Saturday, April 12, 2014

በኢትዮጵያ የመብቶች ትግሎች ሁሉ ህወሓትን ከሥልጣን ወደ ማስወገድ አቅጣጫ ያመራሉ! (ግንቦት 7)


Ginbot 7 weekly editorialየሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች የክስ ሂደት በበርካታ አሳዛኝ ጉዳዮች የታጀቡ ቢሆኑም የሚሰጡት ትምህርት ግን ከፍተኛ ነው። እነዚህ ወገኖቻችን “ችሎት” በተሰኘው የአገዛዙ የድራማ መድረግ በመገኘት ፍትህን ለመግደል ካባ ለብሰው “ዳኞች” ተብለው ለተኮፈሱ የአገዛዙ ተላላኪ ካድሬዎች እና ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጓቸው ጠንከር ያሉ ንግግሮች ካድሬ “ዳኞችን” አሳፍረዋል፤ ኢትዮጵያዊያንን ግን አኩርተዋል። እኚህ ወገኖቻችን ከወያኔ ችሎት ፍትህ ይገኛል የሚል ብዥታ ባይኖራቸውም መድረኩን መልዕክት ለማስተላለፊያነት ተጠቅመውበታል። በዚሁ መድረክ በአገዛዙ እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ እየደረባቸው ስላለው ሰቆቃ ሲናገሩ አድማጮች ሊቆጣጥሩት የማይችሉት ሐዘንና እልህ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ወያኔ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ የሚፈጽመው በሙስሊም መሪዎች ላይ ብቻ አይደለም። የህግ እውቅና የተሰጣቸው መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው በጠየቁ ወገኖቻችን ሁሉ ተመሳሳይ ሰቆቃ ሲፈጸም ኖሯል፤ አሁን እየተፈጸመ ነው። “ኑሮ ከበደን” ያሉ ወጣቶች ተደብድበዋል። “የእርሻ መሬት አጣን” ያሉ ገበሬዎች ከያዙት ቁራሽ መሬት ተፈናቅለዋል፣ ተግዘዋል፣ ከነልጆቻቸው ለጎዳና ኑሮ ተዳርገዋል። በሀረር እና በአዲስ አበባ ከተሞች እንደታየው “ነግደን እንኑር” ባሉ ነጋዴዎች ላይ ከአቅም በላይ ከሆነ ግብር ጀምሮ በንብረታቸው ላይ እሳት እስከመልቀቅ የደረሰ አረመኔዓዊ ድርጊት ተፈጽሟል።
በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 18 መሠረት እያንዳንዱ ሰው በግሉም ሆነ በጋራ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና የማስተማር፤ ያልፈለገውን ደግሞ የመተው መብት አለው። ስለሆነም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ተግባራት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እውቅና ለተሰጣቸው መብቶቻቸው መከበር ያደረጉት ትግል ነው። ለወጉ ያህል “ሕገ መንግሥት” ተብሎ በሚጠራው ኢትዮጵያዊያንን ለመክሰሻነት ብቻ በሥራ ላይ በሚወለው ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም ዓለምዓቀፍ እውቅና ያገኙ መብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተረግጠዋል። ለእነዚህ መብቶች መከበር በጽናት የቆሙ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ከተራ የመንደር ካድሬና ጆሮ ጠቢ እስከ እስከ ከፍተኛው እርከን ባለ ባለሥልጣኖች ተዋክበዋል፤ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል።
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለእምነት መብቶቹ መከበር እስካሁን ያደረገው ተጋድሎ የሚደነቅ ነው። የተቀናጁ እንቅስቃሴዎቹ፣ ተምሳሌታዊ የተቃውሞ ምልክቶች አጠቃቀሙ የሚያበረታታ ነው። ክርስቲያኑ ከዚህ የሚማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች አሉ።
ከሙስሊም እንቅስቃሴና ወያኔ ይህንን እንቅስቃሴ ለማፈን እየሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች የምንረዳው አንድ ትልቅ ሐቅ የቱን ያህል ጨዋና የሰለጠነ ቢሆን ወያኔ የሕዝብ ድምጽ ለማዳመጥ ፍላጎት የሌለው መሆኑን ነው። ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸውን በሚያስገርም ቁጥብ ሥነሥርዓት (ዲሲፕሊን) ቢያቀርቡም ከወያኔ የተሰጠው ምላሽ ግን አፈና፣ ረገጣ፣ ቶርቸር እና ከእስከዛሬዎቹ ይበልጥ አፋኝ የሆኑ ደንቦችና ድንጋጌዎችን ነው። ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ያደረጓቸው ትግሎችም እንደዚሁ ወደ ባሱ የመብት ጥሰቶች እያመሩ ነው። ከዚህ የምንማረው ነገር ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ስትራቴጂዎችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ነው።
እንደሚታወቀው፤ ሰብዓዊ መብቶች እርስ በርሳቸው የተቆራኙ፤ እርስ በርሳቸውም የሚደጋገፉ ናቸው። አንዱ የመብት ዓይነት ሲጓደል፤ ሌላውም አብሮ ይጓደላል። ለምላሴ የመናገር መብት ተገፎ እያለ የማምለክ መብት ሊፋፋ አይችልም፤ ወይም ደግሞ ፍትሃዊ ዳኝነት የማግኘት መብት ተጥሶ እያለ የማምለክ መብትን የሚያስከብር ተቋም ሊኖር አይችልም።
ለመብቶች መከበር የሚደረጉ ትግሎች፤ በተለይም ደግሞ የሙስሊም ወገኖቻችን ትግል የደረሰበት ደረጃ በአንክሮ ሲጤን ስትራቴጂን በተመለከተ በጥልቀት ልናስብባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን እንገነዘባለን። ለጊዜው ሁለት ነገሮች ላይ አጽንዖት ሰጥተን እናልፋለን።
  1. ከላይ እንደተገለፀው የመብት ትግሎች ሁሉ መደጋገፍ ይኖርባቸዋል። ቀደም ሲል በባህርዳር፣ በኋላም በአዲስ አበባ በሴቶች ዓለም ዓቀፍ ቀን አሁን ደግሞ በደሴ ውስጥ እንደታየው የመብት ጥያቄዎች ሁሉ ተደጋግፈው መነሳት ይኖርባቸዋል። ይህ የመደጋገፍ ልምድ የሁለቱ ትላልቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች ለየእምነቶቻቸው ነፃነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መኖር ይኖርበታል። የሙስሊሞች የመብት ጥያቄዎች የክርስቲያኖችም፤ የክርስቲያኖች ደግሞ የሙስሊሞችም መሆን ይኖርበታል።
  2. በሥልጣን ላይ ያለው የህወሓት አገዛዝ አንዱንም የመብት ጥያቄ መመለስ የማይችል መሆኑ ግልጽ መሆን ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመብት ጥያቄዎች ግብ ወያኔን ከሥልጣን ከማባረር ያነሰ መሆን አይችሉም። ስለሆነም የመብት ማስከበር ትግል ስናካሂድ ይህን አልመን እና ለዚህም ተዘጋጅተን መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የስነልቦና፣ የድርጅትና የስልት ዝግጅት ይጠይቃል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ህወሓት ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል ብሎ ያምናል። ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ መገለል፣ መረገጥ፣ መጋዝ፣ መሰደድ፣ መደብደብ፣ የማይቀርልን በመሆኑ ሥቃያችንን ለመቀነስ ወያኔን ማስወገድ ይኖርብናል ብሎ ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶችና ምክንያቶች የምናደርጋቸው ትግሎች ወደ አንድ አቅጣጫ ያመራሉ ብሎ ያምናል። ትግሎቻችን ዞሮ ዞሮ ህወሓትን ከሥልጣን ወደ ማስወገድ ማምራታቸው ግልጽ ስለሆነ ለዚህ የሚያስፈልገውን ስነልቦናዊና ቁሳዊ ዝግጅቾችን እናድርግ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment