Monday, December 21, 2015

ፍልስፍና አልባ የሆነ አገዛዝና የፖለቲካ ትግል ዘዴ የአንድን ህብረተሰብ አስተሳሰብ ያዘበራርቃል - የመጨረሻ መጨረሻም አገርን ያወድማል!

 ፍልስፍና አልባ የሆነ አገዛዝና የፖለቲካ ትግል ዘዴ የአንድን ህብረተሰብ አስተሳሰብ ያዘበራርቃል - የመጨረሻ መጨረሻም አገርን ያወድማል! ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር 
 ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በብዙ አፍሪካ አገሮች የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት፣ የህዝቦች ኑሮ መዘበራረቅና ዓላማ-ቢስ መሆን፣ እንዲያም ሲል በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ አሳቦ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ማድረግና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ወደ ርስ በርስ መተላለቅ እንዲያመራ መንገዱን ማዘጋጀት፣ በተራ አነጋገር ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከአምባገነናዊ አስተዳደር መስፈንና ከዲሞክራሲ አለመኖር ጋር ሲያያዝ ይታያል። አንዳንዶች እንዲያውም እንደዚህ ዐይነቱን ዓላማ-ቢስ የህብረተሰብ ጉዞ የአፍሪካ መሪዎች ወይም የጥቁር ህዝብ ችግር አድርገው የሚመለከቱ አሉ። በእርግጥ ለአንድ አገር ስርዓት ባለው መልክ መተዳደርና፣ ህብረተሰቡም በዕቅድና በዓላማ እንዲመራ ከተፈለገ በዚያ የሰፈነው አገዛዝ ህብረተሰቡን በማደራጀት ረገድ የሚጫወተው ሚና አለ።
ጥያቄው ግን አንድ ህብረተሰብ ዓላማ ባለው መልክ እንዳይደራጅና ቆንጆ ቆንጆ ስራዎችን እንዳይሰራ የሚያግዱት ነገሮች ምን ምን ናቸው? በስነ-ስርዓት እንዲደራጅስ ከተፈለገ መሪዎችም ሆነ ህብረተሰቡ መከተል የሚገባቸው ኖርሞች፣ ፍልስፍና፣ ሞራልና ስነ-ምግባር አሉ ወይ? ምንስ ይመስላሉ ? ወይስ አንድ ህዝብ እየተዋከበና ርስ በርሱ እየተፋጠጠ መኖሩ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው ወይ ? አንድ ህብረተሰብስ በምን መልክ ነው መታየት ያለበት? በሌላ አነጋገር፣ ለመብላትና ለመጠጣት ብቻ የሚኖርበት ? ወይስ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ ጥበባዊና ኢኮኖሚዊ፣ እንዲሁም ሌሎችም ነገሮች ተደራጅተው ህብረተሰቡ እንደሰውነታችን በብዙ ነርቮች ተሳስሮ፣ ልክ እንደደም ዝውውር ሳያቋርጥ፣ በተለይም ኢኮኖሚው አንድኛው መስክ ከሌላው ጋር በመያያዝ ውስጠ-ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ የሚጓዝበት መድረክ ነው ወይ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በአሁኑ ዘመን የግሎባል ካፒታሊዝም አይሎ መውጣትና፣ የብዙ ህብረተሰቦችን ህይወት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያመሩ ማስገደድና ማዘበራረቅ፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ፈራቸውን እየሳቱና በቀላሉ የማይመለሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል። በተለይም የየመንግስታቱ መኪና በከፍተኛ ደረጃ ሚሊታራይዝድ መሆንና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጦር ስልት ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ በዚህም ላይ የስለላው ድርጅት መጠናከርና ህዝብን አላላውስም ማለት፣ ብዙ የአፍሪካ መንግስታት አንድ መንግስት ለአገሩና ለህዝቡ ምን መስራት እንዳለበት እንዳይገነዘቡና አትኩሮአቸውንም በሀገር ግንባታ ላይ እንዳያደርጉ አግዷቸዋል ማለት ይቻላል። የየመንግስታቱትም ሚና ህብረተሰቡን ከማደራጀት፣ ህብረ-ብሄርን ከመገንባት፣ በሳይንስና በቲክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ ራስን ወደ ማጠናከሪያና ሀብት ዘራፊነት ተለውጧል። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና አገዛዞች የህዝቦቻቸው ተጠሪዎች ሳይሆኑ፣ በውጭ ኃይሎች የሚታዘዙና፣ በተለይም ጦርነትንና ህዝባዊ ሀብትን ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው። ከዚህ ስንነሳ በፍጹም ልናልፈው የማንችለው ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኖ ይገኛል። ይኸውም ብዙ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ከሞላ ጎደል ስርዓት ባለው መልክ ተደራጅተው ሲጓዙና፣ የብዙ ሚሊያርድን ህዝቦች ዕድል ወሳኝ መሆን ሲችሉ፣ እንደኛ ያለውንስ ህዝብ ስነ- 2 ስርዓት ያለው አደረጃጀት ለምን ተሳነው? ስነ-ስርዓትስ ባለው መልክ ለመደራጀት የሚጎድሉን ነገሮች ምንድናቸው? ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ህብረተሰብአዊ ? ወይስ የፖለቲካ ፍልስፍና እጦትና መሪዎች የሚመሩበት አንዳች ፍልስፍና አለመኖር ? ለአንድ ህብረተሰብ በስነ-ስርዓት መደራጀትን አስመልክቶ ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮም ሆነ ከዚያም በፊት ህግና ስርዓት አስፈላጊ መሆናቸውን በብዙ ምርምር የተደረሰበትና በኢምፔሪካል ደረጃም የተረጋገጠ ነው። ይሁንና ግን በተለይም ፍልስፍናን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝና፣ አንድም ህብረተሰብ ሚዛናዊ በሆነ መልክና በስነ-ስርዓት የማደራጀትን አስፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ውይይት የተካሄደበት ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የተነሱና ብዙም ምርምር የተካሄደባቸው የፖለቲካ ፍልስፍናዎች፣ ህብረተሰብን በአንድ ስርዓት ባለው መልክ ማደራጀት፣ በግሪኩ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ላይ ተመርኩዞ ነው። እዚህ ላይ ሌላው የሚነሳው ጥያቄ፣ የተለያዩ የግሪክ ፈላስፋዎች አትኩሯቸውን ለምን በፍልስፍና ላይ፣ በተለይም በፖለቲካ ፍልስፍና ላይ አደረጉ ? የሚለው ከባድ ጥያቄ መመለስ ያለበት ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ለህይወቱ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያና ራሱንም ለመከላከል መሳሪያዎች ቢያስፈልጉትም፣ ከዚህ ዘልቆ በመሄድ የማሰብ ኃይሉን በማዳበርና ራሱንም በማደራጀት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም መሆን እንደሚችል የታወቀ ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ጉዳዮች በየጊዜው ሊሻሻሉና በቁጥር እየጨመረ ከሚሄደው ህዝብ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉት የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ሚናነት በግልጽ ከተቀመጡና፣ በነዚህ ላይ ከፍተኛ ርብርቦሽ ከተደረገ ብቻ ነው።፡ይሁንና አንድ ህዝብ የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር፣ አዳዲስ መሳሪዎችን በመፍጠር ከዝቅተኛ ህብረተሰብ ወደ ከፍተኛ እንዳይሸጋገር፣ ከቁም ነገር ስራ ይልቅ በሆነ ባልሆነው ነገር በመያዝ ወይም በጦርነት በመጠመድ ዝብርቅርቅ ኑሮ እንዲኖርና፣ በዚያው እንዲገፋበት የሚያደርጉትና፣ ይህ ዐይነቱም ኑሮ እንደ ባህልና እንደ ልማድ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ይህንን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመራመሩት የግሪክ ፈላስፎች የሰው ልጅ ከእንስሳ የተለየ ከሆነና፣ ራሱንም ማደራጀትና በሰላም መኖር የሚችል ከሆነ ለምንድን ነው ወደ ጦርነት የሚያመራው? ለምንድን ነው የተዘበራረቀ ኑሮ የሚኖረው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ነበረባቸው። ሶክራተስና ፕላቶ ብቅ ከማለታቸው በፊት በስድስተኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያ በፊት የግሪክ ህዝብ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር። የርስ በርስ መተላለቅ፣ መጠን የሌለው ብዝበዛና ድህነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች መደጋገምና ሌሎችም የግሪክን ህዝቦች ኑሮ ያመሰቃቀሉና፣ ዕረፍትና ሰላም አንሰጥም ያሉ ሁኔታዎች የህዝቡ ዕጣዎች ነበሩ። እነዚህን የመሳሰሉ የኑሮን ትርጉም ያሳጡ ሁኔታዎች በእነ ሆሜርና በሄሲዮድም ሆነ በግሪክ ህዝብ ዕምነት የአምላኮች ድርጊት እንደነበሩና፣ ባስፈለጋቸው ጊዜ ህዝቡን ለመቅጣት ሲሉ የሚልኩት ውርጅብኝ እንደነበርና፣ ህዝቡም ካለ አምላኮች ፈቃድ በራሱ አነሳሽነት ምንም ሊያደረገው የሚችለው ነገር እንደሌለና፣ የነሱንም ትዕዛዝ መጠበቅ እንደነበረበት የታመነበት ጉዳይ ነበር። ከሶክራተስና ከፕላቶ በፊት የነበሩ የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላስፎች ይህንን አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነና፣ በተፈጥሮ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ አደጋዎች፣ ለምሳሌ እንደ ብልጭታና የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ሌላ ነገሮች የአምላኮች ተልዕኮዎች ሳይሆኑ የተፈጥሮ ህግጋት እንደሆኑና፣ ማንኛውም ነገር ካለምክንያት እንደማይከሰት ለማመልከት ቻሉ። ይህ የመጀመሪያው የተፈጥሮ ፍልስፍናና፣ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በታላቁ የግሪክ መሪ በሶሎን ተግባራዊ የሆኑት የመጀመሪያው የፖለቲካ ሪፎርሞች በግሪክ ህዝብ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከተሉ። ህዝቡ ከማንኛውም የባርነት ማነቆዎች እንዲላቀቅ መደረጉ፣ የነበረበትን ዕዳ እንዳይከፍል መሰረዝና፣ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እንደነፃ ዜጋ እንዲታይ መደረጉ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥን ሊያመጣ ችሏል። ከፍተኛ የባህል ለውጥ የታየበትና ልዩ ልዩ የፍልስፍና አስተሳሰቦችና፣ የሂሳብ ምርምሮችና ሳይንሳዊ አስተሳሰብም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በተለይም 3 የግሪክን ምሁር ጭንቅላት መያዝ የጀመሩትና ዕውነተኛ ዕድገት የታየበት። በፒታኩስና በሶሎን የአገዛዝ ዘመን የግሪክ ህዝብ ከጦርነት ተላቆና በአጉል ጀግንነት ላይ የተመሰረተን ዝናን ጥሎ ራሱን በማግኘት ዕውነተኛ የሲቪክ አገዛዝን የተቀዳጀበት ዘመን ነበር። የማቴሪያል ደስተኛነት ብቻ ሳይሆን የመንፈስንንም ነፃትና ደስተኛነት በመቀዳጀት የመፍጠር ችሎታውን ያዳበረበት ዘመን ነበር። ከፒታኩስና ከሶሎን አገዛዝ በፊት የግሪክ ህዝብ በጦርነት የተጠመደና ይህንን እንደሙያው አድርጎ በመያዝ የሚዝናናበት ዘመነ ነበር። ይሁንና ግን የፒታኩስና የሶሎን የፖለቲካ ሪፎርሞች በግሪክ ህዝብ ላይ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ቢያመጡም ይሁ ሁኔታ ግን በዚያው ሊገፋበት አልተቻለም። በመሆኑም የስልጣን ሽግግር ሲካሄድና የኃይል አሰላልፍ ሲቀየር፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና አደረጃጀት እነሶሎን በቀደዱት መልክ ሊጓዝ አልቻለም። በተለይም የስልጣንን ምንነት ከራሳቸው ዝናና ጥቅም አንፃር መተርጎምና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት አንዳንድ የግሪክ መሪዎች የፖለቲካውን አቅጣጫ ይቀይራሉ። ህብረተሰብአዊ ስምምነትን የሚያጠነክር ፖለቲካዊ አካሄድ ሳይሆን ውዝግብነትን የሚፈጥር፣ የህዝቡን መንፈስ የሚረብሽና የጥቂት ኦሊጋርኪዎችንና ቡድኖችንም ሆነ ግለሰቦችን ጥቅም የሚያስቀድም ፖሊሲ መቀየስ ይጀምራሉ። በመሆኑም የኦሊጋርኪዎችን አመለካከት የሚያስተጋቡና ይህም ትክክል ነው ብለው የሚያስተምሩ ፈላስፋዎች፣ ሶፊስቶች ተብለው የሚጠሩ፣ የፖለቲካውን መድረክ እየተቆጣጠሩና ብዙ ወጣቶችንም በማሳሳት የበላይነትን እየተቀዳጁ በመምጣት በስምምነት የተመሰረተውና ለከፍተኛ ስልጣኔ የሚያመቸውን የእነሶሎን የፖለቲካ ፍልስፍናን ከመከተል ይልቅ ስግብግብነትንና ዝናነትን በማስቀደም ህብረተሰባዊ መዛባት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በተለይም የአቴን የበላይነትን መቀዳጀትና ከሌሎች ደሴቶች ጋር ሲወዳደር በስልጣኔ ቀድሞ መሄድ የግሪኩን የመጀመሪያውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየደመሰሰው ሊመጣ ቻለ። የመንፈስን የበላይነት፣ ጥበብና ህብረተሰብአዊ ስምምነትን የሚቀናቀነው የሶፊስቶች አመለካከት በመስፋፋት አገዛዙን ይበልጥ ለጦርነት የሚገፋፋና፣ የህዝቡን ሰላም የሚነሳ ስርዓት በመሆን በስንትና ስንት ጥረት የተገነባው ስልጣኔ በተሳሳተ ፍልስፍና መፈራረስ ይጀምራል። በወቅቱ የተለያዩ የግሪክ ግዛቶች፣ በአንድ በኩል በራሳቸው ውስጥ በሚደረግ ሽኩቻ የተወጠሩ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የፐርሺያ አገዛዝ አቴንና ሌሎችንም ግዛቶች በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጦርነት ይከፍትባቸዋል። በፐሪክለስ የሚመራው አገዛዝ ሌሎችንም በማስተባበር ከፐርሺያ ወራሪ ጦር በኩል የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ይመልሳል። ይሁንና ግን እነ ፐሪክለስ ሌሎችን ግዛቶች በማስተባበር በፐርሽያ ጦርነት ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ የጥጋብ ጥጋብ ይሰማቸዋል። ቀደም ብሎ የተደረሰበትን የእኩልነትና ስምምነት ውል በማፍረስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ ወረራ ያደርጋሉ። እጅ አልሰጥም ያሏቸውን ግዛቶች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር በማካሄድ በተለይም ወንድ ወንዱን በመጨረስ ሴቶችንና ህፃናትን ገባር ያደርጓቸዋል። ድርጊቱ እጅግ አሰቃቂ ነበር። የግሪክን ህዝብ ትርምስ ውስጥ የከተተ ነበር። ይሁንና ይህ የአቴን ጥጋብና ግፍ በስፓርታ የገዢ መደብ ሊከሽፍና ሊገታ ቻለ። በዚህ ድርጊቱ ፐሪክለስ አቴን ለሌሎች ግዛቶች በስልጣኔዋ ምሳሌ ትሆናለች ብሎ እንዳለተመጻደቀ ሁሉ፣ በተግባር ያሳየው ግን በኃይሉ በመመካት ወረራንና ጭፍጨፋን ነበር ያረጋገጠው። እነ ሶክራተስና ፕላቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና፣ በአራተኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ሲሉ ይህንን የወንድማማቾችን ርስ በርስ መተላለቅና፣ ህዝቡን ሰላም ማሳጣትና ኑሮውም ትርጉም እንዳይኖረው ማድረግ የተረጎሙት ከተሳሳተ ፍልስፍና ጋር የተያያዘ ስልጣን መሆኑን በማመልከትና፣ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀርና አገዛዙ የሚመራበትን ፍልስፍና በመመርመር ነበር። በሶክራተስ ዕምነትና አመለካከት፣ በጊዜው ፐሪክለስ ታላቅ መሪ ቢሆንም በሱ ዘመን አቴን ወደ ኢምፔርያሊስትነት የተለወጠችና፣ የአገዛዙም ፖሊሲ ዝናን በማስቀደም ኃይልንና ስግብግብነትን(Power and Greed) ዋና ፍልስፍናው አድርጎ የተነሳ 4 አገዛዝ መሆኑን በማመልከት ነበር። በመሆኑም ይላል ሶክራተስ፣ በፐሪክለስ ዘመን ወጣቱ ሰነፍ፣ ለፍላፊና አጭበርባሪ የሆነበት ዘመንና፣ አሳሳች አስተሳሰብ በማበብ በተለይም የወጣቱን ጭንቅላት በመያዝ ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንዲያመራ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። ባህላዊ ኖሮሞችና መከባበር የጠፋበት፣ ሽማግሌ የማይከበርበትና፣ ህዝቡም ይዞ የሚጓዘው አንድ ዕምነት አልነበረውም። አስተሳሰቡ ሁሉ የተዛበራረቀበት ነበር። በጊዜው የነበረው ትግል ይህንን አቅጣጫ የሌለውን ጉዞና በስልጣን መባለግ አስመልክቶ በሶክራተስና በፕላቶ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከል የጦፈ ትግል ይካሄድ ነበር ። ሶፊስቶች የእነ ፐሪክለስን የአገዛዝ ፍልስፍናን ሲደግፉ፣ መሰረተ- ሃሳባቸውም በጊዜው የነበረውን ሁኔታ መቀበልና ይህም ትክክል መሆንኑ ማስተማር ነበር። ሶፊስቶች በአነሳሳቸው ተራማጅ ቢሆኑም፣ ፍልስፍናቸው በቀጥታ በሚታይ ነገር ላይ ተመርኩዞ ትንተና መስጠትና፣ በጣፈጠ ግን ደግሞ በተሳሳተ አቀራረብና አነጋገር የሰውን ልብ መማረክ ነበር። ስለዚህም በሶፊስቶች ዕምነት ስልጣን ላይ ያለው የገዢ መደብ የሚያወጣውን ህግ አምኖ መቀበልና፣ ከዚህ ሌላ አማራጭ ነገር እንደሌለ ሲከራከሩና ለማሳመን ሲጥሩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ፣ በተለይም ፕላቶ በሶክራተስ በመመሰል ይሉት የነበረው የጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀር ለመረዳት ከነበረው ሁኔታ አልፎ(Trnascedental) መሄድና መመርመር እንደሚያስፈልግ ያመለክቱ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ሶፊስቶች ኃይልንና ለስልጣን መስገብገብን ትክክል ነው ብለው ሲሰብኩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ጉዞ እጅግ አደገኛ እንደሆነና፣ የመጨረሻ መጨረሻም አንድ ህብረተሰብ ሊወጣ የማይችልበት ማጥ ውስጥ የሚከተው ነው ብለው በጥብቅ ያሳስቡ ነበር። ካሊክለስ የሚባለው አንደኛው የሶፊስቶች መሪ የእነሶክራተሰን በአርቆ አስተዋይነትና በሚዛናዊነት ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ ፍልስፍናን ሞኞች ብቻ ናቸው የሚከተሉት ብሎ በመስበክና በማንቋሸሽ፣ ፖለቲካ በስምምነት ላይ ሳይሆን በአሽናፊና በተሽናፊነት ላይ የተመረኮዘና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ኃይል ያለው ብቻ ነው ሊገዛ የሚችለው በማለት ሽንጡን ገትሮ ይከራከር ነበር። በተጨማሪም በሶፊስቶች ዕምነት አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና፣ ሁሉም ሰው ሊቀበለው የሚችለው ዕውነት ነገር የለም። ሁሉም ሰው አንድን ነገር እንደፈለገው ሊተረጉምና ሊረዳ ይችላል። ፕሮታጎራስ የሚባለው የሶፊቶች ሌላው መሪ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የዕውነት መለኪያ አለው፤ (Man is the Measure of Everything) አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው ዕውነት የለም በማለት የሶፊስቶችን የተሙለጨለጨ አመለካከት ያስተጋባ ነበር። በሶክራተስና በፕላቶ የፍልስፍና ዕምነት ግን ማንም ሰው ዓላማና ተግባር ሲኖረው፣ በመጀመሪያ ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር ነው የሚፈጠረው። ይሁናን ግን እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህች ዓለም ላይ ሲወረወር እንደየህብረተሰቡ ሁኔታ ከተፈጠረበት ዕውቀት ጋር እየራቀ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ነገሮች ርስ በራሳቸው እንደተያያዙና የተወሳሰቡ መሆናቸውን ይገነዘብ የነበረው ጭንቅላት፣ የተያያዙ ነገሮችን እየበጣጠሰ መመልከት ይጀምራል። ነገሮች ሁሉ ብዥ ይሉበታል። ዕውነትን ከውሽትን ለመለየት ይቸገራል። ከዚህም በላይ ለአንድ ችግር መነሻ የሆነውን ዋና ምክንያት ለመረዳት ችግር ውስጥ ይወድቃል። በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት ወደ ጥንቱ ሁኔታ ለመመለስ ማንኛውም ሰው ሀቀኛውን መንገድ ለመፈለግ የማያቋርጥ ትግል ማድረግ አለበት። እየመላለሰ ራሱን መጠየቅ አለበት። በቀላሉ በሚታዩ ነገሮች ላይ መማረክና እነሱን ትክክል ናቸው ብሎ መቀበል የለበትም። ስለሆነም፣ በሁለቱ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት ከመንፈስ ተነጥሎ የሚታየው አካል ነው። ሰዎች ራሳቸውን ለማጎልመስ ሲሉ በሆነው ባልሆነው ነገር ይታለላሉ። አስተሳሰባቸው በማቴርያል ነገር ላይ ሲጠመድ ስግብግብነትንና አብጦ መገኘትን፣ ሌላውን ሰው ደግሞ ማንቋሸሽና መናቅን እንደ ዋና የኑሮ ፍልስፍናቸው አድርገው ይመለከታሉ። ይህ ዐይነቱ አመለካከትና ከቆንጆ ስራ እየራቁ መሄድና በራስ ዓለም ውስጥ መኖርና መሽከርከር ለጦርነትና ለአንድ ህብረተሰብ መመሰቃቀል ምክንያት ነው ብለው ያስተምሩናል። በሌላ አነጋገር የሰዎች ንቃተ-ህሊና ዝቅ እያለ ሲሄድ፣ ወይንም ደግሞ 5 በተሳሳተ ኢንፎርሜሽንና ዕውቀት በሚመስል ነገር በሚጠመድበት ጊዜ እያንዳንዱ ግለሰብ የህብረተሰቡ አካል መሆኑን ይዘነጋል። እንደዛሬው ባለው ሁኔታ ደግሞ ሃይማኖትንና ጎሳነትን በማሰቀደም እያንዳንዱ ግለሰብ የእኔ ሃይማኖት ወይም ጎሳ ከሌላው ይበልጣል በማለት ሰብአዊነትን ከማስቀደም ይልቅ ወደ አለመተማመንና እንዲያም ሲል ወደ ርስ በርስ መጨራረስ ያመራል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ብልጥ ነን ለሚሉና ለስልጣንና ለገንዘብ በሚሽቀዳደሙ ጥቂት ኃይሎች እንደመሳሪያነት በማገልገል አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖርና፣ ድህነትና ረሃብ እጣው እንዲሆን ይደረጋል። በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር ወይም የዕውቀት ችግር ነው። ዕውነተኛ ዕውቀትን የምንጎናጸፈው ትምህርት ቤት በምንማረው ወይም እንደ ዳዊት ሸምድደን በምንደግመው ዐይነት የሚገለጽ አይደለም። በሁለቱም ዕምነት ሆነ ኋላ ብቅ ላሉት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች፣ ዕውነተኛ ዕውቀት ማለት ራሳችንን እንድናውቅ የሚያደርገን፣ ወደ ውስጥ ራሳችንን ለመመልከት እንድንችል ግፊት የሚያደርግብን፣ የበለጠ ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስችለን፣ የተፈጥሮን ህግጋት ጠለቅ ብለን እንድንረዳ የሚያስችለንና፣ በጥንቃቄም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በማውጣትና ቅርጻቸውን በመለወጥ እንድንጠቀምባቸው የሚያግዘን፣ ህብረተሰብን በስነ-ስርዓትና መልክ ባለው ሁኔታ እንድናደራጅ የሚረዳን፣ ከሰውነታችን ፍላጎት ይልቅ የመንፈስን የበላይነት በማረጋገጥ በመንፈስ ኃይል በመመራት ከሌላው ተመሳሳይ ወንድማችን ጋር ተሳስቦ መኖር መቻል፣ በፍጹም የራስን ጥቅም በማስቀደም ዓላማ አለመመራት...ወዘተ. ናቸው። ለተንኮልና ለምቀኝነት ተገዢ አለመሆንና ወደ ብጥብጥ አለማምራትና፣ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን አለማዘጋጀት፣ የማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር ጥረት አርቆ በማሰብ ኃይል በመመራት ወደ እግዚአብሄር ለመጠጋት መጣር ነው። በፕላቶ ዕምነት ሌላው ለአንድ ህብረተሰብ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ወይም ለጦርነት ምክንያት የሚሆኑ ከሰብአዊነትና ከወንድማማችነት ይልቅ የብሄረ-ሰብ/ጎሳ አድልዎነት(Ethnic Solidarity) ምልክት የሆኑ ቅስቀሳዎች ቦታ ከተሰጣቸው ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለሚከሰት ችግር ዋናው ምክንያት የተለያዩ ብሄረሰቦች በመኖራቸው፣ ወይም አንደኛው ብሄረሰብ በሌላው ላይ ጫና ስለሚያደርግ ሳይሆን፣ በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ራሳቸው በሚፈጥሩት ልዩነትና ስልጣን ላይ ለመቆየትና ህዝቡን አደንቁረው ለዘለዓለም ለመግዛት እንዲችሉ የብሄረሰብን ጥያቄንና ሃይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ሳይንሳዊውንና የስልጣኔውን ፈር ያሳስታሉ። ስለዚህም ለአንድ ህብረተሰብ ችግር ዋናው መፍትሄ እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌላው የማይበልጥ መሆኑን ሲረዳና፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ብሄረሰቦች መኖር የታሪካዊ ግዴታ እንጂ እንደክፋት መታየት የሌለባቸው መሆኑን ሲገነዘብ ነው። የእያንዳንዱም ግለሰብ ግንዛቤ የሰውን ልጅ ሁኔታ ልክ እንደተፈጥሮ ህግ መረዳት ሲሆን፣ ተፈጥሮ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች፣ ለምሳሌ የተለያዩ አበባዎች፣ የተለያዩ ዛፎችና የተለያዩ ከብቶች መኖር የተፈጥሮን ውበት እንደሚያመለክቱና፣ የተፈጥሮም ግዴታ የሆኑትን ያህል፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ ጥቁርና ቀይ መልክ ያለው ሰው፣ ረዥምና አጭር ሰው... ወዘተ. መኖር እንደ ውበት መታየት ያለባቸው ነገሮች እንጂ መበላለጥን የሚያረጋግጡ አይደሉም። ስለሆነም ልዩ ልዩ ነገርችና አንድነት(unity in muliplicity) እዚያው በዚያው መኖር የተፈጥሮ ህግጋት መሆናቸውን በመረዳት ልዩነት ለጠብ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እንደመሰረተ ሃሳብ መወሰድ ያለበት መመሪያ ነው። ስለዚህም በአንድ ህብረተስብ ውስጥ የሚከሰቱ ብጥብጦች የተፈጥሮን ውስብስብነትና ውበት ለመረዳት ካለመቻልና ጠለቅ ብሎ ለማየት ካለመፈለግ የተነሳ ወይም በተሳሳተ ዕውቀት በመመራት አንድን ህብረተሰብ ለመግዛት መቻኮል ነው። ለዚሁ ሁሉ መፍትሄው ይላል ፕላቶ፣ ማንኛውም ግለሰብ አርቆ አሳቢነትን በማስቀደም በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ ለመግንባት መጣር አለበት። ማንኛውም ግለሰብ ይህንን የዩኒቨርስ ህግ ሲረዳና ስምምነትንና ስርዓትን(Harmony and Order) በጭንቅላቱ ውስጥ ሲቀርጽ በምድር ላይ ዕውነተኛውን ገነት ይመሰርታል ይላል። 6 ወደድንም ጠላንም ከብዙ ሺህ ዐመታት ጀምሮ በዓለም ላይ የተከሰቱ የርስ በርስ መተላለቆች፣ በአገሮች መሀከል የተካሄዱ ጦርነቶች፣ ረሀብና የወረርሽኝ በሽታዎች፣ በዘመነ- ሳይንስ እሰካዛሬም ድረስ ዘልቆ ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የሚያምሰውና፣ የአንድ አገር ህዝብ እየተሰደደ እንዲኖር የሚያደርግ፣ ጊዜ ያመጣላቸው ኃይሎች ድንበር እየጣሱ የሌላውን አገር የሚወሩ፣ እነ ሶክራተስና ፕላቶ ከፈለሰፉት የሰብአዊነት(Rational Humanism) ይልቅ ሳይንሳዊ „አርቆ-አሳቢነትን“(Scientific Rationalism) በማስቀደምና በበላይነት በመመካት ነው። ለምሳሌ ሜስትሮቪክ „The Barbarian Temperament“ በሚለው እጅግ ግሩም መጽሀፉ ውስጥ የሚያረጋግጠው፣ በሃያኛውና በሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን የምዕራቡ ዓለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቢራቀቀም፣ እንዲሁም ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲን አስፍኛለሁ ቢልም የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን፣ የኬሚካልና የባዮሎጂ መርዞችን በመስራት በሚያስፈልገው ጊዜ ጠላቴ ነው በሚለው ላይ እንደሚበትንና፣ ብዙ ሺህ ህዝቦችን መጨረስ እንደሚችል ነው። ይህ ዐይነቱ ዕልቂት በፋሺዝም ዘመን በጉልህ የታየና የተረጋገጠ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት እንደገና ሊከሰት የሚችልበትም ሁኔታ አለ። በኢራቅ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ፣ በየቀኑ በአፍጋኒስታን ህዝብ ላይ የሚደርሰው ዕልቂት፣ ከአራት ዐመት በፊት ደግሞ አንድን አምባገነን ገዢ አዳክማለሁ ወይም ጥላለሁ ብሎ በዚያውም አሳቦ በሊቢያ ህዝብ ላይ የወረደው የቦንብ ናዳ የምዕራቡን ዕውነተኛ ገጽታ የሚያሳየን ነው። እንደዚሁም ከአራት ዐመት ጀምሮ በውጭ ኃይሎች በተጠነሰሰ ሴራና በገንዘብና በመሳሪያ በመደገፍ በሶሪያ ህዝብ ላይ የደረሰውና የሚደርሰው ዕልቂትና የታሪክ ቅርስ መፈራረስ በዘይት ሀብትና በመሳሪያ እንዲሁም በስልጣን በተመኩና ስልጣንን መባለጊያ ባደረጉ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አማካይነት ነው። በአሜሪካ የኒዎ-ኮም(Neo-Com) አራማጆችም ሆነ በጠቅላላው የአሜሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪና የኢንተለጀንስ ኤሊት ዘንድ ያለው ስምምነት ዓለምን ለመግዛት ከተፈለገና፣ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ ህብረተሰብ እንዳይገነቡ ከተፈለገ የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ እርስ በርሳቸው ማጫረስ ነው የሚል ነው። ይህንንም በገሃድ ይናገራሉ። ከዚህም ስንነሳ ጠቅላላው የአሜሪካ የፖለቲካ ኤሊት ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ቢኖረው ኖሮና፣ ስልጣኔንም ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ የፖለቲካ ስሌቱ የተለየ መሆን ነበረበት። በኢራቅ፣ በሊቢያና በሶሪያ አገሮች አምባገነን አገዛዞች ቢኖሩም፣ የእነዚህን አገዛዞች አስተሳሰብ መቀየርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን የሚቻለው ጥቂት ኃይሎች እንዲያምጹ እነሱን በመርዳት ሳይሆን የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ ብቻ ነበር። በሌላ አነጋገር መሆን የነበረበት የፖለቲካ ስሌት እነዚህ አምባገነን አገዛዞች የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲያራምዱ ማስተማር ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ ሀብረተሰብ ውስጥ አምባገነናዊ አገዛዝ አለ ከተባለ ከውስጥ በሚደረግ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ግፊት ብቻ ነው ሁኔታዎችን መለወጥ የሚቻለው። እንደምናየው የውጭ አገሮች ጣልቃገብነት በሶስቱም አገሮች የነበረውን ሁኔታ የበለጠውን አዘበራረቀው እንጂ መሻሻልን በማምጣት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን አላደረገም። ስለሆነም በእንደዚህ ዐይነቱ ቅጥ ያጣ የቦምብ ውርጅብኝ እነዚህ አገሮች እንደገና በእግራቸው ሊቆሙ ወደማይችሉብት ሁኔታ ወስጥ መወርወር ቻሉ። ሃምሳና ስድሳ ዐመታት ያህል የሰሯቸው ስራዎች፣ የገነቧቸው ከተማዎችና የመሰረቷቸው ህብረተሰቦች ከፈራረሱና ከተመሰቃቀሉ በኋላ እንደገና እነሱን መልሶ ለመገንባት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። የህዝቡም አቅም የሚፈቅድና አስተሳሰቡም የተዳከመ ስለሆነ ህልሙ ከቀን ተቀን ችግር አልፎ ህብረተሰብአዊ ግንባታ ላይ ሊያተኩር አይችልም።፡ በሌላ ወገን ደግሞ የሰለጠንኩኝ ነኝ የሚለውን የምዕራቡን የካፒታሊስት የገዢ መደቦችና ጠቅላላውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖኢና የሚሊታሪ ኤሊት ተንኮል የማይረዱ የሶስተኛው ዓለም አገዛዞችና መንግስታት የማያስፈልግ ቀዳዳ በመስጠት ሁኔታውን ያባብሱታል። የኢራቅ፣ የሊቢያና የሶሪያ አገዛዞቹ ብልሆች ቢሆኑ ኖር ከውስጥ ተቃውሞ ሲነሳ ነገሩ እንዳይባባስ በውይይትና በስምምነት መፍታት በቻሉ ነበር። በፖለቲካ ጥበብ ያልተካኑት እነዚህ መሪዎች ግን ነገሩን ረገብ ለማድረግ ከመሯሯጥ ይልቅ የእልክ ፖለቲካ በመከተላቸው አገራቸው እንዲፈራርስና የብዙ መቶ ሺህ ሰው ህይወት እንዲጠፋ ለማድረግ በቁ። በዚህም 7 የተነሳ አንዳንድ ነፃ አውጭ ነኝ የሚሉ ድርጅቶች የማያስፈልግ እሳት እየጫሩ መጨረሻ ላይ ማቆም የማይቻል እሳት እየሆነ በመምጣት ታሪክን አውዳሚና ህዝብን ጨራሽ ለመሆን በቅቷል። የዚህ ሁሉ ችግር ዋናው ምንጭ ምንድነው? ቢያንስ ባለፉት 70 ዐመታት የዓለምን ፖለቲካ የሚቆጣጠረው የምዕራቡ ዓለም ስለዲሞክራሲ ይዘትና አመለካከት ያለው አካሄድና ግንዛቤ ለየት ያለ መሆኑን ነው። የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ቢኖራቸውም ዕድገታቸውና ተቀባይነታቸው እንደየአገሮቹ ታሪክ፣ ህብረተሰብ አወቃቀርና የማቴሪያል ሁኔታና እንዲሁም ንቃት-ህሊና የሚወሰን ነው። ዲሞክራሲን ከላይ ወደ ታች ወይም በጠብመንጃ ኃይል የሚተከል ሳይሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከንቃተ-ህሊና ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። ችግሩ ግን የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም አካሄድ ዲሞክራሲን በየአገሮች ውስጥ ለማስፈን ሳይሆን እንዴት አድርጌ አገሮችን አተረማምሳለሁ የሚል ነው። የዕድገት ሂደታቸውን አዛባለሁ የሚል ነው አካሄዱና የፖለቲካ ስሌቱ። የዚህ ሁሉ ችግር ታላቁ ሺለር እንደሚለን፣ የሰው ልጅ ከአርስቲቶለስ ጀምሮ ዲሞክራሲ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ሰምቷል፤ ሆኖም ግን በመሰረቱ ከአረመኔ ባህርዩ አልተላቀቀም። ፍሪድርሽ ሺለር፣ „ታሪክ ማለት ምን ማለት ነው፣ ለምንስ ዓላማ የዓለምን ታሪክ ማጥናት አለብን“ በሚለው እጅግ ግሩም ስራው ውሰጥ የሰውን ልጅ እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ከመረመርና፣ የግሪክን ስልጣኔና የአውሮፓን የህብረተሰብ ታሪክ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ፣ የሰው ልጅ ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረውና ታሪክን እንዲሰራ ከፈለገ የግዴታ ውጣ ውረድን ማሳለፍና ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ መስራት እንዳለበት በጥብቅ ያሳስባል። ይሁንና ግን የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ሰብአዊነትን ሊጎናፀፍ የሚችለው መንፈሱን ከልቡ ጋር ያገናኘ እንደሆነ ብቻ ነው ይላል። ሺለር እንደዚህ ዐይነቱ ድምደማ ላይ የደረሰው በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥ በፕሮቴስታንትና በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የተለኮሰውንና፣ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት የሆነውን ሰላሳ ዐመት ያህል የፈጀውን ጦርነት በሰፊው ከመረመረና፣ የመሪዎችን የተሳሳተ ፖለቲካ በጥልቀት ካጠና በኋላ ነው። በአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመንም በጣሊያን ሰፍኖ የነበረውም ሁኔታ የሚያረጋግጠው የአሪስቶክራሲውንና የቀሳውስቱን ቅጥ ያጣ ፖለቲካና፣ ህዝቡም ራሱን በራሱ ማግኘት አቅቶት የሆነ ያልሆነውን የሚሰራበት ወቅት ነበር። አንድ ህዝቡን የሚያግባባ ቋንቋ ባለመኖሩም ለስራና ለሃሳብ ልውውጥ የማያመችና ለስልጣኔ እንቅፋት የሆነበት ወቅት ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳና በገዢ መደቦች ቅጥ ያጣ ኑሮ ህዝቡ በረሃብ፣ በድህነትና በልዩ ልዩ በሽታዎች ይሰቃይና ህይወቱ ይቀሰፍ ነበር። ይህንን በጥብቅ የተከታተለው ዳንቴ በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ህዝቡን የሚያግባባ ቋንቋ ይፈጥራል። ቀጥሎም የአምላኮች ኮሜዲ በመባል የሚታወቀውን ትልቁን የሌትሬቸር ስራ በመጻፍ፣ አንድ ህዝብ እንዴት አድርጎ ከጨለማ ኑሮው ተላቆ የብርሃኑን ዓለም እንደሚጎናጸፍ ያመለክታል። ዳንቴ በዚህ ስራው ለተከታዩ ትውልድ መነሻ የሚሆን ትልቅ ስራ ሰርቶ ያልፋል። በመሆኑም ሬናሳንስ የሚባለው የግሪኩን ዕውቀት እንደገና ማግኘትና ከጊዜው ሁኔታ ጋር ማቀናጀት የተጀመረው እነዳንቴ በቀደዱት የብርሃን መንገድ አማካይነት ነው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት ጭንቅላትን ለማደስና፣ ከኋላ ቀር አስተሳሰቦች ለመላቀቅ፣ ፍልስፍናን፣ ሳይንስን፣ ጥበብን፣ ግጥምንና አርክቴክቸርን የጭንቅላት ተሃድሶ መመሪያ ማድረግ ለአንድ ህዝብ ስልጣኔን መስራትና ተስማምቶ መኖር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር የዳንቴ ስራዎችና በሬናሳንስ ዘመን ተግባራዊ የሆነው ስልጣኔ ያረጋግጣል። ስለዚህም አንድ ግለሰብም ሆነ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለውና፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስም ተፈጥሮን በመቆጣጠር፣ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለራሱ መጠቀሚያ በማድረግ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊሽጋገር የሚችለው፣ የሬናሳንስ ወይም የግሪኩን ፍልስፍናና፣ በኋላ ደግሞ የጀርመን አይዲያሊስቶች፣ማለትም ሺለር፣ ጎተ፣ኸርደር፣ ዊንክልማንና፣ በተጨማሪም ላይብኒዝና ካንት ያዳበሩትን ፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት መመሪያ ማድረግ የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው። 8 ከዚህ ስንነሳ ማቅረብ ያለብን ጥያቄ፣ በተለይም አገርን አስተዳድራለሁ የሚል አንድ መሪ ወይም አገዛዝ እንዴት አድርጎ ነው ጭንቅላቱን በአዲስ ዕውቀት በማነፅ ህብረተሰብአዊ ስምምነትና ስርዓት እንዲፈጠር የሚያደርገው? እንዴትስ አድርጎ ነው ቆንጆ አስተሳሰብን ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ የራሱን ጥቅም ሳያስቀድምና አድልዎን የፖለቲካ ዘይቤው ሳያደርግ፣ እንዲሁም ደግሞ የርዕዮተ-ዓለም ሰለባ ሳይሆን አገር ማስተዳደር የሚችለው? እንዴትስ ለስልጣኔና ለቆንጆ ስራዎች ታጥቆ ሊነሳ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር እንመልከት። በብዙዎቻችን ዕምነት ትምህርት ቤት የተማረና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ኢኮኖሚክስም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት አጠናቆ በማስትሬት ወይም በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ አገርን በስነስርዓት ማስተዳደርና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ሚዛናዊ ዕድገት በማምጣት በስልጣኔ እንድትታወቅና ህዝቦቿም በደስታና በስምምነት እንዲኖሩ ሊያደርግ የሚችል ይመስለን ይሆናል። የሶክራተስን፣ የፕላቶንና፣ እንዲሁም በኋላ የተነሱትን፣ ሃይማኖትን ከፍልስፍና ጋር በማጣመር በአውሮፓ ምድር ስልጣኔ እንደገና እንዲያንሰራራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉትን የታላላቅ ቀሳውስት ስራዎች ስንመለከት፣ እንዲሁም ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በኋላ ብቅ ብቅ ያሉትን ሳይንቲስቶችንና ለሰው ልጅ ያስተላለፉትን ዕውቀት ስንመረምር፣ በግጥምና በቲያትር እንዲሁም የፖለቲካ ተዋንያንን አእምሮ በፍልስፍና ለመቅረጽ የታገሉትን እንደ ሺለር፣ ላይብኒዝና ካንት እንዲሁም ጎተን ስራዎች ስንመለከት እኛ ትምህርት ቤት ገብተን የተማርነው ትምህርት፣ ከነዚህ ጠቢባን ጋር በፍጹም የሚጣጣሙ አይደሉም። ከነዚህ የፍልስፍና ምሁራንና ሳይንቲስቶች ጽሁፎች መገንዘብና መማር የምንችለው በአንድ አገር ውስጥ ስልጣኔ ማምጣት ከተፈለገና ህዝቡም በስምምነት እንዲኖር ከተፈለገ የግዴታ የማያቋርጥ ትግል ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ነው። ስለዚህም ልክ እንደ ግሪክ ፈላስፋዎች ኋላ ላይ ብቅ ያሉት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ለሌላ ነገር ሳይሆን ለአዕምሮና መንፈስ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ምርምራቸውን አካሄዱ። በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ አዕምሮ/መንፈስ ጥሩ ወይም መጥፎ አስተሳሰብ ይዞ ሊቀረጽ ይችላል። ጥሩ አስተዳደግ ካለውና አዕምሮው በጥሩ ዕውቀት የተገነባ ከሆነ ሰብአዊ ባህርይ ሊኖረውና ታሪክንም ሊሰራ ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሰው በልጅነቱ በጥሩ ሁኔታ ካልተያዘና ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት ካልተገራ ሃሳቡና ተግባሩ ተንኮልን ማውጠንጠንና የታሪክን ሂደት ማጣመም ይሆናል። ይሁንና ግን አንድ ሰው ራሱን በራሱ ለማግኘት ከፈለገ ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት የተገራውም ሆነ የተዛባ አስተሳሰብ ያዳበረው በየጊዜው የጭንቅላት ጂምናስቲክ መስራት አለባቸው። የሰው ልጅ አስተሳሰብ የሚለዋወጥ በመሆኑ አርቆ አሳቢ የሆነውም ቢሆን አልፎ አልፎ ኢራሽናል ስለሚሆን ወደ መጥፎ ተግባር እንዳያመራ ከፈለገ ሰውነቱ ጂምናስቲክ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጭንቅላቱም በስራ መወጠር አለበት። ስለዚህም አንድ ግለሰብም ሆነ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ታሪክን ይሰሩ ዘንድ ራሳቸውን ከጥሩ ነገር ጋር ማገናኘት መቻል አለባቸው። ከአንድ አካባቢ የሚመጡ ግፊቶችን ለመቋቋም የሚችሉና በክርክር ለማሳመንና ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ የማያቋርጥ ትግል ማድረግ አለባቸው። ለዚህም ደግሞ በተከታታይ ደቀ-መዝሙራንን ማስለጠን በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የተለመደ አሰራር ነበር። እንደኛ አገር ያለው ጋ ስንመጣ ተከታታይነት ያለው ሃሳብ ማዳበር ያለመቻልና ደቀ-መዝሙሮችንም አለማሰልጠንና ዝግጁም አለመሆን ነው። ከዚህ ስንነሳ በዛሬው የግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን አንድ ሰው ቀና አስተሳሰብ ቢኖረውምና ለስልጣኔ የቆመ ቢሆንም ባለው የላላና የሳሳ ምሁራዊ ኃይል ምክንያት ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ሊቋቋም የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በአካባቢውም ተንሸራታች ኃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሳይወድ በግድ ስልጣኔን የሚቀናቀነውን ሬል ፖለቲካ የሚባለውን እንዲቀበልና እንዲያራምድ ይገደዳል። ይህም ማለት ዕውነተኛ ዕውቀትና ሀቀኝነት በራሳቸው የሚበቁ 9 መመዘኛዎች አይደሉም። ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ለመቋቋም ዋናው መፍትሄ በራስ መተማመንና ለውጭ ኃይል መግቢያ ቀዳዳ አለመስጠት ነው። ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች የሚሰሩትን የሚያውቁና ለአንድ ዓላማ የተሰለፉና በአንድ ራዕይ የሚመሩ መሆን አለባቸው። ከዚህ በሻገር በአገር ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ሊንቀሳቀስ የሚችል ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይል እንዲሰለጥን አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ትችታዊ አመለካከት በዳበረበት አገርና፣ ምሁሩም ለውጭ ኃይል ሳይሆን ለአገሩ ህዝብ ብቻ ጥብቅና የቆመ መሆኑን በሚያረጋግጥበት አገርና ህዝቡንም የሚያስተምር ከሆነ የውጭ ኃይሎች እንደፈለጋቸው እየገቡ ሊያሳስቱና በአገዛዛዙ ላይ ግፊት ሊያደርጉ አይችሉም። በሌላ ወገን ግን ዛሬ በሁላችንም ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ሁላችንን ሊያስማማንና እንደመመሪያ ሊሆነን የሚችል ፍልስፍናና ራዕይ አለመኖሩ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች ነን የሚሉትም ሆነ ለመጽሄትም ሆነ ለድህረ-ገጾች በየጊዜው በተለያዩ አርዕስቶች ላይ የሚጽፉ ምሁራን እንደፈለጋቸው የሚጽፉ እንጂ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መለኪያን እንደመመርኮዢያ በማድረግ አይደለም ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሞክሩት። ስለሆነም በየጊዜው የሚቀርቡት ጽሁፎች ከምን ተነስተው እንደሚጻፉ አይታወቅም። አቀራረቦችም በጣም ተደጋጋሚ ከመሆናቸው የተነሳ በአገራችን ምድር ያለውን የህዝባችንን የቀን ተቀን ኑሮ የሚዳስሱና የችግሮችንንም ዋና ምክንያቶች እንድንረዳና መፍትሄም እንድንፈልግ የሚጋብዙን አይደሉም። ሁሉም የፈለገውን የሚጽፍ ከሆነና ራሱን እንደመለኪያ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ደግሞ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ሶፊስታዊ ነው የሚሆነው። ስለዚህም ነው ሶክረተስና ፕላቶ እንደዚህ ዐይነቱን አመለካከትና አካሄድ አጥብቀው የታገሉት። ምክንያቱም እያንዳንዱ ምሁር ራሱን እንደዋና መለኪያ የሚቆጥርና፣ ከሌላውም የተለየ መሆኑን ለማረጋግጥ የሚጥር ከሆነ አንድን ህዝብም ሆነ ታዳጊ ወጣት ሃሳቡን ሊሰበስብለትና እንደመመሪያም አድርጎ ሊወስደው የሚችለው ሳይንሳዊ ፈለግ አይኖረውም ማለት ነው። ስለሆነም ለአንድ አገርና ህዝብ እታገላለሁ የሚል ምሁር ኃላፊነቱ ተጨባጩን ሁኔታ በጥልቀትም ሆነ በስፋት መረዳት ብቻ ሳይሆን ችግሩ ሊቀረፍ የሚችልበትን ዘዴ መጠቆም ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ የሚመራበት ግልጽ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴ እንዲኖረው ያስፈልጋል። እኔ እስከማውቀው ድረስም በአውሮፓ የህብረተሰብ ትግል ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ ምሁር፣ ምሁር ነኝ ብሎ ዝም ብሎ ይታገል የነበረ ሳይሆን በምን ዐይነት ፍልስፍናና ነው በጊዜው የነበረውን ችግር መረዳትና መፍትሄስ ማግኘት የሚቻለው ብሎ ነበር ራሱን ያስጭንቅ የነበረው። በዚህም ምክንያት ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍልስፍናዊ አመለካከት ስር ሊሰድ የቻለውና፣ አገሮችም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተወሳሰበ፣ የጠራና ግልጽ የሆነ ህብረተሰብ መገንባት የቻሉት። ሌላው በአገራችንም ሆነ ውጭ አገር በኢትዮጵያዊ ኮሙኒቲ ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር አካዳሚክ ዕውቀትን ሰፋ ካለው ምሁራዊ ዕውቅት ነጥሎ ለማየት አለመቻል ነው። ሁሉም ሰው ትምህርትን ለመቅሰም የሚያስችለው ውስጣዊ ኢንተለጀንስ ቢኖረውም፣ ምሁራዊነትንና(Intellectualism)ሎጂካዊ አስተሳሰብን ሊጎናጸፍ የሚችለው ስርዓት ያለው ጥናት(systematic reading)ሲያካሂድና፣ በምድር ላይ የሚታየውን ነገር ለመረዳት ራሱን ሲያስጨንቅ ነው። ለዚህ ነው አብዛኛውን ጊዜ በንጹህ አካዳሚ ትምህርት የሰለጠኑ ሰዎች በምድር ላይ ያለውን ነገር በሚገባ ማንበብ የማይችሉትና የችግሩንም ዋና ምንጭ ለመረዳት የሚያስችል መሳሪያ የማይኖራቸው። ስለሆነም አንድ ሰው በትምህርት ጎበዝ ቢሆን እንኳ የስልጣኔ ትርጉምን እስካልተረዳ ድረስና፣ ለስልጣኔና ለእኩልነትም ሽንጡን ገትሮ ሊታገል እስካልቻለ ድረስ ለህብረተሰብ ግንባታ የሚያደርገው አስትዋፅዖ ከቁጥር ውስጥ የሚገባ አይሆንም። አንድ ወጥ አስተሳሰብ ይዞ ያደገ በመሆኑም የአንድን ነገር ሂደት ከሁሉም አቅጣጫ የመመርመርና የማመዛዘን ኃይል ሊኖረው በፍጹም አይችልም። እንደዚህ ዐይነቱ ሰው ከራሱ ጥቅም ተሻግሮ የዕውነት ጠበቃ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ስለሆነም አንድ ሰው በዚህ ወይም በዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እመራለሁ ቢልም እንኳ ይህ ማለት ግን ቀናና ጥሩ ሰው፣ ወይም 10 ደግሞ ምሁራዊ ኃይል ያለውና ከተንኮል የጸዳ ነው ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ርዕዮተ- ዓለም ሽፋን እንጂ የአንድን ሰው ምንነት መግልጫ አይደለም። አንድ ሰው ማርክሲስት ነኝ ወይም ሊበራል ነኝ ወይም ደግሞ ይህንኛውን ወይም ያኛውን የፖለቲካ ዕምነትና ሃይማኖት እከተላለሁ ቢልም እነዚህ ሽፋኖች ድብቅ ዓላማውን የሚገልጹ ወይም ማንነቱን የሚያሳዩ አይደሉም። ወይም አንድ ሰው ሊበራል ነኝ ስላለ የተቀደሰ ዓላማ፣ ማርክሲስት ነኝ የሚለው ደግሞ የሰይጣን ዓላማ አለው ማለት አይደለም። እነዚህ ዐይነቱ ግለሰቦች በተናጠልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅተው ለዚህ ወይም ለዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እንታገላለን ቢሉም የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገሉባቸው መሳሪያዎች እንጂ በራሳቸው ዕውነተኛ ስልጣኔ አጎናጻፊ አይደሉም። እንዲያውም የዕውነተኛውን የስልጣኔ መንገድ የሚያደናቅፉና ወደ ሌላ ውዝግብ ውስጥ የሚከቱን ናቸው። ዛሬ በንጹህ የካፒታሊዝም ሊበራል ስርዓት ውስጥ እያለን እንኳ ዓለም ወደ ሰላም እያመራች አይደለችም፤ እንደምናየው የዓለም ህዝብም ብልጽግናን እያየ አይደለም። ጦርነትና ድህነት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሀብት ዘረፋና በጥቂት ሰዎች እጅ የሀብት ክምችት የሰው ልጅ እጣ ሆነዋል። በየአገሮችም ውስጥ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ የመከሰቱ ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ የየመንግስታቱ ሚና ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግና ህዝብን ማሳሳትና አትኩሮውን ወደ ውጭ ማድረግ ነው። እዚህ ላይ መቅረብ ያለበት ጥያቄ የምዕራቡ ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣ በኋላ ለምንድነው አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ ዕጣ ጦርነትና መፈናቀል፣ እንዲሁም መበዝበዝ የሆነው? ካፒታሊዝም ከፊዩዳሊዝም ጋር ሲወዳደር ተራማጅ ስርዓት ቢሆንምና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ቢታይበትም፣ ከ17ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ እያለ የበላይነትን እየተቀዳጀ የመጣው ኢምፔሪሲስታዊ ወይም ሶፊስታዊ አስተሳሰብ የየመንግስታቱ መመሪያ ሆነ። በመሆኑም ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ሰብአዊነትን ሙሉ በሙሉ ለማስፈን የተደረገውን ትግልና አስተሳሰብ በመደምሰስ በነፃ ገበያ ስም የሚመራን፣ የአንድን ህዝብ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ወደ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚቀይር ርዕዮተ-ዓለም በማዳበርና በማስፋፋት ካፒታሊዝም የበላይነትን ተቀዳጀ። የሰው ልጅም ኑሮ ንጹህ በንጹህ ኢኮኖሚያዊ ነው የሚለውን በማስፋፋት፣ የኑሮው ፍልስፍናም ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊና ስነ-ምግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ በቃ። በዚህ ምክንያት በሰብአዊነት ፈንታ የብዝበዛ ስርዓት ሊፈጠር ቻለ። ይህ ሁኔታ ከሰላሳኛው ዐመት ጦርነት በኋላ በ1648 ዓ.ም በዌስት ፋልያ ላይ የየአገሮችን ነፃነት የሚያውቅ ስምምነት ሲደረስበትና ተቀባይነትን ሲያገኝ፣ በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የብሄረተኝነት ስሜት ማየል ጀመረ። ከውስጥ የአገርን ኢኮኖሚ በሰፊ መሰረት መገንባትና ወደ ውጭ ደግሞ ያላደጉ አገሮችን የጥሬ ሃብት አምራች አገሮችና አቅራቢዎች የሚሆኑበትን ሁኔታ ታለመ። በተለያዩ አውሮፓ አገሮች መሀከል እሽቅድምደም በመጀመር የሶስተኛው ዓለም አገሮች በካፒታሊዝም ሎጂክ ውስጥ ሊገቡና እጣቸውም በዚያው የሚወሰን እንዲሆን ተደረገ። ከዚህ አጭር ትንተናና በመነሳት ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአሽናፊነት የወጣውንና እየተወሳሰበ የመጣውን ካፒታሊዝም በተለይም በአፍሪካ አህጉር ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖና እስካሁን ድረስም አላላቅቅ ያለንን የጭቆና፣ የብዝበዛና እንዲሁም የምስቅልቅል ሁኔታ የፈጠረብንን ስርዓት ጠጋ ብለን እንመልከት። ከአስራስምንተኛው ክፍለ- ዘመን ጀምሮ ካፒታሊዝም የበላይነትን እየተቀዳጀ ሲመጣ የስልጣኔው ፕሮጀክት እየተደመሰሰና የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ፣ በተለይም የአፍሪካ ሁኔታ እየተበላሽና እየተዘበራረቀ ይመጣል። የካፒታሊዝም ተልዕኮ በዓለምአቀፍ ደረጃ ስልጣኔን ማስፋፋት ሳይሆን በጉልበት ላይና በስግብግብነት እንዲሁም በማጭበርበር ላይ በመመርኮዝ በተለይም የአፍሪካን አህጉር ንጹህ የጥሬ ሀብት አምራችና አቅራቢ ማድረግ ነበር ዋናው ፕሮጀክቱ። በመጀመሪያ በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የባርያን ንግድ ማስፋፋት፣ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የቅኝ ግዛት አስተዳደር በመመስረት ከውስጥ ቀስ በቀስ እያለ የሚያድግ ስርዓት እንዳይፈጠር 11 ሁኔታውን ያዘባራርቃል። በተለይም በቅኝ ግዛት ዘመን የተቋቋሙት አስተዳደሮች ከቅኝ ገዢዎች አገሮች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ወደ ውስጥ የስራ ክፍፍል እንዳይዳብርና የውስጥ ገበያም እንዳይስፋፋ እንቅፋት ይፈጥራል። ወደ ቅኝ ግዛትነት የተለወጡ አገሮችም የተወሰኑ የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት ማውጣትና ማምረት፣ እንዲሁም ውጤቱንም ወደ ውጭ መላክ ስለነበረባቸው በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የስራ ክፍፍል በማዳበር ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ ገበያ ለመገንባት እንዳይችሉ ታገዱ። ይህ ሁኔታ በራሱ መንደሮችን፣ ትናንሽና ትላልቅ ከተማዎችን በስነስርዓት በመገንባት ወደ ህብረተሰብ እንዳይለወጡ እንቅፋት ሆነባቸው። የተተከሉትም የባቡር ሃዲዶች የጥሬ-ሀብት የሚወጣባቸውን ቦታዎች ከወደብ ጋር ማገናኘት ሰለነበር ወደ ውስጥ ህዝቡን የሚያስተሳስር የመመላለሻ መንገድና የባቡር ሃዲድ እንዳይሰራ ታገደ። በዚህም ምክንያት ህብረተሰብዊ ውህደት እንዳይፈጠር መሰረት በመጣል፣ በአንድ አገር ውስጥ ጎሳዎች በጎሳ ደረጃ ሊደራጁ የሚችሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታና፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ እንቅፋት የሆነን እንደ ስርዓት ሊቆጠር የማይችል ሁኔታን በመፍጠር የሰዎች አትኩሮ ጠባብ እንዲሆን ለማድረግ በቃ። ከፖለቲካ ነፃነት „መቀዳጀት“ ከ50ኛዎቹ ዐመታት መጨረሻና ከ60ሳዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የብዙ አፍሪካ አገሮች ዕድል በሌላና በረቀቀ መልክ ህብረተሰብአዊ ዝብርቅርቅነት የሚኖርበትና ብዝበዛው የሚቀጥልበት ሁኔታ በመፍጠር በየጊዜው የሚነሱ አገዛዞች አስተሳሰብ በትናንሽ ነገሮች እንዲጠመዱ ተገደዱ። አስተሳሰባቸው ብሄራዊ አጀንዳ እንዳይኖረው ተቆለፈ። የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውና ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ እንሸጋገራለን ያሉትን ደግሞ በመንግስት ግልበጣ አማካይነት በመጣል የአገዛዝ አለመረጋጋትና አለመተማመን ሊፈጠር ቻለ። ስልጣን ላይ የሚወጣው መሪ ከዚህ ወይም ከዚያኛው የምዕራብ አገር መንግስታት ጋር በማበርና ታዛዥ በመሆን አገሩን ሊገነባ እንዳይችል ተደረገ። በዚህ ላይ ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩት ኢንስቲቱሽኖችና፣ በአዲስ መልክ የተከሰተው የኃይል አሰላለፍ የብዙ አፍሪካ አገሮችን የወደፊት ዕድል የሚወስኑ ነበሩ። ከ1945 ዓ.ም በኋላ ሁለት ዐይነት የኃይል አሰላለፎች ቢከሰቱም፣ በመሰረቱ ግን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የካፒታሊስቱ ጎራ ነበር/ነውም ዓለምአቀፍ ኢንስቲቱሹኖችን በመቆጣጠር የአብዛኛዎቹን የሶስተኛው ዓለም አገሮችን፣ በተለይም ደግሞ የአፍሪካን ህዝብ ዕድል ይወስን የነበረውና ዛሬም የሚወስነው። በዚህ ላይ ደግሞ ዶላር ዋናው ዓለምአቀፋዊ የንግድ መገበያያና የሀብት ማከማቻ ገንዝብ በመሆኑ አብዛኛዎቹ አገሮች የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ሲሉ የግዴታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውን በተወሰነ መስክ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተገደዱ። በዚህም ምክንያት የአገር ውስጥ ገበያን ማዳበር ባለመቻላቸው በገንዘብና በምርት፣ እንዲሁም በገንዘብ አማካይነት የሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ውስን በመሆኑ፣ የየአገሮቹ የገንዘብ ኃይል ሊዳከም በቃ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ሊሆንና ተቀባይነትም ሊያገኝ የማይችል ሆነ። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር የገንዘብ ጥንካሬ ሊወሰን የሚችለው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ሲዳብርና፣ በየኢኮኖሚ መስኮችም መሀከል የንግድ ልውውጥ ሲኖርና፣ በዚህም አማካይነት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሽከረከረው ገንዘብ ፍጥነቱ ሲጨምር ነው። ከዚህም በላይ አንድ አገር ገንዘቧ ጠንካራና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በፋብሪካ የተፈበረከና ያለቀለት ምርት መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አገር ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ምርት የእርሻ ምርት ውጤት ወይም ያልተፈበረከ የጥሬ ሀብት ብቻ ከሆነ ገንዘቧ ደካማ ይሆናል፤ ተቀባይነትም አያገኝም። ከዚህ አጭር ትንተና ስንነሳ የካፒታሊዝም ውስጣዊ ሎጂክና እንቅስቃሴን መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ወደ ሌሎች ነገሮችም ስንመጣ አካሄዱ ለየት ያለ ቢመስልም ዋናው ባህርዩ ግን የበላይነትን(Dominanz) መቀዳጀት ነው። ይህም ማለት እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያንም ጨምሮ እንደ ነፃ አገር መታየት የለባቸውም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካርና በራሱ የሚተማመን ህብረተሰብ መገንባት የለባቸውም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ወደ ውስጥ ህብረተሰብአዊ ስምምነትና ውህደትን 12 ስለሚያመቻችና ብሄራዊ ስሜትን ስለሚያጠናክር የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርና ግፊት በማድረግ የየመንግስታቱ አጀንዳ አትኮሮአቸው በትናንሽ ነገር ላይ መጠመድ አለበት። እንዲያም ሲል ወደ ጦርነት እንዲያመራ ይደረጋል። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መፈጸሚያ በኋላ ሙሉ በሙሉ በአሽናፊነት የወጣው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተልዕኮው ህብረተሰቦችን ማዘበራረቅና፣ በህብረተሰቦች ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር ሁኔታውን ማመቻቸት ሆነ ተግባሩ። ለዚህ ደግሞ የትምህርት መስኩ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። የአንድን ሰው አእምሮ ስትቆጣጠረውና በገንዘብ ስትገዛው የህብረተሰቡንም አቅጣጫ ታዛንፋለህ። የስልጣኔውን መንገድ ሁሉ ታጨልምበታለህ። አብዛኛው ህዝብ የማሰብ ኃይሉ ሲዳከም በቀላሉ ወደ ባርነት ይለወጣል፤ በራሱ ላይ ዕምነት አይኖረውም። የዓለም ገበያና የዓለም ንግድ እንዲሁም ለዚህ እንዲያመች ተብሎ የረቀቀው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዋናው ዓላማቸው የብዙ አፍሪካ ህዝቦችን ዕድል በዚህ ዐይነት የካፒታሊስት ሎጂክ ውስጥ እንዲሽከረከሩ በማድረግ ለዝንተዓለም ባርያ አድርጎ ማስቀረት ነው። ለምሳሌ ለትምህርት ቤትና ለዩኒቨርሲቲ ተብሎ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀውን የኢኮኖሚክስ መማሪያ መጽሀፎችን ለተመለከተ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ተቀባይነት ያገኘ(Conventionalism or normative positivism) የመማሪያ መጽሀፍ በራሱ አርቀን እንዳናስብና የዕውነተኛውን ስልጣኔን ትርጉም እንዳንረዳ ሊያደርገን የቻለ ነው። ዕድገትንና ስልጣኔን ከህብረተሰብ አወቃቀርና ከታሪክ አንፃር፣ እንዲሁም የተለያዩ አገሮችን ልምድ መሰረት አድርጎ እንደመነሻና እንደመማሪያ ከመወሰድ ይልቅ፣ ርዕዮተ-ዓለምንና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅሞችን የሚያንፀባርቅ ትምህርት በመማር የታሪክ ወንጀል ተሰራ፤ እየተሰራም ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመለከት ግን ንፁህ የምርምርና የጭንቅላት ውጤት መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን። ኢኮኖሚክስ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ከፊዚክስ፣ ከኬሚስትሪና ከባዮሎጂ ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ ያላካተተ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የመጨረሻ መጨረሻ አገሮችን መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከታቸው። ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ ታሪክ ውስጥ መርካንትሊዝም፣ ፊዚዮክራሲ፣ በእነ አዳም ስሚዝና ፔቲ ኢንዲሁም ሪካርዶ የሚወከለው ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ ይህንን እያረመ ወይም እያስተካከለ የወጣው የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ፣ ከዚያ በኋላ ማርክሲዝምን በመቃወም የወጣው የማርጂናሊስት ወይም የኒዎ- ክላሲክል፣ ዛሬ ደግሞ ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ተብሎ የሚታወቀው፣ በእነ ሹምፔተር የሚወከለው ኢቮሉሺናሪ ኢኮኖሚክስ፣ በቬብለን ቶርስታይን የሚወከለው የኢንስቲቱሽን ኢኮኖሚክስ፣ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ ኢኮኖሚዎች የተገነቡበት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ፊዚካል ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚታወቀው በጣም ጠቃሚ ዕውቀት፣ እነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚክስ ዘርፎች ናቸው። ተማሪው ይህንን ሁሉ እንዳያውቅና፣ በተለይም ምዕራብ አውሮፓ የአደገበትን ምስጢር እንዳይገነዘብ በሃያኛው ክፍል-ዘመን በእነሳሙኤልሰንና በሌሎች የተደረሱት እንደ መመሪያ በመውሰድና እነሱን በመሸምደድ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የአፍሪካ ምሁራን ሊሳሳቱና ለየአገራቾቻው መቆርቆዝና ድህነት እንደ ዋና ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። ዛሬ በአፍሪካ ውስጥ ለሚታየው መዝረክረክና ድህነት ዋናው ምክንያት ፖሊሲ አውጭዎቹ ሳይሆኑ በመሰረቱ በርዕዮተ-ዓለም ላይ የተመሰረተው ለምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሚያመቸው የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንደመመሪያ በመወሰዱ ነው። ከዚህም በላይ በየአገሮቹ የሰፈነው መንግስታዊ አወቃቀርና የፖለቲካ ኤሊት ለዕድገትና ለስልጣኔ ሽንጡን ገትሮ እንዳይታገል በመኮላሸቱ በቀላሉ የዕድገትን ፈለግ ማጣመም ተቻለ። ኒዎ-ሊበራሎች የበላይነትን በመቀዳጀት ከዩኒቨርሲቲ አልፈው ኢንስቲቱሽኖችን ሁሉ በመቆጣጠር አብዛኛው ተማሪ ዐይኑን እንዳይከፍትና፣ የዕውነተኛ ዕድገትንና ስልጣኔን ትርጉም እንዳይረዳ ሊደረግ በቃ። ለዚህም ነው ሶክራተስ፣ ፕላቶና የእነሱን ፈለግ ይዘው የተነሱት ምሁራን ተቀባይነት ያገኘን ዕውቀት መሳይ ነገር አጥብቀው የታገሉት። ምክንያቱም ተቀባይነት ያገኘ ነገር ሁሉ ካለንበት ቦታ ርቀን እንዳንሄድ ያደርገናል። በማሰብ ኃይልና በኮመን ሴንስ ልንፈታ የምንችላቸውን ችግሮች እንዳንፈታ መንገዱን ሁሉ ይዘጋብናልና። 13 ዛሬ አገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳትና ምክንያቱንም ለመገንዘብ የምንፈልግ ከሆነ ከሞላ ጎደል የላይኛውን ትንተና ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያለብን ይመስለኛል። ሌላው ችግራችን ደግሞ የኛንም ሆነ የሌሎች አፍሪካ አገሮችን የተወሳሰበ ችግር ለመረዳት በሚሞከርበት ጊዜ አውሮፓውያን እስከ አስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የተጓዙበትን የምሁር ውይይትና ክርክር እንደልምድና ትምህርት አድርገን ለመውሰድ አንቃጣም። ያም ሆነ ይህ በአውሮፓ የህብረተሰህብ አወቃቀርና በአፍሪካ አገሮች የህብረተሰብ ሂደት መሀከል ያለውን ልዩነት ትንሽም ቢሆን ጠጋ ብለን እንመልከት። ይህ ዐይነቱ ግምገማ ከሞላ ጎደል ዛሬ ብዙ አፍሪካ አገሮች ለምን በዚህ ዐይነቱ የተመሰቃቀለና ደካማ የሆነ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ ለመገኘት እንደተገደዱ የተወሰነ ግንዛቤ ሊሰጥን የሚችል ይመስለኛል። አንደኛ፣ የብዙ አፍሪካ አገሮች ህብረተሰብ አወቃቀር ከብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ይለያል። አበዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በፊዩዳሊዝም ስርዓት ያላለፉ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አወሮፓው ህብረተሰብ የርዕዮተ-ዓለም ግጭት አልተካሄደባቸውም። ሁለተኛ፣ ብዙ የአፍሪካ ህብረተሰቦች ከሌላው ዓለም ጋር የነበራቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እጅግ የላላ ነበር። ለምሳሌ የግሪክ ስልጣኔ በአረቦችና በአይሁዲዎች አማካይነት ከግሪክ ቋንቋ ወደ ላቲን እየተተረጎመ ወደ አውሮፓ ሲገባና ሲስፋፋ፣ ብዙ አፍሪካ አገሮች ይህ ዕድል አላጋጠማቸውም። ሶሰተኛ፣ የብዙ ምዕራብ አውሮፓ የህብረተሰብ አወቃቀር በሩቅ ንግድ አማካይነት ሲበለጽግና ውስጠ-ኃይል በማግኘት ወደ ተሻለ የህብረተሰብ አወቃቃር ሲሸጋገር፣ አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ይህ ዐይነቱ ዕድል አላጋጠማቸውም። አራተኛ፣ በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በባርያ ንግድና፣ በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ በቅኝ አገዛዝ አማካይነት ህብረተሰብአዊ አወቃቀራቸው ይበላሻል። በማበብ ላይ የነበረው የስራ ክፍፍል ይኮላሻል። አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ለምዕራብ አውሮፓ ጥሬ-ሀብት አቅራቢ ብቻ እንዲሆኑ ይፈረድባቸዋል። ለዚህም የየመንግስታቱ አወቃቀር ወደ ውስጥ ዕድገትንና ስልጣኔን እንዳያመጣ ሆኖ ይዘጋጃል። አምስተኛ፣ ከቅኝ አገዛዝ መላቀቅ በኋላ በዓለም አቀፍ ላይ አዲስ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ የአፍሪካን ዕድገት የሚጻረር ነበር። ስደስተኛ፣ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓው ምድር ፍጻሜ ያገኘው ጦርነት ወደ አፍሪካና ወደ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ይሸጋገራል። አንጎላንንና ሞዛቢክን፣ ከብዙ ዐመታት ጀምሮ በኮንጎ/ዛየርና በማዕከለኛው አፍሪካ የሚካሄደውን ጦርነት ስንመረመር፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ጦርነት ፍጻሜን ሲያገኝና የተደላደለ ህብረተሰብ ሲመሰርቱ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ግን በጦርነት መድማት ነበረባቸው፤ አለባቸውም። አውሮፓውያን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሲበለጽጉ አፍሪካ በጦርነት መድማት አለባት፤ ህዝቦቿም የሰከነና የሰለጠነ ኑሮ መኖር የለባቸውም፤ መዋከብና መበዝበዝ ዕጣቸው መሆን አለብት። ሰባተኛ፣ ለዚህ ደግሞ ፍልስፍና አልባ የሆኑ መሪዎች እንደ አሻንጉሊት በየቦታው መቀመጥ ቻሉ። በተዋቀራላቸው የስለላ መሳሪያ፣ በሰለጠነላቸው ወታደርና የፖሊስ ሰራዊት አማካይነት ማንኛውንም ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማፈንና ብልጽግና እንዳይመጣ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረላቸው። በአገራችንና በሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋሙት የወታደር ተቋሞች፣ የስለላ መዋቅሮችና የፖሊስ ሰራዊት በመሰረቱ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ኃይል አሰላለፍ የሚያንፀባርቁና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት አጋዦችና ታዛዦች እንጂ ከየህብረተሰቦቻቸው ፍላጎት አንፃር ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እየተደራጁና ሲቪክ የሆነ ባህርይ እንዲኖራቸው ሆነው የሰለጠኑ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንም ጨምሮ የሲቪልና የወታደሩ ቢሮክራቶች እጅግ አረመኔና ህብረተሰብአቸውን ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው እንዲሰጡ የተዘጋጁ ናቸው ማለት ይቻላል። በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ሁኔታው ምስቅልቅልና ለብዙ ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናዮች ግልጽ ያልሆነ ሁኔታ የተፈጠረበት ዘመንን እንመለከታለን። በተለይም ከ1989 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ካፒታሊዝም ለጊዜውም ቢሆን በአሸናፊነት እንዲወጣና ሁሉም 14 አገሮች ቢያንስ በመርህ ደረጃ የነጻ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን እንዲከተሉ አስገደዳቸው። አብዛኛዎቹ አገሮች ወደ ውስጥ ከማተኮር ይልቅ ይበልጥ ወደ ውጭ በማተኮር በማኑፋክቱር ላይ የተመረኮዘ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዳይገነቡና እንዳያስፋፉ አገዳቸው። አብዛኛዎች አገሮች በተለይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ተግባራዊ በማድረግ ከአገርና ከህብረተሰብ ግንባታ ይልቅ የአገልግሎት መስኩ እንዲስፋፋ ሁኔታዎችን አመቻቹ። ስለሆነም ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭ ኤክስፐርቶች በየአገሩ በመሰማራትና በየመንግስታቱ ላይ ግፊት በማድረግ የተዛባና ሀብት ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ አደረጉ። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአንድ አገር ውስጥ ያልተመጣጠነ ዕድገትና የሀብት ፍሰት በማስከተል በየአገሮች እየተሰፋፋ ለመጣው ድህነት ዋና ምክንያት ሆነ። በዚህ መልክ ግሎባል ካፒታሊዝም በልዩ ልዩ መስኮች በመሰማራትና በየመንግስታቱ ላይ ግፊት በማድረግ መንግስታቶችን የበለጠ ከህዝቦቻቸው እንዲርቁና ወደ ጨቋኝነት እንዲለወጡ ሁኔታው ገፋፋቸው። በዚህም መሰረት አገር፣ ህብረ-ብሄር(Nation-State)፣ ብሄራዊ ኢኮኖሚና ብሄራዊ ነፃነት፣ እንዲሁም የመንግስት ትርጉምና ሚና በአንድ አገር ዕድገት ውስጥ የሚኖረው መሰረታዊ ተግባር፣ ህብረተሰብአዊ እሴትና ህብረተሰቡን ሊያቅፍና የመፍጠር ኃይሉን ሊያዳብር የሚችል ብሄራዊ ባህል፣ የግለሰብ ነፃነትና ሚና፣ የሚያድጉ ልጆች ሁኔታና እንክብካቤ፣ እንዲሁም ጤናማ የሆነ የቤተሰብ ምስረታና፣ ይህም የአንድ አገር ምሰሶ መሆን... ወዘተ... ወዘተ. ቦታና ትርጉም እንዳይኖራቸው ተደረገ። አንድ አገር ማንም እየመጣ የሚፈነጭበትና ከየመንግስታቱ ጋር በመቆላለፍና በመባልግ ሀብት የሚዘርፍና ህብረተሰባዊ እሴቶች የሚበጣጠሱበት መድረክ ሆነ። ይህ ሁኔታ በየአገሮች ውስጥ የሴተኛ አዳሪዎችን መስፋፋት፣ ህጻናትን ማባለግና ከሰው ልጅ ጤናማና ተፈጥሮአዊ ኖርም የራቁ ግኑኝነነቶች በመፍጠርና በማስፋፋት ህዝቡ ስለ ህብረተሰብ ትርጉም ደንታ እንዳይኖረው ተደረገ። ስለሆነም በብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንም ጨምሮ፣ እነዚህ አገሮች እንደ አገሮች ቢታዩም፣ ህዝቦች ግን ህበረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊና(Social Consciousness) እንዳይኖራቸው ተደረጉ። ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች አምባገነንነት ሰፍኗል፤ ዲሞክራሲ የለም እየተባለ የሚለፈፈውና የሚወደሰው ይህንን ውስብስቡን የዓለም ሁኔታ ለመመርመር ካለመቻል የተነሳ ይመስለኛል። የብዙ የአፍሪካ አገሮች ችግር ፕላቶ እንደሚለን ዕውነትን ከውሸት ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ለመስፋፋት አለመቻሉና፣ ዕውነተኛ ሁለ-ገብ የሆነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ነው። ሰፋ ያለ የዳበረ ምሁራዊ እንቅስቃሴና፣ በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ ብሄራዊ ባህርይ ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር የውጭ ኃይሎች ከውስጡ ኃይል ጋር በማበር የጨለማውን ዘመን ያራዝማሉ። የጭቆና መሳሪያዎችን እየላኩና እያስታጠቁ የጸጥታ ኃይል በሚሉት አማካይነት አንድ ህብረተሰብ ተዋክቦ እንዲኖር ያደርጋሉ። ህብረተሰቦች ታሪክ የሚሰራባቸው፣ ህዝብ ተረጋግቶ እንዲኖር ነገሮች በስነስርዓት ከሚዘጋጅባቸው ይልቅ ወደጦርነት አውድማ እንዲቀየሩ ይገደዳሉ። ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብትን በማይፈጥር በተራ ሸቀጣ ሸቀጥ አማካይነት ህብረተሰብን ማዋከቡ በከፍተኛ ፍጥነት መካሄድ አለበት። እንደ አገራችን ባሉት ደግሞ ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምሮ የኮሞዲቲ ገበያ የሚባል በማቋቋም ሰፊው ገበሬ አመለካከቱን ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያዞር በማድረግ ለዓለም ገበያ የቡናና የሰሊጥ ምርት አቅራቢ፣ ለውስጥ ገዢዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል። ከውጭ ሰልጥነው የገቡትና ዝናን ያገኙት አዲሶቹ ኤሊቶች ዋና ተግባር ህዝባችንን ወደ ባርነት መለወጥ ነው። ይህ በግሎባልይዜሽን ዘመን ንቃተ-ህሊናቸው የደከሙ ህብረተሰቦችንና፣ በኒዎ- ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑ ተውረግራጊዎችን እየፈለጉና እያሰለጠኑ በአንድ በኩል ህብረተሰቦች ርካሽና የቆሻሻ ፍጆታ ዕቃ መጣያ ሆነዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ብዙ ቀናትና ወራት የለፋበትን የቡናም ሆነ የሰሊጥ ምርት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ በመገደድ ወደ ባርነት እንዲለወጥ ተደርጓል። በዚህ መልክ ባለፈው ሃያ አራት ዐመታት በህብረተሰብአችን ውስጥ አዲስ ድህነትን ፈልፋይና የአገራችንን አቅጣጫና ዕድገቷን ያጣመመ እጅግ አደገኛ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል ችሏል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል በዓለም አቀፍ 15 ደረጃ በተዋቀረው የፊናንስ ሰንሰልት ውስጥ በመካተት በካፒታሊስት አገሮች የሚካሂደውን የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) አጋዥ ሆኗል። ወደ ውስጥ ደግሞ የህብረተሰቡን ሀብት በመምጠጥና የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሆኗል። በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር፣ ዐይን ያወጣና ህብረተሰቡም ወደ ጥፋት መንገድ ሲያመራ ማየት የማይችልና፣ ማየት ቢችል እንኳ ደንታ የሌለው የህብረተሰብ ክፍል ሊሆን በቅቷል። ፍልስፍና አልባ የሆነና ህብረተሰብአዊ ኖርሞችን መከተል የማይችል፣ ወይም ህብረተሰቡ በተወሰኑ ኖርሞች ላይ እንዲተዳደር ማድረግ የማይችል ከሰፊው ኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሚኖር፣ የራሱ መዝናኛና ልዩ የመገበያያ ቦታ(Shoping Center) ያለው ኃይል ብቅ ብሏል። በዚህ መልክ ብቻ ነው የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮችን የሚቆጣጠረውና ለመቆጣጠር የሚችለው። ዛሬ በአገራችን ምድር የሰፈነውን ፍልስፍና አልባ ፖለቲካና ህዝብን ማዋከብ ከዚህ ቀላል ሁኔታ በመነሳት ነው መመርመር መቻል ያለብን። በቀላል የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላ፣ ወይም በአምባገነን ስርዓት መስፈንና በዲሞክራሲ እጦት የህብረተሰብአችንን የተወሳሰበ ችግር ለመገንዘብ አንችልም። የአገዛዙ ችግር የፖለቲካ ፍልስፍና አልባነት ችግር ነው ስል ምን ማለቴ ነው? በመጀመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ። ይኸውም ወያኔ/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ የፈለቀና የፊዩዳሊዝምና እጅግ የተዘበራረቀው ካፒታሊዝም ውጤት አገዛዝ ነው። በተለይም በአርባዎቹ መጨረሻና በሃምሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የተተከሉት በፍጆታ ምርትና አጠቃቀም ላይ የተመሰረቱት፣ ግን ደግሞ የውስጥ ገበያን ማስፋፋትና ማዳበር የማይችሉት ኢንዱስትሪዎች ለዛሬው አገዛዝም ሆነ ቀደም ብለው ለነበሩት ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮች የባህርይና የአሰራር መሰረቶች ሆነዋል። ከአዋቂነትና ከብልህነት፣ ከጥበብና ከቆንጆ ቆንጆ ስራዎች ይልቅ ተንኮለኛ፣ ዳተኛና አራዳ እንዲሁም አገር ከፋፋይ ሆነው ብቅ ሊሉ የቻሉት አርቆ ባለማሰብ በተዋቀረው በተቆራረጠና ህብረተሰብአዊ መተሳሰርን በማያጠናክር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው። የዛሬውን የወያኔ አገዛዝ ከተቀሩት ለየት የሚያደርገው የብሄረሰብን ወይም የጎሰኝነትን ጥያቄ አንግቦ በመነሳቱና፣ የተለየም መሆኑን ለማረጋገጥ መሞከሩ ብቻ ነው። የጎሰኝነትን ወይም የብሄረሰብ ፖለቲካንም የሚጠቀመ ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው እንጂ ለየብሄረሰቦቹ ነፃ መውጣት በማሰብ አይደለም። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የሚደገፍ ሲሆን፣ በተለይም እንግሊዝና ሌሎች የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ደጋፊዎች ናቸው። ስለሆነም ከራሱ ባሻገር ማሰብ የማይችለው አገዛዝ ለስልጣንና ለሀብት ክምችት በማለት ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር የዘጠና ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል ማጨለም ችሏል። የባርነቱንና የድህነቱን፣ እንዲሁም የጥገኝነቱን ዘመን ለብዙ መቶ ዐመታት ማራዘም ችሏል። ሁኔታው የባሰ እንዲመሰቃቀልና መጠገኛና መፍቻ መንገድም እንዳይገኝ ማድረግ ችሏል። በተለይም የአገዛዙ መሪዎች ያደጉበት ሁኔታና ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ለመቀላቀል አለመቻል የተለዩ መሆናቸውን በማስመሰል በእንደዚህ ዐይነት አገርን ከውስጥ የሚያስቦረቡርና ለውጭ ጠላት ደግሞ ካለምንም መከላከል ትጥቅን ፈቶ እጅ የሚያሰጥ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። ከዚህም ስንነሳ በአስተሳሰባቸው አንድ ወጥና ድርቅ ማለት፣ በምንም ዐይነት ለሰው ልጅ አለማሰብ፣ ወይም ህብረተሰብአዊ ፍቅር አለመኖር፣ አሁንም ቢሆን ጦርነትንና ድንፋታን ማስቀደም፣ ሶክራተስና ፓላቶ እንዳሉት ከህዝባዊ ስነ-ምግባርነት(Civic Virtue) ይልቅ፣ ህብረተሰቡን ማመሰቃቀል፣ ታዳጊው ትውልድ ኃላፊነት እንዳይኖረው ማድረግና ቀማኛ እንዲሆን ሁኔታውን ማመቻቸት፣ ከፋፋይነትና ለውጭ ኃይሎች ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛትና፣ ይህንን እንደትልቅ ፈሊጥ አድርጎ መያዝ ዋናው የፖለቲካ „ፍልስፍናቸው“ በመሆን አገራችንን ከሁሉም አቅጣጫ ለማዳከም ችለዋል። ይህ ዐይነት የፖለቲካ ዘይቤ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሲወዳደሩ ልዩ ሊያስመስላቸው ይችል ይሆናል፤ ነውም። በአንዳንድ ነገሮች ከቀደመው የኃይለስላሴና የደርግ አገዛዝ ቢሮክራቶች የሚመመሳሰሉበትም ሁኔታ አለ። 16 ይኸውም ብሄራዊ ባህርይ ማጣት፣ በተለይም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሰጥ ለጥ ብሎ ማጎብደድ፣ ወይም አሜሪካንን እንደ አምላክ ማየትና አገርን መካድና የአገርን ምስጢር አሳልፎ መስጠት፣ ሰፊውን ህዝብ መናቅና ተንኮሎኝነት፣ በዚህ የሚመሳሰሉ ናቸው። ይህንን በጭንቅላታችን ውስጥ ስንቋጥር ነው የነገሮችን ሂደት መገንዘብ የምንችለው። ዝም ብሎ ግን አገዛዙ ለኢትዮጵያ አጀንዳ የለውም፤ ማርክሲስት ነው፤ የአልባንያውን ዐይነት ሶሻሊዝም ነው የሚያካሂደው፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው የሚያራምደው፤ ህገ-መንግስቱ ስታሊኒስታዊ ነው፤ የሚሉት አነጋገሮች የህብረተሰብአችንና የአገዛዙን የህሊና አወቃቀር፣ እንዲሁም ደግሞ የታሪክን ሂደት እንዳንረዳ የሚያደርገን አይደለም። በተጨማሪም የተበላሹ ማቴሪያላዊ(Socioeconomic formation) አወቃቀሮች በሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ባለመገንዘብ የሚሰነዘሩ መንፈሰ ሀተታዎች እንጂ ሀቁን የሚነግሩን አይደሉም። ስለዚህም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ ከራሱ ስሜት በመነሳት እንጂ አንዳች ፍልስፍናንና ስልትን(Methodology) በመከተል አይደለም የዛሬውን አገዛዝ ባህርይና ፖለቲካ የሚባለውን ፈሊጥ ለመተንተን የሚሞክረው። እንደዚህ ዐይነቱ በአንዳች ፍልስፍናና ስልት ላይ ያለተደገፈ አቀራርብ ደግሞ የችግሩን ዋና ምንጭ እንዳንረዳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ፍቱንና ህብረተሰብአችንን ሊያረጋጋና ወደስልጣኔ ሊያመራው የሚያስችል መፍትሄ እንዳንሰጥ ያግደናል። ለመጻፍ ተብሎ የሚጻፍ፣ ወይም ደግሞ ቁጭትን ለመወጣት ተብሎ የሚጻፍ ነገር የለም። ስለሆነም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ አጠቃላዩን የህዝባችንንና የአገዛዙን የህሊና አወቃቀር ለመረዳት፣ በፍልስፍና፣ በህሊና ሳይንስ፣ በህብረተሰብ ሳይንስና እንዲሁም በተነፃፃሪ የታሪክ ምርምር(Comparative studies) የሚደገፍ ጥናት ቢካሄድ ተቀራራቢ መልስና መፍትሄ ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ የዛሬው የወያኔ/የኢህአዴግ አገዛዝ የፖለቲካ ስልጣንን ሲጨብጥ ሜዳው ክፍት ነበረለት። የሚጋፈጠውን ሲያጣ ፍቅርና ሰላምን ከማስቀደም ይልቅ እንደልቤ መፈንጫ አገኘሁ በማለት ህብረተሰቡን ማዋከብ የፖለቲካው ዘይቤው አድርጎ ተያያዘው። የህብረተሰቡን ሀብት በመንጠቅና ጥቂቶችንም በማባለግ እያበጠ መምጣት ጀመረ። ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ዕርዳታ ሲፈስለት እኔ ነኝ ብቸኛው ኃይል በማለት በግሎባላይዜሽን ጉያ ስር በመውደቅና በመታሸት የህብረተሰቡን ችግር ውስብስብ አደረገ። ለዚህም ደግሞ መለሰ ወዳጃችን ነው፤ በአካባቢውም ሰላምንና መረጋጋትን የሚያመጣ ነው እየተባለ መወደስ ቻለ። በሌላ ወገን ግን የምዕራቡ ዓለም የተከተለውና ዛሬም የሚከተለው ፖለቲካ ከአጭር ስሌት አንፃር የተተለመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ጋር የቆመና እሱንም የደገፈ፣ ራሱም እንደ ዋና ጠላት መታየቱ በፍጹም አልገባውም። ስለሆነም መለስ ከመሞቱ በፊትና ስልጣን ላይ 20 ዐመታት ያህል በቆየበት ዘመን፣ ልክ ሶክራተስ ፐሪክለስን እንደወነጀለው፣ ሰነፍ፣ ለፍላፊ፣ አጭበርባሪ፣ አገር ሻጭና ከሃዲ፣ በዝሙት ዓለም ውስጥ የሚዋኝ፣ ዕውነትን ከመፈለግ ይልቅ ለውሸት ጠበቃ የቆመ ትውልድ፣ በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን የሚክድና፣ ተቀባይ ሲያጣ ደግሞ ቃታ የሚሰነዝር ትውልድ ለማፍራት በቅቷል። ይሁንና ግን መለስ ከፐሪክለስ ጋር ሊወዳደር የሚችል መሪ አልነበረም። ፐሪክለስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ የአቴንን የበላይነት ለማስፈን የታገለና በአቴን ስልጣኔ የሚኮራ ነበር። በመለስ ይመራ የነበረው የወያኔ አገዛዝና የዛሪው ወያኔ ግን „ከአሜሪካን ጋር እየተመካከርን ነው የምንሰራው“ በማለት የበታችነቱን ያረጋገጠንና የሚያረጋግጥ፣ ለስልጣኔ ጠንቅ የሆነ አገዛዝ ነበር፤ ነውም። ብሄራዊ አጀንዳ የሌለውና ኢትዮጵያችንን ከውስጥ በማዳከም የሚደሰት ነበር፤ ነውም። የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን የኒዎ-ሊበራል አንጀት አጥብቅኝ የሞኔተሪ ፖሊሲ በመከተልና በዚህ በመዝናናት ድህነትን የፈለፈለ ነው። የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ደግሞ በስልጣን መታወርና የማንአለብኝ ብሎ እየተመጻደቁ መኖር ነው። በዚህ ዐይነት በውሸት ላይ በተመሰረተ አገዛዝ ግን ደግሞ ነገ እንደዱቄት የሚበን፣ አገዛዙ መግቢያና መውጫ የሚያጣበት ቀን መምጣቱ አይቀሬ ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ጨቋኝ አገዛዝ ለብዙ ዘመናት የቆየበት ጊዜ የለም። በሌላ ወገን ግን በህዝባችንና በአገራችን ላይ ያደረሰው አደጋ በቀላሉ ተገልጾ የሚያልቅ 17 እይመስለኝም። ብዙ ጥናትንና ምርምርን የሚጠይቅ ነው። በአጭሩ ግን አገዛዙ ህዝባችንን በሀዘን ዓለም ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፤ ግራ የገባው፣ ለምን እንደሚኖርና ወዴት እንደሚጓዝ የሚያውቅ አይመስልም። ለማኝ እንዲሆን ተደርጓል። በራሱ ላይ ዕምነት እንዲያጣ ሆኗል። ተፈጥሮአዊ ነፃነቱ ተገፏል። ወጣት ልጆቹን ለውጭ ከበርቴዎች ካለ ዕድሜያቸው ለጋሽ እንዲሆን ተደርጓል። ብሄራዊ ነፃነታችን ተገፏል። በአንድ በኩል አሽረሽ ምችው፣ በሌላው ወገን ደግሞ ተስፋ መቁረጥና መዘናጋት የህብረተሰብአችን ልዩ ባህርይ ሆነዋል። በዛሬው ወቅት ወደ አስራ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝባችንን የሚያሰቃየው ረሃብ ከአገዛዙ ባህርይ፣ አወቃቀር፣ ብሄራዊ ባህርይ ማጣትና በዘረፋ ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በተጨማሪም የረሃቡና የድህነቱ መስፋፋት የሚያመለክተው አገራችን የቱን ያህል በውጭ ኃይሎች መዳፍ ቁጥጥር ስር እንደወደቀች ነው። የአገዛዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከውጭ የመጣና በውጭ ኃይሎች የተደነገገ በመሆኑ ወደ ውስጥ፣ በተለይም ሰፊውን አምራች ገበሬ ሊያግዝ የሚችል የማምረቻ መሳሪያና ማዳበሪያ እንዲመረት ማድረግ የሚያስችልና፣ ቀስ በቀስ ደግሞ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዲፈጠር የሚያደርግ ባለመሆኑ ሰፊው ህዝባችን የግዴታ እንደገና ለረሃብና ለድህነት ተጋልጧል። የአገዛዙ የሃሳብ ድህነትና ህዝብን መናቅ ህዝባችን ሊወጣው የማይችለው ፍዳ ውስጥ ከቶታል። ይህ በብዙ ድሮች የተቆላለፈው ችግርና የህብረተሰቡና የገዢው መደብ አስተሳሰብ በከፍተኛ ደረጃ መዳከም፣ 70% በመቶ የሚሆነው የአገራችን ምድር ለእርሻ የሚያገልግል ቢሆንምና፣ አገራችንም በውሃ ብዛት ክምችት በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስተኛ ቦታን ብትይዝም፣ አሁንም ቢሆን በረሃብ የምትታወቅና ህዝባችንም በልመና እንዲኖር የተገደደ ነው። በአገራችን ምድር ውስጥ እየተደጋገመ ረሃብ መከሰት በዛሬው አገዛዝ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአገራችን ምድር የተከሰተውን ህብረተሰብአዊ አወቃቀር ለተከታተለና ላጠና፣ አዲስ የተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት ብሄራዊ ባህርይ የነበረውና ያለው አልነበረም። በመሆኑም እንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት ከሰፊው ህዝብ ርቆና ተገልሎ የሚኖርና፣ ፈጣሪም ባለመሆኑ በየጊዜው በአገራችን ምድር ረሃብ እንዲከሰት አድርጓል። ይህ ሁኔታ እንደባህል በመወሰዱና እስከዛሬ ድረስ በመዝለቁ በሰፊው ህዝብና በየጊዜው ብቅ በሚለው አዳዲስ ኤሊት መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኝነት እንዳይፈጠር ተደርጓል። አዲስ አበባ የተቀመጠው ኤሊትና የገዢው መደብ ገበሬው በስንትና ስንት ልፋት በብርድና በጠራራ በባዶ ሆዱና ካለጫማ እያረሰ እንደሚያቀርብለት የገባው አይመስልም። ስለሆነም የአስተሳሰብ ለውጥ እስካልተደረገ ድረስና፣ ሃላፊነትን ሊቀበልና ብሄራዊ ስሜት ሊኖረው የሚችል አዲስ የህብረተሰብ ኃይል እስካልተፈጠረ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ለሚቀጥሉት ሰላሳና ሃምሳ ዐመታት ድህነትና ረሃብ ይሆናል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የወያኔን አገዛዝ የተበላሸና ህዝብን ለዝንተዓለም የሚያወዛግብ ፖለቲካን ስንመለከት በጣም የሚያሳዝኑና የሚያስቁ ሁኔታዎችን እንመለከታለን። ወያኔ ለዘለዓለም ስልጣን ላይ ለመቆየት ባለው ፍላጎት መሰረት ከውስጥ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ገንዘብ ከኢኮኖሚው ዕድገት ሁኔታ ጋር እየተመጣጠነ እንዲታተም ከማድረግ ይልቅ፣ በብዛት እንዲታተም በማድረግና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ ሊያደልብ ችሏል፤ አባልጓልም። ይህ አዲሱ መጤ የህብረተሰብ ክፍል አምራችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የስራ መስክ የሚፈጥር ሳይሆን፣ በተለይም በአገልግሎት መስክ ላይ በመረባረብ በከፍተኛ ደረጃ የፍጆታ ዕቃ ተጠቃሚና የህብረተሰቡን ሀብት የሚመጥ ሊሆን ችሏል። ይህ በራሱ አገራችን ውስጥ መረን በለቀቀ መልክ ለተስፋፋው ድህነትና ድብቅ ረሃብ እንደ አንድ ዋና ምክንያት ሊቆጠር የሚችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ራሱ የሚቆጣጠረው የኢንዱስትሪ መስክና አዳዲስ የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች በመሰረቱ ወደ ውስጥ ህዝባዊ ሀብትን(National and Social Wealth) ለመፍጠር የሚያስችሉና የስራ መስክ ለመከፍት የሚበቁ አይደሉም። በዚህም ምክንያት የውስጥ ገበያው ሊስፋፋና ሊዳብር የቻለበትን ሁኔታ 18 አንመለከትም። በየቦታው ያሉ የቢሮክራሲው ማነቆዎች ደግሞ ህዝቡን የሚያሰሩና ወደ ውስጥ የጥሬ-ሀብት እንዲወጣና ሰፊው ህዝብ ወደ ስራ ዓለም እንዲሰማራ ለማድረግ የሚያስችሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት አገዛዙና ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ሚኒስትሪዎች የሰፊው ህዝብ ተጠሪዎች ሳይሆኑ የህዝብን ሀብት የሚዘርፉና ህዝቡ በራሱ አነሳሽነት ችግሩን እንዳይቀርፍ ትልቅ እንቅፋት ለመሆን የቻሉ ናቸው። የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ሚኒስተሮችን ዋና ተግባር በምንመረምርበት ጊዜ በመሰረቱ በየክፍለ ሀገራት ወይም በየክልሉ እየተዘዋወሩ የየአካባቢውን የኢኮኖሚና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማጥናትና፣ ከዚህ በመነሳት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የሚገባቸው ነበሩ። ሁኔታውን ስንመረምር ግን ሁሉም ሚኒስተሮች ማለት ይቻላል፣ ከህዝቡ ርቀው የሚኖሩና በየክፍላተ ሀገራት ምን ምን የስራ ክፍፍል እንዳለና፣ የገበያውም ሁኔታ በምን መልክ የተደራጀ መሆኑን ለመቃኘት የሚጥሩ አይደሉም፤ ፍላጎትም የላቸውም። ይህ እንግዲህ የአገዛዙን ፖሊሲ ሲመለከት፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዙ ለረጅም ዘመናት በስልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ፍላጎት የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ ባሉት ኢንስቲቱሽኖችና እስከመጠጥ ቤት ድረስ ሰርጎ በመግባት ህዝቡን ፍዳ እያሳየ ነው። ምንም የፖለቲካ ዕውቀት የሌላቸውን ሁሉ ደጋፊዎች በማድረግ ፖለቲካን ወደ ርካሽነት የለወጠ አገዛዝ ነው ማለት ይቻላል። ይሁ ጉዳይ እስከውጭ ድረስ በመዝለቅና አንዳንድ በኢትዮጵያውያን የሚተዳደሩ ቡና ቤቶችን በማቀፍ በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ እንዲቃቃርና እንዳይቀራረብ እያደረገ ነው። በተለይም በብዛት ለትምህርት እየተባሉ የሚላኩ ምንም ነገር የማይገባቸው ልጆች በካድሬነት በመመልመል የማይሆን ነገር እየሰሩ ነው። ስለሆነም እነዚህ ወጣት ትግሬዎች/ኢትዮጵያውያን በማያውቁት ነገር ውስጥ በመግባት በሌላው ወያኔን በሚጠላው ኢትዮጵያዊ እንደጠላትነት እየታዩ ነው። አገዛዙ ህብረተሰቡን በመከፋፈልና የተወሰነውን ህብረተሰብ ክፍል በጥቅም በመደለል የሚያካሂደው ፍልስፍናዊ አልባ ፖለቲካ በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ማጥ ውስጥ እየከተተን ማለት ነው። ኢትዮጵያን እንደ አገርና እንደ ህብረ-ብሄር በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረተ ላይ የመገንባቱ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዐመታት እንዲተላለፍ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ለራሱ ለአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ለትግሬ ብሄረሰብም የሚያመች አይሆንም። ወያኔ ቢወድቅ እንኳ የተቀሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲሁም አባቶቻችንና እናቶቻችን የሆኑት የትግሬ ብሄረሰብ ተወላጆች በጥርጣሬ እየታዩ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገለሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ የዚህን የተወሳሰበና አደገኛ ሁኔታ በመረዳት አዲስ የትግል አቅጣጫ መቀየስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ከዚህ ስንነሳ የተቃዋሚውን ኃይል የትግል ስትራቴጂ ወይም ፍልስፍና በጥቂቱም ቢሆን መቃኘቱ አስፈላጊ ይመስለኛል። አጠቃላዩንና የተወሳሰበውን የአገራችንን ሁኔታ ስንመረመር ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ይህንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል ትንታኔ ሲሰጥ አይታይም። በብዙዎቻችን ዕምነት የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ብቻውን የሚጓዝና፣ የተከተላቸውና የሚከተላቸውም ፖሊሲዎች ከውጭው ዓለም ጋር በተለይም፣ ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ከሚባለው ጋር የሚያያዙ አይደሉም። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ደርጅት(IMF)፣ የዓለም ባንክ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የአውሮፓ አንድነት በአገራችን የኢኮኖሚ ፖሊስና ተግባራዊ መሆን ላይ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ የላቸውም። ስለዚህም ትግሉ ከወያኔ ጋር ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ በሳይንስና በቲዎሪ እንዲሁም በፍልስፍና ደረጃ ዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለውን መጋፈጥ አያስፈልግም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ አገዛዝ ከተላቀቀ ሁሉ ነገር ይሰተካከላል የሚል ከዓለምና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም አመለካከት በተቃዋሚው ኃይል ጭንቅላት ውስጥ የተቋጣረ ይመስላል።፣ ይህ ዐይነቱ አመለካከትና የትግል ስትራቴጂ ከታሪክ ልምድና በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር የሚደገፍ አይደለም። እኔ እስከተከታተልኩትና እስካጠናሁት ድረስ 1ኛ) ተቃዋሚው ነኝ የሚለው ኃይል ብሄራዊ አጀንዳ ያለው አይመስለኝም። አገር ወዳድነቱና ብሄራዊ ስሜቱም ያጠራጥራል። 19 ምክንያቱም ሳይንቲስቱ ላይብኒዝ እንደሚለው አንድ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ህዝብ ወዳድና ለአገሩ የሚቆረቆረው በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ብቻ ነው። 2ኛ) ፍልስፍናዊ መሰረት የለውም ወይም ደግሞ በምን ዐይነት ፍልስፍና እንደሚመራ ግልጽ አይደለም። 3ኛ)ባለፉት 24 ዐመታት በአገራችን ምድር የተፈጠረውን እጅግ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ፣ የህብረተሰብና የማህበራዊ እሴቶች መበጣጠስና፣ የህዝባችንንም ኑሮ የመረመረና ለነዚህም ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ጠጋ ብሎ ለመገንዘብ የቃጣና፣ የሚቃጣ አይደለም። በየጊዜው ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው እዚህ አውሮፓ የሚመጡትን የተቃዋሚ ተጠሪዎች ንግግር ለተመለከተ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ በቅጡ የተገነዘቡ አይመስሉም። አነጋገራቸው በነፃነት እጦት፣ በዲሞክራሲ አለመኖርና ምርጫ በስነ-ስራዓት አለመካሄድ አኳያ የሚደረጉ ንግግሮች እንጂ፣ ሰፊና ጠለቅ ያሉ ትንተናዎችን ሲሰጡ አይታዩም። ውጭ አገር ያለውም ችግሩን በምርጫና በህገ-መንግስት ዙሪያ ከማየት አልፎ በህብረተሰብአችን ውስጥ የቱን ያህል የአዕምሮ መዛባት(Austim) እንደሰፈነና፣ ለዚህም ደግሞ ልዩ ጥናትትና መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ጥናት ሲያቀርብ አይታይም። 4ኛ) በአጠቃላይ ሲታይ የተቃዋሚው ኃይል ነኝ የሚለው በአገራችን ውስጥ የምዕራቡን ዓለም፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ጣልቃ-ገብነት ከምንም አይቆጥረውም፤ ወይም ደግሞ ከፖለቲካ ስሌቱ ውስጥ የለም። አንዳንዶች ይህንን ጉዳይ ሲያነሱ አይ ግራ ቀደም ተብለው ይወነጀላሉ፤ ከወዳጃችን ከአሜሪካን ጋር አታጣሉን ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ እንኳ ውይይት እንዳይካሄድ በሩን በመዝጋት ምሁራዊና ሳይንሳዊ ክርክር እንዳይደረግ ለማድረግ በቅተዋል። 5ኛ)ሌላው ትልቁ ችግር የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ነኝ የሚባሉት ምሁራዊ ሁኔታና፣ የአንዳንዶችም በየጊዜው የመለዋወጥ አስተሳሰብና አካሄድ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ መጥቷል ማለት ይቻላል። በመሰረቱ በአገራችን ያለው ችግር የብሄረሰብ ችግር ወይም ጭቆና አይደለም። የንቃተ-ህሊና ጉድለትና የታሪክንና የህብረተሰብን ዕድገትና ሂደት ያለመረዳት ጉዳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ እዚህና እዚያ እንቀሳቀሳልን የሚሉት የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን ባዮች ፍልስፍናቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም። ተበድሏል የሚሉትን ወገናቸውን እንዴትስና በምን መንገድ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥበብና የኢኮኖሚ ዕድገት ባለቤትና ተጠቃሚ ለማድረግና ቆንጆ ኑሮ ሊኖር የሚችልበትን መንገዱን ሲያሳዩን አንመለከትም። የዲሞክራሲና የነፃነት እጦት መፈክሮች ብቻ የትም አያደርሱትም። ከሌሎች አገሮች ልምድ እንደምናየው፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የአንጎላና የሞዛምቢክ፣ እንዲሁም የዚምባብዌ ህዝቦች የነፃነት ትግሉ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ በፍጹም አልቻሉም። በድሮው አገዛዝ አዲስ የገዢ መደቦች በመቀመጥና ከውጭው ዓለም ጋር በመቆላለፍ ሀብት ዘራፊዎችና አቆርቋዦች ሆኑ እንጂ ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጉ አልቻሉም። እንደምናየው በእነዚህ አገሮች ሁሉ በተለይም ወጣቱ ስራ አጥ በመሆንና የማስለጠኛ ቦታ በማጣቱ ተፈጥሮአዊ ችሎታውን ተግባራዊ እንዳያደርግ ተገዷል። ስለሆነም በዚህም ሆነ በዚያ መስክ ብሄረሰባችንን ነፃ እናወጣለን የሚሉት ቡድኖች በመሰረቱ ከነዚህ የሚለዩ አይሆኑም። ምናልባትም እንደጆከር በመቀመጥ ማስፈራሪያ የሚሆኑና፣ የድህነቱንም ዘመን የሚያራዝሙ ይሆናሉ። ከዚህ ስንነሳ ከፍልስፍና፣ ከሳይንስ፣ ከቲዎሪና ከጥበብ፣ እንዲሁም ከህብረተሰብ ሳይንስ ውጭ በነፃነት ስም ብቻ የሚካሄዱ ትግሎች የትም አያደርሱም። የዛሬው አገዛዝ ቢወድቅ እንኳ ምናልባት የደቡብ ሱዳን ዐይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም እያንዳዱ የነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚል እዚህና እዚያ ከመሯሯጡና ከምዕራቡም ምክር ከመጠየቅ ይልቅ እስቲ በአንድነት ተቀምጠን በየአንዳንዱ ጥያቄ ላይ ክርክርና ውይይት እናድርግ። እስከምረዳው ደረስ የአንደን አገር ችግር፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ ችግሮች በፖለቲካ ዲስኮርስና በዲሞክራሲያዊ ውይይት ብቻ ነው መፍታት የሚቻለው። ስለሆነም ለስልጣን ከመቻኮል ይልቅ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታና የዓለም አቀፍ የፖለቲካን፣ የሚሊታሪ፣ የርዕዮተ-ዓለምና የኢኮኖሚ አወቃቀር ጠጋ ብለን እንመርምር፤ አብረን ተቀምጠንም እናጥና። ለዚህም ደግሞ ድፍረቱ ይኑረን። ለብቻችን መሯሯጥና ለአውሮፓው አንድነትም ሆነ ለአሜሪካ መንግስት ተጠሪዎች እሮሮ ማሰማቱ ትክክለኛው የትግል ዘዴ አይደለም። እንዲያውም ራስን አለመቻልና የነፃነቱንም 20 መንገድ ውስብስብ የሚያደርገው ነው። የአውሮፓንና የአሜሪካንን መንግስታት በዲፕሎማሲ ማሳመን አይቻልም። የአሜሪካም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታቶች ተቃዋሚውን ኃይል እንዲደግፉ ከተፈለገ ተቃዋሚው ኃይል ከወያኔ የተሻለ የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ይህም ማለት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይሰፍንና ጠንካራ ህብረተሰብ እንዳይመሰረት ጠንክሮ መስራት አለበት። ከዚህ አጭር ሀተታ ስነሳ፣ ከዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና አገርን ለማውደም ከተቃረበ ችግር እንዴት እንወጣለን ? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄያችንና መመለስ ያለብን ጉዳይ። በተራ የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ ፎርሙላ ወይስ አስቸጋሪ በሆነው ግን ደግሞ ፍቱን በሆነው በሬናሳንስ ፍልስፍና አማካይነት ነው የተወሳሰበውን የህብረተሰብአችንን ችግር ልንፈታ የምንችለው። በእኔ ዕምነት ተራ የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላዎች ለኛ ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ችግር በፍጹም መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም። መፍትሄው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድመውን የሬናሳንስን ሁለ-ገብ የህብረተሰብን ችግር መፍቻ ስልት የተከተለን እንደሆን ብቻ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን ዛሬ የተቀረው የዓለም ህዝብ የሚመኘው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድምና የኑሮን ትርጉም እንድንረዳ የሚያደርገንን መንገድ ነው። በእርግጥ ይህ አካሄድ ከአገራችን ሁኔታ ጋር የሚጣጣምበትን ዘዴ መፈለግ የሚያሻ ይመስለኛል። ለማንኛውም ከየት እንደመጣን፣ በዚህ ዓለም ላይ ለምን እንደምንኖርና፣ ምንስ ማድረግ እንዳለብንና ወዴትስ እንደምናመራ የተገነዘብን እንደሆን ብቻ ተቀራራቢ መፍትሄ ማግኘት የምንችል ይመስለኛል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄውም የፒታጎራስን፣ የሶክራተስንና የፕላቶንን ወንድማዊ ወይም የእህትማማች ፍቅር እንደመመሪያ አድርገን የወሰድን እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ፍቅር ግን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ምሁራዊ ፍቅር ማለት ነው። ዕውነትን ለመፈለግ የሚረዳንና ሶፊስታዊውን የመሙለጭለጭ መንገድ አሽቀንጥረን የሚያስጥለን መሆን አለበት። በሃሳብና በልብ እንድንገናኝ የሚያደርገንና፣ ራሳችንን አውቀንና ለውጠን ህብረተሰብአችንን ከገባበት ማጥ ውስጥ እንዲወጣ የሚያስችለው ፍልስፍናና መመሪያ መሆን አለበት። ፈቃዱ በቀለ fekadubekele@gmx.de ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com December 19, 2015   

No comments:

Post a Comment