- ‹‹አገራዊ ታሪክንና የብሔረሰብ ታሪክን ለማጣጣም ችግር እየተፈጠረ ነው››
- ‹‹ብሔርን ከብሔር ከማናቆር ያለፈ ፋይዳ የሌለው ሐውልት እስከመገንባት ተደርሷል››
- ‹‹የተለየ ሐሳብ ያላቸው በፀረ ሽብር፣ በሙስናና በግብር አዋጆች ይጠለፋሉ›› በምሁራን የቀረቡ ጥያቄዎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ከተወጣጡ ምሁራን ጋር፣ በብሔራዊ መግባባትና በበርካታ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ፡፡
መንግሥት ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ማነቃነቅና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚፈልግ ማብራሪያ በመስጠት ማክሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ውይይቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከፍተውታል፡፡ በዚህ የመግቢያ ንግግራቸው መንግሥት ኅብረተሰቡን ለማንቀሳቀስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚያስችል አኳኋን ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ እየጣረ ቢሆንም፣ ፖለቲከኛው ጥግ ጥጉን ይዞ ከመታኮስ ባለፈ የመቻቻልና የመወያያት ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር እንዳቃተው ገልጸዋል፡፡
‹‹በአንድ ትውልድ የተጣመመ የፖለቲካ ባህል ተሸክመን ቁርሾን ለዚህ ትውልድ እያስተላለፍን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አመፅ የማይቀሰቀስ የሐሳብ ብዝኃነት እንዴት ነው እዚህ አገር መፍጠር የሚቻለው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ለምሁራኑ ውይይት እንዲመች የቀጣዩ አምስት ዓመት የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶችን አቅርበዋል፡፡
በመቀጠል ምሁራኑ የሚሰጡትን ሐሳብ ወይም ጥያቄ ለመቀበል መድረኩን ክፍት ያደረጉ ሲሆን፣ የመጀመርያ ዕድል ያገኙትም ዕውቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ለጥያቄያቸው መነሻ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋነኛ የመዋያያ ሐሳብ በሆኑት፣ የኢትዮጵያ ህዳሴና አገራዊ መግባባት በሚሉት ሐሳቦች ላይ ነው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ከታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ህዳሴውን ዕውን ለማድረግ የኢትዮጵያን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹አሁን ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ከፍተኛ ብዥታ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰብ ታሪክና አገራዊ ታሪክን ለማጣጣም ችግር እየተፈጠረ እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ከሚያቀራርቡን ይልቅ የሚያለያዩንን ማጋነን እየተለመደ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ብሔርን ከብሔር ከማናቆር ያለፈ ፋይዳ የሌለው ሐውልት እስከ መሥራት ተደርሷል፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡
‹‹እነዚህን ችግሮች አስወግዶ አገራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ መንግሥት ምን ያህል ተዘጋጅቷል?›› ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ጠይቀዋል፡፡
ሌላ አንድ ምሁር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዳሴ የተባለበት ምክንያት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማንቀሳቀስ ታስቦ መሆኑ እጅግ እንደሚያስደስት በመጠቆም፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን ሕዝቡን ለህዳሴ ከማነሳሳት ይልቅ ቀዝቃዛ ውኃ የሚቸልስበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ባለው ፖለቲካዊ ሥርዓት የተለየ አመለካከት ማስተናገድ የማይችል፣ እንዲያውም የሚያሸማቅቅ በመሆኑ በዚህ የህዳሴ ጉዳይ ወይም አገራዊ መነቃቃት ላይ ውኃ እንዳይቸልስበት ሥጋታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል ይላሉ፡፡ ነገር ግን የጠበበው ሁሉም ነገር ነው፡፡ የጋዜጠኝት ምኅዳሩ፣ የሲቪል ሶሳይቲ ምኅዳሩ፣ የነጋዴነት ምኅዳሩ፣ ወዘተ›› ብለዋል፡፡ ይኼ የሆነው የወጡትን የፀረ ሽብር፣ የፀረ ሙስና፣ የግብር፣ የበጎ አድራጎት አዋጆች በመቀጠም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሞጋች የሆኑ ጋዜጠኞች በፀረ ሽብር ሕጉ እንጠለፋለን ብለው ይሠጋሉ፡፡ ነፃነታቸውን ያጣሉ፡፡ ነጋዴውም በግብር ሕጉ እጠለፋለሁ ብሎ ይሠጋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛውም በፀረ ሽብር ሕጉ ይሸማቀቃል፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
‹‹ኢሕአዴግ መስከረም ላይ ባካሄደው ጉባዔ በአገሪቱ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ጠቅሶ በዋናነት ከፍተኛው አመራርን ተጠያቂ ማድረጉን ከገለጸ በኋላ፣ እርስዎ በጥቅምት ወር ካቢኔዎን ሲያሾሙ ፓርላማ ይዘዋቸው የመጡት ግን እንዳለ ያንኑ የድሮ ካቢኔ ነው፡፡ በካቢኔው ያላካተቷቸውን ደግሞ አማካሪ ብለው አጠገብዎ አድርገዋቸዋል፤›› ያሉት ጠያቂው፣ ይኸው በመጋቢት ወርም ለውጥ የለም ሲሉ ተችተዋል፡፡
ዘመቻው ሁሉ የታችኛው አመራር ላይ ነው ሲሉም ተችተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ራሱን ከመገምገም ባለፈ በሌላኛው አባል ፓርቲ ላይ የመግባት ዕድሉና ድፍረቱ አለው ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቀረቡት ጥያቄዎች ቅደም ተከተል መሠረት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ላነሱት የኢትዮጵያ ታሪክን በተመለከተ ስላለ ብዥታ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም በተመሳሳይ ተጋርተውታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ አንዳንዱ መቶ ዓመት ብቻ ነው ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ ሌላ ይላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያችን አሁን ያላትን ቅርፅ ይዛ ላይሆን ይችላል እንጂ፣ ሕዝቦቿ በያሉበት ታሪክ የሠሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይኼንን ማወቁ ራሱ ረዥም ዘመን ይወስደናል፤›› ብለዋል፡፡
በማከልም፣ ‹‹በመጀመርያዎቹ ምዕተ ዓመታት አካባቢ የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ የእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ታሪክ ነው፣ በዚህ ላይም መግባባት አለብን፤›› ብለዋል፡፡
አንዳንድ ሰው የብሔር ብሔረሰብ ታሪክ ሲነሳ እንደሚደነግጥ፣ የዚህ መንስዔውም ይከፋፍለናል ያጠፋፋናል የሚል መሆኑንን ገልጸው ለምንድነው የሚለያየን? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የቅኝት ጉዳይ እንጂ ታሪኩ ያለ ነው፡፡ የተፈጠረ እንጂ ማንም አሁን ላይ ሊፈጥረው አይችልም፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የአገሪቱ ታሪክ አልጋ በአልጋ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ጠንካራ ጎኑን አጎልብተን የተዛባውን ደግሞ ትምህርት የምንወስድበት መሆን እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡
‹‹የተዛቡ ግንኙነቶቻችንን መገደብ የለብንም፡፡ ሐውልት የምንሠራው ልንማርባቸውና ዳግመኛ አይከሰትም በሚል ቃል ለማሰር ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዳይ ሲነሳ ወይም ኢትዮጵያ ታላቅ ነበረች ወደ ታላቅነቷ እንመልሳት የሚል መሪ ቃል አንግበን፣ ነገር ግን በታሪክ ላይ አገራዊ መግባባት ሳይፈጠር ጉዞው የትም አያደርስም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በእርግጥም ከሚያግባቡን ታሪኮች ይልቅ የሚለያዩን በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይኼን የሚበትኑና የሚዘሩ አሉ፡፡ ያው እኛው ምሁራን ነን፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተለየ አመለካከትን የማይቀበል የፖለቲካ ሥርዓት የህዳሴው ጉዞ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ እንዳይቸልስ በማለት ከላይ በዝርዝር የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የተለያየ አመለካከትን የማይቀበል ሥርዓት የጊዜ ጉዳይ እንጂ መውደቁ አይቀርም፤›› የሚል ጠቅለል ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም የሚመሩት ፓርቲና መንግሥት ይህንን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ፣ የተለየ አመለካከት ስለተፈጠረ ሥጋት ውስጥ የሚወድቅ አይደለም ብለዋል፡፡
ነገር ግን ኢሕአዴግ ችግር የለበትም አለማለታቸው እንዳልሆነ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ ችግር መስሎ የሚታያቸው ‹‹ሞቼ እገኛለሁ›› የሚል ፖለቲካዊ አመለካከት ከማመቻመች (Compromise) ከማድረግ የገነነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹እልኸኝነት ባህሪያችን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ነገሮችን በቀላሉ አንቀበልም፡፡ የኢሕአዴግ አባላትም ከማኅበረሰቡ የወጡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
የሃይማኖትና የብሔር ብዝኃነት እንዳለ ሆኖ የሐሳብ ብዝኃነት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹እውነት ለመናገር ይህንን ችግራችንን የተረዳሁት ምርጫ 2002 ላይ ነው፡፡ በቅንነት የተከራከርኩበት ቀላል ነገር ቋቅ እስኪለኝ ተወሳስቦ ቁጭ ይላል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢሕአዴግን በተመለከተ የሐሳብ ልዩነቶች ብዙ አያስፈሩንም፡፡ የሚገለጹበት መንገድ ነው የሚያስፈራው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከኋላ ጦር አሠልፎ ከፊት በሐሳብ ልፋለም ነው የሚለው ነው ያስቸረገን፤›› ብለዋል፡፡ ሕጎችን ያላግባብ ከመጠቀም ጋር በተገናኘ የሰጡት ምላሽ በዋነኝነት ያጠነጠነው መንግሥት ያለው መረጃና ሰፊው ሕዝብ ያለው መረጃ የተለያየ በመሆኑ የተፈጠረ የግንዛቤ ችግር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹አንድ የማታምኑትን ልንገራችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ትልቅ ነጋዴ የራሱ እስር ቤት አለው ቢባል ታምናላችሁ? እኛ እነዚህን ነው የምናስረው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መንግሥት ዓይኑም፣ ጆሮውም፣ አካሉም በየቦታው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹በዚህ የተነሳም ከእናንተ የተሻለ መረጃ አለው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹መርካቶ ላይ እከሌ የሚባል ሰው ቦምብ ሊያፈነዳ ነው፣ እከሌ የሚባል ጋዜጠኛ አብሮት አለ የሚል መረጃ ሲቀርብልኝ በምን አቅሜ ነው ዝም የምለው? የሕዝቤን ደኅንነት የማልጠብቅ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ለምን እቀመጣለሁ?›› ብለዋል፡፡
ከከፍተኛ አመራሩ መበላሸትና ካቢኔው በአዲስ ደም አለመተካቱን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ካቢኔያቸው 30 በመቶው አዲስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ለካቢኔ ሹመት ሳቀርብ ማወቅ በምችለው ደረጃ የማውቃቸውን ነው የመረጥኩት፡፡ እገሌ የሚባል ሌባ ነው የሾምከው የሚል መረጃ ካልመጣ እኔ ምን አባቴ ላድርግ… አሁንም ማስረጃ ካላችሁ ስጡኝ?›› ብለዋል፡፡
ኢሕአዴግ በአባል ፓርቲዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚችልም ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ አንደኛው መንገድ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በኩል የእያንዳንዱ ፓርቲ ችግር ይነሳል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በእያንዳንዱ ፓርቲ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ለሥራ አስፈጻሚው ሪፖርት ይደረጋል ብለዋል፡፡ የኢሕአዴግ ፕሮግራም ቃሉ ሳይቀየር ሁሉም አባል ፓርቲዎች መቀበል ግዴታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከፓርቲው ደንብ ውጪ የሚያፈነግጡ ሊሰረዙ እንደሚችሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢሕአዴግን ከግንባር ወደ አንድ የተዋሀደ ፓርቲ የማሸጋገር ሥራም ጎን ለጎን ወደፊት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment