Sunday, August 4, 2013

የሐገራችን የፍትህ አካል ከኬንያ ፍርድ ቤት ብዙ መማር ይጠበቅበታል!!

ህዝብና መንግስት ተለያይተው የሚኖሩባትን አገር መስፈርት የሚያሟሉ ደረጃቸው ቢዘረዘር ኢትዮጵያችን የመጀመሪያውን ተርታ ትመራለች፡፡ ይህንን አሳብ አስመልክቶ የተለያዩ አያሌ ድርጊቶችን መስቀመጥ ይቻላል፡፡ ከድርጊቶቹ ውስጥ የሃገራችንን የፍትህ ሥርዓት መመልከት በቂ ነው፡፡ ይህ የፍትህ ሥርዓት የተቋቋመው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ለመጠበቅና የኢሕአዴግን እድሜ ለማራዘም አይነተኛውንና ዋነኛውን ሚና እንዲጫወት ታስቦ ነው፡፡ ሐገርንና ሕዝብን የበደለ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለውን ወንጀል የፈጸመ ከፍተኛው የኢሕአዴግ ባለስልጣን ሕገ - መንግስታዊ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የትኛውንም አይነት ወንጀል ለመፈጸም ያስብም ይፈጽምም ሕገ - መንግስቱን ጣሰም አልጣሰም የባለስልጣናትን ደህንነት እስከ ጠበቀና እነሱን እሰካልተቃወመ ድረስ ባለው ላይ ይጨመርለታል፡፡ ለከፍተኛ ኃላፊነትም ይታጫል፡፡ 
ፍርድቤቶች እንዴት ተቋቋሙ? ዳኞችስ እንዴት ተሰየሙ? የሚለው ጥያቄ በየትኛውም የሃገራችን ጫፍ ላይ ቢነሳ መልሱ አንድ አይነት ነው፡፡የመንግስት ባለስልጣንን ለመጠበቅ፡፡ በቃ፡፡ በእንደዚህ አይነት መልኩ የተቋቋመ ተቋምና በዚህ አይነት መልኩ የተሰየመ ዳኛ እንዴት አድርጎ ለሕዝብ ጥቅም ሊሰራ ይችላል? መልሱን ለታዳሚ ትቻለሁ፡፡
የጹህፌ መነሻ የሆነኝ አንድ የኬንያ የአካባቢ ፍርድ ቤት በኬንያ መንግስት ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመስማቴ ነው፡፡ ውሳኔው ይህ ነው- የኬንያ መንግስት 11 ጠርጣሪ አሸባሪዎችን በሶማሊያ በኩል ለኢትዮጵ አሳልፎ በመስጠቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚረግጥና የሚያፍን በመሆኑ፤ አስረአንዱ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችም በኢዮጵያ መንግስት ድብደባና እንግልት የደረሰባቸውና እንዲሁም አያያዛቸው ሰብዓዊነት የጎደለው በመሆኑ ተከሳሹ የኬንያ መንግስት ለተበዳዮቹ $464000.00 (አራት መቶ ስልሳ አራት ሽህ የአሜሪካ ዶላር) እንዲከፍል ነው፡፡ የኬንያ መንግስትም ውሳኔውን ተቀብሎ በፍርድ ሂደቱም በጭብጥ መረታቱን አምኗል፡፡ ለዚህ ነው የእኛ አገር የፍትህ አካል ከኬንያ ፍርድ ቤት መማር አለበት ያልኩት፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ከፍተኛ ሙህራን ያለአግባብ ከስራ ሲባረሩ ትክክል አለመሆኑን የተቃወመ የፍትህ አካልና የህግ ባለሙያ ነበር?
በመዋቅር ሰበበ የገዥው ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ሠራተኞች ከሥራ ተባረው ከነቤተሰቦቻቸው ሲቸገሩ ለህዝብና ለመንግስት ቁሜያለሁ የሚለው አቃቢ ህግ የት ደረሰ?
