የሳዲቅ አህመድ ንግግር (ዋሽንግተን ዲሲ)
የምንወዳት የምንሳሳላት እናት ሀገራችን ኢትዮጲያ ልጆቼን አያለች በምትጣራበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የናት አገር ጥሪንም ሰምተን እዚህ መገኘታችን ታላቅ ዋጋ አለው! በዚህም ሳቢያ የታደልን የኢትዮጲያ ለጆች ነን ለማለት እወዳለሁ።እርስ በርስ እንድንፈራራ አንዱ-አንዱን እዲጠራጠር የተከፈተብን የስነ-ልቦና ጦርነት ቀላል አይደለም፤ ይህንን የስነ-ልቦና ጦርነት ለመርታትም እዚህ ተገኝተናል። የዜጎች ሁለንተናዊ አንድነትን ለመናድ የሚደረግ ሴራ እዉን አይሆንም፤ ለምን ካላችሁ እኛ ለዘመናት ያካበትነው ውዴታ፣ እኛ ለዘመናት በራሳችን ላይ አስርፀን ያቆየነው ፍቅር፣ አንድ ኣምባገነናዊ ስርአት ሊፈጥረው ከሚችለዉ ስነ-ለቦናዊ ጫና በጣሙን የላቀ ነውና በኢትዮጲያዊነታችን ሁሌም ልንኮራ ይገባል! በኢትዮጲያዊነት ፍቅር ሁለም ልንፀና ይገባል። አላሁ-አክብር!
የአለማችንን ታሪካዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከቃኘን በዘር ሃያልነት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በሃይማኖት ልዩነት፣ በኢኮኖሚ የበላይንት፣ በተበደልኩ ባይነት ሰዎች አክራሪ አሸባሪ ሲሆኑ ይታያል፤ ብዙዎቻቹ ለዘመኑ ቴክኖሎጂና መገናኛ ብዙሃን ሩቅ አይደላቹምና የምትሰሟቸዉን የዘር፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ የበላይነት ለመቀዳጀት የሚከሰቱ የአሸባሪነት ተግባራትን እናቆይና የዛሬን የውይይት መድረክ የሚመለከቱን በተለያዩ መንግስታትና ህዝባዊ ተቋማት ብሎም አገራት አሸባሪ ተበለው የተሰየሙ ቡድኖችን እንጥራ። አልቃኢዳ፣ አልሸባብ፣ ቦኩ-ሃራም እና አንሷረል-ኢስላም፤ እነዚህ ቡድኖች በሽብር ፈጠራ ይታወቃሉ፤ ንፁህንን ሲቪሎችን ይገድላሉ፤ ንብረትን ያወድማሉ፤ በሃሳብ ልዩነት ተግባብተው ተቻችለው መኖርን የማይቀበሉ ከመሆናቸወም ባሻገር በመጀመርያ የጥቃታቸው ሰለባ የሚያደርጉት የራሳቸወን ወገን የሚቀርባቸውን ሙስሊሙን በመሆኑ ያለማችን አብዛኛው ሰላም ወዳድ ሙስሊም በጽኑ ይቃወማቸዋል፤ ይህን እዚህ ጋር ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።የአለማችን አብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ ቢቃወማቸወም፤ እኛም እንደ ኢትዮጲያዊና እንደ ኢትዮጲያዊ አሜሪካዊ በፅኑ የምንቃወማቸው መሆኑን ዳግም ላረጋግጠላችሁ እወዳለው።
ከላይ ስለተጠቀሱት አሸባሪ ቡደኖች በዙ ይባላል፤ አሸባሪ ተበሎ ለተሰየመ አሸባሪነቱ በገሃድ ስለሚተገበር እና ስለሚታይ ስለቡድኑ ብዙ ከማለት ይልቅ በነዚህ አሸባሪ ቡድኖች ላይ ሰላም ወዳድ ሙስሊሞች ያላቸውን አቋም ማሳወቁ ግድ ይላል። የብዙ ኢስላማዊ ምሁራን ጥምረት የሆነው የሰሜን አሜሪካ የፊቅሂ ምክር ቤት ይህንን ሃይማኖታዊ ብያኔ ወይም ፈትዋ ሰጥቶዋል።
1) በሲቪሎች ላይ የሚደረግ ማንግኛውም ሽብር የመፍጠር ተግባር የተከለከለና ሃራም ነው ።
2) በሽብር ፈጠራና ረብሻ/ሁካታ ከሚሰማሩ ቡደኖችሀና ግለሰቦች ጋር ማበር ብሎም መተባበር የተከለከለና ሃራም ነው።
3) የንጹሃንን የሲቪሎችን ህይወት ለመጠበቅ ለማዳን ከህግ አስፈፃሚ አካላት ጋር መተባበሩ የበጎ ኣድርጎት ሃይማኖታዊ ተግባር ነው።
ከላይ የተጠቀሰው ሐይማኖታዊ አቋም በሰሜን አሜሪካም ይሁን በኣውሮፓ፤ እሴያም ይሁን በአፍሪካ ብሎም በመላው አለም የሚገኙ ሰላም ወዳድ የሆኑ ሙስሊሞች አቋም ነው። በሰላማዊ መንገድ ዲሞክራሲያዊና ህገመንግስታዊ መብታቸውን የሚጠይቁት ኢትዮጲያዊ ሙስሊሞች ከዚህ የተለየ አቋም እንዳላቸው አላሳዩምና የመንግስትን የማስፈራራት የማፈራራት የከፋፍለክ ግዛዉ ፕሮፓጋንዳና የስነ-ልቦና ጦርነት ውድቅ ማድረጉ አኩሪ ኢትዮጲያዊ ተግባር ነውና በጋራ ውድቅ ልናደርገው ይገባልነው። ኢንሻ አላህ!
ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች ከአንድ አመት በላይ በጽናት በሰላማዊነት በጀግንነት መብታቸውን እየጠየቁ ነው ።ጀግና ስንል ‘መቼ ግዳይ ተጣለና?’ ትሉ ይሆናል፤ ትውልዱ ስለጀግንነት ያለውን አመለካከት በእስር ከሚገኘዉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ከሆነው ወጣት አህመዲን ጀበል ልዋስ አህመዲንም እንዲህ አለ‹‹በተለያየመልኩግፈኞችሰዎችንየሚያሰቃዩትአካላቸውንለመጉዳትሳይሆንለሰውልጅእጅግወሳኝየሆነውንተስፋናወኔለመስበርነው።የነፃነትስሜትያላቸውንሰዎችበዳይለሆኑሰዎችሁሉእራስምታትናቸው።ተስፋእንዲቆርጡምወኔእንዲያጡምበቃልምበጉልበትምየሚችሉትንሁሉያደርጋሉ።ጀግናማለትእነዚህንየስነ-ልቦናጦርነቶችተቋቁሞሊሰብሩትየፈለጉትንስነልቦናበተስፋሞልቶበፅናትየሚጓዝነው›› አህመዲን ጀበል።ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞችም ይህን እያደረጉ ነው፤ኢትዮጲያዊያን ክርስቲያኖችም ይህንን አድርገዋል። አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ላይ የተሰዉት በዚሁ የጀግንነት መንፈስ ነው። አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ላይ ሲሰዉ ለክርስቲያን ብቻ አይደለም! ለሙስሊሙም ለክርስቲያንም ለዋቄፈታም ነው አቡነ ጥጴሮስ የተሰዉትና በኢትዮጲያዊነታችን ልንኮራ ይገባል። አላሁ አክበር!
ውድ ኢትዮጲያዊያን ሆይ! ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ተጠይቆ ለመመለስ የፈራው መንግስት ምንም ያድርግ ምን ከፈሪዎች ጎራ የሚመድብ ነዉ። ስለምን ካላችሁ ጀግናዉ ሰላም የሆንው ወጣቱ ትውልድ ነዉና! የዚህ ወጣት ወንድም እህት በመሆናችሁ ሙስሊመም ሁኑ ክርስቲያንም ሁኑ ዋቄፈታም ሁኑ ልትኮሩ ይግባል።አላሁ አክበር!
ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች ለሚያቀርቡት ጥያቄ መንግስቱ በፐሮፓጋንዳ እንደሚለው ኢስላማዊ መንግስትን ለመመስረት የሚደረግ የአሽባሪዎች ጉዞ ሳይሆን፤ እንደምን ሰላማዊና ፍጹም ሰላማዊ፤ ብሎም ህገመንግስታዊ ነው የሚለውን ለማመላከት ። ከሃያ የሚበልጡ ነጥቦችን ይዣለሁ።ኢንሽ አላህ በሰአቱ ለመጨረስ ሞክራለሁ።
ከጥልቅ ዝምታ ወደ መንግስታዊ ብዥታ
የባሰውን አያምጣ በሚል አመለካከት ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በደል ጭቆናውን ችለው በጥልቅ ዝመታ ውስጥ በመሆን እምነታቸውን እንደ ብርሃን እየተከተሉ ሳሉ፤ መንግስት በዚህ ብርሃን ላይ ብዥታ ለመፍጠር መጤ እምነትን ከሊባኖስ አምጥቶ ጫነባቸዉ…በእምነት ማስገደድ የለም በማለት ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተነሱ… ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች እና መሪዎቻቸዉ በህገ-መንግስት የተረጋገጠውን መብት ለመተግበር የተነሱ ናቸው እንጂ አሽባሪዎች-አክራሪዎችም አይደሉም።
ከሁካታ ይልቅ ሰላማዊ ስሞታ
እምነት በግድ ሲጫን ህዝቡ ሆ…ብሎ ለረብሻ አልተነሳም፤ ሁካታም አልተፈጠረም፤ ምን እናድርግ በማለት ወጣቱ በአወሊያ ትምርት ቤት ቅጥር-ግቢ ዉስጥ ተሰባሰበ። በቀጣይም ሳምንት በድምጹና በፊርማው መፍትሄ ያፈላለጉ ዘንድ 17 ኮሚቴዎችን መረጠ፤ የተለያዩ ክለሎችም ተወካዮቻቸውን ወደ አዲስ አበባ በመላክ የተወከሉትን ወይም የተመረጡትን ወገኖች አረጋገጡ! መሪዎቻቸዉ አድርገዉ ተቀበሉ።እንግዲህ ኢትዮጲያ ውስጥ 10 ሰው መሰባሰብ በማይችልበት ሁናቴ ነው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን ባደባባይ እዉን ያደረጉት።
የተረጋጋ የሚያረጋጋ የህዝብን ቁጣ የሚያበርድ እንቅስቃሴ
የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ግብታዊነት (ስሜታዊነት)ያልታከለበት መሆኑን በገሃድ አስመስክሯል። ህዝብን ሊያስቆጡ የሚችሉ እስራቶች፣ድብደባና ግርፋት፣ብሎም በንጹሗን ላይ ግድያ ሲፈጽም የተቆጣውን ህዝብ ለማብረድ በአርቆ አሳቢንት የሚንቀሳቀስ የሰከነ አመራር ያለው እንቅስቃሴ በመሆኑ የአሽባሪዎች እንቅስቃሴ ሊሆን አይችልም። የዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ የአመራር አካላት የአገሪቱን ህገ-መንግስት ተከትሎ መፍትሄ ለማምጣትብዙ ጥረዋል፤ ውይይትን እንደ መርህ በመከተል ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በግል ተወያይተዋል፤ በባለስልጣናት አንደበትም ‘እናንተን አሸባሪ ናችሁ የሚል እራሱ አሸባሪ ነው’ ተበሎ ተመስክሮላቸዋል። ዛሬ ግን በውሸቱ ድራማቸዉ-በቅጥፈቱ ‘ጂሃዳዊ ሃረካታቸው’ አሸባሪ አድርገዉ ሊፈርጇቸዉ ቢሞክሩም የህዝብ አይን ሁሉንም እየተመለከተ ነዉና አይሳካላቸዉም።
ለአገር ሰላም ለህዝብ ደህንንነት ቅድሚያ የሰጠ እንቅስቃሴ
ትዕይንተ ህዝብ ሲደረግ የኢትዮጲያን ነባራዊ ሁናቴ ባጤነ መልኩ ነዉ። ጥምቀት ሲከበር አንዋር መስጂድ የነበርው ትዕይንተ ህዝብ ጥምቀትን ለሚያከብሩ ክርስቲያን ወገኖች ክብር ሲባል ወደ ፒያሳ ወይም ሰፈር በኒ- ኑር መስጂድ ተዛውሯል። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል በህይወት ቢኖሩ ተጠያቂ ይሆኑ የነበሩት ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ ሲሞቱ የሚደግፋቸውን ተከታይ እና ቤተሰብ በማክበር ብሎም የኢትዮያዊነትን ባህላዊ ተሞክሮዎች ከግምት ዉስጥ በማስገባት ለአንድ በወር ሙሉ በኢትዮጲያ ዉስጥ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ አልተደረገም ነበር። መለስ ዜናዊ ተጠያቂ ሆነዉ ሳለ እርሳቸዉ በመሞታቸዉ ለአንድ ወር ተቃውሞ አልተደረገም! ታዲያ ይህ እንቅስቃሴ እንዴት የአሸባሪ ሊሆን ይችላል እህቶቼና ወንድሞቼ? ኢትዮጵያዊ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ እንቅስቃሴ ነዉ።ይህ የመብት ጥያቄ በሌሎችአገራት ሊረዳ ቀርቶ ባህር ማዶ ያለውም ኢትዮጵያዊ በውሳኔ ደረጃ ተጽኖ የማድረግ አቅም የለውም፤ ሁላችንም የትግሉ ደጋፊዎች ነን፤ ትግሉ የሚመራው ኢህአዴግ ስልጣን ሲጭብጥ ህጻን በነበሩ ወይም ኢህአዴግ ስልጣን ሲጭብጥ ገና ጥርሳቸውን በነቀሉ ካልያም ኢህአዴግ ሰልጣን ሲጨብጥ ገና በተወለዱ ወጣቶች ነው። ይህ ሰላማዊ ትግል የውጭ ዕርዳታ፣ የሌሎችየሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነት ቢኖርበት ኖሮ መንግስቱ አነፍንፎ ይፋ ባደረገ ነበር፤ ግን የለም! ትግሉ ኢትዮጵያዊ ነው! ትግሉ ፍጹምኢትዮጵያዊ ነው።
ሰላማዊ ቃልኪዳን በአደባባይ የተገባበት ሰላማዊ ትግል
የሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች ብሔር ብሔረሰቦች በጥምረት የሚኖሩባት አገር መሆኗን በጽኑ በማመን በፍጹም በጭራሽ ለሌሎች ስጋት አለመሆናቸዉን ለለማብሰር ሰላማዊና ሰላማዊ የሆነ ጎዳናን መርጠዋል።እስር፣ግርፋት፣ግድያ እና ሌላም የመብት ረገጣ ቢኖር በሰላማዊ የትግል መርህ ብቻ ለመታገል በአንዋር መስጂድ ፊት ለፊት እጅ ለጅ በመያያዝ ከተከታዮቻቸዉ ጋር ቃል ገብተዋል።ታዲያ ይህ ትግል እንደምን የአክራሪዎች ወይም የ አሸባሪዎች ሊሆን ይችላል?
“የምንገልበት አላማ ባይኖረንም የምንሞትበት አላማ አለን”
ሌሎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሚመጣ ለውጥን ያልተቀበለ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነው። ማንንም አናጠቃም ግን ይህንን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ በመጠየቃችን የሚፈጽምብንን ጥቃት ለመቀብል ዝግጁ ነን። የሚል ጽኑ አላማ ያለው እንቅስቃሴ ነው። ተመሪዎች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑበት ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ እራሳቸውም መስዋትነትን በመክፈል አርአያ የሆኑበት እንቅስቃሴ ነው። መሪዎችሁ አልፈረጠጡም! መሪዎችሁ አገርን ጥለው አልኮበለሉም! መሪዎቹ በቃን አንታገልም አላሉም!እሰሩን ግደሉን የምንገልበት አላማ ባይኖረንም የምንሞትለት አላማ አለን ነው ያሉት…ይህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በፍጹም በጭራሽ የአክራሪዎች ወይም የአሸባሪዎች ሊሆን አይችልም ወገኖቼ።
ከአገር መሰደድን መሰረት ያላደረገ እንቅስቃሴ
ዉድ ኢትዮጵያዊያን ሆይ! ይህንን ነዉ አቡነ ጴጥሮስ ያደረጉት አውሮፓ ተንፈላሰው መኖር ይችሉ ነብር ግን አልፈለጉም። አገር ዉስጥ በመሆን ሊመጣ የሚችለወን መከራና ስቃይ ተቀብሎ እንደሻማ ቀልጦ ብርሃን ሆኖ ለማለፍ አላማ ያለው ትግል በመሆኑ ነው መሪዎቹ በእስር እየተሰቃዩ የሚገኙት። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት መንግስቱ በሽምግለናና በቤተሰብ በኩል ብሎም በማስፈራራት ወደ መረጡበት አገር እንድሚሸኛቸውና እንደሚገላግላቸው ቃል ገብቶ ነበር። ታጋዮችን ለሰደት በመዳርግ የሚታወቀው ስርአት የማያውቀው አይነት ትግል ገጥሞታል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ተቀናቃግኖች ተጽዕኖን በሚፈጥሩበት ወቅት አገርን ጥለው እንዲሰደዱ ግፊትን ይፈጥራል።የሙስሊም መሪዎች ግን አንሰደድም ‘የምንገልበት አላማ ባይኖረንም የምንሞትለት አላማ አለን’ ብለው በአሁን ሰአት እስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ ይገግኛሉ። ስለዚህ ምን ይበላቸው? አሸባሪዎች አክራሪዎች እያለ ነው።
የሌሎችን አመኔታ ያገኘ የመብት ጥያቄ
ሌሎች በፕሮፓጋንዳ ሳይሆን እውነታውን በራሳቸም ህሊና እንዲመዝኑ በማድርግ ተቀባይነትን በሌሎች ወገኖች ላይ ያሰረጸ ትግል ነው። ባህር-ማዶ ያለችው ቅዱስ ሲኖዶስ ድጋፏን ሰጥታዋለች፤ ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉ ይ ሃይማኖት አባቶች በግልጽ ድጋፋቸውን መስጠት ባይችሉም ድጋፍ ከራጉኤል ቤተክርስቲያን መምጣቱ ተስተዉሏል። በአንዋር ተቃውሞ ሲደረግ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ምንም በድምጿ ድጋፍ መስጠት ባትችልም በቅዳሴ ወቅት የድምጽ ማጉያዋን (speaker) በማጥፋት ተባብራለች።’ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ ተዘነጋሽ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ’ የሚባለዉ ለዚህ ነዉ። በአገርም በዉጭም ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣የሲቪክ ማህበራት፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ሌሎችም በዲፕሎማሲ ጫና ማሳደር የሚችሉ አለም አቀፍ አካላት ለዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ድጋፍና እዉቅና ሰጥተዉታል።
ሴቶች የጀመሩት ሴቶች የተሳተፉብት እንቅስቃሴ
በደሉ ጭቆናዉ ሲበዛ ከአወሊያ ትምርት ቤት ቅጥር-ግቢ የነጻነት ድምጽ ተሰማ… አንዲት የአወሊያ ተማሪ ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች ‘በአሁን ሰዓት ወንድ አጥተናል እኛ እንታገል ስንል ወደ ጓዳ ግቡ ትሉናላችሁ የማትነሱ ከሆነ በቃ ተዉን እንሙትበት’ አለች…ቆራጥ የሆኑትም ሴቶች ለትግል ተነሱ።በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሴቶች በነቂስ የሚሳተፉብት ድጋፋቸውን የሚሰጡት እንቅስቃሴ ነው።እንግዲህ የአለማችንን ታሪክ እንቃኝ በየትኛዉ ቦታ ሴቶች ጥልቅ በሆነ የ አሸባሪነት ቦታ ሲሳተፉ ታይተዋል? ግን አንድ የሚታወቅ ነገር አለ ሴቶች የጀመሩት አብዮት ግቡን እንደሚመታ! ስለዚህ ለሴቶች ሞቅ ያለ ጭብጨባ እናድርግላቸዉ።
በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሙስሊም ኢትዮጲያዊያን የተሳተፉበት
ህጻን ልጅ በአንዋር መስጂድ አካባቢ እንባ በጉንጮቹ ላይ ኮለል ሲል የታየብት ፎቶ ልብን ይነካል…ከህጻናት እስከ አረጋዊያን ጾታን ሳይለይ ኢትዮጲያዊው ሙስሊም በነቂስ የሚሳተፍበት ድምጹን የሚያሰማብት በኢትዮጲያዊያን ተወልዶ በኢትዮጲያዊያን ያደገ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነው። ይህ የአሸባሪ የአክራሪ በፈጹም ሊሆን አይችልም!
ሁሉም ሙያዊ ግዴታውን እየተወጣ ያለበት ህዝባዊ ትግል
ሁሉም በሙያው መስክ ተሰማርቶ ለጋራ ስኬት የሚጥርበት ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነው።ጸሃፍት በስነ-ፅሁፋዊ ቅኝት የቃኙት፣ከያኒያን የከየኑበት፣ድምጽዉያን ያንጎራጎሩበት፣የኮምፒተር ባለሙያዎች ሙያዊ ግዴታቸዉን የተወጡበት፣ነጋዴዎች የቸሩበት፣የእድሜ ባለጸጋዎች ምርቃታችዉን የሚለግሱበት ከላይ እስከትች መናበብ ያለበት በሰው ልቦና ውስጥ ሰርጾ የገባ ልዩ ህዝብዊ እንቅስቃሴ ነዉ።
ተመሪው ለመሪው ያለውን ታማኝነትና ጽናት ያረጋገጠበት
እንደለሎች የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ተመሪው መሪውን አሳልፎ ሰጥቶ ቤቱ የገባበትየገባበት ትግል አይደለም። ለመሪው ያለውን ታማኛነት እያስመሰከረ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ቀጥሏል።መሪዎቹ ቢታሰሩም ተከታያቸዉ እነርሱን መከተሉን አላቆመም በእለት-ተእለት ኑሮው መሪዎቹን ሳይዘነጋ ለከፈሉት መስዋዕትነት አመስጋኝ በመሆን የመብት ትግሉን አፋፍሞት ይገኛል።
የእስር ቤትን አስፈሪነት ያመከነ ሰላማዊ ትግል
በኢትዮጲያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቃሊቲ እስር ቤት ድረስ በመሄድ የቻሉትን ያህል ታሳሪዎች ጠይቀዋል። ታሳሪዎች ዉጪ ካሉ እጮኛዎቻቸዉ ጋር በእስር ቤት ዉስጥ ጋብቻ የፈጸሙበት ለጽናታዊ ተምሳሊትነት የበቁበት ልዩ ሰላማዊ ትግል ነዉ።
በህዝባዊ ድጋፍ ኢፍትሃዊ ችሎትን ያጋለጸ እንቅስቃሴ
በሺዎች በመሆን ፍርድ ቤት በመሄድና በአካባቢው በመገኛት ለመሪዎቻቸው ያላቸወን ጽናት አሳይተዋል።በካንጋሮዉ ፍርድ ቤት (kangaroo court)ኢፍትሃዊ ብያኔን ለመስጠት የተሳነዉ ፍርድ ቤትም ችሎቱ በዝግ እንዲሆንና ወደ ቃሊቲ እስር ቤት እንዲዛወር አድርጎ ነበር። ባለጉዳዮቹ እና ህዝቡ ችሎቱ ለጋዜጠኞችና ለዲፕሎማቶች ክፍት ይሁን እያሉ ሳሉ መንግስቱ ፍትሃዊነትን ማስፈን የሚፈልግ ከሆነ ለምን ችሎቱን በድብቅ ማረግ ፈለገ? ምን የሚደብቀዉ ነገር አለ? ምን አልባትም መንግስት መደበቅ የሚፈልገዉ የራሱን አሸባሪነት ይሆናል።ታዲያ ማነው አሸባሪ?…ማነው ተሸባሪ?
የስርአቱን አምባገነናዊ ጸብ አጫሪንት ጠንቅቆ ያወቀ ትግል
አውቶቢስን ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች እንዲሰብሩ ደህንነቶች ቢያመጡ ወጣቶቹ አንሰብርም እያሉ ድምጽ ያሰማሉ… እጅ ለእጅ ተያይዘው አውቶቢሱ የህዝብ ንብረት ነው በማለት ከለላ (human chain) ሲሰሩ ታይቷል ። ጸብ-አጫሪ ፈደራል ፖሊስ ታርጋ በሌለው ሞተር ሳይክል ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች መሃከል በፍጥነት ሲነዳ ገለል በማለት በጭብጨባ አስተናግደውታል።ደህንነቶች ድንጋይ (Cobblestones) እያመጡ የበተኑበት አጋጣሚ እንዳለ ተስተዉሏል፤ ጎረምሳ ወጣት ‘እባካችሁን ድንጋይ ወርውር ድንጋይ ወርውር ይለኛልና አጆቼን እሰሩልኝ’ እያለ የተንሰቀሰቀበት ሰላማዊ ትግል ነው። ይህ የመንግስትን ጸብ አጫሪነት የተቋቋመ ሰላማዊ ትግል በመሆኑ የአሸባሪዎች ሊሆን አይችልም።
በቤታችን ሰላም አጣን
ህዝብን ለማሸበር በወጣ የጸረ-ሽብር ህግን ከለላ በማድረግ ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ ያለ ፖሊስ ማዘዣ ጭንብል(mask) ለባሽ ካድሬዎች፣ደህነቶችና ፖሊሶች በየሰው ቤት በመግባት ፍተሻ፣ማስፈራራት፣ማሸማቀቅ፣ማሸበር፤ ዝርፊያን ሲያከናዉኑ ትዉልዱ ከመሪዎቹ ባገኘዉ መመሪያ መሰረት ይህንን የማሸበር ተግባር በትእግስት ተቋቁሟል።በዚህም ፍተሻ ወቅት ገንዘብም ንብረት ተዘርፏል ፤የሴቶች ጌጣጌጧጦች ተሰርቀዋል፤ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶችም እንደሚያመላከቱት በፍተሻው ወቅት ሴቶች በፖሊሰና በካድሬዎች (rape)ተደፍረዋል። በየሰዉ ቤት እየሄዱ በፍተሻ ስም ሽብርን ለምን የሚፈጽሙ ይመስላቹሃል? ወንዱ ቤቴን አላስደፍርም በማለት ከነርሱ ጋር እንዲፋለምና አሸባሪን አግኘን ብለው የሚፈልጉትን ለማድረግ ነዉ። በቤቱ ሰላም እያጣ ሰላምን ለማምጣት መስዋእትነትን እየከፈለ ያለዉ ትዉልድም ይሁን መሪዎቹ አሸባሪ ሊሆኑ አይችሉም! በዚህ ሰላማዊ የትግል ሂደት ዉስጥ አሸባሪነቱ የተረጋገጠዉ ግን መንግስት ነዉ።
ግልጽነት በእጅጉ የተሞላበት ትግል
የትግሉ ሂደት በሙሉ በቪዲዮ እየተቀረጸ ለአለሙ ማህበረሰብ ታይቷል።የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዉ ህጋዊ እንቅስቃሴዎች በመጽሃፍ መልኩ ተጠርዘው ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ይመለክተው ዘንድ በአለም ላይ ተበትኖዋል። እያንዳንዱ የሄዱበት ጎዳና ፍንትዉ ብሎ ለህዝብም ለታሪክም ተቀምጧል ትግሉና ታጋዮች ግልጽነትን ተላብሰዋል ግን እራሳችዉን መንግስት በሚል ስያሜ ዉስጥ የሸጎጡ አሸባሪዎች ግልጽነትን በማመናመን ለሰሩት ኢፍትሃዊ ተግባር ከመጠየቅ አይድኑም።
በመንግስት የፕሮፓጋንዳ የስነ-ልቦና ጫና ያልደረሰበት በመንግስት አመራር ላይ የስነ-ልቦናጫናያሳደረ እቅስቃሴ
መንግስት ህዝባዊ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የዉሸት አታሞዉን በመደለቅና ፕሮፓጋንዳዉን በመንዛት የስነ-ልቦና ጫናን ለመፍጠር ሞክሯል…የሙስሊሙ መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ግን ፍጹም የሆነን ሰላማዊ ወኔን ታጥቀዉ በመንግስት የአመራር አካላት ላይ ጫና ፍጥረዋል። የፖሊስ ሐይላት ዱላችውን ሲጥሉ ተሰተውለዋል፤ የኢህአዴግ አባላቶች በግልጽ በቪዲኦና በድምጽ እየተቅዱ ፓርቲያቸው ስተት ላይ መሆኑን በመናገር ፓርቲውን ጥለው እንደሚወጡ አስጠንቅቀዋል፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቅዋሜያቸውን ገልፀዋል፤ ትዛዝ አንቅበልም ብለው ትጥቅ የፈቱ የፖሊስ ሃይላትም አሉ፤ባለሰልጣን ብቻም ሳይሆኑ ክርስቲያን ባለ ሰልጣኖችም ቅሬታቸውን እየገለጹነው፤ አንባገነናዊ ስርዓትም ዉስጥ ከፍተኛ መከፋፈል እንዳለም በይፋ ይነገራል፤ይህ ሰላማዊ እና ህዝባዊ እንቅስቃሴ ስርዓቱን ለመቦርቦር የበቃ በመሆኑ በስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጫናም እየፈጠረ ይገኛል።
ስልጡን ትዉልድ የሰለጠነ ትግል
የዘመኑን ቴክኖሎጂ በአግባቡ የተጠቀመ ሰላማዊ ትግል ነው። መንግስት ሬዲዮ ቴሌቪዝንን በማፈን (Jamming) በማድረግ መረጃን ሲያፍን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴን በተገቢዉ መልኩ በጥቅም ላይ ያዋለ ትውልድ ነው።በፌስቡክ፣በቲዊተር፣ በቴክስት፣ ድረ-ገጽና የእጅ ስልክ (cell phone) ብሎም መልክት በማስተላለፍ(word of mouth) መረጃን በማንሸራሸር የመንግስትን ሙሉ ለሙሉ የማፈን ሴራን ያከሸፈ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው ።
አለም አቅፋዊ እውቅናን ያተረፈ ሰላማዊ እንቅሰቃሴ
የአለሙ ማህበረሰብ ያጣውን የፍትህ የዲሞክራሲ እጦትን በሰላማዊ መንገድ ማግኘት እንደሚቻል ያበሰረ፤ ከአፍሪካ ቀንድ የፈነጠቀ ብርሃን ነው። አምንስቲ ኢንተትርናችናል፣ ሂይውማን ራይትዎች ፣የአሜሪካ አለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን ፣ለጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄና ሌሎችም አገራዊና አለም-አቀፋዊ ተቋማት እውቅና የሰጡት ሰላማዊነቱን ያረጋገጡለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው።
ውድ ኢትዮጲያዊያን ሆይ! አክራሪነትና አሸባሪነት በሌሎች ላይ የራሰን አመለካከት በሃይል ለመጫን የሚደረግ ተግባርና ጥረት ነው። ከላይ የጠቀስናቸውን እውነታዎችን ከቃኘን እራሱን መንግስት ነኝ ብሎ በሚጠራው የኢትዮጲያ መንግስት እንደ አክራሪና አሸባሪ እየተንቅሳቀሰ ነው። አክራሪዎች-አሸባሪዎች ፊታቸውን ይሸፈናሉ፤ ፊታቸውን የሸፈኑ ፖሊሶችና ካድሬዎች ጥቃትን በማታ እየሄዱ የፈፅማሉ። አክራሪዎችና አሸባሪዎች ይዘርፋሉ፤ መንግስት ነኝ የሚለው አካል እየዘረፈ ነው። አክራሪዎችና አሸባሪዎች ያፍናሉ፣ ያስራሉ፣ ይገድላሉ መንግስቱም ተመሳሳይ ድርጊትን በህዝቡ ላይ እየፈፀመ ነው። አንባገነናዊዉ መንግስት የስልጣንእድሜዉን ለማራዘም በሙስሊሙና በክርስቲያኑ ላይ የሰነ-ልቦና ጦርነት ከፍቷል። እኛ ደግሞበአልበገር ባይነት በኢትዮጲያዊ ጀግንነት እምቢኝ ለፍቅር እምቢኝ ለአንደነት ልነለው ይገባል።
ዉድ ኢትዮጵያዉያን ሆይ! ብዙ የግፍ መዓት በእናት አገራችን ላይ ተስተዉሏል፤ ሴቶች እህቶቻችንን እና እናቶቻችንን በጎረምሳ ልጃቸው ወይም በጎረምሳ ወንድማቸው ፊት የፌዴራል ፖሊሶች በጥፊ ይመታሉ፤ ጎረምሳው ተናዶ እጁን እንዲሰነዝር…እናቶች አዛውንት አሮጊቶችን በከስክስ ጫማ ይረግጣሉ ጎረምሳው ልጃቸው ተነስቶ ድንጋይ እንዲወረወር እጁን እንዲሰነዘር …ይህን ሁሉ በመታገስ ከወራትም ባሻገር ወደ አመታት የዘለገዉ ሰላማዊ ትግል የሁሉም በመሆኑ በዘር በሐይማኖት ሳንለያይ ልንከባከበዉ ይገባል።
እናንተ የተስፋ ባለቤት የሆናችሁ ወገኖቼ! ይህ ትግል ልቦች የተጣመሩበት ነዉ። ልቦች የተጣመሩበትን ትግል መቀልበሱ የልምዣት በመሆኑ ልቦቻችን ሁሌም በተስፋ ይሞሉ። ልቡ በተስፋ የተሞላዉ ታዛዡ ትዉልድ ቁም ሲባል ይቆማል፣ተነስ ሲባል ይነሳል፣አፍህን ያዝ ሲባል ይይዛል፤ እንዲህ በግብረገባዊ ብቃት የታነጸን ትዉልድ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም አምላክ ይጠብቀዋል። የልብ ባለቤት የሆነዉ ጥራትና ልዕልዕና የተገባዉ አላህ የምንወዳትን የምንሳሳላትን እናት አገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቃት። አመሰግናለሁ…አላህ ይስጥልኝ! ልብ ያለዉ ልብ ይበል።
ድምጻችን ይሰማ እንበል በጋራ.. ድምጻችን ይሰማ… ድምጻችን ይሰማ…
ድሮ ባገራችን ሰላም አጣን ነበር የሚባለዉ አሁን ደግሞ በቤታችን ሰላም አጣን ስለሚባል ይህንኑ እዚህ አዳርሽ ዉስጥ ለማስታወስ በቤታችን ሰላም አጣን እንበል….በቤታችን ሰላም አጣን…በቤታችን ሰላም አጣን…
ልብ ያለዉ ልብ ይበል!
No comments:
Post a Comment