“ማረሚያ ቤቱ የጠያቂ ገደብ ጥሎብናል” ተከሳሾች
“ለደህንነታቸው ሲባል ነው” የማረሚያ ቤት ተወካይ
በአሸናፊ ደምሴ
የፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ በመሰረተባቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ግብረ-አበሮቻቸው ላይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የክስ መሰማቱ ሂደት የቀጠለ ሲሆን፤ በትናንት የችሎት ውሎውም በቀደሙት ጊዜያት በአካል ያልተገኙ አዳዲስ ተከሳሾችን ጨምሮ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን በመመርመር ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ ላይ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸው በችሎት ካልተገኙት አስራ ሁለት ተከሳሾች ውስጥ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና አማካሪ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አማሃ አባይን ጨምሮ፤ አቶ ግርማ ታፈሰ፣ አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ አቶ ሙሉጌታ ባልቻ፣ አቶ ለሚ አበራ፣ አቶ ተስፋዬ ቤተ እና ወ/ሮ ሃይማኖት አለሙ የተሰኙ የባለሥልጣኑ ሰራተኞች ከፍርድ ቤት የደረሳቸውን ጥሪና ከመገናኛ ብዙሃን ያገኙትን መረጃ መሠረት አድርገው ችሎት ቢቀርቡም የተመሠረተባቸው ክስ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣቸው እንደሚችል ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳቱ ምንም አይነት ምርመራ ያልተካሄደባቸው ሰባቱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
እስከትናንት በስቲያ ድረስ በባለስልጣኑ የተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ሆነው ስራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበር የተናገሩት ሰባቱ ተከሳሾች በችሎቱ ፊት ሲቀርቡም መነሻ ቦታቸው የነበረው ከተከሳሾች መቀመጫ ሳይሆን ችሎቱን ሊታደም ከመጣው ህዝብ ጋር እንደነበር ታይቷል። በችሎቱ ትዕዛዝ በተከሳሾች ቦታ ላይ እንዲሆኑ የተደረጉት እነዚህ ተከሳሾች የመከሰሳቸውን ዜና በሚዲያ ሰምተው ክስ ወደ መሰረተባቸው የፌዴራሉ የሥነ ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን መስሪያ ቤት በመሄድ ጉዳያቸውን ስለመረዳታቸውና በቀጠሮም ቀን ችሎት መቅረባቸውን አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱም ለተከሳሾቹ የተከሰሱበትን ጉዳይ የሚያስረዳ የክስ ቻርጅ እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ ክሱ በችሎቱ ተነቦላቸዋል።
በዚህም መሰረት ተከሳሾቹ በተዘረዘሩበት የክስ መዝገብ ስር መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን የስራ ኃላፊነት ተገን በማድረግ የታክስ አሰባሰብ መመሪያን በጣሰ መንገድ ግብር እንዲሰበሰብ አድርገዋል፤ የህገ-ወጥ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በመሆን ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ግብርና ታክስ እንዲቀነስ በማድረግ የተለያዩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በመጥቀም ለራሳቸው የማይገባቸውን ጥቅም አግኝተዋል ሲል ተከሳሶቹየባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተባለው መንገድ ግብርና ታክስ እንዳይሰበሰብ በማድረግ፣ ታክስ በመቀነስ፣ የጉምሩክ አሰራርን በሚፃረር መልኩ እቃዎች እንዳይፈተሽ በማድረግ ሀሰተኛ ደረሰኞችን በማዘጋጀትና የተለያየ መጠን ያለውን ጉቦ ተቀብለዋል በማለት የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመስራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል። ይህንንም ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አሉኝ ሲል ዐቃቤ ሕግ ከክሱ ቻርጅ ጋር አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ክሱ በችሎት የተነበበላቸው ተከሳሾቹም ምንም አይነት ምርመራ ያልተካሄደባቸው መሆኑን በመጥቀስ የክሱን ሂደት ከመገናኛ ብዙሃን በሰማነው መሰረት ፍርድ ቤት ይቅረቡ በመባላችን ከስራ ገበታችን ላይ ተነስተን መጥተናል፤ ሲሉ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፤ በተከሰሱበት ወንጀል ላይ የሕግ ባለሙያዎችን አናግረው በቀጣይ ቀጠሮ መልሳቸውን ይዘው በችሎቱ እንደሚቀርቡ በመጥቀስ የዋስትና መብታችን ተከብሮ ወደስራ ገበታችን እንመለስ ሲሉ ጠይቀዋል። ተከሳሾቹ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ቢጠይቁም ዐቃቤ ሕግ የጠቀስኩባቸው አንቀፅ ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል በመሆኑ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ይደረግልኝ ባለው መሰረት የግራ ቀኙን ሀሳብ የመረመረው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15 ወንጀል ችሎትም ሁሉም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ከዚህ መዝገብ በኋላም ካለፈው ሳምንት በይደር የቆየው 3ኛው የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ በእነአቶ መላኩ ፈንታ ላይ ቀርቦ ታይቷል። በዚህም መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶባቸው በችሎት ያልቀረቡት የጌታስ ትሬዲንግና የጌታስ ኢንተርናሽናል ባለቤት የሆኑትን አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ አቶ ነጋ ፊኔ፣ አቶ ገና በሽርና አቶ ታፈሰ ፈይሳ በዚህም ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። በዚህም ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ምክንያቶችን በጽሁፍ ለችሎቱ በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ትዕዛዝ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን አስሮ እንዲያቀርብ አዟል።
በሌላም በኩል ከተከሳሾቹ ከተሰሙት አቤቱታዎች መካከል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የጠያቂዎቻችን ቁጥር ላይ ገደብ ጥሎብናል የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይም 1ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታና የገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል ዋና ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ መርክነህ አለማየሁ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ከትዳር አጋር፣ ከልጆችና ከጠበቆቻቸው ውጪ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቋቸው ገደብ ተጥሎብናል። ጓደኞቻችንና የሃይማኖት አባቶች ሊጎበኙን ይገባል ያሉ ሲሆን፤ በተለይም አቶ መርክነህ አለማየሁ ጉዳዩ ከታራሚዎች አያያዝ አንፃር ለሁሉም ታራሚ ተመሳሳይ አሰራርን መከተል እንደሚገባና ይህም በህገ መንግስቱ የሚደገፍ ሰብዓዊ መብት ጭምር መሆኑን በማስታወስ አስመዝግቡ በተባልነው ልክ ብቻ ሰው እንዲጠይቀን መደረጉ ያላስመዘገብናቸው ወዳጅ ዘመዶቻችን እንዳይጠቁን ክልከላ እንደመጣል ሆኖብናል ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተወካይ ሆነው የቀረቡት ኃላፊ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ምንም አይነት የጠያቂ ገደብ አላደረግንም ያሉ ሲሆን፤ ተከሳሾቹን በማረሚያ ቤት ተገኝተው የሚጠይቋቸው ሰዎች በእነርሱ እውቅና ላይ የተመሰረቱና እንዲጠይቋቸው የፈለጉትን ሰዎች ብቻ እንዲገቡ ማድረጋችን ለታራሚዎች ደህንነት ሲባል ያደረግነው ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በተለያዩ መዝገቦች ላይ ትዕዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ ክስ ተመስርቶባቸው ያልቀረቡ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ፤ ከማረሚያ ቤቶች ጋር በተያያዘ የቀረበው አቤቱታንም ለተመለከተ የተከሳሾቹ መብት በህገ መንግስቱ የተቀመጠ መሆኑን በማስታወስ፤ የተከሳሾቹ ሰብዓዊ መብት በተሟላ መልኩ መከበር እንዳለበት፤ ይህም የማረሚያ ቤቱ ግዴታ ጭምር መሆኑን ለመጠቆምና ተለዋጭ ቀጠሮውን ለጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም በማድረግ ቋጭቷል።
No comments:
Post a Comment