በሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)
ክፍል ሁለት
በቀደመዉ ጽሁፍ ሰበአዊ መብት ምን እንደ ሆነ እና እንዴት በአለም የፖለቲካ አስተምህሮቶችን ፈተና ዉስጥ እንደጣላቸዉ ከሞላ ጎደል ለመዳሰስ ሞክረናል:: በተለይም የሰበአዊ መብት አስተምህሮት አንዳንድ አንባገነን እና ብልጣብልጥ መንግስታት ልማታዊ መንግስት ነን በማለት ልማት የማህበረሰቡ ሰበአዊ መብት መሆኑን በመዘንጋት ልማት የእነሱ ብቻ አጀንዳ እንደሆነ በማስመሰል ጥቂት ልማት ስለሰራን ለዘላለም በወንበሩ ላይ እንኑር የሚለዉን ክርክራቸዉን የሰበአዊ መብት አስተምሮት እንዴት ዉሃ የማይቁዋጥር ክርክር እንዳደረገባቸዉ ለማዬት ሞክረን ነበር::
ይሄንኑ ጭብጥ ሳንለቅ ወደ ዋናዉ ጉዳይ እንዝለቅ:: በርከት ያሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት በአለም ላይ እጅግ በርካታ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች ቢኖሩም በዋናነት ጠቅለልና ሰብሰብ ተደርገዉ ቢገለጹ በአምስት ዋና ዋና ክፍል ሊመደቡ ይችላሉ ይላሉ:: እነዚህም አናርኪዝም (Anarchism): አብሶሉቲዝም (Absolutism) : ሊበራሊዝም (Liberalism) : ኮንሰርቫቲስዝም (Conservatism) : እና ሶሻሊዝም (Socialism) ናቸዉ ሲሉ ያብራራሉ:: በእነዚህ በያንዳኑ ዉስጥ በርካታ ክፍልፋይና የተወሰነ የመርህ ልዩነት የሚያራምዱ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ርዕዮት አለሞች አንዳሉ ሳንዘነጋ ውይይታችንን እንቀጥል::
እነዚህን አምስት የርዕዮት አለም አከፋፈሎች አዉርደዉና አቅጠነዉ በመጠቅለል በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ ያለዉን ተግባራዊ ርእዮተ አለም በሁለት ዘርፍ ብቻ የሚከፍሉዋቸዉም የፖለቲካ ተመራማሪዎችም አሉ:: ለምሳሌ የሀገራችን የፖለቲካ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሀይለየሱስ በትሬ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚለዉ መጽሃፋቸዉ ይህን ሁኔታ እንደሚከተለዉ ይገልጹታል “የምስራቆቹ ሶሻሊስት ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ እኩልነትን በመልካምነቱ ሲያቀነቅን የፖለቲካ እኩልነትን ግን በአምባገነንነት ይረግጣል::
በአንጻሩ የካፒታሊስቱ የምዕራባዉያን ዲሞክራሲ የፖለቲካ እኩልነትን በመልካምነቱ ሲንከባከብ የኢኮኖሚ እኩልነትን ግን በመንግስታዊ አምባገነንነቱ ይረግጣል:: ስለዚህ ሁለቱም ዲሞክራሲዎች እዉነቶች አይደሉም::” ሲሉ ያብራሩታል:: ይህ የአቶ ሀይለዬሱስ አባባል ሰፋ ተደርጎ ሲመነዘር ሁሉቱም ርዕዮተ አለሞች ሰበአዊ መብቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማህበረሰቡ ለማጎናጸፍ አልቻሉም ማለት ነዉ ተብሎ ሊፈታ ይችላል::
የአቶ ሀይለየሱስን አገላለጽ የሚደግፉላቸዉ የበርካታ ምሁራን እሰጥ እገባን ከሁለቱም ወገን ጠቅለል እያደረገን እነመልከት:: የሶሻሊስት ጽንሰ ሀሳብ አራማጅ ምሁራን ሊበራሊዝምን ሲተቹት እኩልነት : ነጻነት እና ዲሞክራሲያዊነት ተብሎ በሊበራሊስቶች የሚሰበከዉ ስብከት የዉሸትና የማስመሰል ነዉ ይላሉ:: ምንም እንኩዋን በወሬ ደረጃ እኩልነት ነጻነት : እና ዲሞክራሲያዊነት ቢባልም ጥቂት የገዥ መደብ አባላት እና ከእነርሱ ጋር በተዘዋዋሪ ቁርኝት ያላቸዉ ሀይሎች ሀብትንም : መንግስትንም የምርት ሀይሉንም ስለተቆጣጠሩት ብዙሃኑ ህዝብ እንደ መንግስተ ሰማያት ስብከት የሚሰበክለትን እኩልነት : ነጻነትና ዲሞክራሲያዊነት ከመስማት በዘለለ የሚጠቀምበት አይሆንም ሲሉ ይሞግታሉ::
አስከትለዉም በሊበራሊዝም የገበያ ነጻነት ተብሎ የሚለፈፈዉ ሁሉ ሀሰት ነዉ ምክንያቱም ገበያዉን የተቆጣጠረዉ የምርት ሀይሉን የተቆጣጠረዉ መደብ ስለሆነ ነዉ ሲሉ ይተቻሉ:: በመደምደሚያነትም ሊበራሊዝም ብዙሃኑን መጨቆኛ ስልት ስለሆነ የመደብ ትግል በማድረግ ሊበራሊስቶችን እና በሊበራል ስርአት ተጠቃሚ የሆኑትን ወገኖች መደምሰስ ወሳኝ ነዉ ሲሉ ይሰብካሉ:: በእነሱ አባባልም መኪናዉን መሰባበር ተብሎ ይገለጻል::
የሆነ ሆኖ በአንድ ወቅት ትንታኔዉ ዉስጥ ሌኒን ሳይቀር በሊበራሊዝም ዉስጥ የሚፈጠረዉ ብልጽግና የሰራተኛዉን መደብ በሂደት ተጠቃሚ ሊያደርገዉ እንደሚችል ከጠቆመ ብሁዋላ ሂደቱ ግን አዝጋሚና እጅግ ዉስብስብ ሊሆን እንደሚችል አብራርቶ ነበር:: በእርሱ አባባል ካፒታሊስቶች ኢኮኖሚዉን በስፋታ ማስፋፋት የቻሉ ጊዜ እና የገበያ እሤት ተዳራሽነቱ በስፋት ወደ ማህበረሰቡ መፍሰስ ሲጀምር የሰራተኛዉ መደብም ከሚፈጠረዉ የኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሚ ሊሆን ንደሚችል ሳይሸሽግ ካስረዳ ብሁዋላ ሂደቱ ግን አታካችና አሰልች ብሎም እዉን ለመሆን በርካታ እንቅፋቶች ሊኖርበት ስለሚችል የሶሻሊስት አቢዎቱን ማፋጠን ብቸኛዉ መፍተሄ መሆኑን አስረድቶ ነበር::
ከሌኒን ትንታኔም አንድ እዉነት መዞ ማዉጣት የሚቻለዉ የሊበራሊዝምን ሁለንተናዊ ማንነትና አዎንታዊ ገጽታ በዜሮ ማባዛትና መደምሰስ እንደማይቻል ነዉ:: ይህችን አዎንታዊ ሀሳብ መዞ ማዉጣት በሶሻሊዝም ፍልስፍና ፍቅር የተነደፉ ሰዎች ቢናደዱባትም አስምረንባት እንለፍ:: ሊበራሊዝም የራሱ አዎንታዊ ገጽታ እንዳለዉ ማለታችን ነው::
በተቃራኒዉም ሊበራሊስቶች ሶሻሊስቶችን በብዙ ሁኔታዎች ይከሳሉ:: ሊበራሊስቶች ሶሻሊዝም የፖለቲካ እኩልነትን በመግፈፍ የሰራተኛዉ መደብ የበላይነት በሚል ሽፋን የተለዬ አመለካከት ያላቸዉን ወገኖች ሁሉ ከምድረ ገጽ በመደምሰስ እና በማስወገድ የፖለቲካ እኩልነትን የሚደፍቅ የሀሳብ ነጻነትን የሚገፍ እና የዜጎች ተሳትፎን የሚገል ነዉ ሲሉ ይከሳሉ:: እንዲያዉም የማህበረሰብን አጠቃላይ መብት ገፋፊ ወሮ በላ ህሳቤ ሲሉ የከረረ ትችት የሚሰነዝሩበት አሉ:: ይህም ማለት አቶ ሀይለየሱስ የምስራቆቹ ሶሻሊስት ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ እኩልነትን በመልካምነቱ ያቀነቅናል የሚሉትን ሀሳብ ዉድቅ ያደርጉባቸዉና ሶሻሊዝም ተግባራዊ የሆነ የማህበረሰብ የኢኮኖሚ ድቀትን የሚሰብክ ነዉ ሲሉ ይደመድማሉ::
የሆኖ ሆኑ ዘመናት ባለፉ ቁጥር የተፈራቀቀዉን የርዕዮተ አለም አስተምህሮቶችን የመቆሚያ መሰረት ለማቀራረብ በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል:: በሂደትም አንዳድን ምሁራን በዘመናዊዉ አለም ዉስጥ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ብዙም መሰረታዊ ዋጋ የለዉም እስከማለት ሲደርሱ ይደመጣል:: ለምሳሌ በዴቪድ ሮቪኒስክ ጥናት መሰረት ከእንግዲህ ብሁዋላ በሶሻሊስታና በሊበራሊዝም መካከል የርዕዮተ አለም ልዩነት ቁም ነገርና መሰረታዊ ክፍተተ ሊሆን አይችልም ሲል ይደመድማል:: ጄኔቭ ቪዝ የሚባለዉም ጸሃፊ በዚህ ዘመን ያሉ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች ተመሳሳይ እየሆኑ የመጡበትን ሁኔታ ያብራራል::
ይህም ቢሆን እንኩዋንስ በመላዉ አለም በተሰራጩት ፖለቲከኞች ይቅርና በዲሞክርሲያዊነት መርህ ብቻ እንመራለን በሚሉትና በአንዲት አሜሪካ በሚኖሩ ፖለቲከኞች መካከል እንኩዋን የፖለቲካ ርዕዮታለም ልዩነቱ እንደ ዋና የፖለቲካ ስልጣን መጨበጫ/ መወጣጫ ተደርገዉ ቀጥሎዋል:: ሁለቱ አገሪቱን የሚዘዉሩዋት ዲሞክራቶች (ግራ ዘመም ሊበራሊዝም ማለትም ሰፋ ያለ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በማህበረ-ምጣኔ ሀብት ዘርፉ የሚያራምዱ ይመስላል) እንዲሁም ሪፐብሊካን (ቀኝ ዘመም ሊበራሊዝም እጅግ በጣም ዉስን የመንግስት ጣልቃ ገብነት በማህበረ-ምጣኔ ሀብት ዘርፉ የሚያማልላቸዉ ይመስላል) የሚካሰሱትም ሆነ የሚተቻቹት ብሎም የህዝባቸዉን ጆሮ ለማግኘት የሚሽቀዳደሙት በዚሁ የፖለቲካ ርዕዮተ አለማቸዉ ልዩነት መሆኑን ለመረዳት በኦባማና በተቃዋሚዎቻቸዉ መካከል ያለዉን ክርክር ማስተዋል በቂ ነዉ::
በአሁኑ ወቅት ሪፐብሊካኖች ፕሬዝዳንት ኦባማን ከሚከሱበት ዋና ማጠንጠኛ ነቅሰን ብናወጣ እንኩዋን ኦባማ ሊበራሊዝምን በሶሻሊዝም ቀየረዉ የሚልና ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ አለምን ወደ ምድረ አሜሪካ አመጣብን የሚል ክርክር ያነሳሉ:: በተለይም ለኮንሰርቫቲዝም ርዕዮተ አለም ከፍተኛ ፍቅር ያላቸዉ ሪፐብሊካኖች ማህበረሰብ ቀጣይ በሆነ መልክ ያለዉን እሴት የሚያስከብርበት ስርዓት ወሳኝ ነዉ ብለዉ ይከራከራሉ::
በተቃራኒዉ የሪፐብሊካንን ክርክር የጥቂት ሀብታም ነጮቹን የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስቀጠል የሚያገለግል አስተምህሮት ነዉ ሲሉ ዲሞክራቶች ይተቹታል::
የኦባማ ወገኖችና ዲሞክራቶች አንድ የሚያነሱዋት ተደጋጋሚ ነጥብ አለች:: እሱዋም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሂደት ዘርፉ ወስጥ መንግስት ጣልቃ ገብነት ካላደረገ አንደኛ ድሃ ያገሪቱ ዜጎች በብዙ ዘርፉ ይጎዳሉ እንዲሁም የሀገሪቱ አጠቃላይ ማህበራዊ ግስጋሴ ይገታል ሲሉ ያብራራሉ:: ይህን ሂደት እነሱ big government (ሰፋ ያለ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በማህበረ-ምጣኔ ሀብት ዘርፉ ) ሲሉ ይገልጹታል:: ለዚህም የፕሬዝዳንት ኦባማ መንግስት በጤናዉ ዘርፍ ዉስጥ የወሰደዉ ማህበራዊ ጣልቃገብነት ጥሩ ማሳያ ነዉ::
ፕሬዝዳንት ኦባማ በስፋት እንዳብራሩትና አሜሪካዉያንን ለማሳመን በስፋት እንደደከሙት ዋናዉ የዚህ ማህበራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነት ምንጩ የሚያጠነጥነዉ በርካታ አሜሪካዉያን በገንዘብ እጦት ጤናቸዉ ሳይጠበቅ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑ ነዉ:: በሰበአዊ መብት አስተምህሮት መርህም የፕረዝዳንት ኦባማን ትንታኔ ስንገልጸዉ አሜሪካ ዉስጥ በርካታ ዜጎች የሰበአዊ መብታቸዉ በማህበራዊዉ ዘርፍ አልተረጋገጠላቸዉምና በርካታ ስራ ይጠብቃል ማለት ነዉ::
እዚህ ጋ ልብ ልንል የሚገባዉ በተቃራኒዉ ሪፐብሊካኖች ይሄን እዉነት ሽምጥጥ አድርገዉ ክደዉ ችግሩ አሳሳቢ አይደለም :: ማህበራዊ ጣልቃ ገብነቱም አስፈላጊ አይደለም ሲሉ መከራከራቸዉ ነዉ:: እነዚህ ሪፐብሊካኖች እንደሚያብራሩት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ መንግስት ጣልቃ መግባት የለበትም (በእነሱ አገላለጽ እጅግ ዉስን የመንግስት ጣልቃ ገብነት በማህበረ-ምጣኔ ሀብት ዘርፉ ወይም samll government ያስፈልጋል) የሚል አቁዋም አላቸዉ:: በእነሱ ትንታኔ መሰረትም ነጻዉ የገበያ ስርዓት በራሱ ችግሩን ይፈታዋል:: ይህ የሚሆነዉ ደግሞ መንግስት በማህበራዊ ዘርፉ ዉስጥ በምንም መልኩ ጣልቃ ሳይገባ ሲቀር ነዉ::
እነደሚታወቀዉ መንግስት በምንም መልኩ በኢኮኖሚዉና በማህበራዊ ዘርፉ ዉስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለዉን የሊበራሊስቶች መሰረታዊ ህሳቤ ከመነሻዉ ያራመደዉ ኢኮኖሚስቱ አዳም ስሚዝ ነበር:: በተቃራኒዉ መንግስት በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ዉስጥ በዋናናነትና በብቸኝነት ጣልቃ ገብቶ መዘወር አለበት የሚለዉን ህሳቤ ያራመደዉ ማርክስ ነበር::
በሂደት የሁለቱ ሰዎች ሀሳብ በሁለት ጽፈኛ ጠርዝ ላይ መቆሙን ምሁራን እየተረዱ ሲመጡ ሁለቱን ጽንፈኛ ሀሳቦች ለማዳቀልና ማእከላዊ ሀሳብ እንዲወለድ ለማድረግ በማሰብ ካር-አዳም (ማርክስ-ስሚዝ) የሚል ህሳቤን ይዘዉ መጥተዋል:: ይህም ማለት በባህሪዉ አንድ ጠርዝ ላይ ያልቆመ ህሳቤን ለማራመድ የሚያመች ሁኔታን ፈጥሮአለ:: በዚህና በሌሎችም ምክንያት አንዳንድ ምሁራን የሶሻሊስትና የሊበራሊስት ወሰን እና ድንበር ባልታወቀበት ሁኔታ ስለ ርዕዮተ አለም ልዩነት ማዉራት አግባብ አይደለም ይላሉ ::
እዚህ ጋ የህንድን ምሳሌን ማምጣቱ ጥሩ ነዉ:: ህንድ በአንድ ወቅት ሶሻሊስትን ተቀብያለሁ ያለች ሀገር ነበረች:: በሂደት ግን አካሄዱዋን እያጠናችና እየከለሰች አሁን የኢኮኖሚ ዘርፉዋን የምትመራዉ ካር-አዳም (ማርክስ-ስሚዝ) የሚለዉን ህሳቤ አቀናጅታ ይመስላል:: የኢኮኖሚ ዘርፉን በሶስት በመክፈል መንግስት ብቻ የሚገባበት: ግለሰብ ብቻ የሚገባበት እንዲሁም ግለሰብና መንግስት በቅንጅት የሚገባበት በማለት ከፋፍላቸዋለች:: ይህ የኢኮኖሚ ዘርፉን አከፋፈል ሙከራ የሚያሳዬን ህንድ ሶሻሊስታዊም ሆነ ካፒታሊስታዊ ጽንፍ ላይ ከመንጠልጠል ማዳቀሉ ይሻላል ወደሚል ህሳቤ መራመዱዋን ነዉ::
ይህም ሆኖ ግን በህንድ የማህበረሰቡ ሰበአዊ መብቶች በሙሉ ተመልሰዋል ማለት አይደለም:: ገና በርካታ ፈተናዎች አሉባት:: ማሳዬት የተፈለገዉ ግን ሀገራት የሚያደርጉዋቸዉን ልዩ ልዩ ጥረቶች ብሎም የሰበአዊ መብት የሆነዉን ልማት ለማፋጠን እንዴት እየሰሩ እንዳሉ ማስገንዘብ ነዉ::
ሊተኮርበት የሚገባዉ ነጥብ የትኛዉ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ነዉ ትክክል የሚለዉ ነጥብ አይደለም:: እያንዳንዱ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ከሰበአዊ መብት አስተምሮት አንጻር ሲቃኝ ምን ያህል የሰበአዊ መብት አስተምህሮትን ይመልሳል የሚለዉ ነጥብ ነዉ:: ፕሬዝዳንት ኦባማ እንዳብራሩትና የሰበአዊ መብት አስተምህሮትም አስረግጦ እንደሚያብራራዉ ዜጎች በሃገራቸዉ የጤና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አለባቸዉ::
አሜሪካ ይህን የዜጎች ሰበአዊ መብት ተግባራዊ ለማድረግ በቂ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ዜጎቹዋ ግን ያንን አገልግሎት ሳያገኙ ኖረዋል:: የዚህም ዋና ምክንያቱ ቀኝ ዘመም ሊበራሊስቶች በአንድ ጽንፍ ላይ ብቻ ቆመዉ ፖለቲካዉን በቀኝ ዘመም ሊበራሊስት ህሳቤ ብቻ ስለዘዎሩት ነዉ:: ፕሬዝዳንት ኦባማ ወደ መንበረ ስልጣኑ እስኪመጡ ድረስ ይህ የጤና ችግር የማህበረሰቡ የሰበአዊ መብት ጉዳይ መሆኑን አሜሪካዉያን በገሃድ ለማወጅ ተቸግረዉ ነበር ማለት ነዉ::
የሆኖ ሆኖ በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንቱ ይሄን የጤና አገልግሎት ለድሆችና አቅም ለሌላቸዉ ለማድረስ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ወሳኝ ነዉ ማለታቸዉን ሊበራሊዝምን መናድ : የአሜሪካን እሴት መሸርሸር ነዉ በማለት የሚቃዎሙት ሪፐብሊካኖች ወደፊት በዚህ በፕሬዝዳንቱ ዉሳኔ (የጤና ህግ ላይ) ምን አይነት እርምጃ ሊወስዱ ይችሉ ይሆን የሚለዉ እንዳለ ይሁንን እና ማሳረጊያ ነጥባችን ግን አሜሪካ አሁንም ቢሆን ሁሉንም የሰበአዊ መብቶ ለዜጎቹዋ የመለሰች ሀገር እንዳይደለች ጥሩ ማሳያ ነዉ::
አንባቢ ከዚህ ጽሁፍ እንዲጨብጠዉ የሚፈለገዉ ዋናዉ ነጥብ አንድ ነዉ:: ይሄዉም በቀደመዉ ጽሁፍ ዉስጥ በሰበአዊ መብት አስተምህሮት ስር በስፋት የተተነተኑትን በርካታ የሰበአዊ መብቶች ሊበራሊስቶችም ሆኑ ሶሻሊስቶች ሊመልሱዋቸዉ ስላልቻሉ ከፍተኛ የሆነ የመሳሳብና ማዕከላዊ ነጥብን የመፈለግ ሁኔታ በምሁራኖች ዘንድ ቢኖርም አሁንም በሶሻሊስትና በሊበራሊስት መስመር ላይ ድርቅ ብለዉ የቆሙ በርካታ መንግስታትና ሀገራትም መኖራቸዉን አብሮ ልብ ማለት ይገባል የሚል ነዉ:: በዚህም ሂደትም ዉስጥ አንድ ጥያቄ ይጫራል:: ይሄዉም የትኛዉ አማካይ መስመር ላይ ተሳስቦ መቆም ቢቻል ነዉ ከሶሻሊስትና ከሊበራሊዝም ተዉጣጥቶ የሚወለድ ህሳቤ በሙሉ የሰበአዊ መብቶችን የሚመልሳቸዉ የሚለዉ ነጥብ ነዉ:: ይህ ጥያቄ ግን ቀላል አይደለም::
የዚህ ጽሁፍም ተዛማጅ አላማ በአንዲት ሀገር የሚመሰረት አንድ መንግስት የመጀመሪያዉ እና ዋናዉ ስራዉ የሰበአዊ መብትን እንዴት መመለስ እንደሚችል ጥናትና ምርምር ማድረግ ነዉና ለሀገራችን ፖለቲከኞች የሀሳብ ብልጭታን መፈንጠቅ ጭምር ነዉ:: እንደሚታወቀዉ በአሁኑ ወቅት በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ርዕዮት አለማችን ሊበራሊዝም ነዉ ሲሉ ይደመጣሉ:: ሊበራሊዝም ሁሉንም የሰበአዊ መብቶችን እንደማይመልሳቸዉ ግን ማብራሪያ ሲጠየቁ ሌላዉ አለም የሰለጠነዉ በሊበራሊዝም ነዉ ብለዉ ደምሳሳ መልስ ይመልሳሉ::
ይህ አይነት የነጭ ወይ ጥቁር ፖለቲካዊ አካሄድ ግን ወደፊት ለሚታሰቡ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሂደቶች ጥሩ አይመስልም:: ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ በርካታ ምርምርና ጥናቶችን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አብሮ መጠቆሙም የዚህ ጽሁፍ ትንሹዋ ስራም ነች:: የማህበረሰብ : የመንግስት : የቡድኖች እንዲሁም የግለሰቦች የጋራ ግንኙነት መሰረት የሚቆመዉ በሰበአዊ መብት የህግ ህሳቤዎች ላይ ተነተርሶ ነዉ::
የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ህሳቤዎች ለምን በሰበአዊ መብት አስተምህሮት መነጽር ሊቃኙ ይገባል የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ አካልም መልሱ አጭር ነዉ:: የማህበረሰብ : የመንግስት : የቡድኖች እንዲሁም የግለሰቦች የጋራ ግንኙነት መሰረት የሚቆመዉ በሰበአዊ መብት የህግ ህሳቤዎች ላይ ተነተርሶ በመሆኑ ሰበአዊ መብት በአንዲት ሀገር ዉስጥ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሰረት ብሎም ምሰሶና ዋልታ በመሆኑ ነዉ::
No comments:
Post a Comment