Saturday, August 3, 2013

ፎቅና መንገዱንማ ጣሊያንም ሠርቶት ነበር!!

በመጀመሪያ አልፎ አልፎ ለንባብ በማቀርባቸው ጹሑፎቼ ህወሃት እያልኩ የምጽፈው ኢህአዴግ ማለት ቸግሮኝ አይደለም ። የይስሙላ ግንባሩ ወይም ክልሎች የሚባሉት ሁሉም
የሚተነፍሱት በህወሃት ሳንባ በመሆኑ ከህወሃት ትእዛዝ ውጭ አንዲት ስንዝር አልፎ መሄድ የማይችሉ በመሆኑና የዚህ ስብስብ አባላትም ምንጫቸው አብዛኛዎቹ ከደርግ በውጊያ
የተማረኩና ከኢህአፓ ተገንጥለው ወጥተው መታጠፊያው ሲጠፋ ለህወሃት እጅ በመስጠት ህወሃት እንደጭቃ አብኩቶ ጠፍጥፎ የሠራቸው ፤ የህወሃትን ደም በደም ሥራቸው ያስገቡና
የህወሃትን ትእዛዝ ከማስፈፀም ውጭ የማያስቡ ሆዳቸውን ሞልተው ለማደር የተጠራቀሙ ቡክኖች (ፈሪዎች) ስለሆኑ በዓምላካቸው ህወሃት ስም አብሮ ቢጠሩ ስለሚቀል ነው ።
ህወሃት
በማለት የምጠራቸው እንጅ የድሮ ኢህዴን የዛሬው የማራ ሕዝብ ቅኝ ገዥ (ብአዴን)፤ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)በምሮኮ የተያዙ የደርግ ወታደሮች የተሰለፉበት? ፤
ድሮ የስምጥ ሸለቆ ሕዝቦች እየተባሉ የተሰባሰቡና በኋላ የደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ደህዴድ)ተብሎ የሚጠራውና የአባል ድርጅቶች ሁሉ ንጉሠ- ነገሥት የሆነው ህወሃትን
ያካተተ እንደሆነ አጥቸው አይደለም ። ነገር ግን አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን መንግሥትና ኢህአዴግ እያሉ ዜና ሲያቀርቡ ስለምሰማ ይህ ጉዳይ የሚቀፍ ሆኖ ስለአገኘሁት ነው ።
ምክንያቱም ገዥዎቻችን አንድን መንግሥት እንደ መንግሥት የሚያስቆጥር መስፈርትን አሟልተው ሳለማይገኙና የግንባሩ አባላትም ድምጽ ለመስጠት እንጅ ሃሳብ የማፍለቅ ወይም
መፍትሄ የሚያመጡ ፖሊሲ የሚነድፉና መመሪያ የሚያወጡ ሆነው ባለመገኘታቸው ሁሉም መንግሥታዊ ይሁን ድርጅታዊ ተቋማት ህወሃት የሚመራውና ለህውሃት ጠቀሜታ ብቻ
የተቋቋሙ በመሆናቸው ገዝፈውና አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ጠፍረው የያዙት እነሱው ስለሆኑ ተራ ነብሰ ገዳይና ውርጋጦችን ያቀፈ ቡድን ነው ። እነ አያ በረከት ፤ አዲሱ ለገሠ፤ ተፈራ
ዋልዋ ፤ ታደሰ ካሣና ህላዊ ዬሴፍ እንዲሁም ካሣ ሸሪፎና ተሰማ ገብረሕይወት በዚህ አባባሌ የሚያዝኑብኝ ከሆነ እነርሱ ራሳቸውም በጣም የሚያሳዝኑ የተነሱበትን ዓላማ ሽጠው
በቅጥፈት ህወሃትን እያገለገሉ ከርስን ከመሙላት በስተቀር ሌላ መንገድ የሌለ መስሏቸው እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደርና ሕሊናዊ ነፃነት ማግኜት ተገቢ መሆኑን እንደዘነጉ
እንዲረዱልኝ በዚህ አጋጣሚ ጠቁሜ ማለፍ እፈልጋለሁ። በተጨማሪም የዛሬዎቹ ቱባ-ቱባ ባለሥልጣኖችና ሚሊየነሮች የድል አጥቢያ አርበኛውን እንተወውና ትጥቅ አንግባችሁ ከበርሃ
