Tuesday, October 22, 2013

ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል? በሆላንድ

መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2006
በአሥራ አምስተኛው  ምዕተ-ዓመት ግድም ሆላንድ የታወቀ የባሕር ኃይል ሆኖ ከደቡብ አፍሪካ እስከደቡብ አሜሪካ፣ የኔዘርላንድ የቆዳ ስፋት 41 526 ኪሜ ካሬ ወይም የትግራይ ግማሽ ነው፤ የሕዝቡም ቁጥር አሥራ ስድስት ሚልዮን ተኩል አይሞላም፤ የትግራይን ግማሽ በሚሆን መሬት ላይ የትግራይን ሦስት እጥፍ ግድም የሚያህሉ ሰዎች ይኖሩበታል፤ ሆኖም ጥንት ከደቡብ አፍሪካ እሰከደቡብ አሜሪካ፣ በእስያም ኢንዶኒዝያ ላይ የቅኝ ግዛት የዘረጋ ትንሽ አገር ነበር፤ አሁንም ትንሽ አገር ነው፤ አሁንም ሀብታም አገር ነው፤ ዋናው ሀብቱ ሕዝቡ ነው፤ አሥራ አምስት ሚልዮን ግድም የሚሆን ሕዝብ ከባሕር ጋር እየታገለ ያገኘውን መሬት ይዞ እንዲህ ያለ ሀብታም መሆኑን ሳይ እኛ በጣም ሰፊ መሬትና ስድስት ጊዜ ያህል ከኔዘርላንድ የሚበዛ ሕዝብ እያለን ቆሞ-ቀር ብቻ ሳይሆን ወደኋላ መገስገሳችን ሳይሻክረኝ አልቀረም።

ኔዘርላንድ በከፊል በባሕር ተሸፍኖ የነበረ ነው፤ በሰው ኃይልና በሰው ጥበብ ባሕሩ ተገፍቶና ተገድቦ መሬቱ ለጥቅም እንዲውል ተደርጓል፤ በዓለም ውስጥ እንደኔዘርላንድ ከባሕር ጋር ታግሎ ያሸነፈና ከባሕር ጠለል በታች የነበረውንና ረግረጉን መሬት ለጥቅም ያዋለ አገር የለም፤ በተለይ የሰሜኑ ክፍል ከባሕር የወጣ መሬት ነው።
በኔዘርላንድ ገጠርና ከተማ እየገጠሙ ናቸው፤ በየመንገዱ ላይ እርሻ፣ ላሞችና በጎች፣ አንዲሁም ፈረሶች ሲግጡ ይታያሉ፤ እዚህ ከባሕር ጋር እየታገሉ ባወጡት መሬት ላይ ቤታቸውንም ሆነ እርሻቸውን በፈለጉት ሁኔታ መጠቀም ይችላሉ።
ኔዘርላንድ በዴሞክራሲያዊ የዘውድ መንግሥት የሚተዳደር አገር ነው፤ በቅርቡ የኔዘርላንድ ንግሥት ዕድሜያቸው ስለገፋ ዘውዱን ለልጃቸው አስረክበው እሳቸው በክብር እቤታቸው ወይም እግቢያቸው ውለዋል፤ በኔዘርላንድ የመብት ጉዳይ ዋና ሥፍራን የሚይዝ ነው፤ በአምስተርዳም ከተማ ከሚኖር ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንጫዋወት በኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነው ስለፍትሕ ጉዳይ አነሣሁ፤ በዚሁ ላይ እንዳለን አንድ ታሪክ ነገረኝ፤ በዚሁ አገር አንድ ቤተሰብ አገር ሰላም ብለው ተኝተዋል፤ ድንገት ስልክ ይደወልና የቤት እመቤቲቱ ስልኩን ለመመለስ ወደሳሎን ስትገባ የሳሎኑ በር ተከፍቶ ታያለች፤  ሁኔታው ቀፈፋትና ዘወር ስትል አንድ ጎረቤት የሆነ ሰው የእስዋን ቴሌቪዥን ይዞ እንደቆመ ዓይን ለዓይን ይጋጠማሉ፤ እየተርበደበደች ለፖሊስ ስልክ ስትደውል ጎረቤትዋ ቴሌቪዥኑን እንደያዘ ከሴትዋ ቤት ወጥቶ ወደራሱ ቤት ይገባና በሩን ቆልፎ መብራቱን አጥፍቶ ይቀመጣል።
የተጠሩት ፖሊሶች ይመጣሉ፤ ሴቲቱ የደረሰባትን ትናገርና የ‹‹ሌባው››ን ቤት እያሳየች አሁን ብትገቡ ቴሌቪዥኔን ታገኛላችሁ ትላቸዋች፤  አስቲ ቴሌቪዥኑን የገዛሽበትን ደረሰኝ አሳዪን ይላሉ፤ ደረሰኝ የላትም፤ የቴሌቪዥኑን መለያ ቁጥር ይጠይቃሉ፤ ያንንም አታውቀውም፤ ፖሊሶቹ ግራ ተጋብተው ታዲያ ሰውዬውን ከመኝታው አስነሥተንና በሩን አስከፍተን ምን አድርግ ልንለው ነው፤ እዚያ ቤት ውስጥ ያለው ቴሌቪዥን የአንቺ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ ስለሌለሽ ሰውዬውን አናሸብረውም ብለዋት ሄዱ! ይህ ትምህርት ይሆነዋል፤ ይገባዋል፤ ለምትሉት ሰው፣ በተለይ ሕግ አስከባሪ ነው ለምትሉት ንገሩ!
በዚህ ታሪክ ስደነቅ ሌላ አስደናቂ ታሪክ ነገረኝ፤ አንድ ወሮ-በላ ቢጤ አንድ ቤት ውስጥ በቀዳዳ ገብቶ ተኝቶአል፤ የቤቱ እመቤት ልታስወጣው ብትሞክር አልቻለችም፤ ቢቸግራት ለባልዋ ትነግራለች፤ አበሻ ባልዋ ይሄድና ሰውዬውን አስወጥቶ ሁለተኛ እዚህ ብትመጣ እጅህን እቆርጠዋለሁ፤ ይለዋል፤ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቱ የቤቱን በር ደወል ሰምቶ ሲከፍት ፖሊሶች ያያል፤ ከፖሊሶቹ ጋር ቀደም ሲል እጅህን እቆርጠዋለሁ የተባለው ሰው ቆሞአል፤ ፖሊሶቹ እጅህን እቆርጥሃለሁ ያለው እሱ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ሰውዬው በዛቻው እንደተጨነቀና የዚህም ጭንቀት ምክንያት አንተ ነህ፤ ሰውዬውን አስሸበርከው! በማለት ማስፈራራቱ ማሰቃየት እንደሆነ አስረድተው እንዳይደግምህ ይሉትና ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው ብለው ይጠይቁታል፤ ከአፍሪካ ሲላቸው አፍሪካ ሂድና እጅ እቆርጣለሁ እያልህ አስፈራራ፤ እዚህ ግን እንዲህ ማለት አይቻልም፤ ብለውት ይሄዳሉ፤ መለስ ዜናዊ ጣታችሁን እንቆርጣለን፤ እጃችሁን እንቆርጣለን፤ እያለ በሕዝብ ምክር ቤት ሲናገር ሁላችንም ሰምተናል፤ እሱ አሸባሪ ሳይባል እኛም ተሸበርን ብለን የምንጮህበት ሳናገኝ ተላልፈናል።
በኔዘርላንድ አንዳንድ ቦግ ብለው የሚታዩ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ መንገዶቻቸው በጣም ግሩም ናቸው፤ ለቢስክሌት ልዩና ራሱን የቻለ መንገድ አላቸው፤  በኔዘርላንድ የባህል ጭቆና የሚባል ነገር የለም፤ እንዲያውም የባህል ጭቆናን የሚሽር ባህል እየገነቡ ናቸው ለማለት ይቻላል፤ እኛ የባህል ባሪያዎች ሆነን እንኖራለን፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ባይስማሙበትም የመክሸፋችን ዋና ምክንያት ተጨቁነን ጭቆናን አክባሪዎች መሆናችን ነው፤ የችግራችን ሁሉ መሠረት ይህ ክፉ ባህል ነው።
mesfinwoldemariam.wordpress.com

No comments:

Post a Comment