Monday, April 20, 2015

“አይማረኝ አልምራችሁም” ቦኮ ሃራም ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት

boko
ደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው ዓመጽና ግድያ ቦኮ ሃራም የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ግጭቱንና ግድያውን እንዲያስቆም ገደብ ሰጠ፡፡ “አይማረኝ አልምራችሁም” አዘል መልዕክት ማስተላለፉ ተገልጾዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ያዕቆብ ዙማ ልጅ የውጭ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ መባረር አለባቸው በማለት ከተናገረ በኋላ የተነሳው ዓመጽና አሰቃቂ ግድያ በርካታዎችን ያስደነገጠና ያስቆጣ ሆኗል፡፡ ከኤድዋርድ ዙማ በተጨማሪ የዙሉው ንጉሥ ተመሳሳይ ንግግር በማድረጋቸው አፍሪካውያን በአፍሪካውያን ላይ ለማመን የሚከብድ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡

ይህ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ዘግናኝ ሞት ምክንያት የሆነው ቀውስ በቶሎ እንዲቆም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ የተለያዩ የዜና መዋዕሎች ዘግበዋል፡፡
እስካሁን በእርግጠኝነት ባይታወቅም ከተገደሉት መካከል ናይጄሪያውያን መገኘታቸው ያስቆጣው ቦኮ ሃራም ደቡብ አፍሪካ ደም መፋሰሱን፣ ግድያውንና ዘረፋውን ካላስቆመች የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ በተሰጠው ገደብ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በውጭ አገር ዜጎች ላይ እየተከሰተ ያለውን ለማስቆም እምቢ የሚል ከሆነ ቦኮ ሃራም ደቡብ አፍሪካን በቦምብ እንደሚያናውጣት አስጠንቅቋል፡፡ በዚህ በዩትዩብ ተሰራጨ በተባለ አጭር የቪዲዮ መልዕክት መሠረት ቦኮ ሃራም በአጸፋው በናይጄሪያ፣ በቻድ፣ በኒጀር እና በአካባቢው አገራት የሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያንን በሞት እንደሚቀጣ ማስታወቁ ተገልጾዋል፡፡
የቦኮ ሃራም መልዕክት እርግጠኛ መሆኑ አልታወቀም ያለው አንድ የናይጄሪያ ጋዜጣ ቦኮ ሃራም ጥቃቱን ከላይ በተጠቀሱት አገራት በሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎችም ጭምር ላይ እንደሚያደርስ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡
የስሙ ትርጓሜ “የምዕራባውያን ትምህርት ሃራም (እርኩስ) ነው” የሆነው ቦኮ ሃራም እኤአ ከ2009 ጀምሮ በናይጄሪያና አጎራባች አገራት እስከ13ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን መግደሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት በርካታ ዜጎችን ያፈናቀለው ቦኮ ሃራም በዚህን ወቅት “ጥሩ ሰው” መስሎ ለመታየት መሞከሩ ያስቆጣቸው ናይጄሪያውያን በማኅበራዊ ገጾች አጸፋውን መልሰዋል፡፡ አንዱ አስተያየት ሰጪ “ቦኮ ሃራም አፉን ቢዘጋ ይሻለዋል፤ እነሱ ራሳቸው የሚያደርጉት (ዘግናኝ ተግባር) በደቡብ አፍሪካ ከሚደረገው የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ፤ ማፈሪያዎች” ብሏል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት ቦኮ ሃራምን አሸባሪ ድርጅት በማለት የፈረጀው ሲሆን የናይጄሪያ መንግሥት እስካሁን ከቦኮ ሃራም ጋር ጦርነት እያካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል

No comments:

Post a Comment