ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
“መልእክት” ያልኩት አቀራረቤን ቀለል በማድረግ የአንባቢያንን ቀልብ ላለመግፈፍ ነው፡፡ እንጂ መነሻየ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው፡፡ ማስጠንቀቂያም ይባል መልእክት ዋናው ጉዳይ በግሌ የተሰማኝንና የማምንበትን ለወገኖቼ ድኅነት ስልም የምጽፈው ነገር ለባለአድራሻዎቹ መድረሱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ድረገጾች ትብብር በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እባካችሁን ለሁሉም ካድሬ መልእክቴን አድርሱልኝ፡፡
ሰው ክርስቶስን መሆን እንዳይችል ጠላት መንገድ እየዘጋበት መቸገሩ የሚታወቅ ነው፡፡ መሆን ቢፈልግ ግን ይችላል፤ የሚከለክለው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ክርስቶስ ራሱም ያለው “እንደኔ ሁኑ፤ እኔን ምሰሉ” ነው፡፡ ችግሩ ክርስቶስን ለመሆን ወይም ቢያንስ ለመምሰል የእምነት ጽናትና እውነተኛ ፍቅርን የተላበሰ ስብዕና ማጣት ነው፡፡ ተራራን ሊያዞር የሚችል እምነት፣ የሚጠላንን ብቻም ሳይሆን የሚገድለንንም ጭምር የሚያፈቅርና ለጨካኞች የሚራራ ልብ፣ የማይወላውል እምነትንና የማያዳላ ፍቅርን የሚገልጥ በጎ ሥራ ካለ ከፈጣሪና ከአንድያ ልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ውህደት መፍጠርና ጓደኛ መሆን የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ የሚጠይቀው እውነተኛ የልብ መሰበርን ብቻ ነው፡፡