(ኢ.ኤም.ኤፍ) ጋዜጠኛ ሚልዮን ሹርቤ በስደት አለም ላይ በነበረበት ወቅት ህይወቱ አልፏል። ከዚያ ጋር በተያያዘ፤ በተለይ የሟች እህት እና ባለቤቱ የሰጡት ቃለ ምልልስ ግን አሁንም አነጋጋሪ እንደሆነ ነው። ኢሳት ቴሌቪዥንም ጉዳዩን በ”እንወያይ” አምዱ ላይ አየር ሰጥቶ ለህዝቡ ዝግጅቱን አስተላልፏል። ከተለያዩ ወገኖች የሚሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶችም እንደቀጠሉ ናቸው።
ከኢሳት ዝግጅት በኋላ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም የደረሰውን መረጃ መሰረት አድርጎ እንደገለጸው ከሆነ፤ ከሚልዮን ሹርቤ ህልፈት በኋላ ቃል የሰጠችው ባለቤቱ ሰላም ውድነህ የገዢው ፓርቲ አገልጋይ ናት። እንዲህ በማለት ነው ፋሲል የኔአለም ስለሰላም ውድነህ ማንነቷን የገለጸው።
የሟች ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ ባለቤት ፣ ሳላም ውድነህ፣ “ሚሊዮን ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ ይሰራ ነበር፣ ኑሮየን ለማሸነፍ ስራ መቀየር አለብኝ ” በማለት ወደ ኬንያ እንደተሰደደ ስትናገር ስሰማ በጣም ገረመኝ፣ በጣምም አዘንኩ። ሰላም ውድነህ ማን ናት? እርሷን በቅርብ የሚያውቁ የኢህአዴግ አባላት እንደነገሩኝ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የፖለቲካ ዘርፍና የህዝብ ግንኙነት ዋና አማካሪ ናት። የካቢኔ አባልና የስርአቱ ዋና ካደሬ ተብላ የምትታወቅ ስትሆን፣ በታማኝነቷም በስርዓቱ ሰዎች የተመሰገነች ናት። ማንም የዚያ አካባቢ ሰው በመሄድ በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላል። ይች ሰው ናት እንግዲህ የሚሊዮንን ታሪክ ጥላሸት በመቀባት ሁለት ጊዜ ሞት የፈረደችበት። መቼ ይሆን ለህሊናችን መኖር የምንጀምረው?
በመቀጠል ደግሞ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በዚህ ጉዳይ የሰጠውን አስተያየት እናቀርባለን።
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ በስደት በሄደበት ኬንያ ህይወቱ አልፎ አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት የነበረውን ጭንቅ አይተናል ። በወቅቱ አርቲስት ታማኝ በየነ በኢሳት የተደጋገመ የእርዳታ ቅስቀሳ ሲያደርግ ሰምቻለሁ ። እርዳታ አሰባሰቡ አዘኔታ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ መሆኑ ግልጽ ነው ። በፖለቲካም ሆነ በአስማት አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ መሰጠቱን መልካም ነው ። ይሁንና የአስከሬኑ መመለስ በእነ አቶ አንተነህ አብርሀም በኩል መሆኑም በራሱ የጋዜጠኞች ማህበር በመሆኑ ለጋዜጠኛው ቆሞ ወይም በንጹህ ወገንተኝነት እንዳልሆነም ግልጽ ነው ። የፖለቲካ ንግድ ነው የተካሄደው ። ወዳጄ አንተነህ አብርሀም ማህበሩን ወክሎ ለኢብኮ በሰጠው ቃለመጠይቅ የግል ጋዜጠኝነትን የመሰደጃ ስንቅ ብቻ አድርጎ ከመግለጹም በላይ አንድም ቀን ለጋዜጠኛ ቆሞ አልታየም ። ከየት መጥቶ አዛኝ እንደሆነ አይታወቅም ።
ቴዎድሮስ አስተያየቱን በመቀጠል ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ ትንታኔ ሰጥቷል። ዘርዝር ጉዳዩን በመተው በመጨረሻ ያስቀመጠውን ቁም ነገር ልናካፍላቹህ ወደድን። ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።
ይህም ሆኖ የመጀመሪያዎቹ ተስፋዎች በስደት ላይ ያሉ የሙያ አጋሮቻችንና የታማኝ በየነ መሆኑን መዘንጋት አይቻልም ። በተለይ ታማኝ በየነን እጅግ አመሰግነዋለሁ ። እህቱና የልጁ እናት በተናገሩት አዝንላቸዋለሁ እንጂ አልናደድባቸውም ። ያ ቃላቸው ለሚሊዮን የከፈሉት ዋጋ እንደሆነ አድርጌ ነው የምወስደው ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመንግስት ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩትን ደጋፊዎቻቸው በንፁህ ህሊናቸው የተናገሩት እንወዳልሆነ አምነው ከተቀበሉት የሚሊዮን ቤተሰቦች ላይ የሆነውም ተመሳሳዩ ነው ። የግድ መታሰር የለባቸውም ። አሁን ሚሊዮን የለም ። ከዚህ የህይወት ድካም ተገላግሏል ። በህይወቱ ከተባለለት በላይ በመቃብሩ ላይ የበቀለው የፖለቲካ አረም እውነቱን እየደበቀው ይገኛል ። ” ሀገሬ ገመናሽ ” አይደል ዶ/ር በድሉ ያለው? ሀገሬ ግን ገመናዋን መሸፈን አቅቷታል ። የህይወት ሳይሆን የፖለቲካ ሀገር ሆናለች ። ከፖለቲካ ውጭ መተንፈስ አልቻልንም ። ወደ 90 ሚሊዮን ፖለቲከኛ ያለባት ሀገር ምን ገመና ይኖራታል ? እንደ ሀገርም ይሁን ህዝብ የምንሄድበት መንገድ ያሳዝናል ። ወላጆቻችን እንዲህ ያለ ጉዳይ ሲገጥማቸው ” እስቲ አስከሬኑ ይረፍበት ” ይላሉ ። እስቲ አስከሬኑ ይረፍበት ።
እኛም የኢ.ኤም.ኤፍ ባልደረቦች የሚልዮን ሹርቤን ነፍስ ይማር በማለት ዘገባችንን እዚህ ላይ እናበቃለን።
No comments:
Post a Comment