በንግዱ ዓለም ለተሰማራችሁት ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤
በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሁሉንም የኢኮኖሚ መስክ ጠቅልሎ በመያዙ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚገባችሁን አስተዋጽኦ እያደረጋችሁ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ለይስሙላ ብቻ ነጻ ገበያን ‹‹ፈቅጃለሁ!›› የሚለው ገዥው ፓርቲ ኢኮኖሚውን በራሱ ድርጅቶች ተቆጣጥሮ ለስልጣን መቆያ መሳሪያ አድርጎታል፡፡ የመንግስት ድርጅት የሚባሉትም ቢሆኑ ኢኮኖሚው ጠቅልለው ለተመሳሳይ አላማ መሳሪያ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎም አገራችን ነጻ ገበያና የግል ባለሃብቶች የተዳከሙባት ግንባር ቀደም አገር ሆናለች፡፡
ይህ በአንድ ኃይል የተጠቀለለ የኢኮኖሚ ስርዓት እናንተ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በነጻነት እንዳትሰሩ ከማድረጉም ባሻገር ህዝባችን በኑሮ ውድነት እንዲታመስ አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ በቅርብ አመታት ከስርዓቱ ጋር አብሮ መሄድ ያልቻለውን የንግዱን ማህበረሰብ ለስርዓቱ እጁን እንዲሰጥ ለማድረግ እንዲመች ከሚሰራው ስራ ጋር የማይመጣጠን ግብር በመጫን ላይ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡ ሱቅ በደረቴ የሚሰሩ፤ እንጀራ ጋግረው የሚሸጡ እናቶች፤ የጀበና ቡናና ሌሎቹንም አነስተኛ ስራዎች የሚሰሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ የማይችሉት ግብር ተጨኖባቸዋል፡፡ የንግድ ፈቃድ እድሳት፤ የመስሪያ ቦታና ሌሎችም ነጋዴው በኢትዮጵያዊነቱና ለህዝብ በሚሰጠው ጥቅም ሊያገኛቸው የሚገባቸው መብቶች በሙስና ለፓርቲ ባለው ቅርበትና በሌሎች በዚህ ስርዓት በተሳሳቱ አሰራሮች የንግዱን ማህበረሰብ አስረው ይዘውታል፡፡
ነጋዴውን የሚፈራው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ነጋዴዎች ደጋፊ ማህበር አቋቁሟል፡፡ ይህም ነጋዴውን በነጻነት ከመስራት ይልቅ የኢሕአዲግ ተለጣፊ እንዲሆን ካለው ፍላጎት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በአንጻሩ ሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የራሳቸውን ነጻ የነጋዴ ማህበር ሲያቋቁሙ አይታዩም፡፡ የመስሪያ ቦታ፤ ግብር እና ሌሎችም ነጋዴው የሚጣልበት ግዴታና የሚገባው መብት ላይ ያለውን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ጥረት የሚያደርግ የንግዱ ማህበረሰብ አካል አይታይም፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ሊሳካለት ባለመቻሉ እንዲሁም ነጻ ገበያ ተግባራዊ እንዲሆን አለመፍቀዱ የአገራችን ኢኮኖሚ ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ተባብሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን በሰፊው የሚያመርቷቸው ምርቶችም ጭምር ለህዝብ የሚደፈሩ አልሆኑም፡፡ የእነዚህ ምርቶች እጥረት ሲከሰት ጥያቄውን ከእሱ ትከሻ ለማውረድ የሚከሰው የንግዱን ማህበረሰብ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ‹‹ዘይት የደበቀ፣ ስኳር ያልሸጠ፣…›› እየተባለ በሰበብ አስባቡ የስርዓቱ ግፍ ገፈት ቀማሾች ሆናችኋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ድሃ ከሚባሉት አገራት ቀዳሚውን ተርታ መያዟን ለንግዱ ማህበረሰብ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት ይሆናል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ይህን መሰረታዊ ችግር ከስር ከመሰረቱ ለመፍታት በሚደረገው ትግል የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ባለመሆኑ አገሪቱን ከገባችበት አረንቋ ለማውጣት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መጠቆም ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ይህን ለማድረግም መጀመሪያ የራሱን ነጻነት በማስከበር፣ በመደራጀት የንግዱን ማህበረሰብና ኢትዮጵያውያን አቅርቦቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበትን አጋጣሚ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ በተለይ የራሱን የፖሊሲ ችግር ተለጣፊ ባልሆኑት የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ላይ ለማላከክ የማይታክተውን የገዥውን ፓርቲ ተግባር በማጋለጥ እና ከህዝብ ጎን በመቆም ግዴታችሁን መወጣት ይገባችኋል እንላለን፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም ጃን ሜዳ ‹‹የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን!›› በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ መብታችሁን የተነጠቃችሁት የንግዱ ማህበረሰብ አካላትም የራሳችሁንና የቀሪ ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስመለስ በሰልፉ ቀዳሚ ተሳታፊ እንድትሆኑ ፓርቲያችን ጥሪውን አቅርቦላችኋል፡፡
ኑ ራሳችንን ነጻ በማውጣት የአገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!
No comments:
Post a Comment