Thursday, April 30, 2015

የአንደበትህ ፍሬ ሕይወት እንጂ ሞት አይሁን!!! – ከተማ ዋቅጅራ

የልብ ሃሳብ የሚገለጸው በአንደበት ነው። የተሰወረን ሚስጢር የሚገለጸው በምላስ ነው። የሰው ልጅ ከግዜ ጋር ይሮጣል እውነተኛው እውነት ይዞ.. ሃሰተኛው ሃሰት ይዞ እየተቀዳደሙ ወደፊት ይሔዳሉ። ሃሰት በጥርርጥር የተሞላ ነው። ጥርጥርን የሚያስወግድ በእውነተኛ መንገድ የሄደ  ነው። የፍቅር እርሻ አራሽ፥ የፍቅር ዘር ዘሪ፥ የፍቅር ቡቃያ  አብቃይ፥ የፍቅር ሰብል ሰብሳቢ እውነትን ይዞ  ከሚሄደው ከልቡ የሚወጣ የሕይወት ቃል ነው።
አንደበት ትንሽ ሆና ሳለ ታላላቅ ነገሮችን የምትሰራ ቀላላ ሆና ሳለ ከበባድ ክንውኖችን የምታከናውን ሃያል ናት። ክብርም የምናገኝበት ውርደትም የምንቀበልበት በጎ የምንሰራበትም ክፉም የምናደርግበት ጽድቅና ሐጥያትም የሚከናወንባት ሕይወትንም ሞትንም የምናስተናግድበት በአንደበት ነው። ልብ ያቀናውን አንደበት ያወጣዋል… ልብ ያጠመመውን አንደበት ይገልጸዋል። ልብ ያሰበውም አንደበት ይናገረዋል።

ወገኖቹን በፍቅር የሚገዛ.. በእውነተኝነት እና በታማኝነት የሚያገለግል… በጎውን መንገድ የሚጠቁም… ከልብ የወጣ ቃል … በአንደበት የተገለጸ … እውነተኛ ፍቅርን ለህዝቡ እኩል የሚሰጥ… ውጪአዊውን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊንም ይገዛል። በማስገደድ አልያም በውሸት በአንደበቴ ቀጥፌ እገዛለው የሚል ውስጣዊ ማንነትን መለወጥ ስለማይችል በከንቱ ይደክማል። አፋዊ ማንነትን አፍኖ በግፍ የሚገዛ  ውስጣዊ ማንነትን ማፈን ስለማይችሉ አስተዳዳሪዎች እንዲሁ በከንቱ ይለፋሉ።
አስተዋይ ሰው ነገርን ልብ ብሎ ያዳምጣል። አካሄዱም በእውነት ላይ ስለሆነ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ሰው እርስ በራሱ ለመግባባት በጣም ቅርብ ነው፥ ለመጣላትም እንዲሁ። የፍቅር ገበሬ ማለት ለልጁ ጥበብንና እውነትን፣ ትህትናንና በጎንትን፣ እያስተማረ የሕይወትን መንገድ የሚያሲዝ ማለት ነው። እንደዚ አይነቱ ዘር በልቦናችን ከተዘራ  አንዱ ከአንዱ መግባባት እንጂ መለያየት… መዋደድ እንጂ መጣላት … መከባበር እንጂ መናናቅ አይኖርም።
ብዙ ከመናገር ብዙ ዝምታን ምረጥ። ተናጋሪም ከሆንክ ፍሬ ያለው ነገርን ተናገር ከአነጋገርህ ሊማሩብህ እና መልካምነትን ለማፍራት መሆን አለበት እንጂ ለመሳደብ አልያም ድብቅ ተንኮልህን ለማሳካት ከሆነ ላሰብከው ተንኮል ቀድመህ ቀማሽ ስለምትሆን ተጠንቀቅ። በዚህ አለም ላይ እንደ ስይጣን ተናጋሪ አልያም ለፍላፊ የለም። ንግግሩ በሙሉ የተንኮል፣ የጥፋት፣ የሞት፣ የውርደት እና የውድቀት ነው። ስንናገር ተንኮልን ያዘለ፣ ጥፋትን የሚያመጣ፣ ውድቀትን ያረገዘ፣ ሞትን የሚወልድ ከሆነ  ከኤረር ከመላእክት አገር በራሱ አንደበት ባመጣው የሞት እና የውድቀት ቃል ሰይጣን ወደ እንጦሮጦስ መጣሉን አትዘንጋ። ያንተም እድል ፈንታ እንደዚሁ ነውና  ክፋትንና ጥፋትን አትናገር አወዳደቅህ የከፋ እንዳይሆን።
ወደ  ውስጣችን ጥቁር ሃሳብ አናስገባ ውስጣችንን ያሳውረዋልና። ውስጡ የታወረ ሰው በንግግሩ የሚወልዳቸው ልጆች ገደሉ ሜዳ መስሏቸው ወደ ገደሉ ገብተው እንዳይሞቱ ሰውነታችንን በክፋት አንመርዝ።
ክፉ መንግስት እረጅም እድሜ እንዲኖረው የሚያደርገው ህዝብ ነው። እንዴት ቢሉ ፍቅር ጠፍቶ ጥላቻን ካበቀለ፣ ጥላቻን ኮትኩቶ ቂምን ካፈራ፣ የምንሰበስበውም ቂምን ነው። ጥላቻን አብቅለን ቂምን የምንሰበስብ ከሆነ  መልሰን ብንዘራው የሚያበቅለው ሞት ነው። ምክንያቱም በጥላቻ እና በቂመኛ ልቦና ውስጥ እግዚአብሔር ስለሌለ ነው። እግዚአብሔር የሌለው ምንም የለውም። ሃይላችንም ጉልበታችንም የለንም ማለት ነው። ሃይላን ጉልበት የሌለው ደግሞ  የተጫነበትን የግፍ ቀንበር መስበር አይችልም። ለማሸነፍ መጀመሪያ ቅንነት እና እውነተኛነት ከዛ ቆራጥኝነትና ታማኝነት ያስፈልጋል እንዲህ ሲሆን ክፉ የሚባለውን ኃይል በቀላሉ መጣል ይቻላል።
አንደበት እሳት ናት። ትጥቅ ከፈታው አንደበት የፈታው ይበልጣል። ዱላ ከሰበረው አንደበት የሰበረው ይከብዳል። ከአንደበቱ ቅለት የተገኘበት መቼም ሊከበር አይችልም። በአንደበቱ የቀጠፈ  መቼም ታአማኒነት አይኖረውም ስለዚህ በአንደበታችን ፍቅርን እንዝራበት፥ ጽናትን እናስተምርበት፥ እውነትን እንናገርበት፥ ይህ የመጀመሪያው ድላ ሲሆን ወደ ነጻነት የሚያደርስ የፍቅር መንገድ ነው።
ከተማ ዋቅጅራ
28.04.2015
Email- waqjirak@yahoo.com

No comments:

Post a Comment