Wednesday, April 15, 2015

በፋሲጋችን… (ዳዊት ዳባ)

ዳዊት ዳባ
እንኳን በደህና ከዘመን ዘመን አሸጋግሮ ለፈሲጋ በዓል አደረሰን። በአሉን የፍቅር የሰላም ያድርግልን።
Anger at injustice as martin luter king wrote. Is the political expression of love?Ethiopian ester
የፋሲጋ ሳምንት (ህማማት) ድንቅና አስገራሚም ነው። ፍቅር፤ መሰዋትነት፤ ክህደት፤ ታማኝነት፤ ፅናት፤ፍርደገምድልነት፤ምቀኝነት፤ ተንኮል፤ ደባ፤ አፍቅሮ ሰልጣን፤ አፍቅሮ ንዋይ፤ ሰም ማጥፋት፤ ይቅርታ፤ አብሮ መብላት፤ ጉቦ፤ ተስፋ፤ ሀዘን፤ ደስታ፤ ስቃይ፤ሞት፤ ይሰቀል{Mop Justice}፤ ብቻ ጠቅለል ባለ የዚህን አለም ሂወታችንን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሲከወን እናይበታለን።
ህማማቱ ከተፈፀመ ረጅም ጊዜ ሆነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አለም የሰው ልጅም በእጅጉ ተቀይሯል። ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶ በዚህ ምድር ላይ የተመላለሰው በዚህ ዘመን ቢሆንስ ኖሮ ብለን ብንጠይቅ?። የሰው ልጆች ይህ ሁሉ ግፍ እንዲፈፀምበት፤ በመጨረሻም እንዲሞት አይፈቅዱም ማለት የሚቻልበት ደረጃ ድረስ ተለውጧል ማለት ይቻላል። ሞቱም ሆነ ያን ሁሉ መከራን መቀበሉ ከንቱ አልቀረምና ስለተለገስነው ዘላለማዊ ሂወቱ ብቻ ሳይሆን ምድርን በዚህ ደረጃ ስለቀየረው ደስ ያሰኛል። ይህ ግን ጠቅለል አድርገን በአለም ደረጃ ከወሰድነው ነው።
የዘመኑ ሀያል ህዝቦች በአደገ ስብእና ላይ እና ለሰው ልጅ ሂወት ክብር የሚሰጡ በመሆናቸው ነው ። ብቃት ደረጃ ደርሰዋል ባይባልም ፍትህ እንዳይጓደል አሰልሰው የሚጥሩና ለእውነት የሚቆሙ ስለሆነ ነው። አቅሙ ለሌላቸው ተቆርቋሪ መሆንን ስራቸው ያደረጉ ብዙዎች ያለቡት ማህበረሰብ ስለሆነም ነው። በዋናነት ክርስትናቸው ይህንኑ ታላቅ ቁም ነገር መሰረት ያደረገና በሚታይ በሚጨበጥ ስራ የታገዘ ስለሆነ ነው። ነጣጥለን በየሀጉሩና በየአገሩ የሰው ልጅ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ብለን ካየነው ግን ግምታዊም ቢሆን የምንደርስበት ድምዳሜ በእጅጉ የተራራቀ በዙም በህማማቱ ዘመን ከነበሩ የሰው ልጆች ከነበራቸው ስብእና ያልተለወጠ ሊሆን ይችላል።
አያድርገውና መመላለሱ በዚህ ዘመን ኢትዬጵያ ውስጥ ሆኖስ ቢሆን?። ጥያቄው ለበዛው አማኝ አናዳጅ የሚሆን አይመስለኝም። ሲጀመር ጥያቄውን ያስነሱት ሰባኪ ነን ያሉ ናቸው። ዝም ሲባል ይባስ ብለው ትንኮሳ ስለበዙ ነው። አሁንም ለምን ተነሳ ብለው ይሰቀሉ የሚሉና አዋራ ሊያስነሱ ይችላሉ። መነሳት ግን የግድ አለበት። አዎ በዚህ በኛ ዘመን ህማማቱ ኢትዬጵያ ውስጥ ቢሆንስ ኖሮ?።
ከሳሾች፤ አስገዳይና፤ ገዳዬች አሉን። በእርግጥ በሰለጠነው ማህበረሰብ ውስጥ እነዚህን በመንግስት ስልጣን ላይ አናገኛቸው ይሆናል። ቢኖሩም ስልጣናቸው የተገደበ ስለሆነ አይችሉም። በየትኛው የአለም ክፍል ላይ ሊኖሩ ግን ይችላሉ። የውሸት ምስክሮችንም መግዛቱም ሆነ ፈራጆችን ማግኘቱ ቀላል እንደሆነ ከኑሯችን የምናያው ነው። ይህን አይነት እኩይ ወንጀል ቅቤ ቀብተው የሚያሰማምሩና ህዘብን የሚያደናግሩም የካድሬ መአት፤ ጋዜጠኛ ተብዬና አደርባይ ምሁራን ሞልተዋል። በዋናነት በየእምነቱ የቁጩ ሀዋርያቶችም እንዲሁ። ያም ሆኖ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ከጠቅላለው ህዘብ ጥቂቶች ናቸውና እንደህዘብ ከሌሎች የሚያሳንሱን አይሆንም።
መክሰሻውም በገፍ ነው ያለን። ከአስተምሮቶቹ ውስጥ በቀላሉ በመምዘዝና ትርጉም በመስጠት። በእምነቶች መሀል ግጭት በመፍጠር። በሽብርተኛነት፤ በአገር ክህደት፤ መንግስት ላይ በማሴር፤ የህዳሴ ጉዟችንን በማደናቀፍ የሚለው ሁሉ በቀላሉ መክሰሻና ማሰቃያ ሲያልፍም መግደያ ሊሆን እንደሚችል ያለንበት ሁኔታ መስካሪ ነው። አይደለም አገርን አልፎም አለምን የሚያነቃንቅና የሚለውጥ መልካም ሀሳብ ይዞ የመጣው መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሽ የሆነች አገራዊና ህዝባዊ መልክም ሀሳብ ለዛውም ምድራዊ አላችሁ ተብለው ብዙ ንጹሀን ዜጎቻችን እየተገደሉ፤ ሰቆቃ እየተፈፀመባቸው በየማጎርያ መኖራቸው የማንክደው ነው። ያም ሆኖ ይህንኛውም በመንግስት ደረጃ የሚራመድ ስለሆነ እንደ ህዘብ አያሳንሰንም ብለን እንውሰደው።
ዛሬም “ይሰቀል”፤ “ይሰቀል” ልንል የምንችል ምን ያህላችን ነን የሚለው ላይ ብዛታችን ነው አስፈሪም አሳፋሪም ሊያደርገን የሚችለው ። ሲጀመር የመጠየቅ እድሉም ስለሌለን ይሰቀል ማለቱንም አንችልም። ወናው ጉዳይ ይህ ሰው ንጹህ ነው፤ ሰቆቃ ሊፈጸምበት አይገባም ብለን ልንመሰክር የምንችል ምን ያህላችን ነን?። አጥብቀን የምንቃወም፤ ፍትህን የምንጠይቅና ድምጻችንም የምናሰማስ?። ወጋም የሚያስከፍል ቢሆን ለመክፈል የምንፈቅድስ?። ንጽህናውን ልቦናችን እያወቀ እሷስ ብትሆን በመጀመርያ “አጭር ቀሚስ ማን ልበሺ አላት” አይነት አመክነዬ መደርደሩም ሆነ የተካንበት ተጠቂው ላይ ጉድፍ መፈለጉ ዘመንኛ መሆኑ ነው እንጂ ያው “ስቀለው” ውስጥ የሚካተት ነው።
አምላክ በማቲዌስ ወንጌል 25፤31-46 ግልጽ አድርጎ ነግሮናል። አመክንዮ ለመደረድር እንኳ እንዳያመቸን አድርጎ። ለተራቡት፤ ለተጠሙት፤ ለተጨቆኑት፤ ፍርድ ለተጓደለባቸው፤ ለሚሳደዱት፤ ባጠቃላይ ለሰው ልጆች አሁን በምድር ላይ የምናደርገውን ለሱ እንዳደረግነው አድርጎ እንደሚወስደው ነግሮናል። በዬሀንስ 4፤20 ደግሞ አጠገብህ ያሉ ወንድምና እህቶችህን ሳትወድ አምላክን እወዳለው ብትል እየቀጠፍክ ነው ብሎ መፈናፈኛ እንዳይኖር ቁም ነገሩን አጠናክሮ ዘግቶታል። ቃሉን ላመሰጠርው ልሞክር። መንፈሳዊ ስራችን ሲገለፅ ስለውለታ፤ ስለጉልበተኛነት፤ ስለትውውቅ ሳይሆን ስለሰባዊነት፤ ስለፍትህና ስላእውነት ለዛውም ከልባችን ደስ እያለን ብቻ የምናደርገው ይሁን ነው የሚለን።
ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ከመጣ አይደል ‘ሀ’ ተብሎ ቀን መቆጠር የተጀመረው። አሁን 2007 ላይ ነን ። በዚህ ረጅም ጊዜ ክርስትናው በአገራችን ብዙ ተከታዬች አፍርቷል። ብዙ አብያተ ቤተክርስትያናትና የአምልኮ ቦታዎች አሉን። ብዙ አስተማሪዎች ሰባኪዎች እንዲሁ። ጿሚው አገሬው ነው። ስሙን ከፍ ከፍ የሚያደርገውም እንዲሁ። በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ ሰላት የሚያደርሰውም ያገሬው ግማሽ ነው። ሁሉም አይነት እምነቶቹ ረጅም ዘመንን አገራችን ውስጥ አስቆጥረዋል። ታዲያ ለምን ነፃነት የበዛልን ዜጎች መሆን አልቻልንም?። ማን ሀላፊነቱን በአግባቡ ስላልተወጣ? ምንስ ስለጎደለ ነው?።
በዬሀንስ ወንጌል 2፤20 ላይ የአምላክ ቃል “ስራ የሌለው እምነት ሙት ነው ይላል።” በሌላ አገላላጽ ፍቅሩ አለ እንበልና እምነቱና ፍቅሩ መኖሩ የክርስትናው ግማሹ ነው። ሌላኛው ግማሽ ያን እምነትህና ፍቅርህን በስራ ላይ ማዋሉ ነው። እምነታችን ስራ የሌለበት ቢሆን ነው እንጂ ይህ ሁሉ ችግረኛ፤ ይህን ያህል ጥላቻ፤ በዚህ ደረጃ የፍርድ መጓደል። ቆጥሮ መስፈርት የሌለው ተሰዳጅ፤ አድሎ፤ዘረኝነት…. ባጠቃላይ ስቃይና መከራ በአገራችን ባልነገሰ ነበር።
የዘመኑ ስልጣኔ እንደሁሉም ነገር የአምላክን ቃል ማግኘቱንና መረዳቱንም ቀላል አድርጎታል። ኮንቢዩተሬን ስለሌሎች መብት መከበርና ስለነፃነት ስለመቆም ቅዱስ መፀሀፍ ምን ይላል ብዬ ጠየኩት?። ከሰባ በላይ ጥቅሶች ሰጠኝ። ለፍትህ ስለመቆምስ ምን ይላል ብዬ ጠየኩት። ከየትኛውም ቁምነገር በበዛ ወደ ሁለት መቶ ቦታዎች ላይ ስለፍትህ ግልፅ አድርጎ ይነግረናል። እንዲሁ በራስ ስለመተማመንና አንገትን ቀና አድርጎ ስለመሄድስ ምን ይላል ብዬ ጠየኩት። ዘረገፈልኝ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ስጠይቅ አብዝቶ መልስ ሲሰጠኝ በመጨረሻ የደረሰኩበት ድምዳሜ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ አማኝና ፖለቲከኛ ልዩነት የሌለው መሆኑን ነው።
ሲጀምር የበዛነው አይደለንም እያልን በግድ ፖለቲከኛ መባላችን ይሰመርበት። ይህ እንግዲህ ለነጻነት፤ ለመብት፤ ስለፍትህና ስለእውነት የሚጮህው ሁሉም ባይሆን እንኳ የበዛው አማኝ መሆኑን ያውቃሉ። ከዘም በላይ አመነም አላመነም ክርስትናው የሚያዘውን ነው የምናደርገው። እንደሚመስለኝ ፖለቲከኛና ፖለቲካ የሚለው ዘመቻ መልካም በሆነው ስራችን እያሳጣን ስለሆነ ያልተመቻቸው ክፍሎች አሸማቀው ዝም ሊያሰኙን ነው ፍላጎታቸው። የሚገርመው ግን መሳጣቱ የተፈራው ለአምላክ ወይስ ለምእመኑ?።
እወቁት መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር የተመላለሰው በዚህ ዘመን ኢትዬጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ። ይህው ፖለቲከኛ ተብሎ ልታሳንሱት የምታስቡት ወገናችሁ በግፍ ለሚገደሉት፤ ፍትህ ለተነፈጉት፤ ከቄያቸው ለሚሳደዱት፤ አገር ለቀው ለተሰደዱት ወገኖቹ መቆምን ደስ እያለው የሚያደርገው፤ የሚታወቅበትና ለምድም ያደረገው ነው። በእርግጠኛነት ካሳዳጆቹ ወገን አይቆምም ። ሌላው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ጽዋው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሁላችንም መዳረሱ አይቀርም። ነገ ለሁላችንም የሚጮህው ይህው ወገን ነው። አለቀ።

No comments:

Post a Comment