ከጳጉሜ5 2006 ጀምሮ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመዥንገር ዞን ጎደሬ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ለህልፈተ ህይወትና ስደት መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። በአካባቢው ለረጅም አመታት በመምህርነት እንዳገለገሉ የሚናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ራሳቸውን የአካባቢው ነባር ብለው በሚጠሩት ነዋሪዎችና መጤ በሚሏቸው ደገኞች መካከል መፈጠሩን ገልፀዋል።
አቶ ተስፋዬ ጌታነህ በአካባቢው የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የወረዳ ሰብሳቢ ናቸው። እንደ አቶ ተስፋዬ ጌታነህ ገለጻ ግጭቱን ለመፍታት የፓርቲዎችና የመንግስት ባለስልጣናት አድርገውት የነበረው ጥረት ስኬታማ አልሆነም። ግጭቱን ለመፍታት ወደ አካባቢው የተሰማራው የፌዴራል ፖሊስ በቂ ባለመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አባቢው በማምራት መረጋጋት መፈጠሩን አቶ ተስፋዬ ጌታነህ ተናግረዋል። ሆኖም በግጭቱ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ በአቅም ውስንነት ምክንያት አልተሳካም ብለዋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የፌዴራል ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ ወርቁ በበኩላቸው በአካባቢው የሚገኝ የቡና ደን የይገባኛል ጥያቄ ለግጭቱ መነሾ መሆኑን አስረድተዋል። በግጭቱ ለሞትና ስደት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርና ለውድመት የተዳረገ ሃብት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ ነው ያሉት የፌዴራል ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ ወርቁ ተመሳሳይ ግጭት በዚሁ አካባቢ የኪ ወረዳ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል። ሙሉ ዘገባዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።
No comments:
Post a Comment