያነባ ሰው ይገኛል? ፊልም የሚሰራ ደፋር ጠፋ እንጂ ከዚህ በላይ ምን ፊልም አለ? ኤርትራ ቤተ መንግስት ውስጥ አንድ ክፍል በድብቅ ሃዘን ተካሂዶ ነበር ብሎ የፈተለ ሰው አጋጥሞኛል። የኤርትራ ባንዲራ ዝቅ ስለማለቱ ግን መረጃ የለውም። የስምዖን ልጅ ሲሽቀነጠር እናያዋለን።
ባገራችን ምርጫ ያለ ፈቃድ ማልቀስና ደረት መምታት ነው። ባገራችን ምርጫ የራስ ሳይሆን የሌሎችን ምርጫ ማጽደቅ ነው። ባገራችን ምርጫ የራስን መብት ለሌሎች በህጋዊ ሰነድ ስም ማስረከብ ነው። ምርጫ!! በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ምርጫ ብሎ ነገር የለም። አለመስማማት ተፈጥሯዊ ነው። አለመቀበልና አለመስማማት ግላዊ ነው። ልዩነት ያለ፣ የነበረ፣ የሚኖር እውነት ነው። ምርጫ በነዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ ውጪ ያለ የጫና ምርጫ የሰውን ልጅ አሻንጉሊት አድርጎ የማሳነስ ያህል ነው። የሰው ልጅ ክቡር ነው። ምርጫውን ያውቃል። ግን የእኛን አገር አይመለከትም።
ምርጫ በመጣ ቁጥር አየሩ ሁሉ ይከረፋል። ምርጫ በመጣ ቁጥር የህወሃትና ኢህአዴግ እብደት ይገንናል። እነሱ ሰማይና ምድሩን አፍነው የፈጣሪ ያህል የሆኑ ይመስላቸዋል። ቅጠሉና ዛፉ እንኳ አይታመንም። ወይ አንደኛውኑ ምርጫውን ቢዘጉት አይሻልም? ቀጭኑ ይህንን ሃሳብ ያቀርባል። ምርጫ የሚኖረው ምርጫና የመምርጥ መብት ሲከበር ነው። አስመራጩ ባንዳ፣ አስፈጻሚው ባንዳ፣ የበላዩ ባንዳ፣ የበታቹ ተላላኪ፣ መቃወም፣ መተንፈስ፣ ማስተማር፣ መናገር፣ መዝለፍ፣ ማጋለጥ፣ ነጻ ሚዲያ፣ ነጻ የመጫወቻ ሜዳ ሳይኖር ምርጫ? ይቀፍፋል። መቼ እንደምንሰለጥን አይታወቅም። ሁሉም ጋር ችግር አለ። የዜናዊ ልጅ ግን ናፍቀውኛል። መልካም ነገር አስተምረውን አለፉ፣ ተፈተለኩ፣ ተነቀሉ፣ ተደለቱ፣ አሁንም ለሳቸው ማልቀስ የሚፈልጉ አሉ። የማልቀሻ የአየር ሰዓት ይፈቀድ ብለው የሚጠይቁ አሉ። ለመለስ የለቅሶ ምርጫ ክፍለ ጊዜ ይመደብልን። ከየብሔሩ እያፈራረቅን መስማት የምንፈልግ ቧልተኞችም አለን። ቀጭኑ የምርጫ እድል ቢሰጠው “ያ አባ ኮ” በሚል የኦሮሞ አርሶ አደሮች ያነቡበትን ለቅሶ ቀዳሚ ክሊፕ አድርጎ ይመርጠዋል። ከዚያም “ሰለሜ ሰለሜ” የሚለውን በለቅሶኛ ያስከትላል። ቸር እንሰንብት!! ቀጭኑ ዘ-ቄራ!!
No comments:
Post a Comment