Friday, March 7, 2014

ብሄር ብሄረሰብ፤ የዘር ፓለቲካ…

ደስታው አንዳርጌ (ዶ/ር)
destawats@yahoo.com
እውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ
ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ።
ተስፋ ገብረሥላሴ
ፊደል የቆጠርሁት በአገራችን የህትመት ፋናወጊ (እና አርበኛ) የሆኑት ተስፋ ገብረሥላሴ ያሳትሟት በነበረው የባለ ፲ ሣንቲም ፊደል ነበር። ከፊደሏ ሽፋን ላይ ታዲያ ‘ተስፋገብረሥላሴ
ዘብሄረ ቡልጋ’ ይላል። መጠየቅ እወድ ነበርና መርጌታን ‘የንታ ብሄረ ቡልጋ ምን ማለት ነው?’ ብየ ጠየኳቸው። የንታም ልጄ ብሄር ማለት በግእዝ አገር ማለት ነው። ቡልጋ ደሞ ሽዋ ክፍላገር ውስጥ የሚገኝ አውራጃ ነው። የተስፋ ገብረሥላሴ አገር እዚያ ነው፤ አሉኝ።
ከዚያ አስኮላ ትምርት ገብቸ ፬ኛ ክፍል ህብረተሰብ መጽሀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ‘ብሄረሰቦችን’ የሚያሳይ ስዕል ተደርድሮ አየሁ። በተለይ ሲዳማን የዎከሉት ቆንጃጅት ሙገጫ ሲዎግጡ የሚያሳየው ስእል አይረሳኝም። ይሁን እንጅ ብሄረሰብ የሚለው ቃል አልገባኝም ነበርና አስተማሪየን ጠየኳት። እሷ ግን ጎሳ፣ ነገድ ቅብጥርሴ ብላ የባሰ ግራ አጋባችኝ። ደግነቱ ማታ ማታ የንታ ዘንድ ወንጌል እማር ነበርና ወንበር ከመጀመሩ በፊት ቀደም ብዬ ሄጄ የንታን ‘ብሄረሰብ ምን ማለት ነው?’ ብዬ ጠየኳችው።
የንታም ብሄር ማለት አገር ነው፣ ሰብ ደሞ ሰው ማለት ነው። እንግዲህ ብሄረሰብ ያው የሰው አገር መሆኑ ነዋ አሉኝ። የበለጠ ግራ ተጋባሁ። ህብረተሰብ መጽሀፌ ውስጥ ያዬሁት የሚያማምሩ ቆንጃጅትን ምስል እንጅ ወንዝ ወይ ጋራና ሸንተረር አልነበረማ።Ethiopia and Eritrea map
ሁሉ ሆነና ደርግም በኢሕአዴግ ተተካ። አሁን ግራ ያጋባኝ የነበረው ‘ብሄረሰብ’ የሚለው ቃል ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ ተብሎ ተራብቶ መጣ። የግዕዙን ቀጥተኛ ትርጉም ካየን እንግዲህ አገራት፣ የሰው አገራትና ህዝቦች እያልን መሆኑ ነው። ይሁንና ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የሁሉም ቋንቋ ተናጋሪዎች አሁን ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ ሆነው የተባዙት አንዳንዶቹ ብሄረሰቦች ወደ ብሄርነት ሌሎቹ ደግሞ ወደ ህዝብነት ተለውጠው ይሁን በሌላ ምክንያት በውል አይታዎቅም። በአንጻሩ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎ ነገር የለም። በኢትዮጵያ ሕገ፡መንግስት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚል ቃል አይገኝም። ፖለቲከኞችም ‘የኢትዮጵያ ህዝቦች’ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሉ አትሰሙም። ይህ አጋጣሚ የሚመስለው ካለ እሱ የዋህ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት (ልክ በኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ ሰባት የስልጣን አመታት ኢትዮጵያ አገሬ የሚል ዘፈን እንደማዳመጥ ያለ) በትምክህተኝነት ሊያስከስስ የሚችል የፖለቲካ ፋውል መሆኑን እያንዳንዱ ካድሬ ስለሚረዳ ነው።
የኢትዮጵያ ሕገ፡መንግስት በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ስልጣኑም ሆነ ምድሩ አንዲሁም በላዩና በውስጡ ያለው ሀብት ሁሉ ‘የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ የጋራ ሀብት ነው ይላል። ይህ ደግሞ ከሌሎች ኣገሮች ሕገ፡መንግስታት ሁሉ ልዩ ያደርገዋል (ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚለው ሀረግ እንደ ዋሊያ ኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚታወቀው)። ይህ ይገርመኝ ነበርና ከአስር ኣመታት በፊት ከህገ፡መንግስት ጋር በተገናኘ የመመረቂያ ጽሁፍ ሳዘጋጅ ለመሆኑ አነዚህ የኣገሪቱን የፖለቲካ ስልጣንና ሀብት ኣንድም ሳያስቀሩ ጠቅልለው የያዙ ፍጡራን በትክክል አነማን ናቸው? ኣንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩት በምን ነው? በአገሪቱ ውስጥስ ስንት ብሄሮች፣ ስንት ብሄረሰቦችና ስንት ህዝቦች አሉ? ለምሳሌ የቀበሌ መታወቂያ ስትወስድ ብሄርህን ተጠይቀህ ጉራጌ ብለህ ከሞላህ በኋላ ማታ በኢቲቪ የጉራጌ ብሄረሰብ ስላስመዘገበው ልማት ትሰማለህ። ታዲያ ብሄርና ብሄረሰብ አንድም ሁለትም ናቸው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ይዠ መልስ ፍለጋ ሰነዶች ማገላበጥ ነበረብኝ። የህገ፡መንግስቱን ረቂቅ (ፕሪፓራቶሪ ዎርክስ) ሳይቀር አገላብጨ የሚረባ ነገር ላገኝ አልቻልሁም። ሕገ፡መንግስቱን በማርቀቅ የጎላ ድርሻ ነበራቸው የሚባሉትን ሰዎችም ጠይቄ ያገኘሁት ውጤት ኣልነበረም። በጣም ተገረምሁ። በአገራችን ላይ ከፈጣሪ ቀጥሎ ሁሉን ሀብትና ስልጣን ‘የተቆጣጠሩት’ ግኡዛን ማንነት እንዴት አይታዎቅም? ይህ እኮ እጅግ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
በተለይ ህዝቦች የሚለው ቃል ግራ አጋቢ ነው። በአለም ላይ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም እንድ አይነት ማንነት ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚኖሩባቸው አገራት ከአምስት አይበልጡም፤ ይህም ቢሆን በጣም የሚያከራክር ነው። ይሁን እንጅ የብራዚል ህዝቦች ወይንም የኬንያ ህዝቦች ቢባል እንግዳ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ህዝብ በትርጉሙ ያልተወሰነ ቁጥርና ማንነት ያላቸው ሰዎችን ያካተተ የጥቅል (የወል) ስም ስለሆነ ነው። ለዚህም ነው የአለም ህዝብ ቁጥር እንጅ የአለም ህዝቦች ቁጥር የማንለው። በርግጥ ፈረንጆቹም ከቅኝ በፊት ይኖሩ የነበሩ ቀደምት ጎሳዎችን (ትራይብስ) ለማመልከት ኢንዲጅነስ ህዝቦች ወይም አማዞን ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ይላሉ። ይህ ግን ቀደምት ጎሳዎችን (ነገዶችን)የሚተካ ተለዋጭ ቃል እንጂ ተደራቢ ስያሜ አይደለም። ስለሆነም ቀደምት ጎሳዎችና ኢንዲጅነስ ህዝቦች አይሉም። እንዲያውም ኢንዲጅነስ ህዝቦች የየአገራቸው (ሰፊ)ህዝብ አካል ናቸው። ለምሳሌ የካናዳ ህዝብ በአገሩ የሚኖሩ ኢንዲጅነስ ህዝቦችን ያጠቃልላል። በዚህ አግባብ ከመደበኛ ሰዋሰው ርባታ ተቃራኒ ቢመስልም በአንድ አገር ውስጥ ህዝብ የሚለው ቃል ህዝቦች ከሚለው ቃል ይሰፋል ማለት ነው። ከላይ በጠቀሁት ምሳሌ የካናዳ ህዝብ ካናዳዊያንን በሙሉ ሲያመለክት የካናዳ ኢንዲጅነስ ህዝቦች ግን የካናዳ ህዝብ አካል የሆኑ (ከአጠቃላዩ ህዝብ ፭ ፕርሰንት እንኳን የማይሞሉ) ግን ደግሞ የየራሳቸው የተለየ ማንነት ያላቸውን ነገዶችን ብቻ የሚያመለክት ነው። በሁሉም አገሮች የሚኖሩ የተለያዬ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ሁሉ በአንድ ላይ የዚያ አገር ህዝብ ተብለው ነው የሚታዎቁት።
ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ሁለት አደናጋሪ ነገሮችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ህዝቦች የሚለው ቃል አግባብ በሌላው አለም እንደሚታወቀው ሁሉ ቀደምት ነዋሪወችን (ኢንዲጅነስ ትራይብስ) ለማመልከት ነው እንዳይባል ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ያልሆነው ማን እንደሆነና ማን ከማን እንደሚቀድም አይታወቅም። እንዲያውም ሁሉም ‘ብሄር ብሄረሰቦች’ ቀደምት ነዋሪወች ናቸው ማለት ይቻላል። ቢያንስ ይህ ላለመሆኑ ተቃራኒ ማስርጃ የለም (እንዲያውም እኮ እንደ ሳይንሱ ከሆነ የአለም ህዝብ ሁሉ የተገኘው ከኢትዮጵያ ነው)። ‘ህዝቦች’ የሚለው ቃል አንዳንዶች እንደሚሉት አናሳ ቁጥርና አገራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለማመልከት ነው እንዳንል እነሱው መልሰው ታዳጊ ብሄረሰቦች (አንዳንዴ አናሳ ብሄረሰቦች) ሲሏቸው እንሰማለን። ያ ከሆነ ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦች በሚለው አገላለጽ ብንስማማ እንኳን ‘ህዝቦች’ የሚለው ቃል አላስፈላጊ ድግግሞሽ ከመሆንና ከማደናገር ኣልፎ የሚጨምረው ነገር የለም ማለት ነው። ሁለተኛውና በጣም የሚገርመው በአለም ላይ ባልተለመደ ሁኔታ በአገሪቱ የሚኖሩት ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ በአንድላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አይሆኑም። ይህ የሆነው አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ሕገ፡ መንግስታዊ ቃልኪዳን ገብተናል ያሉት ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ የሚጋሩት ማንነት ሳይኖራቸው ቀርቶ ይሁን በሌላ ምክንያት አይታወቅም። ለነገሩ የአንድ አገር ህዝብ አካል ለመሆን የዚያ አገር ዜጋ ከመሆን ሌላ ምን የተለየ የጋራ ማንነት ያስፈልጋል?
ግድየለም፤ ያ ሁሉ ፖለቲካ ነው ብለን እንለፈው። እኛስ ቢሆን ቃላትን (አንደኣብዛኛዉ ነገራችን) እንደልባችን የምንጠቀመው ለምን ይሆን? ኢትዮጵያ በዘር ተከፋፈለች፣ የዘር ፖለቲካ ያጠፋናል፣ የጦር ሰራዊቱ ከኣንድ ዘር በወጡ አዛዦች ቁጥጥር ስር ነው፣ አቶ እከሌ በተቋሙ ውስጥ የነገሰውን ዘረኝነት በመቃዎም ስልጣናቸውን ለቀቁ፣ ወዘተ…በየቀኑ የምንሰማው ሮሮ ነው። ለመሆኑ ዘር ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ዘር አለ? ለምሳሌ አማራ አንድ ዘር ትግሬ ደግሞ ሌላ ዘር ናቸው? ከሆነስ ከየት ነው የመጡት? እንደሚታወቀው ያን ያህል ሩቅ ከማይባል ጊዜ በፊት ግእዝ እንጂ ትግርኛም አማርኛም ኣልነበሩም። ታዲያ ያኔ ትግሬ ነበር? ኣማራስ? ሌላው ቀርቶ ሴሜቲክ፣ ኩሽቲክ የሚባለውስ ምናልባት ቋንቋን ከመግለጽ (ይህም አከራካሪ ይመስለኛል) የዘለለ ያለው አንድምታ ምንድን ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ችሎታየም አላማየም አይደለም፤ ነገር ግን በጥንቃቄ መታየት የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ይመስሉኛል። እንዲያውም ስለማንነታችን ሳይንሳዊ ብንሆን ብዙ ችግራችን የሚቃለል ይመስለኛል። ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ እንጅ እናንተ ቦታ የላችሁም፤ መሬቱ በሙሉ የእነሱ በመሆኑ እናንተ የመሬት ባለቤት መሆን አትችሉም ሲለን ቢያንስ እነዚያ ‘ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች’ በትክክል እነማን እንደሆኑ እንዲነግረን እንጠይቃለን። በአንጻሩ ደግሞ እኛ የዘር ፖለቲካ ወዘተ…ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ መረዳትና ማስረዳት ያለብን ይመስለኛል።
በዚሁ ላብቃ።
ሰላም

No comments:

Post a Comment