Wednesday, April 15, 2015

የአባይ ልጅ ውሃ ጠማው!!

የሺ ዘመን እንቆቅልሽ የአበው ተረትና ምሳሌ፤
እነሆ ዛሬ ተፈታ ባዕድ፤ ባንዶች፤ የሸረቡብን ሴረኛ ውል እንደ ‘ውጫሌ’፤
ተጋለጠ፤ የወያኔ የትውልድ የዘመናችን ደባ አባይን ሲሸጡ እንዳልባሌ፤
ሃያ ዓመት ተወይኖብን ስንጠላለፍ በእዚመኛ፤ ዘውገኛ ተከልለን በቀበሌ፤
መንደር እንጅ አገር የለን፤ ኢትዮጵያን የነጠቀን የነገር ሰው ‘አፎሌ’፤
‘ሕዳሴ’ ብሎ አባይ ግድብ ትልቁ ሊጥ የተፈጨው፤ የተቦካው በአፈ - ጮሌ፤
በዲስኩር ራዕያቸው ሲያገምጡን የህልም አምባሻ ‘ደግ~ሰው’ ከመቀሌ፤
ጥሪት፤ሕይዎት እያስገበሩን ከጐጃም እስከ ወለጋ፤ ሸዋ፤ሀረር፤ አርሲ፤ከፋና፤ባሌ፤
ለካስ ቃል አባይ ኖረዋል፤ አፈር ቀማሹ ወደ ምድር ‘የሰረጉት’ ቀድመው በሃምሌ፤
ወንዛችንን እያቆሩ፤ ተስፋችንን የቀበሩ፤ ውሃ ያስጠሙን ‘የኛ ጌቶች’ የባዕድ ሎሌ፤
የኢትዮጵያን ‘እህል-ውሃ’ አስቀንነው ግብጽ፤ሱዳን ሲያስጋግሩ፤ካገር ሳይመክሩ ሽማግሌ፤

ዛሬ አረዱን! ኢትዮጵያ የአባይ ቋት እንጅ፤ አይደለችም እመቤት፤ባለቤት፤የበኩር ልጇ ‘ሾተሌ’፤
መንታላ እናት አፈር ዱቄቷን የተቀማች፤ ‘ጡት አጉርሳ’ የነከሷት ‘እማ~ወራ’ ባተሌ፤
ልጆቿን ውሃ ቢጠማቸው፤ አባይ ኩራዝ እንጂ፤ ኮዳ አይሞላም ከጓዳቸው፤ካልፈረሰ ማነቂያ ውሉ እንደ ‘ውጫሌ’።
እናማ! የአባይ ልጅ ካሁን ወዲያ አባይ ላንተ የስለት ጠበል እንጂ ውሃ አይደለም፤
ከጊዮን የመነነ ስደተኛ፤አሮጌ አድባር፤ግብጽ የሻተው መንትዮሽ ካይሮ ሊያከትም፤
ጠላትና ገዥዎችህ ቆፈረው፤ ፈርመው የቀበሩት እንዳይፈስ በማሳህ በምድርህ ዳግም፤
ይብላኝ ላንተ፤ አባይ አንጀትህን፤እትብትህን፤አፈርህን እንጅ ራብ፤ጥምህን አይቆርጥም፤
አንጡራህን፤ ገመናህን ተራቁተህ በህዳሴ መዋጮ፤ በአገርህ፤ በተፈጥሮህ ላትጠቀም፤
ምን ብትማስን፤ መስኖ ላትተልም፤ ሺህ ብትቆፍር ጅረትህ በጓሮህ፤ በማሳህ አይወርድም፤
ከምድርህ ከርስ ቢሻቸው ቧንቧ አንጥፈው፤ አንጠፍጥፈው እንዲያስግሩት በሽልም፤
ሆድ ያዘዘበት ፓርላማ፤ አጨብጭቧል፤ ተፈራርሟል፤ ህሊና ቢስ፤ ‘ምድረ ዳፍናታም’፤
የአባይ ልጅ! አባይ ላንተ ስም እንጂ ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ርሃብ ጥምህን አይቆርጥም።
የጐንቻው!
አንተንማ ማን ሰው ብሎህ፤ የአባይ ልጅ !፤ ሊያማክሩህ፤ ከመጤፍስ ሊቆጥሩህ፤
አይጉደል እንጂ ‘ወንዛቸው’ አንተንማ ‘አሳንሰው ያሰሉህ’ ‘አሃዝ ሁነህ’፤ በስድስት ዜሮ የቀነሱህ፤
ዛሬን እንጂ ‘ነገ አትኖርም’፤ ‘ተቆርጧልና’ በቀነኞች ‘ቀን እድርህ’፤
‘ግዑዝ ፓርላማ’ አጭብጮ የሸጠህ፤ የሸፈጠህ፤
ለፈርዖን ንጉሥ እጅ መንሻ ለዳርጎት ‘የቸረህ’፤
ዘመንህን፤ ለኅዳሴ፤ ቦንድ መግዣ ያጫረተህ፤
‘መንግሥትና ዘመን ወይነው ቢያራቁቱህ፤
ትሰደድ ይሆን የአባይን ፈለግ ተከትለህ?
‘በባቢሎን ከተማ የቀን ሥራው አማሎህ’
እርስትህን ትለቅ ይሆን ውለህ አድረህ?
የአባይ ልጅ እውን አንተን ውሃ ቢጠማህ፤
አታጎርፍም ወይ? በከተማህ፤ በመዲናህ፤
ቤተ-መንግሥት፤ውሃ ልኩን አጥለቅልቀህ፤
ዋናተኛው አትወጣም ወይ ከሥር ጠልቀህ፤
ዶሴ ፊርማውን ቀዳደህ፤ፈራሚውን አድፍቀህ፤
አንት የአባይ ልጅ! እንደ ጥንቱ ቃል ኪዳኑን አድሰህ፤
ልትነግር ለዓለም፤ ሰለ ዓለም ብለህ፤
አባይ ወንዛችን፤ መድህናችንም መሆኑን አስረግጠህ።
yegonchaw@yahoo.co.uk 30.03.2015.
ማስታወሻነቱ፡-
አባይ ከብሄራዊ ስነ- ልቦናችን፤ ማንነታችን፤ ከታሪካችን፤ መልካ ምድራዊ አሰፋፈራችን፤ተፈጥሯዊ ትሥሥራችን ጋር ተቆራኝቶ ሺህ ዘመን አብሮን የነጐደ ከወንዝ የበለጠ ትርጉም፤ስላለውም እንደየዘመኑ የኑራችንን ፈተና ልንሻገርበት ምኞትና ሕልም ቋጥረን የምንፈታበት፤የእድገትና የልማታችንን ቁጭት የምንገልጽበት ሚስጥራዊ ኃይል መሆኑን የተረዱ የዘመኑ ‘ብልጣብልጥ ገዥዎች’ በቀውጢው ሰዓት፤በፊታውራሪነት ከሚስጥር ኪሳቸው ሳይታሰብ ‘ህዳሴ ግድብ’ ብለው የመዘዙት ካርድ፤ነበርና አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ከኪስ ባለፈ፤በገዘፈ ብዙ፤ብዙ አስወጥቶታል።
በሌላ ወገን ደግሞ የዘመነኞችን ታሪክና ምግባር የመረመሩ፤ ሌላ ድብቅ አጀንዳ ወይም ማዘናጊያ፤ከዚያም ቢያልፍ ብር መሰብሰቢያ እንጂ ብዙ ጥናት ሳይደረግ፤ ትርፍና ኪሳራው ሳይሰላ፤ ዓለም አቀፍ ብድርና እርዳታን ያላማከለ፤ ሕግን በአግባቡ ያልተከተለ ‘የሕወኃት እድሜ ማራዘሚያ ክኒን’ ነው ብለው በጥብቅ ሲተቹት ቆይተዋል።
እነሆ ሰሞኑን የቀድሞው ፊታውራሪ አደራ ጠባቂና ጀሌዎቻቸው በድብቅ መክረውና አጥንተው ካርቱም የተመረቀ ‘የሶስትዮሽ ኃዳሴ ፊርማ’ ነጠላ ዜማ ለቀዋል። የግብጹ መሪም፣ ‘ፕረዚደንት አብድል ፋታህ ኢልሲሲ’ ድላቸውን በኛ ፓርላማ ተሰይመው በአሸናፊነት ሲያቀነቅኑ ማጨብጨብ የለመደው ግብዝ፤ግዑዝ ‘የሕዝብ ተወካይ’ ተብዬ እስክታ መውረድ ብቻ ነበር የቀረው።
እኒህ ያሏቸውን ደጋግመው የምያቀነቅኑት በቀቀን ‘የኛው’ ጠ/ር ተብየና ትራፊና ፍራፊ ጉርሻ/ቀለብ የሚሰፈርላቸው የትውልድና የዘመኑ ድውያኖች፤ ወዶ-ገብ ተስፈኞች" የድስኩር ምናብቸውንና ለክታቸውን እየለጠጡ ይህ የሶስትዮሽ ውል ኢትዮጵያ ከአድዋ ወዲህ ለሁለተኛ ግዜ የተቀዳጀችው ድል-ገድል እንደሆነ በማስመሰል የወሬ ፍሪዳ ጥለው በሽሚያ ሲራኮቱብት፤ሲጎራረሱ ሲናከሱም ሰንብተዋል።
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ እንዲሉ በሉዓላዊ ሃገር ዙፍን ተሰይመው (ወረው) ሃያ አመት የሚያብሉት መሪ(ተመሪ) የጫካ ዝሆኖች ቤተመንግስት ምሽግ ቀንዳቸውን ቀስረው የግጥሚያ አፈር እየጫሩብን ባድመን የሚቀማ፡አሰብን ሽራሮን፡መተማን ለባዕድ የሚያስማማ ኢትዮጵያን ከጥሊያን የከፍ ጠላት ወረራት! ደፈራት! ብለው ‘እየፎከሩ(እያስፎከሩ) የህዝብን ስሜት ቀስቅሰው አተራምሰው ወደ ጦር አውድማ ጅምላ ማገዱ።፡እነሆ በዚህም ትርጉመ-ቢስ ጦርነት መቶ ሺህ ወንድማማች ህዝብ አጫርሰው ደመ-ከልብ ያደረጉ ናቸውና እንደለመዱት እኒሁ በውሸትና በደም የደለቡ ‘የኛ ኮርማዎች‘ አልጀርስ ላይ ሁሉን በነፃ ፈርመው ካስረከቡ በኋላ ዳግም ሲሳለቁብን ህዝብ አደባባይ አሰልፈው ባድመን በዲፕሎማሲ ረተን በተባበሩት መንግስታት ፊርማ አስረገጠን ለኢትዮጵያ አስመልሰንልሃልና ‘ሕዝባችን ሆይ‘ መስቀል አደባባይ ወጣና እልል በል!፤ ከበሮም ደልቅ!፤ለኛም ምስጋናና ችሮታ አትረፍርፍልን! ብለውን አልነበርም እንዴ?።
እኮ! በለመደ አፋቸው ዛሬስ ግብጽን ወዳጇን ሱዳንን አማላጅ ይዘው ካርቱም በጓዳ ተገናኝተው (አድፍጠው) እጅ መንሻ ከርቤና እጣን ይዘው በመማጠን ተፈራርመው ከተዋዋሉብን በኋላ ቀድሞ የአባይ ጠብታ ውሃ ቢቀንስ ግንቡን በቦንብ አደባያለሁ፤ ጀቶቸን በኢትዮኦያ ሰማይ ላይ አክሮብት አሰራለሁ፤ ተቃዋሚ አስታጥቃለሁ፤ የሰለጠነ ጎሪላ ተዋጊ ሰራዊት አሰልፋለሁ፤ ፊታውራሪ ሁኘም እወጋለሁ፤አዋጋለሁ እምቢ አሻፈረኝ! ስትል የባጀችውን የግብጽን ጄኔራል የኛው ግርማ ሞገሳቸው እንዳንበሳ የሚያስፈራ ጠ/ሚር ግጢጥ ብለው ምን ሹክ ቢሏቸው ወይስ ሽብርክ ቢሉላቸው ነው እኒህ የግብጽ መሪ፤ የሰው አገር ሰው አቋማቸውን፡ዜግነታቸውን ቀይረው ለስካሁኑ ጥፋትና በደላቸው "ብሄራዊ ፓርላማችን"ፊት ቀወርበው ንስሃ ሊገቡ "በተከበሩ፤ በተኮባበሩ" እንደራዲዎቻችን በሰላ አንደበት በአጣብቂኝ ሊሞገቱ፡ በመስቀልኛ ጥያቄ ሊዋከቡ ደፍረው እንዲህም አሉን። "••• ከንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ ያለማቋረጥ ቀን በጠሃይ ሌሊት በጨረቃ ያለምንም ስጋት ታንጽ ዘንድ እውቅና ብቻ ሳይሆን ግብጽም በገንዘቧ ድጋፍ ታረጋለች፤ የግብጽ ህዝብም ቦንድ ይገዛል፤ይለውጣል፤ይሸጣልም፤ግድቡንም ያሳራል፡ ያሻሽጣል፤ ወዘተ••• " አሉን።
አክለውለም " ••• ካሁን በኋላ በኢትዮጵና በመንግስቷ ላይ የመጣ ሁሉ በግብጽም አይን ላይ እንደመጣ እንቆጥረዋለን••• " አሉን።
እኒሁ ‘እንግዳ ሰው’ ኢትዪጵያን በግድብ ብቻ ሳይሆን በእንዱስትሪም አጥለቀልቃታልሁ ብለውናል መቸስ ውለን አድረን በአረብኛ ሰምና ወርቅ የሚፈታልን ‘ተርጓሚ’ እስከምናገኝ ድረስ ለቸሮታቸው በፓርላማው ስም ‘አላህ ይስጥልን! ብለናል የኛን አምላክ ይቅር ይበለን እያልን። መቸስ እኛ ፓርማ የሚሰራው ድራማ ከሆሊውድ የሚያስንቅ እጡብ ድንቅ ነገር ነው፤ "ደሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጠልፈው ጣሏት" እንዳሉት የአበው ተረትና ምሳሌ ሆነና የነገሩ፤የውሉ እንቆቅልሽና ሚስጥር።
ለማንኛውም የጽሁፌ መቋጫና መልዕክት ወንዛችን አባይ እንገድበው፤እንጠጣው፤እናዘምረው፤የፈለግነውን የፈቀድነውን እንዲሆን፤ ከአምላክ ፈቃድና ችሮታ ጋር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ ነፃነት ይመክር፤ ይዘክር፤ ይወስንም ዘንድ እነዚህ ስንኞቸ ለሁላችን ማስታወሻና፤መታሰቢያም ይሁኑልኝ በማለት ነው።
እስኪ የከርሞ ሰው ይበለንና ከግድቡ ጸበል፤ከልማቱም እሸትም ለመቋደስ ያብቃን! አሜን! የጐንቻው!

No comments:

Post a Comment