ከመልካም-ሰላም ሞላ
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ከ12 አመት በላይ የሰራ ወጣት ጋዜጠኛ “ነበር”፡፡ በነሃሴ ወር ውስጥ በመንግስት ወከባ ህይወቱን ከእስር ለማትረፍ ተሰዶ ወደሀገሩ በሳጥን ለመመለስ እየጠበቀ ያለ ወጣት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ…ሚሊዮን፡፡ ተስፋ የነበረው ስደተኛ ጋዜጠኛ የመልካም ባህሪ እና ስብእና ባለቤት የነበረው ሚሊዮን፣ ስለሀገሩ ፍቅር ብዙ መሰናክሎችን ሊጋፈጥ ስደትን መርጦ ባሰበበት ሳይሆን በታሰበለት ሊኖር የተገደደው ሚሊ እንደወጣ በሰው ሀገር ልጄን እህቶቼን ቤተሰቦቼን ሃገሬን እንዳለ በድንገት ታሞ እንደፈራው ላይመለስ አሸለበ፡፡
ከሚሊ ጋር ላለፉት ሶስት ሳምንት አብረን ኖረናል፡፡ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ እንደመጣ ከጓደኛው መላኩ ጋር ከኖረው እና ሆስፒታል እስከገባበት የመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት፤ የተረፉትን ሶስት ሳምንታት አብረን ነበር፡፡ እኔ ባሴ እና ሚሊ በጠባቧ ክፍላችን ያለፉትን ሶስት ሳምንታት ተጋርተን ነበር፡፡
ሚሊ ከሃገሩ ከወጣ በኋላ ወደ ሃገሩ በድጋሚ እንደማይመለስ ሲያውቀው አንድም ቀን ከጭንቀት ወጥቶ አያውቅም ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ “ከሃገሬ ስወጣ ሰማዩን አይቼ አለቀስኩ ካሁን በኋላ ሃገሬን አላይም” ብሎ ከመጨነቀን እና ከመተከዝ ያረፈበትን ጊዜ አላስታውሰውም፡፡ የህመም ስሜት እየተሰማው እንደሆነ ሲነግረን ስለምትጨነቅ ነው ነገሮችን አምነህ መቀበል አለብህ እያልን እናጽናናው ነበር፤ ቅሉ ሚሊ በድጋሚ እስከመጨረሻው ለሃገሩ እንደማይበቃ ያወቀው ይመስል የሃገሩን ሰማይ እያየ እንዳለቀሰ እያለቀስን በሳጥን ልንሸኝው እየተዘጋጀን ነው ….
ሚሊ ከመስቀል በዓል ጀምሮ የጤንነት ስሜት እየተሰማው አልነበረም፡፡ ራሱን በጣም ያመው ነበር፡፡ ስለ ልጁ ስለእህቶቹ ስለቤተሰቦቹ በጣም ይጨነቅ ስለነበር ሀገሩ አለመግባቱን ናፍቆቱን እያሰበ እንባ ይተናነቀው ስለነበር የህመሙን ምክንያት ጭንቀት ነው ስለዚህ አትጨነቅ እያልን ልናረጋጋው ብዙ ሞክረን ነበር፡፡ በኋላ ላይ በምንኖርበት አቅራቢያ ወደሚገኝ ክሊኒክ ወሰድነው፡፡ ታይፎይድ እንደታመመ እና ምን አልባት ለሃገሩ አዲስ ስለሆነ የምግብ አለመስማማት እንደሚሆን ገልጾልን ግሉኮስ ወስዶ መድሃኒት ተሰጥቶት ወደቤት ተመለሰ፡፡ ሃሙስ ቀን ንጋት11 ሰዓት ተንስቶ በጣም ራሱን እየታመመ እንደሆነ እየገለጸ “ወይኔ በስደት ልሞት” እያለ ሲያለቅስ በድንጋጤ እኔ እና ባሴ ተነስተን መጀመሪያ ወደወስድነው ክሊኒክ ወሰድነው፡፡ ዝግ ነበር፡፡ ከዛ የተሻለ ህክምና ያገኝበታል ብለን ወደአሰብነው ሆስፒታል ወሰድነው፡፡ ሶስት አይነት ምርመራ ካደረጉለት በኋላ መድሃኒት አዘውለት ወደቤት ተመለስን፡፡ ሚሊ የጤናው ሁኔታ እየተሻሻለ ነበር፡፡ ግን የምግብ ፍላጎቱ አነስተኛ ስለነበር አቅም እያነሰው ነበር፡፡ መዳህኒቱን እየወሰደም በቅርባችን ባለ ክሊኒክ ግሉኮስ ይወስድ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ አቅሙ እየተዳከመ መጣ፡፡ የመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት ግን ፍጥነቱን ያልገመትነው እና ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ፡፡
ሆስፒታል ከመግባቱ ሁለት ቀን በፊት ጓደኛው መላኩ ቤት ሄዶ ህክምናውን እየተከታተለ ነበር፡፡ ቅዳሜ ጤንነቱ መሻሻሉን አይቼ ደስ ብሎኝ ነበር ወደቤት የገባሁ፡፡ የዛን ቀን ምግብ ስለማይበላ ግሉኮስ ለመውሰድ እንደሚፈልግ ነግሮን ከባሳዝነው ወንድምነህ (ባሴ) ጋር ወደ ክሊኒክ ሄዱ፡፡ ማታ ላይ ሚሊ በጣም ደክሞ ነበር፡፡ ህመሙ በፍጥነት እየተባባሰ መጣ፡፡
የመጨረሻዎቹን ሁለት ቀናት ሚሊ ራሱን አያውቅም ነበር፡፡ ሆስፒታል ተኝቶ መታከም ቢጀምርም ሚሊ ራሱን እንደሳተ ሳይሰናበተን “ሀገሬን አላይም ዳግመኛ እንዳለ” አሸለበ፡፡ ሚሊዬ አንተ ራስህን አታውቅም እንጂ በመጨረሻዎቹ የጭንቅህ ቀናት በምን ያህል ጋዜጠኛ ተከበህ፤ ምን ያህል ሰው አብሮህ እንደነበር ብታየው እንዴት ጥሩ ነበር፡፡
ፍርሃታችን እውን ይሆናል ብለን አልጠበቅንም፡፡ ፈጣሪ በስደት ይጠብቀናል እግዚአብሔር አለን ብለን አስበን ክፉን ከኛ ያርቀዋል ብለን ሁላችንም ተመኝተን ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ሚሊዬ ሃገሬ ናፈቀኝ ልጄ እህቴ ጓደኞቼ…ከእንግዲህ አላያቸውም እኮ እንዳለ ከሃገሩ ከወጣ ከአንድ ወር ከ10 ቀን በኋላ ህይወቱ አለፈ፡፡ መጨረሻ በኦክስጅን በሚተነፍስበት ሰአት እግዚአብሔር እንዲያድነው አልቅሰንለት ነበር፤ ራሴን ያመኛል ምግብ መብላት አልቻኩም ብሎ በተጨነቀበት ሰዓት እግዚአብሄርን ለምነን ነበር…. ሚሊየ “ወይኔ ከሀገሬ እንደወጣሁ ልሞት” ብለህ እንደፈራህ እውን ሆኖ ተለየኸን፡ ምን ማድረግ እና ለማን መደወል እንዳለብን ማወቅ ሳንችል በሰው ሀገር እንደልባችን ማልቀስ ሳንችል ወደየትኛው ቤታችን አስክሬንህን ይዘን መሄድ እንዳለብን ግራ ገብቶን መሃል ሆስፒታል የሰው ያለህ ብለን ብንጮህም ሰሚ አጥተን…ሀገር ማለት ፣..ሰው ማለት ….ስደት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንተን ውድ ጓደኛችን አልፈህ …ምን ማድረግ ለማን መናገር እንዳለብን ግራ ገብቶን ሁላችንም ከአስክሬንህ ጎን አለን ….፡፡ከተሳካልን በክብር ለሀገርህ አፈር እናበቃሃለን፡፡ ሚሊ እስከመጨረሻው ሰዓት ይሄ ይመጣልን ብለን አልበቅንም፡፡ ግን በፈጣሪ ስራ መግባት አንችልም፡፡ ቤተሰቦችህ ምን ይሉ እህት እንዴት ትችዋለች.. ለልጅህ እንዴት ይነግሯት ይሆን…ለጓደኞችህ እንዴት ብለን….
ጋዜጠኛው ስደተኛው ሚሊ ቁመህ ወጥተህ በሳጥን አሽገን እንዴት እንደምንልክህ ዛሬም በሰው ሃገር ሰው በሞላበት የሰው ያለህ እያልን ነው፡፡ ሚሊ ፈጣሪ ነፍስህን በገነት እንደሚያኖራት አምናለሁ፡፡ በሞትህ መጨረሻ ቀናት በድካም 1 ቀን በፊት መድሃኒያም ቤተክርስቲያን ሄደህ ጸበል ተጠምቀህ ንስሃ ገብተህ በብጹህ አባታችን ቅባ ቅዱስ ተደርጎልህ ነበር፤ “ይቅር ላላችኋቸው ይቅር እላቸዋለሁ” ይላልና መጽኀፉ ፤ ፈጣሪ በሰማይ በመልካም ቦታ እንደሚያኖርህ አምናለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን ሆነን የጸለይከውን ድህነት በሰማይ እንደሚከፍልህ አመንኩ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ስትወጣ የነበረህን ተስፋ ፈጣሪ በሰማይ ቤት እንደሚሰጥህ አመንኩ፡፡ ከቤተክርስቲያን ከህመም እንዲያሳርፍህ የጸለይከውን ጸሎት በሰማይ በሰላም ያሳርፍ ዘንድ አመንኩ፡፡
እሽ ሌላ ምን ልበል ..ሚሊ የሃገርህ ሰማይ እንደናፈቀህ ሀገሬን እንዳልክ ነገን በተስፋ እንዳየህ ላይሳካ መኖር ሳትጀምር መንገድ አጭር ሆኖ በዚህ ተቋጨ፡፡ የመኖርህን የመጨረሻ ቀናት በስደት ሞት…በስደት ሞት… ከቤተሰብ ርቆ ህመምን አየህ፡፡ በስደት እንኳን ለቅሶ እንኳን ህመም መልካም ነገር መልካም አልነበረም …ሚሊ እውነት ይሆን…እንደ አፈታሪኩ ሞትህን “ለማመን ስትቅበር የማየት” እድሉ ባይኖረንም ፈጣሪ አስክሬንህን ለሃገርህ ለማብቃት ሃይል ይስጠን …
እሽ ሌላ ምን ልበል ..ሚሊ የሃገርህ ሰማይ እንደናፈቀህ ሀገሬን እንዳልክ ነገን በተስፋ እንዳየህ ላይሳካ መኖር ሳትጀምር መንገድ አጭር ሆኖ በዚህ ተቋጨ፡፡ የመኖርህን የመጨረሻ ቀናት በስደት ሞት…በስደት ሞት… ከቤተሰብ ርቆ ህመምን አየህ፡፡ በስደት እንኳን ለቅሶ እንኳን ህመም መልካም ነገር መልካም አልነበረም …ሚሊ እውነት ይሆን…እንደ አፈታሪኩ ሞትህን “ለማመን ስትቅበር የማየት” እድሉ ባይኖረንም ፈጣሪ አስክሬንህን ለሃገርህ ለማብቃት ሃይል ይስጠን …
መታመምህን ሰምተው…ስደትህን ሰምተው ጭንቀትህ ሰምተው ሳይጨርሱ ሞትህን የሰሙት ምን ይሉ ይሆን …እኛ ሁሉም ነገር ጨልሞብናል ሚሊየ ድንገተኛ ህመም አፋጥኖ ላፈር አበቃህ፡፡ አሁንም የስደት ጣጣውን ፈጣሪ ሸፍኖ ለሃገርህ አፈር ያብቃህ፤ ሚሊ ሚሊ ሚሊ ስደተኛው ጓዴ ሚሊ ሚሊ……….. ሚሊ
No comments:
Post a Comment