(ECADF) ትላንት አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (Agence France‑Presse) እንደዘገበው ከሆን ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ ብለዋል “ኢትዮጵያ በሁቲ አማጽያን ከስልጣን የተባረረውን የየመን መንግስት በቆራጥነት ትደግፋለች፣ ሳውዲ አረብያ የየመን መንግስትን ወደስልጣን ለመመለስ ጣልቃ መግባትዋም ትክክለኛ እርምጃ ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኃይለማርያም ኢትዮጵያ “በቆራጥነት ትደግፈዋለች…” ያሉት የየመን ምንግስት ፕሬዝዳንት አገር ጥለው በመሸሽ ሳውዲ አረብያ የሚገኙ ሲሆን አማጽያኑ ደግሞ ዋና ከተማዋን ሰንዓንና የወደብ ከተማዋን ኤደንን ተቆጣጥረው ይገኛሉ።
በቅድሚያ ከ50,000 በላይ ኢትዮጵያውያውያን መውጫ አጥተው በሳውዲ አረብያ የጦር አውሮፕላኖች እየተደበደቡ ባለበት ሁኔታ እና አማጽያኑ መላውን የመን እየተቆጣጠሩ ባለበት ሁኔታ ለተባረረው ይየመን መንግስት በግልጽ ድጋፍ መስጠት የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወያኔ አዛዦቻቸው ምን ያህል በየመን መውጫ አጥተው ለሚገኙት ለኢትዮጵያውያን ደንታ እንደሌላቸው ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመሩት ቴድሮስ አድሃኖም የተለመደ “የአዛኝ ቅቤ አንጓች” ውሸታቸውን ማውራት ቀጥለዋል።
ቴድሮስ አድሃኖም በራሳቸው ጌዜ በጀልባ ተንጠላጥለው ጅቡቲ የደረሱትን ኢትዮጵያውያን ከየመን ያስወጡ በማስመሰል “እስከ አሁን 30 ኢትዮጵያውያን ጅቡቲ ደርሰው ኢንባሲያችን ተቀብሏቸዋል” ብለዋል።
ቴድሮስ አድሃኖም አያይዘውም “ሰንዓ የሚገኘው ኤምባሲያችን ወደ ዛሬ አጥቢያ የጦር መሳሪያ ድብደባ ደርሶበታል፡፡ አምባሳደሩም ሌሎች ዲፕሎማቶችም ደህና ናቸው፡፡ የብዙ አገሮች ኤምባሲዎች የተዘጉ ቢሆንም ከዜጐቻችን በፊት አንወጣም ብለው ዜጐቻችንን ለመርዳት ጥረት እያደረጉ ላሉ ዲፕሎማቶችና አስተዳደር ሰራተኞች ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬው ለተባረረው የየመን መንግስት በግልጽ ድጋፋቸውን እየሰጡ ባለበት ሁኔታ ነው እንግዲህ ቴድሮስ አድሃኖም አማጽያኑ በተቆጣጠሩት ከተማ የሚገኘው ኢምባሲያቸው እና ሰራተኞቹ በየመን የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ በሰንዓ መሽገው እንደሚገኙ እየተናገሩ ያሉት።
ቴድሮስ አድሃኖም ቀደም ሲል በፌስቡክ ገጻቸው የአዲስ አበባ ስልክ ቁጥሮችን አስቀምጠው በየመን የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ከፈለጋችሁ ደውሉልን ማለታቸው ይታወሳል።
ሌሎች ሃገሮች አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን ወደ የመን በመላክ ዜጎቻቸውን በማውጣት ላይ ናቸው።
No comments:
Post a Comment