የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የነፃ ፕሬስ አስፈላጊነት
ትልቅ ቦታ እንዳለው ከልብ እናምናለን፡፡ ያለነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲ
አለ ብሎ መናገር ማወናበድ እንጅ እውነት ሊሆንም አይችልም፡፡
የነፃ ፕሬስ መኖር በራሱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መኖር መገለጫ
ነውና፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖርም ነፃ ፕሬስ ይኖራል፡
፡ ወደ እኛ ሃገር ስንመለስ ግን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነው
እናገኛቸዋለን፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ሆኖ ለባለፉት 21 ዓመታት
ሃገሪቱን ሲያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በወረቀትና በቃል
እንጂ ከዚያ በዘለለ በተግባር ሲፈፅም አላሳየንም፡፡ ለመተግበር
የሞከራቸውንም እንደ ቀንዳውጣ ቀንድ መልሶ ሸሽጎታል፡፡ ስለዚህ
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማያምን ገዢ ፓርቲ ስለሆነ ለነፃው ፕሬስ
ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በመስጠት ፈንታ አጥፊና ደምጣጭ
ሆኖ እየሰራ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ህገ-መንግስታዊ ከለላ
ቢሰጠውም፤ ሳንሱር መነሳቱ በህግ ቢደነገግም፣ በገቢር ግን ሃሳብን
በነፃነት መግለፅ የሚያሳስር፣ የሚያሰድድና የመንግስት ጠላት
የሚያሰኝ ሆኗል፡፡
ፕሬስ ፍፁም ነፃነት የሚያስፈልገውና መንግስት ጣልቃ
የማይገባበት ህዝብን የሚያገለግል የማህበረሰብ ተቋም ነው፡
፡ እንደዚህ የምንለው ነፃ-ፕሬስ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም
ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ነፃ-ፕሬስ የሌለው መንግስት ኩራዝ
በሌለው ጨለማ ቤት ውስጥ የሚኖር ግለሰብ እንደማለት ነው፡
፡ ነፃ-ፕሬስ የሌለው ህዝብ በሃገሩ ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ
እንዳያውቅ የተፈረደበት ህዝብ ነው፡፡ ነፃ-ፕሬስ ለነፃነት፣ ለፍትሕና
ለእኩልነት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዥዎች ፕሬሱ
ለአምባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤
ይጠሉታል፤ ያጠፉታል፡፡ ኢህአዴግም እያደረገ ያለው ይሄንኑ ነው፡፡
ነፃው ፕሬስ ለህዝቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና መዳበር የሚያደርገውን
አስተዋጽኦ፣ ህዝቡ ባሪያ ከሚያደርግ አስተሳሰብ እንዲላቀቅ፤
ከአምባገነኖች የሚደርስበትን ጫና አልቀበልም እንዲልና የኑሮው
ሁኔታ እንዲሻሻል (improve people’s standard of living)
የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንደ ኢህአዴግ አይነቱ ዴሞክራሲያዊ
ያልሆነ መንግስት አይፈልገውም፡፡ ስለዚህ የማጥፋት ዘመቻ ያካሂዱበታል፡
፡ ገዢ ፓርቲ የሆነው ኢህአዴግ ለ9ዐ ሚሊዬን ህዝብ የሚመጥን ነፃ
ፕሬስ እንዲኖር ባለማድረጉ አገዛዙ ያልተሳካለት እንደሆነ አመላካች
ነው፡፡ “ፕሬስ ለዴሞክራሲ ዘብ ይቆማል” የሚለው የሰለጠነ አባባልም
የሚገባው አይደለም፡፡ ለፕሬሱ ዘብ መቆሙ ቀርቶ ማጥፋቱን በተወ።
ስለዚህ አገዛዙ ነፃው ፕሬስ ላይ ጥርሱን ማፋጨት ብቻ ሳይሆን
በማጥፋት ላይ መጠመዱን በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን።
የአገዛዙ የጥፋት ዘመቻ ሰለባ የሆነችው ፍትሕ ጋዜጣ ግልጽ
ባልሆነና በተድበሰበሰ መንገድ ህትመቷ እንዲቋረጥ መደረጉ፤ ዋና
አዘጋጇ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይና አሳታሚው ማስተዋል
የህትመትና የማስታወቂያ ስራ ኃ/የተ/የግ/ማ ላይ የተመሠረተው
ግልጽነት የጎደለው ክስ ሁሉ ተገቢ ያልሆነና መንግሥት የሚባለውን
አካል ጥርጣሬ ላይ የሚጥል የማንአለብኝነት ተግባር ነው ብለን
ስለምናምን በአስቸኳይ እንዲስተካከል እንጠይቃለን፡፡
በግል ህትመት ላይ ያሉትን ጋዜጦች መንግስት በጣልቃ ገብነት እንዳይገባና
እጁን እንዲያነሳም እንፈልጋለን !
ጋዜጣን ከህትመት ውጭ መሆን በጠቅላላው ፕሬስ ላይ የተቃጣ
ዘመቻ በመሆኑ የሚገባውን ያክል ርብርብ እና ተቃውሞ አለማሰማቱ
የመንግስትን ገለልተኛነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው የሚል
ጥርጣሬ አለን፡፡
3ዐ ሺ ኮፒ ትታተማለች የተባለች ፍትሕና በየሳምንቱ ከመቶ ሺ
ሰው በላይ ያነባታል ተብሎ የሚገመተው ጋዜጣ ነፃ ፕሬስ በሌለበት
ሀገር ላይ ስፍር በማይሞላ ሰበብ መዝጋት ራሱ አርቆ አለማሰብ
ነው፡፡ የፍትሕ አንባቢ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መብትም ሊጠበቅ
ይገባዋል፡፡ በጠቅላላ ከመንግሥት ሆደ ሠፊነትና አርቆ ማሰብ
ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ለፕሬሱ ዘብ ቋሚ እንጂ ራሱ አሳዳጅና
አጥፊ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ስህተቱን አርሞ ጋዜጣዋ መደበኛ
ህትመቷን እንድትቀጥል ማድረግ ይጠበቅበታል።
በመጨረሻም ማጥፋትና ማዳፈን ለችግሮች መፍትሔ አይሆኑም፡፡
ስለዚህ ገዢ የሆነው ኢህአዴግ ነፃውን ፕሬስ ከምድረ ገጽ የማጥፋት
ዘመቻውን በአስቸኳይ በማቆም ለሌሎችም ፈቃድ በመስጠት
ወደ ፕሬሱ የሚሰነዝረውን ሰይፍ ወደ ሰገባው መመለስ ሳይሆን
ጨርሶ እንዲጥል እንጠይቃለን፡፡ ህዝቡም መንግስትን “ለምን?” ብሎ
በመጠየቅ ወደ ትክክለኛ መስመሩ እንዲገባ ጫና ማሳረፍ ይገባዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር !!!
ከሰብኣዊ ብሎግ
No comments:
Post a Comment