ኢሳት ዜና ፦ ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ የሥራ ፈላጊዎችን መረጃ ለማጠናቀር ታስቦ በተካሄደ ምዝገባ በመላ ሀገሪቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሥራ ፈላጊዎች በፈቃደኝነት መመዝገባቸውንና ከነዚህ ውስጥ ከ351ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጆች ምሩቃን መሆናቸውን ከከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተገኘ ጥናት አመለከተ። ይህ ጉዳይ መጪው ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የገመተው ኢህአዴግ በተለይ በአዲስ አበባ ባለፉት ሳምንታት የሥራ አጦች አዲስ ምዝገባ ቤት ለቤት በማካሄድ ላይ ይገኛል። በ2006 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ የተመዘገቡት ሥራ ፈላጊዎች 1 ሚሊዮን 759 ሺ 768 ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 41 ሺ 298 የዩኒቨርሲቱ ምሩቃን፣ 310 ሺ 10 የኮሌጅና ቴክኒክና ሙያ ምሩቃን፣ የተቀሩት 1 ሚሊዮን 444 ሺ 460 ያህሉ በተለያየ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ ሥራ ፈላጊዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።
ከሥራ ፈላጊዎች መካከል 41 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል። ምዝገባ መኖሩን ባለመስማትና በተለያዩ ተጨማሪ ምክንያቶች ያልተመዘገቡ ሊኖሩ እንደሚችሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቅሰው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የራሱ አባል ያልሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በቅጥር ወቅት ግልጽ አድልዎ እንደሚፈጽም፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ታቅፎ ብድር ለማግኘት ሳይቀር አባልነት ትልቅ መስፈርት መሆኑ በርካታ ወገኖችን ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑና አነስተኛና ጥቃቅን አዲስና ነባር አንቀሳቃሾች ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ሶስት ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር የተሰጠ መሆኑን ስለጉዳዩ በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች ገልጸው፣ እነዚህ በፈቃደኝነት ብቻ የተመዘገቡ ሥራ አጦች በዚህ ደረጃ ቢደገፉ ሥራ ለመፍጠር የማይችሉበት ምክንያት አልነበረም ብለዋል። በአዲስ አበባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካይነት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባ ቤት ለቤት የሥራ አጦች ምዝገባና ተስፋ መስጠት ሥራዎች በመከናወን ላይ ነው። ከየወረዳው ቤት ለቤት የሚዞሩ መዝጋቢዎች ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው ብድር በመውሰድ መሥራት እንደሚችሉ፣ ሙያዊ ሥልጠና ከፈለጉም እንደሚመቻችላቸው በመንገር ተሰፋ የሰጧቸው ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በተለየ ሁኔታ በየወረዳው በመጥራት ምዝገባው እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment