ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ምንስ እየሠራ ነው? የተዛባ አመለካከት የማይጋርደው ገሐድ እውነታ
ከማህበሩ ድረ-ገፅ የተወሰደ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ብራና ዳምጠው፤ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርጸው በየአብያተ ክርስቲያናቱ የመቃብር ቤቶች ውስጥ በማስተማር ትውልዱ የሀገር መሪ፣ የቤተክርስቲያን አለኝታ፣ የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ እንዲሆን ያበረከቱት አገልግሎት ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ ለትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔ በር ከፋች ሆና የኖረች ከመሆኗም በላይ ዛሬ ላለው ዘመናዊ ሥልጣኔም መሠረት የጣለች ባለውለታ ናት፡፡ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ኖረው ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ከምትገኝበት የዕድገት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡
በዚህ ዘመንም የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ይህን ከአበው የተማሩትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀውና አስጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ የማቆየት ሓላፊነት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በመሆኑም ይሔንን አባቶች ወዛቸውን አንጠፍጥፈው፣ ዐይናቸውን አፍዘው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በሰማዕትነትና በተጋድሎ ያቆዩትን ሃይማኖት ለማስጠበቅና ለቀጣዩም ትውልድ በተመቻቸ ሁኔታ ለማስተላለፍ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድጋፍና ዕውቅና የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን በውጪ በአጽራረ ቤተክርስቲያንና በአሕዛብ፣ በውስጥ ዓላማውን ባልተረዱ፣ ዓላማውን ተረድተው የኑፋቄ ትምህርታቸውን እንደልብ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለማስረግ ሌት ተቀን በሚተጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰሰ እየተወቀሰና ያለ ስሙ ስም እየተሰጠው ይገኛል፡፡
እነዚህ በውስጥና በውጭ የሚገኙት የቤተክርስቲያን ጠላቶች ቤተክርስቲያን ላይ በየዘመኑ በሚነሳው ፈተና እየተጠቀሙና በምክንያት እየተሳቡ ለቤተክርስቲያን ወዳጅ መስለው እየቀረቡና እያስቀረቡ ማኅበረ ቅዱሳንን ቢቻላቸው እንዲፈርስ፣ ባይቻላቸው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማፍረስ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ የሚያስታጥቋቸው መናፍቃን ሴራና ዓላማ እንዳይጋለጥ እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ ማኅበሩ አገልግሎቱ ተገድቦ እንዲዋቀር ለማስደረግና ለማድረግ የጥፋት ዘመቻዎችን በመክፈት ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላት ወዳጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጊዜ በሰጣቸው ጊዜ ሁሉ በመጠቀም ማኅበሩን ለማሳጣትና ለማጥላላት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በርካቶች ናቸው፡፡
ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል «ማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ ከሰጠው ደንብና መመሪያ ውጪ እየሠራ የሚገኝ፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ገቢና ወጪው የማይታወቅ ማኅብረ» እንደሆነ አድርገው» ሚያናፍሱት አሉባልታ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ግን ባለፉት 17 ዓመታት እነዚህ የውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ጠላቶች በየጊዜው ማኅበሩ ላይ የሚያናፍሱትን ወሬ ችላ በማለት ከወሬ ሥራ ይቀድማል በማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበለውን ዓላማ በዓይን በሚታይ፣ በእጅ በሚዳሰስ መልኩ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን «ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል» እንዲሉ ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድን ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ሓላፊነት እንዴት እየተወጣ ነው? ለ17 ዓመታትስ ምን ሠራ? የሚሉትን ጥያቄዎት በስፋት ማቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን ለምእመናን መግለጽ ግድ ብሎናል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አጽራረ ቤተክርስቲያንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱት ተላላኪዎቻቸው የውስጥ ዐርበኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በሰው ውስጥ የጥላቻ መንፈስ እንዲያድር ከሚጣጣሩበት መንገድ አንዱ ማኅበሩ የሚጠራበትን ስያሜውን በማዛባት ነው የሚጀምሩት፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ነገር ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስያሜው ላይ አጭር ትንታኔ በመስጠት ወደ ማንነቱና አመሠራረቱ እንለፍ፡፡
የማኅበሩ ስያሜ
አንዳንድ ሰዎች ስያሜውም ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው አባላቱ ለራሳቸው ያወጡት አስመስለው የሚነግሯቸው ሰዎች አሉና የዋሀኑ ግራ ቢጋቡ አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ ስያሜ እኩያኑ ማኅበሩን ለማጥላላት ከሚጠቀሙት ፕሮጋንዳ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ማኅበረ ሚካኤል «የሚካኤሎች ስብስብ»፣ ማኅበረ ማርያምም «የማርያሞች ስብስብ» ካልሆነ /እንዳልሆነ/ ማኅበረ ቅዱሳንም «የቅዱሳን ሰብስብ» አይደለም፣ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ማኅበረ ጊዮርጊስን የመሠረቱ ሰዎች ራሳቸውን «ጊዮርጊሶች»ነን እንደማይሉት፤ እንዳልሆኑትም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱሳን ነን የሚሉ ሰዎች ስብስብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኅበረ ማካኤል የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት፣ ተራዳኢነት የሚታሰብበት ማኅበር እንደሆነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐት ከመጠበቅና ከማስተማር በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት ክብ ራቸው፤ ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ አማላጅነታቸውና በረከታቸው፤ በሰፊው እንዲታወቅና ትውልዱም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ትምህርት የሚሰጡበት ማኅበር ነው፡፡ ምእመናን በነዚህ ቅዱሳን አማላጅነትና ረድኤት እየታገዙ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግም ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
ከዚህ የተነሣ የእነዚያ ብዙ ማኅበራት ኅብረት የሆነው ማኅበር የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታትና የቅዱሳን መላእከት ሁሉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ተባለ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴትስ ተመሠረተ?
ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር 1977 ዓ.ም፡፡
በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ /ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች/ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መሰማት የማይታሰብበት ወቅት ነው፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ከቤተክርስቲያን የራቀበት ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ አምስት ወጣቶች ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በቅዱስ ገብርኤል ስም ተሰባስበው ጽዋ መጠጣት የጀመሩት፡፡ ይህ መንፈሳዊ እንቅስቀሴ በዚሁ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በየሳምንቱ እሑድ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ በመጠለያ ሥር እየተሰባሰቡ በተደራጀ መልክ ባይሆንም መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩ ጀመር፡፡ ከዚያም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት መማር ቀጠሉ፡፡
እንዲህ የተጀመረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የቤተክርስቲያን ልጆች ዘንድ የተዳረሰበት አጋጣሚና ሁኔታ የተፈጠረው ደግሞ በዚሁ በ1977 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ በነበረው የመንግሥት ሠፈራ ፕሮግራም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሙሉ በመንደር ምሥረታና መልሶ ማቋቋም ዘመቻ ወደ ጋምቤላ፣ መተከል እና ፓዌ እንዲዘምቱ ተደረገ፡፡ በዘመቻው ወቅት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየመጡ የተገናኙት የቤተክርስቲያን ልጆች ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ በማኅበር ጸሎት በማድረግ እና ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ በመወያየት ጊዜውን ተጠቀሙበት፡፡
በዚህ ዓይነት የተጀመረው እንቅስቃሴ ከዘመቻው መልስ በ1978 ዓ.ም ተጠናከረ፡፡ ውስን የነበረው የተማሪዎች ቁጥርም ጨመረ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ግቢዎች እስከ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎች በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ማኅበር አዳራሽ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል ይማሩ ነበር፡፡ የተማሪዎቹን ዓላማና ጥረት የተገነዘቡ አባቶች መምህራነ ወንጌልም በቅርብ ሆነው እየተከታተሉ ሲያስተምሯቸው ቆይተዋል፡፡
በቀጣዩ ዓመት ከ1979 ዓ.ም እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ ተማሪዎቹ በተምሮ ማስተማር ማኅበር አደራሽ ከሚከታተሉት መንፈሳዊ ትምህርት መርሐ ግብር ጋር ይህ መንፈሳዊ እን ቅስቃሴ ተጠናክሮ በስፋት የሚቀጥልበትን መንገድ ይወያዩ ነበር፡፡ በወቅቱ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ይደረግበት የነበረው ዐቢይ ጉዳይ ከመካከላቸው ሰባኪ ወንጌል ማፍራት ነበር፡፡ ለዚህም በተለይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት በቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተሳተፉ በሰንበት ትምህርት ቤት ያደጉና በመጠኑም ቢሆን ልምድ ያላቸውን ተማሪዎች እንዲያስተምሩ ማድረግ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ለዘለቄታው ግን ከተማሪዎቹ መካከል በወቅቱ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ገብተው እንዲሠለጥኑ ማድረግ የታመነበት መሠረታዊ ጉዳይ ሆነ፡፡
ይህንኑ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ፤ አስቀድመው በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ስለስብከተ ወንጌል ሥልጠና የወሰዱ፤ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና የካህናት ማሠልጠኛው የበላይ ጠባቂ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር ይቀራረቡ በነበሩ ተማሪዎች አማካኝነት ግንኙነት ተደረገ፡፡
እንዲሁም በ1980 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ ትምህርታቸውን ሊከታተሉ ከገቡት መካከል እስከ ሃምሣ የሚደርሱ ተማሪዎች በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብር ኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ተሰብስበው ይማሩ ጀመር፡፡ በዚሁ ዓመት በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎችም ተመሳሳይ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ጀምረው ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ1980 ዓ.ም ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ በግቢ ቆይታቸው በቤተክርስቲያን ተሰባስበው መንፈሳዊ ትምህርት ሲማሩ የነበሩት የቤተክርስቲያን ልጆችም ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረቁ፡፡ የምረቃው መርሐ ግብር የተካኼደው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ማኅበር አዳራሽ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮሰ ካልዕ ጋር ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተው፤ ተመራቂዎቹ ተማሪዎች ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዲተጉ አስተምረው ባርከው መርቀዋል፡፡
ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር በተደረገው ግንኙነት መሠረት በዚሁ ዓመት ከተመረቁት መካከል ዐሥራ ሁለት ተመራቂ የቤተክርስቲያን ልጆች በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በክረምቱ ወራት፤ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ትውፊት እንዲሁም የስብከት ዘዴ ሲማሩ ከረሙ፡፡ ሥልጠናውን የተከታተሉት ተማሪዎች ተመርቀው ከገዳሙ ሲሔዱ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎር ዮሰ ካልዕ፤ «ከዚህ ስትወጡ ተበትናችሁ እንዳትቀሩ አደራ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችሁ እየተገናኛችሁ መወያያ ይሆናችሁ ዘንድ መሰባሰቢያ አብጁ» በማለት፤ ተመራቂዎቹ በጽዋ ማኅበር ስም በመሰባሰብ፣ በሚሔዱበት ቦታ ሁሉ ስብከተ ወንጌልን እንዲያስፋፉ፣ በየዓመቱም በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየተገናኙ ስለ ዓመቱ የአገልግሎት ቆይታቸው ሪፖርት እንዲያቀርቡና እንዲወያዩ አሳስበው አሰናበቷቸው፡፡
ተመራቂዎቹ የቤተክርስቲያን ልጆች የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕን አባታዊ ምክርና መመሪያ አልዘነጉም፡፡ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ «ማኅበረ ማርያም» በሚል ስያሜ የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያው በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓውደ ምሕረትና ሌሎች መርሐ ግብሮች ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማሩ በየወሩ እየተገናኙ ስለአገልግሎታቸው ይወያዩ ነበር፡፡ በዓመቱ መጨረሻም በዝዋይ ተገኝተው ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በ1981 ዓ.ም ክረምት ለሁለተኛ ዙር ሥልጠና በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በግቢ ገብርኤል ዓምደ ሃይማኖት አዳራሾች ይማሩ ከነበሩት መካከል ዐሥራ ሁለት ተማሪዎች ተወክለው በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አማካኝነት ሥልጠና ተሰጠቷቸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች መንፈ ሳዊ እንቅስቃሴው እየተጠናከረ ቀጥሎ በተለይም በ1982 ዓ.ም በብዙ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተዳረሰ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ፋኩልቲዎች፤ በጥቁር አንበሳ ሕክምና ፋኩልቲ፣ በልደታ ሕንፃ ኮሌጅ፣ በደ ብረ ዘይት እንስሳት ሕክምና ፋኩልቲ እንዲሁም በጅማ ጤና ሳይንስ፣ በዓለ ማያ ዩኒቨርሲቲ፣ በወቅቱ በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ወዘተ ተስፋፋ፡፡ በዓመቱ የክረምት ወራት ከየዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆቹ የተውጣጡ አርባ አምስት ተማሪዎች ዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በሥል ጠናው በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ከሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ ሥልጠና ወቅት ነበር ባልታሰበ ሁኔታ ታላቅ ኃዘን የደረሰው፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎር ዮስ ካልዕ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ነዐረፉ፡፡
በ1983 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው መንግሥት በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ሲታዘዝ፤ በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጆችና ተቋማት የሚማሩ አሥራ አንድ ሺሕ ያህል ተማሪዎች በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቹ ግቢዎች ተጀምሮ ቀስ በቀስ የተስፋፋው መንፈሳዊ እንቅስቃሴም የበለጠ የሰፋበትና የተጠናከረበት ጊዜ ሆነ፡፡ ተማሪዎቹ ቀን ከሚሰጣቸው ወታደራዊ ሥልጠና መልስ ማታ ማታ እየተገናኙ መንፈሳዊ ትምህርት መማር በጋራ መጸለይ ጀመሩ፡፡ መንፈሳዊ ትምህርቱና ጸሎቱ በኅብረት የሚካኼደው በወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፑ በሚገኝ በሌላ አገልግሎት ያልተያዘ አዳራሽ /ኬስፖን/ ውስጥ ነበር፡፡ ትም ህርቱ ከዚህ ቀደም በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በሠለጠኑ እና ሌሎችም በቤተክርስቲያን ትምህርትና አገልግሎት በቆዩ ተማሪዎች እየተሰጠ በየቀኑ ምሽት መርሐ ግብሩ ሳይታጎል ለሁለት ወራት ቀጥሏል፡፡ በዚህ ጉባኤ እስከ አምስት መቶ የሚደርሱ ተማሪዎች ያለማቋረጥ ይከታተሉ ነበር፡፡
በወቅቱ በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ ካምፕ ለወታደራዊ ሥልጠና የገቡት ተማሪዎች ማታ ማታ እየተ ሰበሰቡ በአንድነት ከሚያደርጉት ጸሎት እና ከሚማሩት የቤተክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ፤ በአካባቢው ወደሚገኘው ብላቴ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እየተደበቁም እያስፈቀዱም በመሔድ ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን ይሳተፉ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰባሰቡት ተማሪዎች ኅብ ረት እየጠነከረ መንፈሳዊ እንቅስቃሴው እየሰፋ መጣ፡፡ እነዚህ የቤተክርስቲያን ልጆች በወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ በነበሩበት ጊዜ የ1983 ዓ.ም የእመቤታችንን የልደት በዓል /ግንቦት ልደታ/ ለጸሎትና ለመንፈሳዊው ትምህርት በሚሰበሰቡበት አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል፡፡
በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ ካምፕ የነበረው የተማሪዎቹ ወታደራዊ ሥልጠና የሁለት ወር ቆይታ በመን ግሥት ለውጥ ምክንያት ሊበተን ግድ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ በወታደራዊ ካምፑ ቆይታቸው የነበረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴና ኅብረታቸው ዕጣ ፈንታ አሳሰባቸው፡፡ ይህ መንፈሳዊ አንድነት እንዴት መቀጠል እንዳለበት ተነጋገሩ፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላም ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በየዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቻቸው ሲመለሱ በቅዱስ ሚካኤል ስም ተሰባስበው ቤተክርስቲያንን ለማገልገል በመስማማት ቃል ገብተው ተለያዩ፡፡
በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዕረፍት ዓመታዊ መታሰቢያ ላይ የተገኙ ደቀመዛሙርትና መምህራን ነሐምሌ 22 ቀን 1983 ዓ.ም፤ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ የገዳሙና የካህናት ማሠልጠኛው የበላይ ጠባቂ በነበሩበት በብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት ጉባኤ ተደርጎ ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ «በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተምራችሁ በማኅበረ ማርያም የታቀፋችሁ፣ በየቦታው ያላችሁ፣ በገዳሙም የምትኖሩ መነኮሳት እንዳትበታተኑ በአባታችን ስም ማኅበር አቋቁሙ» በማለት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሐሳብ አቀረቡ፡፡ በሐሳቡ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለጊዜው «የዝዋይ ደቀመዛሙርትና መምህራን ማኅበር» በሚል ስያሜ እንዲጠራ ተወስኖ ማኅበር ተመሠረተ፡፡
ከዚህ ቀደም በ1981 ዓ.ም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም በተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ጉባኤ አንድነት በመፍጠር የተጠናከረ እንቅስቃሴ ባያደርግም «ማኅበረ እስጢፋኖስ» የሚባል ማኅበር መሥርተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን እንቅስቃሴአቸው የተጠናከረ ባይሆንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋኩልቲ ተማሪዎች «ማኅበረ ሥላሴ» በሚል ስያሜ፤ በሌሎችም ፋኩልቲዎችና ኮሌጆች ግቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በተለያዩ ቅዱሳን ስም በሰየሟቸው ጽዋ ማኅበራት ተሰባስበው ነበር፡፡
በጥር ወር 1984 ዓ.ም በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው «ማኅበረ ሚካኤል» የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ አመራሩንም መርጧል፡፡ ሆኖም በቅዱሳኑ ስም ማኅበር መሥርተው የተሰባሰቡት አባላት፤ «ዓላማቸው፣ አገልግሎታቸውም ሆነ ታሪካቸው አንድ ነው፡፡ ለምን አንድ ስያሜ ይዘው በአንድነት አይንቀሳቀሱም?» የሚል ሐሳብ በውስጣቸው እየተነሣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጉዳዩ ሲወያዩበት ቆይቷል፡፡
በዝዋይ ለተመሠረተው ማኅበር ስያሜ ለመስጠት አዲስ አበባ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቤት በዚሁ ዓመት በየካቲትና መጋቢት ወራት በተካኼደው ስብሰባ ላይ ሐሳቡ ቀርቦ ውይይት ተደረገበት፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል «ሁላችሁም የያዛችሁት አገልግሎት የቅዱሳን ክብር የሚገለጽበት ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበራችሁም ስም ‘ማኅበረ ቅዱሳን’ ይባል፡፡» በማለት ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ የ«ማኅበረ ማርያም»፣ «ማኅበረ ሚካኤል» እና «የዝዋይ ደቀመዛሙርትና መምህራን ማኅበር» ተዋሕደው የሁሉም ማኅበራት የጋራ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ተመሠረተ፡፡
አባላቱም መንፈሳዊ አገልግሎታቸው የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና መዋቅር ጠብቆ በቤተክርስቲያን አስተዳደር ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት አምነው፤ «በጠቅላይ ቤትክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆነን እናገልግል» በማለት መተዳደሪያ ደንባቸውን ይዘው ወደ መምሪያው ጽ/ቤት ቀረቡ፡፡ በዚህ ዓይነት ማኅበረ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተክርስቲያኒቷ መዋቅር ዕውቅና አግኝቶ ግንቦት 2 ቀን 1982 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር መደራጀቱ ይፋ ሆነ፡፡
ምንጭ:
No comments:
Post a Comment