ባለፈው ዓመት ‹‹ስለ ሀገር ያገባኛል›› የሚል አዲስ መንገድ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ተጀምሮ ነበር፡፡ ይህ፣ በምንወዳት ሀገራችን ወቅቱ የሚጠይቀው ቃል ሲሆን ብዙዎች እውነተኛ መርህ አድርገው በተግባር ሊኖሩበት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
በእኔ አረዳድ፣ ‹‹ስለ ሀገር ያገባኛል›› ማለት ከምንም በላይ ሀገርን ማስቀደም ማለት ነው፡፡ ስለሀገር ህልውና መቆርቆር ማለት ነው፡፡ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ዘብ መቆም ማለት ነው፡፡ ትክክለኛ ፍትህ እንዲረጋገጥ ድምጽን ማሰማት ማለት ነው፡፡ ሰብዓዊነት በተግባር እንዲገለጥ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ለዓላማ መሬት ረግጦ ለመቆም መወሰን ማለት ነው፡፡ የዜጎችን በደል አይቶ አለማለፍ ማለት ነው፡፡ አስተዳደራዊ በደሎች ሲፈጸሙ ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ አድርባይ እና የዳር ተመልካች አለመሆን ማለት ነው፡፡ ‹‹የሀገር ችግር የእኔም ችግር ነው›› ብሎ ማመን ነው፡፡ ከጥቂቶች ይልቅ ለሰፊው ህዝብ መወገን ማለት ነው፡፡ የተሻለች ሀገርን ለመፍጠር የራስን መልካም አስተዋጽኦ ማበርከት ማለት ነው፡፡
ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው ለእውነተኛ መብታቸው፣ ለተፈጥሯዊ ነጻነታቸው፣ ለተፈጠሩለት ዓላማቸው …ወዘተ. ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩ፣ ሲገደሉ፣ ሲዋከቡ፣ ሲደበደቡ፣ ሲሰደቡ፣ ሲንገላቱ፣ …አይቶ እንዳላየ እና ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን ተገቢ አይሆንም፡፡ የዜጎች ኢ-ፍትሃዊ እስር፣ ስቃይና እንግልት …ከምር ሊሰማን ይገባል! የእነዚህ ዜጎች መከራ ከልብ ተሰምቶን ብቻ ማለፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በቻሉት ሁሉ፣ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን በቁርጠኝነት መቃወም ያሻል፡፡ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች ወደፍትሃዊነት ህልው እስኪቀየሩ ድረስ ተስፋ ባለመቁረጥ ለለውጡ መንቀሳቀስ እና መታተርም አስፈላጊነቱ አሻሚ አይሆንም፡፡ የትኞቹም ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎች፣ ትክክለኝነታቸው ተረጋግጠው መታመን እስከቻሉ ድረስ፣ ጥያቄዎቹን እና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸውን በሚችሉት ሁሉ መደገፍ የዜግነት ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የኤች አይ ቪ/ኤ አይ ዲ ኤስን ሥርጭት ለመግታት፣ እንዲሁም ህመሙን ተከትሎ ማግለል እና አድልዎን ለማስቀረት ታልሞ፤ በሀገራችን በተወሰኑ ወንድ እና ሴት ድምጻዊያን አማካኝነት በጋራ ተሰርቶ በተሰራጨው ‹‹ማፍቀር ነው መሰልጠን›› በሚለው መልዕክት ሰጪ ዜማ ውስጥ፣ የአንዱ ቤት ሲንኳኳ የሌላኛው ቤት ድረስ ሊሰማ እንደሚችል የሚገልጽ የሙዚቃ ስንኝ አለ፡፡ ይህ የሙዚቃዊ የዜማ አገላለጽ፤ በዚህ ጽሁፍ ላነሳሁት ርዕሠ ጉዳይም የሚሰራ ይመስለኛል፡፡
በአንዳችን ቤት ውስጥ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት መፈጸሙን በአንክሮ አውቀን፣ በፍርሃት እና በዳር ተመልካችነት ዝም ማለት መቻል ትልቅ ስህተት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊትን በመቃወም ‹‹ያገባኛል›› ብሎ ለመንቀፍ፣ ለመተቸት፣ ድምጽን በድፍረት ለማሰማትና ለመታገል የግድ በራስ ላይ እስኪደርስ መጠበቅ አይገባም፡፡ ብዙዎች ግን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት በዜጎች ላይ ሲፈጸም ዝምታን ሲመርጡ፣ አይተው እንዳላዩ ሲሆኑና ‹‹‹አያገባኝም›› ሲሉ በግልጽ ይስተዋላል፡፡
እነዚህ ግን፣ ሌሎች ላይ የደረሰው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በአንዱ ቀን በራሳቸው ላይ ሲፈጸም፣ ወዲያው ድርጊቱን፣ ድርጊት ፈጻሚውንና ‹‹ድርጊት አስፈጻሚ ነው›› ብለው ያሰቡትን አካል ወይም ግለሰብ ወይም ቡድን ሲኮንኑ ወይም አምርረው ሲተቹ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቱን እና አድራጊውን ወይም እንዲደረግ ያስቻለውን አካል መንቀፍ፣ መተቸትና ማብጠልጠል ያለባቸው በራሳቸው ሲደርስ ብቻ ሳይሆን በሌላ ወገናቸው ላይ በሚፈጸምበትም ጊዜ ነው፡፡
ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፣ በ2005 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር ከተዳረጉት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የግል ባለሃብቶችና በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት ሰራተኞች መካከል፤ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገብረህዋድ ወልደጊዮርጊስ አንዱ ነበሩ፡፡
እኚህ የመንግሥት ባለሥልጣን፤ ከፖሊስ ምርመራ በኋላ፤ በከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡበት ወቅት፣ እኔም እንደጋዜጠኛ ጉዳዩን ተከታትሎ ለመዘገብ በችሎቱ ታድሜ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት አቶ ገብረህዋድ በዚሁ የሙስና ክስ ጉዳይ ከባለቤታቸው ኮሎኔል ኃይማኖት ተስፋዬ ጋር አብረው በችሎት ተገኝተው ለችሎቱ አቤቱታ አቀርበዋል፡፡ በግርድፉ አቤቱታቸው ይህን ይመስል ነበር፡- ‹‹በእስር ላይ ሰብዓዊ መብቶቼ ተጥሰዋል፡፡ ባለቤቴም ራቁቷን ሆና እንድትፈተሽ ተደርጓል፡፡ ልጄም የሚጠቀምበት ኮምፒውተር ተወስዶበታል፡፡ …ይህቺ ሀገር ወደየት እየሄደች ነው? …››
ምንም እንኳን፣ የማንም ተጠርጣሪ ሠብዓዊ መብት በመርማሪ አካል መጣስ አለበት ብዬ ባላስብም፣ በዕለቱ ግን በአቶ ገብረህዋድ አቤቱታ መገረሜ አልቀረም፡፡ ለምን? ከመርህ አኳያ፣ አቶ ገብረህዋድ ወልደጊዮርጊስ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚፈጸምን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቃውመው አቤቱታ ማቅረብ የነበረባቸው እሳቸው ላይ ሲደርስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ፣ እንደመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንነታቸው፣ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የዜጎች መብት እንደሚጣስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማወቃቸው ወይም መስማታቸው አይቀርም፡፡ በዚያ እስር ቤት፣ በምርመራ ወቅት አሳዛኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው ዜጎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች …ወዘተ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለችሎቱ እሳቸው እንዳቀረቡት አይነት እና እሳቸው ካቀረቡት የከፋ አቤቱታ ማቅረባቸውን የግል የሀገር ሚዲያዎች እና የውጪ ሀገራት የዜና አውታሮች ሲዘግቡ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች በየመግለጫዎቻቸው እና በየሪፖርቶቻቸው አካትተው ይፋ ሲያደርጉ መስማታቸው እሙን ነው፡፡
አቶ ገብረህዋድ፣ የሥርዓቱ ሹመኛ ከመሆናቸው አኳያ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን ያኔ ተረድተው ቢሆን ኖሮ፣ ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት ነበር ድርጊቱን መንቀፍ፣ መተቸትና እንዲቀየር ጥረት ማድረግ የነበረባቸው! በራስ ሲደርስ ብቻ ድምጽን ማሰማት ያስተዛዝባል፣ ያስገምታልም፡፡ ‹‹ይህቺ ሀገር ወደየት እያመራች ነው?›› ብሎ በፍርድ ቤት ከመናገር ያስቆጥብ ነበር፡፡ ሌላም ሌላም ….
ወሳኙ ዓላማ
የታቀደበትንም ሆነ ያልታቀደበትን ዓላማ ለማሳካት በግለሰቦች፣ በስብስቦች፣ በቡድኖችና በተቋሞች የሚቀየዱ የትኩረት አቅጣጫዎች ማነስ እና መተለቅ በውጤቱ ላይ ጉልህ ልዩነትን መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትንሽ ሲታሰብ ውጤቱም ትንሽ ይሆናል፡፡ ዓላማ ትልቅ ሲሆን ውጤቱም የማታ ማታ ከፍተኛ የመሆን ሁነቱ አሻሚ አይሆንም – ለዓላማ እስከመጨረሻ ድረስ በጽናት መቆም ከተቻለ፡፡
ወሳኙ ዓላማ
የታቀደበትንም ሆነ ያልታቀደበትን ዓላማ ለማሳካት በግለሰቦች፣ በስብስቦች፣ በቡድኖችና በተቋሞች የሚቀየዱ የትኩረት አቅጣጫዎች ማነስ እና መተለቅ በውጤቱ ላይ ጉልህ ልዩነትን መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትንሽ ሲታሰብ ውጤቱም ትንሽ ይሆናል፡፡ ዓላማ ትልቅ ሲሆን ውጤቱም የማታ ማታ ከፍተኛ የመሆን ሁነቱ አሻሚ አይሆንም – ለዓላማ እስከመጨረሻ ድረስ በጽናት መቆም ከተቻለ፡፡
ግለሰባዊ የተለያዩ ዓላማዎችን ከትልቁ ሀገራዊ ግብ ጋር ማቆራኘት ከተቻለ ግለሰቡ፣ ቤተሰቡ፣ ቡድኑ፣ ተቋሙ፣ ሀገሪቷ፣ ከዚያም አልፎ አህጉሪቷ እና ዓለም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ አሊያ ግሰለብ-ተኮር ትንሽ ግብ መወጠን አይደለም ለሌሎች ለራስም እምብዛም ትርፍ የለውም፡፡
ሰፊዋን እና ትልቋን ሀገር በቀዳሚነት አስቦ በተሰማሩበት የሕይወት ዘርፍ በንቃት፣ በተነሳሽነት፣ በድፍረት፣ በቀናነት፣ በጥንካሬ እስከመጨረሻ ድረስ ዓላማን ለማሳካት መወጠን እና መንቀሳቀስ ስኬቱም፣ ትርፉም፣ ፍቅሩም፣ ክብሩም፣ ሀብቱም፣ አሸናፊነቱም …የላቀ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የተወጠነውን እውነተኛ ዓላማ ጀማሪው ማየት ባይችል እንኳ ተተኪው ያሳካዋል፤ ይፈጽመዋል፡፡ ሀገሪቷም ሆነች የሀገሪቷ ህዝቦች ከላቀው የዓላማ ውጤት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከፍሬውም ይበላሉ፤ ይቋደሳሉ – ትልቁ ዓላማ ሀገር ሲሆን፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹ስለሀገር ያገባኛል›› የሚለውን ቃል ከመርህ አኳያ፣ ከእውነት እና ስለእውነት ይዞ ለተግባራዊነቱ በጽናት ቆሞ መንቀሳቀስ መቻል ታላቅነት ነው – ፍሬውም ቅዱስ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
No comments:
Post a Comment