የኢትዮጵያውያን የውርደት ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሰሞኑን ከተከሰተው እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ አድርሶናል፡፡ የመን ውስጥ በተከሰተው ጦርነት ተጎጂ የሆኑትን የውጭ ዜጎች መንግስታቶቻቸው ቀድመው ሲያስወጡ ለኢትዮጵያውያን ግን የሚደርስላቸው አልተገኘም፡፡ ይህንን ውርደትም ወገኖቻችን ‹‹የመን ውስጥ የቀረነው እኛና ውሻ ብቻ ነን፡፡›› ሲሉ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ገልጸውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ላይ የመድፍ፣ የሞርታርና የአውሮፕላን ድብደባ ሲዘንብባቸው በመከራ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስልክ እንዲደውሉ በፌስ ቡክ ላይ በመለጠፍ ከማላገጥ ውጭ ምንም ያላደረገው የህዝብ ስልጣንን በሀይል የተቆጣጠርው ገዥው ፓርቲ ለራሱ ስልጣን ይጠቅሙኛል ያላቸውን የጦርነቱ ተሳታፊዎች ደግፎ መግለጫ ሲሰጥ የኢትዮጵያውያንን ስቃይ እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡
በአጭሩ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ በማያገባውና በማይወጣው ዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ ሀገራችንን ሲዘፍቅ ጦርነቱን ያወጀው የሚደርስላቸው ባጡ ምስኪን ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ ይህም የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመቸውም ጊዜ በላይ የወደቀና ለዜጎች እንደማይቆም በድጋሚ ገሃድ የወጣበት ነው፡፡በየመን የተከሰተውን መርዶ ሰምተን ሳንውል ሳናድር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አስደንጋጭ አደጋና እና ሰቆቃ ልንሰማ ተገደናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረታቸው መዘረፉ ሳያንስ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታትለናል፡፡ የዚህ አሰቃቂ አደጋ ሰለባ የሆኑ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በቶሎ ከደቡብ አፍሪካ ሲወጡ፣ እንዲሁም ሀገራቱ ዜጎቻቸውን መታደግ ያስችላል ያሉትን መፍትሄዎች ሲያስቀምጡ እና ሲያስጠነቅቁ ቢደመጥም ኢህአዴግ ግን እንደተለመደው የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃና ስቃይ ከምንም እንዳልቆጠረው በግልፅ እየታየ ነው፡፡
በእርግጥ ላለፉት 24 ዓመታት ኢህአዴግ ሀገር ውስጥ የሚኖሩትን ዜጎች ሲያሰቃይ፣ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንም የሆነ ያልሆነ ስም እየለጠፈ በጠላትነት ሲፈርጃቸው እንደቆየ አይተናል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የራሱን የግል ጥቅም ሲያሳድድም ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ወገኖቻችን ከፍተኛ በደል ሲደርስባቸው ይህ ነው የሚባል እገዛ ያላደረገው ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን በደል በማውገዝ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የሳውዲ ኤምባሲ ላይ ተገኝቶ ሲቃወም የሳውዲ ፖሊሶች ሀገራቸው ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፈፀሙት በደል ያልተናነሰ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰልፍ በወጡት ኢትዮጵያውያን ላይ በጭካኔ ድብደባ ፈፅሟል፡፡ ይህም ኢህአዴግ ለኢትዮጵያውያን የቆመ ሳይሆን በበእድ አገራት በኢትዮጵያውያን ላይ በደል ከሚፈፅሙት ያልተናነሰ ጨካኝ ስርዓት መሆኑን ያሳየበት ነው፡፡
ኢህአዴግ ለስሙ ‹‹የዳያስፖራ ፎረም›› በሚል የራሱን ደጋፊዎች አደራጅቶ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለልማት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ እየሰራ እንደሚገኝ በስሩ በያዛቸው ሚዲያዎች ሲያሰራጭ ከርሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያውያኑ ለእነሱና ለሀገራቸው እንደማያስብ በመረዳታቸው ምክንያት ፊታቸውን ስላዞሩበት ውጤታማ አልሆነም እንጅ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወረ ለአባይ ግድብ የበኩላቸውን እንዲያዋጡ ሲወተውት ታይቷል፡፡ ሳንቲም ለመልቀም በተለያዩ የዓለም ከተሞች እየዞረ ኢትዮጵያውያንን የሚሰበስበው ገዥው ፓርቲ በችግራቸው ወቅት ግን ምንም አይነት እርዳታ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ ይብሱንም ችግር ላይ ባሉት ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ በደል ሲፈጽምና በስቃያቸው ላይ የማላገጥ ያህል ፕሮፖጋንዳ ሲሰራባቸው እያየን ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ገዥው ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን አባብሎ ገንዘብ ከመቀበል ያለፈ ለውድ ህይወታቸው ደንታ እንደሌለው ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ባሉት ተደጋጋሚ ግፎች ተሸፈነ እንጅ ሰሞኑን ሌላ ኢህአዴግ ለዜጎች እንደማይጨነቅ የታየበት ክስተት እየተፈፀመ እንደሆነ በተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ ለመከታተል ችለናል፡፡ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ለሱዳን መንግስት አሳልፎ በሰጠው ሰፊና ለም የሀገራችን ሉዓላዊ መሬት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አሳፋሪ እና አሰቃቂ ወንጀል እንደተፈፀመ ተዘግቧል፡፡ የሱዳን መንግስት ወታደሮች ድንበሩን ጥሰው የሱዳን አዋሳኝ በሆነው የሰሜን ጎንደር ዞን ጠረፋማ ቦታዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ሰቆቃ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ውስጥ ቢሆኑም ቢሰደዱም ከመከራው ሊላቀቁ እንዳልቻሉ አመላካች ነው፡፡ በውጭም ሆነ በሀገር ቤት የሚኖሩ የአንድ ሀገር ዜገች መብታቸውና ክብራቸው ሊጠበቅ የሚችለው ሀገር ውስጥ ለሀገርና ዜጎች የሚያስብና የሚቆረቆር መንግስት ሲኖር ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን የሚገዙት ኢህአዴግን በመሰለ ለሀገርና ለህዝቡ ደንታ በሌለው ስርዓት በመሆኑ የሰሞኑ ሰቆቃ የሚገርም አይደለም፡፡ መቼውንም ኢህአዴግ የሀገርና የዜጎቹን መብትና ክብር ያስጠብቃል ብሎ መጠበቅም ዘበት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ አስተዳደር፣ ዴሞክራሲያዊና ለዜጎች የሚያስብ ስርዓት ቢኖር መጀመሪያውኑም ወገኖቻችን በገፍ ለአደጋ ወደሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ባልተሰደዱ ነበር፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ክብራችንን ለማስመለስ የነፃነት ትግሉን አጠናክረን በመቀጠል፣ እንዲሁም በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ለጊዜውም ቢሆን ራሳችን ከአደጋ ለማዳን በተለያዩ ማህበራት ተደረጃቶ በመንቀሳቀስ ብሎም ስርዓቱ እስካለ ድረስ ችግሮቻችን እየተባባሱ እንጂ እየተቀረፉ እንደማይመጡ በመገንዘብ በሀገር ቤት ስርዓቱን ለመቀየር የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል በማገዝ የችግራችንን ሁሉ መሰረት የሆነውን አምባገነናዊ አገዛዝ ለመለወጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ክብራችንን ልናስመልስ የምንችለው ሀገራችን ውስጥ እንዳንኖር ያደረገንን ስርዓት ቀይረን አንድም በገዛ አገራችን መኖር ስንችል፣ አንድም በአደጋ ወቅት ሊደርስልን የሚችል ተቆርቋሪና ለዜጎች የሚያስብ መንግስት መመስረት ስንችል ብቻ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በደቡብ አፍሪካ ሰቆቃ እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖቻችንን ለመታደግ በዓለም ላይ ተበትናችሁ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በችግር ውስጥ ለወደቁት ወገኖቻችን አጋርነታችሁን በማሳየት ዓለማቀፍ የተቃውሞ ድምፃችሁን እንድታሰሙም ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ እልባት እንዲያገኝ ፓርቲያችን የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆም አዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በኩል የራሱን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የመን ውስጥና በሱዳን አዋሳኝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ስርዓቱ ከባዕዳን ጋር ተባብሮ የሚፈፅመውን በደልም ለህዝብና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በማጋለጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መረጃዎችን እያሰባሰበ ይገኛል፡፡

በትግላችን የሀገራችንና የራሳችን ክብርና መብት እናስጠብቅ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ሚያዝያ 9/2007 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment