እረፍት አደርግ ብየ ከማህበራዊ መገናኛ መድረኩ ገለል ባልኩባቸው እንደ ብርሃን ፍጥነት በሚወረወሩት ባለፉት ጥቂት ቀናት ከበርካታ ወዳጆቸ በርካታ መልዕክቶች ይደርሱኛል። ብዙው መልዕክት ደግሞ የሚያጠነጥነው በጅዳ እና በአካባቢው በተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች አሰቃቂ ስቃይ ላይ ያተኮራል … ለነገሩ የአብዛኞቹ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆኑ ከመልዕክቶች ጋር የሚላኩልኝ መረጃዎች እረፍት የሚነሱ ናቸው! …
አዎ ተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር በመረጃነት የታጨቀባቸውን የመልዕክት መረጃ ጭብጦች እውነታ ለማረጋገጥ ወደ ጅዳ ቆንስል አመራሁ … መኪናየን አቁሜ ትንሽ እንደ ተራመድኩ እያለ ከፊት ለፊቴ አንዲት ልጅ እግር ኢትዮጵያዊ ብቻዋን እያወራች ስታልፍ ስመለከት በመደናገጥ ሰላምታ አቅረብኩላት፣ መልስ ሳትሰጠኝ አለፈች! ደነገጥኩና ባለሁበት ቆሜ በአይኔ ተከተልኳት …
በፈጣን እርምጃ የሚያቃጥል የሚለበልበውን መሬት የምትደቃበትን የጠቆረ ባዶ እግሯን፣ እንደነገሩ ከላይዋ ላይ ደረብ ያደረገችውን ጥቁር “አበያዋን” እና ከፍ ሲል የተንጨፈረረ ጸጉሯን እያየሁ ፈዝዠ ቀረሁ … ከድንጋጤና ከፍርሃት ለአፍታ ነፍሴ መለስ ሲልልኝ ጠደፍ ጠደፍ ብየ ወደ ሔደችበት አቅጣጫ ተከተልኳት … ርቃኛለች … ሮጨ ልደርስባት ባለመቻሌ መኪናየን ወዳቆምኩት በመሔድ አስነስቸ ተከተልኳት … በደቂቃዎች ልዩነት ተሰወረችኝ! ምናልባት በዙሪያው በቆሙት መኪኖች መካከል፣ በመንገዱ ዳርም ሆነ በቤቶች አጥር ጥላ ፈልጋ ደክሟት አረፍ ብላ እንደሆነ በማለት መኪናየን አቆሜ ፍለጋየን ቀጠልኩ … ብዙ ሞክሬ አልተሳካልኝም … ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰላም እያልኳት ገላምጣኝ የሄደቸው እህት የለችም!
በትካዜ ተውጨ በአሳቻ መንገድ አገኛት እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባው እያማተርኩ ሳቀና ከጅዳ ቆንስል ግቢ በግምት 600 መቶ ሜትር ርቀት በአንድ አረብ ቱጃር ቤት አጥር ስር በሚገኝ አንድ ዛፍ ስር፣ ከመንገዱ ዳር አንዲት እህት ወድቃ ተመለከትኩ! ክው ክው ብየ ደነገጥኩ … ተጠጋኋት! የሚያምረው አይኗ ወይቧል፣ ሰውነቷ ደግሞ ዝላለች፣ ላብ ፊቷን አውዝቶታል፣ አፏ ግን አመድ መስሎ ደርቋል! ጠይም ባለ ሰልካካዋ አፍንጫ ለግላጋ መልከ መልካሟን እህት ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ማውራት ቻልኩ … ለነገሩ ማውራት አይባልም! ለረጅም ደቂቃዎች ለማውራት ያደረግኩት ሙከራ በሰጠችኝ ጥቂት መልስ አፏ ተፈታ ማለቱ ይቀላል! ዝርዝር ማውራት ግን አትፈልግም … ምንም አይነት እርዳታ እንደማትፈልግ በአጭሩ ገለጸችልኝ! … በቃ ከዚህ ባለፈ ብዙ ማውራትና መቀጠል አልቻልኩም! የማደርገው ባጣ ቢያንስ በቆንስሉ መጠለያ ግቢ ከታጨቁትና በከፋ አደጋ ላይ እንዳሉ ከሰማሁትና አይቸ ካረጋገጥኩት 150 ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ጋር ቢደባልቋት በሚል ለጅዳው ቆንስል ሃላፊ ለአቶ ዘነበ ከበደና ለዲያስፖራው እና በመጠለያ ላሉት ተፈናቃዮች እህቶች ተጠሪ ዲፕሎማት ለወ/ሮ ሙንትሃ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩላቸው አያነሱም …
የማደርገውን እያሰላሰልኩ ሳልራመድ በአጋጣሚ አይኔን ወደ ቀኝ አሻግሬ ስመለከት አንድ ሌላ እህት ከቅርብ ርቀት ወድቃ ተመለከትኩ … ይህችው እህት በቁራጭ ካርቶን ቢጤ ተቀምጣና ጀርባዋን ለመንገዱ ሰጥታ እጇን እያፍተለተለች ትዘፍናለች ትስቃለች! ይህችንም ደጋግሜ ጠየቅኳት እየገላመጠች እያየችኝ መልሳ ትስቅና ትዘፍናለች! ዘፈኑ ኦሮምኛ መሆኑን እንጅ ዘፋኝና ትርጉሙን አላውቀውም! … ፈዝዠ ቀረሁ!
ደጋግሜ ወደ ቆንስሉ ሃላፊዎች፣ ወደ ኮሚኒቲ ሹሞች ብደውልም ስልኬን አይመልሱትም! … እንዲህ ስባዝን አንድ ለቆንስል እና ከኮሚኒቲ ሃላፊዎች ቅርበት ያለው ወንድም ከበስተኋላየ መጥቶ ጀርባየን ቸብ አድርጎ አስደነገጠኝ! ድንጋጤየ ገርሞት “አቶ ነብዩ ምነው? ደነገጥክኮ!” አለኝ በአግራሞት እንደ መሳቅ እያለ … የደነገጥኩት ከበስተኋላ የተኛቸው እህት ተነስታ የነረተችኝን መሰሎኝ መሆኑን እውነቱን ገልጨለት እንደ ቀልድ አድርገን ተሳሳቅን፣ ብዙም ሳንቆይ ስለ ወደቁት ለእህቶች አንስተን ተጨዋዎትን … ወዳጀ በቅርብ ርቀት የወደቁ እህቶች እያሳየኝ እንዲህ አለኝ “አየህ ይህችኛዋ ለሶስት ቀናት አንዴ እዚህ ትወድቃለች አንዴ እዚያ ታገኛታለህ ፣ ያችኛዋንም እንደዚያው …” ብሎ ሊቀጥል ሲል በጥያቄ አስቆምኩት ታዲያ ምን አደረግክ? “እኔ ምን አደርጋለሁ! የእኛ ዜጋ ረክሷል እኮ … እስኪ ወደ መጠለያውና ግባ፣ ያበዱ የታመሙ ደህና መጥተው በመጠለያው የሚያብዱትን ሲያዩ እነሱም የሚያብዱት ቁጥር እኮ ቀላል አይደለም!” ሲል የመርከሳችን ነገር ሊያስረግጥልኝ ሞከረ! ግን ይህንን ስታይ ለምን ወደ ምትቀርባቸው ሃላፊዎች ደውለህ አታስረዳቸውምና ሌላው ቢቀር ከግቢው ውስጥ ከተደባለቁ ይበዱም ይሙቱ ማንነታቸው ቢያንስ ይታወቃል? አልኩት፣ ከግቢ ውጭ እንዲህ ሲወድቁ የሚከተልባቸው አደጋ እንደሚከፋ፣ ከወራት በፊት ከቆንስሉ እና ከመጠለያው ግቢ በር ካለው ዛፍ ራሷን ሰቅላ ስለሞተቸው፣ ከቅርብ ርቀር ከሚገኘው ሌላ ዛፍ ወድቃ ስለሞተችው እህት የሚያውቀው የምናውቀውን አሳዛኝ ክስተት ለማስረዳትም ላማስረዳትም እየሞከርኩ ብየ አከልኩለት … አይገባህም እንደ ማለት የለበጣ ሳቁን ከፊቱ ላይ እየነሰነሰ ምላሽ ንግግሩን ቀጠለ … “ያንተ ነገር እኔ መቸም እንዳንተ አላበድኩም፣ ፓስፖርት ማደስ፣ ቤተሰቦቸን ሃገር ቤት ሔጀ መጠየቅ እፈልጋለሁ፣ አንተ እንኳ ዱላውንና መገፋቱን ለምደህዋል፣ በል አሱን ተወው!” ሲል እያሳሳቀ ደገመና “እንዳንተ መች አበድኩ!” ብሎኝ አረፈው …
ፍርሃትን ፈርቶ ሰብዕናውን የደፈጠጠበት ይህ አጋጣሚ ቢያስቆጣኝም የተሰማኝን አፈንድቸ ወዳጀን ላስበረግገው አልፈለግኩም … እንዲያውም ላግባባው ሞከርኩ … ለሁሉም እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥም አንድም ለሃላፊዎች አለያም ያገባኛል ለምንል ሰወች መረጃውን ብታቀብሉን መልካም ነበር በማለት ሃላፊዎች ለማግኘት እና ለማሳወቅ ፈልጌ አይመልሱም ብየ ወሬየን ሳልጨርስ ንግግሬን ከአፌ አቋረጠው እና መለሰልኝ “አትድከም ማናቸውም ላንተ አይመልሱልህም፣ እያጋለጥካቸውና ድክምታቸውን ለአለም እያሳየህ ባይመልሱልህ አይደንቀኝም፣ በነገራችን ላይ ሳልፈልገው ልንገርህ አስገደድከኝ፣ ባለቤቴ የፌስቡክ ጓደኛህ ነች፣ በጣም ትከታተልሃለች፣ ታከብርሃለች፣ ባንተ ነገር ሁሌ እንጣላለን። እኔ በሃላፊዎች አካባቢ የምትባለውን ስለምሰማ ለእለት ጉርሱ ሳያነሰው ለምን ይጽፋል፣ ለምን ከመንግስት ጋር ይፋጠጣል፣ ልጆቹን ለምን አርፎ አያሳድግም ባይ ነኝ። እርሷ ግን በእኔ ሃሳብ ፍጹም አትስማማም። መረጃውን የሚቀበል አጣ እንጅ ጠቃሚ ነው ትላለች። እኔም የምለው ያንን ነው ሰሚ ሳይገኝ መጮህ አንተን ይጎዳሃል ባይ ነኝ … እና ብዙ ጊዜ በዚህ ተጣልተን ሁሉ እናውቃለን። አንድ በቅርቡ የሰራችውን ልንገርህ … ከሁለት ቀን በፊት ስለ መጠለያው ቪዲዮ በፌስቡክ መልዕክት መቀበያ አልደረሰህም?” ሲል ጠየቀኝ፣ ማን እንደላከው ንገረኝና ልነገርህ አልኩት፣ ነገረኝ፣ መረጃው እንደደረሰኝ አረጋገጥኩለት፣ ተግባባን … ንግግሩን ቀጠለ …
“አየህ ሚስቴ እኔ እንድታየው ብሰጣት ላንተ ላከችልህ። ያበዱትን እና በጸሃይ ላይ የሚንቀለቀሉ እህቶች ቢያሳዝኑኝ፣ በቅርቡ በድብቅ በመጠለያው ያነሳሁት ነው። እንግዶች ሃገር ቤት ይመጣሉ ስለተባለ እና ለሃላፊዎች ሁኔታውን ለማሳየት ያነሳሁትን ቪዲዮ ነው!” ብሎ በጠራራው ጸሃይ አቁሞ ካወራኝ በኋላ ከእኔ ጋር እዚህ አካባቢ መቆሙን ከአሸባሪ ጋር እንደ መተባበር ይቆጠራል የሚል በነገር ቀልድ ሸንቁጦኝ መልሴን ሳይጠብቅ እየሳቀ ተሰናብቶኝ እየተጣደፈ ወደ ቆንስሉ ግቢ አመራ …
ፊቴን ወደ ወደቁት ሁለት እህቶች መለስ ቀለስ እያደረግኩ ብቻየን ቀረሁ! የማደርገው ጠፋኝ … አሁንም መልሸ መላልሸ ወደ ቆንስል ሃላፊዎች ደወልኩ … ወዳጀ እውነቱን ነው፣ አያነሱም!… ሁሌ ሲከፋኝ እና መፍትሔ ሳጣ የምጠይቀውን ጥያቄ ራሴን ጠየቅኩት … ግን ለምን? አልኩ … መልስ ባላገኝም …!
ብዙም ሳልቆይ ወደ ቆንስሉ ግቢ አመራሁ፣ ወደ ግቢው ዘልቄ ገባሁ፣ ግቢው በሰው ተሞልቷል። ኢትዮጵያዊው ወገን የሳውዲ ምህረት አዋጅ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከመጠናቀቁ በፊት የተለያዩ ሰነዶችና አገልግሎት ፈልጎ የመጣ መሆኑን አውቃለሁ፣ እኒህኞቹ ችግር ቢገባኝም፣ ዛሬ አንገብጋቢ ሆኖ አልታየኝም። ተጋፍቸ ወደ ቆንስል ሃላፊው የሚወስደው በር ብደርስም ወደ ፎቅ የሚወስደው በር በካሜራና በአውቶማቲክ በር ተጠርቅሟል። የበሩን መክፈቻ በመጫን አያንጫረርኩት ለማስከፈት ሞከርኩ፣ አልተቻለም … ተሰላችቸ ልመለስ ስል መልስ ተሰጠኝ “ሁሉም ዲፕሎማቶች ስብሰባ ላይ ናቸው” የሚል መልስ! ከቶ ለማን ይሆን የሚሰበሰቡት? አልኩ … ለእኛ መሆኑ አልዋጥልህ አለኝ እና እያጉረመረምኩ ግቢውን ለቅቄ ወደ መጠለያው አመራሁ …
ወደ መጠለያው ከመግባቴ በፊት ወድቀው ያየኋቸውን እህቶች ለማንሳት ከመጠለያው በር ያገኘኋትን እህት ትተባበረኝ ዘንድ ለምንኳት፣ “እሽ!” አለችኝ! ተያይዘን ወደ ወደቁት እህቶች አመራን … አገኘናቸው አግባብተን ማስገባት ቀርቶ ማነጋገር አልቻልነም … ይህች እህቴ ያየችውን ማመን አቅቷት በእንባ ተሞላች፣ ሳታስበው ሃዘን ውስጠ ከተትኳት፣ አዘንኩ! እሷኑ አይዞሽ ብየ ሸኝቸ፣ ለራሴው ሰላም አጥቸ ወደ መጠለያው አመራሁ …
ከዚህ ቀደም በደረሰኝ መረጃ የተመለከትኳቸው ያበዱ የታመሙትን ጨምሮ ጤነኞች ተፈናቃይ እህቶች ከግቢው ፈሰው ተመለከትኩ … ልብስ ታጥቦና ሳይታጠብ እንደ ሃገር ቤት በየአጥሩ፣ በደረጃው፣ በመሰላሉና በበሮቹ ላይ ተሰቅሏል … ሻንጣው በአንድ ጥግ ተከምሯል … ይህን ጨምሮ አሳዛኙን የተፈናቃዮች ውሎ በፎቶ ሆነ ቪዲዮ ማንሳት ክልክል ነው ስለተባለ ማንሳት አልፈልግኩም! ግቢው ጉስቁልናቸው ከፊታቸው በሚነበብ እህቶች፣ ባዘኑ በተጨነቁ፣ በውስጥ ደዌ የተደቆሱ፣ በአዕምሮ ጭንቀት በተለከፉ፣ በተዳከሙ፣ ተስፋ በቆረጡ እህቶች ጢም ብሎ ሞልቷል፣ ወደ 150 ደርሰዋል፣ የሚያድሩት በጠባቧ ክፍልና ሜዳ ላይ እንደሆነ ሰምቻለሁ … ያየሁት አንገቴን አስደፍቶ አሳፈረኝ! ወደ ካፍቴሪያው ዘለቅኩ …
በካፍቴሪያው እንደገባሁ መቀመጫ ስፈልግ ቅድም በር አግኝቸው የነበረው ወንድምና ካፍቴርያውን ሳይሳለሙ ውለው ከማያድሩት ሌሎች ባልንጀሮቸ ተቀምጦ አየሁት … የደመቀ ወሬ ይዘዋል።እንዴት እንዳየኝ ባይገባኝም እጁን እያወናጨፈ ጠርቶ እንድቀመጥ ጋበዘኝ! ራመድ ራመድ ብየ ሄጀ ሰላምታ ከተለዋዎጥኩ በኋላ ተቀመጥኩ፣ ከቀናት በፊት በካፍቴርያው ያለውን የሟች ጠቅላይ ሚኒስትርን ፎቶ በቦርሳዋ ስትደበድብ ያየኋት እህት በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከጓኛዋ ጋር ተረጋግታ ተቀምጣለች። ዛሬ ተሽሏታል ብየ ሳላበቃ “ወግዱልኝ!” ብላ አምባርቃ ጮኸች … ከወዳጆቸ ጋር ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩባት ቅጽበት እስክነሳ በጠረጴዛው ይወራ የነበረውን ወሬ ለመጻፍ ግን ይከብደኛል … ብቻ በግቢው ችግረኛ ግፉዕ ወገን እየተንገላታ እንደሆነ ተረስቷል … ሰብዕና ሳይሆን ተራ የፖለቲካ ቡትቶ ጉዳይ ሆኖ እና የባጥ የቆጡን ወሬ እያመጡ የማውራቱ እና የመፈላሰፉ ወሬ ግን ያስጠላል …. በሽታ ሆነኝ …
ከቶ ይህ መከራ እየታየ እንዴት ይታረፋል! ብጣቂ መረጃ እንኳ እንካችሁ! ከእረፍት ስመለስ ከደረሰኝ እና ከማውቀው መረጃ አልፎ አልፎ ጨልፊም ቢሆን በቅርቡ ሳላስቃኛችሁ አልቀርም …
ለሁሉም አንድየ ቸር ያሰማን! የምስራች የምናዎራ ያድርገን!
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment