Monday, February 17, 2014

የፈረደበትስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ግንቦት 7 እና የኤርትራ መንግስት አይደሉም! (ለአቶ ተክለሚካሄል አበበ፤ ጥያቄዎች ምላሽ ቢሆን) ያሬድ ኃይለማርያም

በመጀመሪያ በአቅርቡ በተከታታይ ለአንባቢያን ያቀረብኩዋቸውን ሁለት ጽሁፎች አንብበህና ጊዜህንም ወስደህ በዝርዝር ላቀረብከው የሙግት ሃሳብ ምስጋናዮ የላቀ ነው። ለነገሩ የጽሑፌም ዋና አላማ ጉዳዩን ሕዝብ እንዲያውቀው ብቻ ሳይሆን በተነሱት ነጥቦችም ዙሪያ በአንባቢዎች ዘንድ የውይይት ሃሳብንም በማጫር ጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝም ጭምር ስለሆነ ያንተ ምላሽ እኔንም በዚሁ ጉዳይ ላይ በድጋሚ እንድመለስበት አድርጎኛል። ምንም እንኳን ባነሳሃቸው በርካታ ሃሳቦች ፍጹም የተለያየ አቋም ያለን ቢሆንም ከእንዲህ አይነቱ የውይይትና ሃሳብን ሥልጡን በሆነ መልኩ የማንሸራሸር ልምድ ከየኮምፒቱሩ ጀርባ ተደብቀው በፈረስ ስማቸው መረን የለቀቀ እና ድንቁርና የታከለበትን ስድባቸውን ለሚወረውሩት የሳይበር አርበኞች ትምህርት ሊሆን ይችላል ብዮ አምናለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ከእኔም አልፈው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጭምር ጸያፍ በሆነ መልኩ ለመዝለፍና ለማንቋሸሽ ሞክረዋል።

ለምሳሌ ያህል እጅግ ድንቁርና በሚታይበት መልኩ በቤልጂየም ከሚገኙ የግንቦት 7 ደጋፊዎች ወይም አባላት መካከል በአንዱ ECADForum በተሰኘው ድኅረ-ገጽ ላይ Anicent Ethiopia በሚል ቅጽል ስም እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ከቀረቡት ሃሳቦች አንዱን ቃል በቃል ከነ አጻጻፍ ግድፈቶቹ ልጥቀስ፤ እንዲህ ይላል ‘… ethiopia’s hostory teaches us that when ethiopia’s unity and it’s children face such problems, not all ethiopians were ethiopia’s defenders, 80% of the population were bandas, only ethiopia’s brave children had resisted and won all the wars against ethiopia’s enemies. …’ ምንጭ http://ecadforum.com/Amharic/archives/10949/)። እንግዲህ እንዲህ የኢትዮጵያን ሕዝብና ታሪክ ፍጹም አሳፋሪ በሆነ መልኩ ጥላሸት የሚቀቡ የግንቦት 7 ደጋፊዎች እና አንዳንድ አባላቱ ህልማቸውም ሆነ ቅዠታቸው ምን እንደሆነ ግልጽ ስለሆነ በየድኅረ ገጹ ለሚጭሩት ነገር ሁሉ መልስ መስጠት ጊዜ ማጥፋት ነው። በነጻነት ትግል ስም ግን ቀጣዮቹ ወያኔዎች ለመሆን ማቆብቆባቸውን ግን መረዳት አያዳግትም። ለማንኛውም የሚማር አእምሮ ካላቸው ተቃውሟቸውንም ሆነ ነቀፌታቸውን ሥርዓት ባለው መልኩ ለማቅረብ ከአንተ የሙግት ሃሳብ አቀራረብ በመጠኑም ይማራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለእነዚህ ሰዎች በዝርዝር ምላሽ መስጠቱ ጊዜ ማባከን ብቻ ሳይሆን ወደወረዱበት አዘቅትም አብሮ ማቆልቆል ስለሚሆን “ግንቦት 7 ሆይ በየመንደሩ ያፈራሃቸውን እንደ አባይ በሬ ያልተገሩ ተሳዳቢ ‘ነጻ አውጪዎቻችንን’ ከሕዝብ ጋር ሳያጣሉህ በፊት ቢያንስ በሥነ-ምግባር አንጽ” ብሎ ማለፉ ሳይሻል አይቀርም።
በዝርዝር ወዳቀረብካቸው ትችቶችና የሙግት ሃሳብህ ከመግባቴ በፊት ለጽሑፍህ ከሰጠኸው ርዕስ ልነሳ። ከዛም በአግባቡ መልስ ለመስጠት ያመቸኝ ዘንድና አንዱን ነጥብ አንስቼ ሌላውን እንዳልተው ልክ አንተ ባቀረብከው ቅደም ተከተል መሰረት እኔም ምላሼን እሰጣለሁ። “የፈረደበት ግንቦት 7፤ የፈረደባት ኤርትራ” የሚለው ርዕስህ ለነዚህ ሁለት አካላት ያለህን የረዥም ጊዜ ቅርበትም ይሁን አዎንታዊ ምልከታ ለሚያውቅ ሰው ብዙም አይደንቅም። ይሁንና እንደ እኔ እምነት የፈረደበትስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እንጂ እነሱ አይደሉም። ከብዙ የአፈና እና የአገዛዝ ዘመን ቆይታም በኋላ ዛሬም ታሪክ እራሱን እየደገመ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የፍትሕ፣ የዲሞክራሲና የነጻነት ምኞትና ተስፋው ቂምና ጥላቻን ባረገዙና በዘረኝነት መርዝ በተበከሉ ገዢዎች፣ ‘ነጻ አውጪዎች’ እና ከጀርባ ባሉ አናቋሪዎች ወይም አጫፋሪዎች እጅ መውደቁ እጅግ ያሳዝናል። ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ አገር፤ ልጆቿ ዛሬም እርስ በርስ መስማማትና የአገዛዝ ሥርዓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ አቅቷቸው ከወያኔ እኩል ኢትዮጵያን ያደማና ለውርደትም የዳረጋት ሻቢያ ጉያ ስር መወሸቅንና ደጅ ጠኚዎች መሆንን እንደ አንድ አማራጭ ለመውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ውስጥ መሆናችን እጅግ ያሳፍራል። ስለዚህ እንደኔ እንደኔ ሊታዘንለት የሚገባውም ሆኑ የፈረደበት አገሩን፣ ክብሩን፣ የባህር በሩን እና ተስፋውንም ጭምር በጎጠኞችና በጽንፈኛ ‘ታጋዮች’ የተነጠቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ከወያኔ ጋር በፍቅር በቆየበት ዘመን ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት መጥፋትና ታፍኖ መሰወር በግንባር ቀደምነት ሊጠየቅ የሚጋባው እና ‘ለኢትዮጵያ የመቶ አመት የቤት ሥራ ሰጥቻታለው’ እያለ ሲያቅራራ ለነበረው ለሻቢያ ወይም በሱ ጉያ ስር የህዝብን ትግል ወስደው ለቀረቀሩት እንደ ግንቦት 7 ላሉ ኃይሎች አይደለም።
ይህን ካልኩኝ ዘንዳ በዝርዝር ወዳስቀመጥካቸው የሙግት ነጥቦችህ ልመለስ። የጽሑፍህን ይዘት በጥቅሉ እንዳየሁት ብዙ የአስተሳሰብ ግድፈት ብቻ ሳይሆን ጭብጦችንም (ሆነ ብለህ ባይሆንም እንኳን) አጣሞና አዛብቶ የመተርጎም አዝማሚያም አይቼበታለሁ። ለማንኛውም ወደ ዝርዝር ጉዳዮቹ ልግባ።
1. ‘ለሰብአዊ መብት መሟገት አመል ሆኖበት’ በሚል ስላቅ በሚመስል መልኩ ነገር ግን አዎንታዊ ብለህ በምታስበው መንገድ ያቀረብከው መደርደሪያ የጽሑፍህን ጠቅላላ ይዘትም ሆነ እስከ ማጠቃለያህ ድረስ ለዘለቅክበት ትችትና ደጋግመህ ለጠቃቀስካቸው አመለካከቶችህም ጭምር መነሻ መስሎ ስለታየኝ በእሱ ላይ አጠር ያለ ነገር ልበል። ይህ አገላለጽ ምንም እንኳን አንተ በአዎንታዊ መልኩ ብታቀርበውም ለእኔም ሆነ ለአንባቢዎች የሚሰጠው ትርጉም ተቃራኒውን ነው። ብዙ ጊዜ እንደ ወያኔ እና ሻቢያ ያሉ አንባገነናዊ ሥርዓቶች በሰብአዊ መብቶች አያያዛቸው ላይ ለሚቀርብባቸው ትችትና ወቀሳ ምላሽ የሚሰጡት በዚሁ መልኩ ነው። እነሱም አንተ በገለጽከው መልኩ፤ ነገር ግን አሉታዉ በሆነ ጎኑ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን በሆነ ባልሆነው የመጮህ ‘አመል’ ወይም ‘ሱስ’ የተጠናወታቸው አድርገው በመግለጽ ያንቋሽሿቸዋል። መልዕክታቸውም ባደባባይ እየገደሉም እኛ የፈጸምነው አንዳችም በደል ወይም የመብት ረገጣ ሳይኖር ነው ተሟጋቾቹ በባዶ ሜዳ የሚጮሁት የሚል የአይነ ደረቅ መከላከያ ነው። ኢሰመጉ የዚህ አይነቱ ዘለፋ አንዱ ሰለባ ነው። ይህ አይነቱን ነቀፌታ በእኔ ጽሑፎች ላይ ሃሳብ በሰጡት የግንቦት 7 ደጋፊዎችም ተንጸባርቋል። የእነዚህን ሰዎች ትችት ‘አወይ መመሳሰል’ (ከገዢዎቻችን ጋር ማለቴ ነው) በሚል ትዝብት አልፌዋለው። ይሁንና የአንተን ከገዢዎቻችን አገላለጽ ለየት የሚያደርገውና ምናልባትም የከፋ የሆነው ግንቦት 7ም ሆነ የኤርትራ መንግሥት የሚነቀፉበትን ተግባር አልተፈጸሙም ከሚል መነሻ ሳይሆን ድርጊቱን ቢፈጽሙም ትክክል ናቸው፤ ትክክል ባይሆኑም እንኳን ሊጠየቁ አይገባም ወይም በገለጽካቸው ምክንያቶች በዝምታ ልናልፈው እንጂ ልንወቅሳቸው አይገባም የሚል ነው። ባጭሩ ‘አመል’ ሆኖብኽ ነው በማይጮኽበት ጉዳይ ለሙግት የቆምከው የሚለው ምልከታህ መሰረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ግድፈት የሚታይበት ሆኖ ነው ያገኘሁት። ‘አመል ሆኖብህ’ የሚለውም አገላለጽ በጽሑፌ ላይ ደረሱ ያልኳቸውን በደሎች ለማቃለልና የተበዳዮቹንም አቤቱታ ለማጣጣል ሆነ ብለህ የተጠቀምክበት መንገድም ሆኖ ነው ያገኘሁት። ለአመል ተብሎ የሚደረግ የሰብአዊ መብቶች ሙግት ቧልት ስለሆነ አሉታዊ ነገርም የለውም። የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታ በማስረጃና በእውነት ላይ እስከተመረኮዘ ድረስ ከልብ የመነጨ ሙግት እንጂ አንድን ወገን ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም ወይም ለአመል ሲባል የሚፈጸም አይደለም። ተበድለናል የሚሉት ወገኖች ለቅሶ የበለጠ እውነቱን እንዳረጋግጥና በቂ ማስረጃዎችንም እንዳሰባስብ በጎ እልህ ውስጥ ይከተኛል እንጂ አንተ እንዳልከው እውነታውን በጥሞና እንዳልመረምርና ግራ ቀኙንም እንዳላይ አይጋርደኝም።
2. እውነት ነው እኔና ተክሌ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እንተዋወቃለን። ጽሑፌን ያነበቡ የግንቦት 7 ደጋፊዎች ከሥነ-ምግባርም ጭምር በራቀ መልኩ ለሰጡዋቸው ነቀፌታዎች ለያንዳንዱ ምላሽ አለሰጠሁም። በእንዲህ ያሉ ፍሬ ከርስኪ ጎዳዮችም ጊዜዬን አላጠፋም። ሆኖም ስለኔ ማንነት ለሰጠኸው ምስክርነት አመሰግናለሁ።
3. ኦሬንጅና አፕልን የመደባለቅ ያህል አብረው የማይነጻጸሩ ነገሮችን በማነጻጸር የመገናኛ ብዙሃንን፣ ግንቦት 7ን፣ ኢሳትን እና የኤርትራ መንግሥትን ተችተሃል፤ ይህም ስህተት ነው በሚል ወዳቀረብከው ዝርዝር ጉድያ ልምጣ። የምንወያይበት ትልቁ ፍሬ ጉዳይም እሱ ቢሆንም በመካከላችን ያለው የሃሳብ ልዩነት ግን እጅግ ሰፊ ነው። በዚህ ዙሪያ ያነሳሃቸው ፍሬ ነገሮች ባጭሩ ሦስት ናቸው። የመጀመሪያው ለነጻነት ትግል ብሎ ወዶና ፈቅዶ ጫካ በገባ ሰውና ኑሮን ለማሸነፍ በየአረብ አገሩ ከባርነት ባልተናነሰ መልኩ ተሰዶ እየተሰቃየ ባለው የህብረተሰብ ክፍል መካከል ያለው ልዩነት አልገባህም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሽምቅ ውጊያ ለማካሄድ በፈቃዳቸው ወደ ጫካ የገቡ ሰዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ለአላማዎቻቸው ሲሉ ትተው የሸፈቱ ሰዎች ስለሆኑና የዘመቱትም ለመግደል ወይም ለመሞት በመቁረጥ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች በየትኛውም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ቢገኙ እኳን የሰብአዊ መብት ጥያቄ ሊነሳ አይችልምና ያለቦታው ነው ሙግት የገጠምከው የሚል ነው። ሦስተኛው ነጥብህ ግንቦት 7 በትጥቅ ትግል የሚያምን እና በተግባር ላይ ያለ ድርጅት በመሆኑ፤ እንዲሁም የኤርትራ መንግስ ለኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች ጥላ ከለላ በመሆኑ ሊመሰገኑ እንጂ ሊወቀሱ አይገባም የሚል ነው። ካልተሳሳትኩ የጽሁፍህ መልዕክት ከነዚህ ሦስት ነጥቦች የዘለለ አይደለም። እያንዳንዱን በየተራ ልመልስ።
4. እርግጥ ነው ወደ ኤርትራ ለትግል በሄዱትና ወደ አረብ አገሮች በተሰደዱት ወገኖቻችን መካክል ያለው ልዩነት አንተም እንዳስቀመጥከው ግልጽ ነው። ይሁንና ሁሉም አገራቸውን ለቀው የወጡበት ምክንያት ግን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ሁሉም በአገራቸው እንደ ሰው ልጅ ተከብረው ሊኖሩበት የሚያስችል የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ነጻነትና መፈናፈኛ መታጣት ነው። ሁሉም የወያኔ የአፈና ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነት ቢኖርና ሁሉም በሃገሩ እንደልቡ ሰርቶና ሃብት አፍርቶ የሚኖርበት አመቺ ሁኔታ ቢኖር ኖሮ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ወዳለችው ኤርትራም ሆነ ወደሌሎች አረብ አገሮች ኢትዮጵያዊያን ነፍጥም ሊያነሱ ይሁን በባርነት ሊያገለግሉ አይሰደዱም ነበር። እኔ እና አንተም ብንሆን ኑሮዋችንን በአውሮፓና ካናዳ ባላደረግን ነበር። የእዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ አገሪቷ ያለችበት አስከፊ የሆነ ሁኔታ ነው። በመጀመሪያ እራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ነጻ ለማውጣት በመወሰን ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ‘ዱር ቤተ’ ብለው ለዘመቱት ወገኖቼ የሄዱበትን መንገድ ፈጽሞ ባልደግፈውም እንኳን ነፃነታቸውን ለማግኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ። ዋናው ቁምነገር ግን ኢትዮጵያዊያን በማናቸውም ምክንያት ይሰደዱ፣ በየትኛውም አገር ይገኙ፣ ለየትኛውም አገራዊ ተልዕኮ ይሰማሩ ሕይወታቸው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ወድቆና ቀን ጨልሞባቸው ለወገን የድረሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ ‘አይ እናንተ ወዳችውና ፈቅዳችው ለነጻነት ትግል የሄዳችው ሰዎች ስለሆናቸው ሻቢያም ሆኑ ግንቦት 7 ያሻችውን ቢያደርጉዋችሁ መብታቸው ነውና የበላችሁ’ የሚል ምላሽ ኃላፊነት ከሚሰማው ወገን የሚጠበቅ አይደለም። እንኳን መደብደብ ቢገሉዋቸውም እንኳን ልናዝንላቸው አይገባም የሚል ጭካኔ የተሞላበት አቋምህ አስገርሞኛል፤ አሳዝኖኛልም። እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቻችንም ሆነ አንዳንዶቹ የሞቱት ከወያኔ ጋር ፍልሚያ ሲያደርጉና በጦር አውድማ ላይ ቢሆን ኖሮ አንድ ወታደር በጦርነት ውስጥ ለምን ተገደለ ብሎ የሚጠይቅ ቂል ሰው ያለ አይመስለኝም። እኔ ያነሳሁት ጭብጥና የእነዚኽ ወገኖቻችንም ጥያቄ ከዚህ አንተ አጣመህ ካቀረብከው ታሪክ ጋር እጅግ የተለየ ነው። ጉዳዩንም ለማጣጣል በማሰብ አንተ እንዳቀረብከው ለቅንጦት የቀረቡ የመብቶች ይሟሉልን ጥያቄዎች አይደሉም። እኔ የሳኡዲና የኤርትራውን ክስተቶች ያነጻጸርኩበት እና አንተ የተረዳህበት ወይም ልትረዳ የፈለክበት መንገድ ፍጹም ለየቅል ነው። ትልቁ የአስተሳሰብ ስህተትህም የሚጀምረው ከዛ ላይ ነው።
5. በጽሑፌ በየትኛውም ክፍል በኤርትራ ውስጥ በእስር የሚገኙት የነጻነት ታጋዮች ሳኡዲ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ሠርቶ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት፣ ሃሳባቸውን ባደባባይ የመግለጽ፣ እንደፈለጉ የመንቀሳቀስና ሌሎች ላንተ የቅንጦት የሚመስሉህ መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው ሊከበሩላቸው ይገባል የሚል ሃሳብም ሆነ ክርክር አላቀረብኩም። እኔ እየተሟገትኩ ያለሁት በግፍ ታስረው የግፍ ተግባር እየተፈጸመባቸ ስላሉ ሰዎች ነው። የመብት ጥያቄ የሚነሳው እንደ ጉዳዩ ባህሪ እና እንደምትገኝበትም ስፍራ ነው። አንድን የሕግ እስረኛም ብትወስድ በመታሰሩ ብቻ አብዛኛዎቹን መብቶቹንና ነጻነቶቹን ይነፈጋል። ያ የቅጣቱ ዋነኛ አላማም ነው። ይህ ማለት ግን ለሰው ልጆች የሚገቡ መሠረታዊ መብቶችን ሁሉ ተነፍጎ ከሰው ተራ እንዲወጣ ይደረጋል ማለት አይደልም። በቂ ምግብ፣ ህክምና፣ መጠለያ እና ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን የማግኘት መብት አለው። ይህ መብት በቃሊትም ላሉ ይሁን በአስመራ ማጎሪያ ቤቶች አመታትን እያስቆጠሩ ላሉት ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾችም ባልተከበረብት ሁኔታ በጦርነት ላይ ላለ ወታደር ወይም ሽምቅ ተዋጊ ይከበር ብሎ መጠየቅ ላንተ፤ ይገደሉ ብለህ ለፈረድክባቸው ሰዎች ቅንጦት መስሎ ሊታይህ ይችላል። የእነዚህ መብቶች አለመከብር በአዲስ አበባና በአስመራ ያሉትን ግፈኛና አንባገነናዊ ሥርዓቶች የባህሪ አንድነትና መጥፎነት ያሳያል እንጂ ከልቡ ለሰዎች መብት ለሚጨነቅ ሰው የቅንጦት ጥያቄዎች አይደሉም።
6. ለነገሩ ለእዚህ አይነቱ ጭካኔ የተሞላበት ፍርድ የዳረገህ በአዋጅ በታወቀ የጦርነት ጊዜም ይሁን በሽምቅ ውጊያ ወቅት የመንግስትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ኃይሎች (Non-state actors) (አማጺያን፣ የተደራጁ ሽፍቶች ወይም ሽምቅ ተዋጊዎች) በአለም አቀፍ ሕጎች ስለተጣለባቸው ኃላፊነትም ሆነ የተጠያቂነት ግዴታ ያለህ ግንዛቤ ወይ የተሳሳተ ነው ወይም በኤትራና በግንቦት 7 ፍቅር ታውሯል። ይህ ካልሆን ግን እንዳንተ ሕግ የተማረ ሰው ይህን ማንም ሊስተው የማይችለውን እውነታ ይገድፋል ብሎ ማሰብ ይቸግራል። ለነገሩ በጽሑፍህ ተ.ቁ. 6 ላይ የሄግንና የጄኒቫን ስምምነቶችና በዚያ ዙሪያ የተጻፉ ትንታኔዎችን ባነብ እንደሚጠቅመኝ መክረኸኛል። እንዲህ ያለ ምክር የሚሰጥ ሰው ከላይ የተጠቀስትን ያፈጠጡ ግድፈት ይፈጽማል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እንደው በግርድፉ ከጠቀስካቸው አለም አቀፍ ድንጋጌዎች ውስጥ Protocol I additional to the Geneva Conventions, 1977
(http://www.icrc.org/applic/ihl/ihl.nsf/Treaty.xsp?action=openDocument&documentId=AA0C5BCBAB5C4A85C12563CD002D6D09) እንዲሁም አራቱንም የ1949 የጄኒቫ ስምምነቶች (http://www.icrc.org/eng/war-and-law/treaties-customary-law/geneva-conventions/) ብንመለከት በየትኛውም ሁኔታ መሳሪያቸውን አስረክበው በቁጥጥር ስር በዋሉ እስረኞች ላይ ድብደባና ማሰቃየት፣ ያለ ፍርድ (በወታደራዊ ፍርድ ቤት) ግድያ፣ የሕክምና እና የምግብ አቅርቦትን መንፈግን፣ እንዲሁም በባርነት የጉልበት ሥራን ማሰራትና ሌሎች ለሰው ልጅ የማይገቡ አያያዞች እንዲፈጸምቻቸው የሚፈቅድ አንድም የሕግ ማእቀፍ የለም።
7. ብዙ ጊዜ በአንተም ተደጋግሞ እንደገለጽውና የግንቦት 7 ደጋፊዎችም እንደሚሉት የሽምቅ ውጊያ ውስጥ የገባን አማጺ ኃይል የሚዳኝ ወይም በሰብአዊ ጉዳዮች ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ የለም፤ ያሻውን ማድረግ ይችላል የሚለው መከራከሪያ ከወዴት እንደመጣ ሊገባኝ አይችልም። እንደዛማ ቢሆን የአለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት የአፍሪቃ አማጺያን መሪዎች ባልሞሉት ነበር። እነዚህ ሕጎች በመንግሥታት ስምምነቶች የጸደቁ ቢሆንም ተፈጻሚነታቸው ግን በመንግሥታት ላይ ብቻ ሳይሆን ነፍጥ አንግበው በተደራጁና በአማጺነት እውቅና ባገኙ ኃይሎች ላይ ሁሉ እንደየአግባቡ ተፈጻሚ ይሆናሉ። በተለይም መሳሪያቸውን ጥለው በቁጥጥር ስር የዋሉ ምርኮኞችና ወታደራዊ እስረኞች ስለሚደረግላቸው የሕግ ጥበቃና እንክብካቤ በግልጽ ተደንግጓል (http://www.icrc.org/eng/war-and-law/protected-persons/prisoners-war/overview-detainees-protected-persons.htm) ። መንግሥትም ይሁን አማጺ ቡድን እንኳን የራሱን ሠራዊት አባላት ይቅርና የጠላት ወታደሮችንም በማረከ ጊዜ አንተ እንዳልከው ቢሻው ሊረሽን፣ ቢሻው አስሮ እንዲያሰቃይ፣ ቢሻው በባርነት እንዲያቆያቸው የሚፈቅድ አለም አቀፋዊ ድንጋጌ የለም። በሰላም ጊዜም ይሁን በጦርነት ወቅት ለነዚህ እስረኞችና ምርኮኞች የተሰጡት የሕግ ጥበቃዎች አንተ ባስቀመጥከው መልኩ የሚሸራረፉ ወይም እንደ ሁኔታው የሚቀያየሩ አይደሉም። በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ እነዚህ ታሳሪዎች ከላይ የጠቀስኳቸው መብቶች አሏቸው። ወንድሜ ተክሌ ከጋርዮሽ ዘመን ከወጣን ብዙ እርቀናልና እንዲህ ያለው ነፍጥ ያነገቡ ብድኖችን ከሕግ በላይ አድርጎ የማንገሱ አዝማሚያ መዘዙ ብዙ እንደሆነ ልትረዳው ይገባል። ከዚህ ደግሞ ለመማር ሕጉን ትተነው ያለፉ ታሪኮቻችንን እንኳን በቅጥ ማጤን በቂ ነው።
8. ከላይ ከተነሳው የታጠቁ ቡድኖች የሕግ ኃላፊነት አንጻር ግንቦት 7 ያለበትን አቋም በመጠኑ መቃኘት ተገቢ ይመስለኛል። በእኔ እይታ ግንቦት 7 አንተም ሆንክ ደጋፊዎቹና አባላቱ እንደሚሉት እንደ አንድ በትጥቅ ትግል ውስጥ እንደተሰማራ አማጺ ኃይል ተደርጎ መውሰዱ የድርጅቱን አቋም የማይመጥን የተጋነነ ገለጻ ነው። ግንቦት 7 አማጺ ለመሆን ምኞቱ ነው እንጂ ያለው በዛ አቋም ላይ ያለ ድርጅት አይደለም። የግንቦት ሰባት ምሽግ አስመራና ኢሳት ቢሆኑም፤ ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ የሚለውን አገራዊ አባባል በደንብ አጢኖ ይመስላል ከአስመራ ይልቅ ግዳጅ እየጣለ ያለው የድርጅቱ ልሳን በሆነው ኢሳት ነው። ኢሳት ግንቦት 7ን በሚገልጽበት አኳኋን ቢሆን ድርጅቱ ያለው ቀጣዩን ምርጫ ከወያኔ ጋር ሳይሆን ከግንቦት 7 ጋር ነበር የምናሳልፈው። ወያኔ የሚሰራቸው የአኬል ዳማ እና ጂሃዳዊ አረካት ፊልሞች አልበቃ ብሎ ከዚህ ክሽፈት ልምድ የወሰደው ኢሳት በቅርቡ በብዙ ክፍሉች እየደጋገመ በኢሳት ያቀረበው የ’ሚሊኒየም ኦፕሬሽን’ የግድያ ሙከራ ፊልም ጥሩ ማጣቀሻ ነው። እንኳን ለፍልሚያ ለልምምድም እንኳ ጥይት ተኩሰው የሚያውቁ የማይመስሉት የግንቦት 7ን ኃይሎች ከሌሎች የአፍሪቃም ሆኑ የላቲን አሜሪካ አገሮች አማጺ ታጣቂዎች እኩል ማስቀመጡ አጉል መንጠራራት ነው የሚሆነው። ከዚህ ግንቦት 7ን ከካብክበት ማማ ላይ ሆነህ የሰጠኽው አስተያየትም በእኔ እይታ ፈር የሳተ ነው። ይህውም ግንቦት 7ን የተደራጅና የራሱ ውታደራዊ የዳኝነት ሕግና ስልት እንዳለው አድርገህ በማስቀመጥ ተበዳዮቹ በዛ እንደሚዳኙና ፍትሕ እንደሚያገኙ አድርገህ ያስቀመጥከውን ሃሳብ የሳምንቱ ምርጥ ቀልድ አድርጌ ወስጄዋለሁ። ያም ሆኖ ግን ግንቦት 7ም ሆኑ የኤርትራ መንግሥት መሬት ላይ በሌለ የነጻነት ትግል ስም የኢትዮጵያን ወጣቶች እየመለመሉ ወስደው የሻቢያ ቂም መወጣጫ ማድረጋቸው በታሪክም ይሁን በሕግ ከመጠየቅ አያድንም።
9. ሌላው አስገራሚውና አስቂኝ ጉዳይ ሆኖ ያገኘሁት የሻቢያንና የወያኔን የድል ጉዞ የቃኘህበት መንገድ ነው። እነዚህ ኃይሎች በትግላቸው ወቅት በራሳቸው አባላትም ላይ ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ግፍና በደል በታሪክም ሆነ በሕግ ይቅር የማያስብል ነው። የትግሉ መሥራቾች የሆኑትና ድርጅቶቹን በጊዜ ጥለው የወጡት አባላቶቻቸው ሳይቀሩ ድርጅቶቹ ከጦር ውድማ ውጪ በሰበብ አስባቡ ያጠፉት የሰው ሕይወት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር እንደሆነ እየመሰከሩ ነው። ይሁንና የአለማችን መጥፎ የፖለቲካ አቅጣጫ እድል ሰጥቷቸው ለፈጸሙት በሰው ዘር ላይ የተነጣጠረ ወንጀል (crime against humanity) ሊጠየቁና በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ሲገባ በለስ ቀንቷቸው በእነ አሜሪካና እንግሊዝ አጃቢነት መንግስታት ለመሆን በቅተዋል። ተጋዳላይ እያሉ የጀመሩትንም የወንጀል ተግባራት ‘ያዲያቆነ ሴጣን ሳያቀስ አይለቅም’ አይነት መንግስታት ሆነውም ቀጥለዋል። እንግዲህ ፍርደ ገምድል የሆነው የአለማችን ፖለቲካ ከወያኔ እና ከሻቢያ ያነሰ ወንጀል የፈጸሙ ሌሎች የአፍሪቃ አማጺያንን ከገቡበት ጉድጓድ እያወጣ ከፍርድ አደባባይ ሲያቆም የእኛዎቹን ደግሞ ‘ተራማጅ መሪዎች’ በሚል እያሞካሸ ከነተሸከሙት ወንጀል እና ሃጢያት በላያችን ላይ አንግሷቸዋል። ዛሬም ባደባባይ ሕዝባቸውን እየረሸኑና እያሰቃዩም እንዲቀጥሉ ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸዋል። እንግዲህ ወንድሜ ተክሌ ወያኔና ሻቢያ የገዛ ሕዝባቸውን እየረሸኑና እያስወገዱ የመጡበት መንገድ ወደ ሥልጣን ለመወጣጣት አዋጪ መንገድ ስለሆነ ‘የመረሸንና የማስወገድ’ ሕጋዊ ወይም ፖለቲካዊ ፈቃድ ለግቦት 7 እና ለኤርትራ መንግስት ይሰጥ የሚል ሙግት ነው እያቀረብክ ያለኸው። አትታዘበኝና እውነት እውነት እልሃለው እጅግ የወረደ እና በብዙ ሰዎች ዘንድም ትዝብት ውስጥ የሚከትህን ሃሳብ ነው፤ አውቀኸው ይሁን ሳታውቅ የገለጽከውና እስኪ ቁጭ ብለህ በጥሞና የተናገርከውን እንደገና መርምረው። አንድ ሰው ሲገደል እኮ እንደው እንደ ልጆች የቃቃ ጨዋታ ወይም እንደ ሆሊውድ ፊልፎች አይደልም። አንድ ሰው ያለ አግባብ በግፍ ሲገደል አብሮት የሚሞተው ፍትህ ነው። አንድ ሰው ያለ አግባብ ሲገደል የሚያዝነውና የሚጎዳው አገርና ህዝብ ነው። የሚበተን ቤተሰብ፣ ልቡ በሃዘን የሚሰበር ወገን እና በተለይም በግፍ ፈጻሚዎቹ ላይ ቂም የሚቋጥር ቀሪ ወገን አለ። ለማንኛውም አንድ በአንተና በእኔ እድሜ ያለ፣ ዘመናዊ ትምህርትን የዋጀና በተለይም የሕግ ትምህርትን የቀሰመ፣ የወያኔን እና ላንተ ባይዋጥልህም የሻቢያን ክፉ ተግባራት ለመታዘብ የቻለ ሰው እንዲህ ያለ ፍርደ ገምድል አስተሳሰብ ይይዛል ብሎ ማሰብ ይቸግራል።
