Tuesday, October 29, 2013

ንጉሠ ነገሥት አብርሃም ያዬህ ሆይ! መፍትሔው ይሄው ነው በቃ?

ይሄይስ አእምሮ
“የአፄ አብርሃም ያዬህን ጽሑፍ አንብበን ስንጨረስ ነገር ማብላላታችንን ትተን ዝም ብለን መጋደም አልቻልንም፡፡ ዘመናችን ብዙ የሚሠራበት ሣይሆን ብዙ የሚወራበትና የሚጻፍበት መሆኑን እናውቃለንና አግራሞታችን ወሰን አልነበረውም፡፡ ጥሎብን “ሌላ ሥራ የላቸውም ወይ?” እስክንባል ድረስ በዬቀኑ ብዙ እናነ(ብ)ባለን፤ ስለዚህም ሲሆን በምታዘበው ሁሉ እናነባለን፡፡ ሕዝባችንን የሚጠቅም ነገር ለማከናውን የዛሬ አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ ብዙ ብንጥርም የአማራ ኤሊቶች እያወኩን ጥረታችን ስንዝር ሳይራመድ ተኮላሽቶ እንዲቀር አደረጉብን፡፡ ያዘጋጀነው በመቶ ሺዎች የሚገመት ዘመናዊ ጦርም ሳይዋጋ ወደየመጣበት ተበተነብን፡፡ አሁን ደግሞ እነሙሉጌታ ሉሌ ትናንት እንዳልሰደቡን አሁን ደግሞ እኛን ተመሳሰሉና ለነአንትና እየሰገዱ አስደሰቱን፤ በሣቅም ፈጁን፡፡
አማርኛችን በጣም መሻሻሉን ወዳጆቻችን ስለጠቆሙን በጣም ተኩራርተናል፤ ከእሥራቷ እንደተለቀቀች ጥጃም ፈንጥዘናል፡፡ እነዚህ የአማራ ሙንጣዦች ግን ቢመከሩ ይመከሩ፤ አለበለዚያ ዋጋቸውን እንደምንሰጣቸው ለሕዝባችን ቃል እንገባለን፡፡ እነዚህ የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ የአማራ ልሂቃን “ትግሬ ነገሰ” ብለው በምቀኝነት ሊያብዱ ደርሰውልናል፡፡ በፊት ብንመክራቸው እምቢ ብለዋል፤ አሁን ደግሞ እንገስጻቸዋለን ወይ እንቆነጥጣቸዋለን፡፡ አለበለዚያም ብትር ቢጤ እናቀምሳቸዋለን፡፡ ….”
ባይቆጭ ያንገበግብ፡፡ይሄ አማራ እሚባል ‹ፍጡር› ፈረደበት፡፡ ስደተኛውም፣ የፖለቲካ ጥገኛውም፣ የኢኮኖሚ ጥገኛውም፣ የስኳር ሌባውም፣ የጨው ሌባውም፣ የወርቅ ሌባውም፣ ሁሉም ይረባረብበታል – አሃ፣ አሸሞርኩ መሰለኝ፤ ይቅርታ፡፡ ምን ይደረጋል – ጥላሸት ሲቀቡህ መቼም ቅቤ አትቀባ ነገር ሆነብኝ እኮ – ስለዚህ  የሀሰትም ልትሆን ብትችል ጠባብ ቀዳዳ እየፈጠርህ መሸሟሞር ጉደኛው ዘመናዊ ባህላችን የሚጠብቅብን አነስተኛው መሥፈርት ነው፡፡
አብርሃም ያዬህ የአማራ ልሂቃንንና አማሮችን በጅምላው ምን አድርጉ እያላቸው እንደሆነ አልገባህ አለኝ – የሞተ ፈረስ ጋላቢ ሆነብኝ፡፡ እግር እጁ በማይጨበጠውና ከቁም ነገሩ ይልቅ አትርሱኝ ባይነቱ በሚያሳብቅበት በዚህ የተውገረገረ ዘባዘቦው የአማራ ልሂቃን የሚላቸውን ወገኖች እንደምን አድርጎ በአግቦና የስድብ ቾኬ እንደጠረባቸው ስመለከት እንኳንስ ልሂቅ አልሆንኩ ብዬ የጨዋነት ዕድሌን አመሰገንኩ፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ብሆን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? ገመድ ቢጤ ይዤ ወደሚቀርበኝ ዛፍ እሮጥ እንደነበር አሁን ሳስበው በልጆቼ ዕድል ቀናሁ፡፡ ግን እኮ የማንሰማው ጅላጅልና ብሶት ወለድ ነገር እንዳይኖረን እየሆን ነው ጃል! ምን ዓይነት ዘመን ነው፡፡ በነገራችን ላይ የላይኛው አንቀጽ ጌታው አብርሃም ያዬህን እንዳቅሚቲ ለመተረብ በርሱ አነጋገር ማለትም የአጻጻፍ ሥልት ብዕሬን ማናገሬ ነው፡፡ ሰውዬው ግን እዬለየለት መጣ ልበል? ምነው ዐርፎ ቢቀመጥ? አሽሙርና አግቦስ ባይሆን ‹እኛ ወጣቶቹ› ጽሑፍና ንግግራችንን እናሳምርበት እንጂ በርሱ ያምራል እንዴ? በአሽሙር ዕድሜን መጨረስስ እግዜር ይወደዋል? ኧረ አቅል ጀባ! መካሪ ማጣት እንጂ እንዲህ ከሁሉም ጋር መናጀስ ማንን ይጠቅማል? ይህን ስል ግን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጹን ያልተሸራረፈ መብት ከማክበር ጭምር ነው፡፡ ያንን መብቱን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ግን እጠቁማለሁ፡፡
ትልቁ የአብርሃም ችግር የሚጀምረው የጽሑፉ የትርክት አቅጣጫ (point of view) ላይ ነው፡፡ የመረጠው የትርክት አቅጣጫ ሥልጣን ወዳድነቱን የሚያሳይ ነው – አብርሃም ከመጠን ያለፈ ሥልጣን አፍቃሪ ነው፡፡ ያን ፍላጎቱን የሚያጨናግፍበት የመሰለውን ግለሰብም ሆነ ቡድን በዛቻና በነገር ውርጅብኝ ለማደባየት ደግሞ በምንም ዓይነት መንገድ ወደኋላ እንደማይመለስ ከአጻጸፍ ሥልቱ መገንዘብ ይቻላል፤ የሠለጠነበት ይመስላል፡፡ በዚህ ‹ጥንቆላየ› ትክክል መሆኔን የአቶ ያዬህ ልጅ አብርሃም ራሱ ይመሰክርልኛል፡፡
የመረጠው  የትርክት አቅጣጫ ንጉሣዊ ነው – ልክ እንደቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዓይነት፡፡ አብርሃም ንጉሥ አይሁን እያልኩኝ አይደለሁኝም፤ አሁን ግን ስደተኛ እንጂ ንጉሥ አይደለምና እንዲያ መናገሩ ትርጉመቢስ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የትርክት አቅጣጫ ስል “የጽሑፉን ታሪክ ማን ነው የሚነግረን?” የሚለውን ጥያቄ የሚመልስልን ነው፡፡ አብርሃም የተጠቀመው የአንደኛ መደብን ብዙ ቁጥር ነው – በንጉሣዊ የአነጋገር ሥልትነት የሚታወቀውን መጠቀሙ ነው፡፡ እንግዲህ ለመንገሥ እያሰበም ሊሆን ይችላልና ይቅናው፡፡ አብርሃም ያዬህ “የምንወድህና የምትወደን ሕዝባችን…” ለማለት የቀረው ጊዜ ምናልባት ቀጣዩ ጽሑፉ እስኪወጣ ነው፡፡
አብርሃም ጥቂት ማሰብ ቢችልና ነባራዊ የትርክት አቅጣጫ ቢጠቀም ኖሮ ከእንደኔ ዓይነቱ ሥራ-ፈት አቃቂረኛ ትችት ይድን ነበር፡፡ ከራሱ ጽሑፍ ምሳሌ ልውሰድና እንዳመጣብኝ ራሴው በመረጥኩት አንድ መንገድ ላሻሽልለት – ሌላም ዘዴ ይኖራልና፡፡
ከቅርብ ቀናት በፊት ያስተላለፍነው ማስታወቂያ መሰረት በማድረግ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ የለቀቀናቸውን ሁለት ኣበይት ጉዳዮች ያዘሉ ፅሑፎቻችንን በጥሞና ኣጢናችሁ ምስጋና ለለገሳችሁንና ላበረታታችሁን እጅግ በርካታ ወገኖቻችን ከልብ የመነጨ ምስጋናችን ይድረሳችሁ። ለወደፊቱም ምክራችሁና ድጋፋችሁ፥ ጉድለት ሲኖርም ተግሳፃችሁ፥ እንዳይለየን በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን።ከሁሉም በላይ ያስደሰተንና ያስፈነደቀን ግን የኣማርኛ ቋንቋ ኣቅማችን መዝናችሁ ከፍተኛውን የማለፊያ ቁጥር/ማርክ ሰጥታችሁ ያበሰራችሁን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ያደረጋችሁት መልካም ተሳትፎ ነው።
ከቅርብ ቀናት በፊት የተላለፈውን ማስታወቂያ መሠረት በማድረግ ባለፉት ሁለት ሣምንታት በተከታታይ የተለቀቁትን ሁለት ጉዳዮች ያዘሉ ጽሑፎችን በጥሞና አጢናችሁ ምሥጋና ለለገሳችሁኝና ላበረታታችሁኝ እጅግ በርካታ ወገኖቼ ከልብ የመነጨ ምሥጋናየ ይድረሳችሁ፡፡ ለወደፊቱም ምክራችሁና ድጋፋችሁ፣ ጉድለት ሲኖርም ተግሣጻችሁ እንዳይለየኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝና ያስፈነደቀኝ ግን የአማርኛ ቋንቋ አቅሜን መዝናችሁ ከፍተኛውን የማለፊያ ቁጥር/ማርክ የሰጣችሁኝ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ያደረጋችሁት ተጨማሪ ጥረት ነው፡፡
በመሠረቱ አብርሃምን በአማርኛ ችሎታው ማማት የሚቻለው የለም – ጎበዝ ነው፤ በዚያ በደርግ የመጨረሻ ዘመን በሚያምር ንግግሩ ያላማለለው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቲቪ ተከታታይ አልነበረም፡፡ ይህም ችሎታው የዛሬውን አያድርገውና እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ ያገኘው የጋራ ሀብት እንጂ ለ‹ወደር ለሌለው ጀግንነት ኒሻን› ወይም ለ‹ኖቤል የሥነ ልሣን ለመዳ› ሽልማት የሚያሳጭ ታላቅ ጀብድ አልነበረም፤ አይደለምም፡፡ አማርኛን ከአማሮች በላይም እንኳን አሣምሮ መናገር መቻል ብርቅ አይደለም/ሊሆንም አይችልም፤ በ”ቋንቋችሁን ዐወቅሁላችሁ”ም የሚያንቀባርር አይደለም – እነአሉላ ፓንክረስት ምን ይበሉ ታዲያ፡፡ በመሠረቱ እኮ አንድን ቋንቋ አጣርቶ ለማወቅና ለመጠቀም በአማካይ ስድስት ወራትን ብቻ እንደሚፈጅ ባለሙያዎቹ የሚናገሩት ጉዳይ ነው – በዚያም ላይ ማንኛውም ቋንቋ የሰው ልጅ ጠቅላላ ሀብት እንጂ ‹የኔ የብቻየ አንጡራ ሀብት ነው› ሊባል የሚገባው አይደለም – እንደዚያ የሚሉ ጅሎችና የቋንቋን ሥነ ተፈጥሮ የማይረዱ ናቸው፡፡ እንግሊዝኛን ከእንግሊዞች በላይ የሰለጠኑበት የዓለም ዜጎች ሞልተዋል ይባላል፡፡ አማርኛን በሚመለከት ግን እነበዓሉ ግርማ፣ እነሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን፣ እነጥላሁን ገሠሠ፣ እነማህሙድ አህመድ፣ … እና ሌሎቹም ሚሊዮናት የኢትዮጵያ ፈርጦች ምን ሊባሉ እንደሚችሉ አብርሃም ያዬህ ብቻ ነው ሊነግረን የሚችል – ደግሞም እኮ አማርኛና ትግርኛ ተለያይተው ሞተው – ፒ! በዚህም አለ በዚያ እሱ በቀጥታ ሳይናገረው በሾርኒ እንደተናገረው ቆጥሬ እንደምረዳው  እሱን መሰል ትግሬዎች ለአማርኛና ለአማሮች ባላቸው ቀረቤታና ታሪካዊ ዝምድና ሲሉ አማርኛ ቋንቋን አጥርተው መናገራቸው እንዳለ ሆኖ በታሪካዊ ኹነቶች መገጣጠም ምክንያት እንግሊዝኛ የዓለም ቋንቋ ሊሆን እንደተቃረበ ሁሉ ከ80 ቋንቋዎች በላይ በሚነገሩባት ኢትዮጵያም በሆነ ታሪካዊ አጋጣሚ ይህ የጭቁኖች ቋንቋ ለሀገሪቱ ሕዝብ እንደጋራ የመግባቢያ ድልድይ ሆኖ ቢያገለግል ያሸልመው እንደሆነ እንጂ አያስኮንነውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ወርቅ ላበደረ ጠጠር መመለስ እንደባህል እየተቆጠረ ስለመጣ አማርኛ አለአበሳው እንደክርስቶስ እየተወገረ ያለበት ሁኔታ ነው ተፈጥሮ ያለ፡፡ በውጤቱም ኢትዮጵያ ነጻ ስትወጣ በቀላሉ ወደማትወጣው ሥነ ልሣናዊ ውጥንቅጥ ውስጥ እየገባች እንደሆነ መገመት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለ፡፡ በሃፂሩ ዘይተፈጥረ ኹኔታ የለን ምባል ይኸሸና አኅዋተይ፡፡ “ዝዛረቦን ዝፅህፈሎን ኣምሃርኛ ፅቡቕ ተባሂሎለይ፤ እንኳዕ ቃህ በለኩም፤ አነ ቃህ ኢሉኒ ” ኢልካስ ከምዚ ምርጓድ? ቧይ! አታ አብርሃም፣ እንታይ’ሞ ኮይንኻ? …
እባካችሁን እያልኩ ያለሁት ግልጽ ይሁንልኝ፡፡ አማርኛ በግድ የጋራ ቋንቋ ይሁን የሚል ሥነ ልሣናዊ ህልምም በሉት ቅዠት የለኝም፡፡ የማምንበት ጉዳይ ግን ኢትዮጵያውያን በአንድ የግዛት አንድነት ሥር ለመኖር እስከፈለጉ ድረስ ከ80 በላይ በሚገመቱ ቋንቋዎች በሁሉም መግባባት ይቸገራሉና ቢያንስ አንድ ኦፊሴል የሥራ ቋንቋ የሚያስልጋቸው መሆኑን ነው፡፡ ያም ቋንቋ ሲፈልግ ኑዌርኛ ሲፈልግ ደግሞ ዳዋሮኛ ይሁን፡፡ ችግሩ እሱ አይደለም፡፡  በ80 ቋንቋ ቲቪ ፕሮግራም መክፈት፣ በ80 ቋንቋ ዐዋጅ ማርቀቅ፣ በ80 ቋንቋ ጋዜጣና መጽሔት ማተም፣ በ80 ቋንቋ የትምህርት ሥርዓት መንደፍ … ይህን እንኳንስ እኛ ያደጉ አገሮችም አይችሉትም፤ እስካሁን የሠራነውም የጅሎች ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ውድ አብርሃም እንዲያውቀው የሚገባው ነገር አማርኛን የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ለአማርኛ ባለውለታ ናቸው እንጂ አማርኛ ተገልብጦ ውለታ ከፋይ ሊሆን የሚገባው አለመሆኑን ነው፡፡ ቋንቋን ከመሣሪያነቱ በላይ አዝልሎ የሚመለከት በሽተኛ እንጂ ጤናማ ሰው ሊባል አይችልም፡፡ ላወቀው ቋንቋ ልክ እንደሸሚዝና ከናቴራ ሊጠለቅና ሊወልቅ የሚችል በጣም ተራ ነገር ነው፤ ሰዎችን የሚያባላውስ የግል ወይም የቡድን እንስሳዊ ጥቅምና ፍላጎት ነው፡፡ ቋንቋ ልባስ ናት – ጭምብል፡፡ በዛሬ ዘመን ደግሞ የአንዲት እናት ልጆች እንኳን እርስ በርስ ይባላሉ – ይቅርና የአንድ በሄረሰብ አባላት፡፡ ሶማሌን ተመልከቱ፡፡ በሁሉም ነገር አንድ ሆነው ሲያበቁ ከኛ በበለጠ መንግሥት አልባ ሆነው በዓለም ዙሪያ ተበትነዋል፡፡ የበተናቸው በቋንቋ ያለመስማማት ጣጣ አይደለም፡፡ ሆድ እንጂ የቋንቋ ልዩነት አያፋጅም፡፡ ዐመል እንጂ በምትናገረው ቋንቋ ምክንያት አትጨራረስም፡፡ እውነቱ ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡
አማርኛን በሚመለከት እንዲያውም በአሁኑ ወቅት በገዢው የወያኔ ቡድን ምክንያት የኢትዮጵያውያን የጋራ መግባቢያ ድልድይ እየተሰባበረ በመሆኑና የሚተካውም ባለመዘጋጀቱ ብዙ ዜጎች እየተጎዱ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ ሰውነቷን በጋሬጣ መለጎጠች እንደተባለችው ቂል ሴት፣ ወያኔም አማራ እሚባሉትን ዜጎች ከጨዋታ ውጪ ያወጣ መስሎት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በተለይ የገጠራማይቱ ኢትዮጵያ ዜጎችን ከሁለት ያጣ ጎመን አድርጓቸው መቅረቱን መገንዘብ አይከብድም፡፡ በስመ ብሔር/ብሔረሰብ የማላገጫ “ፌዴራል” ተብዬ የፖለቲካ ቁማር ሰበብ ጆሮውን ቢቆርጡት አማርኛን መናገር የማይችል ኢትዮጵያዊ ዜጋ አምርቶ ወደመናገሻ ከተማ ለሥራ ፍለጋ ሲመጣ ከቢጤዎቹ በተለዬ ባይተዋር እንዲሆን ማድረግ ዛሬም ባይሆን ከነጻነት በኋላ ዳፋውን የምናየው ይሆናል፡፡ ከደምቢዶሎ በእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ አዲስ አበባ ለሥራ ፍለጋ የመጣና ኦሮሚፋ በስተቀር እንግሊዝኛም አማርኛም መናገር ባለመቻሉ ገና በኢንተርፈቪው ያለማለፉን መርዶ እየሰማ ይሰቃይ የነበረ ወጣት በቅርብ አውቃለሁ፡፡ ወያኔዎች በቂም በቀልና በድንቁርና ተነሳስተው የኢትዮጵያን ወጣት በዚህ መልክ ቢጫወቱበትም ታሪክ ፍርዱን ሲሰጥ የሚገባቸውን ምንዳ እንደሚያገኙ አይጠረጠርም፡፡ የነሱን ልጆች ግን እንዴትና የትም እንደሚያስተምሩ እናውቃለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በኔ ግምባር ላይ የምትገኘዋ ያቺ 11 ቁጥር መለያ እንኳን በነሱ ልጆች ግምባር እንዳታርፍና የባህል ተከታይ እንዳይባሉባቸው ያደርጋሉ፤ አቸፈርና ወይንማ የገጠር ትምህርት ቤት “የተማረው” የስንሻው አገሩአደመ ልጅ “ኧሯ!” ሲል በአማርኛው ጎጃሜ መሆኑን ተረድተህ ስታፌዝበት የወያኔዎችን ልጆች ግን በምንም መንገድ አትለያቸውም – “ሥልጡናን” ናቸው፡፡ አነሳሴ ሌላ ሆነ እንጂ በዚህ ዙሪያ ብዙ የሚያሳዝኑ ገጠመኞችን መናገር በቻልኩ፡፡
አብርሃም ያዬህ በተለይ የአማራ ልሂቃን የሚላቸውን በጅምላ ለምን እንደጠላቸውና በዴሞክራሲያዊ ልቅ ብዕሩ ለምን በስድብ እንደሚሞልጫቸው ገርሞኝ ባነሳሁት ብዕር ስላልተነሳሁበት ነገር ከፍ ሲል ጥቂት ዘባረቅሁ መሰለኝ፡፡ ምን እንዲያው – የዚህች አገር ነገር እኮ ሳይጠጡ እያሰከረን ብዙዎች ተቸገርነ፡፡ ምን ይብቃነ? ሁሉም እየተነሣ የስድብና የአቃቂር መለማመጃ አደረገነ፡፡ በቁም ሞትነ፡፡
አንድ የኔ አገር ሰው ነው አሉ፡፡ አንድ ጓደኛው “እናንት ጎንደሬዎች ስትባሉ – በየቃሉ መጨረሻ ‹ነ› ታበዛላችሁ ይባላል፤ መጣነ፤ ገደሉነ፤ በላነ… ነው አሉ እምትሉት፤ ለምንድነው?” ብሎ ቢጠይቀው “ለምዶብነ!” አለው ይባላል፡፡ ዘና በሉና አንብቡ፡፡ ሊያልፍ ዓለም የምን መጨነቅ ነው፡፡ ጠላታችሁ ይጨነቅ፡፡
አብርሃም ያዬህ ጥላቻህን በቅጡ ያዘው ወንድማለም፡፡ ከአንተ እንዲህ ያለ “ኮምፕሌክስ” አይጠበቅም፡፡ የአማራ ልሂቃን፣ የትግሬ ልሂቃን፣ የኦሮሞ ልሂቃን፣ የኮንሶ ልሂቃን፣ የወላይታ ልሂቃን፣ የሶዶ ልሂቃን፣ የወለንጪቲ ልሂቃን፣ የቡታጅራ ልሂቃን፣ የጨቦና ጉራጌ ልሂቃን …  ይህ የዘረኝነትና የጎጠኝነት ልክፍት ለካንስ ማቆሚያው የለውም …  እንዴት የሚያስጠላ አነጋገር መሰላችሁ፤ አንድ የተማረ ሰው ዜጎችን እንዲህ በመሰለ አጸያፊ መነጣጠያ እንዴት ይከፋፍላል? ለዚህ ለዚህማ ከወያኔ በምን እንሻላለን? ዋጮን ቢገለብጡት ያው ዋጮ ነው እንደሚሉት መሆኑ እኮ ነው፡፡ ልዩነቱ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በመግባትና ባለመግባት ሆነ እንጂ በቤተ መንግሥት ውስጥና ከቤተ መንግሥት ውጪ ያሉ ወገኖቼ አነጋገራቸው እዬተመሳሰለብኝ መጥቷል፡፡ “መንግሥቱን፣ መንግሥቱን መሰልከኝ!” ነበር አይደል ያሉት ዶር. ነጋሦ? አበጁ! ልኩን ነግረውት ሄደ፡፡ እንኳንም የነገሩት፤ እሱም እንኳንም ጥርግ ያለ፤ ሐምሌና ነሐሴም ነጉደዋል፡፡
አብርሃም ተመለስ፡፡ የማትመለስ ከሆነ ግዴለህም ዝም ብለህ ስደትህን ብቻ አሰላስል፤ ከ14ሺህ ማይል ማዶ ሆነህ ያልበላንን ለማከክ አትሞክር፡፡ ያውጡብሽ እምቢ ያግቡብሽ እምቢ አትሁን፡፡ የዱሮውንም ተቃውመህ፣ የአሁኑንም ተቃውመህ፣ ያንንም ጠልተህ፣ ይህንንም ጠልተህ… ደግሞ የምትዘልቀው አትመስለኝም፡፡ ለመሆኑ ትግሬ ነገሠብኝ ብሎ ያኮረፈው የአማራ ልሂቅ የትኛው ይሆን? አለ ካልክና ካጋጠመህ በጅምላ አማራውን የአገም ጠቀም አዘኔታ ባጀበው መርዛማ አነጋገርህ ከምትወርፍ ስሙን ጠቅሰህ ለምን አትወቅሰውም? ምን ዓይነት የጠብ ስንጥቃት እየፈጠርህ ነው? የነበሩን ቅራኔዎች አነሱንና ነው በትግሬና በአማራ መሃከል ሌላ ሽብልቅ እያበጀህ ልትቀበቅብብን የምትዳዳው? እንደውነቱ አማርኛን ማወቅ አማሮችን በማይፈለግ ቅራኔ ውስጥ እየከተቱ በስቃይ ለማዳከር ጥቅም ላይ መዋል አልነበረበትም – ኩነኔ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥርሱን ከነቀለ ሰው በፍጹም አይጠበቅም፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው የአስታራቂነት ሚና እንጂ እንደቀድሞ የትግል አጋርህ እንደመለስ ዜናዊ ዜጎችን በማጋጨት የመርካት ፍላጎት ልታዳብር አይገባህም ነበር፡፡ አጋጫቸው፣አፋጫቸው የሚል ስሜት የሚፈታተንህ ከሆነ – መቼም አይታወቅም – ወደሚቀርብህ ጠበል ሂድና አንድ ሦስት ሰባት ያህል ተጠመቅ – በአጠገብህ ካገኘኸው ያን ተስፋዬ ገብረአብ የሚባለውን ሰውዬም አብረህ ይዘኸው ሂድና አብራችሁ ተጠመቁ – የያዟችሁ ፀረ-ሕዝብ አጋንንት ውልቅ ይሉላችሁ ይሆናል፡፡ ስለኢትዮጵያ ነጻነት የዐዞ ዕንባ እያነቡ አንድ የነጻነቱ ትልቅ ኃይል ሊሆን የሚገባውን የአማራ ብሔር በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ እንደእባብ መቀጥቀጥ ከሞራልም ሆነ ከሃይማኖት አንጻር አግባብነት የለውም፡፡ የሚቀጠቅጠንና የሚያቀጣቅጠን አላጣንምና አንተ እንኳን እባክህን ማረን፤ በሞቱ ዘመዶችህ አጥንት ይሁንብህ፡፡
አማሮች እኮ ዘራቸው እንኳን እንዳይራባ በመርፌና በበሽታ እንዲያልቁ ሤራ የተሸረበባቸው የዘመናችን ምንዱባን ናቸው – በዚህ ላይ ዛሬ አንተ ተነስተህ በጭቃ ጅራፍህ ብትሸነቁጣቸው ላንተስ ግፍ አይሆንብህምን? ታውቃለህ አብርሃም ያዬህ – መለስ ዜናዊ በተላላፊ በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች ከየቦታው በመብራት እየተፈለጉ ወደአማራው አካባቢ እንዲሄዱና በዚህ ምሥኪን ሕዝብ ላይ የተኩስ ድምፅ የሌለበት ዳግማዊ የክተት ዘመቻ ታውጆባቸው ብዙዎች እንዲያልቁ ማድረጉን ሳትሰማ አልቀረህም – እሱ ሺህ ዓመታትን ሊኖር፡፡ ይህች ቆሻሻ ዘመን ያላሳየችንና ያላሰማችን ነገር የለም፤ እናም እባክህን በድጋሚ ልማጸንህና ልጆች ካሉህ በልጆችህ ይሁንብህ አማሮችን ተዋቸው፤ ነጻ ልታወጣን አስበህ እየታገልክልን ከሆነም እንደኔ እንደኔ ይቅርብን – ከዕብሪት አነጋገርህ ነጻ መሆናችን ራሱ ትልቅ እገዛ ነው፡፡ የፈጠረን አይረሳንምና እርሱ ራሱ እንደፍጥርጥሩ ያድርገን፡፡ ይልቁንስ ላንተው ተጨነቅ፡፡ ደግሞም አታስፈራራን፡፡ ፈርቶ የጨረሰን ለማስፈራራት መሞከር ትርፉ ትዝብት ነው አባት ዓለምዬ፡፡ በዚያ ላይ እንኳን ከፎከረ ከተወረወረም የሚያድን አምላክ አለንና በወያኔ ኃያልነት እያሳበብህ በልጆች አማርኛ ‹አታስቦካን›፡፡ እስኪ ይህን ልብ በል፡- እሳት ውስጥ ገብቶ እየተቃጠለ ያለን ሰው “መጪው ዕድልህ ከዚህ የባሰ መሆኑ ያሳዝነኛልና ዐርፈህ ብትቃጠል ይሻልሃል! ዋልህ አንት ዋልጌ! ለዚህ ያበቁህ አስተምረህ ለወግ ለማዕረግ ያበቃሃቸው ልጆችህ ናቸው፡፡ …” እያልክ ቲሪሪም ቲሪሪምህን ብትነፋበት ምን ያህል የሞራል ልዕልናና የመንፈስ እርካታ ታገኝበታለህ? ታዲያ ከመጡበት ዘጠኝ ሞቶች አንዱን ግባ ብሎ በወያኔ እየተቃጠለ የሚገኝን ማኅበረሰብ የግፍ ግፍ አሁን ላይ ሆነህ ስለወደፊቱ ማስፈራራት ምን ትርጉም አለው? ጉደኛ ነህ ጃል!
መመጻደቅህንም ቀነስ ብታደርገው አንተው ነህ ከተጨማሪ ትዝብት የምትድነው፡፡ ኤዲያ – ምነው ይሄን ኢንተርኔት የሚባል ነገር የሚያጠፋልኝ ባገኘሁ! ስንቱን እንቶፈንቶ ዝግንትል መሰላችሁ የሚያስነብብ፡፡ ጥቂት የአብርሃምን ዕንቁ ንግግሮች ከምዝስዕብ ከቕርብለኩም እየ’ሞ ቕሩብ ምዕንቲ ክትዘናግዑ የኽትት፡፡ ብዚ አገጣሚ አብርሃም ያዬህ ብፍላይ ንክልቴኦም ብሔራት ዝአዳለዎ ድግምቲ መስተፃልዕ ክሠርኽ ከምዘይክእል አፀቢቐ ከርገግጸልኩም እደሊ፡፡ ኳርት ቀየርኩ ልበል? ሆን ብዬ ነው – አማርኛና ትግርኛ ምን ያህል “አራምባና ቆቦ የሆኑ”ና በምንም ዓይነት መንገድ “የማይቀራረቡ ቋንቋዎች” መሆናቸውን በጨረፍታ ለመጠቆም ፈልጌ ነው፡፡ ለማንኛውም ወደአብርሃም ጽሑፍ በቀጥታ እናምራ፡፡ ከ12 ገጾች ጽሑፍ የሚከተሉትን ብቻ ነው ለአብነት ያህል የጠቀስኩት፡፡ በክፍል በክፍል ተመድቦ የቀረበውን ዋናውን ቅራቅንቦ በየድረገጹ ተለጥፎ ታገኙታላችሁና ማወቅ አይከፋም ተዝናኑበት -በበኩሌ እስኪገባኝ እየደጋገምኩ ሣይቀር ‹ተላጥኩበት›፡፡
ኧረረረረረረረረረረረረረረ ….
የኣማራ ኤሊቶች በሽታ ኢትዮጵያ ከኛ በላይ የሚቆረቆርላትና የሚያስብላት ሌላ ሰው የለም ብለው ስለሚያስቡ (እንዲያውም “ኢትዮጵያን የሰራት ኣማራ ነው” የሚሉንም ኣልጠፉም)፥ ከኣማራ ውጭ ሌላ ሰው ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ቢያስረዳቸውም እንኳ ሃሳቡን ኣዳምጠው መመርመርና ማስላት የማይፈቅዱ መሆናቸው ነው። እኛ ደግሞ ከፋም በጀ የትግራይ ህዝብ ስትራተጂካዊ ወገን የኣማራ ህዝብ ነው ብለን ስለምናምንና ትክክልም ስለሆነ፥ የነዚህ ወገኖቻችን ኣጉል መተራመስና ትጥቅ/ዝግጅት የለሽ ባዶ ፉከራና ሽለላ ለደጉና መከረኛው የኣማራ ህዝባችንም ሆነ ለምንቆረቆርላት ኣገር የማይበጅ በመሆኑ የኣማራ ሊሂቃን ወገኖቻችንን ኣበክረን ስንወቅሳቸው ኖረናል። ለወደፊቱም ሸውራራ ኣመለካከታቸውና ባዶ ፉከራቸው እስከሚገታና ሰከን ብለው የተቆርቋሪ ወገኖቻቸው ተግሳፅና ምክር ምን ይዘት እንዳለው ተረድተው ኣደብ እስኪገዙ ድረስ ወቀሳችን ከመሰንዘርና ኣቤቱታችንን ጥፋት በላዩ ላይ ላንዣበበው የኣማራ ብሄር ህዝባችን ከማቅረብ ኣንቦዝንም። ይቺን ኣጋጣሚ በመጠቀም፥ የኣማራ ሊሂቃን ወገኖቻችንን ለመውቀስና በተሳሳተ መንገድ ሲነግዱ ከዚያ የተሳሳተ መንገድ እንዲታቀቡ የምንወተውትበት ምክንያት ባጭሩ ጠቅሰን እናልፋለን።
ኧሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮ ….
ስለሆነም፥ ከኣማራ ሊሂቃን ወገኖቻችን ጋር የምንዳረቀው፥ በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉት ሁሉም ህዝቦች ወገኖቻችን ቢሆኑም፥ በተለየ ታሪካዊና ተፈጥሮኣዊ ምክንያት የትግራይና የኣማራ ህዝብ ኢትዮጵያን በወረፋ እየተቀባበለ ለመግዛት ሲል በስልጣን ከሚሻኮት በቀር መጥፊያውም መዳኛውም መንገድ ኣንድ ስለሆነ፥ የትግራይ ኤሊቶች ሲያጠፉ እንደምንቃወማቸውና እንደምንዋጋቸው ሁሉ ኣማራ ነን የሚሉ ፍጥረቶች ሲያጠፉም እነሱንና ኣገራችንን ከጥፋት ለማስጣል ካለን ቁጭት ተነስተን ያለ ምንም ምህረት እንወቅሳቸዋለን፤ እንገስፃቸዋለን። ከዚህ ውጭ፥ በማጠያይቅ ሆኔታ፥ ኢትዮጵያዊያን ነን ብለን በፅናት የምናምን እኛ የትግራይ ተወላጅ ዜጎች እንደ ህወሓት መሪዎች በኣማራ ጥላቻ በሽታ የተለከፍን ሆነን ሳይሆን፥ ከኣማራ ኤሊቶች ጋር ያለን ግብግብ “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ነደደች፥ እንዳትተወው ደግሞ ወለደች” ከሚል ኣገራዊ ብሂል የሚመነጭ ለመሆኑ በሚገባ መታወቅ ያለበት መሆኑን ከታላቅ ትህትና ጋር ባጭሩ ጠቁመን እናልፋለን።
ኧረረረረረረረረረረረረረረረረ …..
ባለፉት ሃያ ዓመታት ሌሎች ኢትዮጵያዊያን (ባብዛኛው የኣማራ ሊሂቃን) በትግራይ ህዝብ ላይ ከረጩት መጠነ ሰፊ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ኣንፃር የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ውድቀት በኋላ የሚኖረው ዋስትና በምንና በማን ይረጋገጣል? ሌትና ቀን ሳይሉ የሚታገሉና በራሳቸውና ኣገርቤት በሚኖሩ ዘመዶቻቸው ላይ ብዙ መከራ እየተቀበሉ ያሉ እውቅ የትግራይ ህዝብ ታጋይ ልጆች ላይ (እነ ስየ ኣብርሃና እነ ገብሩ ኣስራት፤ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም ወንጀል ያልፈፀሙትና የወያነ መንግስት ሰለባ ከመሆን ኣምልጠው በስደት የተቀላቀሉን ወንድሞቻችን እነ ወጣት ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሳይቀሩ)፥ በዘረኛ ኣማሮች የሚወረወርባቸው ጦርና የሚመዘዝባቸው ሰይፍ እያየ፥ እየሰማ፥ እያነበበና፥ እየታዘበ ያለው የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ጠልቶ የልጆቹን ኣሳዳጆች የሚመርጥበት ምን ምክንያት ኣለው?
ኧሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮ …
የ”ትግሮች ነገሱብን” ኣባዜያቸው የሚጋለጠው ደግሞ ኣገር የሚያጠፋውን የወያነ ኣመራር በመቃወም ሳይሆን፥ “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ኣብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ፥ ኣብርሃም ያየህን ጨምሮ ሁሉም የትግራይ ተወላጅ የሆነውን ሁሉ በማቀላቀል ጠላት ነው በሚል ፈሊጥ የተጨማለቀ ነው። ይህ ፈሊጥ ደግሞ ኢትዮጵያን ከሚበትን በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም። ለነገሩ ኢትዮጵያ ብትበተን ምን ገዷቸው! ጉዳቱ ለኛ ይተርፈን እንደሆነ እንጂ እነሱማ የፈረንጅ ኣገርና ዜግነት ኣዘጋጅተው የለ! እኛ በእግዚኣብሔር ድጋፍ ብዙ ደክመንና ጥረን ያስገኘነው ጠቃሚ ግኝት የተስተጓጎለውም ከዚህ የመከነና ኣፍራሽ ፈሊጥ የመነጨ ነው። እኛ የሰራነው ታላቅ ስራ ያመከኑት ያማራ ኤሊቶችም “ኤርትራን ያስወሰዱ ኣፄ ምኒልክ ናቸው ብለው የሚከሱን ትግሮች ኤርትራን ከሚያመጡልን ትቅርብን፤ ወይም ደግሞ ትግሮቹ ያስወስዷትን ኤርትራ የምትመለስ ከሆነም በኛ ባማራዎቹ ብቻ መሆን ኣለበት” ያሉትም ያንን ኣፍራሽ የእብዶች ፈሊጣቸው የወለደው ኣባዜ ነበር።
ኧረረረረረረረረረረረረረረረረረረረረረ….
ዛሬ በሞተ ሰዓት ላይ ግንቦት ሰባቶች በኤርትራ በኩል ተኣምር ይሰሩልናል ብለው የሚያሽካኩት ፍጥረቶችና እንደነ ሙሉጌታ ሉሌ ያሉ “ኣንጋፋ ጋዜጠኛ” ተብየዎች ትናንት እኛ በትክክለኛው ጊዜና መንገድ ልንሰራው ያቀድነውን ኣንገባቢ ስራ ሲያደናቅፉና ሲያበላሹ የነበሩቱ መሆናቸውን ስንመለከት ባንበሳጭም በመገረም እንደመማለን። እየተገረምናና እየተደመምን ደግሞ ደግነቱ የማያልቅበት ፈጣሪያችን ዕድሜ ሰጥቶን የትናንቱ ኣውጋዦቻችንና ኣደናቃፊዎቻችን ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀው የኢሳያስ ኣፈወርቂ ኣሞጋሾችና ተነጣፊዎች ሆነው መገኘታታቸው ስናይ በእጅጉ እንደሰታለን። እንኮራለንም!
ኧሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮሮ…..
ይህንን መጣጣፍ የምንቋጨው ኣጭር መልእክት በማስተላለፍ ነው። ግንቦት ሰባቶች በጉራና በፉከራ ከየዋህ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብር መዛቅ ይችላሉ። ይህ ቀላል ነው። በዚያ ብር ልክ ግን ፈተና ይጠብቃቸዋል። ይህንን የሚያፍሱት ብር በተላለፉት የግንቦት ሰባቶች ዲስኩሮች መሰረት በመሬቱ ላይ ባጭር ጊዜ ተጨባጭ ቁምነገር ካላስገኘ ብሩ እሳት ሆኖ እንደሚለበልባቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። እኛ ይህ እንዲሆን ባንፈልግም ውጤቱ ግን ይህ እንደሚሆን ኣንጠራጠርም። ስለዚህ፥ ይህ ከመሆኑ በፊትና ኋላ ደብቁኝ ሰዉሩኝ ማለት ሳይመጣ፥ ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ የሚደረግ ማንኛውም ግኑኝነትም ሆነ ትብብር ፋይዳ የሚኖረው ከሆነ፥ ግንቦት ሰባት ትህዴን በተባለ የትግራይ ፈረስ ተፈናጦ በመጋለብና የሻዕቢያ ጎራዴ ኣንግቶ ኣካኪ ዘራፍ በማለት ሳይሆን፥ ካገር ሽማግሌዎችና ወሳኝ ሚና ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመመካከር፥ በተለይ ደግሞ የቀድሞ የህወሓት መሪዎች የነበሩትን በማማከርና በማሳተፍ ብቻ መሆን እንደሚገባው ኣስታውሰን ኣንባቢዎቻችን በትህትና እንሰናበታለን።
መዘምዘሚያ፡- ይህ የፖለቲካ ጎምቱ ሰውዬ ምን ማለት እንደፈለገ የገባችሁ ሰዎች እኔም ይገባኝ ዘንድ እባካችሁን አስረዱኝ፡፡ ጠላታችን ግራ ይግባውና ግራ ግብት ነው ያለኝ፡፡ ምን አባቴን ልሁን? አብርሃም እውነቱን ይሆን እንዴ ወያኔ በሽምግልና ሥልጣን ይለቃል የሚለን ያለ – ሊያውም አሥሮ ጢባጢቤ በተጫወተባቸው የትግል ጓደኞቹ ሽምግልና? ወይንስ እያሾፈብን  ነው ያለ?

No comments:

Post a Comment