ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ ተወግዶ በምትኩ ሌላ የተሻለ የአገሪቱን መላ ዜጐችና ማህበረሰቦች የጋራ ብሔራዊ ጥቅም የሚጠብቅ መንግሥት የሚቋቋመው እንዴት ነው? ዛሬ ይህን ጥያቄ የማያነሳና የማይጥል አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የለም። ጥያቄውን ለመመለስ የሚሞክሩ ተፎካካሪ አስተያየቶች፣ ትችቶችና ክርክሮች ከአገሪቱ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ተንቀሳቃሽ ግለሰቦችና ተቆርቋሪ ዜጐች በመገናኛ ብዙሃን፣ በአለም አቀፉ ድርና በፓልቶክ ከመሰራጨት ቦዝነው አያውቁም። ሆኖም በየፊናው ሲደረጉ የነበሩ፣ አሁንም የሚደረጉ የለውጥ ትግል ሃሳብ ልውውጦችና ግጭቶች በሚገባ የማይፈትሹት አንድ ዋና ነባር ችግር አለ። ይህ ጣጣ የዛሬው የለውጥ ትግል መወጣት ያለበት፣ በአገር ጉዳዮችና በፖለቲካ መካከል ያሉ ከሥር መሠረታቸው የተዛቡና የተመሳቀሉ ግንኙነቶችን የሚመለከት ነው። በዝች መጣጥፍ የማነሳው ይህን ዋና ጉዳይ ነው።
ፖለቲካ ለአገር አስፈላጊነቱ ወይም ለአንድ ማህበረሰብ ያለው ጥቅም እሳት ለሰው ልጅ በሚሰጠው በጐ አገልግሎት ይመሰላል። እሳት ለሰው ጥሩ አገልጋይ እንደሆነ ሁሉ፣ ፖለቲካም የአገርና የህዝብ ጥቅም መጠበቂያ ዋና መሣሪያ መሆን ይችላል። ነገር ግን በአግባቡ ካልተገለገሉበት እሳት ከቁጥጥር የወጣ ቃጠሎ ሆኖ የሰው ሕይወትና ንብረት አጥፊ የበላይ ጌታ እንደሚሆን ሁሉ፣ ፖለቲካም በልኩና በቦታው ካልተጠቀሙበት የአገርን ህልውና የሚለበልብና የሚያሳርር፣ በጠቅላላ ነፃ ህብረተሰብን የሚጻረርና የተለያዩ የጐሳ ማህበረሰቦችን “ብሔራውነት” ሳይቀር የራሱ ፍጡር፣ ተቀጥላና ታዛዥ አገልጋይ የሚያደርግ አምባገነናዊ ባህሪ ወይም እምቅ ሃይል አለው።
ያለፈው ወደ አራት አስርተ ዓመታት የሚጠጋው የእትዮጵያ ድህረ አብዮት ዘመን በሚያሳዝን ሁኔታ ያሳየን ነገር ቢኖር ፖለቲካ አገርንና ስቪል ህብረተሰብን የሚያፍንና በበላይነት የሚቆጣጠር፣ የሚከፋፍልና የሚጨቁን መሆኑን ነው። በደርግም ሆነ በዛሬው የወያኔ አገዛዝ፣ ፖለቲካ ብሔራዊ ህልውናችንን ያኮሰሰው በጠባብ ወገናዊና ርዩተዓለማዊ ይዘቱ ብቻ ሳይሆን እንዲያው በለከት የለሽ አጥቂ ተስፋፊነቱ፣ በሁሉም የአገርና የህዝብ ጉዳይ አለሁበት፣ ሁሉንም አልሚም አጥፊም እኔ ነኝ ባይነቱ ነው። ከዚህ የተትረፈረፈ ቅኝ ግዛቱ ያመለጠና አንጻራዊ ነፃነቱን የጠበቀ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ክፍል ወይም የአገር ጉዳይ ዘርፍ አለ ማለት ያዳግታል። በአገሪቱ በሰፈነው ያለገደብ የመስፋፋት ባህሪ ባለው ፖለቲካ ግርዶሽ ከተጣለባቸው መካከል የአገር ታሪክና ህልውና፣ የጐሳ ማህበረሰቦች ማንነት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ከፍተኛ ትምህርት፣ ሃይማኖትና መንፈሳዊ ኑሮ፣ ልማት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ የአገርና የህብረተሰብ ጥቅም ዘርፎች የሚገባቸውን ብርሃንና ድምቀት ተነፍገው ደብዝዘዋል፣ ፖለቲካ ቅኝ ግዛት አጨልሟቸዋል።
ይህ ማለት ዛሬ በየረድፉና በየደረጃው መደረግ ያለበት አገር አቀፍ መሰረታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ የወያኔ አገዛዝ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ተቃዋሚ ወገኖችም ከሞላ ጐደል የሚጋሩትን አለገደብ ተስፋፊ ፖለቲካን ራሱን ለመለወጥ፣ ለማሻሻልና በቦታው ለማስቀመጥ ነው። እዚህ ላይ መንስኤ ግንዛቤያችን ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ውጥረት ምንጩ የአገሪቱ የራሷ ተጨባጭ ጉዳዮችና ችግሮች ሳይሆኑ ስር ነቀል ወይም ተራማጅ ለውጥ እናመጣለን ብለን ችግሮቹን የቀረጽንባቸው ከብሔራዊ ህልውናችን ጋር የተቃቃሩ የፖለቲካ ሃሳብ ፎርሙላዎች፣ ረቂቅ የርዩተአለም ፈርጆችና ተጨባጭ የሃሳብ ይዘታቸው የመነመነ ሸንጋይ የፖለቲካ ቃላት ክምችቶች መሆናቸው ነው። እነዚህን ሁሉ ዝባዝንኬዎች ያካተተውን ተራማጅ የተባለ የፖለቲካ ባህላችንን በጠቅላላ አዙረን ሳንፈትሽና ሳንለውጥ ወይም ሳናሻሽል በእትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንፈጥራለን ማለት ሙጃ የዋጠውን መሬት ሳያርሙና ሳያርሱ እላዩ ላይ ዝም ብሎ ዘር በትኖ ሰብል ለማምራት እንደመሞከር ይቆጠራል። የሚሆን ነገር አይደለም። በተለየ ሁኔታም ቢሆን የቅርቡ የግብጽ ዲሞክራሲያዊ ምርጫና ውጤቱ ያሳዩን ይህንኑ ነው።
እንግዲህ የኢትዮጵያ ተሃድሶ ትግል አላማ አገሪቱን ከዚህ ወይም ከዚያ የፖለቲካ ወገን ጭቆና ለማዳን ብቻ ሳይሆን ለአርባ አመት ከተጫናት ጠቅላላ የፖለቲካ ባርነት ለማላቀቅ፣ ነፃ ህብረተሰብ ለማዳበር፣ ብሎም የአገር ጥቅም በሚገባ የሚጠብቅ፣ ለህዝብ ተጠያቂነት ያለው ብሔረ-መንግሥት ለመገንባት ነው። በዚህም መልክ በአገሪቱ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ መሠረት ለመጣል ነው።
ከዚህ ዋና ገንዛቤ በመነሳት፣ የዛሬው የለውጥ ትግል ፖለቲካን በልኩና በቦታው ይዞ፣ የአገርን ህልውና በማያወላውል መልክ ተቀብሎና ጠብቆ መኪያሄድ ይኖርበታል። ነገደ ብዙው አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህ የፖለቲካ ወገኖች ወይም እነዚያ ጐሰኛ ሊሂቃን ከፋፍለው እንደ ከብት የሚነዱት፣ ተወልዶ ከአደገባቸውና ከተቋቋመባቸው የገዛ አገሩ አካባቢዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የሚያፈናቅሉት ሳይሆን ሉአላዊነቱ የተከበረና የተጠበቀ መሆኑን ትግሉ በመርህ፣ በስልትና በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህ ፈታኝ ግን አስፈላጊ የለውጥ ትግል በተማሪዎች ንቅናቄ ተጀምሮ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” በተባለው የወያኔዎች ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ በተገባደደው ረጅምና መራር የፖለቲካ ጉዟችን ላለቀው፣ ለተጐዳውና አሁንም መከራ ለሚያየው የኢትዮጵያ ህዝብ መከፈል ያለበት ዕዳ ወይም ውለታ ነው።
ትግሉን ከሚጠብቁት ፈተናዎች መካከል በኔ ግምት በዋነኛነት የሚፈረጁ ሶስት ተልዕኮዎች አሉ። አንደኛው አገርን በዘር ፖለቲካ የመቃወም ልምድ መስበር ነው፣ ሁለተኛው ተቃዋሚ የፖለቲካና የጐሳ ወገኖችን መለጣጠፍ ወይም “ቅንጅታዊ” እንቅስቃሴዎች ውስንነት መወጣት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ አገርና ፖለቲካ ያላቸውን ግንኙነት በአዲስና የተሻለ መንገድ መገንዘብ (ብሎም የአገሪቱን ዜጐችና ማህበረሰቦች ማስገንዘብ) ይሆናል። በዝች ጽሑፍና በክፍል ሁለት ተከታይዋ በነዚህ ጉዳዮች አካባቢ የማቀርባችው ጥቂት ሃሳቦችና አስተያየቶች አሉኝ። የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጉዳዮች እዚህ እመለከትና ሶስተኛውን በተከታዩ መጣጥፍ እሄድበታለሁ። ጽሑፎቹን የማቀርበው በቀላል ወገናዊነት መልክ ወይም በድፍን የተቃራኒ ተከራካሪነት ስሜት ሳይሆን የዛሬው የለውጥ ትግል ላይ በጐ ተጨባጭ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ ተስፋ በጣልኩበት የትንተናና ትችት መንፈስ ነው።
አገርን በዘር ፖለቲካ የመቃወም ልምድ እንስበር
ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን ብሔራዊ ውጥረትና አስጊ ሁኔታ ጠለቅ ብለን ስንፈትሸ ሁለት መወገድ ያለባቸው የተዛመዱ ነባራዊ ፖለቲካ ልምዶች እናያለን። አንዱ የጐሳ ማህበረሰቦችን ራስነት ወይም ልዩነቶች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልውና ጋር በድፍኑ የማጻረር ወይም ጐሳዊ ማንነትንና የኢትዮጵያን አንድነት እርስ በርስ የማጋለል ጽንፈኛ የግራ ክንፍ ፖለቲካ ልምድ ወይም አዝማሚያ ነው። ይህ አዝማሚያ የኢትዮጵያ ህልውና “ከብሔረሰቦች” ድምር ወይም ጥርቅም ባሻገር የማይታየው፣ ቢታየውም በፖለቲካ ትክክለኛነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ተነሳስቶ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን ሲያንስ ችላ የሚልና በጐሪጥ አይን የሚያይ፣ ሲበዛ ደግሞ የሚቃወምና የሚጫን ነው።
ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሌላው ችግር ደግሞ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የጎሳ ማህበረሰቦች ጉዳዮች፣ ማንነታቸውና የጋራ ኢትዮጵያዊነታቸውም ጭምር፣ በቀጥታና በጅምላ ከተወሰኑ ለብሔሮች ነፃነትና እኩልነት ቆመናል ከሚሉ ራሳቸውን ከኢትዮጵያዊነት ያገለሉ ወይም ያራቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊ እይታዎች፣ ስሌቶች፣ ግቦችና እንቅስቃሴዎች ጋር መደባለቅ ነው። ይህን የተምታታ ዘር ላይ በፖለቲካ እግር ቆሞ አገርን የማራቅና የመቃወም ልምድ መስበር ግድ ይላል። ብሔረሰብ ከጠባብና ብቸኛ ብሔርተኝነት፣ ዘር ከአክራሪ ዘረኛነት ጋር መዘባረቁ መቆም አለበት። በዚህ ጐጂ መልክ፣ ትስስር ያላቸው እውን የአገሪቱ ነገዶችና ባህላዊ ማህበረሰቦች በተወሰኑ ከፋፋይ ረቂቅ የርዩተዓለም ፈርጆች፣ አብዮታዊ በተባሉ የፖለቲካ ምስሎችና ትረካዎች ተውጠው ወይም ተተክተው ማየታችን ይብቃ።
የዚህን መሠረታዊ ችግር ዋና ክስተት ለመጥቀስ፣ ሕወሓት/ኢህአዴግ ስለ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ነፃነትና እኩልነት ቃል በቅል ያለውን ቢልም ይህ የሚባልላቸው የጐሳ ክልሎች የመንግስት ሥልጣን ጨባጩ የወያኔ ፓርቲ ራሱ የበላይ ገዢ ሆኖ እንደፈለገውና እንደተመቸው የፈጠራቸው፣ የቀነሳቸው፣ ያስፋፋቸውና የደማመራቸው መሆኑ አያጠያይቅም። በአስመሳይ “ፌደራላዊነት” አከማችቶ ከውስጣቸው በወጡና ለበላይ ገዢው ወገን ተባባሪ በሆኑ አጐብዳጅ የጐሳ ሊህቃን አማካኝነት በተዘዋዋሪ እንዳሰኘው የሚገዛቸው መሆኑ ምንም ያህል ስውር አይደለም። ሆኖም ይህን እውነታ መረዳትና ለኢተዮጵያ ህዝብ በሚገባ ማስረዳት ወገንተኛ ጐሰኝነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጋጪ የሆነን የፖለቲካ ልምድ ለመክላት የሚወሰድ ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። የአገሪቱንና የተለያዩ ማህበረሰቦቿን ነፃነት እውን ለማድረግ የሚያስችል ወይም የሚረዳ የዛሬው የለውጥ ትግል መነሻ ግንዛቤ ነው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንግዲህ “ብሔራዊነት” በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ፣ በርዩተዓለም ቅርጹም ሆነ በተግባራዊ ይዘቱ በአንድ አናሳ አምባገነናዊ ገዢ ወገን ቁጥጥር ሥር እንደወደቀ፣ አገርና ፖለቲካ እንደተመሳቀለ ግልጽ ነው። ግልጽ ያልሆነው፣ እንዲያውም የሚገርመው ለወያኔ አገዛዝና በጠቅላላ በአገሪቱ ለተስፋፋው የማንነት ፖለቲካ ርዩተዓለማዊ ምሰሶና ርብራብ የሆነው፣ ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ያልተለየን “የብሔር፣ ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን” ቀኖና ወይም አፈታሪክ በኢትዮጵያዊያን መካከል፣ በተለይ በምሁራኑ ክፍል፣ ለመሠረታዊ ጥያቄ፣ ግምገማና የሃሳብ ልውውጥ፣ በፖለቲካ ወገኖች ዘንድ ደግሞ በመርህ ደረጃ ለውይይት፣ ለድርድር፣ ለአቋም ሽግሽግና ለስምምነት በሚገባ ተከፍቶ አለማወቁ ነው። በኔ ግምት ይህ ዋና ጉድለት በዛሬው የለውጥ ትግል መሟላት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ተሃድሶ ከዚህ ያላነሰ ክንውን ይጠብቃል፣ ይገባዋልም።
ለምን ቢባል የእውን ፍችው ከቃል በቃል ትርጉሙ ጋር የሚጻረረው አፈታሪክ እንደ ሻብዕያ፣ ሕወሓትና ኦነግ ላሉ የኢትዮጵያዊነት ደመኞች የአገሪቱን ብሔራዊ ህልውና መካጂያና መቃወሚያ የፖለቲካ መሳሪያ የነበረና ዛሬም የሆነ ነው። ከዚያ አልፎም ይህ አፈታሪካዊ የፖለቲካ ፎርሙላ አስተሳሰባቸው ምንም ያህል እንደገና ባልታነጸ የአገሪቱ ግራ ክንፈኞች ዘንድ ተቀባይነቱ የተጓደለ አይምስልም። ለምሳሌ የግንቦት ሰባት መሪ አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ አመለካከቱን ይለውጥ አይለውጥ ባላውቅም በ1985 ያለውን መጥቀስ ይቻላል። የተማሪዎች ንቅናቄ አክትሞ፣ ደርግ ለአስራ ሰባት ዓመት አገሪቱን ቀጥቅጦ ከገዛ በኋላ አገዛዙ ፈርሶ፣ ወያኔዎች የመንግስት ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ አመታቸው የአማራው ሕዝብ ከዬት ወዴት? በተባለች ትንሽ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ጐሳዊ ብሔርተኝነት “ፈጠራ ሳይሆን…እውነታ” መሆኑን፣ ነገር ግን “አንድ ሃገር፣ አንድ ሕዝብ” ላይ የቆመ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት “ፈጠራ” መሆኑን ገልጾልን ነበር። ከጥቂት ጊዜ በፊት አንዳርጋቸው ያወደሰው የኤርትራው አምባገነናዊ ገዢ ኢሳያስ አፍወርቂ ባለፈው ሰሞን ባለው መልክ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት (በኢሳያስ አባባል ያውም ከመቶ አመት ያነሰ) ታሪክ እንደሆነም በተጠቀሰችው መጽሐፍ የዛሬው የግንቦት ሰባት መሪ ነግሮን እንደነበር ይታወሳል።
እዚህ ላይ ዋናው ፍሬ ነገር አንድ ግለሰብም ሆነ ድርጅት በአገር ጉዳይ ላይ የነበረው ወይም ያለው አመለካከት ሳይሆን ለአርባ አመት ያልተለየን፣ በዛሬው ብሔራዊ ትግል ከሥር መሠረቱ መለወጥ ያለበት የተመሳቀለ አገር ጐጂ ጠቅላላ የፖለቲካ አስተሳሰብና እነቅስቃሴ ልምድ ወይም ባህል ነው። ባህሉ ላይ በተለያዩ ደረጃዎች የጽንሰሃሳብና የእሴት ጥያቄች፣አክሎም ተግባራዊ ጉዳዮች ማንሳት፣ መወያየትና ብሔራዊ ስምምነት መፍጠር ይቻላል፣ ያስፈልጋልም። በዚህ መልክ በስፋትና በጥልቀት የምናደርጋቸው ምሁራዊ፣ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ጥረቶች የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማስወገድ ከሚደረገው ብሔራዊ እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተያያዙ ናቸው። አገዛዙን ለማወላለቅና አማራጩን ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የጠቅላላው የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ለውጥ ትግል አካል ነው እንጂ ተለይቶ የሚታይና የሚኪያሄድ አይደለም።
“የቅንጅት” ተቃውሞን ውስንነት እንወጣ
አገር ቤትና ከአገር ውጭ በሚገኙ የተደራጁ የፖለቲካ ወገኖች በኩል (እንዲሁም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አካባቢዎች) ከሃያ ዓመት በላይ ሲካሄዱ የቆዩት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የተወሰነ እድገትና መሻሻል ቢያሳዩም፣ የወያኔን አገዛዝ ከማስወገድ ወይም ራሱን በማሻሻል መልሶ እንዲያንጽ ተጽዕኖ ከማድረግ አኳያ ምንም ያህል ለውጥ እንዳላመጡ የታወቀ ነገር ነው። በተመጣጣኝ እርግጠኛነት የማናውቀው መሠረታዊ ጉድለታቸው ወይም ድክመታቸው እምን ላይ እንደሆነ ነው። ይሁን እንጂ ለዚህ ሁኔታ ብዙ ማሰብ የማይጠይቅ፣ ማንም የሚሰጠው የተለመደ መልስ አለ። ይኸውም የተቃዋሚ ወገኖችን መከፋፈል፣ ትብብረ መፍጠር አለመቻል የሚጠቁም ነው። ከብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚደመጠው እሮሮ ምነው ተቃዋሚ ሃይሎች ተባብረው መሥራት አቃታቸው፣ ለምን አንድነት ተሳናቸው ነው።
እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን የፖለቲካ ልዩነቶች የግድ አገር ጐጂ እንዳልሆኑ ነው። እንዲያውም አንዳንዴ ከማይሆን የተሟዘዘ የወገንተኛ አካሎች ክምችትና ትብብር ይልቅ አማራጭ ሃሳቦችና ፖሊሲዎች የሚያፈልቅ የንቁ ፓርቲዎች ውድድር (“የፖለቲካ ገበያ” እንበለው) አገርንና ህዝብን ይበልጥ ሊጠቅም ይችላል። ለአለፉት ሃያ አመታት አገር ቤትና ከአገር ውጭ በፖለቲካ ድርጅቶችና ወገኖች መካከል የጦፈ የለውጥ ሃሳቦች፣ ስልቶች፣ ዘዴዎችና እንቅስቃሴዎች ፉክክር ሰፍኖ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላለንበት ብሔራዊ ብዥታና ውጥረት ምናልባት ይህን ያህል አንጋለጥ ይሆን ነበር። ፉክክሩ በሃሳብ ጥራታቸውና የእንቅስቃሴ ስልታቸው የላቁ አንድ ሁለት ፓርቲዎች አንጥሮ ያወጣ ይሆን ነበር። ስለዚህ ዋናው ችግራችን የነበረውና ዛሬም የሆነው የተቃዋሚ ወገኖች መለያየትና መፏከት ሳይሆን ልዩነቶቹና ፉክቻዎቹ አማራጭ ሃሳቦች በማቅረብ ረገድ ወይም አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከማፍራት አኳያ ባመዛኙ ፋይዳ ቢስ መሆናቸው ነው።
አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ስላሉ ፀረ ወያኔ ወገኖች መከፋፈል ኢትዮጵያዊያን ላሰሙት ብሶት መልስ የሚመስል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ የታየ አዝማሚያ ቢኖር የፖለቲካና የጐሳ ቡድኖች “ቅንጅት” መፍጠር ነው። እርግጥ በመርህም ሆነ በስልት ደረጃ የተቃዋሚ ወገኖች ትብብር ተገቢ ሊሆን እንደሚችል ብዙ አያከራክርም። በሆነው ባልሆነው እየተከፋፈሉ በአክራሪ ወገንተኛነትና ዘረኛነት መንፈስ እርስ በርስ መነታረክና መናቆር ለማንም ወገን እንደማይበጅና የተቃውሞ ትግሉን የትም እንደማያደርሰው ግልጽ ነው። እንዲያውም የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ እድሜ ይበልጥ ማራዘም ነው የሚሆነው።
ነገር ግን በሰላማዊ እንቅስቃሴም ሆነ በትጥቅ ትግል መስክ የተለያዩ ወገኖችና ድርጅቶች በድፍኑ መለጣጠፍ ወይም መደማመር ብሎ ነገር የለም። መቀናጀትን በሚመለከት ልንገነዘባቸው የሚገባና መወጣት ያለብን ችግሮች አሉ። በጥቅል ለመናገር የተለያዩ ወገኖች ቅልቅል ወይም ቅንጅት ራሱን የቻለ አቅም ወይም ብቸኛ እሴት ሳይሆን ከሌሎች አቅሞችና ጥንካሬዎች ጋር መጣጣምና መገናዘብ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ትብብሩ ሩቅ አይሄድም። እንዲያውም ከመሬት አይነሳም። ለምሳሌ ብሔራዊ ንቃት ወይም እውቀትና የፖለቲካ ስልት የሚሰጡት የትግል አቅም የጐደለው፣ ወይም የነዚህ አይነት አቅሞች አስፈላጊነት የማይታየው የተቃዋሚ ወገኖች ክምችት የህዝብን ህብረትም ሆነ የአገርን አንድነት የሚያዳብር አመራር በብቃት ሊሰጥ አይችልም። የራሱን ውስጠ-ትብብር እንኳን አረጋግጦና አጥብቆ መንቀሳቀስ ያዳግተዋል። ዘላቂ የእድገት አቅጣጫ የያዘ፣ በሂደት የሚጐለብትና የሚሰፋ፣ ብሎም ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ አስወግዶ የተሻለ አማራጭ የፖለቲካ ሥርዓት የሚገነባ ብሔራዊ ትግል ማቀናበር ይሆንለታል ማለት አዳጋች ነው።
ከዚህ መሠረታዊ ውስንነት ጋር የተያያዙ በይበልጥ ተዘርዝረው ሊጠቀሱ የሚችሉ ችግሮችም አሉ። እዚህ ብዙ ሐተታ ውስጥ ሳንገባ የተቀናጅ ወገኖችን ተንቀሳቃሽ ራስነት ወይም ማንነት በሚመለከት የሚከተሉትን ጥቂት ነጥቦች ባጭሩ ማስቀመጥ ይበቃል። ከድርጅታዊ ተንቀሳቃሽነት አኳያ፣ መለጣጠፍን እንደ ዋና የትግል መርህና ዘዴ አድርገው የሚወስዱ ወይም ለሌሎች ቡድኖች በውስጣቸው መሰባሰብ ቅድሚያ የሚሰጡ ወገኖች ሲጀመር ፖለቲካዊና አገራዊ ማንነታቸው የደበዘዘ፣ ባመዛኙ ራሳቸውን በራሳቸው ከማሳደግና ከማጐልበት ይልቅ በሌሎች ድጋፍ ለመጠናከር የሚሹ ናቸው። ራሳቸውን ችለው ሰፊና ጥልቅ የለውጥ ትግል ሃሳብና ስልት የማፍለቅ አቅምም ድፍረትም ይጐላቸዋል። በቅንጅት ሥራቸውም የተወሰኑ የፖለቲካና የጐሳ ቡድኖችን ቅልቅል ከመፍጠር ባሻገር በሰፊው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ክፍሎች አንድነትና ትብብር ላይ ያተኮረ ራዕይ ወይም መንፈስ የራቃቸው ወገኖች ናቸው።
ስለዚህ ወገኖቹ በተናጠልም ሆነ በቅንጅት ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ከመሠረቱ ብልሹ የሆነ ፖለቲካዊና ብሔራዊ ሁኔታ የመቀልበስ እውን ወይም እምቅ ችሎታ ምንም ያህል አይታይባቸውም ማለት ይቻላል። ይህ ድክመት ከአንዳንዶቹ ተቀናጅ ድርጅቶች የለውጥ አመለካከት ጋር የተያያዘ ነው። ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን ማውረድና የተወሰኑ የፖለቲካ መልሶ እነጻዎች ቢፈልጉም ከአገዛዝ ሥርዓቱ ጋር ጥልቅ ቅራኔ ወይም ጥል አላቸው ማለት ያዳግታል። አኪያሄዳቸው ያለውን ሥርዓት – ጐሳ ላይ የተማከለ “ብሔራዊ” አጀንዳውንና አሠራሩን – በዝርዝር ለማሻሻል፣ ግርድፍ ስህተቶቹን ለማረም፣ ክፍተቶቹን ለመዝጋትና የጐደለውን ለመጨመር እንጂ ከሥር መሠረቱ ለመለወጥ አይመስልም።
እንግዲህ የቅንጅት ፖለቲካ ዋና ውስንነት ኢትዮጵያ በውስጧ ከተካተቱ የተለያዩ የጐሳ፣ የማህበረሰብ፣ የባህልና የፖለቲካ ወገኖች ድምር ያለፈ፣ በታሪካዊና ዘመናዊ ዜግነት ላይ የተመሠረተ ህልውና ያላት አገር መሆኗን በሚገባ ተገንዝቦና አምኖ ይህን እምነት ወደ አመርቂ ብሔራዊ የተቃውሞ ትግል ስልት መተርጐም አለመፈለግ ወይም አለመቻል ነው ማለት ነው። ይህ ውስንነት ራሱ ደግሞ ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለግማሽ ምእተ ዓመት ያህል ኢትዮጵያዊነትን ሲቦረቡር የቆየው ጽንፈኛ የግራ ክንፍ ፖለቲካ ተጽእኖ ውጤት ነው። የፖለቲካ ባህሉን የተከተሉ፣ ዛሬም የሚከተሉ ወገኖች የተለያዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን “እኩልነት” ወይም “ራስ ገዝነት” በቀኖናዊ መልክ ሲያራምዱ ያየነው ነገር ስለ ማህበረሰቦቹ መብቶች ማሰባቸውን ብቻ ሳይሆን ለመብቶቹ ሰፊ አገራዊ አገባብና መመዘኛዎች ወይም መስፍርቶች ምንም ያህል የተጨነቁ እንዳልነበረና ዛሬም እንደማይጨነቁ ነው። አገርን በፖለቲካ፣ በተለይ በጐሳ ብሔርተኝነት ፖለቲካ መተካት ይሏል ይሄ ነው።
ለማጠቃለል፣ በማንነት ፖለቲካና በኢትዮጵያዊነት መካከል ያለን አለመግባባት አድበስብሰው ይዘው፣ በውስጣቸው መሠረታዊ አንድነት ወይም ስምምነት ሳይፈጥሩ፣ እንዴት አድርገው ነው የተቃዋሚ ወገኖች ቅንጅቶች ወይም ስብስቦች ከአገር ወዳድ ዜጐችና ማህበረሰቦች ጋር ለዘለቄታው መስማማት የሚችሉት? ይህ ጥያቄ የፓርቲ መዋቅር አይደለሁም፣ የተለያዩ ወገኖችን ያካተትኩ እንቅስቃሴ ነኝ የሚለውን ግንቦት ሰባትን በተለይ ይመለከታል።
በተከታይ መጣጥፍ አከራካሪ የሆነውን የግንቦት ሰባት እንቅስቃሴን በመቃኘት ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋውን የተዛባ የአገርና የፖለቲካ ትስስር በዛሬው የለውጥ ትግል እንዴት መለወጥና ማሻሻል ይቻላል ከሚል ሃሳብ በመነሳት መጠነኛ ትንተናና ትችት አቀርባለሁ። ወደዚያው መሸጋገሪያ በሚሆን ነጥብ ይችን ጽሑፍ እንግዲህ ልደምድም። የግንቦት ሰባትን አወዛጋቢ የአገር ጉዳይ አቀራረብና እንቅስቃሴ በሚመለከት ፍሬ ነገሩ ድርጅቱ ከእንከነ ብዙው የኢትዮጵያ ግራ ክንፍ ፖለቲካ ልምድ መማር ያለበትን አሉታዊ ትምህርት፣ በሌላ አባባል ምን ማድረግ እንደሌለበት፣ በሚገባ ተምሯል ወይ ነው።
The writer can be reached at tdemmellash@comcast.net
No comments:
Post a Comment