የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት አነጋጋሪ ሆኗል። የሪፖርቱ አነጋጋሪነት የሚጀምረው ከርዕሱ ጀምሮ ነው። የሪፖርቱ ርእስ <<ምክኒያቱም ኦሮሞ ስለሆንኩ>> Because I am Oromo የሚል ሲሆን በኦሮምያ ክልል ውስጥ በገፍ እና በግፍ ስለሚፈጸመው ጭቆና ያወሳል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግስትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲከስ ቆይቷል። የአሁኑ ሪፖርት ለየት የሚያደርገው በኦሮሞዎች ላይ በተለየ እየደረሰ ያለውን ጅምላ እስር፤ ማሰቃየት፤ ግርፋት፤ ስደት፤ መደፈር፤ የፍትህ ማጣት እና ሞት አካቶ ይዞ መውጣቱ ነው። በመቶ የሚቆጠሩ ምስክሮችን ቃል አካቶ የተዘጋጀው ሪፖርት የተለያዩ ሰለባዎችን ታሪክ ይዘረዝራል።
ይሄ ሪፖርት ከብዙ ምስክሮች በተሰበሰበ ታሪክ ቢደጎስም የኢትዮጵያ መንግስት ግን እንደተለመደው በፍጥነት አስተባብሏል። ከአቶ መለስ ዜናዊ በኋላ በንግግር ችሎታቸው የሚደነቁት አፈ ቀላጤው አቶ ሬድዋን ሁሴን ሪፖርቱ የውሸት ነው በማለት ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ተናግረዋል። አንዳንድ የዋህ የመንግስት ደጋፊዎችና ካድሬዎች ደግሞ ሪፖርቱ ተዓማኒነት ይጎድለዋል ለማለት ሞክረዋል። ለዚህ የሰጡት ምክኒያት ደግሞ አብዛኛዎቹ ምስክሮች በስደት ላይ ያሉ ስለሆነ የራሳቸውን ኬዝ ለመስራት የፈጠሩት ውሸት እንጂ በኦሮሞዎች ላይ ይሄ አልተፈጸመም የሚል ነው።
የኢትዮጵያን ፖለቲካን በቅርበት ለሚከታተል ሰው ግን ይሄ ሪፖርት ፈጽሞ እንግዳ አይሆንም። በኦሮሞች ላይ የሚደርሰው ጅምላ እስር የተጀመረው ዛሬ አይደለም። ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ከወጣ ጀመሮ በኦሮሚያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ውክቢያ ሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው። የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ከእስር ቤት ሲወጡ በሰጡት ቃለ <<እስር ቤቱ ኦሮሚኛ ይናገራል>> በማለት የኦሮሞዎችን ጅምላ እስር አረጋግጠዋል።
ይሄ ሪፖርት ከወጣ በኋላ አምስት ሺ የኦሮሞ እስረኞች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት የኦሕኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሰጡት ምላሽ <<አምስት ሺ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው ... ምክኒያቱም በቅርቡ እንኳን የአዲስ አበባን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተተቃውመው ሰልፍ በማድረጋቸው ምክኒያት በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ታፍሰው ታስረዋል። ከመላ ኦሮሚያ ከሆነ ደግሞ አምስት ሺ እጅግ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው>> በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
እንግዲህ እውነታው ይሄ እንደሆነ ሁላችንም እያወቅን አሁን ፈረንጆቹ ሲናገሩት ብቻ ትልቅ ጩኸት መፍጥሩ መንግስታችን ለምእራባውያን ከሚሰጠው አክብሮት ካልሆነ በስተቀር ለእኛ አዲስ አይደለም። "የአዋጁን በጆሮ" እንዲሉ የምናውቀውን እውነታ መካድም መደበቅም አያስፈልግም።
መንግስታችን ይህን እውነት ለማስተባበል ከመሞከር ይልቅ የሕዝቡን ጥያቄ አዳምጦ መፍትሔ መስጠት ይኖርበታል። ለተወሰነ ጊዜ ሕዝብን በጅምላ እያሰሩ፤ እያዋከቡ፤ እየጨፈለቁ መቆየት ይቻላል። ሆኖም ግን ችግሩ የፈነዳ ቀን ለሁላችንም የማይበጅ አደጋ መከሰቱ አይቀርም። ይሄ ክፉ ምኞት ሳይሆን በተጨባጭ ብዙ አገሮች ውስጥ የተከሰተ እውነታ ነው።
የመንግስት ደጋፊዎችም ቢሆን በርካታ ሕዝብ በጅምላ ማሰር እና ማወከብ ትክክል አለመሆኑን በመጠየቅ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር አለባቹ። ነገ አገራችን ሱማሊያ ብትሆን የመጀመሪያው ተጎጂዎች እናንተ እንደምትሆኑ አትጠራጠሩ። አይናቹን ከፍታቹ ለመመልከት ሞክሩ እንጂ በገሃድ የሚታየውን እውነታ የኒዎሊበራሎች ጥላቻ፤ ወይም የስደተኞች ቅጥፈት በማለት መካድ ከሚመጣው ጥፋት አያድንም።
ልማት እያለማሁ ስለሆነ የፈለኩትን እገላለሁ፤ አስራለሁ ማለት አይቻልም። ሕዝብ ዝም ቢልም አያውቅም ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አሳሳች ባህሪይ አለው። ሃይለ ሥላሴ፤ ደርግ እና ኢህአዴግ (በምርጫ 97) ተመሳሳይ ስህተት ሰርተዋል። ሕዝቡ ዝም ስለሚል ተስማምቶታል ማለት አይደለም። ቀን ሲያገኝ ሙሉ ለሙሉ በገዢዎቹ ላይ እየተነሳ አሳይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እየታየ ያለው የጅምላ እስር የሚያሳየው የመንግስት ቅቡልነት (Legitimacy) እየተሸረሸረ መምጣቱን ነው። በአደጉት አገሮች እንደሚደረገው በነጻነት የሕዝብ አስተያየት (public opinion polls) የሚሰበስቡ ተቋማት ቢኖሩ የመንግስት ተቀባይነት ምን ያህል እንደወረደ መገንዘብ ይቻል ነበር። ሆኖም ግን ይህ ለእኛ አገር አይሰራም። ስለዚህ የሕዝብ አመጽ እንደ ምጽዓት በድንገት አለመከሰቱን ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም። በማስፈራራት ሺ አመት ከመግዛት በፍቅር እና በነጻነት አንድ አመት መግዛት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል። ጭቆና ለተገዢው ብቻ ሳይሆን ለገዢውም ሰቀቀን ነው።
መንግስታችን በሰቀቀን እንደሚኖር ለማወቅ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የሚያስራቸው ጋዜጠኞችን ብዛት መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደሚያመለክተው የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ18 መብለጡን ያመለክታል። በርካታ ጋዜጠኞች ተሰደው ወጥተዋል። የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ፌስ ቡክ ላይ በመጻፋቸው ብቻ ከስድስት ወር በላይ በወህኒ ተከርችመዋል።
መንግስት ሆይ እባክህ ልብ ግዛ። የሕዝቡን ቀይ መስመር አትለፍ።
ለሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ስጥ እላለሁ ... Because I am Oromo
No comments:
Post a Comment