“ይምርጡን ሳናዳላ፤ ሳንገል፤ ሳናስር፤ሳንዋሽና ሳንሰርቅ ፍፁም በሆነ አገራዊ ፍቅር አክብረንህ እናስተዳድራለን ”። የምርጫ መሪ ቃል ብትሆን ያልኳት።
ጎሽ እንዲህ ነው መቅደም። አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ዘጠኝ ድርጅቶች በጋራ ለመታገል መስማማታቻውን ስሰማ ሀሴት ነው ያደረኩት። መጀመርያ ዜናውን ስሰማ ጥሩ ነው አልኩ። አንድነትና መድረክ ስይካተቱ የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም በሚል አላካበድኩትም ነበር። ደስታዬን ሙሉ ያደረገው ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በኢሳት ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እነዚህ ድርጅቶች ሀይላቸውን ተጨማሪ ጉለበት የማድረግቸው እድሉ የሰፋ መሆኑን መስማቴ ነው። ፅሁፌን ብዴና እጄ ላይ ቢያስረጀውም ለማንኛውም ብዬ ለቅቄዋለው።
ቀጣዩ ምርጫ ሊደረግ ሰድስት ወር ነው የቀረው። ምርጫው የሚካሄደው በከፋ አፈናና በበዛ ፖለቲካል ውጥንቅጥ ውስጥ ነው። መንግስታዊ ሽብር ጣሪያ ነክቷል። ከየድርጅቶቹ ትግሉ ላይ ወደፊት የመጡት ወጣቶች ተለቅመው ታስረዋል። በአገሪቷ ውስጥ ያሉ ነፃ ጋዜጠኞች በሙሉ ማለት በሚችል እንዲሁ ታስረዋል ወይ ተሳደዋል። ይህ ቀጣይም ነው። በተናጠል ቀደም ብለው አማሮች፤ ሙስሊሞች ኦሮሞዎች እያሉ ሆን ብለው ህዝብን ተንኩሰው ሀሞቱ ያላቸውን ዜጎች ለቅመው ገድለዋቸዋል። ብዙዎችን በየእስር ቤቱ አጉረዋል። የቀሩትን መዝገበው በአይነ ቁራኛ እየተከታተሏቸው ተራ እየጠበቁ እንዳሉ መገመት ይቻላል። ጋንቤላ፤ አንድ አድርጋቸው ፅጌ። ማህበረ ቅዱሳን ቴዲ አፍሮ። አፋር፤ተመስገን ደስአለኝ። ኦጋዴን ይቀጥላል እያሉ ገና ለገና በፍራቻ ለምርጫው ሲባል ወንጀላቸው ቀጥሏል። ልዩነቱ በከረባት መሆኑ ነው እንጂ ልክ እንደቦኩ ሀራሙ ሰውዬ በተራ እየወጡ የሚያሰሙትን ቀረርቶ መስማቱ ካሁኑ አላኖረን ብሏል። በተጓዳኝ ደግሞ ሁሉን ተቆጣጥረው ስላሉ ያለ ጠያቂ የሚያዝበትን ገንዘብ፤ ሜዲያና መንግስታዊ መዋቅር እየተጠቀሙ የቅጥፈት የምርጫ ዝግጅትና ቅስቀሳ ብቻቸውን አበርትተው ተያይዘዋል። ይህ እንግዲህ የወያኔ የቀጣዩ የምርጫ እቅድ ነው። ለእቅዱ ተፈፃሚነት ሲባል ጭካኒያዊ በሆነ ሁኔታ እየጎዷቸው ያሉትን ወገኖቻችንን ማሰባችን ስለማይቀር የዘንድሮውም እቅዳቸው እንደሁሌው አህያነት እንዳለበት ማንችንም ብንሆን የምንስማማ ይመስለኛል። ዞሮ ዞሮ እቅድ ያሉት ሁሉም መራገጥ ነው። ይህ ሁሉ እርግጫና ወንጀል በመጨረሻ ኮሮጆ መገልበጣቸው ላይቀር ለምን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ከጣርን ብቻ ነው የፍራቻቸውን ምክንያታዊነት፤ እንዴት ምርጫውን ሊያልፉት እንዳሰቡ እቅዱ በመጠኑም ቢሆን የሚገባን። እኛ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናስብ የሚያደርገን።
አገዛዙ ይህን ሁሉ ሽብር ፈፅሞና ከተንደፋደፈ በሗላም አካሄዱ የማያዋጣው ከመሰለው ምርጫ የሚባል ነገር እስከጭራሹ ቀርቷል ማለት ድረስ ሊሄድ ይችላል። እስካላለ ግን ይህን በመሰለ አስቸጋሪና አስፈሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ምርጫውን መጠቀም በእርግጥም አለባቸው። በግሌ መጠቀማቸው ትክክል ነው ብዬ አጥብቄ አምናለው። ስለማምን ብቻ ሳይሆን ምርጫው ውስጥ መግባታቸው ስለማይቀርም ደግሞ ነው። ስለዚህም መነሻ የማደርገው በምርጫው ላይ የለውጥ ፈላጊው ድርሻ ከሚለው ነው።
ትኩረት መሆንና በቶሎ ሊሰራበት የሚገባው በየምርጫ ጣቢያው ከሁለትና ሶስት ተቃዋሚ መሀል እንዴት ነው አንድኛውን የተቃዋሚ እጩ ለይቶ አሸናፊ የሚያደርገውን ድምፅ ሳይበታተን እንዲያገኝ ማድረግ የሚቻለን?። ከጊዜና ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ተለያይተው ባሉበት ሁኔታ እንዴት ነው ሁለንተናዊ አቅማቸውን ተረባርበን ማጠንከር የሚቻለን?። ምርጫው ሙሉ በሙሉ ሊሰኝ በሚችል የሚገባውን ትኩረት በዜጎች ገና አላገኘም። ይህን በቶሎ መቀየር የሚቻለው እንዴት ነው?። የመሳሰሉት ጥያቄዎች ናቸው።
ምርጫው በዜጎች ዘንድ ትኩረት ያልተሰጠው አገዛዙ እቅድ አደርጎ ተግባራዊ እያደረጋቸው ካሉና የእብደት ሊሰኙ ከሚችሉ ተግባራትና ከቀደሙ ምርጫዎች የመጨረሻ ውጤት አኳያ ብቻ ስለታየ ይመስለኛል። ሌላው ምርጫ የሚባለው ጉዳይ ላይ ያለ ግንዛቤ ነው። ላብዛኞች ምርጫ ትግል አይደለም። እውነታው ግን አይደለም ከወያኔዎች ጋር ህግና ስርአት በአለበት ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች የሚደረገውም ምርጫ ይዘቱ ይለያያል እንጂ ትግል ነው። አንባገነኖች ኖረው ደፍረው ምርጫ አለ ካሉ በፈለገው አይነት እርግጫና ህገ አልባ በሆነ እቅዳቸው ውስጥ፤ በከፋ አፈናና መሰዋትነት ውስጥ ሆኖም በደስታ ልንለው የሚገባ የተከፈተ የትግል አውድማ ነው። ትግልም ብቻም አይደለም። መታገያ ሜዳ ብቻም አይደለም። ለሌዋም አይነት የትግል አይነት መሰረትና ማጎልበቻ ነው።
ለማንኛውም ለሁላችንም ለአገርም ደህንነትና ጥቅም ሲባል ቀጣዩ ምርጫ በጭራሽ እነሱ እንዳሰቡትና እንዳቀዱበት አልጋ በአልጋ መሆን የለበትም። ከምርጫ97ቱ ያነሰ ነብስ ግቢ ነብስ ውጪ ውስጥ የማይከታቸው መሆንም የለበትም። ከጥቂቶች በቀር የበዛው ዜጋ ይህ ዘረኛና አድሏዊ አገዛዝ እንዲያበቃ ይፈልጋል። ይህ እስከሆነ ደደብ ወይ ተስፈኛ ወይም ሌላም በሉኝ አሁን በአላው ጠቅላላ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን አስቸጋሪ ጠንካራ ህዝባዊ ቡጢ የምናቀምስብት ማድረግ ይቻላል። ከዘም አልፎ ኮሮጆ መገልበጡንም አስቸጋሪ ማድረግ እርግጠኛ ሆኜ ይቻላል እላለው።
እነሱ መንግስታቸውን በምርጫ አይደለም። ብዙ ሆነን አይደለም። አንድ ስው ዘፍኖ ወይ ፅፎ አፈር ድሜ እንደሚያስገባው ነው የሚያምኑት። በጣምም ትክክል ናቸው። እኛ ደግሞ ተመስገን “ተግዳድሮት” ነው የሚለው ብቻ አሉብን የምንላቸውን ችግሮች መፍትሄ አልባና ተራራ አሳክለን ነው ሁሌም የምናያው። በዛ ላይ የነሱን እጅግ ብዙ የሆኑ ስስ ብልት አሳንሰን ነው የምናየው። ሲጀመር በዚህ አለም ላይ ምንም መፍትሄ የሌለው ችግር የለም። አባባሉን የበለጠ እውነት የደረገልኝ ከዚህ አድሏዊ ዘረኛ ስርአት ጋር እየተደረገ ባለው ትግል በገጠሙን ችግሮች ካገዛዙ ይምነጩ ወይ ለለውጥ በቆመው አካል ስህተት ይፈጠሩ ሁሌም መፍትሄ እንደነበራቸው በእርግጥ አይቻለው። ይህ ወደፊትም ትግሉ ላይ አሉ የምንላቸው ችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሌላቸው እንዳልሆኑ አሳምኖኛል። ሁሌ ግን መፍትሄዎቹ ሁኔታዎች ግድ ያሉት እንጂ ተመራጭ ላይሆኑ ይችላሉ።
የዚህ ፅሁፍ አላማ ከለው ጊዜና ከተደጋጋሚ የብዙ ዜጎች አድማጭ ያጣ ውትወታ በሗላ በአስራ አንደኛው ሰአት ላይም በምርጫ ለሚሳተፉ እውነተኛ ተቃዋሚዎች በስም መ. ኢ. አ ድ፤ አንድነት፤ ሰማያዊና መድረክ እያለ ሰላሳ ሶስት ሆነው መነጋገር የጀመሩ ድርጅቶችን መጎትጎት ነው። በየምርጫ ጣቢያው አንድ ብቻ እውነተኛ ተቃዋሚ እጩ መራጮች ማግኘት አለብን። ይህን እንዴትም አድርጋችሁ ስሩት ግድ የሚል ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ ለማሳሰብ ነው። ከውያኔ ጋር የሚሞዳሞዱት ተቃዋሚዎች የፈለገውን አይነት ፕሮግራም ነድፈው ቢመጡ ወይ ዋው የተሰኘለት የቅስቀሳ ስራ ቢሰሩም በየምርጫው ጣቢያው መራጩ ላይ የሚኖራቸው ተመራጭነት ከቤተሰብና ከትውውቅ አልፎ እንቅፋት ሊሆን የሚችል ወይ ውጤቱን የማያዛባ ስላልሆነ ነው።
እነዚህ እውነተኛ ተቃዋሚዎች አሁን ላይ ምን ቢያደርጉ በየምርጫ ጣቢያው አንድ አንድ እጩ ተቀናቃኝ ብቻ ያቅርቡ የሚለው ችግር መፍትሄ ካላበጁለት ሁላችንንም ተሸናፊ ስለሚያደርግ አሳሳቢ ነው። ይህን ጉዳይ የት ድረስ ወስጄ እንደማየው ለማሳየት ተቃዋሚዎቹ በየምርጫ ጣቢያው አንዳንድ ተቃዋሚ እጩ ብቻ ማቅረቡን ሳይስማሙ ቀርተው ወድ ምርጫ የሚገቡ ከሆነ ዜጎችም ብንሆን ቀድምን በሆነ መንገድ መላ አበጅተንለት ልንመርጥ መሄድ ይኖርብናል። መላ ደግሞ ይኖራል። አንዱ መንገድ ውጫዊ በሆነ አካል ለየድርጅቶቹ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ጣቢያዎቹን ማከፋፈል ነው። ማከፋፈሉ ላይ የሚቀርቡ እጩዎችን ተመራጭነትና የመራጩን ህዘብ ፖለቲካዊ ዝንባሌ ግምት ውስጥ ባስገባ ማደላደል ይቻልል። ይህን ማድረግ እኔም እናኳ ይዳዳኛል።
ተቃዋሚዎች እዚህ ሳይደርስ መላ ልትሉበት ትችላላችሁ። አግባብ የሚኖረውና በእርግጥ የሚቀለውም በናንተ ሲሰራ ነው። የተሰባሰባችሁበትን መድረክ መጠቀም ትችላላችሁ። ሰማያዊ ፓርቲዎች ተመለሱ። ይኑሩበት። ሁላችሁም የእጩዎቻቸሁን ስም ዝርዝርና የምትወዳደሩበትን ምርጫ ጣቢያ ዝርዝር አቅርቡ። በዚሁ ቁም ነገር ላይ ብቻ በቀናነት መነጋገር ጀምሩ። መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን አጥኑ። በየድርጅቱ የቀረቡትን እጩዎች አጥኑ። ምን አልባት መደራደር፤መደላደል፤ መቀያያር ይፈለግ ይሆናል እንጂ ይቻላል። ብቻ ሳንቲብ ወደሰማይ አጡዞ ዘውድ ወይ ጎፈረ ማለት ድረስ መፍትሄ ተደርጎ መሞከር ግን አለበት።
ሁሉን ወገን የሚያስማማ አገራዊ መፍትሄ መቅረፁና በዛ ስር ተሰባስቦ ባንድ ሆኖ መግጠሙ ጉልበታም ነበር። ካለው ጊዜ አኳያ አሁን ስለማይቻል ይቆይ። በተቃዋሚነት ደረጃ ተሆኖ በዛ ላይ ዜጎች በከፋ አፈና ውስጥ ስላለን ልንዳኛችሁ የማይቻለን ሆኖም ነው ያስቸገረው። ተችሎም ቢሆን መሰረት ለመጣልና ሂደቱን ለማስጀመር ነበር። አሉ የምንላቸው ዋናዎቹ ልዩነቶች የትኛውንም አይነት ስምምነት ቢደረግ፤ እኔነኝ ያለ ዲሞክረሲያዊ መንግስት ቢፈጠርና ፈጣን በሆነ ሁለንተናዊ እድገት ማድረግ ብንችልም። ከልዩነቶቹ ባህሪ የተነሳ መፍትሄያቸው ረጅም በጣም ረጅም ጊዜ የሚፈልጉና የሂደት ያላሰለሰ ስራንና ትኩረትን የሚፈልጉ ናቸው። መተጋገሉ ገና ለመቶ አመት ይቀጥላል። ይህን ታሳቢ አድርጋችሁ እስካለው ልዩንት በጋራ ስልጣኑን ከወያኔ ለመረከብ መስራት አንድና አንድ ትኩረት ይሁን። አንድም ልዩነቱን ህግና ስርአት ባለበት፤ ከከበደ ሀላፊነትና ተጠያቂነት ጋር ፓርላማ ውስጥ ማስገባት ስለሚሆን አገር ከዚህ ሊጠቀም ይችላል። ያኔ የሚመች ሶፋ ላይ ፈልሰስ ብሎ ውስኪ እየተቀዳ ዘና ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ ስለሚሆን ይቀላል። ባዛ ላይ ልዩነት እየለዘበ ይሄዳል። ቢበዛ ፓርላማ ውስጥ ቡጢ ስትወራወሩ ደግሞ እያየን ፈን እንይዛለን።
ኮሮጆ መገልበጡንም የማይቻል ማድረግ ይቻላል ብያለው። መጀመርያ እናንተ እንድትመቹ ባግባቡ ሁኑ እንጂ ይቻላላ።
“ይምርጡን ሳናዳላ፤ ሳንገል፤ ሳንዋሽና ሳንሰርቅ ፍፁም በሆነ አገራዊ ፍቅር አክብረንህ እናገለግላለን ”።
ምን ማድረግ እንዳለብን ሁሉን ነግሮናል። ይሄን ልጅ ፍቱ ብያለው።
No comments:
Post a Comment