የአፍሪካን ቀንድ ሰሞኑን ትኩሳት ይዞታል፤ ሁኔታውን ለማብራራትና ለመተንተን ሰፊ ቦታን ስለሚፈልግ አንባቢው ራሱ እንዲያስብበት በመተው ሁነቶችን ብቻ ማቅረቡ የተሻለ ነው፤ የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታ ትተን በአፍሪካ ቀንድ የሚከተሉትን የተለያዩ ግጭቶችን እንመለከታለን፤
1. በጦርነት ሁኔታ ሁኔታ ላይ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች፤–
ኤርትራና አትዮጵያ
ሰ.ሱዳንና ደቡብ ሱዳን
ሰ.ሱዳንና ደቡብ ሱዳን
1.በውስጥ ብጥብጥ ላይ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች
ሰ.ሱዳን በውስጥ
ደ.ሱዳን በውስጥ
ሶማልያ
ደ.ሱዳን በውስጥ
ሶማልያ
በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለጊዜው ግጭት የማይታይባቸው አገሮች ኬንያና ጂቡቲ ብቻ ናቸው፤ ኬንያ ከብሪታንያ ጋር ባለው የቆየ ትስስርና በኬንያ በሚኖሩ የብሪታንያ ሰዎች ምክንያት ጋሻ አለው፤ ጂቡቲም የቆየ የፈረንሳይ ጋሻ ቢኖረውም በአሁኑ ጊዜ አሜሪካም ተጨማሪ ጋሻ ስለሆነ የውጭ ኃይል አይደፍርም፤ ጂቡቲና ኬንያ በእውነትም እንደጌታዋን የተማመነች በግ ናቸው!
የአፍሪካ ቀንድን ውስብስብ የፖሊቲካ ሁኔታ ለመገንዘብ አገሮቹን የሚያካትቱ ማኅበሮች ብዛት መመልከት ነው፤– የአረብ ማኅበር፤ የአሜሪካ ማኅበር፤ የፈረንሳይ ማኅበር፤ የአፍሪካ ማኅበር፤ የትኛው አገር የየትኛው ማኅበር አባል መሆኑን ብቻ ሳይሆን የየትኛው ማኅበር ተቃዋሚ መሆኑንም መረዳት አካባቢው ያለበትን ውስብስብ ሁኔታ ያሳያል፤ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማልያና ጂቡቲ የአሜሪካ ማኅበር አባሎች ናቸው ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ጂቡቲና ሶማልያ የአረብ ማኅበር አባሎችም ናቸው፤ በዚያ ላይ አራቱም የአፍሪካ ማኅበር አባሎች ናቸው፤ የማኅበር ትርጉም ትንሽ ያሳስባል።
የአረብ ማኅበር በሰሜን ሱዳን በኩል ሌሎች የማኅበሩን አባላት ግብጽንና ሊብያን ኤርትራን (ተመልካች አባል) ይነካል፤ በሁለቱ ሱዳኖች በኩል የማእከላዊ አፍሪካና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነበልባል ይታያል፤ በተጠቀሱት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የሚነደው እሳት በሁለቱ ሱዳኖች በኩል አድርጎ ወደሶማልያና ወደኦጋዴን ሲዘልቅ ከግብጽና ከሊብያ የሚወጣው ነበልባልም ወደሰሜን ሱዳን ይደርሳል፤ በዚህ በእሳት በታጠረው የአፍሪካ ቀንድ ሰፈር አንድ የአሜሪካን አውሮጵላን ተመትቶ ጉዳት ሲደርስበት ሁለት ያህል ሰዎችም ቆስለዋል፤ ይህ ሁሉ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን የተከፈተውን የአሜሪካንን ‹‹በሽብር ላይ ጦርነት›› ወደአፍሪካ መሻገሩን የሚያመለክት ይመስላል።
ዛሬ በሁለቱ ሱዳኖች፣ በሶማልያና በኦጋዴን ሰላማዊ ሰዎች ምኑንም በማያውቁት ምክንያት ቤታቸው እየተቃጠለና እየፈረሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ በደሀነታቸው ላይ መፈናቀልና ስደት ተጨምሮ እየተሰቃዩ ናቸው፤ ነገ አንዳንዶቹ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች እንደኢራቅ፣ እንደአፍጋኒስታንና እንደፓኪስታን ሉዓላዊነታቸውን ያጡ አይሆኑም ለማለት ይቻላል? ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ እስካሁን ለአሜሪካ ያልገበረው ኤርትራ ብቻ ነው፤ ይህንንም ሁኔታ ለመለወጥ ኤርትራን ማባበል የተጀመረ ይመስላል።
የአፍሪካን ቀንድ ከከበበው ነበልባል ኢትዮጵያ እንዴት መውጣትና ማምለጥ ትችላለች? የውስጥ ጉዳይ አመራሩ ሳይለወጥ የውጭ ጉዳይ አመራሩ አንዴት ይለወጣል? የውጭ ጉዳይ አመራር አብዛኛውን ጊዜ የውስጥ ጉዳይ አመራር ነጸብራቅ ነው ይባላል፤ እስቲ በዚህ አስተሳሰብ እነዚህን በእሳት የተከበቡ አገሮች እንመልከታቸው፤ ከአዲሱ አገር ከደቡብ ሱዳን እንጀምር፤ ገና በሕጻንነት እሳት ነደደበት፤ እሳቱን የፈጠረው ብሶት ነው፤ አዲሱ ፕሬዚደንት እንደኢትዮጵያ የአገዛዙ ሎሌዎች በቤተ ክርስቲያንም የማይወልቅ ሰፊ ባርሜጣ አድርጎ በሱፍ ልብስ እየተንሳፈፈ በጎሣ አድላዊነት መሥራት ሲጀምር ምክትሉ ተቃውሞውን በመግለጽ ሸፈተ፤ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ከሰሜን ሱዳን ጋር በጦርነት ሲደማ የኖረው ሕዝብ አሁን ወደሌላ የጎሣ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ገባ።
ለየጎሣው ራሳቸውን በመወከል ሥልጣንን መጋራት የሚፈልጉ ሁሉ ለራሳቸው እንጂ ለሕዝብ የሚያስቡ አይደሉም፤ በመሀከላችንም ብዙ ሰዎች፣ የፖሊቲካ መሪዎች ነን ባዮችም የፖሊቲካ መብትን ጉዳይ በሚገባ ያላሰቡበት ናቸው፤ ለምሳሌ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአመራር ላይ የነበሩት ሰዎች በፓርቲው ፕሮግራም ላይ የነበረውን የግለሰብ የፖሊቲካ መብት የግለሰብና የቡድን መብት በእኩልነት ደረጃ እንዲታይ በሚል የለወጡት ይመስለኛል፤ ይህም የሆነው አቶ ግዛቸው፣ አቶ ዓሥራትና ዶር. ኀይሉ አቶ ስዬንና ዶር. ነጋሶን ለመያዝ ሲሉ ነው፤ ግለሰብ የሚያዝ፣ የሚጨበጥ ፣ግዙፍ አካል ያለው ነው፤ ቡድን የፈቃደኛች ግለሰቦች ስብስብ ነው፤ ግለሰቦች ሲገቡና ሲወጡ ይለዋወጣል፤ ግለሰቦች ሳይስማሙ ሲቀሩ ይፈርሳል፤ ግለሰቦች ተስማምተው ዓላማቸውን ሲለውጡ ይለወጣል።
በጎሣ ማኅበረሰብ ውስጥ ብጥብጥ የሚፈጠረው በብሶት ነው፤ ብዙውን ጊዜ የሥልጣን ጥሙን ያላሙዋላ ጎሠኛ በድንገት ጎሣው ከረጢት ውስጥ ይገባና የሙጥኝ ይላል፤ የግሉን ሥልጣን ማጣት ብሶት ወደጎሣው የሥልጣን ማጣት ብሶት ይለውጠውና የፖሊቲካ እንጀራውን መጋገር ይጀምራል፤ በእንደዚህ ያለ የግለሰብ ብሶት የጀመረ መሬት እነዚህን ጎሠኞች ብቻ ሳይሆን፣ ጎሣቸውንም፣ አገሩንም መከራ ውስጥ ይከታሉ፤ ቆስቁሰው እሳት ያነዳሉ፤ የሚቃጠልላቸው ሲጠፋም ራሳቸው እየነደዱ ያልቃሉ፤ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሣ እሳትን የሚቆሰቁሱትን ሰዎች ብንመለከት አብዛኛዎቹ ከሕዝቡ ጋር እየኖሩ ሲጠቃና ሲበደል ሲጮሁለት አይደሉም፤ በየፈረንጅ አገሩ ያገኙትን እየቃረሙ ራሳቸውን ያበለጸጉና በተደላደለ ጡረታ ሠላሳና ዓርባ ሺህ ብር በወር የሚያገኙ ናቸው፤ ለጎሣ መቆርቆር በስተርጅና ሥራ ሲጠፋ የተፈጠረ ፐሮጄክት ነው፤ በሥልጣን ላይ ላሉትም ቢሆን ጥልቅ ሕንጻ ሠርቶ በአምስት ሺህ ዶላር ማከራየት የራስን የሥልጣን ብሶት ወደጎሣ ብሶት በብልጠት በመለወጥ የተገኘ የፖሊቲካ ጥቅም ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ እስካልነቃ ድረስ፣ ለራሳቸው ጥቅም የሻረ የጎሣ ቁስል የሚያሹትንና በእውነት ለአጠቃላይ የአገር ጥቅም የሚሠሩትን ለይቶ ካላወቃቸው የጀመረው እሳት እየተስፋፋ የእልቂት ዘመን እንደሚያመጣ መገንዘብ የሚያሻ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment