የወያኔ መንግስት የተመሰረተበትና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የመንግስታዊ ስርዓት መሰረት የሆነው የጎሳ ፌደራሊዝም የጎሳን ማንነትና ልዩነትን ዓይነተኛ የፖለቲካ ማደራጃ አድርጎአቸዋል። የጎሳ ፌዴራሊዝም ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን
ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው። ዲሞክራሲ ሁሉን አሳታፊ እንጂ አንድን ግለሰብ በጎሳ ማንነቱ ምክንያት ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሚያደርግ አይደለም። ፖለቲካ በጎሳ ማንነትና መስፈርት ላይ ተመስርቶ አንድን ሰው አንተ የእኔ ጎሳ አባል አይደለህም ብሎ በጎሳ ማንነቱ ምክንያት ሲያገል፤ ሌላውን ደግሞ አንተ የጎሳ አባሌ ነህ ብሎ ሲያሳትፍና ሲያቅፍ፤ ይህን አይነቱ ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ዲሞክራሲ የሚባለውን አስተሳሰብ በጽኑ ይቃረናል።
በዚህም ምክንያት በጎሳ ማንነት ላይ ተመስርቶ የሚደራጅ የፖለቲካ ስርዓት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ የተለያየ የእምነት ተከታዮች፤ የተለያዩ የጎሳ ተወላጆች እንደ ሰው ወይም እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሚያስተሳስሯቸውና በሚጋሯቸው በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደ አንድ ሀገር ዜጎች እንዳይገናኙ የሚያደርግ በመሆኑ አፍራሽ እንጂ ገንቢ አይደለም። የጎሳ ፌዴራሊዝም በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በልዩነቶቻቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ሊያቋርጥ የማይችል ጥላቻን በማራገብ ለጋራ ጥፋትና እልቂት የሚጋብዝ፤ በባህል መጠበቅ፤ በጎሳ መብት መጠበቅ ስም ያንድ ጎሳ ልሂቃን እኛ የዚህ ጎሳ ብቸኛ ተወካዮች ነን ብለው ባንድ ነጻ ማህበረስብ ውስጥ ሊደረግ የሚገባውን በጎሳ ማንነት ሳይሆን በፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ጤናማ የፖለቲካ ውድድር ወይም ፉክክር የሚሸሹበትን ኢ-ዲሞክራሲያዊ አመለካከትና አሰራር ያራምዳል። ይህም የጎሳን ማንነት መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ወደ ፋሽስታዊ የዘር ፍጅትና የእርስ በርስ ጥላቻ የሚያመራ አደገኛ ርዕዮተ ዓለም ነው። የፈረሰችው የትላንትናዋ ዩጎዝላቪያ የጎሳ ፌዴራሊዝም በአንድ ሀገር ላይ የሚያስከትለውን ጥፋትና ፍጅት አሳይታናለች። የጎሳ ፌዴሊዝም አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ያነሳሳል ምክንያቱም የጎሳ ፌደራሊዝም ባፈጣጠሩ ህዝብን በሚለያይ ማንነት ላይ የተመሰረተና በልዩነት ላይ ያተኮረ ስለሆነ ነው። የጎሳ ፌደራሊዝም የጎሳን ማንነት ብቻ በማጉላት ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን ያደበዝዛል፤ ያንድ ሃገር ዜጋዎች በመካካላቸው የግንብ አጥር እንዲሰሩ ያደርጋል፡ ያለያያል፡ ያቃቅራል። አንድ-ወጥ ጎሳ ለመፍጠርና “ንጹህ ደም ያላቸውን የአንድ ጎሳ ተወላጆች” ባንድ ኩታ-ገጠም ክልል ውስጥ ለማሰባሰብ የሚደረገው ጥረት በግድ ከዚያ ከንጹሁ ጎሳ ተወላጆች ውጭ ያሉትን የሌሎች ጎሳ ተወላጆችን “ከንጹሁ ጎሳ ተወላጆች” ክልል በሃይል ወደ ማስወጣቱ የጭፍጨፋ ሂደት ያመራል። ትላንት በምስራቅ ወለጋ፤ በጉራ ፈርዳ ዛሬ ደግሞ በቢኒሻንጉል የታየው ዘግናኝ ድርጊት የጎሳ ፌዴራሊዝም ውጤት ነው። የጎሳ ፌዴራሊዝም ዋና አራማጅ የሆኑት የኦሮሞ ብሄረተኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አሜሪካን ሀገር ይታተም በነበረ ኢትዮጵያን ኤክዛምነር (Ethiopian Examiner) በሚባል መጽሄት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በሰኔ ወር 1993 በጻፉት አንድ መጣጥፍ ውስጥ የሚከተለውን ሃሳብ አስፍረው ነበር። “ኦሮሞዎች የኦሮሞ ዞኖች ወይም ቀጠናዎች ሁሉ ባንድ ላይ ተጠቃለው አንድ የኦሮሞ ክልል ሥር እንዲሆኑ ይፈልጋሉ” (Bulcha Demeksa, Ethiopian Examiner, June 1993)። ይህ የአቶ ቡልቻ ሃሳብ በረጅም ትልሙ አንደ-ወጥ የሆነ ያንድ ጎሳ ተወላጆች ብቻ የሚኖሩበት ክልል ለመፍጠር፤ ብሎም ከኦሮሞ ጎሳ ውጭ ያሉ ሌሎች ጎሳዎችን በማስወገድ ራሱን የቻለ አንድ ነጻ ሀገር ወደ ለማቋቋም ያለመ ሂደት እየተከተለ መሆኑን ማንም የማገናዘብ ችሉታ ያለው ሰው ይረዳል። ጎሳን መሰረት ያደረገ ክልል በመጨረሻ እናንተ የእኛ ጎሳ አባሎች ስላልሆናቸሁ ከዚህ ውጡ ወደሚለው የጎሳ ጽዳት ( ethnic cleansing ) እንደሚያመራ ትላንት በምስራቅ ወለጋ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በቤኒሻንጉልና በኦጋዴን የተከሰተው ሁኔታ ያሳየናል። አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለውና ጭራሽ ሊቀለበስ የማይችል እውነታ መሆኑን በሚከተለው መንገድ እርግጠኛ ሆነው በዚሁ ኢትዮጵያን ኤክዛምነር በተሰኛው ባንድ ወቅት በአሜሪካ ይታተም በነበረው ወርሃዊ መጽሄት ላይ እ. አ. አቆጣጠር በግንቦት 1993 በጻፉት ጽሁፍ ውስጥ ይነግሩናል። “በኢትዮጵያ በጎሳ ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝም ወደ ኋላ ሊመለስ አይችልም ምክንያቱም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ይፈልገዋልና”( Bulcha Demeksa, Ethiopian Examiner, May 1993)። አቶ ቡልቻ ይህንን ከፍተኛ ድፍረት የተሞላበት፤ በጥናትና መረጃ ላይ ያልተመሰረተ አስተያያት ሲሰጡ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ እሳቸው በደንብ አውቀዋለሁ፤ ጥቅሙን አስጠብቅለታለሁ የሚሉትን የኦሮሞን ህዝብ እንኳን ጠይቀው፤ አስተያየቱንና ፍላጎቱን ሰብስበው አይደለም። በወያኔ ትግሬዎች መንግስት ከተደረገው ከአስራ አራት ዓመታት የጎሳ ፖለቲካ ሰበካ እንኳን በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጎሳ ፌዴራሊዝም ልቡን እንዳልሰጠ በግንቦት ወር 1997 ዓ. ም የተደረገው ብሄራዊ ምርጫ አሳይቷል። በጎሳ ሳይሆን ሀገር-አቀፍ አጀንዳ አንግቦ ውድድር ውስጥ የገባው የቅንጅት ድርጅት ያገኘው ከፍተኛ ድጋፍ የአቶ ቡልቻንና ከወያኔ ጀምሮ እስከ ዛሬዎቹ የመድረክ አባሎች ድረስ ያሉትን የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ክፉኛ አስደንግጦአል። መድረክም የዚህ የጎሳ ፖሊቲካ ክስረት ያስደነገጣቸው የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ሆኖ ብቅ ያለው ይህንን የጎሳን ፖለቲካ ውድቀት በጋራ ሆኖ ለመከላከል፤ ጎሳ-ዘለልና ሀገር-አቀፍ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸውን ወገኖች በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ለመዋጋት ነው። የእነ ሰዬ አብርሃም ከወያኔ ወጥቶ መድረክ መግባት አልሸሹም ዞር አሉ ነው።
* የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ አሰፋ ነጋሽ በሆላንድ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሲሆን በዚሁ በተሰደደበት ሀገር በተማረው የህክምና ሙያ የአይምሮ ሀኪም (ሳይካትሪስት ሆኖ እየሰራ ይገኛል)።
No comments:
Post a Comment