Monday, October 20, 2014

ወያኔ፣ ፍትህ እና እኛ – ያሬድ ኃይለማርያም

ያሬድ ኃይለማርያም
ከብራስልስ፣ ቤልጅየም
ጥቅምት 5፣ 2007 ዓ.ም.
ያሬድ ኃይለማርያም ለ7 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጋር አብሮ የሠራና የኖቬምበር 1 እማ 2ቱን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከሃገር ብዙ ምስጢሮችን ይዞ በመውጣት ለአውሮፓ ሕብረት ያቀረበ ነው።
ያሬድ ኃይለማርያም ለ7 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጋር አብሮ የሠራና የኖቬምበር 1 እማ 2ቱን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከሃገር ብዙ ምስጢሮችን ይዞ በመውጣት ለአውሮፓ ሕብረት ያቀረበ ነው።
በመጀመሪያ “ወያኔ፣ … እና እኛ” በሚል ርዕስ የማቀርባቸውን ጽሁፎች ዋና ዓላማ ለአንባቢያን ግልጽ ላድርግ። ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት አስከፊና ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታም ሆነ በየግላችን ለደረሰብንና ለገጠሙን ቁሳዊና መንፈሳዊ ኪሳራዎች ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ ነው ብለን ስለደመደምን እርግማኖቻችን፣ ነቀፌታችን፣ ዝልፊያችን፣ ወቀሳችን፣ ውንጀላችን፣ ዛቻና ማስፈራሪያችን ሁሉ ወያኔ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። እርግማንና ዝልፊያ ግፍንና ግፈኞችን ጠራርገው የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ባለፉት ሃያ አመታት በወያኔ ላይ ያዘነብነው እርግማንና ውርጅብኞች ወያኔን ብቻ ሳይሆን የተቀሩትንም የአፍሪቃ አምባገነኖች ሁሉ ጎርፍ ሆኖ በወሰዳቸው ነበር። በጸሎታችንም ብዛታ እኛ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን ቀሪውም የአፍሪቃ ሕዝብ ከግፈኞች መዳፍ ነጻ በወጣ ነበር። ያ ግን አልሆነም። የሚያሳዝነው ታዲያ በጩኸታችን፣ በጸሎትና በእርግማን ለአሥርት ዓመታት የተሸከምናቸውን ግፈኞች ከጫንቃችን ላይ ማውርድ አለመቻላችን አይደለም።
ይልቅስ ዛሬም ከዚሁ ከቆረብንበት የመረጋገም፣ የመጠላለፍና የመጯጯ አባዜ ሳንላቀቅ ከወያኔ ጋር ያሳለፍነውን የሰቆቃ ዘመን እያደስን ማራዘማችን ነው። ወያኔ ሰብዓዊ መብቶችን በገፍ በመጣስ፣ አገርንና ሕዝብን በማዋረድ፣ ዘረኝነትን በማስፋፋት፣ በሙሰኝነት፣ የአገሪቱን ተቋማት በማዳከምና መሁራንን በማሳደድ አለም ያውቀዋል። ቀሪው አለም ታዲያ የሚታዘበው ወያኔን ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለውን ክፉና አፋኝ ሥርዓት ተሸክመን እዚህ ያደረስነውን እኛንም ጭምር ነው። እንደ እኔ እምነት ወያኔ ሕዝብ የፈቀድንለትን ዕድሜ ነው እየኖረ ያለው። ምራኝ በሎ የፖለቲካ ፈቃዱን በነጻነት ሰጥቶታል እያልኩ አይደለም። በተገዥነት ለመኖር ግን ተመቻችቷል።
ሕዝብ በተለያዩ መንግዶች የፖለቲካ ፈቃዱን ይገልጻል። ጤናማ በሆነ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የሕዝብ የፖለቲካ ፈቃድ በነጻና ፍትሐዊ በሆነ የምርጫ ሥርዓት ወይም በሌሎች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገዶች ይገለጻል። እነዚህን እድሎች ሲነፈግ ደግሞ ቁጣውን ባደባባይ ወጥቶ በማሳየት መልዕክቱን ያስተላልፋል። ኃይሉንም ያሳያል። የፖለቲካ መዘውሩን የጨበጡትን ኃይሎች ያርቃል፣ መስመር ያሲዛል፣ ካልሆነም ያስወግዳል። በእንዲህ ያለ ማህበረሰብ ውስጥ እያፈኑ፣ እየገደሉ፣ ሕዝብን እያሸበሩ፣ ንጹሃንን አስረው እያሰቃዩና በሙስና ውስጥ እየዋኙ መቀጠል አይቻልም። ቢሞከርም የሥርዓቱ ዕድሜ አጭር እንጂ እንደኛ በአሥርት አመታት የሚቆጠር አይሆንም። ይህ አይነቱ ማህበረሰብ አፋኝ ሥርዓትን ተሸክሞ ለመዝለቅ እኛ ያለንን ትእግስቱም ሆነ የደነደነ ሰፊ ተከሻ የለውም። እየተራቡና እየደኸዩ ባለሥልጣናትን ማጠብደል፣ ከእወቀትና ከእውነት ጋር ለተጣሉ የሥርአቱ ተከታዮች አገርን ጥሎ መሸሽና እራስን ለውርደት ማመቻቸት፣ በሌሎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆኖ በራስ ጉዳይ ብቻ መጠመድ፣ ለሐይማኖተኝነት የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠትና የራስን ፍርሃት ለመደበቅ የአገር ጉዳይና ፖለቲካ አይመለከተኝም በሚል የኃይማኖት ተቃማትንና ቅዱስ መጻህፍትን የቀበሮ ምሽግ ማድረግ በተዘዋዋሪ የአገዛዝ ሥርዓቱ እንዲያፈረጥም ድጋፍ እንደ መስጠት ነው የሚቆጠረው። ይህ ደግሞ አገሪቷ ዛሬ ለተዘፈቀችበት አዘቀት፣ በሥርዓቱ ውስጥ ለሚታየው ብልሹነትና ለሚፈጽማቸው ወንጀሎች ሁሉ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ እያንዳንዳችን ድርሻ ያለን መሆኑን ያሳያል። ማድረግ የሚገባንን ያህል ባለማድረጋችን ይሁን ወይም ማድረግ የማይገባንን በማድረጋችን የጥፋቱ ተጋሪዎች እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህ የወያኔን ጥፋቶች እያነሳን በተወያየን ቁጥር በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖረንን የዜግነት ወይም የተወላጅነት ድርሻ አብረን ልንፈትሽ ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን በርካታ ነገሮች አሉ። በአገሪቷ ውስጥ ይህ ሁሉ ወንጀልና ግፍ ሲፈጸም፣ ወያኔ ባለፉት ሃያ ዓመታተ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎችን ሲገድል፣ በመቶ ሺዎችን አስሮ ሲያሰቃይና አፍኖ ሲሰውር፣ ገበሬዎችን ሲያፈናቅልና ሲያሰድድ፣ ወጣቶችን ለአረብ አገራት ባርነት ሲያመቻችና ሲያሰድድ፣ አገሪቱን በዘር ከፋፍሎ ሲያምስና ሲያጫርስ የት ነበርን? ሰምተንስ ምላሻችን ምን ነበር? ምንስ የማደረግ አቅም ነበረን? ድርሻችንን ተወጥተናል ወይ? የበኩላችንን አድርገናል ብለን ካሰብንስ ታዲያ ለምን ሥርዓቱን ማረቅ አቃተን? የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተን ራሳችንን መሞገት ይገባናል። ለዚህም ነው ቀደም ሲል “ወያኔ፣ ሽብርና እኛ” በሚለው ጽሁፌ ወያኔ ብቻ ሳይሆን የወያኔን እኩይ ገድል እየዘከዘክንና መፍትሄን በማያመላክቱ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳዎች ላይ ተጠምደን ሕዝብን አብረን አናሸበር ያልኩት።
ወደ ዛሬው ጽሑፌ ልመለስና “ፍትሕ” በሚለው ቃል ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ አለ ብዮ ስለማምን በዙ ማለት አይጠበቅብኝም። ፍትሕን በተመለከተ ከጥንታዊቷ ግሪክ ፈላስፎች አንስቶ የዘመኑ የፍልስፍ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የሚስማሙበት የጋራ ነጥብ አለ። ይሄውም ፍትሕ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በግለሰቦች መካከል በእኩልነትና በመከባበር መንፈስ ላይ የተመሰረተ ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር፣ እንዲሁም ዘላቂነት ያለውና የተረጋጋ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲኖር ከሚያስችሉት መሰረታዊ እሴቶች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑ ላይ ነው። አንድ የፖለቲካ ሥርዓት ምንም አንኳን ጥሩ የሆነ መንግስታዊ አወቃቀር፣ ሕገ-መንግሥትና የዳበረ የኢኮኖሚ መሰረት ቢኖረውም ፍትሕ እስከ ከተጓደለበት ድረስ ሊፈተሽ፣ ሊስተካከልና እንዳስፈላጊነቱም ሊወገድ ይገባዋል። ታዋቂው የፍልስፍና መምህርና ፈላስፋ ጆን ራውልስ “A Theory of Justice” በሚለው መጽሐፉ መግቢያ ላይ በጥሩ አገላለጽ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል “A theory however elegant and economic must be rejected or revised if it is untrue; likewise laws and institutions no matter how efficient and well-aranged must be reformed or abolished if they are unjust”።
ፍትሕ ባልሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኀበራዊ መረጋጋቶች አይታሰቡም። ፖለቲካው በውጥረትና በቀውስ የተሞላ ነው የሚሆነው። ኢኮኖሚውም ለጥቂቶች መደላደልን ፈጥሮ ብዙሐኑን የሚያቆረቁዝና ለከፋ ድኀነተና ባርነት የሚያመቻች ነው የሚሆነው። ማኅበራዊ ቀውሶች ይፈጠራሉ። ፍትሕ በተጓደለበት ሥፍራ ሁሉ ሰዎች በዘራቸው፣ በጽኦታቸው፣ በቋንቋቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውና በሙያቸው የሚገለሉበት፣ የሚዋከቡበትና ለጥቃት የሚመቻቹበት ሥርዓትም ይፈጠራል። መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን እና ነጻነታቸውን የተነፈጉ፣ በባለሥልጣናት የወንጀል አድራጎት የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችና ግፉአን በሞሉበት አገር የሚኖረው ሰላም ሁሌም አንጻራዊ ነው። ተበዳዮች የፍትሕ ጥማታቸውን የሚወጡበት ሕጋዊ መስመር ሰለሚያጡ ቂምና በደልን አንዳረገዙ ነው የሚቆዩት። ኃይልና ጉልበት ያገኙ የመሰላቸውም ቀን ቁጣቸውን የሚገልጹት ፍጹም ቅጥ ባጣ የአመጽ እርምጃ ነው። የፍትሕ ጥማታቸውን እንደማያረካ ቢረዱትም ቁጣቸውን ለመግለጽ በሚወስዱት እርምጃ የመጀመሪያው የጥቃት ሰለባዎች የልማትና የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ባለሃብቶች ያፈሯቸው ንብረቶች እና ባለስለጣናት ናቸው። የሩቁን እንተወውና በቅርቡ እንኳን የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎችን ቁጣ ተከትሎ በአንቦ ከተማ የተስተዋለው የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት ህልፈትን ልብ ይለዋል። ፍትሕ በሌለበት ሥፍራ የሚኖር ልማትና የኢኮኖሚ እድገት የገዢዎቹ መፎከሪያና መሟሰኛ ከመሆን ባለፈ ሕዝብ እንደ ራሱ ሃብት የሚቆጥረው የለውጥ መሰረት አይሆንም። ሕዝብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ በሚደረግበት ሁኔታ ውስጥ በፖለቲካወም ሆነ በልማቱ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም።
ወያኔና ፍትሕ
በበቀል መንፈስ የተሟሸው የወያኔ የአገዛዝ ዘመን ገና ከጅምሩ ነበር ለፍትሕ ያለውን የወረደና የተዛባ ምልከታ ባደባባይ ማሳየት የጀመረው። በጠራራ ጸሐይ በየአውራ ጎዳናው መግደል የጀመሩት ድንበር ተጋዳላዮች በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ባለፉት ሃያ አመታት ቀጥፈዋል። የሥርዓቱን ብልሹነት የሚያጎላው የግድያዎቹ መፈጸም ብቻ ሳይሆን ገዳዮች በሕግ አግባብ ሊጠየቁና ለፈጸሙትም የወንጀል አደራጎት ኃላፊ ሲሆኑ አለመታየቱ ነው። ተበዳዮችንና የሟች ወገኖችን እያስፈራሩና አያሸማቀቁ በያደባባዩ ሲንጎማለሉ፣ ሲሾሙና ሲሞገሱ መታየቱ የተለመደ ነው። በጸጥታ ኃይሉ በኩሉ ይታይ የነበረው ሥርዓት አልበኝነትና ከሕግ በላይ የመሆን አዝማሚያም አያደር ተቋማዊ ቅርጽ የዟል። ሕገ-መንግሥቱን በሚጻረር መልኩ የውጡት እንደ ጸረ-ሽብር አዋጁ አይነት አዳዲስ ሕጎችና በካደሬዎች የተሞላው የሕግ ተርጓሚው አካል የወያኔን የአፈና መዋቅር ሕጋዊ መልክ እንዲይዝ አድርገውታል። ሕግን በመጣስ ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት እረገጣዎች ሁሉ ዛሬ በእነዚህ ሕጎች የተፈቀዱ ተግባራት ሆነዋል። በጠመጃ አፈሙዝ ላይም ተወስኖ የቆየው የአፈናው መዋቅር ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ በሕግና በፍትሕ ተቋማት እንዲጠናከር ተደርጓል። ፖሊሱም፣ ዐቃቤ-ሕጉም ሆነ ዳኞች የባለሥልጣናትን ቀጭን ትዕዛዝ አሰፈጻሚዎች ስለመሆናቸው ሰሞኑን በፍርድ ሂደት ላይ ያሉትን የዞን ዘጠኝ አባላትን፣ የጋዜጠኞቹን፣ የፓርቲዎች አመራር አባላትንና ከኦሮሚያ ክልል ተይዘው የታሰሩ ተማሪዎችን ክስና የፍርድ ቤት ደራማ ማጤኑ ብቻ ይበቃል።
በበርካታ አገራት ደረጃው ይለያይ እንጂ የሕግ አስፈጻሚው አካል ብዙውን ጊዜ የሰዎችን መብት ከመጣስና ፍትሕን ከማጓደል የጸዳ አይደለም። ይሁንና በብዙዎቹ አገራት የዳኝነት ክፍሉ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከአስፈጻሚው አካል ነጻ ሆኖ የመሥራት ዕድልና አቅምም ስላለው ፍትሕ ቢጓደል የመቃናት እድሉ ሰፊ ነው። እሩቅ ሳንሄድ በጎረቤቶቻችን ኬኒያና ኡጋንዳ እንኳን ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ዳኞች ከመንግስት በተቃርኖ ሲፈርዱ ማየት የተለመደ ነው። የአገራችንን ሁኔታ ከብዙዎቹ አገራት የተለየና የከፋ የሚያደርገው በጊዜ ሂደት የሕግ ተርጓሚውም በዚሁ የጥፋት መስመር እንዲሰለፍ መደረጉ ነው። ‘አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ’ አይነት ግንኙነት አንዲኖራቸው ተደርገው የተዋቀሩት እነዚህ የመንግስት ተቋማት የኢትዮጵያን የፍትሕ ሥርዓት ወደ ከፋ አዘቅት ውስጥ ጨምረውታል።
እኛስ?
እንግዲህ እራሳችንን እንጠይቅ። እኛስ? ሥርዓቱ አገሪቱን ፍትሕ አልባ ሲያደርግና ከገለጽኩትም በከፋ መልኩ ሰብአዊ መብቶችን ሲጥስ እያየን ምን አደረግን? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳትና መወያየት የግድ ይላል። በተበላሸው የፍትሕ ሥርዓት ቀጥተኛ ተጠቂ የሆነውን ያህል ለሥርዓቱ ፍትሕ አልባ ሆኖ መቀጠል በአንድ ወይ በሌላ መንገድ አስተዋጽኦ ላለማበርከታችን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ከወያኔ በተቃርኖ በቆመው ኃይልና በቀረው ፍትሕ ናፋቂ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ለፍትሕ የተሰጠውን ግምትና ቦታ በመጠኑ መቃኘት ግድ ይላል።
• የፍትሕ ጥያቄን በጎሣ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በኃይማኖት፣ በአገርም ሆነ ሌሎች መስፈርት ከልሎ ማየት ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም። በየትም ቦታ ይሁን በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም የመብት ጥሰትና የፍትሕ መጓደል ሌላውን ሰው ሊያሳስብና እንቅልፍ ሊነሳው ይገባል። ለዚህም ነው ታዋቂው የሲቪል ነጻነት ታጋይ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ “Injustice anywhere is a threat to justice everywhere.” በማለት ያስተላለፈውም መልዕክት ይህንን ሃሳብ ለማንጸባረቅ ይመስለኛል። ወደ አገራችን መለስ ብለን ሥርዓቱን ለመቀየር በትግል ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የታዘብን እንደሆነ በፍትሕ ጥያቄ ዙሪያ ጎልተውና ተደጋግመው የሚስተዋሉ ችግሮችን እናገኛለን። ስለ ፍትሕ በጥቅሉ ከማውራት ባለፈ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት የድርጀታቸው አባል ወይም ደጋፊ የሆነ ሰው ችግር ሲገጥመውና ሲበደል ብቻ ነው። የተወሰኑ ፓርቲዎች አልፎ አልፎ ከሚያሰሙት እሮሮ ባሻገር አብዛኛዎቹ በሌሎች ሰዎች ላይ ወይም የሌላ ድርጅት አባል በሆኑ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችንና የፍትሕ መጓደልን ችላ በለው ሲያልፉ ነው የሚስተዋለው። ይህ ከድርጅት ማዕቀፍ ውጪ ማሰብ ያለመቻል ችግር አባላችን ወይም ደጋፊያችን አይደለም ብለው የሚያስቡትን ሰው በደልና ስቃይ እንዳይጋሩ አድርጓቸዋል። በተለይም በጎሣ በተከለሉ ደርጅቶች ላይ ይህ ችግር ጎልቶ ይስተዋላል። የፍትሕ ጥያቄን በጎሣ ወይም በፓርቲ መነጽር ማየት በድርጅቶቹ ውስጥ ያለውን የግንዛቤ ችግር አጉልቶ ከማሳየቱም በላይ ማንን ነው ከወያኔ የአገዛዝ ቀንበር ነጻ ሊያወጡ የሚታገሉት? ሕዝብን ወይስ …? የሚል ጥያቄን ያጭራል።
• ይህ የሌሎችን በደል ችላ የማለት ልማድ ማኅብረሰባዊ መሠረትም የያዝ ችግር ነው። ኢሰመጉ ውስጥ በመብት ጥሰቶች አጣሪነት በሰራሁበት ወቅትና ከዚያም ወዲህ ለመታዘብ እንደቻልኩት ለተገፉ ሰዎች ድምጽን የማሰማትና ከጎናቸው የመቆም ባህል በቡዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ቦታ የተሰጠው አይመስልም። ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት እና እጅግ የከፋ የሰብአዊ መብቶች አረገጣ ባለበት አገር ከኢሰመጉም ጎን ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ጎን ቆሞ ለራሱና ለሌሎች ሰዎች መብት መከበር ለመታገል የቆረጠው ሰው ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለምን?
• ሌላው አሳሳቢውና ተደጋግሞ እየተስተዋለ ያለው ችግር ፍትሕን የፖለቲካ ጥቅም መደራደሪያ የማድረግ መጥፎ አካሄድ ነው። “የጠላቴ ጠላት …” በሚል የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት ከአገዛዝ ሥርዓቱ ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን በማንኛውም የሥልጣን ደረጃ ላይ የቆዩና የወያኔን የወንጀል ተግባራት ሲደግፉና በቀጥታም ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ ባለሥልጣናት ሥርዓቱን በከዱ ጊዜ ተቃዋሚዉ ኃይል ተቀበሎ የሚያስተናግድበት መንገድ በቅጡ ሊፈተሽ ይገባዋል። ለዚህም እነ አቶ ስዮን፣ አስመራ የገቡትን የወያኔ የጦር ጀነራሎችን፣ በጋንቤላው እልቂት ሊጠየቁ የሚገባቸው የክልሉ ባለሥልጣናትን፣ በበደላችን ብቻ ሳይሆን በወሬ ጥማታችንም ሊያተርፉ የጥፋት ተሳታፊነት ገድላቸውን ያለ አንዳች ሃፍረት በመጽሐፍ ጠርዘው እየቸበቸቡልን ያሉትን እንደ ተስፋዮ ገብረአብ እና ኤርሚያስ ለገሠን የመሳሰሉ ጮሌ ወያኔዎችን ያስተናገድንበት ሁኔታም በቅጡ ሊፈተሸ ይገባዋል።
Corruption
• ሰብአዊ መብቶችን በመጣስ በማናቸውም መልኩ ተሳትፎ የነበራቸውን የወያኔን ሹማምንትና ደጋፊዎች ሥርዓቱን ስለከዱና ወደ ተቃዋሚው ጎራ ስለተቀላቀሉ ብቻ በሕዝብና በአገር ላይ ሲፈጽሙት የቆዩትን ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት እንደ ጀግና ማሞካሸትና የሌላቸውንም ስብዕና ማላበስ ላጥፊዎቹ መደበቂያ ጫካ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ይህ አይነቱ አካሄድ ዛሬ ከሥርዓቱ ጋር ሆነው ሕዝብን እየበደሉ ላሉትም የወያኔ ሹመኞች የሚሰጠው ትምህርትም ሆን የሚያስተላልፈው መልዕክት እጅግ የተሳሳተ ነው የሚሆነው። ‘በሕዝብ ላይ ያሻችሁን ብትፈጽሙም ወያኔን እስከ ከዳችሁና ወደ እኛ ካምፕ እስከ ተቀላቀላችሁ ድረስ ሃጢያታችሁ ሁሉ ይሰረያል፣ የፈጸማችሁትም ወንጀል ካለ የሚጠይቃችሁ አይኖርም’ የሚል መልክት ነው። ይህ ደግሞ ለጥቅምም ይሁን ከልብ ከወያኔ ጋር የቆሙ የጥፋቱ አጋሮች ዛሬ ላይ ሆነው ለሚፈጽሙት ጥፋት ወደፊት ተጠያቂ እንሆናለን በለው እንዳይሸማቀቁ ና ይልቅስ የተንጠለጠሉበት ዛፍ ያዘመመባቸው ጊዜ እግራቸው አፈር ሳይነካ ተቃዋሚው ወዳዘጋጀላቸው ሌላ ዛፍ እንዲጠላጠሉ አድል እየፈጠረላቸው ነው። እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ የምፈልገው የሥርዓቱን ብልሹነት በቅርበት ከተረዱ በኋላ ከሕዝብ ጎን በመቆም ለፍትሕና ለነጻነት መታገል ለሚፈለጉ የወያኔ ሹማምንት በሩ የዘጋባቸው እያልኩ አይደለም። ከጥፋታችው ታርመውና በቅጡ ተጸጽተው የበደልነውን ሕዝብ እንካስ ሲሉ መንገዱ ሊዘጋባቸው አይገባም። ጸጸታቸውም ከልብ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያው በሥራ አጋጣሚ የሰበሰቡትን ወሬና የሕዝብ መረጃ ሲበድሉት ለቆዩት ሕዝብ በነጻ በመግለጽ የሚሰራበትን ደባ እንዲያውቅ ሲያደርጉ ነው። እነ አቶ ኤርሚያስ ካለቆቻቸው የቃረሙትን ተራ ወሬና በሕዝብ ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን በደል በመጽሐፍ መልኩ ካልሆን አንገልጽም በሚል ለሁለተኛ ጊዜ በሕዝብ በደል መነገድና ማትረፍ ለትዝብት ይዳርጋል። ግለሰቡ አስቀድመው በኢሳት ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ላሰተዋለ ሰው የወሬያቸውን ዳርዳሩን እየነካኩ ዝርዝሩን ከመጽሐፌ ታገኙታላችሁ እያሉ አይን ባወጣ መልኩ ነበር ያስተዋውቁ የነበረው። እንደ እነዚህ አይነቶቹ ብልጣብልጥ ወያኔዎች ከሆነ በቅርቡ የአሜሪካን የስለላ ድርጅት ሰራተኛ የነበረው ስኖውደን በሕዝብ ላይ የሚሰራውን ደባ ለማጋለጥ መንግሥትን ከድቶ በስደት የለቀቀውን ከፍ ያለ የሚስጢር መረጃ በፈለገው መልኩ ቢያሳትመው ኖሮ ከአለማችና ሃብታሞች ጎን በተሰለፈ ነበር። ስኖውደን ያደረገው ግን ይህ መረጃ የሕዝብ ሃብት ነው ስለዚህም ሕዝብ በነጻ መረጃውን የማግኘት መብት አለው በሚል ጋዜጠኞች ያረፈበት ሆቴል ድረስ ጠርቶ መረጃው ይፋ እንዲሆን አድርጓል። ለዚህም ቤሳቤስቲ ሳንቲም አላገኘበትም። እኛ ዘነድ ያለው የሥነ-ምግባር ችግርና የሞራል ግሽፈት ስር የሰደደ በመሆኑ በእነ አቶ ተስፋዮ ገብረአብና በአቶ ኤርሚያስ ለገሰ የወሬ ነጋሪ መጽሐፍት የሚታተርፉት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እነሱን ጀግና አድርገው ወደ አደባባይ የወጧቸውና መጽሐፎቻቸውን ያሳተሙላቸው ‘ተቃዋሚ’ ኃይሎች ጭምር ናቸው።
• ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመንግሥት ባለሥለጣናትን ፍርድ አደባባይ ለማቆም ከኢትዮጵያ ውጪ የሚደረጉ ጥረቶችን መፈተሸ ይገባል። ከምርጫ 97 ወዲህ በአውሮፓና በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለውጤት ያልበቁ በርካታ ወጥኖች ተጀምረው ከመንገድ ቀርተዋል። ሥርዓቱ በሃያ አመታተ ውስጥ የፈጸማቸው በርካታ በሰው ስብዕና ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎች በአለም አቀፍ የፍትሕ አደባባይ ተጠያቂ ሊያደርጉት እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አይደለም። ይሁንና መረን የለቀቀውና አይን ያወጣው የምዕራቡ አለም ኢ-ፍትሐዊነት እንደ ወያኔ ላሉ ታዛዥ አንባገነኖችና ወንጀለኞች ለጊዜውም ቢሆን የማይጠየቁበትን ከለላን ፈጥሮላቸዋል። ይሁንና እድሉ ሙሉ በሙሉ የተሟጠጠ ባለመሆኑ በአንዳንድ አገሮች የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የተፈጠሩትን አመቺ ቀዳዳዎች ለመጠቀም የሚቻልባቸው እድሎች ነበሩ። ሆኖም የተጀመሩት ውጥኖች ከእቅድ ሳይዘሉ እንደተወሩ በመቅረታቸው እነዚህንም እድሎች ባግባቡ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል። ይህም አንዱ የክሽፈታችን መገለጫ ይመስለኛል። ለዚህም እንደ ዋነኛ መክንያት ከሚቆጠሩት ነገሮች አንዱ የፍትሕን ጥያቄዎች ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በዘለለ ለማየት ያለመቻላችን ነው። በባዶ ሜዳ የወያኔ ባለሥልጣናትን ልንከስ ነው፣ ከሰስን፣ ተደራጀን፣ ወዘተ… እየተባሉ ከአንድ ሳምንት ለማይበልጥ የዜና መወያያ የሚውሉ ማሰፈራሪዎች ለፍትሕ ጥያቄዎች ያለንን የወረደ ምልከታና ቁርጠኝነትም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በቅርቡ በሲውዲን አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአገዛዝ ሥርዓቱን በፍትሕ አደባባይ ለመፈተን ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው። ይሁንና ገና ከጅምሩ ጉዳዩ እንደ ሰበር ዜና ተደርጎ በኢሳት የቀረበበት ሁኔታ ግን እጅግ አሳፋሪና ከእውነት የራቀም ነው። የነገርን ጫፍ ይዞ እያጋነኑ የግምት ትንታቴ መስጠት በኢሳት ዜና አቀራቢዎች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም ማንም ሊያረጋግጠው የሚችለውን ሃቅ ሰበር ዜና በሎ አጋኖ ማቀረብ ከሙያ ስነ-ምግባርም ሆነ ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ያለፈ ነው። በሲውዲን አገር የተጀመረው ጥረት እውነት ሆኖ ሳለና ያንኑ በአግባቡ መዘገብ ሲቻል በኢሳት ሰበር ዜና ላይ ‘የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲውዲን አገር በሚገኘው አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተባቸው’ በሚል መንደርደሪያ መቅረቡ የኢሳትን ተአማኒነት ብቻ ሳይሆን እየለፉ ያሉትንም ሰዎች ድካም ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። ማንም ሰው በቀላሉ የሚያነሳው ጥያቄ በሲውዲን አገር እንዲህ አይነት ክስ ሊቀርብለትና ሊያስተናግድ የሚችል ‘አለም አቀፍ’ የሆነ ‘የጦር ፍርድ ቤት’ አለ ወይ? የሚል ነው። መልሱ ቀላል ስለሆነ እያንዳንዱ ሰው ኮመፒዉተሩን ይፈትሽ።
ስለ ፍትሕ ጥያቄዎች ስናወራ በአገዛዝ ሥርዓቱ ስለ ተገደሉ፣ ስለ ታፈኑ፣ ስለ ታሰሩ፣ ስቃይ ሰለተፈ ጸመባቸው፣ የአካል ጉዳት ሰለ ደረሰባቸው፣ ከአገር ስለተሰደዱ፣ ከቄያቸው ስለተፈናቀሉ፣ በዘርና በአስተዳደር መድሎ መሸሻና መጠጊያ ስላጤ ግፉአን ነው የምናወራው። እነዚህ ሰዎች ጊዜው የፈለገውን ያህል ይርዘም እንጂ ፍትሕ የሚያገኙበትን ቀን ይጠብቃሉ፣ ይናፍቃሉ። ለበደላቸውም ካሳም ይሻሉ። በፍትሕ ጉዳይ በቧለትን እና ለፖለቲካ ግብ ማሳለጫነት በተጠቀምንበት ቁጥር ተበዳይ በሆነው ሰው አይን የምንታየው ከዋና በዳዮቹ ጎን የተሰለፍን ያህል ነው። በደልን በመፈጸምና በሰዎች በደል ሌላ አላማን ለማሳካት በመጣር መካከል ያለው የሞራል ክስረት ቡዙም የተራራቀ አይደለም። ለዚህም በዚህ ሳምንት ወደ ቃሊቲ የተወረወረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የኮብላዩ ሚኒስትር ወጎች” በሚል ከተበዳይ ወገን ሆኖ አቶ ኤርሚያስ የፈጸሙትን አንዳንድ ነገር እያስታወስ ላቀረበባቸው ትችት እሳቸውን አቅፎ ከያዘው ክፍል ወደ ጋዜጠኛ ደሳለኝ የተወነጨፉት ነቀፌታዎች ጠሩ ማሳያዎች ናቸው። ተመስጌን ለሙያው በጽናት የቆመ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ነው። እስርና መከራ ሊገጥመው እንደሚችል ጠንቀቆ እያወቀም እንደ ብዙዎቻችን በርገጎ አገርሩን ጥሎ ለመፈርጠጥም ሆን በፍርሃት አፉን ለጉሞ ለመቀመጥ አልወሰነም። የአቶ ኤርሚያስንና ያለቆቻቸውን ግልምጫና ማስፈራሪያ ሁሉ ችሎ ለአመታት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም አቶ ኤርሚያስ እቅፍ አበባ ተበርክቶላቸው በውጭ የሚገኝውን የተቃዋሚ ኃይል እንዲቀላቀሉና አዲሱ የፖለቲካ ተንታኝ ተደርገው ሰላሳ ጊዜ በኢሳት ብቅ ጥልቅ ሲሉ ጋዜጠኛ ተመስጌን ግን የሕዝብ ልሳን ሆኖ ለእውነትና ለፍትሕ በመታገሉ በወታደሮች ተከቦ ወደ ቃሊቲ ተልኳል። የሥራ ባልደረቦቹም በደረሰባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ተሰደው በጎረቤት አገሮች እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል በዚህ ሳምንት በተሰደደበት ኬኒያ ሕይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ አንዱ ነው። አሳዳጆቹ ግን ከአንደኛው ዛፍ ወደ ሌላኛው ዛፍ እየተንጠላጠሉ ኑሮዋቸውን በሕዝብ ብሶትና የወሬ ጥማት አደላድለዋል።
ለፍትሕ በእውነተኝነትና በሙሉ ልብ ልንቆም የገባል። የጥፋትና የወንጀል አድራጎት ተሳታፊ ለሆኑ ሰዎች የመደበቂያ ጫካ ከመሆን ይልቅ የበደሉትን ሕዝብ ከወሬ ነጋሪነት ባለፈ እንዲክሱት እድል ልንሰጣቸው ይገባል።

በቸር እንሰንብት!
ያሬድ ኃይለማርያም

No comments:

Post a Comment