ቋሚ ሲኖዶሱ ፓትርያርኩን ያስጠነቀቀው፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ሳምንታዊ ስብሰባውን ባካሔደበት ወቅት ነው፡፡ የቤተ ክህነቱ የፋክትምንጮች እንደተናገሩት፣ የማስጠንቀቂያው መንሥኤ÷ አቡነ ማትያስ ምክራቸውን ለሥልጣነ ፕትርክናቸው አይመጥኑም ከተባሉ አማሳኝ ግለሰቦች እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ክብርና ነፃነት በመጋፋት ከሚወቀሱ አፅራረ ሃይማኖት አካላት ጋራ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና ልዕልና የሚፃረር ተግባር በየጊዜው መፈጸማቸው የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት ክፉኛ በማሳሰቡ ነው፡፡
- ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾነው ቋሚ ሲኖዶስ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየተወሰኑ የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊነት እንዲከታተል ካለበት ሓላፊነትና አሠራር ጋራ የማይጣጣሙ የፓትርያርኩ የአፈጻጸም አካሔዶችና አቋሞች መበራከታቸው፤
- ቋሚ ሲኖዶሱ ሳይወስንና የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሳያውቀው የጽ/ቤት ሓላፊያቸውን አቶ ታምሩ አበበን ያለሞያቸው ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአካዳሚክ ምክትል ዲን አድርገው በማዘዋወር፣ በቦታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ነፃነት ከሚዳፈሩ ባለሥልጣናት ጋራ በሙሉ አቅማቸው በመሥራት የሚታወቁትን የአማሳኞች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን መተካታቸው፤
- ከፍተኛ ገቢና የአገልግሎት አቅም ባላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት የአማሳኞችን የምዝበራ ሰንሰለት እያጋለጡ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመዋጋት፣ ካህኑንና ምእመኑን አንድ አድርጎ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ አጋር በመኾን የተመሰገኑ አለቆች፣ ፓትርያርኩ ከአማሳኞች ጋራ እየመከሩ በሚያስተላልፉት ቀጥተኛ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸው፤
- አገልጋዩ እና ምእመኑ በአንድነት የውጤታማና ምስጉን አስተዳዳሪዎችን ያለአግባብ ከሓላፊነት መነሣት በተመለከተ ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ በቋሚ ሲኖዶሱ መመሪያ መሠረት አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥባቸው የፓትርያርኩ የዝውውር ውሳኔ ተፈጻሚ መኾኑና የመሳሰሉት ጉዳዮች፤
የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ከፓትርያርኩ ጋራ በከፍተኛ ደረጃ የተጠያየቁባቸውና ፓትርያርኩን ያስጠነቀቁባቸው ዐበይት ነጥቦች እንደነበሩ ምንጮቹ አስታውቀዋል፡፡
በሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው ላይ ለፓትርያርኩ ጥያቄ ያቀረቡት የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ፣ ሳይገባቸውና ደረጃቸውን ሳይጠብቁ ‹ፓትርያርኩን ያማክራሉ› ያሏቸውን ቀንደኛ አማሳኞች እነኃይሌ ኣብርሃን በስም በመጥቀስ፣ ‹‹ለመኾኑ ከማን ጋራ ነው የሚሠሩት? ማንን ነው የሚሰሙት? ምክርዎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሚጎዱና ከሚያጠፉ ስማቸውም በመልካም ከማይነሣና ምግባር ከጎደላቸው ሰዎች ጋራ ነው፤ ከእነርሱ እየመከሩ አብረውን የወሰኑትን ውሳኔ ይገለብጣሉ፤ ዓላማዎ ምንድን ነው?›› በሚል ጠንክረው እንደጠየቋቸው በምንጮቹ መረጃ ተመልክቷል፡፡
ፓትርያርኩ በሰብሳቢነት በሚመሩት የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ አብረው የወሰኑበትን ጉዳይ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በስም ከተጠቀሱት ቀንደኛ አማሳኞችና አድርባይ ፖለቲከኞች ጋራ እየመከሩ በአፈጻጸም ስለሚገለብጡበት አካሔድ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የኔ ቃልና የነሱ ቃል አንድ ስለኾነ፣ የሚያመጡት ሐሳብ ስለሚመቸኝ›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተዘግቧል፤ አብረዋቸው የሚሠሩትም ‹‹ዓላማዬን ስለሚያስፈጽሙልኝ ነው›› በማለት አቋማቸውን ለመከላከል መሞከራቸው ተዘግቧል፡፡
የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በበኩላቸው፣ ‹‹አገልጋዩንና ምእመኑን ከሚዘርፉና ከሚያሠቃዩ ጋራ ምን ዓይነት ዓላማ ሊኖርዎት ይችላል? አገልጋዩና ምእመኑ የሚዘረፍበትና የሚሠቃይበት ዓላማ ሊኖርዎት አይችልም፤›› የሚል ጠንካራ ምላሽ በመስጠት ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሚጎዳ ፀረ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አካሔድ እንዲታረሙ አስጠንቅቀዋቸዋል፤ በዚኽ ዓይነቱ ድርጊታቸው የሚቀጥሉ ከኾነ ደግሞ ቋሚ ሲኖዶሱ ከእርሳቸው ጋራ የመሥራትን አስፈላጊነት እንደሚያጤነው፣ አስፈላጊም ከኾነ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌዎች መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ ለመጥራት እንደሚገደድ በግልጽ እንደተነገራቸው ተገልጧል፡፡
በቋሚ ሲኖዶሱ ያልተለመደ ጽናትና ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ፓትርያርኩ በአካላዊ ኹኔታዎች የሚገለጽ ከፍተኛ ድንጋጤ ይታይባቸው እንደነበርና በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ለመከላከል የሞከሩት ፀረ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አቋማቸው ስሕተት መኾኑን በማሔስ በፍጥነት የመሰብሰብ እርማት እንዳደረጉ ተመልክቷል፡፡ ‹‹ከእኛ[ቋሚ ሲኖዶስ] ጋራ ይሠራሉ ወይስ አይሠሩም?›› ለሚለው ርምጃ አዘል (consequential) መጠይቅም አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ተነግሯል፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያንን ሥራ ይጎዳል በሚል እንጂ ተመራጩ ነገር ከእሳቸው[ፓትርያርኩ] ጋራ መሥራትን ማቆም ነበር፤›› ማለታቸው የተጠቀሰላቸው አንድ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል፣ ፓትርያርኩ በየአጋጣሚው በብፁዓን አባቶችና በቅርብ ወዳጆቻቸው* ጭምር ቢመከሩም ለመታረም ስላልፈቀዱና ከሚገኙበት አሳሳቢ የአሠራር ኹኔታ አንፃር ቋሚ ሲኖዶሱ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አግባብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ ለመጥራት የሚገደድበት ደረጃ ከመድረስም በላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴም አድርጎ እንደነበር አረጋግጠው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
አቡነ ማትያስ በቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በተጠየቁባቸው ጉዳዮች ስሕተት መፈጸማቸውን አምነው መቀበላቸውና ‹‹ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ ይሠራሉ ወይስ አይሠሩም?›› በሚል በቁርጥ ተጠይቀውበታል ለተባለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መስጠታቸው፣ በቃለ ጉባኤውም ላይ መፈረማቸው የምልዓተ ጉባኤውን የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ እንቅስቃሴ ለጊዜው እንደገታው የዜናው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልናና የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅሞች ከመሰል የውስጥ አማሳኞች ፈተናና የአፅራረ ሃይማኖት ተግዳሮቶች የማስጠበቅ ጥንቃቄውን በተተኪ ተለዋጭ አባላቱም አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አስታውቀዋል፡፡
ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጋፋት ስሕተት መፈጸማቸውን አምነው ከተቀበሏቸው ርምጃዎቻቸው መካከል፣ ብልሹ አሠራርንና ሙስናን በመዋጋት የአገልጋዩና ምእመኑ ከፍተኛ ተቀባይነት ማትረፋቸው የሚነገርላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ ዝውውር ዋነኛው ነበር ተብሏል፡፡
ለአብነት ያኽል ከወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አራት ተለዋጭ አባላት አንዱ የኾኑት የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ የፓትርያርኩ አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት በተከበረበት የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ምሽት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ባዘጋጀው የራት መርሐ ግብር ላይ ለአባ ማትያስ የሰጧቸው ወንድማዊ ምክር የሚከተለው ነበር፡-