በሕገ - መንግስቱ የመዘዋወር ነጻነት በትክክል ሰፍሮ እያለ በተለያዩ ክልሎች በቅርቡም በቤንሻንጉል ጉምዝ የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ ብቻ ያለአግባብ ቤት ንብረታቸው ሲወረስ ሲደበደቡና ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው (እንግልቱ አሁንም እንደቅጠለ ነው) የህግ ሰዎቻችን የት ደረሱ? በኢሕአዴግ የተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥፊዎች ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡ ይሄው በርካታ ወራቶች ተቆጠሩ አጥፊዎቹ ለህግ አልቀረቡም ፡፡ እንግልቱና መፈናቀሉ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለዎን አላከበሩም በማለት ሰውየውንና ችግሩን የፈጠሩትን የቤንሻንጉልን መንግስትንና የሥራ ኃላፊዎችን ለመክሰስ ባለሙያዎቻችን ምን ዋጣቸው?
ከአማራ ክልል ከሰሜን ጎንደር ዞን መሬት ያለአግባብ ተቆርሶ ለሱዳን መንግሥት ሲሰጥ (የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ላነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከኢትዮጵያ መንግስት መሬታችንን ትንሹን አስመልሰናል፡፡ ቀሪዎቹን ለማስመለስ በሂደት ላይ ነን) ነበር ያሉት፡፡ታዲያ ይህንን እያየና እየሰማ ያለ የክልሉና የፌደራሉ የህግ ሥርዓቱ አካላት ባለሙያዎች መሬት ተቆርሶ ለሱዳን መንግስት ሲሰጥ ምነው የበላቸው ጅብ አልጮህ አለ? መሬቱ ተቆርሶ እንዲሰጥ በፊርማቸው ያጸደቁትን ባለስልጣን፤ የክልሉን መንግስትና የፌደራል መንግስቱን ለመክሰስ መራጃ ጠፍቶ ነው?
• 424
የሚሆኑ የጋምቤላ ተወላጅ ዜጎቻችን በሟች ጠቅላይ ሚንስትር ትዕዛዝ ሲጨፈጨፉ የህግ ባለሙያዎቻችን ከተጎጂ ወገን ለመቆም ምን አገዳቸው? ወዘተ……………
የሃገራችን በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከዝቅተኛው ከኬንያ አካባቢ ፍርድ ቤት ብዙ ብዙ መማር ይኖርባቸዋል፡
ዛሬ በየእስር ቤቱ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንደነ እስክንድር ነጋ ርዕዮት አለሙ ሌሎች ፖለቲከኞች በማጎሪያ ጣቢያ ሆነው መከራቸውን የሚያዩት እንደ ኬንያዊ ያለ ኢችዮጵያዊ ዳኛ በማጣታቸው ነው፡፡ ለሐገርና ለሕዝብ ማሰብ አያሳስርም፡፡ የመንግስትን ስህተት ነቅሶ ማውጣት አያስወነጅልም፡፡ ፍትህን ነጻነትን ዲሞክራሲያዊ መብትን መጠየቅ አሸባረ አያሰኝም፡፡ ያገራችን አቃቢያን ህግ ዳኞች በጠቅላላው በፍትህ ሥርዓት አካላቱ ያላቸሁ ባለሙያዎች ምንጊዜም ከሕዝብ ጎን መቆም ይኖርባችኋል፡፡ መንግስት ይለዋወጣል፡፡ ሕዝብ ግን ያው ሕዝብ ነው፡፡ ከቶም ተለውጦ አያውቅም፡፡ አንድ ጊዜ ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ ያስተማራችሁ ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት እንድትበቁ ያደረገ ሳይማር ያስተማራችሁ አሁን በፍትህ እጦት የምታንገላቱት ሕዝብ ነው፡፡ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ያለሃጥቱ መንግስትን ለማስደሰት ብቻ የተሳሳተ ውሳኔ ወስናችሁ በኢሕአዴጎች ወህኒ ቤት በእስር እንዲሰቃይ ያደረጋችሁትን ዜጋ በአየነ ህሊናችሁ በመመልከት ወደራሳቸሁ ተመለሱ፡፡ ከራሳችሁና ከሕዝባችሁ ጎን ቁሙ፡፡ ከኬንያው ያካባቢ ፍርድ ቤት ብዙ ብዙ ተማሩ፡፡ አሁንም ዛሬም ነገም ተማሩ! ተማሩ!

No comments:

Post a Comment