የመጣችሁ በሙሉ ለተወሰነች ደቂቃ ሰከን ብላችሁ እንድታስቡና በየአውደ-ግንባሩ ለዴሞክራሲ ፤ ለፍትህና ነፃነት ከራሱ ወንድሞች ጋር ገጥሞ ያለቀው ታጋይ ፤ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት
የረገፈው ኢትዮጵያዊ እናንተን በሀብት ክብረትና በሥልጣን እንድታብጡ ነበር ወይ? መልሱን እኔው ራሴ ልመልሰውና አይደለም። ቃሉን አልጠበቃችሁም ክዳችሁታል እግዚአብሔር
ፍርዱን ይስጣችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አንድ ቀን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተሞ ሲነሳ ቀልባችሁን ሳይገፈው እንደማይቀር ከዚህ በፊትም አስመስክሯልና አይቀሬውን ጠብቁ ።
ለህወሃት እድሜ መራዘም ምክንያቱ የሕዝቡ በአድን አቋም ፀንቶ የመቆም ባህል አለማደግ ወይስ የተቃዋሚ ኃይሎች የውስጣዊና ውጭያዊ ችግሮች አፈታት የፖለቲካ ባህል አለመኖርና
ችግሮችን ትዕግስት በጎደለውና በጠምንጃ ለመፍታት የመሄድ አባዜ ናቸው? አንድ እናት በጫንቃዋ ከአንድ ልጅ በላይ ማዘል አትችልም ። ኢትዮጵያም አንድ ድርጅት እንጅ መቶ
ድርጅቶችን የምታዝልበት አንቀልባ ሊኖራት አይችልም ? በቅርቡ አንድ የተቃዋሚ ኃይል ድርጅት አመራር በኢሳት ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው የራሳቸውን ድክመት ሸፍነው
ሕዝቡን በአንድ አቋም ፀንቶ የመቆም ባህል አላዳበረም ሲሉ ከሰዋል ። ይህ በእጅጉ ሰውየው ወደፊት ሥልጣን ቢይዙ ምን አይነት ገዥ እንደሚሆን የሚያመላክትና የወቅቱን ነባራዊ
ሁኔታ ያልቃኘና ግምታዊ አነጋገር ከመሆን አይዘልም ወይም የኢትዮጵያን ሕዝብ አያውቁም ማለት ነው። አዲስ አበባ በሰማያዊ ፓርቲ ፤ ጎንደርና ደሴ በአንድነት አስተባባሪነት ብሶቱን
ለማሰማት የወጣው ሕዝብ እኮ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ እየመጣ ይመዝገብና የድርጅታችን አባል ይሁን የሚሉ ፖለቲከኞች በበዙበትና ሕዝብ በገዥውም ሆነ በተቃዋሚ ኃይሎች
አመኔታ መሪና አታጋይ እየጠበቀ ባለበት ወቅት ይህን መሰል መልዕክት ማሰራጨት በህዝብ ላይ ያለን ንቀት የሚያሳይና ግለሰቡ በፖለቲካው ዓለም ላይ የሚቀራቸው መሆኑን በግልጽ
የሚያሳይ ነው ። የተከበራችሁ አንባቢዎቼ አሁንም ወደተነሳሁበት ዋና ነጥብ ገና አልገባሁም። ወደዚያ ከመሄዴ በፊት ኢሳትና ኢትዮ-ሜዲያ ትኩስ ትኩሱን የአገራችን በጎም ሆነ መጥፎ
ዜና እንዲደርሰን እያደረጉ ይገኛሉ መጀመሪያ ሁሉም ሜዲያዎች በሚያደርጉት ጥረትና በሚሰጡት አገልግሎት ሊመሰገኑ ይገባል ። በተለይ ደግሞ ኢሳት በ3ዓመት ውስጥ እየመገበን
የመጣውን የዜና ጥማታችን ሲታይ ለቃለ-መጠይቅ ወይም ለውይይት እየመዘዙ የሚያቀርቡልን ሰዎችና ከሰዎቹ የምናገኘው ልምድ ቀላል አይደለም ስለዚህም ኢሳት ሊደገፍና ሊበረታታ