‹‹ቅዱስነታቸው በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ኤጲስ ቆጶስነት ከተሾምነው 13 አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ ከመካከላችን ወንድማችን ለዚኽ ክብር በመብቃታቸው ኹላችንም ደስ ይለናል፤ በተለይ እኔ ካለኝ ቅርበት ወንድምም ስለኾንኩ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኹሌም አዲስ ነው፤ የሚመከረውም በእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ፓትርያርክም ቢኾኑ ወንድም ነዎትና እንግዲኽ በእግዚአብሔር ቃል ልምከርዎ፡፡
አንድ ፓትርያርክ ከማን ጋራ ነው ምክሩ? ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ሲሰጥዎ ዐዲስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ዐዲስ የጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሰጥዎታል፡፡ መምከር ያለብዎ ከእነርሱ ጋራ ነበር፤ ከዚያ ካለፈ ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ ነው፤ አስፈላጊም ከኾነ ጠቅላላ ጉባኤው ይሰበሰባል፡፡ እርስዎ ግን ወርደው ከማን ጋራ ነው እየተማከሩ ያሉ? ጌታችንኮ ምክር አስፈልጎት ባይኾንም ‹‹ስዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ የተጠያየቀውና የተማከረው ከሐዋርያት ጋራ ነው፤ የተማከረው ከ120 ቤተሰብ ጋራ ነው፡፡
ቅዱስነትዎ ረዥም ዘመን የኖሩት በውጭ አገር ነው፡፡ እንግዳ እንዳይኾኑ ዐዲስ ዋና ጸሐፊ ዐዲስም ዋና ሥራ አስኪያጅ ተመድቦልዎታል፡፡ ምክርዎት ከሌላ ጋራ ከኾነ ግን በጣም አስቸጋሪ ይኾናል፡፡ በአገራችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ሲያገልግሉ ከዬት መጣኽ አልተባባሉም፤ ዘር፣ ጎጥ አልጠያየቁም፡፡ ጎሳ፣ አገር ሳይለያያቸው በመላው ኢትዮጵያ ያገለገሉ አባቶች ናቸው፡፡ ከሥራ ጓደኞችዎ ጋራ ከየት መጣኽ ሳንባባል በጋራ በአንድነት እየተመካከርን ማገልገል ነው፡፡ ከዚያ ወርደን መገኘት የለብንም፡፡
የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ከቅዱስ ወንጌል የቅዱሳን ሐዋርያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት የሊቃውንት እያለ እንደሚሔደው ቅዱስነትዎም ከዋና ጸሐፊ፣ ከዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከቋሚ ሲኖዶስና ከምልዓተ ጉባኤ ጋራ ነው ምክርዎ ሊኾን የሚገባው፡፡ በቅዱስነትዎ ደረጃ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወርዶ ከታች መምከር ማለት ከሊቃውንት መጻሕፍት ወርዶ ልቦለድ መጽሐፍ እንደማንበብ ነው፡፡
በክብረ በዓሉ ምሽት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብዙዎችን ደስ ያሰኘውን ይህን የብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ወንድማዊ ምክር በአድንኖ (አንገታቸው ዝቅ አድርገው) በጸጥታ ሲያዳምጡ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና በበዓለ ሢመታቸው የራት መርሐ ግብር ታዳሚዎች ተስተውለው ነበር፡፡ አዳምጠው ሲያበቁም ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤ እንደዛሬው ለዓመቱ ያገናኘን›› በማለት በጸሎት ከማሳረግ በቀር የተናገሩት አልነበራቸውም፡፡
ሰሞኑን በልዩ ጽ/ቤታቸው ያደረጉት ዝውውርና ምደባ ግን ይህን ታላቅ ምክር አለመስማታቸውን ብቻ ሳይኾን በተለያዩ ዘገባዎች እንደታየው፣ ፀረ አማሳኝ መስለው ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ የአማሳኞች አጋርና ከለላ የመኾናቸውን ዓይነተኛ ፍፃሜ በማያሻማ መልኩ ያረጋገጠ ኾኗል፡፡
ፓትርያርኩ ሰሞኑን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን የጽ/ቤታቸው ሓላፊ በማድረግ መድበዋቸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የሚመሩትና ሠራተኛውን የሚመለከቱ ቅጥሮችን፣ ዕድገቶችንና ዝውውሮችን የማስጠናትና የማስፈጸም ሥልጣንና ተግባር ያለው ጠቅላይ ጽ/ቤት በግልባጭ እንኳ የማያውቀው ምደባው፣ ወትሮም ከመጋረጃ ጀርባ የውጭ ኃይል እጅና የተጽዕኖው አሳላፊ ኾነው በመንቀሳቀስ የሚታወቁትን የንቡረ እዱን የክፉ አማካሪነት ተግባር ይፋ የሚያወጣው ይኾናል፡፡
ቋሚ ሲኖዶስ ከግለሰቡ መሠሪነትና ከጉዳዩ አሳሳቢነት በመነሣት ከያዘው ጠንካራ አቋም አንጻር ቀጣዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ የግለሰቡን ምደባ በቀላሉ እንደማያየው መገመት ቢቻልም፣ ከእንግዲኽ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት በመደበኛነት በመቆጣጠር እንደሚከተሏቸው ለሚገመቱ ፀረ – ሲኖዶስና ፀረ – ሕገ ቤተ ክርስቲያን በኾኑ የአድርብዬ ፖሊቲከኝነት አሠራሮች ከፓትርያርኩ ጋራ የሚኖራቸውን የታሪክ ተጠያቂነት ከባድ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም፡፡
No comments:
Post a Comment