ኢምሩ ዘለቀ | የካቲት ፪ሺ፯
ለማስታወስ ያህል የዛሬ ሶስት ዓመት “ሞረሽ የአማራ አብሮነት ድርጅት” ብለን እኔ ራሴ፡ አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ፡ አቶ ይስሃቅ ክፍሌና ዶክተር ምስማኩ አስራት ሁነን ግቡ ለአማራዉ እርዳታ ለመስጠት የሆነ ማሃበር አዘጋጅተንና አስመዝገበን ነበር፤ የድርጅቱም አላማ ከማናቸዉም የፖሊቲካ ንቅናቄ ነጻ የሆነ የመረዳጃ ማህበር ብቻ እንዲሆን ነበር።
ይህንን እርምጃ ለመዉሰድ የገፋፋን ባለፉት ዓመታት በተለይ የወያኔ ቡድን የመንግሥት ስልጣን ከያዘ ወዲህ በተለይ በአማራዉ ሕዝብ ላይ የሚያካሂደው ወሰን የለሽ ጭቆናና ግፍ፤ ሕዝቡን ለማጥፋት የምያደርገው ሙከራ በጣም አሳስቦንና አስጭንቆን ነው። በዚህም አንጻር በየቀኑ የሚወርድብት በደል አንሶ የአማራዉ ሕዝብ ቁጥር እስከ ስድስት ሚልዮን ተቀንሷል ይባላል። ይሄም የሕዝቡ ቁጥር ከሃገሪቷ ጠቅላላ እድገት ጋር እየተመዛዘነ እንዲካሄድ፤ እርጉዝናን ለመቆጣጠር በሚሰጠዉ ክትባትና ልዩ ልዩ መድሃኒት ስበብ፤ ሴቶችን ጭርሶ የሚያመክኑትን እንዲሰጥ ተብሎ በተቀናጀ ሴራ መደረጉ የማያጠራጥር ሆኗል።
ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ሁሉ ኢሰባዊ በደልና ጥቃት የሚጣልበት የአማራ ወይንም የሃበሻ ሕዝብ ማን ነው፧ በራረጅም የታሪክ ጉዞ ከብዙ ነገዶችና ጎሳዎች ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ተዛምዷል፤ በዚህ ታሪካዊ ሂደት አብረን ተጉዘናል፤ ብዙ ችግር በጋራ አሳልፈናል፤ አበርን ደምተን አብረን ሞተን ኢትዮጵያ አገራችንን ነጻነቷንና ክብሯን ጥበቀን አቆይተናል፤ በኢትዮጵያዊነታችን ጸንተን እስካዛሬ ተጉዘናል።
ስለዚህ በቋናቋና በባህል አማራ ነን ስንል፤ በዘር ደግሞ ከልዩ ልዩ ነገድ ስለምንዋለድ የኢትዮጵያ ፍሬዎች ነን እንላልን፤ አማራ ወይም ሃበሻ የሚባለው በአንድ ጎሳ ወይም ባንድ አካባቢ አይተመንም፤ አይከለልም፤ በረጅም ክፍለ ዘመናት ታሪክ የተጥነሰሰ፤ የራሱን ቋንቋ፤ ፊደላትና ድርሰት፤ ፍልስፍናና ጥበባት ያመነጨ፤ የመንግሥት ሕግና ስርዓት የደነገገ፤ ይታላቅ ሃይማኖቶች ባለአደራ የሆነ፤ ከፍተኛ ስልጣኔ ለዓለም ያበረከተ ሕዝብ ነው።
የአማራው ብዛት ከግማሽ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያላነሰ ሲሆን፤ በጉልበትም፤ በችሎታም፤ በእዉቀትም የጎደለው ነገር ሳይኖር፤ ራሱን አዋርዶኖ አጎልብሶ የማንም መሳለቅያ ሁኗል፤ ይደበደባል፤ ይታሰራል፤ ይገደላል፤ ከተወልደበት ቦት እየተፈናቀለ በገዛ አገሩ ስደተኛ ሁኗል፤ የወያኔዎችና የአንድ አንድ ግለሰቦችና ፖሊቲከኞች የልፈፋና የግል አላማ የሚሰበክበት መሳርያ ሁኗል። ስለ አማራው መጎሳቆልና መወገር ብዙ ይወራል ይተቻል ነገር ግን እስካሁን ድረስ ካለበት ችግር ሊያድነው የሚችል አንድም አካል አልተገኘም። እንደዚህ ያለ ተግባር ለማድረግ በተመኮረ ጊዜ ከራሱ ከአማራው መሃል አፍራሽና ተቃራኒ ድርጊት ይፈጠራል፡ በዛሬ ወቅት የወያኔ ቡድን አገርን ቀጥቅጦ የሚገዛው ብቻዉን ሁኖ ወይም የአብዛኛውን ሕዝብ ድግፍ አግኝቶ አይደለም፤ ከአማራዉ ከኦሮሞው ከሌሎች ወገኖች ተባባሪና አብሮ አገብጋቢ ድጋፍ እያገኘ ነው።
በተለይ ባለፉት ስልሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በችግርና በድህነት እየታረዘ መድህን ይሆኑልኛል ብሎ ደሙን ተፍቶ ያፈራቸው ምሁራን ዛሬ በሚልዮን ይቆጠራሉ፤ በተቀረው የዓልም ክፍል ጊዝያዊና ዘመናዊ ዘዴ እያመነጨ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አዉራ ሁኖ የሚመራዉ የተማረዉና ያወቀው መደብ ሲሆን፣ በሃገራችን ያለው ምሁር ይህንን ተግባር ለማሟላት አልቻለም። ነጻነትን ለመጎናጸፍ በሚደረግ ተጋድሎ ህብረሰቡ በሙሉ መሳተፍ አለበት፤ ሃብታሙም ደሃዉም በእኩያ የሚካፈሉት ግዴታ ነው፤ ይሄም የፖሊቲካ ወይም የሌላ ወገናዊነትን የሚነካ አይደለም፤ የዚህ ወይም የዝያ ድርጅት አባል ነኝ የሚያሰኝ አይደለም፤ ዛሬ በአማራው ላይ ነገ በኔ ብሎ የሚያሳስብ ነዉ፤ ወንድ ሴት ልጅ ሽማግሌ ሳይለይ የሁሉም የጋራ ትግል ነዉ።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ዉስጥ የአማራዉ ህዝብ ቁጥር ከአንድ ሲሶ ይበልጣል እንጂ አያንስም፤ ይሔንን ያህል የሰው ጉልበት አቅፎ፤ በርካታ አዋቂዎችና ባለሃብቶች እያሉት፤ እንደዚህ ያለ ዉርደትና መስቃየት እስከ ጥፋት የሚያመራ ዘመቻ ሲካሄድበት አንገቱን ደፍቶ ሲቀበል ማየት ያሳፍራል፤ይጎመዝዛል፤ አለኝታን ያሳጣል። ያለመስዋእትነት የሚገኝ ነጻነትና ክብር የለም፤ ሁሌም አባቶቻችን እንዳደረጉት ተጋፍጦ መታገል አለ፤ ከንቱ ዛቻና ወሬ ድል አያስገኝም።
በተለይ ወጣቱ ትውልድ፤ የነገ ሰዉ የሆነው፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው፤ የተያዘውን የጎሳ አወቃቀርና ዘመን አመጣሽ የባዕድ ባህልና ፖሊቲካ አሽቀጥሮ ጥሎ አዲሷን ኢትዮጵያ በታሪካዊ ቅርሷ ላይ መገንባት አለበት።
ከማክበር ሰላምታ ጋር፤
ኢምሩ ዘለቀ።
No comments:
Post a Comment