ይገባዋል ። በኢሳት መድረክ ብቅ የሚሉ ሃሳባቸውን የሚያጋሩን ሰዎች ላይ ግን ለሕዝብ የሚጠቅም ሃሳብ ካፈለቁ እሰየው ካልሆነና ሕዝብን ግራ የሚያጋባ ወይም ከወቅቱ ሁኔታ ጋር
አብሮ ሊሄድ የማይችል ሃሳቦችን ሲሰነዝሩ ደግሞ መመከትና ማጋለጥ ያለብን ሁላችን መሆን አለበት ። ጉዳዩ ለኢሳት ጋዜጠኞች ብቻ የሚተው አይደለም ። መጭዋን ዴሞክራሲ
የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለመገንባት ከወያኔ የማይሻሉትን የተቃዋሚ ኃይሎችንም ተሸክመን መጓዝ አይገባንም ። በጊዜ እንዲታረሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ። ካልታረሙ ከሕዝብ እንዲነጠሉ
ማድረግ ይገባል ።ይህ ተግባር ደግሞ ከሚሰማው ፤ ከሚያዳምጠው ፤ ከሚመለከተው ሕዝብ ሊመጣ መቻል አለበት። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የአምባገነኖችና የጎጠኞች መፈንጫ መሆን
አይኖርባትም። የሕግ ልዕልና እንዲከበር ሰላም እንዲሰፍንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣ ፤ እኩልነት እንዲሰፍንና የአገር ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ክቡር መስዕዋትነት የከፈሉ ጀግና

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፤ ጀግኖች ወላጆቻችን እንደሻማ የቀለጡበትን ዓላማ ፤ የውድ አገራችን የብዙ ዘመን አኩሪ ታሪክ አናዳፍነው አንቅበረው እንተባበር አንድ እንሁን ።
ሶስተኛው ጉዳይ ሰው ገድሎ የጥይት ሂሳብ የሚጠይቀው ፤ በርሃብተኛ ስም ከለጋሽ አገሮችና ግብረ-ሰናይ ከሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥን እርዳታ ለፖለቲካዊ ጠቀሜታና ለወታደራዊ ትጥቅ
አገልግሎት የሚያውል አሸዋን እህል ነው ብሎ የሚሸጥ ፤ የአብያተ ቤተክርስቲያንን የሙዳይ ገንዘብ የሚዘርፍ አጭበርባሪ ድርጅት እነዚህን የውጭ ባለሀብቶች እውነት እንዲህ በዋዛ
መሬት በነፃ ይሰጣል ተብሎስ ሊታመን ይችላልን? ሊሆን አይችልም? ድርጅቱ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር የበለጠ ጠቀሜታ ያገኛል ወይም እኩል ይጋራል ለማለት ያስደፍራል ጉዳዩን
የሚመለከተው ባለሙያ ትኩረት ሰጥቶ ቢከታተለው መልካም ነው። የሽህ አልሙዲንና የህወሃት ሽርክና በቂ መነሻ ሊሆን ይችላል። አንድ በቅርብ የማውቀውና ዘመዴ የሚሆን ነጋዴ
ቀደም ባሉት ዓመታት እነዚህን ሰዎች እንዲረዱና መንገዱ አልጋ በአልጋ እንዲሆንልህ አስር አስር ሽህ ብር ባፋቸው አስይዘህ እስኪበቃቸው ካሰከርካቸው በማግስቱ አምሳ ሽህ አምስት መቶ
ሽህ ሆኖ ታገኘዋለህና እኔ ተመችቶኛል ብሎ አጫውቶኝ ነበር። ይህም ሌላው መንገድና መነሻ ነው ።
ኢትዮጵያዊ ዜጎችን በማባረር የስኳር ፋብሪካ እንገነባለን ስለመባሉና የተፈለገበት ምክንያት፦
ህወሃት በኢትዮጵያ ውስጥ ቁልፉ የሕዝብ ችግር ስኳር በመሆኑ የሕዝቡን ችግር ለመቀረፍ ሳይሆን የስኳር ፋብሪካ ቢቋቋም ምን ያህል ጥቅም አገኛለሁ ከሚል ሂሳብ ሲሆን በሌላ በኩል
ደግሞ የሕዝቡን ማንነት ለመለካትም የሚጠቀምበት ተግባር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ ። ምክንያቱም ሕዝብ እሰየው ብሎ ቢቀበለው እርግጠኛ ነኝ ህወሃት ይህን የስኳር ፋብሪካ
ሊገነባው ይቅርና ስሙንም ሊጠራው አይችልም ። ነገር ግን ክብር ያላቸውን ገዳማትና አብያተ-ቤተክርስቲያናትን በማፍረስ ሕዝቡን ማስቆጣትና ቁጣውን በጠምንጃ ለማስተንፈስ የታለመ
እንደሆነ ግልጽ ይመስላል ። ከአማራው ነገድ ቀጥሎ የህወሃት የራስ ምታት የኢትዮጵያ ገዳማትና መነኮሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ካህናት ስለሆኑ እነዚህን
ለሥልጣኑ እንቅፋት ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ለማፍረስ የጠብ ማጫሪያው መንገድ ይህ በመሆኑ እስከየት እንደሚሄድ ልናየው እንችላለን መሪ ተብየውም ታዋቂው ሰው በላ አባይ
ፀሐየ መሆኑ ነገሩ ሆን ተብሎ እንደታቀደ ባጭሩ መረዳት ይቻላል።
በአገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶች ወደ ውጭ እንዲወጡ መደረጉና በአገር ውስጥ የተከሰተው የገብያ መናር፦
ከኢትዮጵያ ውጭ በመላው ዓለም በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተሰደው እንደሚኖሩ ይታወቃል ። ሁሉም በየፊናው ሰርቶ የሚያድር ሲሆን አንዳንዶቹ በንግድ የተሰማሩ
ናቸው ። በየግሮሰሪው ገብተን ብንመለከት የሌለ አይነት የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጥ አይነት የለም ። የተመረቱበት ቦታ ኢትዮጵያ ሲሆን በአገር ቤት ያለውን የሸቀጥ መናር ስንመለከት አንዱ
ዋናው ምክንያት ይህ እንደሆነ በግሌ እረዳለሁ ። ለዚህ ነገር አንድ እልባት እስከአልተሰጠው ድረስ የገበያ ንረቱ እየሰፋና በመጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ይታወቃል። ችግሩን ማን
ፈጠረው ሲባል ልቅና ሥርዓት ያጣው የህወሃት መርህ እንደሆነ ይታወቃል። እንደ አንድ ድርጅት ወይም ተቋም ቅድሚያ ተጠቃሚ መሆን ያለበትን የመለየት አቅም የሌለውና ለህዝብ
ደንታ ቢስነቱን የሚያሳይ ሲሆን ለውጭ ባለሀብቶች ከተሰጠው መሬት የተረፈው ለተወላጁ ተከልክሎ ጦም እያደረ ፤ በጠባቡ በኋላ ቀር የማምረቻ መሣሪያ የተመረተው ምርትም ወደ
ውጭ ያለ ምንም ቁጥጥር እንዲወጣ ሲደረግ የሚያመላክተው አገርን በፍጥነት የማጥፋት ሴራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል።
በሌሎች ርዕሶች እስከምንገናኝ ደህና እንሰንብት።!!
(gfuafuate21@gmail.com)
 August 2, 2013

No comments:

Post a Comment