Thursday, October 17, 2013

ከ25 አሳዛኝ ዓመታት የስደት ህይወት በኋላ አካል በማጣትና ሞት መሀል ያለውን የስደተኛውን ህይወት እንታደገው

በግሩም ተ/ሀይማኖት
ከ25 አሳዛኝ ዓመታት የስደት ህይወት በኋላ አካል በማጣትና ሞት መሀል መሰነግ
ከስደትም ስደት አስከፊውን የአረብ ሀገር ስደት…ከአረብ ሀገርም ስለየመን እናውራ ካልን ሰቅጣጭ እና መፈጠርን የሚያስጠላ ነው፡፡ እኔም ተደምሬ ችግሩን ተቸግሬ፣ አንብቼ አልፌዋለሁ፡፡ ግን ዛሬም እያየሁ እየቆሰልኩ፣ እያነባሁ መፈጠሬን ስረግም እኖራለሁ፡፡ ሁላችንም እንኖራለን፡፡
ይህም ስደት ነው።
የተሻለ ሳይሆን ብዙ ብዙ እውነት የማይመስሉ እውነቶች የተሰገጡበት ህይወት ነው በየመን ያለው። ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል ኮካኮላን ያስተረተው በየመን ያለ ሀበሻን ኑሮ ታይቶ ነው ማለት ይቻላል። በየመን ከሚኖረው በከፋ ሁኔታ የሚኖሩም አሉ፡፡ ሶማሊያ እና ጅቡቲም የሚኖሩ መኖራቸውን ሳትረሱ ማለት ነው።

ችግር የማይነቅለው የለም፡፡ችግር የማያሰድደው የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም ተሰዷል። ነብዩም ተሰደዋል። አረ ቆራጡ እና ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን ያሉት ኮረኔል መንግስቱም ተሰደዋል። እኛ ለስደት አዲስ አይደለንም። አለም ለስደት አዲስ እንዳልሆነ ሁሉ እኛም እየተሰደድን ነው። ተሰደናልም ገናም እንሰደዳለን። ሀበሻ በየመን እጅጉን አሰልቺ የሆነ ደግሞም ያልሆነ ዝብርቅርቅ ህይወት ከጥሩ ጎኑ መጥፎው ያመዘነበት ኑሮ መሀል ተሰንጎ ነው የሚኖረው። ኑሮ ከተባለ ማለት ነው፡፡ በዚህም ሰቅጣጭ ህይወት መካከልም ሳዛኑ ነገር በዝቶ ወጣል፡፡
አንዳንዴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው በመከራ የሚያሳልፉ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ለምን እላለሁ፡፡ እላለሁ እንጂ ምላሽ የለኝም፡፡ እኔም የዛው ምድብ ምድብተኛ፣ የገፈቱ ቀማሽ ነኝ፡፡ ያ-ሆነና የስደተኛውን ስቃይ እየየሁ ምጣቸውን እያማጥኩ፣ ቁስላቸውን ቆስዬ..መኖር ግድ ብሎኛል፡፡ አምጣለሁ፣ አለቅሳለሁ እንጂ ምንም ማድረግ የማልችል እጀ አጭር፣ ኪሰ ጠባብ ነኝ፡፡ ኪስ የማፍሰሱን፣ እጅ የማጠሩን ያህል ቀናትም ስንኩል ይሆናሉ? ከቀናትም ለእኔ የእሁድ ጥቅምት 3/ 2006 አልቀናኝም፡፡ የስደተኛውን ችግር መስማት፣ ማየት፣ አንብቶ ማለፍ..በዝቶ ነገሮች ግራ ባጋቡኝ ወቅት የእግር ኳስ ጨዎታ አይቼ በአጨዋወት ተደስቼ በውጤት ቆዝሜ ባለበት ሁኔታ አንድ ወዳጄ (ነጅብ የሚባል) ይማም ታሟል እባክህ አንድ ነገር እናድርግ ብሎ አማከረኝ፡፡
‹‹..አንድ ነገር…›› የሚለው ቃል ደጋግሞ በጆሮዬ አንቃጨለ፡፡ ሁሉ በአንድ ረድፍ ተሰልፎ አንድ አይነት ኑሮ በሚኖርበት፤ አንዱ ከአንዱ ባልተሸለበት ሁኔታ ምን እናደርግለት ይሆን? የሚለው ጥያቄ በውስጤ እያንጎዳጎድኩ ‹‹ምንድን ነው የሆነው? ምኑን ነው ያመመው?›› የሚለውን ጠየኩት፡፡ ቀደም ብሎ በስኳር በሽታ እንደሚሰቃይ አውቃለሁ፡፡ ኑሮ ክፍ ዝቅ ያላለለት ይማም በሽታውን መቋቋም አልቻለም፡፡ በፊት..በፊት ሀዳ የሚባለው አካባቢ አንድ ሆቴል ነበረው፡፡ ለታመመ፣ ለተቸገረ፣ በባህር ለመጣው ሁሉ ለስንቱ ኢትዮጵያዊ አብልቶ አጠጥቶ ነበር፡፡ ይማም ሀሰን እንድሪስ ለሰዎች ብዙ ነገርን ያድርግ እንጂ ለእሱ ጊዜ አለሁህ ያለው የለም ነበር፡፡ ስኳር በሽታው እንዲንከባከበው ይፈልጋል፡፡ ምግብ ይፈልጋል፡፡ ይሄ ደግሞ እቅም ይጠይቃል፡፡ ምንም የሌለው ሰርቶ ያገኛትን በልቶ ሲያጣም የሰው እጅ ጠብቆ የሚኖር ደግሞ እንዴት ይቋቋመዋል? ወደ የመን ከተሰደደ 25 አልፎታል፡፡ ከድሞው የባህር ኃይል አባሎች ጋር አብሮ ወደ የመን እንደገባ ነው የሰማሁት፡፡ ራሱን ባናገርኩት ወቅት ግን ቀድሞ ገብቶ እንደነበር ነው የነገረኝ፡፡
‹‹..ስኳር በሽታው ተነስቶበት ነው…›› አለኝ፡፡ ከወትሮው የተለየ አይደለም ስል አሰብኩ፡፡ ወዳጄ ነጅብ ግን ሲቀጥል ‹‹..ለካ ነገሩ ተደብቆ ሳንሰማ ብዙ ቀን ተኝቷል፡፡ እግሩ ቆስሎ መቆረጥ አለበት ተብሏል፡፡…›› አለኝ፡፡ በስመአብ…ስቀጠጠኝ፡፡ ተያያዝንና በሽተኛው ያለበት ቦታ ሄድን፡፡ ቦታ ስለሚባል ቦታ አልኩ እንጂ ቤት የሚባል ነገር የለውም፡፡ መርካቶ ቁጭራ ተራ እንጂ የመን ሰነዓ ከተማ ውስጥ ያለሁ አልመሰለኝም፡፡ እዚህ ውስጥ እንኳን በሽተኛ ጤነኛም ሊኖርበት የማይችል ቦታ ነው፡፡ ይማምን አስነስተን ህክምና ቦታ ይዘነው ከሄድን በኋላ ቁስሉን ሳይ ሰውነቴን ከላይ እስከ ታች ነዘረኝ፡፡ ጣቱ ቆስሎ ከሚለው አልፎ ጠቁሮ መፈርፈር ጀምሯል፡፡
ስንት አለህ? ስንት አለህ? እየተባባልን ሳንቲም አሰባስበን ጊዜያዊ ህክምናውን እና ምርመራውን አደረገ፡፡ ቁስለቱ ጋንግሪ ወደሚባለው በሽታ መቀየሩ እና እግሩ መቆረጥ እንዳለበት ተነገረ ግን በምናችን፡፡ 3500 ዶላር አካባቢ ነው ለህክምናው የሚያስፈልገው፡፡ ይህን ያህል ዶላር የመን ያለ ስደተኛ አብዛኛው አሰሪዎቹ ሲቆጥሩ ያየው ይሆናል እንጂ ከእጅ አይሻል ዶማ ኑሮ ነው የምንኖረው፡፡ ይህ ሰው በርካታ ስደተኞች ወገኖቹን ሲረዳ የኖረ ነውና ዛሬ እንታደገው፡፡ እባካችሁ ይህን ሰው ለማዳን ሁላችሁም የአቅማችሁን እርዱት፡፡ በተለይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ባልደረባዎች እና የመን የነበራችሁ ሌሎችም ወገኖች፡፡ ጋሽ ይማም ሀሰን እንድሪስን የምናከብረው የስደተኞች አባት ነውና እናድነው፡፡ በስደት ተንከራቶ መሞት ምን ያህል አስከፊ ነው እያንዳንዳችን እናስበው፡፡ ይህን ወገን ለማዳን እጃችሁን ለመዘርጋት የምትፈልጉ….
በስልክ ቁጥር 00967736471170 ደውሎ ነጅብ የተባለው ጓደኛውን ወይም ራሱ ይማም ሀሰን እንድሪስን 00967736416619 ያግኙት፡፡ ለሚያደርጉለት ትብብር በእግዚአብሄር ስም አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment