የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ፣ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጠባቂነት ወጥቶ፣ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዚዳንትነት ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም በ106 አንቀጾች መጽደቁ የሚታወስ ነው፡፡
መሻሻል አለባቸው የሚባሉ አንቀጾች እንዳሉ ሆነው፣ በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ላይ ሕዝብ በደንብ አለመወያየቱም ሳይዘነጋ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሕገ-መንግሥቱ መጽደቅ እንስማማለን፡፡
የኢህአዴግ ሥርዓትም ይህ ሕገ-መንግሥት የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን፣ የሐገሪቷን ብዙ ችግሮች መፍታቱን፣ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች እኩልነት መሰረት መጣሉንና ሕገ-መንግሥቱም የግድ መከበር እንዳለበት …ወዘተ. ዘወትር አስረግጦ ይናገራል፣ ይገልጻል፡፡ ከመርህ አኳያ፣ ሕገ-መንግሥቱ መከበር እንዳለበት ብዙዎቻችን የምንስማማበት ሀቅ ነው፡፡
መሻሻል አለባቸው የሚባሉ አንቀጾች እንዳሉ ሆነው፣ በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ላይ ሕዝብ በደንብ አለመወያየቱም ሳይዘነጋ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሕገ-መንግሥቱ መጽደቅ እንስማማለን፡፡
የኢህአዴግ ሥርዓትም ይህ ሕገ-መንግሥት የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን፣ የሐገሪቷን ብዙ ችግሮች መፍታቱን፣ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች እኩልነት መሰረት መጣሉንና ሕገ-መንግሥቱም የግድ መከበር እንዳለበት …ወዘተ. ዘወትር አስረግጦ ይናገራል፣ ይገልጻል፡፡ ከመርህ አኳያ፣ ሕገ-መንግሥቱ መከበር እንዳለበት ብዙዎቻችን የምንስማማበት ሀቅ ነው፡፡
ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ፤ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ይገኙ የነበሩ ዜጎች፣ ‹‹ሕገ-መንግሥቱን በሀይል ለመናድ …››፣ ‹‹ሕገ-መንግሥቱን በዐመጽ ለማፍረስ …››፣ ‹‹ሽብር ለመፍጠር…››፣ ‹‹አመጽ ለማነሳሳት …›› ወዘተ በሚሉ ወንጀሎች ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ በተለይ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ክፉኛ መጣሱን ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ያሰሙ ከነበሩት አቤቱታዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በፍርድ ሂደት እና በፍርድ ውሳኔም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት/እርምጃ እንደተወሰደባቸውም የብዙዎቹ ሮሮ ሆኖም ሰምተነዋል፡፡ ‹‹ምን ያህሉ የወንጀል ክሶች ትክክለኛ ፍትህን አገኙ?›› የሚለው እውነተኛ ጥናት የሚያስፈለገው ይመስለኛል፡፡
ከፍርድ በኋላም፣ በወህኒ እና በማረሚያ ቤቶች የበርካታ ዜጎቻችን ሰብዓዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንደተጣሰ እና እየተጣሰ እንደሚገኝ ብዙ ጊዜ በቅሬታ፣ በአቤቱታ፣ በበደል ድምጸት፣ በምሬት ቃልና በሀዘን ዕንባ ሰምተናል፣ በተግባርም አይተናል፡፡
ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ ተማሪዎችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ዜጎች ከማዕከላዊ ጀምሮ እስከቃሊቲ፣ ቂሊንጦና ዝዋይ እስር ቤቶች ድረስ ሰብዓዊ መብቶቻቸው መጣሱን ጉዳያቸው በሚታይበት ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ክስ ቢመሰርቱም ‹‹መብት ጥሰዋል›› በተባሉት አካላት እና ግለሰቦች ላይ ትክክለኛ ምርመራ ተደርጎ ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡
የታሳሪዎች ጥያቄ እና አቤቱታ በአግባቡ አለመመርመሩ፣ አለመፈተሹና ከቃል ያለፈ ተግባራዊ የፍትህ እርምጃ አለመወሰዱ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ይበልጥ እንዲጣስ በር ከፍቷል! የልብ ልብ ሰጥቷል! ትምክህትን አንግሷል! ያልተጻፈ ሕግ ፈጥሯል! ሥርዓት አልበኝነትን አስፍኗል!
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 18/1 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› ይላል፡፡ ይህንና ሌሎች የሕገ-መንግሥቱን አንቀጾች መከበር አለመከበራቸውን አስመልከቶ ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› በሚለው የእኔ እና አቤል አለማየሁ መጽሐፍ ላይ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠተው ነበር፡ –
‹‹ሕጉ አልተከበረም፡፡ ባለፈው ሳምንት እንኳን ከዚህ ጉዳይ ጋር የተገናኘ ነገር እየሰማን ነው፡፡ [ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው 03/08/2005 ዓ.ም ነበር] ከማረሚያ ቤቶች የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፈጸማል፤ ‹‹እመኑ›› ወይም ‹‹በሌላ ሰው ላይ መስክሩ›› ይባላል፡፡ ሠው ወደኋላ ታስሮ፣ መሬት ላይ ተወርውሮ፣ ቀዝቃዛ ውኃ ይደፋበታል፡፡ ስለዚህ ይሄ ሕግ አለመከበሩን፣ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ከሚደርሱን ሪፖርቶች እንረዳለን፡፡››
እንግዲህ በዶ/ር ነጋሶ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው ሕገ መንግሥት በርካታ አንቀጾች አለመከበራቸውን ዶ/ሩ በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ምሳሌ እያቀረቡ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 10/1 እና 2 ‹‹ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡››፣ ‹‹የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ›› በሚል ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን፣ በርካታ ዜጎች እነዚህ ሕገ-መንግሥታዊ መብቶቻቸው ተገፍፈው ነበር አቤቱታተቸውን ደጋግመው የሚሰሙት፡፡
በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ክስ የተመሰረተባቸውና ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙት ሴት ጦማሪያን ማኅሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሳዬ፣ ከአያያዝ ጋር በተገናኘ በማረሚያ ቤቱ ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ያቀርቡት የነበረው አቤቱታ፣ ‹‹በማስረጃ የተደገፈ አይደለም፤›› ተብሎ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተሰጠ ብይን ውድቅ መደረጉን የሪፖርተር ጋዜጣ የፍርድ ቤት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ታምሩ ጽጌ በነጋታው አስነብቦን ነበር፡፡
የጦማሪዎቹ ጥያቄ፣ ከእናትና አባቶቻቸው ውጪ እንዳይጠየቁ መከልከሉ፣ ሽብርተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ፍርድ ሳይሰጥባቸው እንደአሸባሪ መቆጠራቸው፣ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገውን ንጹህ ሆነው የመገመት መብታውን የሚያሳጣ መሆኑ፣ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይቀላለቁ መደረጋቸውንና ሌሎችንም ደርሰውብናል የሚሏቸውን ችግሮች ነበሩ፡፡ ለዚህ መሰል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ‹‹በማስረጃ የተደገፈ አይደለም›› በሚል ምክንያት በቃላሉ አቤቱታ ውድቅ ይደረጋል፡፡ አቤቱታው በትክክል መፈጸም አለመፈጸሙን ማን ትኩረት እና ግድ ሰጥቶት ይመረምረው?! የመብት ጥሰትን ለመከላከል በፓርላማ ኃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመው መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ ሥር ተላቅቶ ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ብሎ ማሰብ ራስን በቀላሉ ማታለል ይሆናል፡፡
ከወራቶች በፊት፣ ጋዜጠኛ ኤዶምና ጦማሪ ማህሌት ጨምሮ በተመሳሳይ ክስ በቂሊንጦ እስር ቤት ታስረው የሚገኙት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወለደየስ እና አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ጦማሪያኑ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ዘላለም ክብረትና አጥናፍ ብርሃኔ በጋራ ሆነው በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ለአራት ወራት ያህል ታስረው በነበረበት ወቅት የደረሰባቸውን አስከፊ እና አሳዛኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለኮሚሽኑ በዝርዝር ቢያቀርቡም ጉዳዩ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› የተባለ ይመስላል፡፡
በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በጸረ-ሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል ፖለቲከኞቹ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ …ከማዕከላዊ ጀምሮ እስከቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰባቸው አስከፊ እና አሳዛኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትናንትም ሆነ ዛሬ ተገቢ መልስ አላገኙም!
በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም ፍትህ ጋዜጣ ላይ የጻፋቸው ጽሑፎች ‹‹አመጽ ቀስቃሽ ናቸው›› ተብሎ (በአንድ በኩል ‹አንድም በጻፈው ጽሑፍ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም› ብለው የመንግሥት ሃላፊዎች እየተናገሩ ባሉበት ሁኔታ) በግፍ የሶስት ዓመት ፍርድ የተበየነበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም በዝዋይ እስር ቤት ህክምና አጥቶ በጀርባ፣ በወገብና በጆሮ ህመም እየተሰቃየ እንደሚገኝ ሰምተናል፣ አድምጠናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ከአንድ ወር በላይ በማንም ሰው እንዳይጠየቅ መከልከሉም አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ቀደምም ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬም ህክምና መነፈጋቸው እንዴት ይረሳል?! ርዕዮት አሁንም ድረስ ይህም ሕገ-መንግሥቱን በግልጽ የሚጻረር የመብት ጥሰት ተፈጽሞባት ይገኛል – ከአንድ ዓመት ከስድስት በር በላይ ከወላጅ እናቷና አባቷ ውጪ በማንም አትጠየቅም፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ፖለቲከኛው አንዷለም አራጌ በእስር ቤት በርካታ የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል፤ እስከንድርን ከጥቂት ሰዎች ውጪ ማንም እንዳይጠይቀው ተከልክሏል፡፡
የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት (እነአህመዲን ጀበል፣ ኡዝታዝ አብበከር አህመድ፣ የሙስሊም መጽሄት አዘጋጅ አሙበከር ዓለሙ …)ና ሌሎች ሙስሊም ወንድምና እህቶቻችንም ላይ መሰል የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ከችሎታቸው ውሎ አድምጠናል ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ አበበ ቀስቶ እና ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር ከድብደባ ባለፈ በጆሮ እና በአንገት ህመም ህክምና አጥተው ተሰቃይተዋል፡፡ በእነብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የነበሩ ከ40 በላይ ተከሳሾች በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት እንባ እየተናነቃቸው ሲናገሩ በችሎት ታድሜ ዘግቤያለሁ፡፡ በተለይ፣ በዚህ መዝገብ የብቸኛዋ ሴት እማዋይሽ ስቃይ ከህሊና አይጠፋም፡፡ በርካታ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በኦነግ ስም ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ በማዕከላዊ የደረሰባቸውን መከራ ለችሎት ሲናገሩ አድምጫለሁ፡፡ ባለፈው ዓመትም በማዕከላዊ ለጥቂት ቀናት ታስሬ በነበረበት ወቅት፣ ከጋምቤላ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ ….ክልሎች በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል የተወሰኑት በ‹‹ጨለማ ክፍል›› እያሉ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት በአዘኔታ፣ ሲልም ሳቅ እያሉ በግልጽ ነግረውኛል፡፡ በዚህች ጽሑፍ፣ ስንቱን አንስቼ እችለዋለሁ?
ይህን ሁሉ ማለቴ፣ ሕገ-መንግሥቱ ላይ በግልጽ የሰፈረው የዜጎች ሰብዓዊ መብት በግልጽ እና በስውር መደፍጠጡን፣ መናዱን፣ ተሰምቶ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› መባሉን አሁንም ይበልጥ ለማስገንዘብ ነው፡፡ አሁንም ‹‹የዜጎች የሰብዓዊ መብት ይከበር!›› እንላለን፡፡
የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9/2 ‹‹ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ-መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው›› ይላልና ኢህአዴግ ሆይ! እባክህ በዋነኝነት ራስህ ያወጣኃቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ብትችል ቀድመህ፣ ባትችል …ሰልሰህም ቢሆን አከብረህ ለማስከበር ድፈር! አሊያ፣ የግፍ እና የመከራ መብዛት ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደምረው እንደአይን ብሌን የምትሳሳለትን ሥልጣን እስከወዲያኛው በእርግጠኝነት ያሳጡሃልና ልብ ያለው ልብ ይበል!
ቸር እንሰንብት!
Elias Gebru Godana
No comments:
Post a Comment