“የትግራይ ተወላጆች ታጥቀናል ሲለኝ – ደነገጥኩ” የሚል አስተያየት የሰጠው ኳስ አፍቃሪ ከጎልጉል የአዲስ አበባ ወኪል ጋር የተገናኘው አዲስ አበባ ስታዲየም ነበር። ጉዳዩ ለሚዲያ ግብዓት እንደሚውል ባይረዳም ገጠመኙን ለመናገር የተገደደው ስለ ምርጫ አንስተው ሲወያዩ ነው። ድንገት ተገናኝተው ቆሎ በመገባበዝ የጀመሩት ጨዋታ ዘጋቢውን ወደ 1997 ምርጫ ትዝታ ወረወረው። ተግባብተው አወጉና ተለያዩ። የትግራይ ተወላጆች ታጥቀናል!! ለምን? መርዝ ዘርቶ በጥይት ለማጨድ?
የስታዲየሙ ሰው የመኪና ማስጌጫ ለመግዛትና ለማስገጠም ሰባራ ባቡር እንደሄደ ይናገራል። እዛም እንደ ደረሰ የሚፈልገውን ገዝቶ እያስገጠመ ሳለ አንድ ጎረምሳ ቢጤ ይጠጋቸውና ወሬ ይጀምራል። ጎረምሳው የትግራይ ተወላጅ ነው። አንዳንድ ማስጌጫዎች የሚፈልግ ከሆነ እሱ ዘንድ በርካሽ እንደሚያገኝ እየነገረው ቃላት መለዋወጥ ጀመሩ። በዛው የተጀመረው ጨዋታ ስር እየሰደደ ሄደና ስለምርጫ ማውጋት ጀመሩ።
“ተቃዋሚዎች የትግራይ ህዝብን የመበቀል አጀንዳ እንጂ ሌላ ምንም ዓላማ የላቸውም። ያስጠሉኛል። ልማት አይወዱም። ከዚህ በላይ ምን እንዲደረግ ይፈልጋሉ? የትግራይ ህዝብ ነጻ አወጣቸው …” ወዘተ እንደ ሰውየው ገለጻ ጎረምሳው ብዙ ተናግሯል። በመሃሉ “አንተ ትፈራለህ እንዴ? እኔ ለምሳሌ ካንተ ጋር በፍቅር እያወራሁ ነው” ሲል ሰውየው በመካከል ጥያቄ አነሳበት። ጎረምሳው እየሳቀ ማብራሪያ ሲሰጥ ድንገት የ1997ቱን ምርጫ አነሳና ቤተሰቦቹና ታላላቅ የአገሩ ተወላጆች የነገሩትን አወሳ።
“ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ያልታጠቅነው ሁሉ ታጥቀናል” አለ። እሱ መሳሪያ እንዳለው ሰውየው ጠየቀው? “አዎ!! ምን ችግር አለው ጠይቀህ መውሰድ ትችላለህ” ሲል እንዴትና ከነማን መሳሪያ እንደሚወስድ ተናገረ። “መሳሪያው ምን ያደርግልሃል? ምን ልታደርግበት” ሰውየው እየሳቀ “አሁን እኔን ትገለኛለህ” ሲል ጠየቀው።
ጎረምሳው ብዙ ብዙ ተናገረ። ከተለያዩ በኋላ ሰውየው ድንጋጤ ውስጥ ስለወደቀ የሰማውን ለማሰላሰል አንድ ጥግ ይዞ ተቀመጠ። “ምን እየሆነ ነው?” ሲል አሰበ። የትግራይ ተወላጆችን ለይቶ ማስታጠቅ፣ ጠላት እንዳላቸው በስውር በማስተማር ማደራጀት፣ ከመደበኛ ስራቸው ውጪም ቢሆን ባልደረቦቻቸውን እንዲሰልሉና ተጠራጣሪ ሆነው እንዲኖሩ ማድረግ፣ በቀልን እያሰቡ ውለው በቀልን እያሰቡ እንዲተኙ ማድረግ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ ያሉት ሁሉ ቂምና በቀል እየጋቱ ሌሎች ህዝቦች ሁሉ የትግራይ ህዝብ ጠላትና ቀን ጠባቂ እንደሆኑ በመሳመን የጥይት ስንቅ ማስያዝ … ለምን? ለምን? እስከመቼ? እንዲህና እንዲያ እያሰበ ተምታቶበት እንደከረመ ለጎልጉል ዘጋቢው አወጋው።
በ1997 ቅድመ ምርጫ የመጨረሻ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት የቅንጅት ሱናሚ አዲስ አበባን የዋጣት ዕለት፣ ሱናሚው አዲስ አበባን አጥለቅልቆ ኢህአዴግን በተለይም ህወሃትን ጣር ውስጥ በከተተበት ወቅት ምንም ነገር ማድረግ ይቻል ነበር። ቤተ መንግስት ገብቶ ሁሉንም የጨዋታ ህጎች መደፍጠጥ ይቻል ነበር። የጎጥም ይሁን የጎሳ ችግር የበቀል አራራ ቢኖር ኖሮ ከዚያን ጊዜ በላይ አመቺ ወቅት አልነበረም። ባድሜ ስትወረር የተመመው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ደጀን የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዩ የትግራይና የተወላጆቿ ነው ብሎ አልተቀመጠም። ፈንጂ ላይ እየሮጠ፣ ፈንጂ ላይ “እናት አገር ወይም ሞት” በማለት እየደነሰ ያለቀው ይህ ትውልድ በእውነት ቂመኛ ነው? የዘጋቢው ጥያቄ ነው!!
በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግ ላይ ቢያቄምስ ይፈረድበታል? ይኮነናል? ሃጢአት ተደርጎ ይወሰድበታል? በሰላም ከሚኖርበት ቀዬ የሚፈናቀል ህዝብ ቢያቄም ኩነኔ ነው? “ከክልላችን ውጣ” ተብሎ ደብዳቤ የተጻፈለት የ1ኛ ክፍል ተማሪ ቂም አርግዞ ቂምን ቢገላገላት ይወቀሳል? በዘሩ ምክንያት በደል የሚፈጸምነት ህዝብ ግፍ በዝቶበት “ቢያስታውከው” በተነፈሱ ቁጥር “አሸባሪ” እየተባሉ እስር ቤት የሚጣሉ ወገኖች በቂም ቢመረቅዙ እንዴት “ተው” ይባላሉ? የአገሪቱን ሃብት ውስን ሰዎችና ድርጅታቸው ሲቀራመቱት በገሃድ እየታየ ሰዎች እልህ ቢጋቡ፣ ጸሎት/ዱዓ ለማድረግና ቤተ እምነትን በነጻነት ማቆም ሲከለከል ዝም ማለት ይቻላል? ጥቂቶች ህንጻ እየገነቡ ሲንፈላሰሱ ቀልባቸው የሚቆጣባቸውን “ልክ አይደላችሁም” ማለት ማን ይቻለዋል? … ዘጋቢውና ሰውየው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም “የወያኔ የጥላቻ ፍሬ” በሚል ርዕስ የዛሬ ዓመት አካባቢ ባወጡት ጽሁፍ ላይ እንደጠቆሙት ግፍ ማብቂያ አለው፡- “ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ ጥላቻ ወደ ንዴት፣ ንዴት ወደ ቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደ አውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።”
ስለዚህ አካሄድን በማሳመርና ሚዛን የጠበቀ አስተዳደር በማስፈን አገዛዝን ወደ ህዝባዊ መንግሥት በመቀየር ወግ ነው። ተስማምቶ መኖር እየተቻለ ወገን እየለዩ ማስታጠቅና ባምስትና በአስር ሰዎች የተመደበ የቀድሞ መከላከል፣ የቀድሞ ማጥቃት፣ ካልተቻለም የሚቻለውን አድርጎ የሚሆነውን ማየት በሚል እሳቤ መንጎድ የትኛውንም ወገን እንደማይጠቅም መረዳት ግድ ይላል። በተለያዩ ወቅቶች አስተያየት የሰጡ እንደሚሉት ህወሃት እንዲህ ካለው አጉል አካሄድ ራሱን በማረቅ ብቸኛ አማራጭ ወደ ሆነው እርቅ ፊቱን እንዲያዞር የሚመለከታቸው ሁሉ ሊያሳስቡት ይገባል።
ኢህአዴግ ዙሪያ ያሉ ድቃይ ድርጅቶችም በዚህ ጉዳይ ላይ በወጉ ሊመክሩና ከወዲሁ የሚበጀውን መንገድ በመከተል ቂምና ምሱን ለማክሰም መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ብዙዎች ይመክራሉ። ለህሊና ዋጋ በመስጠት የመርዝ እርሻን ማክሰም የጊዜው የከረመ ጥያቄ ነውና ሁሉም ልብ ሊሉት እንደሚገባ በተደጋጋሚ መዘገቡም አይዘነጋም። መርዝ እየዘሩ በጥይት አጭዶ ለመከመር መደራጀት ሌላውን ከሚያስፈራው ይልቅ የበደሉንና የቂሙን ቁስል ይበልጥ የሚያመረቅዝ ይሆናልና ህወሃት ልብ ሊገዛ እንደሚገባ የሚመክሩ ጥቂት አይደሉም። ህወሃት “ንፋስ ዘርቶ አውሎ ነፋስ አላጭድም” ማለት አይችልም – ቀን ጎዶሎ ነውና!!
No comments:
Post a Comment