10. በዝርዝር ካነሳሃቸው ሌሎች ሃሳቦች መካከል መልስ በሚያሻቸው አንድ፤ ሁለት ነጥቦች ላይ ሃሳብ ልሰንዝርና ጽሑፌን ልቋጭ። በግንቦት 7 ተበደልን ያሉት ሰዎችን በተመለከተ ቁርጠኝነት የሌላቸው እና በቅጡ ስልጠና ያላገኙ ደካማ ሰዎች አድርገኽ ከዝልፊያ ባልተናነሰ የሰነዘርከውም ሃሳብ ለትዝብት የሚዳርግህ ነው። በመጀመሪያ እኔም ሆንኩ አንተ የአገዛዝ ሥርዓቱን በትር ፈርተን ከመሸግንበት አውሮፓና ካናዳ ሆነን የነኝኽህን ወገኖች ጥንካሬና ቁርጠኝነት ለመፈተሽ አቅም አለን ብዮ አላስብም። ያሉበትንም መከራ እነሱ ስለሆኑ የሚያውቁት ልፍስፍሶች ናችሁ እያሉ ማንጓጠጡ ተገቢ አይመስለኝም። የእነዚህ ሰዎች ቁርጠኝነት የታየው ወደ አስመራ ግንቦት 7ን አምነው ለመሄድ የወሰኑ ዕለት ነው። ይሁንና እነዚህ ሰዎች በአካል ተገኝተው ያዩትና የታዘቡት ግንቦት 7 በኢሳትና በሌሎች ሚዲያዎች እራሱን አገዝፎና አሳብጦ ያቀረበበት መንገድ በተጨባጭ ድርጅቱ ካለበት ሁኔታ ጋር የማይጣጣም መሆኑ አስደንጋጭ እንደሆነባቸው ነው። ከንግግራቸው የምንረዳውም፤ እውነታውም ይኼው ነው። በድርጅቱና በበጎ ፈቃድ ዘማቾቹም መካከል የተፈጠረው አለመግባበት መንስዔው ይኼው ነው። ወንድሜ ተክሌ፤ ታዲያ ግንቦት 7ን በጥሩ ሁኔታ እንደተደራጀና እንደሚወራለትም በጥሩ የትግል አቋም ላይ እንዳለ አስመስለህ በማቅረብ የእነዚህን ወገኖች ጥያቄ ልፍስፍስና አቋመ ቢስነት እንደሆነ አድርገህ ማቅረብህ አጀብ የሚያሰኝ ነው።
11. ለነገሩ በኢሳትና በሌሎች ሚዲያዎች ስለግንቦት 7 ፍጹም የተሳሳተ ገጽታ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለመፍጠር የተሰራውን ፕሮፓጋንዳ ያህል ወያኔም በአገሪቱ ውስጥ ያሉና ስጋት የሚሆኑበትን ግለሰቦችና ቡድኖች በቀላሉ ለማስወገድ ሲል ግንቦት 7ን እና ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችን ሽብርተኛ ብሎ መሰየሙ ሌላው ድርጅቱ እራሱን በአየር እንደተሞላ ፊኛ እንዲያሳብጥና አየር ላይ እንዲንሳፈፍ ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል። ይችን ‘ሽብርተኛ’ ተብሎ የመሰያየሟን ካርድ ሁለቱም (ወያኔ እና ግንቦት 7) ሊያተርፉባት ሞክረዋል። ወያኔ ሰላማዊ ተቀናቃኞቹን በቀላሉ ሽብርተኞች እያለ ለማጥመድና ለማስወገድ (በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና ሌሎች ወገኖችም ጉዳይ ሊጠቀስ ይችላል)፤ ግንቦት 7 ደግሞ ጠንካራ ተቀናቃኝ እና የወያኔ ስጋት ስለሆንኩ ነው ሽብርተኛ የተባልኩት፣ ወያኔ በእኔ መኖር ተርበርብዷል፣ እንቅልፍ አጥቷል ስለዚህ የአርበኝነት ቦድ (እንደ አባይ ቦንድ መሆኑ ነው) እየገዛችሁ ብትደግፉኝ ወያኔን በስድስት ወር ጉሮሮውን አንቄ አወርዳለሁ እያለ የአመታት እድሜን ለማግኘት ችሏል። በእንዲህ ያለው የፖለቲካ ቁማር የሚከስረውም ሆነ ተጎጂው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውና ወያኔም ሆኑ ግንቦት 7ዎችን ‘ሃይ’ ሊላቸው ይገባል።
ማጠቃለያ
የአቶ ተክለሚካሄልን ሙግት ሳይውል ሳያድር ነጥብ በነጥብ ለመመልስ ብዮ ጽሑፌን አንዛዝቼዋለሁና በትእግስት ላነበባችሁት ሁሉ ምስጋናዬ ይድረስ። በግፈኞች እጅ ተይዘውና በስውር ታስረው ለሚማቅቁ ወገኖቻችን ድምጻችንን ለማሰማት ሰዋዊ ብቻ ሳይሆን ወገናዊ ኃላፊነትም አለብን። የግፍን ተግባር ለመቃወም የፈጻሚዎቹ ማንነትም ሆነ የተፈጸመባቸው ሰዎች ምንነት መደራደሪያ ሊሆን አይችልም። የግፍና የጭካኔ ተግባር በማንም የፈጸማ በማን፣ በየትም ስፍራ የፈጸም ያው ግፍ ነው። ወያኔ ስፈጽመው ወንጀልና ግፍ፤ ሻቢያና ግንቦት 7 ሲፈጽሙት ሕጋዊ ወይም ቅዱስ ተግባር የሆነ የመብት እረገጣ የለም። ሁሉም ግፈኞች ነው የሚሆኑት የሚሆኑት።
ግፈኞችን በማውገዝ ለግፉዋን መብት መከበር በጋራ እንቁም!
በቸር እንሰንብት።

No comments:

Post a Comment