ዓለም በሰለጠነችበትና በዘመነችበት ሰዓት የኢትዮጵያን ሁኔታ ስመለከት ይህንን ፅሑፍ እንድከትብ አነሳሳኝ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ መንግሥት ምን እያደረገ ነው መካሪስ የለውም እንዴ ብዬ እንድጠይቅ አስገደደኝ፡፡ ይህን ያስባለኝ ምክንያት ሰሞኑን በተደጋጋሚ ሁኔታ በሰማያዊ አባላት ላይ እየደረሰ ያለው ህገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡
ከዚህ በፊት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. እሁድ ቀን ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም በዋዜማው ቅዳሜ ነሐሴ 25 ከምሽቱ 12፡30 አካባቢ የፌደራል ፖሊስ፣ የደህንነት አባላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ በመተባበር የፓርቲውን ቢሮ ሰብሮ በመግባት አባላቱን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እንነጋገር በማለት ወደተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በመውሰድ ኢሰብዓዊ የሆነ ድብደባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደፈፀሙበን ይታወቃል፡፡ በማግስቱም ኢህአዴግ ሆን ብሎ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ቦታ የሃይማኖት አክራሪነትን እናውግዝ በማለት በሃይማኖት ሽፋን ሰልፍ እንደጠራ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ከዚህ በፊት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. እሁድ ቀን ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም በዋዜማው ቅዳሜ ነሐሴ 25 ከምሽቱ 12፡30 አካባቢ የፌደራል ፖሊስ፣ የደህንነት አባላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ በመተባበር የፓርቲውን ቢሮ ሰብሮ በመግባት አባላቱን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እንነጋገር በማለት ወደተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በመውሰድ ኢሰብዓዊ የሆነ ድብደባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደፈፀሙበን ይታወቃል፡፡ በማግስቱም ኢህአዴግ ሆን ብሎ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ቦታ የሃይማኖት አክራሪነትን እናውግዝ በማለት በሃይማኖት ሽፋን ሰልፍ እንደጠራ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የደረሰብን ግፍ ትግላችንን ከፍ አድርገን አቋማችንን ሳንቀይር መብታችንን ተጠቅመን መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ሰልፍ ለማድረግ አዲስ አበባ መስተዳድር የእውቅና ደብዳቤ ያስገባን ሲሆንም የተሰጠን ምላሽ መስቀል አደባባይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደማይፈቀድ በግልፅ አሳውቀውናል፡፡ ይልቁንም ሰልፉን በጃንሜዳ እንድናካሂድላቸው ወትውተውናል፡፡ እስካሁን በሀገሪቱ በወጡ ምንም አዋጆች ላይ አደባባዩች የኢህአዴግ የግል ንብረት መሆናቸው አልተደነገገም፡፡ ሊደነገግም አይችልም፡፡ አደባባዩች የሕዝብ ናቸው ብለን በማመን በእለቱ መነሻችንን ግንፍሌ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በማድረግ ወደ መስቀል አደባባይ ጉዞ ለማድረግ መንገድ ስንጀምር የታጠቁ የፖሊስ ኃይሎች መንገድ በመዝጋት ማለፍ እንደማንችል ስላስጠነቀቁን በጽ/ቤታችን አቅራቢያ ላይ ጥያቄዎቻችንን አቅርበን ለመግባት ተገደናል፡፡ በወቅቱ ብዙዎቻችንን ያሳሰበንና የተወያየንበት ነገር "ዛሬ የሰማያዊ አባላት ስለሆንን አደባባይ እንዳንወጣ ተከልክለናል፡፡ ነገ ደግሞ በጐዳናዎች ላይ መንቀሳቀስ ሊከለክሉን ይችሉ ይሆናል የሚል ነበር፡፡" ያልነውም አልቀረም የሰማያዊ አባላት ስለሆንን ብቻ በመንገድ ስንሄድ ስላገኙን ለሦስት ቀናት አስረውን ለቀውናል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡ አሁን መንግሥት በሰማያዊ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና በትንሹ ለሕዝብ ለማሳወቅ እሞክራለሁ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት አሁን የሚገኘው አራት ኪሎ ግንፍሌ አካባቢ ቢሆንም የቤቱ ባለቤት እንድንለቅ ካሳሰበን ወራቶችን አሳልፈናል፡፡ ይበልጡንም ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ካደረግነው ሰልፍ በኋላ የልቀቁልኝ አቤቱታው ይበልጥ ተባብሷል፡፡ ይህ ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ ከመጣ በኋላ የአከራዩ የልቀቁልኝ አቤቱታ መጨመር ከኋላው የሚገፋው ኃይል እንዳለ ለመገመት ተገደናል፡፡ በዚህም ምክንያት መነን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚከራይ ቤት ስላገኘን የቤቱ ባለቤትም ቤታቸውን ለፓርቲው ለማከራየት ፈቃደኛ ሆነው በመገኘታቸው አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅመን ከጥቅምት 01 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ቤቱን ለመጠቀም ውል ተፈራረምን፡፡ በውላችን መሠረትም መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ቁልፍ ለመረከብ ወደ ተከራየነው ቤት ስንሄድ ያጋጠመን ነገር በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ በሩ ላይ ወሄነት ፔንሲዮን በቅርብ ቀን ሥራ ይጀምራል የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎበታል፡፡ ባየነዉም ነገር ተገርመን ለቤቱ ባለቤት ስንደውልላቸው ስልካቸው አይሰራም፡፡ የውጩ በር ክፍት ስለነበረ ከፍተን ገባን፤ የፔንሲዮኑ ባለቤት ነኝ የሚል ግለሰብ ቤቱን መከራየቱን በመግለፅ በመሳደብና በማመናጨቅ ከቤቱ እንድንወጣ ቢያዘንም እኛ ተረጋግተን ጉዳዩን ለማስረዳት ስንሞክር፣ ሰውየው ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ለስድብ የቸኮለ በመሆኑ መሳደብ ጀመረ፡፡ ተከራይ ነኝ ባዩ ግለሰብ አቶ በላቸው የሚባል ሲሆን፣ አሁን ከተከራየንበት ቤት በስተጀርባ ወሄነት ባርና ሬቶራንት የሚል ንግድ ቤት አለው፡፡ ይህም ቤት የአካባቢው የቀበሌ ሰዎችና ካድሬዎች መሰብሰቢያ ቤት ነው፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደደረሰን መረጃ ከሆነ የአካባቢው የወረዳ ጽ/ቤት በሚያዘጋጀው ማንኛውም ዓይነት ድግስ ላይ የመጠጥና የምግብ አገልግሎት የሚያቀርበው ይህ ግለሰብ መሆኑን ነው፡፡
እኛም የተዋዋልንበትን ውል ለግለሰቡ በማሳየት የተገኘነው ቁልፍ ለመረከብ እንደሆነ ለማስረዳት ብንሞክርም ከእኔ በላይ ሰው የለም ባይ ነውና የተማመነውን ተማምኖ ለአነጋገሩ እንኳን ምንም ጥንቃቄ አልነበረውም፡፡ ከግቢው በመውጣትም ከአካባቢው ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰኑ ፖሊሶችን ይዞ መጣ፡፡ ፖሊሶቹም ለእሱ በማድላት የእኛን ጉዳይ ለመስማት ፈፅመው ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ በሁለታችንም እጅ ላይ የተከራይ ውል ስለነበረ እኛም ቤቱ የእኛ ነው ስንል እርሱም የእኔ ነው ይል ሲል ስለነበረ መግባባት አልተቻለም ነበር፡፡ ስለሆነም ፖሊሶቹ ሁላችንንም ይዘው በአካባቢው ወደሚገኘው መነን ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ለማስማማት የሞከሩ ቢሆንም ምንም መፍትሄ ሳይገኝ ወደ ተከራየነው ቤት ስንመለስ በር ላይ የግንባታ መሳሪያዎች ተገልብጠው በማግኘታችን ፖሊሶቹን እንዲያስቆሙልን ብንጠይቅም፤ ሰሚ አላገኘንም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሦስት ቀናት ከተጉላላን በኋላ ቅዳሜ ጥቅምት 02 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ተከራየነው ቤት ተሰባስበን ስንሄድ አቶ በላቸው በማን አለብኝነት ስሜት የዘረገፈውን የግንባታ እቃ ወደ ግቢው ውስጥ አስገብቶ አግኝተነዋል፡፡ እኛም ወደ አዲሱ ቢሮአችን በመግባት እየተፈፀመብን ባለው ነገር አዝነን በመወያየት ላይ እያለን፤ የአካባቢው ፖሊሶች፣ የወረዳ 3 ሊቀ መንበር፣ የጉለሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ ኃላፊና የወረዳው ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የተወሰኑ ካድሬዎችን ጨምረው ወደ ግቢው የገቡ ሲሆን፣ ሊቀመንበ ስለ ጉዳዮ ሊያስረዳቸው ሲሞክር በማመናጨቅና በማስፈራራት ለመስማት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን አሳይተውናል፡፡ የእኛ ጥያቄ ሁለታችንም እጅ ላይ ውል ስለሚገኝ መስማማት ስለማንችል ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ ቤቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል ነበር፡፡ ግለሰቡ ግን ቤቱ የእኔ ነው እነሱ ሌቦች ናቸው ሊዘርፉኝ ነው ይውጡልኝ ነበር የሚለው፡፡ በማሂንድራ መኪና በሩ ላይ የመጡ ፖሊሶች ይሁኑ ደህንነቶች ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች ካሜራ ደግነው በመቆም ሲቀርፁ የነበረ ሲሆን፣ ፖሊሶቹ ማንም እንዳይወጣና እንዳይገባ ለሰዓታት አግተው በመያዝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እንነጋገር ያሉ ቢሆንም ከዚህ በፊት ሄደን እንነጋር በማለት የፈፀሙብንን በማስታወስ ለመሄድ ፍቃደኛ ባለመሆናችን ከግቢው እንድንወጣ አዘዙን፡፡ ሆናም ግን ወንጀለኞች ናችሁ የምትሉን ከሆነ አስራችሁ ውሰዱን እንጂ ከተከራየንበት ቤታችን አንወጣም ብለን አቋማችንን ስናሳውቃቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ ቤቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውል ስላሳወቁን አመስግነን ከግቢው በመውጣት ላይ ሳለን ንብረታችንን ይዘን እንድንወጣ በማዘዛቸው ይዘናቸው የነበሩ ባነሮችንና ዓርማዎቻችንን ይዘን ወጥተናል፡፡
በመሆኑም ይዘናቸው የመጣናቸውን ወደ ቀድሞ ቢሮአችን ለማስቀመጥ ይዘናቸው በመጓዝ ላይ እንዳለን ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ስናልፍ በጣቢያው በር ላይ የነበሩ ፖሊሶች ሰማያዊዎች አለፉ ብለው በማስቆም ወደ ጣቢያ ውስጥ እንድንገባ በመሳደብና በማንጓጠጥ ሰብዓዊ ክብራችንን በመንካት 2 ሴቶችና 6 ወንዶችን አስገብተውናል፡፡ በፖሊሶች ተከበን ወደ ውስጥ በመግባት ላይ እንዳለን አንዲት ኢንስፔክተር ማዕረግ የለጠፈች ፖሊስ እናንተ ለምን የማይገፋ ተራራ ትገፋላችሁ ያለችን ሲሆን ይህችው ኢንስፔክተር ከዚህ በፊት በታሰርን ጊዜ እነዚህ የኢህአፓን ጊዜ ሊመልሱት ነው፡፡ ሁሉም ወጣቶችና የተማሩ ናቸው፡፡ ለነዚህ መድኃኒቱ ደርግ ነበር፡፡ እያለች ስትሳለቅብን የነበረች ናት፡፡ ሌላዋም ሴት ፖሊስ እንዲሁ መጣና በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ በማለት የአለቃዋን ፈለግ ተከትላ ተናግራናለች፡፡ በጣም የሚገርመው ፖሊሶቹ ታዘው እንጂ እኛን ጠልተው የሚናገሩን አይመስለኝም ነበር፡፡ ሆኖም ግን የተመለከትኩት ነገር ፍፁም ጥላቻ እንዳለባቸውና እኛ ስልጣን ስንይዝ እንጀራቸውን የሚያጡ በሚመስላቸው አስተሳሰብ ውስጥ እንደሚገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም የተያዝንበትን ነገር እንኳን ሳያጣሩ በስድብና በማመናጨቅ ያጣድፉን ስለነበረ ነው፡፡ ያልተረዱትና ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር ፓርቲው ውስጥ ያለነው ወጣቶች ሁላችንም መብትና ግዴታችንን ጠንቅቀን የምናውቅ ህገ ወጥነትን የምንቃወምና ለህግ የበላይነት የምንሰራ ብሎም ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት የምንታገል፡፡ የገባንለትንም ዓላማ ለመፈፀም እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ መስዋዕትነትን ለመክፈል የቆረጥን ስለሆንን የነሱ ስድብ፣ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ድብደባ ወደኋላ እንደማይመልሰን ነው፡፡
ከተወሰኑ ፖሊሶች ጋር ለመነጋገር ስንሞክር ጥፋተኞች ናችሁ ያሉን ሲሆን፣ ጥፋተኛ አለመሆናችንንና እየተንቀሳቀስን ያለነው መብታችንን ተጠቅመን መሆኑን በማስረጃ አስደግፈን ምዕራፍና አንቀጽ ጠቅሰን ስንነግራቸው ያን ያህል እንኳን የህግ እውቀት የለንም ግን እንደሱ አይመስለንም ነበር መልሳቸው፡፡ ምንም ዓይነት ቃል መተንፈስ አንችልም ነበር፡፡ የጣቢያው ዋና አዛዥ የሆነው ፖሊስ በጣም እየተቆጣ አሁን በእኔ ቁጥጥር ሥር ናችሁ፡፡ የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ፡፡ ሲል ሌላው ደግሞ ይነሳና እልህ አታስገቡን ምንም አታመጡም ዞር አድረገን መደብደብ እንችላለን፡፡ ዝም ስንላችሁ ህግ የሌለ መሰላችሁ እንዴ አለን፡፡ በጣም የገረመኝ የእኛ ሀገር ህግ ከወረቀት አልፎ መቼ ወደ ተግባር እንደሚለወጥ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ ስለወንጀለኛ አያያዝ የደነገገው ህግ አለ፡፡ ሆኖም እንዴት አንድ ፖሊስ ህግ አለ እያለ እንዴት ስለድብደባ ያወራል? ይህ ሁሉ የደረሰብን በጐዳና ላይ ስንጓዝ ነው፡፡ የሁላችንንም ሞባይል ከተቀበሉን በኋላ ለቤተሰቦቻችን መያዛችን እንድናሳውቅ እንኳን አልተፈቀደልንም ነበር፡፡ የአንድ ሰውን አድራሻ ለአምስት ለስድስት ያህል ጊዜ ይቀበሉ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ የወረቀትና የእስክርቢቶ ብክነት ለምን አስፈለገ? አንዴስ ከተቀበሉ አይበቃም ነበር? ይህ የሚያሳየው ምን ያህል በሕዝብ ገንዘብ ላይ እንደሚቀልዱ ነው፡፡ ንብረታችንን በሙሉ ከተረከቡን በኋላ ወደ ወረዳ 9 እስር ቤት ለመሄድ ብርድ ላይ በመሆን መኪና ስላልነበራቸው መጠበቅ ያዝን፡፡ ከለሊቱ 5 ሰዓት አካባቢ ወንዶቹን እዛው ግቢው ውስጥ ወደ ሚገኝ ማረፊያ ቤት አስገብተዋቸው ሴቶቹን ውጭ ብርድ ላይ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ድረስ እንድንቀመጥ አደረጉን፡፡ 8 ሰዓት ላይ መኪናቸው ስለመጣ ወንዶቹን ከረፉበት በማስወጣት ሁላችንንም ወደ ወረዳ 9 እስር ቤት ወሰዱን፡፡
የወረዳ 9 እስር ቤት 5 ክፍሎች አሉት፡፡ አራቱ የወንዶች ሲሆን አንዱ የሴቶች ነው፡፡ በወንዶች ክፍል በአማካኝ ከ30 – 40 ሰው ሊታጐርበት የሚችል ነው፡፡ ሴቶቹ ጋር ግን ብዙ እስረኛ ስለሌለ ከ15 በልጦ አያውቅም የሚል መረጃን አግኝቻለሁ፡፡ ግቢው ደግሞ እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ እስረኛ መጠቀሚያ የተዘጋጀው ሁለት ሽንት ቤትና አንድ ሻወር ብቻ ነው፡፡ የሴቶቹና የወንዶቹ ግቢ የሚለየው ሊወድቅ በደረሰ አሮጌ ቆርቆሮ ሲሆን፣ በውስጡም የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ገመድ ስንገባ ከተወሰደብን የጫማ ማሰሪያ በላይ የሰውን ህይወት በሰከንድ ውስጥ ሊያጠፋ የሚችልና ተዘባትሎና ለሰው ቁመት ቀርቦ ነው፡፡ የእስረኞች አያያዝ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ነው ብሎ እስካልፈረደበት ድረስ ወንጀለኛ ብሎ መጥራት በህግ ቢያስቀጣም እዚህ እስር ቤት ያሉ ታሳሪዎች በሙሉ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያልተቋጨ ቢሆንም ፖሊሶቹ ግን ተጠርጣሪዎቹን በስማቸው ከመጥራት ይልቅ ወንጀለኛና ሌባ በማለት መጥራት ይቀላቸዋል፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው፡፡ ነገር ግን ፖሊሶቹ ከለሊቱ 5 ሰዓት በኋላ የእስር ቤቱን በር በማንኳኳት ሲጋራ የሚፈልግ በማለት አንድ ሲጋራን በ20 ብር ይሸጣሉ፡፡ ሞባይል የሚፈልግ በማለት አስገብተው በደቂቃ በ10 ብር ያስደውላሉ፡፡ እዛ ግቢ ውስጥ ብር ካለ የማይገባ ነገር የለም ይባላል፡፡
አስገራሚውና አስደናቂው ነገር ደግሞ የጠዋቱ ተረኛ ፖሊስ የሲጋራው ቁሩ ወድቆ ሲያይ ማነው ያጨሰው አውጡ በማለት የሚደርስባቸው የዱላ ውርጅብኝ አይጣል ነው፡፡ ከሌላው እስረኛ ገለል አድረገው መቅጣት ቢኖርባቸውም ማን አለብኝነት ስሜት አደባባይ ላይ ሌሎቹ እስረኞች ይቆለፍባቸውና ሲጋራ አጨሰ የተባለው ልጅ ይወጣል፡፡ ከዚያም ድብደባው የሚጀመር ሲሆን ይህንን ትርኢት መመልከት የሚፈልግ በመስኮት ይከታተላል፡፡ ከአጣና አነስ ከመጥረጊያ ወፈር በሚል እንጨት እራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ ይደበደባሉ፡፡ ሲደክሙ ደግሞ በባልዲ ውሃ አምጥተው ይደፉባቸዋል፡፡ ይህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ደግሞ የተለመደ የእስር ቤቱ የእለት ተዕለት ተግባር ነው፡፡
አንድ ታሳሪ በፖሊሶቹ ድብደባ ምክንያት ሽባ የሆነ ሲሆን፣ እኛ ተፈተን ስንወጣ ልጁ ወደ ህክምና ለመሄድ ወጥቶ አግኝተነው የጠየቅነው ሲሆን፣ የሰጠን ምላሽም እዚህ እስር ቤት ሲገባ ጤነኛ እንደነበረና በፖሊሶቹ ድብደባ ምክንያት አሁን በእግሩ ቆሞ መሄድ እንደማይችልና ለመቆም ሲሞክርም እግሩ ተብረክርኮ እንደሚወድቅ ነው፡፡ ይህ ልጅ መታሰሩን የሚያውቅ ጠያቂ ዘመድ የለውም፡፡ አንድ ነገር ቢደርስበት ጠያቂውና ተጠያቂው ማን ነው? በሦስት ቀን የወረዳ 9 ቆይታችን ብዙ ነገር ታዝበን ወጥተናል፡፡ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም፤ አሳሳቢና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ ያመንኩበትን ሕዝብ እንዲያውቀውና መፍትሄ እንድንፈልግለት ከልብ በመነጨ ሀዘን ለንባብ አቅርቤዋለሁ፡፡ ይህንን ድርጊታቸውንም ሕዝብና ፈጣሪ እንዲፋረዳቸው የዘወትር ፀሎቴ ነው፡፡
በመጨረሻም ለፖሊሶቹ የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ፖሊስ የሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሀገር ቋሚ ነው፡፡ የፖሊስ ተግባር ህገ-መንግሥቱን ማስከበርና ለሰላም ዘብ መቆም እንጂ ከገዥው ፓርቲ ጐን በመቆም ሕዝብን ማሰቃየት አይደለም፡፡ ለምትፈፅሙት ተግባር ሁሉ ነግ በእኔን ብታስቡ መልካም ነው፡፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና እናገናዝብ፡፡ በቀጣዩ ፅሑፌ አፈታታችንንና የፍርድ ቤት ውሎአችንን ይዤ እቀርባለሁ፡፡ እስከዛው ቸር እንሰንብት፡፡
እየሩሳሌም ተስፋው
ከሰማያዊ ፓርቲ
No comments:
Post a Comment